በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ከታሪክ ማኅደራችን

“እጅግ ክቡር ወቅት”

“እጅግ ክቡር ወቅት”

በ1870 በፒትስበርግ (አሌጌኒ)፣ ፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አንድ አነስተኛ ቡድን ቅዱሳን መጻሕፍትን መመርመር ጀመረ። በቻርልስ ቴዝ ራስል መሪነት፣ የቡድኑ አባላት ስለ ክርስቶስ ቤዛ ምርምር ያደረጉ ሲሆን ይህ ዝግጅት በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ያለውን ትልቅ ቦታ ብዙም ሳይቆይ ተገነዘቡ። ቤዛው፣ ስለ ኢየሱስ ገና ላልሰሙ ሰዎችም ጭምር የመዳንን መንገድ እንደሚከፍት ሲረዱ ምንኛ ተደስተው ነበር! ልባቸው በአድናቆት በመሞላቱ በየዓመቱ የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር ተነሳሱ።—1 ቆሮ. 11:23-26

ወንድም ራስል፣ የጽዮን መጠበቂያ ግንብ የተባለውን መጽሔት ማዘጋጀት ጀመረ፤ ይህ መጽሔት የቤዛው መሠረተ ትምህርት የአምላክ ፍቅር ዋነኛ መገለጫ እንደሆነ በግልጽ አስታውቋል። መጠበቂያ ግንብ የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል የሚከበርበትን ጊዜ “እጅግ ክቡር ወቅት” በማለት የሰየመው ሲሆን የመጽሔቱ አንባቢዎች በፒትስበርግም ሆነ በሌላ ስፍራ በቡድን ሆነው እንዲያከብሩት አሳሰበ። መጠበቂያ ግንቡ አክሎም “እንዲህ ያለ ውድ የሆነ እምነት ያላቸው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች” ሌላው ቀርቶ አንድም ሰው ቢሆን በዓሉን ሲያከብር “ከጌታ ጋር የልብ ኅብረት” እንደሚኖረው ገልጿል።

ከዚያ በኋላ በየዓመቱ የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር ወደ ፒትስበርግ የሚመጡት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይሄድ ነበር። መጋበዣው “እዚህ የሚገኙት አፍቃሪ ሰዎች ሞቅ ያለ አቀባበል ያደርጉላችኋል” ይላል። በእርግጥም በፒትስበርግ የነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ ለመንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ማረፊያና ምግብ በፈቃዳቸው አቅርበውላቸዋል። በ1886 በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ለብዙ ቀናት “አጠቃላይ ስብሰባ” ተደርጎ ነበር። መጠበቂያ ግንብ “ለጌታና ለወንድሞቹ እንዲሁም ለእውነት ባላችሁ ፍቅር ልባችሁ ተሞልቶ እንድትመጡ ተጋብዛችኋል” የሚል ግብዣ አቅርቦ ነበር።

በለንደን ጉባኤ በመታሰቢያው በዓል ላይ ቂጣውና የወይን ጠጁ የሚዞሩበትን መንገድ የሚያሳይ ሠንጠረዥ

በቤዛው ላይ እምነት ያላቸው ሰዎች የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር ሲመጡ ለበርካታ ዓመታት ትልቅ ስብሰባ ይደረግ የነበረ ሲሆን በፒትስበርግ የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ወደ ስብሰባው የሚመጡትን በእንግድነት ይቀበላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ቁጥር እየጨመረ በሄደ መጠን በመላው ዓለም የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር የሚሰበሰበው ሕዝብ ብዛትም ጨመረ። የቺካጎ ጉባኤ አባል የነበረው ሬይ ቦፕ በ1910ዎቹ ዓመታት የመታሰቢያው በዓል ሲከበር ምሳሌያዊውን ቂጣና የወይን ጠጅ በብዙ መቶዎቹ ለሚቆጠሩት ተሰብሳቢዎች ማዞር ሰዓታት ይፈጅ እንደነበር ያስታውሳል፤ ይህ የሆነው በበዓሉ ላይ የተገኙት በሙሉ ለማለት ይቻላል ከምሳሌያዊው ቂጣና የወይን ጠጅ ይካፈሉ ስለነበር ነው።

በበዓሉ ላይ የኢየሱስን ሥጋና ደም ለማመልከት የሚጠቀሙት ምን ነበር? በጌታ ራት ላይ ኢየሱስ የተጠቀመው የወይን ጠጅ መሆኑ ቢታወቅም “የሥጋ ድክመት” ያለባቸው ሰዎች እንዳይፈተኑ ሲባል በወይን ጠጅ ፋንታ የወይን ወይም የተቀቀለ ዘቢብ ጭማቂ እንዲቀርብ መጠበቂያ ግንብ ላይ ሐሳብ የቀረበበት ጊዜ ነበር። ይሁን እንጂ “መቅረብ ያለበት የፈላ የወይን ጠጅ” እንደሆነ ለሚሰማቸው ሰዎች የወይን ጠጅ ይቀርብላቸው ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ፣ የኢየሱስን ደም ለመወከል ተገቢ የሚሆነው ምንም ያልተቀላቀለበት ቀይ የወይን ጠጅ እንደሆነ ከጊዜ በኋላ ተገንዝበዋል።

ኒካራጓ ውስጥ በሚገኝ እስር ቤት በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙ ሰዎችን ቁጥር ለመመዝገብ ይህ ወረቀትና እርሳስ በየክፍሉ ይዞር ነበር

የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ማክበር በጥሞና ለማሰላሰል አጋጣሚ ይሰጣል። ይሁንና በአንዳንድ  ጉባኤዎች የሐዘን ድባብ ያጠላበት መንፈስ ስለሚሰፍን ፕሮግራሙ ሲደመደም ሁሉም አንድም ቃል ሳይተነፍሱ ይሄዱ ነበር። በ1934 የወጣው ይሖዋ (እንግሊዝኛ) የተባለ መጽሐፍ ግን የመታሰቢያ በዓሉ መከበር ያለበት ኢየሱስ ተሠቃይቶ መሞቱን በማሰብ “በሐዘን” ሳይሆን ከ1914 ወዲህ ንጉሥ ሆኖ እየገዛ መሆኑን በማስታወስ “በደስታ” እንደሆነ ገልጿል።

በ1957 በሞርድቪኒያ፣ ሩሲያ የጉልበት ሥራ በሚሠራበት ካምፕ ውስጥ ወንድሞች የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር ተሰብስበው

በራእይ 7:9 ላይ የተገለጹት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ማንነት በ1935 በግልጽ መታወቁ ከዚያ በኋላ የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት መንገድ ላይ ለውጥ አምጥቷል። እስከዚያ ጊዜ ድረስ የይሖዋ አገልጋዮች ይህ ቡድን (እጅግ ብዙ ሕዝብ) ራሳቸውን የወሰኑ ሆኖም ያን ያህል ቅንዓት የሌላቸው ክርስቲያኖችን እንደሚያመለክት ያስቡ ነበር። በ1935 ግን ይህ ታላቅ ሠራዊት፣ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ ታማኝ አገልጋዮችን እንደሚያመለክት ታወቀ። ራስል ፖጀንሲ የሚባል ወንድም ይህ ማብራሪያ ከወጣ በኋላ ራሱን በጥንቃቄ በመመርመር “ይሖዋ በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት ሰማያዊ ተስፋ በውስጤ አላሳደረም” ብሏል። ወንድም ፖጀንሲና እንደ እሱ ያሉ ብዙ ታማኝ ክርስቲያኖች ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈላቸውን ቢያቆሙም በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘታቸውን ቀጥለዋል።

በዚህ “እጅግ ክቡር ወቅት” የሚካሄዱት ልዩ የስብከት ዘመቻዎች ሁሉም ክርስቲያኖች ለቤዛው ያላቸውን አድናቆት የሚያሳዩበት ግሩም አጋጣሚ ፈጥረዋል። የ1932 ቡለቲን ክርስቲያኖች የእውነትን መልእክት የሚሰብኩ “እውነተኛ ሠራተኞች” እንዲሆኑ እንጂ ከምሳሌያዊው ቂጣና የወይን ጠጅ ቢካፈሉም የስብከቱን ሥራ የማያከናውኑ “የመታሰቢያው በዓል ቅዱሳን” እንዳይሆኑ አሳስቧል። በ1934 ቡለቲን ወንድሞችና እህቶች “ረዳት አቅኚዎች” እንዲሆኑ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን “በመታሰቢያው በዓል ሰሞን 1,000 ረዳት አቅኚዎች ይኖሩ ይሆን?” ብሎ ነበር። ኢንፎርማንት ደግሞ ቅቡዓንን በተመለከተ “ደስታቸው ፍጹም የሚሆነው በመንግሥቱ ምሥክርነት ሲካፈሉ ብቻ ነው” የሚል ሐሳብ ይዞ ነበር። ምድራዊ ተስፋ ያላቸውም ቢሆን ደስታቸው ሙሉ የሚሆነው በዚህ ሥራ ከተካፈሉ ብቻ ነው። *

ሃሮልድ ኪንግ ለብቻው ታስሮ እያለ ስለ መታሰቢያው በዓል ግጥሞችን እና መዝሙሮችን ጽፏል

የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ዕለት ለሁሉም የይሖዋ ሕዝቦች በዓመቱ ውስጥ እጅግ ቅዱስ ምሽት ነው። እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነውም ጭምር ይህን በዓል ያከብሩታል። ለምሳሌ ያህል፣ በ1930 ፐርል ኢንግሊሽ እና እህቷ ኦራ በመታሰቢያው በዓል ላይ ለመገኘት 80 ኪሎ ሜትር ያህል በእግራቸው ተጉዘዋል። ሚስዮናዊው ሃሮልድ ኪንግ ቻይና ውስጥ ለብቻው ታስሮ ሳለ ስለ መታሰቢያው በዓል ግጥምና መዝሙሮች ጽፏል፤ ምሳሌያዊውን ቂጣና የወይን ጠጅ ለማዘጋጀት ሩዝ እና ብላክ ከረንት የተባለውን ፍሬ ተጠቅሞ ነበር። ከምሥራቃዊ አውሮፓ እስከ ማዕከላዊ አሜሪካ እና አፍሪካ ድረስ ባሉት አገሮች የሚኖሩ ደፋር ክርስቲያኖች የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ እንዳያከብሩ ጦርነት ወይም እገዳ አልገደባቸውም። የምንኖረው የትም ይሁን የት ወይም የምንገኝበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ እጅግ ክቡር በሆነው የመታሰቢያው በዓል ወቅት ለይሖዋና ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ለመስጠት እንሰበሰባለን።

^ አን.10 ቡለቲን ከጊዜ በኋላ ኢንፎርማንት የተባለ ሲሆን አሁን የመንግሥት አገልግሎታችን ይባላል።