በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ያልተጠበቀ ስጦታ ለጃፓናውያን

ያልተጠበቀ ስጦታ ለጃፓናውያን

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም አንቶኒ ሞሪስ ሚያዝያ 28, 2013 በናጎያ፣ ጃፓን በተደረገ ለየት ያለ ስብሰባ ላይ አንድ አስገራሚ ማስታወቂያ ተናገረ፤ ወንድም ሞሪስ መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል የተባለ አዲስ ጽሑፍ በጃፓንኛ መውጣቱን ገለጸ። በስብሰባው ላይ የተገኙትም ሆነ በኢንተርኔት አማካኝነት ፕሮግራሙን የተከታተሉ ከ210,000 በላይ አድማጮች ይህን ሲሰሙ ደስታቸውን ሞቅ ባለ ጭብጨባ ገልጸዋል።

በጃፓንኛ ከተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም ተወስዶ የታተመው ይህ ባለ 128 ገጽ ጽሑፍ የማቴዎስን ወንጌል የያዘ ለየት ያለ እትም ነው። ወንድም ሞሪስ ጽሑፉ የተዘጋጀው “የጃፓንን ሕዝብ ታሳቢ በማድረግ” እንደሆነ ገልጿል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ምን ገጽታዎች አሉት? የተዘጋጀበት ዓላማ ምንድን ነው? ሕዝቡስ ምን ምላሽ ሰጥቷል?

ምን ገጽታዎች አሉት?

የማቴዎስ ወንጌል የተባለው ጽሑፍ የተዘጋጀበት መንገድ አንባቢዎቹን አስገርሟቸዋል። ጃፓንኛ ቁልቁል ወደ ታች አሊያም ወደ ጎን ሊጻፍ ይችላል፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚወጡ ጽሑፎቻችንን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ ጽሑፎች ቃላቱን የሚያሰፍሩት ወደ ጎን ነው። በዚህ አዲስ ጽሑፍ ላይ ግን ቃላቱ የተቀመጡት ወደ ታች ነው፤ እንዲህ ያለው የአጻጻፍ ስልት ታዋቂ በሆኑ የጃፓን ጋዜጦችና የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ላይ የተለመደ ነው። ብዙ ጃፓናውያን ይህ የአጻጻፍ ስልት ለማንበብ ቀላል እንደሆነ ይሰማቸዋል። በተጨማሪም በገጾቹ አናት ላይ ያሉት ርዕሶች ልክ እንደ ንዑስ ርዕስ ጽሑፉ መሃል እንዲገቡ ተደርገዋል፤ ይህም አንባቢዎች ዋና ዋና ነጥቦችን በቀላሉ ማየት እንዲችሉ ይረዳል።

በጃፓን ያሉ ወንድሞችና እህቶች የማቴዎስ ወንጌል የተባለውን ጽሑፍ መጠቀም የጀመሩት ወዲያውኑ ነው። በ80ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ አንዲት እህት እንዲህ ብለዋል፦ “የማቴዎስን መጽሐፍ ከአሁን ቀደም ብዙ ጊዜ አንብቤዋለሁ፤ ሆኖም በዚህ ጽሑፍ ላይ ቃላቶቹ ቁልቁል ወደ ታች መጻፋቸውና ንዑስ ርዕሶች መካተታቸው የተራራውን ስብከት ይበልጥ ለመረዳት አስችሎኛል።” አንዲት ወጣት እህት ደግሞ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “የማቴዎስን ወንጌል አንብቤ የጨረስኩት በአንድ ጊዜ ነው። እኔ የለመድኩት ወደ ጎን የሚሰፍረውን የአጻጻፍ ስልት ነው፤ ብዙ ጃፓናውያን ግን ጽሑፉ ቁልቁል መቀመጡን ይመርጣሉ።”

ለጃፓን ሕዝብ የተዘጋጀ

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ብቻ የያዘው ይህ ጽሑፍ በተለይ ለጃፓናውያን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ብዙዎቹ ጃፓናውያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ትውውቅ የላቸውም፤ ሆኖም መጽሐፉን ለማንበብ ፈቃደኛ ናቸው። የማቴዎስ ወንጌል በዚህ መልክ መውጣቱ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ጨርሶ አይተው የማያውቁ ጃፓናውያን የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል የሆነው ይህ ጽሑፍ እንዲኖራቸውና እንዲያነብቡት አጋጣሚ ይከፍታል።

ይሁንና የማቴዎስ መጽሐፍ የተመረጠው ለምንድን ነው? ብዙዎቹ ጃፓናውያን “መጽሐፍ ቅዱስ” የሚለውን ቃል ሲሰሙ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የማቴዎስ ወንጌል የተመረጠው የአብዛኞቹን ጃፓናውያን ትኩረት የሚስቡ ዘገባዎችን ስለያዘ ነው፤ ከእነዚህም መካከል የኢየሱስ የትውልድ ሐረግና ልደት፣ ዝነኛው የተራራ ስብከት እንዲሁም ኢየሱስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት የተናገረው አስገራሚ ትንቢት ይገኙበታል።

በጃፓን የሚገኙ ቀናተኛ የመንግሥቱ አስፋፊዎች፣ ይህን አዲስ ጽሑፍ ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ እንዲሁም ተመላልሶ  መጠየቅ ሲያደርጉ ማበርከት ጀምረዋል። አንዲት እህት እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “በክልላችን ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የአምላክን ቃል ለማበርከት አሁን የበለጠ አጋጣሚ አግኝቻለሁ። እንዲያውም የማቴዎስ ወንጌልን በወጣበት ቀን ከሰዓት በኋላ ላይ አበርክቼዋለሁ!”

የሕዝቡ ምላሽ ምን ይመስላል?

አስፋፊዎች የማቴዎስ ወንጌልን የሚያስተዋውቁት እንዴት ነው? “ጠባቡ በር፣” “ዕንቁዎቻችሁን በአሳማ ፊት አትጣሉ” እንዲሁም “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ” እንደሚሉት ያሉ የተለመዱ አገላለጾች በበርካታ ጃፓናውያን ዘንድ የታወቁ ናቸው። (ማቴ. 6:34፤ 7:6, 13) በመሆኑም እነዚህን አባባሎች የተናገረው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ሲያውቁ በጣም ይገረማሉ። ብዙዎች እነዚህን ሐሳቦች በማቴዎስ ወንጌል ላይ ሲመለከቱ “መጽሐፍ ቅዱስን ቢያንስ አንድ ጊዜ ለማንበብ ሁልጊዜ እመኝ ነበር” ይላሉ።

አስፋፊዎች የማቴዎስ ወንጌልን ወዳበረከቱላቸው ሰዎች ተመልሰው ሲሄዱ ሰዎቹ ከጽሑፉ ላይ የተወሰነውን ክፍል ወዲያውኑ እንዳነበቡት የሚናገሩ ሲሆን ሙሉውን እንዳነበቡ የገለጹም አሉ። በ60ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ አንድ ሰው “ደጋግሜ አንብቤዋለሁ፤ ሐሳቡም አጽናንቶኛል። እባክህ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የበለጠ አስተምረኝ” በማለት አንድን አስፋፊ ጠይቀውታል።

የማቴዎስ ወንጌል የተባለውን ጽሑፍ ወንድሞች በአደባባይ ምሥክርነት እያስተዋወቁት ነው። አንዲት እህት በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ እየተካፈለች ሳለ የማቴዎስ ወንጌልን ለተቀበለች አንዲት ወጣት የኢ-ሜይል አድራሻዋን ሰጠቻት። ከአንድ ሰዓት በኋላ ወጣቷ የመጽሐፉን የተወሰነ ክፍል እንዳነበበችና ይበልጥ ማወቅ እንደምትፈልግ ለእህት በኢ-ሜይል ገለጸችላት። ይህች ወጣት ከሳምንት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመረች ሲሆን ብዙም ሳይቆይ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረች።

መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል የተባለው ጽሑፍ ከ1,600,000 በላይ ቅጂዎች በጃፓን ወደሚገኙ ጉባኤዎች ተልከዋል፤ በየወሩም አስፋፊዎቹ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ቅጂዎችን እያበረከቱ ነው። የዚህ ጽሑፍ አሳታሚዎች በጽሑፉ መቅድም ላይ “ይህን ጥራዝ ማንበብህ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ጥልቅ ፍላጎት እንደሚያሳድርብህ ተስፋ እናደርጋለን” በማለት ልባዊ ምኞታቸውን ገልጸዋል።