በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የይሖዋን ትምህርት’ እንዲቀበሉ ብሔራትን ማዘጋጀት

‘የይሖዋን ትምህርት’ እንዲቀበሉ ብሔራትን ማዘጋጀት

“አገረ ገዥውም በይሖዋ ትምህርት ተደንቆ ስለነበር . . . አማኝ ሆነ።” —ሥራ 13:12

1-3. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “ለሕዝቦች ሁሉ” ምሥራቹን ከመስበኩ ሥራቸው ጋር በተያያዘ ምን እንቅፋቶች አጋጥመዋቸው ነበር?

ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ የሰጣቸው ተልእኮ ቀላል አይደለም። “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት አዟቸዋል። ይህን ሥራ ሲያከናውኑ ቀስ በቀስ “የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል።”—ማቴ. 24:14፤ 28:19

2 ደቀ መዛሙርቱ ለኢየሱስ ፍቅር የነበራቸው ከመሆኑም ሌላ ምሥራቹን ይወዱ ነበር። ይሁንና የተሰጣቸውን ተልእኮ እንዴት ዳር ማድረስ እንደሚችሉ ጥያቄ ሳይፈጠርባቸው አልቀረም። አንደኛ፣ ቁጥራቸው ትንሽ ነው። በዚያ ላይ ደግሞ የአምላክ ልጅ እንደሆነ እያወጁለት ያሉት ኢየሱስ ተገድሏል። ደቀ መዛሙርቱ በሌሎች ዓይን የሚታዩትም “ያልተማሩ ተራ” ሰዎች እንደሆኑ ተደርገው ነው። (ሥራ 4:13) በሌላ በኩል ለሰዎች የሚያደርሱት መልእክት፣ ብዙ ዘመናት ያስቆጠሩ ወጎችን የተማሩትና ገናና ስም ያላቸው የሃይማኖት መሪዎች ከሚያስተምሯቸው ትምህርቶች ጋር ይጣረሳል። ደቀ መዛሙርቱ በገዛ አገራቸው እንኳ አይከበሩም። ታዲያ ኃያል በሆነችው የሮም ግዛትማ ማን ሊሰማቸው ይችላል?

3 ከዚህ በተጨማሪ ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ እንደሚጠሉና እንደሚሰደዱ አልፎ ተርፎም አንዳንዶቹ እንደሚገደሉ አስቀድሞ ነግሯቸው ነበር። (ሉቃስ 21:16, 17) የቤተሰባቸው አባላትና ወዳጆቻቸው ሊክዷቸው ይችላሉ፤ እንዲሁም የሚነሱትን ሐሰተኛ ነቢያትና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደውን ክፋት መጋፈጥ ይኖርባቸዋል። (ማቴ. 24:10-12) ደግሞስ መልእክታቸው በሁሉም ቦታ ተቀባይነት ቢያገኝ እንኳ ምሥራቹን “እስከ ምድር ዳር ድረስ” መስበክ የሚችሉት እንዴት ነው? (ሥራ 1:8) ከፊታቸው የተደቀኑት እንዲህ ያሉ ጋሬጣዎች ፍርሃት ሳያሳድሩባቸው አልቀሩም!

4. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ደቀ መዛሙርት በስብከቱ ሥራቸው ምን ያህል ተሳክቶላቸው ነበር?

4 ደቀ መዛሙርቱ ያሳሰባቸው ጉዳይ ምንም ይሁን ምን፣ በኢየሩሳሌምና በሰማርያ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በነበረው ዓለም በሙሉ ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ እንዳይጠመዱ አላደረጋቸውም። ደቀ መዛሙርቱ የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሟቸውም በ30 ዓመት ጊዜ ውስጥ ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ባለ ፍጥረት ሁሉ መካከል” የተሰበከ ሲሆን “ፍሬ እያፈራና እየጨመረ” መሄድ ችሏል። (ቆላ. 1:6, 23) የዚህን እውነተኝነት ከሚከተለው ማስረጃ ማየት ይቻላል፦ ሐዋርያው ጳውሎስ በቆጵሮስ ደሴት ላይ በተናገረውና ባደረገው ነገር የተነሳ ሰርግዮስ ጳውሎስ የተባለው ሮማዊ አገረ ገዥ “በይሖዋ ትምህርት ተደንቆ . . . አማኝ ሆነ።”—የሐዋርያት ሥራ 13:6-12ን አንብብ።

5. (ሀ) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ማረጋገጫ ሰጥቷቸው ነበር? (ለ) አንዳንዶች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን ሁኔታ በማየት ምን መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል?

5 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የስብከቱን ሥራ በራሳቸው አቅም ማከናወን እንደማይችሉ ተገንዝበው ነበር። ኢየሱስ፣ ሁልጊዜ ከእነሱ ጋር እንደሚሆን እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ እንደሚረዳቸው ነግሯቸዋል። (ማቴ. 28:20) በአንዳንድ ሁኔታዎች ረገድ በወቅቱ የነበረው ዓለም የመንግሥቱን ምሥራች ለማወጅ ምቹ የነበረ ይመስላል። ወንጌላዊነት በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “የዓለምን ታሪክ ከተመለከትን ጨቅላ የነበረውን ቤተ ክርስቲያን ለመቀበል የመጀመሪያውን መቶ ዘመን ዓ.ም. ያህል ተስማሚ የሆነ ወቅት መኖሩ ያጠራጥራል። . . . ክርስቲያኖች፣ . . . በዓለም ላይ ለክርስትና መቋቋም ሁኔታዎችን ያመቻቸው መለኮታዊ ኃይል እንደሆነ በሁለተኛው መቶ ዘመን መናገር ጀምረው ነበር።”

6. (ሀ) በዚህ ርዕስ (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

6 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የስብከቱ ሥራ በስፋት እንዲከናወን አምላክ ነገሮችን ምን ያህል እንዳመቻቸ መጽሐፍ ቅዱስ አይገልጽም። ሆኖም በእርግጠኝነት የሚታወቅ አንድ ነገር አለ፦ ይሖዋ ምሥራቹ እንዲሰበክ ይፈልጋል፤ ሰይጣን ደግሞ የስብከት ሥራውን ይቃወማል። በዚህ ርዕስ ላይ፣ በታሪክ ውስጥ ከሌሎች ዘመናት ይልቅ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ምሥራቹን መስበክ ቀላል እንዲሆን ያደረጉ አንዳንድ ነገሮችን እንመለከታለን። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ደግሞ ምሥራቹን እስከ ምድር ዳር ድረስ ለማወጅ እገዛ ያደረጉ በዘመናችን የተከናወኑ አንዳንድ ሁኔታዎችን እንመረምራለን።

ፓክስ ሮማና ያበረከተው አስተዋጽኦ

7. ፓክስ ሮማና ምንድን ነው? አስደናቂ ወቅት የነበረውስ እንዴት ነው?

7 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የሮማውያን አገዛዝ በአንዳንድ መንገዶች ክርስቲያኖችን ጠቅሟቸዋል። በዚህ ረገድ ፓክስ ሮማና ወይም የሮም የሰላም ዘመን የሚባለውን ወቅት እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። የሮም መንግሥት እጅግ ሰፊ በሆነው ግዛቱ መረጋጋት እንዲሰፍን አድርጎ ነበር። እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ እንደተነበየው “ጦርነትና የጦርነት ወሬ” የተሰማባቸው ወቅቶች ነበሩ። (ማቴ. 24:6) የሮም ሠራዊት በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌምን ያጠፋ ሲሆን በግዛቱ ድንበሮች አካባቢም ቀለል ያሉ ግጭቶች ነበሩ። ይሁን እንጂ ከኢየሱስ ዘመን በኋላ ለ200 ዓመታት ያህል የሜድትራንያን አካባቢ በአንጻራዊ ሁኔታ ከግጭት ነፃ ሆኖ ነበር። አንድ የማመሳከሪያ ጹሑፍ እንዲህ ይላል፦ “በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ይህን ያህል ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ሰላም የሰፈነበት ዘመን ታይቶ አያውቅም፤ ያን  ያህል ብዛት ያለው ሕዝብ በቀጣይነት በሰላም የኖረበት ዘመን ዳግመኛም አልታየም።”

8. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሰላም መስፈኑ ክርስቲያኖችን የጠቀማቸው እንዴት ነው?

8 በሦስተኛው መቶ ዘመን የኖረ ኦሪጀን የተባለ የሃይማኖት ምሁር እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በወቅቱ ብዙ መንግሥታት ቢኖሩ ኖሮ የኢየሱስ ትምህርት በመላው ዓለም ላይ እንዳይሰራጭ እንቅፋት ይሆን ነበር፤ ይህ የሚሆነው . . . በየቦታው የሚኖሩ ሰዎች የውትድርና አገልግሎት መስጠትና የገዛ አገራቸውን ለመጠበቅ መዋጋት ግዴታ ስለሚሆንባቸው ነው። . . . በመሆኑም ኢየሱስ በመጣበት ወቅት የዓለም ሁኔታ ተለውጦና ለዘብተኛ መንፈስ ሰፍኖ ባይሆን ኖሮ ሰላምን የሚያራምደው ብሎም ሰዎች ጠላቶቻቸውን እንኳ እንዳይበቀሉ የሚከለክለው ይህ ትምህርት እንዴት ሊስፋፋ ይችል ነበር?” የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በሮም ግዛት ስደት ቢደርስባቸውም ሰላማዊ የነበሩ ከመሆኑም ሌላ በዚያን ጊዜ ከሰፈነው ሰላም ጥቅም አግኝተዋል።—ሮም 12:18-21ን አንብብ።

ከቦታ ቦታ መጓዝ ቀላል መሆኑ ያስገኘው ጥቅም

9, 10. ደቀ መዛሙርቱ በሮም ግዛት ውስጥ ሲጓዙ ያን ያህል አይቸገሩም ነበር ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

9 ሮማውያን የዘረጓቸው መንገዶች ክርስቲያኖችን በጣም ጠቅመዋቸዋል። ሮም የዜጎቿን ደኅንነት ለማስጠበቅና ተገዢዎቿን ለመቆጣጠር እንዲያመቻት ጠንካራና ብቃት ያለው ሠራዊት አደራጅታ ነበር። ሠራዊቱን በፍጥነት ለማጓጓዝ ጥሩ መንገዶች ያስፈልጋሉ፤ ሮማውያን ደግሞ በመንገድ ግንባታ ረገድ ጥሩ ችሎታ ነበራቸው። ሮማውያን መሐንዲሶች፣ አብዛኞቹን ግዛቶች የሚያገናኝ ከ80,000 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው መንገድ ሠርተው ነበር። እነዚህ መንገዶች ጫካዎችንና በረሃዎችን ለማቋረጥ እንዲሁም ረጃጅም ተራሮችን ለመሻገር ያስችላሉ።

10 ሮም ከእነዚህ መንገዶች በተጨማሪ 27,000 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው ለጉዞ አመቺ የሆኑ ወንዞችና መተላለፊያ ቦዮች ነበሯት። የሮም መርከቦች በመቶዎች የሚቆጠሩ ወደቦችን በሚያገናኙ 900 በሚያህሉ የባሕር መስመሮች ይጓዙ ነበር። በመሆኑም ክርስቲያኖች በመላው የሮም ግዛቶች መዘዋወር ችለዋል። እርግጥ አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች መኖራቸው አይቀርም፤ ይሁንና ሐዋርያው ጳውሎስም ሆነ ሌሎች፣ በመላው የሮም ግዛት ውስጥ ያለ ፓስፖርትና ቪዛ መጓዝ ይችሉ ነበር። የኢሚግሬሽን ቢሮዎችም ሆኑ የጉምሩክ የፍተሻ ጣቢያዎች አልነበሩም። ወንበዴዎች በሮም መንግሥት የሚደርስባቸውን ቅጣት ስለሚፈሩ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ መንገዶቹ ለጉዞ አስጊ አልነበሩም። የሮም የባሕር ኃይል፣ የመጓጓዣ መስመሮቹ ከባሕር ላይ ወንበዴዎች ነፃ እንዲሆኑ ስላደረገ የባሕር ጉዞም ቢሆን የሚያስፈራ አልነበረም። ጳውሎስ በተለያዩ ጊዜያት የመርከብ መሰበር አደጋ እና በባሕር ላይ የሚያጋጥም ችግር ደርሶበት የነበረ ቢሆንም በጉዞ ወቅት የባሕር ላይ ወንበዴዎች ችግር እንዳደረሱበት የሚጠቅስ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም።—2 ቆሮ. 11:25, 26

ቋንቋ ያበረከተው አስተዋጽኦ

ኮዴክስ ጥቅሶችን ማውጣት ቀላል እንዲሆን አድርጓል (አንቀጽ 12ን ተመልከት)

11. ደቀ መዛሙርቱ በግሪክኛ እንዲጠቀሙ ያደረጋቸው ምንድን ነው?

11 ኮይኔ ተብሎ የሚጠራው የጋራ መግባቢያ የነበረው ግሪክኛ በክርስቲያን ጉባኤዎች ውስጥ ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ እንዲኖር ያስቻለ ከመሆኑም ሌላ በመካከላቸው አንድነት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ አድርጓል። ታላቁ እስክንድር ብዙ ቦታዎችን ድል አድርጎ በመቆጣጠሩ በርካታ ሰዎች ግሪክኛ የሚችሉ ሲሆን በዚህ ቋንቋ ይግባቡ ነበር። ይህም የአምላክ አገልጋዮችን ከሁሉም ዓይነት ሰዎች ጋር ለመግባባት ስላስቻላቸው ምሥራቹ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ በግብፅ የሚኖሩ አይሁዳውያን የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ወደ ግሪክኛ ተርጉመዋል። ሰብዓ ሊቃናት ተብሎ የሚጠራው ይህ ትርጉም በብዙዎች ዘንድ የታወቀ ሲሆን የጥንቶቹ የክርስቶስ ተከታዮችም ከዚህ መጽሐፍ ላይ በተደጋጋሚ ይጠቅሱ  ነበር። በተጨማሪም ክርስቲያኖች የሚያዘጋጇቸውን ጽሑፎች በግሪክኛ መጻፍ አመቺ ሆኖላቸው ነበር። ቋንቋው በርካታ ቃላት አሉት፤ እንዲሁም መንፈሳዊ ጉዳዮችን በደንብ ለማብራራት የሚያስችሉ ብዙ አገላለጾች ነበሩት።

12. (ሀ) ኮዴክስ ምንድን ነው? ከጥቅልል የተሻለ የሆነው እንዴት ነው? (ለ) ክርስቲያኖች በኮዴክስ በስፋት መጠቀም የጀመሩት መቼ ነው?

12 ክርስቲያኖች በአገልግሎታቸው የሚጠቀሙባቸው ቅዱሳን መጻሕፍትስ የተዘጋጁት በምን መልክ ነበር? ጥቅልሎች ለአጠቃቀም ምቹ አልነበሩም፤ ምክንያቱም እነሱን መጠቅለልና መተርተር የሚያስፈልግ ከመሆኑም ሌላ አብዛኛውን ጊዜ ብራናው ላይ የሚጻፈው በአንደኛው ገጽ ብቻ ነው። የማቴዎስ ወንጌል በራሱ አንድ ጥቅልል ይወጣዋል። ከጊዜ በኋላ ግን ኮዴክስ (በመጽሐፍ መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ) ጥቅም ላይ መዋል ጀመረ። ኮዴክስ የሚዘጋጀው በርካታ ገጾችን አንድ ላይ በመጠረዝ ነው። አንባቢው ኮዴክሱን ገልጦ የሚፈልገውን ጥቅስ በቀላሉ ማግኘት ይችላል። ክርስቲያኖች በኮዴክስ መጠቀም የጀመሩት መቼ እንደሆነ በእርግጠኝነት ባይታወቅም አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “በሁለተኛው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በኮዴክስ በስፋት ይጠቀሙ ስለነበር ሥራ ላይ መዋል የጀመረው ከ100 ዓ.ም. በፊት መሆን አለበት” ብሏል።

የሮም ሕግ ያበረከተው አስተዋጽኦ

13, 14. (ሀ) ጳውሎስ የሮም ዜግነት ያለው መሆኑ የጠቀመው እንዴት ነው? (ለ) የሮም ሕግ ክርስቲያኖችን የጠቀማቸው እንዴት ነው?

13 የሮም ሕግ በመላው ግዛት ተፈጻሚነት ነበረው፤ የሮም ዜግነት ደግሞ ልዩ ልዩ መብቶችን የሚያጎናጽፍ ከመሆኑም ሌላ ግለሰቦች ጥበቃ እንዲያገኙ ያስችላል። ጳውሎስ የሮም ዜጋ መሆኑ ያስገኘለትን መብት በተለያዩ ጊዜያት ተጠቅሞበታል። ሐዋርያው፣ በኢየሩሳሌም ሊገረፍ ሲል ሮማዊውን መኮንን “አንድን ሮማዊ ያለ ፍርድ ለመግረፍ ሕግ ይፈቅድላችኋል?” በማለት ጠየቀው። ሕጉ አይፈቅድም። ስለዚህ ጳውሎስ በትውልድ ሮማዊ መሆኑን ሲገልጽ “እየገረፉ ሊመረምሩት የነበሩት ሰዎች ወዲያውኑ ከእሱ ራቁ፤ የሠራዊቱ ሻለቃም [ጳውሎስን] አስሮት ስለነበር ሮማዊ መሆኑን ሲያረጋግጥ ፈራ።”—ሥራ 22:25-29

14 ጳውሎስ፣ የሮም ዜጋ መሆኑ በፊልጵስዩስ ሰዎች እሱን በያዙበት መንገድ ላይ ለውጥ አምጥቷል። (ሥራ 16:35-40) በኤፌሶን የከተማዋ ዋና ጸሐፊ፣ በቁጣ የተነሳውን ሕዝብ ካረጋጋ በኋላ የሮምን ሕግ ጠቅሷል። (ሥራ 19:35-41) ጳውሎስ በቂሳርያ እያለ ይግባኝ መጠየቁ በቄሳር ፊት ቀርቦ ስለ እምነቱ መልስ ለመስጠት አጋጣሚ ከፍቶለታል። (ሥራ 25:8-12) ከዚህ ለማየት እንደምንችለው የሮም  ሕግ ‘ለምሥራቹ ለመሟገትና ምሥራቹ በሕግ የጸና እንዲሆን ለማድረግ’ አስችሏል።—ፊልጵ. 1:7

የአይሁዳውያን መፍለስ ያስገኘው ውጤት

15. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የአይሁዳውያን ማኅበረሰብ በዓለም ላይ ምን ያህል ተስፋፍቶ ነበር?

15 የአይሁድ ኅብረተሰብ በሮም ግዛቶች በሙሉ መበተኑ ክርስቲያኖች የወንጌላዊነት ሥራቸውን ማከናወን ቀላል እንዲሆንላቸው አስችሏል። ከበርካታ መቶ ዘመናት በፊት አሦራውያን በኋላም ባቢሎናውያን፣ አይሁዳውያንን ከአገራቸው በግዞት ወስደዋቸው ነበር። በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. እንኳ በ127ቱም የፋርስ ግዛት አውራጃዎች ውስጥ ተበታትነው የሚኖሩ የአይሁዳውያን ማኅበረሰቦች ነበሩ። (አስ. 9:30) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት በግብፅ እና በሌሎች የሰሜን አፍሪካ ክፍሎች እንዲሁም በግሪክ፣ በትንሿ እስያና በሜሶጶጣሚያ የአይሁድ ማኅበረሰቦች ይገኙ ነበር። በዚያን ጊዜ በሮም ግዛት ውስጥ ከሚኖሩት 60,000,000 ሰዎች መካከል ከ14ቱ አንዱ አይሁዳዊ እንደነበር ይገመታል። አይሁዳውያን በሄዱበት ሁሉ የሚከተሉት የራሳቸውን ሃይማኖት ነበር።—ማቴ. 23:15

16, 17. (ሀ) አይሁዳውያን ወደተለያዩ አካባቢዎች መፍለሳቸው አይሁዳዊ ያልሆኑ በርካታ ሰዎችን የጠቀማቸው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ለ) ደቀ መዛሙርቱ የተቀበሏቸው አንዳንድ የአይሁዳውያን ልማዶች የትኞቹ ናቸው?

16 አይሁዳውያን ወደተለያዩ አካባቢዎች መፍለሳቸው አይሁዳውያን ያልሆኑ በርካታ ሰዎች የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዲያውቁ መንገድ ከፍቷል። እነዚህ ሰዎች እውነተኛው አምላክ አንድ ብቻ እንደሆነና አገልጋዮቹም የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹን መከተል እንደሚጠበቅባቸው ተገንዝበው ነበር። ከዚህም ሌላ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ መሲሑ የሚገልጹ በርካታ ትንቢቶች ይዘዋል። (ሉቃስ 24:44) አይሁዳውያንም ሆኑ ክርስቲያኖች፣ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፉ ያምኑ ነበር፤ በመሆኑም ጳውሎስ የጽድቅ ዝንባሌ ላላቸው ሰዎች ሲሰብክ በጋራ የሚያግባባቸው ነጥብ ማግኘት ችሏል። ሐዋርያው ወደ አይሁዳውያን ምኩራብ ገብቶ ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ከእነሱ ጋር የመወያየት ልማድ ነበረው።—የሐዋርያት ሥራ 17:1, 2ን አንብብ።

17 አይሁዳውያን አምልኳቸውን የሚያከናውኑበት ሥርዓት ነበራቸው። በምኩራቦች ወይም ክፍት በሆኑ የመሰብሰቢያ ቦታዎች አዘውትረው ይሰበሰቡ ነበር። መዝሙር ይዘምሩ፣ ይጸልዩ እንዲሁም በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ይወያዩ ነበር። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የክርስቲያን ጉባኤዎችም ተመሳሳይ ሥርዓት ይከተላሉ።

በይሖዋ እርዳታ ተችሏል

18, 19. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ሁኔታዎች ምን አጋጣሚ ከፍተዋል? (ለ) እስካሁን የተመለከትናቸው ነጥቦች ስለ ይሖዋ ምን እንዲሰማህ አድርገዋል?

18 እስካሁን እንደተመለከትነው የተለያዩ አስገራሚ ሁኔታዎች አንድ ላይ መቀናጀታቸው ምሥራቹ በተሳካ ሁኔታ እንዲሰበክ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ፓክስ ሮማና፣ ከቦታ ቦታ መጓጓዝ በአንጻራዊ ሁኔታ ቀላል መሆኑ፣ በስፋት የሚሠራበት ቋንቋ መኖሩ፣ የሮም ሕግ እንዲሁም አይሁዳውያን ወደተለያዩ አካባቢዎች መፍለሳቸው የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አምላክ የሰጣቸውን የስብከት ሥራ ለማከናወን ረድተዋቸዋል።

19 ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከ400 ዓመታት በፊት ግሪካዊው ፈላስፋ ፕላቶ በጽሑፍ ሥራው ላይ ካካተታቸው ገጸ ባሕርያት አንዱ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እኛ ያለንበትን የዚህን አጽናፈ ዓለም ፈጣሪና አባት ለማወቅ መጣር አድካሚ ሥራ ይሆናል፤ እሱን ማግኘት ብንችል እንኳ ስለ እሱ ለእያንዳንዱ ሰው መናገር የማይቻል ነገር ነው።” ይሁንና ኢየሱስ “በሰዎች ዘንድ የማይቻል ነገር በአምላክ ዘንድ ይቻላል” ብሏል። (ሉቃስ 18:27) የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ፣ ሰዎች እንዲያገኙትና እንዲያውቁት ይፈልጋል። ከዚህም ሌላ ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት ነግሯቸዋል። (ማቴ. 28:19) በይሖዋ አምላክ እርዳታ ይህን ተልእኮ ማሳካት ይቻላል። የሚቀጥለው ርዕስ ይህ ሥራ በዘመናችን እየተከናወነ ያለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።