በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

ይበልጥ የሚያረካ ሙያ አገኘን

ይበልጥ የሚያረካ ሙያ አገኘን

እኔና ግዌን ዳንስ መማር የጀመርነው የአምስት ዓመት ልጆች እያለን ነው። በእርግጥ በዚያ ጊዜ አንተዋወቅም ነበር። ባሌ የሚባለውን የዳንስ ዓይነት ሙያችን ለማድረግ ሁለታችንም ቆርጠን ነበር። ያም ሆኖ በሙያው ቁንጮ ላይ ልንደርስ ስንል ይህን ሥራ እርግፍ አድርገን ተውነው። እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስነው ለምንድን ነው?

ዴቪድ፦ የተወለድኩት ሽሮፕሺር በሚባል የእንግሊዝ ግዛት ውስጥ በ1945 ነው። አባቴ ሰላማዊ በሆነው ገጠራማ አካባቢ እርሻ ነበረው። እኔም ከትምህርት ቤት ስመለስ ዶሮዎችን መመገብ፣ እንቁላላቸውን መሰብሰብ እንዲሁም የሚደልቡ ከብቶችንና በጎችን መንከባከብ ያስደስተኝ ነበር። ትምህርት ቤት ሲዘጋ ደግሞ ሰብል በመሰብሰብ የማግዝ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ትራክተሮቻችንን እነዳለሁ።

ይሁን እንጂ ትኩረቴን እየሳበው የመጣ ሌላ ነገር ነበር። አባቴ፣ ገና ከሕፃንነቴ ጀምሮ ሙዚቃ በሰማሁ ቁጥር መደነስ እንደምፈልግ አስተዋለ። ስለዚህ አምስት ዓመት ሲሆነኝ ታፕ የሚባለውን የዳንስ ዓይነት መማር እንድችል እናቴ በአቅራቢያችን በሚገኘው የዳንስ ትምህርት ቤት እንድታስገባኝ ሐሳብ አቀረበ። አስተማሪዬ፣ የባሌ ደናሽ ለመሆን ተሰጥኦ እንዳለኝ ስለተሰማው ይህንን ዳንስም ጨምሮ አሠለጠነኝ። በ15 ዓመቴ ለንደን በሚገኘውና ስመ ጥር በሆነው ሮያል የባሌ ዳንስ ትምህርት ቤት ነፃ የትምህርት ዕድል አገኘሁ። ከግዌን ጋር የተገናኘነው እዚያ ሲሆን አብረን እንድንደንስ አጣመሩን።

ግዌን፦ ግርግር በበዛበት የለንደን ከተማ ውስጥ በ1944 ተወለድኩ። ትንሽ ልጅ እያለሁ በአምላክ ላይ ትልቅ እምነት ነበረኝ። መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ጥረት ባደርግም ለመረዳት አዳጋች ሆኖብኝ ነበር። የአምስት ዓመት ልጅ እያለሁ ዳንስ መማር ጀምሬ ነበር። ከስድስት ዓመታት በኋላ ከመላው ብሪታንያ የተውጣጡ ተማሪዎች በተሳተፉበት ውድድር በማሸነፌ በሮያል የባሌ ዳንስ ትምህርት ቤት የመማር አጋጣሚ አገኘሁ። ትምህርት ቤቱ የሚገኘው ዋይት ሎጅ በሚባል ከለንደን ወጣ ብሎ በሪችመንድ ፓርክ በሚገኝ ውብ የሆነ ሰፊ ግቢ ውስጥ ነው። እዚያም ትምህርቴን ከመከታተሌም በላይ በሙያቸው አንቱ ከተባሉ አስተማሪዎች የባሌ ዳንስ ሥልጠና አገኘሁ። አሥራ ስድስት ዓመት ሲሆነኝ ደግሞ በማዕከላዊ ለንደን ወደሚገኘው ሮያል የባሌ ዳንስ ትምህርት ቤት ገባሁ፤ ከዴቪድ ጋር የተገናኘነው እዚያ ነው። ከጥቂት ወራት በኋላ በኮቬንት ጋርደን፣ ለንደን በሚገኘው ሮያል ኦፔራ ሃውስ የተባለ ቲያትር ቤት ውስጥ ሙዚቃዊ ተውኔቶች ላይ የባሌ ዳንስ ትርዒቶችን አንድ ላይ ሆነን ማሳየት ጀመርን።

የባሌ ዳንሰኞች በነበርንበት ወቅት በመላው ዓለም እየተዘዋወርን ሠርተናል

ዴቪድ፦ ግዌን እንደገለጸችው በዝነኛው ሮያል ኦፔራ ሃውስ ውስጥ እንዲሁም ከለንደን ፌስቲቫል ባሌ (አሁን ኢንግሊሽ ናሽናል ባሌ ተብሏል) ጋር ትርዒት ማሳየት ጀመርን። በሮያል የባሌ ዳንስ ትምህርት ቤት ውዝዋዜዎችን ከሚያቀናብሩት ሰዎች አንዱ በቩፐርታል፣ ጀርመን ውስጥ ዓለም አቀፋዊ ኩባንያ አቋቋመ፤ እሱም፣ ለብቻ ለብቻ የሚሠሩ የውዝዋዜ ትርዒቶች እንድናሳይ ሁለታችንን መረጠን። በመላው ዓለም እየተዘዋወርን የደነስን ሲሆን እንደ ማርጎ ፎንቴይን እና ሩዶልፍ ኑሪዬቭ ከመሳሰሉ ዝነኛ ሰዎች ጋር የመሥራት አጋጣሚ አግኝተናል። እንዲህ ዓይነቱ ፉክክር የተሞላበት ሕይወት አንድ ሰው ኩሩ እንዲሆን ያደርገዋል፤ እኛም ለሙያችን ያደርን ሰዎች ሆንን።

ግዌን፦ ሕይወቴን ለዳንስ ሰጥቼ ነበር። እኔና ዴቪድ በሙያው ቁንጮ የመሆን ምኞት ነበረን። ለሰዎች መፈረምና አበባ መቀበል እንዲሁም የተመልካቾችን ጭብጨባ መስማት ያስደስተኝ ነበር። በተውኔቱ ዓለም ውስጥ እያለሁ በዙሪያዬ ያሉት ሰዎች በፆታ ብልግና የተዘፈቁ እንዲሁም አጫሾችና ጠጪዎች ነበሩ፤ በተጨማሪም በሙያው ውስጥ ያሉ ሌሎች ሰዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ እኔም መልካም ዕድል ያመጣሉ በሚባሉ ነገሮች እጠቀም ነበር።

ሕይወታችን ሙሉ በሙሉ ተለወጠ

የሠርጋችን ቀን

ዴቪድ፦ በዳንስ ሙያ ውስጥ ብዙ ዓመታት ካሳለፍኩ በኋላ ሁልጊዜ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ መኖር ሰለቸኝ። የልጅነት ሕይወቴ ከግብርና ጋር የተያያዘ ስለነበር በገጠር ያለውን ቀለል ያለ ሕይወት መናፈቅ ጀመርኩ። በመሆኑም በ1967 የዳንስ ሙያዬን ተውኩና በወላጆቼ ቤት አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ትልቅ እርሻ ላይ መሥራት ጀመርኩ። ገበሬው አንዲት አነስተኛ ጎጆ አከራየኝ። ከዚያም ቲያትር ቤት ወደምትሠራው ግዌን ስልክ ደወልኩና እንድታገባኝ ጠየቅኋት። በሙያዋ እድገት አድርጋ ነጠላ ዳንሰኛ ወደመሆን ደረጃ ከመድረሷም ሌላ በዚህ መስክ ይበልጥ ስኬታማ እየሆነች ነበር፤ በመሆኑም ከባድ ውሳኔ ከፊቷ ተደቀነ። ያም ሆኖ የጋብቻ ጥያቄዬን ተቀበለችና ለእሷ አዲስ የሆነውን የገጠር ሕይወት አብራኝ መምራት ጀመረች።

ግዌን፦ ከግብርና ሕይወት ጋር መላመድ አስቸጋሪ እንደነበር አልክድም። ክረምት ከበጋ፣ ላሞችን ማለብ እንዲሁም አሳማዎችንና ዶሮዎችን መመገብ እኔ ከማውቀው ሕይወት በጣም የተለየ ነበር። ዴቪድ ከዘመናዊ የግብርና ዘዴዎች ጋር ለመተዋወቅ ሲል በአንድ የግብርና ኮሌጅ የዘጠኝ ወራት ሥልጠና ጀመረ፤ ማታ ላይ ወደ ቤት እስኪመለስ ድረስ ብቸኝነት ይሰማኝ ነበር። በዚህ ጊዜ የመጀመሪያ ልጃችን ጊሊ ተወልዳ ነበር። ዴቪድ የሰጠኝን ማበረታቻ በመቀበል መኪና መንዳት ተማርኩ፤ አንድ ቀን በአቅራቢያችን ወደምትገኝ ከተማ ሄጄ እያለ ጌልን አየኋት። ጌልን የማውቃት በአካባቢያችን ባለ ሱቅ ውስጥ ስትሠራ ነው።

እንዲሁም እንደተጋባን አካባቢ በግብርና ሥራ ላይ

ጌል ቤቷ ወስዳ ሻይ ጋበዘችኝ። ከዚያም የሠርግ ፎቶግራፎችን መመልከት ጀመርን፤ የእሷን ፎቶግራፎች ስመለከት የተወሰኑ ሰዎች የመንግሥት አዳራሽ በተባለ ቦታ ደጃፍ ላይ የተነሱትን ፎቶግራፍ አየሁ። እኔም ይህ ምን ዓይነት ቤተ ክርስቲያን እንደሆነ ጠየቅኋት። ጌል፣ እሷና ባለቤቷ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ስትነግረኝ ደስ አለኝ። ከአባቴ እህቶች አንዷ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነች አስታወስኩ። በሌላ በኩል ደግሞ አባቴ ምን ያህል ይበሳጭባትና ይጠላት እንደነበር እንዲሁም ጽሑፎቿን የቆሻሻ መጣያ ውስጥ እንደጨመረ ትዝ አለኝ። ለወትሮው ወዳጃዊ ባሕርይ ያለው አባቴ እንደ አክስቴ ባለች ደግ ሴት ላይ ያን ያህል የተናደደው ለምን እንደሆነ ሁልጊዜ ይገርመኝ ነበር።

የአክስቴ እምነት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከምታስተምራቸው ትምህርቶች የሚለየው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ አሁን አጋጣሚ አገኘሁ። ጌል ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምን እንደሆነ አሳየችኝ። አምላክ ሥላሴ እንደሆነና ነፍስ እንደማትሞት የሚገልጹትን ጨምሮ ብዙ መሠረተ ትምህርቶች ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር እንደሚጋጩ ስገነዘብ ተገረምኩ። (መክ. 9:5, 10፤ ዮሐ. 14:28፤ 17:3) በተጨማሪም ይሖዋ የሚለውን የአምላክን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አየሁ።—ዘፀ. 6:3

ዴቪድ፦ ግዌን ስለምትማረው ነገር ነገረችኝ። በልጅነቴ አባቴ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንዳለብኝ ይነግረኝ እንደነበረ አስታወስኩ። በመሆኑም እኔና ግዌን ከጌልና ከባለቤቷ ከዴሪክ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማን። ከስድስት ወራት በኋላ በሽሮፕሺር ግዛት በሚገኘው በአዝዌስትሪ ከተማ ለግብርና የሚሆን የራሳችን ትንሽ ቦታ ለመከራየት አጋጣሚ ስላገኘን ወደዚያ ተዛወርን። እዚያም ዲርድሪ የሚባል በአካባቢው የሚገኝ የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱስን በትዕግሥት ያስጠናን ጀመር። መጀመሪያ ላይ እድገታችን አዝጋሚ ነበር። ከብቶቹን መንከባከብ ሥራ እንዲበዛብን ያደርገን ነበር። ያም ሆኖ ቀስ በቀስ እውነት በልባችን ውስጥ ሥር ሰደደ።

ግዌን፦ በእኔ በኩል ለማሸነፍ የከበደኝ ትልቅ መሰናክል አጉል እምነት ነበር። ኢሳይያስ 65:11 [NW] “መልካም ዕድል ለተባለ አምላክ ማዕድ” የሚያሰናዱ ሰዎችን ይሖዋ እንዴት እንደሚመለከታቸው እንዳስተውል ረዳኝ። መልካም ዕድል ያመጣሉ የሚባሉ ዕቃዎቼንና ክታቦቼን በሙሉ ለማስወገድ ጊዜ ወስዶብኛል፤ እንዲሁም ብዙ መጸለይ አስፈልጎኛል። “ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል” የሚለውን ጥቅስ ማወቄ ይሖዋ የሚፈልገው ምን ዓይነት ሰዎችን እንደሆነ እንድገነዘብ አደረገኝ። (ማቴ. 23:12) ለእኛ በጣም ስለሚያስብ ውድ ልጁን ቤዛ አድርጎ የሰጠንን አምላክ ላገለግለው ፈለግሁ። በዚህ ጊዜ ላይ ሁለተኛዋን ልጃችንን ወልደን ስለነበር ቤተሰባችን ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም መኖር እንደሚችል ማወቃችን በጣም አስደሰተን።

ዴቪድ፦ በማቴዎስ 24 እና በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ እንደሚገኙት ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በአስደናቂ መንገድ ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ስረዳ እውነትን እንዳገኘሁ እርግጠኛ ሆንኩ። በዚህ ሥርዓት ውስጥ የማገኘው ማንኛውም ነገር ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ከመመሥረት ጋር ሊወዳደር እንደማይችል ተገነዘብኩ። በመሆኑም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ ትልቅ ቦታ የመድረስ ምኞቴ እየቀነሰ መጣ። ለባለቤቴና ለልጆቼ የራሴን ያህል ትልቅ ቦታ ልሰጣቸው እንደሚገባ ተረዳሁ። ፊልጵስዩስ 2:4 በራሴና ትልቅ የግብርና ቦታ ለማግኘት ባለኝ ምኞት ላይ ማተኮር እንደሌለብኝ አስገነዘበኝ። ከዚህ ይልቅ በሕይወቴ ውስጥ የይሖዋን አገልግሎት ማስቀደም ይኖርብኛል። ማጨስ አቆምኩ። አሥር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚካሄደው የቅዳሜ ምሽት ስብሰባ ላይ መገኘት ግን ቀላል አልነበረም፤ ምክንያቱም ላሞቻችን መታለብ ያለባቸው በዚያው ሰዓት ነበር። ይሁን እንጂ ግዌን ምስጋና ይግባትና ከስብሰባ ፈጽሞ ቀርተን አናውቅም፤ እንዲሁም ሁልጊዜ እሁድ ጠዋት ላሞቹ ከታለቡ በኋላ ልጆቻችንን አገልግሎት ይዘናቸው እንወጣ ነበር።

ዘመዶቻችን ባደረግነው ለውጥ አልተደሰቱም። የግዌን አባት ለስድስት ዓመታት አኩርፏት ነበር። የእኔ ወላጆችም ቢሆኑ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያለንን ግንኙነት እንድናቋርጥ ጥረት አድርገዋል።

ግዌን፦ ይሖዋ እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በጽናት እንድንወጣቸው ረድቶናል። ደግሞም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ በአዝዌስትሪ ጉባኤ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ለእኛ እንደ ቤተሰብ ሆኑልን፤ ያጋጠሙንን ችግሮች ሁሉ እንድንወጣም በፍቅር ደግፈውናል። (ሉቃስ 18:29, 30) ሕይወታችንን ለይሖዋ ወስነን በ1972 ተጠመቅን። የቻልኩትን ያህል ብዙ ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ ለመርዳት ይበልጥ መሥራት ስለፈለግሁ አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ።

የሚያረካ አዲስ ሙያ

ዴቪድ፦ በግብርና ሙያ ላይ ያሳለፍናቸው ዓመታት አድካሚ ነበሩ፤ ሆኖም በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድ ለልጆቻችን ጥሩ ምሳሌ ለመሆን ጥረት አድርገናል። ከጊዜ በኋላ የመንግሥት ድጎማ ስለቀነሰ የግብርና ሥራችንን ለመተው ተገደድን። ቤትም ሆነ ሥራ አልነበረንም፤ በዚያ ላይ ደግሞ ሦስተኛ ልጃችን ገና አንድ ዓመቷ ነበር፤ በመሆኑም ይሖዋ እንዲረዳንና አመራር እንዲሰጠን ጸለይን። ተሰጥኦዋችንን በመጠቀም የዳንስ ትምህርት ቤት ለመክፈትና ቤተሰባችንን በዚህ ለማስተዳደር ወሰንን። መንፈሳዊ ነገሮችን ለማስቀደም ያደረግነው ቁርጥ ውሳኔ ጥሩ ፍሬ አፍርቷል። ሦስቱም ልጆቻችን ትምህርት ሲጨርሱ አቅኚዎች በመሆናቸው በጣም ተደሰትን። ግዌንም አቅኚ ስለነበረች ለልጆቻችን በየዕለቱ ድጋፍ መስጠት ትችል ነበር።

ሁለቱ ትላልቅ ልጆቻችን፣ ጊሊና ዴኒዝ ትዳር ከያዙ በኋላ የዳንስ ትምህርት ቤቱን ዘጋነው። ከዚያም ለቅርንጫፍ ቢሮው ደብዳቤ በመጻፍ እርዳታ ማበርከት የምንችልበት ቦታ እንዲጠቁሙን ጠየቅን። ቅርንጫፍ ቢሮው በእንግሊዝ ደቡብ ምሥራቃዊ ክፍል ወደሚገኙ ከተሞች መራን። በዚህ ጊዜ ቤት የቀረችው ልጃችን ዴቢ ብቻ በመሆኗ እኔም አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ከአምስት ዓመታት በኋላ በስተ ሰሜን ርቀው የሚገኙ ሌሎች ጉባኤዎችን እንድንረዳ ተጠየቅን። ዴቢ ካገባች በኋላ ደግሞ በዓለም አቀፉ የግንባታ ፕሮግራም ሥር ሆነን በዚምባብዌ፣ በሞልዶቫ፣ በሃንጋሪና በኮት ዲቩዋር ለአሥር ዓመታት የማገልገል መብት አግኝተናል። ከዚያም የለንደን ቤቴል ግንባታ ሲካሄድ በሥራው ለመርዳት ወደ እንግሊዝ ተመለስን። በግብርና ሙያ ተሞክሮ ስለነበረኝ በወቅቱ በቤቴል በነበረው እርሻ ላይ እንዳግዝ ተጠየቅሁ። በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝ ሰሜናዊ ምዕራብ ክፍል በአቅኚነት እያገለገልን ነው።

በዓለም አቀፍ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ በማገልገል ታላቅ ደስታ አግኝተናል

ግዌን፦ መጀመሪያ ሕይወታችንን የሰጠነው ለባሌ ዳንስ ነበር፤ ይህ ሙያ አስደሳች ቢሆንም ጊዜያዊ ነው። ሕይወታችንን ለይሖዋ ለመስጠት ያደረግነውና ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ሁለተኛው ውሳኔያችን ግን ከፍተኛ ደስታ ያመጣልን ሲሆን ዘላለማዊ ነው። አሁንም ቢሆን ከዴቪድ ጋር ተጣምረን እየሠራን ነው፤ አሁን ግን እግሮቻችንን የምንጠቀመው ለዳንስ ሳይሆን አንድ ላይ ሆነን በአቅኚነት ለማገልገል ነው። ብዙ ሰዎች ውድ የሆኑትን ሕይወት አድን እውነቶች እንዲማሩ መርዳት ተወዳዳሪ የሌለው ታላቅ ደስታ አምጥቶልናል። ይህ “የብቃት ማረጋገጫ ደብዳቤ” በዓለም ላይ ከምናገኘው ዝና በእጅጉ ይበልጣል። (2 ቆሮ. 3:1, 2) እውነትን ባናገኝ ኖሮ አሁን የሚቀረን ትዝታ፣ አሮጌ ፎቶግራፎችና የተውኔት ፕሮግራሞች ብቻ ይሆኑ ነበር።

ዴቪድ፦ የይሖዋን አገልግሎት እንደ ሙያችን አድርገን መያዛችን በሕይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። እኔ የባልነትና የአባትነት ኃላፊነቴን በተሻለ ሁኔታ እንድወጣ ረድቶኛል። መጽሐፍ ቅዱስ ማርያም፣ ንጉሥ ዳዊትና ሌሎችም ደስታቸውን በውዝዋዜ እንደገለጹ ይነግረናል። እኛም ከሌሎች ብዙዎች ጋር ሆነን በይሖዋ አዲስ ዓለም ውስጥ በደስታ ለመጨፈር እንናፍቃለን።—ዘፀ. 15:20፤ 2 ሳሙ. 6:14