በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ዓለም አቀፉን የማስተማር ሥራችንን ይመራል

ይሖዋ ዓለም አቀፉን የማስተማር ሥራችንን ይመራል

‘እኔ ይሖዋ አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ።’—ኢሳ. 48:17

1. በዚህ ዘመን ክርስቲያኖች ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ምን እንቅፋቶች አጋጥመዋቸዋል?

በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃና በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች * በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸው ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ የሚያውጁት መልእክት በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም። በጊዜው ቁጥራቸው አነስተኛ ሲሆን ዓለም የሚመለከታቸውም ያን ያህል የተማሩ ሰዎች እንዳልሆኑ አድርጎ ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የሰይጣን ዲያብሎስን “ታላቅ ቁጣ” መቋቋም ይኖርባቸዋል። (ራእይ 12:12) ከዚህም ሌላ የስብከቱ ሥራቸውን የሚያከናውኑት “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” በተባሉት “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ውስጥ ነው።—2 ጢሞ. 3:1

2. ይሖዋ በዘመናችን የስብከቱ ሥራ እየተስፋፋ እንዲሄድ ምን ሲያደርግ ቆይቷል?

2 ያም ቢሆን የይሖዋ ዓላማ በዘመናችን ሕዝቡ ምሥራቹን ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን እንዲሰብኩ ነው፤ ይህን ዓላማውን ዳር ከማድረስ ደግሞ ምንም ነገር ሊያግደው አይችልም። ይሖዋ፣ የጥንቱን የእስራኤል ብሔር ከባቢሎን ነፃ እንዳወጣ ሁሉ በዘመናችን ያሉ አገልጋዮቹንም በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ ከምትወክለው ‘ከታላቂቱ ባቢሎን’ ነፃ አውጥቷቸዋል። (ራእይ 18:1-4) ይሖዋ የሚያስተምረን ለጥቅማችን ነው፤ ሰላም በመስጠት ባርኮናል እንዲሁም የተማርነውን ነገር ለሌሎች እንድናስተምር  ይፈልጋል። (ኢሳይያስ 48:16-18ን አንብብ።) ይህ ሲባል ግን ይሖዋ የመንግሥቱ ስብከት ሥራ በስፋት እንዲከናወን ለማድረግ ሲል ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስቀድሞ የማወቅ ችሎታውን በመጠቀም በምድር ላይ የሚከናወነውን እያንዳንዱን ነገር ያውቃል እንዲሁም በሚፈልገው መንገድ ይመራዋል ማለት አይደለም። እርግጥ ለስብከቱ እንቅስቃሴያችን ምቹ የሆኑ አንዳንድ ሁኔታዎች እንደነበሩ አይካድም፤ ይሁንና በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው በዚህ ዓለም ውስጥ ተልእኳችንን አስቸጋሪ ያደረጉብንን እንደ ስደትና መከራ ያሉ ሁኔታዎች በጽናት ማለፍ የቻልነው በይሖዋ እርዳታ ብቻ ነው።—ኢሳ. 41:13፤ 1 ዮሐ. 5:19

3. እውነተኛ “ዕውቀት” የበዛው እንዴት ነው?

3 ይሖዋ እውነተኛ “ዕውቀት” በፍጻሜው ዘመን እንደሚበዛ በነቢዩ ዳንኤል በኩል ትንቢት አስነግሮ ነበር። (ዳንኤል 12:4ን አንብብ።) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሕዝበ ክርስትና ትምህርቶች የተነሳ ለዘመናት ተሰውረው የቆዩ የቅዱሳን መጻሕፍት መሠረታዊ እውነቶችን እንዲገነዘቡ ይሖዋ ረድቷቸዋል። በአሁኑ ጊዜ እውነተኛው እውቀት በመላው ምድር እንዲታወቅ ለማድረግ በሕዝቡ እየተጠቀመ ነው። በዛሬው ጊዜ የዳንኤል ትንቢት ሲፈጸም እየተመለከትን ነው። ወደ 8,000,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተቀበሉ ሲሆን ይህን እውነት በዓለም ዙሪያ በማወጅ ላይ ናቸው። ታዲያ ይህ ዓለም አቀፋዊ የስብከት ሥራ እንዲሳካ አስተዋጽኦ ያደረጉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ለሥራው ያበረከቱት እገዛ

4. በ19ኛው መቶ ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህል በስፋት ተተርጉሞ ነበር?

4 ምሥራቹን በማወጁ ሥራ እገዛ ያደረገልን አንዱ ነገር መጽሐፍ ቅዱስ በብዛት መሰራጨቱ ነው። ለበርካታ መቶ ዘመናት የሕዝበ ክርስትና የሃይማኖት መሪዎች፣ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያነቡ ሲያከላክሉ እንዲያውም ሲቃወሙ ቆይተዋል፤ አልፎ ተርፎም መጽሐፍ ቅዱስን የተረጎሙ አንዳንድ ሰዎችን አስገድለዋል። ይሁን እንጂ በ19ኛው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት፣ የአምላክ ቃል በከፊልም ሆነ በሙሉ 400 በሚያህሉ ቋንቋዎች እንዲተረጎም አደረጉ። በዚያ ምዕተ ዓመት መገባደጃ ላይ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ነበራቸው፤ ሆኖም ቅዱሳን መጻሕፍት ስለሚያስተምሩት ትምህርት ትክክለኛ እውቀት አልነበራቸውም።

5. የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በመተርጎም ረገድ ምን አከናውነዋል?

5 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መስበክ እንዳለባቸው ተገንዝበው ነበር፤ ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ትምህርት ያለምንም መታከት አብራርተዋል። በተጨማሪም የይሖዋ ሕዝቦች የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ተጠቅመዋል እንዲሁም አሰራጭተዋል። ከ1950 ጀምሮ የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉምን በከፊልም ሆነ በሙሉ ከ120 በሚበልጡ ቋንቋዎች አዘጋጅተዋል። በ2013 በእንግሊዝኛ የተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም የአምላክን ቃል ወደ ሌሎች ቋንቋዎች የመተርጎሙ ሥራ ቀለል እንዲል ያግዛል። ለመረዳት የማይከብድና ለማንበብ ቀላል የሆነ መጽሐፍ ቅዱስ መጠቀማችን ደግሞ የስብከቱ ሥራችንን ለማከናወን ይረዳናል።

ሰላም መኖሩ ያስገኘው ጥቅም

6, 7. (ሀ) በዘመናችን የተካሄደው ጦርነት ምን ያህል ስፋት አለው? (ለ) በአንዳንድ አገሮች የታየው አንጻራዊ ሰላም ለስብከቱ ሥራችን ጠቃሚ የሆነው እንዴት ነው?

6 ‘በዓለም ላይ ምን ያህል ሰላም ሰፍኖ ያውቃል?’ ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በ20ኛው መቶ ዘመን በተለይ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች የተነሳ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አልቀዋል። ይሁንና በ1942 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተፋፍሞ እያለ በወቅቱ ለይሖዋ ምሥክሮች ሥራ አመራር ይሰጥ የነበረው ወንድም ናታን ኖር በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ “ሰላም—ዘላቂ ሊሆን ይችላል?” የሚል ርዕስ ያለው ንግግር ሰጥቶ ነበር። በዚህ ንግግር ላይ በራእይ ምዕራፍ 17 ላይ ተመሥርቶ የቀረበው ማስረጃ በወቅቱ የነበረው ጦርነት ወደ አርማጌዶን የሚመራ እንዳልሆነ፣ እንዲያውም ከዚያ በኋላ ሰላም የሚሰፍንበት ጊዜ እንደሚኖር ጠቁሟል።—ራእይ 17:3, 11

7 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ በዓለም ላይ ፍጹም ሰላም አልሰፈነም። አንድ አኃዛዊ ዘገባ እንዳስቀመጠው ከ1946 እስከ 2013 ባለው ጊዜ  ውስጥ መሣሪያ በታጠቁ አንጃዎች መካከል የተካሄዱ 331 ግጭቶች ነበሩ። በዚህ ሳቢያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ያም ቢሆን በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በብዙ አገሮች አንጻራዊ ሰላም የነበረ ሲሆን የይሖዋ ሕዝቦች ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ምሥራቹን አውጀዋል። ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል? በ1944 በዓለም ዙሪያ የሚገኙት የመንግሥቱ አስፋፊዎች 110,000 አይሞሉም ነበር። በዛሬው ጊዜ ግን ወደ 8,000,000 የሚጠጉ አስፋፊዎች አሉ! (ኢሳይያስ 60:22ን አንብብ።) ሰላም በሰፈነበት ሁኔታ ምሥራቹን መስበክ በመቻላችን አመስጋኞች አይደለንም?

ከቦታ ቦታ መጓዝ ቀላል መሆኑ ያስገኘው ጥቅም

8, 9. ከመጓጓዣ ጋር በተያያዘ ምን እድገቶች ታይተዋል? ለስብከቱ ሥራችን እገዛ ያበረከቱትስ እንዴት ነው?

8 በመጓጓዣ መስክ የተደረገው እድገት ለስብከቱ ሥራ የተመቻቸ ሁኔታ ፈጥሯል። በ1900 ይኸውም የመጀመሪያው መጠበቂያ ግንብ ከታተመ ከ21 ዓመታት በኋላ በመላው ዩናይትድ ስቴትስ የነበሩት ተሽከርካሪዎች ብዛት 8,000 ብቻ ነበር፤ ለተሽከርካሪ ምቹ የሆኑት መንገዶችም ከጥቂት መቶ ኪሎ ሜትሮች አይበልጡም ነበር። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከአንድ ቢሊዮን ተኩል በላይ ተሽከርካሪዎች ያሉ ሲሆን ብዙ ሚሊዮን ኪሎ ሜትሮች የሚሸፍኑ ጥሩ መንገዶችም አሉ። መኪኖችና መንገዶች መኖራቸው ብዙዎቻችን፣ ራቅ ባሉ አካባቢዎች ለሚገኙ ሰዎች ምሥራቹን ለማድረስ አስችሎናል። እርግጥ ነው፣ ምቹ የሆኑ መጓጓዣዎች በሌሉባቸው ቦታዎች ረጅም ርቀት በእግራችን መሄድ ቢኖርብንም እንኳ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ አስፈላጊውን ትጋት ከማሳየት ወደኋላ አንልም።—ማቴ. 28:19, 20

9 ሌሎች የመጓጓዣ ዓይነቶችም ለሥራችን አስተዋጽኦ አድርገዋል። የጭነት መኪናዎች፣ መርከቦችና ባቡሮች በጣም ርቀው ወደሚገኙ አካባቢዎች በጥቂት ሳምንታት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማድረስ አስችለዋል። አውሮፕላን መኖሩ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች፣ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት፣ ሚስዮናውያንና ሌሎች ወደ ትላልቅ ስብሰባዎች ወይም ወደ ሌሎች ቲኦክራሲያዊ ምድቦቻቸው በፍጥነት እንዲደርሱ አስችሏቸዋል። በተጨማሪም የበላይ አካል አባላትና በዋናው መሥሪያ ቤት የሚሠሩ ወንድሞች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለማበረታታት ብሎም ለማስተማር ወደተለያዩ አገሮች በአውሮፕላን ይጓዛሉ። በመሆኑም በመጓጓዣ መስክ የተደረጉ መሻሻሎች በይሖዋ ሕዝቦች መካከል አንድነት እንዲኖር አድርገዋል።—መዝ. 133:1-3

ቋንቋ ያበረከተው አስተዋጽኦ

10. እንግሊዝኛ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

10 በመጀመሪያው መቶ ዘመን በመላው የሮም ግዛት የጋራ መግባቢያ የነበረው ኮይኔ የሚባለው  ግሪክኛ በስፋት ይነገር ነበር። በዛሬው ጊዜስ የዚህን ያህል የሚነገር ቋንቋ አለ? ብዙዎች እንግሊዝኛ በስፋት እንደሚነገር ይገልጻሉ። እንግሊዝኛ—ዓለም አቀፍ ቋንቋ (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ “ከዓለም ሕዝብ መካከል አንድ አራተኛ የሚሆኑት እንግሊዝኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ አሊያም በቋንቋው በደንብ መግባባት ይችላሉ” ይላል። በብዙ አገሮች ውስጥ ሰዎች በስፋት የሚማሩት የሌላ አገር ቋንቋ እንግሊዝኛ ሲሆን ይህ ቋንቋ ከንግድ፣ ከፖለቲካ፣ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይሠራበታል።

11. እንግሊዝኛ ንጹሑን አምልኮ በማስፋፋት ረገድ ምን አስተዋጽኦ አበርክቷል?

11 እንግሊዝኛ በስፋት ጥቅም ላይ መዋሉ ንጹሑን አምልኮ ለማስፋፋት አስተዋጽኦ አድርጓል። ለበርካታ ዓመታት መጠበቂያ ግንብ እና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች መጀመሪያ የሚታተሙት በእንግሊዝኛ ነበር። እንግሊዝኛ በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሥራ ቋንቋ ሆኖ ያገለግላል። በተጨማሪም በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል በዋነኝነት ትምህርት የሚሰጠው በእንግሊዝኛ ነው።

12. የይሖዋ አገልጋዮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከመተርጎም ጋር በተያያዘ ምን አከናውነዋል? በዚህ ረገድ ቴክኖሎጂ ምን አስተዋጽኦ አበርክቷል?

12 ከሁሉም ብሔራት ለተውጣጡ ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክ ኃላፊነት ስለተሰጠን ጽሑፎቻችንን ወደ 700 በሚጠጉ ቋንቋዎች እንተረጉማለን። ሜፕስ (መልቲላንጉዌጅ ኤሌክትሮኒክ ፐብሊሺንግ ሲስተም) የተባለው የኮምፒውተር ፕሮግራም መዘጋጀቱን ጨምሮ በኮምፒውተር ቴክኖሎጂ የተደረገው እድገት ይህን መጠነ ሰፊ ሥራ ለማከናወን ረድቶናል። በዚህ ረገድ የተከናወነው ሥራ የመንግሥቱን መልእክት ለማሰራጨት ያስቻለን ከመሆኑም ሌላ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድነት እንዲኖረን አድርጓል። እርግጥ ነው፣ ለአንድነታችን ይበልጥ አስተዋጽኦ ያደረገው በጣም አስፈላጊ የሆነውን የቅዱሳን መጻሕፍት እውነት ማወቃችን ይኸውም ‘ንጹሑን ቋንቋ’ መናገራችን ነው።—ሶፎንያስ 3:9ን አንብብ።

ሕጎች ያስገኙት ጥቅም

13, 14. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ብሔራት ከሚያወጧቸው ሕጎችና ከሚያስተላልፏቸው ብያኔዎች ጥቅም ያገኙት እንዴት ነው?

13 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በመላው የሮም ግዛት ይሠራበት በነበረው የሮም ሕግ ተጠቅመዋል። በተመሳሳይም በዛሬ ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ሕግ በሚያስገኝላቸው መብት ይጠቀማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ዋናው መሥሪያ ቤታችን በሚገኝበት በዩናይትድ ስቴትስ፣ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የሃይማኖት፣ የመናገርና የመሰብሰብ ነፃነት ይሰጣል። ይህ ደግሞ በዩናይትድ ስቴትስ ያሉ ወንድሞች የመሰብሰብና መጽሐፍ ቅዱስን በይፋ የመማርም ሆነ የተማሩትን ለሌሎች  የመናገር ነፃነት እንዲኖራቸው አድርጓል። ይሁን እንጂ እነዚህ ወንድሞች አንዳንድ መብቶችን የመጠቀም ነፃነታቸው በሕግ እንዲከበርላቸው ፍርድ ቤት መሄድ ያስፈለጋቸው ጊዜ አለ። (ፊልጵ. 1:7) በዩናይትድ ስቴትስ መብታቸውን የሚጋፋ ብይን ሲሰጥ ለከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ይግባኝ በመጠየቅ ስለ መንግሥቱ የማወጅ መብታቸውን ብዙ ጊዜ አስከብረዋል።

14 የሌሎች አገሮች ፍርድ ቤቶችም የአምልኮ ነፃነታችንና በይፋ የመስበክ መብታችን እንዲከበር አድርገዋል። በአንዳንድ አገሮች በፍርድ ቤት የተረታን ቢሆንም ጉዳዩ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች እንዲታይ ይግባኝ ብለናል። ለምሳሌ ያህል፣ እስከ ሰኔ 2014 ድረስ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ በ57 ጉዳዮች ላይ ለእኛ የፈረደልን ሲሆን ይህ ብያኔ የአውሮፓ ምክር ቤት አባል በሆኑ አገሮች ሁሉ ተፈጻሚ ይሆናል። ‘በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላን’ ብንሆንም የብዙ አገሮች ፍርድ ቤቶች፣ እውነተኛውን አምልኮ የማራመድ መብት እንዳለን ፈርደውልናል።—ማቴ. 24:9

በማስተማሩ ሥራችን ላይ ለውጥ ያመጡ የፈጠራ ውጤቶች

በምድር ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እንዲያገኙ እናደርጋለን

15. በሕትመት ሥራ ረገድ ምን እድገቶች ታይተዋል? ከዚህስ ምን ጥቅም አግኝተናል?

15 የሕትመት ኢንዱስትሪው ያሳየው እድገት በዓለም ዙሪያ ለሚከናወነው የምሥራቹ ስብከት ሥራ አስተዋጽኦ አድርጓል። ሰዎች፣ ዮሐንስ ጉተንበርግ በ1450 ገደማ በፈለሰፈው የማተሚያ መሣሪያ ለብዙ ዘመናት ይጠቀሙ ነበር። ይሁንና ባለፉት ሁለት ምዕተ ዓመታት ውስጥ የሕትመት ኢንዱስትሪው ከፍተኛ እድገት አሳይቷል። የሕትመት መሣሪያዎች በመጠንም ሆነ በፍጥነት ጉልህ መሻሻል አድርገዋል፤ የጥራት ደረጃቸውም ጨምሯል። ወረቀት ማምረትና መጽሐፍ መጠረዝ የሚጠይቀው ወጪ በጣም ቀንሷል። ዘመናዊ የሕትመት ዘዴዎች መፈልሰፋቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ነገር ማተም እንዲቻልና የሥራው ጥራት እንዲጨምር አድርጓል። ታዲያ እነዚህ ነገሮች ለሥራችን ምን ጥቅም አስገኝተዋል? አንድ ምሳሌ እንውሰድ፦ የመጀመሪያው መጠበቂያ ግንብ (የሐምሌ 1879 እትም) የወጣው በ6,000 ቅጂዎችና በእንግሊዝኛ ብቻ ሲሆን የማስተማሪያ ሥዕሎች አልነበሩትም። ከ136 ዓመታት በኋላ በዛሬው ጊዜ እያንዳንዱ የመጠበቂያ ግንብ እትም ከ50,000,000 በሚበልጡ ቅጂዎች ታትሞ ይሰራጫል። መጠበቂያ ግንብ ማራኪ የሆኑ ሥዕሎች ያሉት ባለ ሙሉ ቀለም መጽሔት ከመሆኑም ሌላ ከ200 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይታተማል።

16. በመላው ምድር እንድንሰብክ እገዛ ያበረከቱልን የትኞቹ የፈጠራ ውጤቶች ናቸው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

16 ባለፉት 200 ዓመታት ውስጥ የተፈለሰፉና የአምላክ ሕዝቦች ምሥራቹን ለመስበክ የተጠቀሙባቸው አንዳንድ የፈጠራ ውጤቶችን እንመልከት። ቀደም ሲል ባቡር፣ መኪና እና አውሮፕላን ጠቅሰናል፤ ብስክሌት፣ የጽሕፈት መኪና፣ የብሬይል መሣሪያዎች፣ ቴሌግራፍ፣ ስልክ፣ ካሜራ፣ የድምፅና የምስል መቅረጫዎች፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎች፣ ኮምፒውተር ብሎም ኢንተርኔት ሳይጠቀሱ የሚታለፉ አይደሉም። እነዚህ ነገሮች ደቀ መዛሙርት የማድረግ ተልእኳችንን ለመወጣት በተለያዩ መንገዶች ረድተውናል። የይሖዋ ሕዝቦች ‘የነገሥታትን ጡት እንደሚጠቡ’ ትንቢት ተነግሯል፤ በዚህ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት መጽሐፍ ቅዱስን እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በብዙ ቋንቋዎች ለማዘጋጀት ስንል እንደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለው የነገሥታት ሀብት በጥበብ ተጠቅመናል።—ኢሳይያስ 60:16ን አንብብ።

17. (ሀ) የምናየው ማስረጃ ምን መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ያስችለናል? (ለ) ይሖዋ ‘ከእሱ ጋር አብረን እንድንሠራ’ የፈቀደልን ለምንድን ነው?

17 አምላክ እየባረከን እንደሆነ የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ አለን። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ዓላማውን ዳር ለማድረስ የእኛ እርዳታ አያስፈልገውም። ያም ቢሆን አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ‘ከእሱ ጋር አብረን እንድንሠራ’ በመፍቀድ ለእሱም ሆነ ለሰዎች ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችልበት አጋጣሚ ሰጥቶናል። (1 ቆሮ. 3:9፤ ማር. 12:28-31) እንግዲያው በምድር ላይ ከሚከናወኑት ሥራዎች ሁሉ የላቀውን ሥራ ይኸውም የመንግሥቱን መልእክት የማወጅ ተልእኳችንን ለመወጣት ባለን አጋጣሚ ሁሉ እንጠቀም። ይሖዋ ዓለም አቀፉን የማስተማር ሥራ እየመራውና እየባረከው በመሆኑ አመስጋኝ መሆናችንን እናሳይ!

^ አን.1 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው ስም መጠራት የጀመሩት በ1931 ነው።—ኢሳ. 43:10