በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ነቅታችሁ ትጠብቃላችሁ?’

‘ነቅታችሁ ትጠብቃላችሁ?’

“ቀኑንም ሆነ ሰዓቱን ስለማታውቁ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።”—ማቴ. 25:13

1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት ምን ተናገረ? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆኖ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ቁልቁል እየተመለከቱ ኢየሱስ በጣም አስገራሚ ከሆኑት ትንቢቶች አንዱን ሲናገር ማዳመጥ ምን ያህል እንደሚያስደስት መገመት አያዳግትም። ኢየሱስ ወደፊት የሚፈጸሙትን ነገሮች ሲናገር ጴጥሮስ፣ እንድርያስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ተመስጠው እንደሰሙት ጥርጥር የለውም። በዚህ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት ውስጥ እሱ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በሚገዛበት ወቅት ስለሚከናወኑት ነገሮች በስፋት ነግሯቸዋል። በዚያ ወሳኝ ጊዜ የኢየሱስ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ለአገልጋዮቹ የሚያስፈልገውን መንፈሳዊ ምግብ በጊዜው በማቅረብ በምድር ላይ እሱን ወክሎ እንደሚሠራ ገልጾላቸዋል።—ማቴ. 24:45-47

2 ኢየሱስ በዚያው ትንቢት ላይ የአሥሩን ደናግል ምሳሌ ተናገረ። (ማቴዎስ 25:1-13ን አንብብ።) ከዚህ ቀጥሎ በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ትኩረት እናደርጋለን፦ (1) የምሳሌው መልእክት ምንድን ነው? (2) ታማኝ ቅቡዓን በምሳሌው ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ያደረጉት እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል? (3) በዛሬው ጊዜ ሁላችንም ከኢየሱስ ምሳሌ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

የምሳሌው መልእክት ምንድን ነው?

3. ቀደም ባሉት ዓመታት ጽሑፎቻችን የአሥሩን ደናግል ምሳሌ ያብራሩት በምን መንገድ ነው? ይህስ ምን አስከትሎ ሊሆን ይችላል?

3 ታማኙ ባሪያ ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ጥቅሶችን ሲያብራራ፣ ይበልጥ ትኩረት እያደረገ ያለው ትንቢታዊ ጥላነት ባላቸው ነገሮች ላይ ሳይሆን ተግባራዊ ሊሆን በሚችለው ትምህርት ላይ መሆኑን ቀደም ባለው ርዕስ ላይ ተመልክተናል። ከዚህ በፊት ጽሑፎቻችን ኢየሱስ ስለ አሥሩ ደናግል የተናገረውን ምሳሌ ሲያብራሩ መብራቱ፣ ዘይቱ፣ የዘይቱ ዕቃ እና የመሳሰሉትን ነገሮች ጨምሮ እያንዳንዱ ዝርዝር ጉዳይ እንኳ ምሳሌያዊ ትርጉም እንዳለው የገለጹባቸው ወቅቶች ነበሩ። ይሁንና ይህ አካሄድ ምሳሌው ከያዘው ቀላልና አጣዳፊ መልእክት ይልቅ ትኩረታችን በሌሎች ነገሮች እንዲወሰድ አድርጎ ይሆን? ከዚህ ቀጥሎ እንደምናየው የዚህ ጥያቄ መልስ ትልቅ ትርጉም አለው።

4. በምሳሌው ላይ (ሀ) የሙሽራውን (ለ) የደናግሉን ማንነት ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ በዚህ ምሳሌ ላይ ሊያስተላልፍ የፈለገውን ዋና መልእክት እስቲ እንመርምር። መጀመሪያ ዋና ዋናዎቹን ባለታሪኮች እንመልከት። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሙሽራ ማን ነው? ኢየሱስ ስለ ራሱ እየተናገረ እንደነበር ግልጽ ነው። እንዲያውም በሌላ ወቅት ራሱን እንደ ሙሽራ አድርጎ ገልጿል! (ሉቃስ 5:34, 35) ደናግል የተባሉትስ እነማን ናቸው? በምሳሌው ላይ ኢየሱስ፣ ሙሽራው ሲመጣ ደናግሉ መብራታቸውን አብርተው የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጿል። ኢየሱስ “ትንሽ መንጋ” ለሆኑት ቅቡዓን ተከታዮቹ የሰጠውን የሚከተለውን ተመሳሳይ ማሳሰቢያ ልብ በሉ፦ “ወገባችሁን ታጠቁ፤ መብራታችሁንም አብሩ፤ ጌታቸው ከሠርግ እስኪመለስ እንደሚጠባበቁ . . . ሰዎች ሁኑ።” (ሉቃስ 12:32, 35, 36) በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስም ሆነ ሐዋርያው ዮሐንስ በመንፈስ መሪነት ባሰፈሩት ዘገባ ላይ የክርስቶስን ቅቡዓን ተከታዮች ከንጽሕት ድንግል ጋር አመሳስለዋቸዋል። (2 ቆሮ. 11:2፤ ራእይ 14:4) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ በማቴዎስ 25:1-13 ላይ የሚገኘውን ምሳሌ የተናገረው ለቅቡዓን ተከታዮቹ ምክርና ማሳሰቢያ ለመስጠት ብሎ ነው።

5. ኢየሱስ፣ ምሳሌው ስለ የትኛው ጊዜ የሚያወሳ እንደሆነ የጠቆመው እንዴት ነው?

5 ቀጥለን ደግሞ ጊዜውን እንመልከት። ኢየሱስ የሰጠው ምክር ስለ የትኛው ጊዜ የሚያወሳ ነው? ኢየሱስ በምሳሌው መጨረሻ አካባቢ የተናገረው “ሙሽራው ደረሰ” የሚለው ሐሳብ ጊዜውን በግልጽ ይጠቁመናል። (ማቴ. 25:10) የሐምሌ 15, 2013 መጠበቂያ ግንብ እንደሚገልጸው በማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25 ላይ በሚገኘው የኢየሱስ ትንቢት ላይ ክርስቶስ ስለ ‘መድረሱ’ ወይም ስለ ‘መምጣቱ’ ስምንት ቦታዎች ላይ ተጠቅሷል፤ በእያንዳንዱ ጥቅስ ላይ የተሠራበት የግሪክኛ ቃል ተመሳሳይ ነው። በሁሉም ቦታዎች ላይ ኢየሱስ፣ በታላቁ መከራ ወቅት ፍርድ ለመስጠትና ይህን ሥርዓት ለማጥፋት ስለሚመጣበት ጊዜ እየተናገረ ነው። እንግዲያው ይህ ምሳሌ የሚያወሳው ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት ሲሆን ኢየሱስ የሚመጣው ወይም የሚደርሰው በታላቁ መከራ ወቅት ነው።

6. የአሥሩ ደናግል ምሳሌ ከተነገረበት አውድ አንጻር የምሳሌው ዋና መልእክት ምንድን ነው?

6 የምሳሌው ዋና መልእክትስ ምንድን ነው? እስቲ አውዱን ለማስታወስ እንሞክር። ኢየሱስ ስለ ‘ታማኝና ልባም ባሪያው’ ተናግሮ መጨረሱ ነበር። ይህ ባሪያ፣ በመጨረሻዎቹ ቀናት በክርስቶስ ተከታዮች መካከል አመራር የሚሰጠውን ጥቂት አባላት ያሉት የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን ያመለክታል። ኢየሱስ፣ እነዚህ ሰዎች ምንጊዜም ታማኝ መሆን እንዳለባቸው ማሳሰቢያ ሰጥቷል። ቀጥሎም ትኩረቱን በመጨረሻዎቹ ቀናት ወደሚኖሩ ቅቡዓን ተከታዮቹ በሙሉ ያደረገ ሲሆን እነዚህ ክርስቲያኖች ‘ነቅተው እንዲጠብቁ’ ለማሳሰብ ሲል የአሥሩን ደናግል ምሳሌ ተናገረ፤ እንዲህ ካላደረጉ ውድ የሆነውን ሽልማታቸውን ያጣሉ። (ማቴ. 25:13) ይህን ምሳሌ በመመርመር ቅቡዓኑ ምክሩን እንዴት ተግባራዊ እንዳደረጉት እስቲ እንመልከት።

ቅቡዓኑ በምሳሌው ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ እያደረጉ ያሉት እንዴት ነው?

7, 8. (ሀ) ልባሞቹ ደናግል ተሰናድተው እንዲጠብቁ የረዷቸው ሁለት ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) ቅቡዓን ዝግጁ መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነው?

7 ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ ከሞኞቹ በተቃራኒ ልባሞቹ ደናግል ሙሽራው ሲመጣ ለመቀበል ተሰናድተው እየጠበቁ ነበር። ይህን ለማድረግ ያስቻላቸው ምንድን ነው? ሁለት ነገሮች ናቸው፤ ይኸውም ዝግጁና ንቁ መሆናቸው ነው። በሌሊት የሙሽራውን መምጣት እንዲጠባበቁ የተመደቡት ደናግል፣ መብራታቸው እንዳይጠፋ መጠንቀቅ እንዲሁም አስደሳቹ ክንውን እስኪደርስ ባለው ረጅም ጊዜ ንቁ ሆነው መቆየት ነበረባቸው። ከሞኞቹ ደናግል በተለየ፣ አምስቱ ልባም ደናግል መብራታቸውን ብቻ ሳይሆን ዘይትም በዕቃ በመያዝ በሚገባ ተዘጋጅተው ነበር። ታማኝ ቅቡዓንስ በተመሳሳይ ዝግጁ መሆናቸውን አሳይተዋል?

8 እንዴታ! በመጨረሻዎቹ ቀናት በሙሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የተሰጣቸውን ተልእኮ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ በታማኝነት ለመወጣት ዝግጁ በመሆን እንደ ልባሞቹ ደናግል መሆናቸውን አሳይተዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች የታማኝነት ጎዳና የሚያስከፍለውን ወጪ አስልተዋል፤ በሌላ አባባል የተሰጣቸውን ተልእኮ ለመወጣት በሰይጣን ዓለም ውስጥ ሊያገኙ የሚችሏቸውን አብዛኞቹን ቁሳዊ ጥቅሞች መሥዋዕት ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ገና ከጅምሩ ተገንዝበዋል። ለይሖዋ ያደሩ ከመሆኑም በላይ እሱን ብቻ ለማገልገል ራሳቸውን አቅርበዋል፤ ይህን የሚያደርጉት አንድን ቀን ወይም የተወሰነ ጊዜን በአእምሯቸው ይዘው ሳይሆን ለእሱና ለልጁ ባላቸው ፍቅርና ታማኝነት ተገፋፍተው ነው። የዚህ ክፉ ዓለም መንፈስ ብሎም የገንዘብ ፍቅር፣ የሥነ ምግባር ብልግና እንዲሁም ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ዝንባሌ ተጽዕኖ እንዲያሳድርባቸው ባለመፍቀድ ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀዋል። በዚህም መንገድ ምንጊዜም ዝግጁ መሆናቸውን ያሳያሉ፤ ሁልጊዜ ብርሃን አብሪዎች ይሆናሉ፤ እንዲሁም ሙሽራው የዘገየ ቢመስልም እንኳ ተስፋ አይቆርጡም።—ፊልጵ. 2:15

9. (ሀ) ኢየሱስ ከእንቅልፍ ጋር በተያያዘ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል? (ለ) ቅቡዓኑ ‘ሙሽራው እየመጣ ነው!’ ለሚለው ጥሪ ምን ምላሽ ሰጥተዋል? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

9 እነዚህ ደናግል ተሰናድተው እንዲጠብቁ የረዳቸው ሌላው ነገር ደግሞ ንቁ መሆናቸው ነው። ለመሆኑ በሌሊት ለረጅም ሰዓት ሲጠብቁ እንቅልፍ የሚጫጫናቸው አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሊኖሩ ይችላሉ? አዎን። ኢየሱስ፣ ስለ አሥሩ ደናግል ሲናገር ሙሽራው የዘገየ በመሰላቸው ወቅት “ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ” ብሏል። ኢየሱስ፣ ፈቃደኛና ዝግጁ የሆኑ ሰዎችም እንኳ ሥጋ ደካማ መሆኑ ሊያስቸግራቸው እንደሚችል ጠንቅቆ ያውቃል። ታማኝ የሆኑ ቅቡዓን በምሳሌው ላይ የተሰጠውን ይህንን ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ በማድረግ ምንጊዜም ንቁ ለመሆን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጥረት እያደረጉ ነው። በምሳሌው ላይ እንደተገለጸው ‘ሙሽራው እየመጣ ነው!’ የሚል ጥሪ በሌሊት ሲሰማ ሁሉም ደናግል ተነስተዋል። እስከ መጨረሻው የጸኑት ግን ንቁዎቹ ብቻ ናቸው። (ማቴ. 25:5, 6፤ 26:41) በዛሬው ጊዜ ስላሉት ታማኝ ቅቡዓንስ ምን ማለት ይቻላል? በመጨረሻዎቹ ቀናት ያሉት ታማኝ ቅቡዓንም ‘ሙሽራው እየመጣ ነው!’ ለሚለው ጥሪ ምላሽ ሰጥተዋል። ኢየሱስ ሊመጣ መሆኑን የሚጠቁመውን ጠንካራ ማስረጃ በማመን እሱ የሚመጣበትን ጊዜ ተሰናድተው እየተጠባበቁ ጸንተው ቆይተዋል። * ይሁንና የምሳሌው መደምደሚያ የሚያተኩረው በአንድ የተወሰነ ጊዜ ላይ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

ልባሞቹ ሲሸለሙ ሞኞቹ ተቀጡ

10. በልባሞቹና በሞኞቹ ደናግል መካከል የተካሄደው ውይይት ምን ጥያቄ ያስነሳል?

10 በምሳሌው ላይ ከተጠቀሱት ነገሮች መካከል ትንሽ ግር የሚለው መጨረሻ አካባቢ ያለው ሐሳብ ሳይሆን አይቀርም፤ ይህም በሞኞቹና በልባሞቹ ደናግል መካከል የተካሄደው ውይይት ነው። (ማቴዎስ 25:8, 9ን አንብብ።) ይህ ውይይት “በአምላክ ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ ሌሎች እርዳታ ሲጠይቋቸው ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ የማይሆኑት መቼ ነው?” የሚል ጥያቄ ያስነሳል። መልሱን ለማግኘት ምሳሌው የሚፈጸምበትን ጊዜ መለስ ብለን እናስብ። ባገኘነው የተስተካከለ ግንዛቤ መሠረት ሙሽራው ማለትም ኢየሱስ ፍርድ ለመስጠት የሚመጣው የታላቁ መከራ መደምደሚያ ሲቃረብ ነው። እንግዲያው ይህ የምሳሌው ክፍል ያተኮረው ከታላቁ መከራ መደምደሚያ ትንሽ ቀደም ብሎ ባለው ጊዜ ላይ እንደሆነ ማሰቡ ምክንያታዊ አይሆንም? እንደዚህ ብሎ መደምደሙ ተገቢ ይመስላል፤ ምክንያቱም በዚህ ወቅት ቅቡዓኑ የመጨረሻው ማኅተም ይደረግባቸዋል።

11. (ሀ) ታላቁ መከራ ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ምን ይከናወናል? (ለ) ልባሞቹ ደናግል ሞኞቹን ወደ ዘይት ሻጮች መላካቸው ምን ያመለክታል?

11 በመሆኑም በምድር ላይ ያሉ ታማኝ ቅቡዓን በሙሉ ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት የመጨረሻው ማኅተም ይደረግባቸዋል። (ራእይ 7:1-4) ወደ ሰማይ መሄዳቸው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እርግጠኛ ይሆናል። ይሁንና ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ስላሉት ዓመታት እናስብ። ንጹሕ አቋማቸውን ሳይጠብቁ በመቅረታቸው ንቁ ሆነው ያልተገኙ ቅቡዓን ምን ይሆናሉ? ሰማያዊ ሽልማታቸውን ያጣሉ። እነዚህ ሰዎች ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት የመጨረሻው ማኅተም እንደማይደረግባቸው ግልጽ ነው። እነሱን የሚተኩ ሌሎች ታማኝ ክርስቲያኖች ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ጊዜ ተቀብተዋል። ታማኝነታቸውን ያጎደሉት ሞኞች ታላቁ መከራ ሲጀምርና ታላቂቷ ባቢሎን ስትወድቅ ሊደነግጡ ይችላሉ። ሙሽራው ሲመጣ ለመቀበል ዝግጁ አለመሆናቸውን የሚገነዘቡት በዚያ ሰዓት ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሰዎች ጊዜው ከሄደ በኋላ ተጨንቀው እርዳታ ለማግኘት ቢጠይቁ ምን ምላሽ ያገኛሉ? የኢየሱስ ምሳሌ፣ አሳዛኙን እውነታ ግልጽ ያደርግልናል። ልባሞቹ ደናግል ዘይታቸውን ለሞኞቹ ደናግል ለመስጠት ፈቃደኛ አይሆኑም፤ ከዚህ ይልቅ ወደ ዘይት ሻጮች እንዲሄዱ ይነግሯቸዋል። ሞኞቹ የሄዱት ግን “እኩለ ሌሊት ላይ” መሆኑን አስታውስ። በዚህ ሰዓት ዘይት ሻጭ ማግኘት ይችላሉ? በምንም ዓይነት። ምክንያቱም በጣም ዘግይተዋል።

12. (ሀ) በአንድ ወቅት ቅቡዕ የነበሩ ሆኖም የመጨረሻው ማኅተም ከመደረጉ በፊት ንጹሕ አቋማቸውን ያጎደሉ ሰዎች በታላቁ መከራ ወቅት ምን አሳዛኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል? (ለ) እንደ ሞኞቹ ደናግል የሆኑ ሰዎች መጨረሻቸው ምን ይሆናል?

12 በተመሳሳይም ታማኝ ቅቡዓን፣ ታማኝነታቸውን ያጓደሉትን ቅቡዓን በታላቁ መከራ ወቅት ሊረዷቸው አይችሉም። እነዚህ ሰዎች ምንም ዓይነት እገዛ ሊደረግላቸው አይችልም። ምክንያቱም እርዳታ ማግኘት የሚችሉበት ጊዜ አልፏል። ታዲያ መጨረሻቸው ምን ይሆናል? ኢየሱስ ሞኞቹ ደናግል ዘይት ለማግኘት ሲሄዱ ምን እንደተከናወነ ሲገልጽ “ሙሽራው ደረሰ፤ ተዘጋጅተው የነበሩት ደናግልም ወደ ሠርጉ ድግስ ገቡ፤ በሩም ተዘጋ” ብሏል። ታላቁ መከራ ሊደመደም አካባቢ ክርስቶስ በክብሩ ሲመጣ ታማኝ ቅቡዓኑን በሰማይ ይሰበስባቸዋል። (ማቴ. 24:31፤ 25:10፤ ዮሐ. 14:1-3፤ 1 ተሰ. 4:17) በሞኞቹ ደናግል በተመሰሉት ታማኝ ያልሆኑ ቅቡዓን ላይ ግን በሩ ይዘጋባቸዋል። ልክ እንደ ሞኞቹ ደናግል “ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ ክፈትልን!” እያሉ ይጮኹ ይሆናል። የሚያገኙት መልስ ግን በፍየል የተመሰሉት በርካታ ሰዎች በዚያ የፍርድ ሰዓት ከሚሰጣቸው ምላሽ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ኢየሱስ “እውነቴን ነው የምላችሁ፣ አላውቃችሁም” ይላቸዋል። ምንኛ የሚያሳዝን ነው!—ማቴ. 7:21-23፤ 25:11, 12

13. (ሀ) በርካታ የክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች ታማኝ አይሆኑም ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ያልሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ የሰጠው ማሳሰቢያ በቅቡዓኑ ላይ እንደሚተማመን የሚያሳይ እንደሆነ አድርገንም ልንመለከተው የሚገባው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

13 እስካሁን ከተመለከትነው አንጻር ምን ብለን መደምደም እንችላለን? ኢየሱስ በርካታ ቅቡዓን አገልጋዮቹ ታማኝ ባለመሆናቸው በሌላ መተካት እንደሚያስፈልጋቸው መግለጹ ነበር? በጭራሽ። ይህን ምሳሌ ከመናገሩ በፊት “ታማኝና ልባም ባሪያ” ክፉ ባሪያ እንዳይሆን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ እንደነበረ እናስታውስ። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ባሪያው ክፉ እንደሚሆን መጠበቁን የሚያሳይ አይደለም። በተመሳሳይም የአሥሩ ደናግል ምሳሌ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ይዟል። አምስቱ ደናግል ሞኞች፣ አምስቱ ደግሞ ልባም እንደሆኑ ሁሉ እያንዳንዱ ቅቡዕ ክርስቲያንም ዝግጁና ንቁ ለመሆን አሊያም በሞኝነት ታማኝነቱን ለማጉደል ሊመርጥ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ቅቡዕ ለሆኑ የእምነት ባልንጀሮቹ በመንፈስ መሪነት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነጥብ አንስቷል። (ዕብራውያን 6:4-9ን አንብብ፤ ከዘዳግም 30:19 ጋር አወዳድር።) ጳውሎስ የሰጠው ማሳሰቢያ ኃይለኛ እንደሆነ ልብ በሉ፤ ሆኖም ቀጥሎ ከተናገረው ሐሳብ ማየት እንደሚቻለው ክርስቲያን ወንድሞቹና እህቶቹ ‘የተሻለ ሁኔታ’ እንደሚጠብቃቸው እርግጠኛ መሆኑን ፍቅር በተንጸባረቀበት መንገድ ገልጿል። በተመሳሳይም ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የሰጠው ፍቅር የተንጸባረቀበት ማሳሰቢያ በቅቡዓኑ ላይ እንደሚተማመንባቸው ያሳያል። ክርስቶስ፣ እያንዳንዱ ቅቡዕ አገልጋዩ እስከ መጨረሻው ታማኝ በመሆን አስደሳች የሆነ ሽልማት ሊቀበል እንደሚችል ያውቃል።

የክርስቶስ “ሌሎች በጎች” ጥቅም ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?

14. ‘ሌሎች በጎችም’ ከአሥሩ ደናግል ምሳሌ ጥቅም ማግኘት ይችላሉ የምንለው ለምንድን ነው?

14 ኢየሱስ የአሥሩን ደናግል ምሳሌ የተናገረው ለቅቡዓን ተከታዮቹ ነው፤ ታዲያ ይህ ጥቅስ ለክርስቶስ “ሌሎች በጎች” ምንም ጠቃሚ ሐሳብ አልያዘም ማለት ነው? (ዮሐ. 10:16) በፍጹም! የምሳሌው መልእክት አጭር ይኸውም “ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ” የሚል እንደሆነ እናስታውስ። ታዲያ ይህ ምክር የሚሠራው ለቅቡዓኑ ብቻ ነው? ኢየሱስ በአንድ ወቅት “ለእናንተ የምነግራችሁን ለሁሉም እናገራለሁ፤ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ” ብሎ ነበር። (ማር. 13:37) ኢየሱስ ከሁሉም ተከታዮቹ የሚጠብቀው ነገር ተመሳሳይ ነው፤ በታማኝነት ለማገልገል ልባቸውን እንዲያዘጋጁና ንቁ እንዲሆኑ ይፈልጋል። በመሆኑም ሁሉም ክርስቲያኖች፣ ቅቡዓኑ በዚህ ረገድ የተዉትን መልካም ምሳሌ ይከተላሉ፤ እንዲሁም ልክ እንደ እነሱ በሕይወታቸው ውስጥ ለአገልግሎት ቅድሚያ ይሰጣሉ። ሞኞቹ ደናግል፣ ልባሞቹን ከዘይታቸው እንዲሰጧቸው ጠይቀው እንደነበርም ሁላችንም መርሳት የለብንም። ያቀረቡት ከንቱ ጥያቄ ማንም ለእኛ ታማኝ ሊሆንልን፣ በእውነት ውስጥ ሊቆይልን ወይም ንቁ ሆኖ ሊጠብቅልን እንደማይችል ሊያስታውሰን ይገባል። እያንዳንዳችን ይሖዋ ለሾመው ጻድቅ ፈራጅ መልስ መስጠት ይኖርብናል። ዝግጁ መሆን አለብን። ምክንያቱም ኢየሱስ በቅርቡ ይመጣል!

ሞኞቹ ደናግል ዘይት እንዲሰጣቸው ያቀረቡት ጥያቄ ማንም ለእኛ ታማኝ ሊሆንልን ወይም ንቁ ሆኖ ሊጠብቅልን እንደማይችል ሊያስታውሰን ይገባል

15. ክርስቶስ ከሙሽራው ጋር የሚያደርገው ጋብቻ ለሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች አስደሳች የሆነው ለምንድን ነው?

15 ሁሉም ክርስቲያኖች በኢየሱስ ምሳሌ ላይ ከተጠቀሰው ዋና ክንውንም ጥቅም ማግኘት ይችላሉ። ከመካከላችን ይህን የጋብቻ ሥነ ሥርዓት በጉጉት የማይጠብቅ ማን አለ? ቅቡዓን ክርስቲያኖች በዚያ ወቅት ወደ ሰማይ ሄደዋል፤ ከአርማጌዶን ጦርነት በኋላ የክርስቶስ ሙሽራ ይሆናሉ። (ራእይ 19:7-9) በዚያ ወቅት በምድር ላይ የሚኖር ማንኛውም ሰው በሰማይ ከሚከናወነው ከዚህ ሠርግ ጥቅም ያገኛል፤ ምክንያቱም ይህ ጋብቻ ፍጹም የሆነ አገዛዝ እንዲሰፍን ያደርጋል። የወደፊት ተስፋችን በሰማይም ይሁን በምድር የአሥሩ ደናግል ምሳሌ ከያዘው አስፈላጊ ትምህርት ጥቅም ለማግኘት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ልባችንን በማዘጋጀት፣ ጽኑ በመሆንና ከምንጊዜውም ይልቅ ንቁ በመሆን ተሰናድተን እንጠብቅ፤ እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ ያዘጋጀልንን አስደናቂ ሽልማት ማግኘት እንችላለን!

^ አን.9 ከምሳሌው ማየት እንደሚቻለው ‘ሙሽራው እየመጣ ነው!’ (ቁጥር 6) የሚለው ጥሪ በተሰማበትና ሙሽራው በመጣበት ወይም በደረሰበት ወቅት (ቁጥር 10) መካከል ግልጽ የሆነ የጊዜ ልዩነት አለ። ንቁ የሆኑት ቅቡዓን የኢየሱስን መገኘት የሚጠቁመውን ምልክት በመጨረሻዎቹ ቀናት ሁሉ አስተውለዋል። በመሆኑም ኢየሱስ ‘እንደመጣ’ ይኸውም ንጉሣዊ ሥልጣን ይዞ እየገዛ እንደሆነ ተገንዝበዋል። ያም ቢሆን ኢየሱስ እስኪመጣ ወይም እስኪደርስ ድረስ መጽናት አለባቸው።