በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የክርስቶስን ወንድሞች በታማኝነት መደገፍ

የክርስቶስን ወንድሞች በታማኝነት መደገፍ

“ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል።”—ማቴ. 25:40

1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ለቅርብ ወዳጆቹ የትኞቹን ምሳሌዎች ነገራቸው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ከበጎቹና ፍየሎቹ ምሳሌ ጋር በተያያዘ ምን ማወቅ ይኖርብናል?

ኢየሱስ የቅርብ ወዳጆቹ ከሆኑት ከጴጥሮስ፣ ከእንድርያስ፣ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር እያወራ ነው። ስለ ታማኝና ልባም ባሪያ፣ ስለ አሥሩ ደናግል እንዲሁም ስለ ታላንቱ የሚገልጹ ምሳሌዎችን ተናግሮ ጨረሰ። ከዚያም አንድ የመጨረሻ ምሳሌ ነገራቸው። ‘የሰው ልጅ በሕዝቦች ሁሉ’ ላይ ለመፍረድ ስለሚመጣበት ጊዜ ገለጸላቸው። ይህ ምሳሌ ደቀ መዛሙርቱን ምንኛ አስገርሟቸው ይሆን! በምሳሌው ላይ ኢየሱስ በሁለት ቡድኖች ላይ ትኩረት አደረገ፤ የአንደኛው ቡድን አባላት በጎች የሌላኛው ደግሞ ፍየሎች ተብለዋል። ቀጥሎም፣ ትልቅ ቦታ ስለሚሰጠው ሦስተኛ ቡድን የተናገረ ሲሆን የዚህ ቡድን አባላት ‘የንጉሡ ወንድሞች’ እንደሆኑ ተገልጿል።ማቴዎስ 25:31-46ን አንብብ።

2 የይሖዋ ሕዝቦች ለረጅም ጊዜ የዚህን ምሳሌ ትርጉም ለማወቅ ሲጥሩ ቆይተዋል። ይህን ማድረጋቸውም የተገባ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ የሰዎች ዕጣ ምን እንደሚሆን በዚህ ምሳሌ ላይ ተናግሯል። አንዳንዶች የዘላለም ሕይወት የሚያገኙት ሌሎች ግን ወደ ዘላለም ጥፋት የሚሄዱት ለምን እንደሆነ በምሳሌው ላይ ገልጿል። ሕይወት ማግኘታችን የተመካው ኢየሱስ የተናገራቸውን እውነቶች በመረዳታችንና ባገኘነው እውቀት ላይ ተመሥርተን እርምጃ በመውሰዳችን ላይ ነው። ጉዳዩ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ከመሆኑ አንጻር የሚከተሉትን ጥያቄዎች ማንሳታችን አስፈላጊ ነው፦ ይሖዋ ስለዚህ ምሳሌ ያለን ግንዛቤ ደረጃ በደረጃ ግልጽ እንዲሆን ያደረገው እንዴት ነው? ምሳሌው የስብከቱን ሥራ አስፈላጊነት ያጎላል የምንለው ለምንድን ነው? የመስበክ ተልእኮ የተሰጠው ለማን ነው? ‘ለንጉሡ’ እና “ወንድሞቼ” በማለት ለጠራቸው ሰዎች ታማኝ መሆን ያለብን አሁን ነው የምንለው ለምንድን ነው?

ግንዛቤያችን ይበልጥ ግልጽ የሆነው እንዴት ነው?

3, 4. (ሀ) ስለ በጎችና ፍየሎች የሚገልጸውን ምሳሌ ለመረዳት እንድንችል የትኞቹን ቁልፍ ነገሮች ማወቅ ያስፈልገናል? (ለ) የ1881 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ ይህን ምሳሌ ያብራራው እንዴት ነው?

3 ስለ በጎችና ፍየሎች የሚገልጸውን ምሳሌ በትክክል ለመረዳት እንድንችል ከዚህ ዘገባ ጋር በተያያዘ ሦስት ቁልፍ ነገሮችን ማወቅ ያስፈልገናል፤ እነዚህም በምሳሌው ላይ የተጠቀሱት ሰዎችና ቡድኖች ማንነት፣ ፍርድ የሚሰጥበት ጊዜ እንዲሁም በግና ፍየል የሚለውን ፍርድ ለማስተላለፍ መሠረት የሆነው ነገር ናቸው።

4 “የሰው ልጅ” እንዲሁም “ንጉሡ” የተባለው ኢየሱስ እንደሆነ የ1881 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ ገልጾ ነበር። ቀደም ባሉት ዓመታት የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ “ወንድሞቼ” የሚለው አገላለጽ ከክርስቶስ ጋር የሚገዙትን ብቻ ሳይሆን የፍጽምና ደረጃ ላይ የሚደርሱ በምድር የሚኖሩ የሰው ልጆችን በሙሉ እንደሚያመለክት ይሰማቸው ነበር። በጎቹ ከፍየሎቹ የሚለዩትም በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት እንደሆነ ያስቡ ነበር። ሰዎች፣ በግ ተብለው የሚመደቡት ደግሞ በአምላክ የፍቅር ሕግ መሠረት ስለኖሩ እንደሆነ ያምኑ ነበር።

5. በ1920ዎቹ ዓመታት ግንዛቤያችን ይበልጥ ግልጽ የሆነው እንዴት ነው?

5 በ1920ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ይሖዋ፣ ሕዝቡ ከዚህ ምሳሌ ጋር በተያያዘ ያላቸው ግንዛቤ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆን አድርጓል። የጥቅምት 15, 1923 መጠበቂያ ግንብ “የሰው ልጅ” የተባለው ኢየሱስ እንደሆነ በድጋሚ ገለጸ። ይሁንና የክርስቶስን ወንድሞች ማንነት ሲያብራራ እነዚህ ሰዎች ከእሱ ጋር በሰማይ የሚገዙትን ብቻ እንደሚያመለክቱ የሚያሳይ አሳማኝ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አቀረበ፤ በጎቹ ደግሞ በክርስቶስ መንግሥት አገዛዝ ሥር በምድር ላይ ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎችን ያመለክታሉ። በጎቹ ከፍየሎቹ የሚለዩበትን ጊዜ በተመለከተስ ምን ሐሳብ ወጥቶ ነበር? በሺህ ዓመቱ ግዛት ወቅት የክርስቶስ ወንድሞች በሰማይ ከእሱ ጋር በመግዛት ላይ ስለሚሆኑ በዚያ ወቅት በምድር ያሉ ሰዎች ሊረዷቸውም ሆነ ችላ ሊሏቸው እንደማይችሉ መጽሔቱ አብራርቶ ነበር። በመሆኑም በጎቹ ከፍየሎቹ መለየት ያለባቸው ከሺህ ዓመቱ ግዛት በፊት ነው። ሰዎች፣ በግ ተብለው እንዲፈረድላቸው መሠረት የሚሆነው ነገር ደግሞ ኢየሱስን እንደ ጌታቸው አድርገው መቀበላቸውና የተሻለ ሁኔታ የሚገኘው ከእሱ መንግሥት መሆኑን ማመናቸው እንደሆነ መጽሔቱ ገልጿል።

6. በ1990ዎቹ ዓመታት፣ ከምሳሌው ጋር በተያያዘ በነበረን ግንዛቤ ላይ ምን ተጨማሪ ማስተካከያ ተደረገ?

6 እንዲህ ያለው የተስተካከለ ግንዛቤ የይሖዋ ሕዝቦች፣ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት የሚሰጡትን ምላሽ መሠረት በማድረግ በዚህ ሥርዓት የመደምደሚያ ቀናት በሙሉ በጎች ወይም ፍየሎች ተብሎ እየተፈረደባቸው እንደሆነ እንዲያስቡ አድርጓቸው ነበር። ይሁንና በ1990ዎቹ አጋማሽ አካባቢ ይህ ግንዛቤ ማስተካከያ ተደረገበት። በጥቅምት 15, 1995 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡ ሁለት ርዕሶች፣ ኢየሱስ ማቴዎስ 24:29-31 (አንብብ) እና ማቴዎስ 25:31, 32 (አንብብ) ላይ በተናገራቸው ሐሳቦች መካከል ያለውን ተመሳሳይነት ገለጹ። * ታዲያ ምን መደምደሚያ ላይ ደረስን? በአንደኛው ርዕስ ላይ “በበጎቹና በፍየሎቹ ላይ ፍርድ የሚሰጠው ወደፊት እንደሆነ” ተገልጾ ነበር። ለመሆኑ ይህ ጊዜ መቼ ነው? መጽሔቱ እንዲህ ብሏል፦ “በማቴዎስ 24:29, 30 ላይ የተጠቀሰው ‘መከራ’ ከፈነዳና የሰው ልጅ ‘በክብሩ ከመጣ’ በኋላ የሚፈጸም ነገር ነው። . . . ከዚያ በኋላ በጠቅላላው የነገሮች ሥርዓት መጨረሻ ወቅት ኢየሱስ ችሎት ላይ ተቀምጦ ለአንዳንዶቹ ሲፈርድላቸው በሌሎች ላይ ደግሞ የጥፋት ፍርድ ይበይንባቸዋል።”

7. በአሁኑ ጊዜ ምን ግልጽ የሆነ ግንዛቤ አለን?

7 በአሁኑ ጊዜ የበጎቹንና የፍየሎቹን ምሳሌ በተመለከተ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ አለን። በምሳሌው ላይ ስለተገለጹት ሰዎችና ቡድኖች ማንነት እንመልከት፤ “የሰው ልጅ” ወይም ንጉሥ የተባለው ኢየሱስ ነው። ንጉሡ “ወንድሞቼ” ያላቸው ሰዎች ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚገዙ በመንፈስ የተቀቡ ወንዶችና ሴቶች ናቸው። (ሮም 8:16, 17) “በጎቹ” እና “ፍየሎቹ” የተባሉት ደግሞ ከሕዝቦች ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ አይደሉም። ፍርድ የሚሰጥበትን ጊዜ በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ይህ ፍርድ የሚካሄደው በቅርቡ ይኸውም በታላቁ መከራ መደምደሚያ አካባቢ ነው። በሰዎች ላይ በግ ወይም ፍየል የሚለውን ፍርድ ለማስተላለፍ መሠረት የሚሆነው ነገር ምንድን ነው? ይህ ፍርድ የሚሰጠው፣ ሰዎች በምድር ላይ ላሉት በመንፈስ የተቀቡ የክርስቶስ ወንድሞች ያደረጉትን ነገር መሠረት በማድረግ ነው። የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በጣም በቀረበበት በአሁኑ ወቅት ይሖዋ ይህ ምሳሌ እንዲሁም በማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25 ላይ የሚገኙት ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ምሳሌዎች ደረጃ በደረጃ ግልጽ እንዲሆኑልን በማድረጉ ምንኛ አመስጋኞች ነን!

ምሳሌው የስብከቱን ሥራ አስፈላጊነት የሚያጎላው እንዴት ነው?

8, 9. በጎቹ “ጻድቃን” የተባሉት ለምንድን ነው?

8 በበጎቹና በፍየሎቹ ምሳሌ ላይ ኢየሱስ ስለ ስብከቱ ሥራ በቀጥታ አልተናገረም። ታዲያ ይህ ምሳሌ የስብከቱን ሥራ አስፈላጊነት ያጎላል ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው?

9 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኢየሱስ እያስተማረ ያለው በምሳሌ ተጠቅሞ መሆኑን ማስተዋል ይኖርብናል። በመሆኑም ቃል በቃል በጎችን ከፍየሎች ስለ መለየት እየተናገረ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በተመሳሳይም በግ እንደሆነ የተፈረደለት እያንዳንዱ ሰው የክርስቶስን ወንድሞች ቃል በቃል ማብላት፣ ማልበስ፣ መንከባከብ ወይም በታሰሩበት ወቅት መጠየቅ እንዳለበት መግለጹ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በበጎች የተመሰሉት ሰዎች ለወንድሞቹ ስለሚኖራቸው አመለካከት መናገሩ ነው። በጎቹ “ጻድቃን” የተባሉት፣ ክርስቶስ በምድር ላይ የተቀቡ ወንድሞች እንዳሉት ስለተገነዘቡና በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ቅቡዓኑን በታማኝነት ስለደገፏቸው ነው።—ማቴ. 10:40-42፤ 25:40, 46፤ 2 ጢሞ. 3:1-5

10. በጎቹ ለክርስቶስ ወንድሞች ደግነት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

10 በሁለተኛ ደረጃ፣ ኢየሱስ የተናገረውን ምሳሌ አውድ እንመልከት። በወቅቱ ኢየሱስ ስለ መገኘቱና ስለዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት እየተናገረ ነበር። (ማቴ. 24:3) ኢየሱስ በንግግሩ መጀመሪያ አካባቢ፣ የዚህን ምልክት አስደናቂ ገጽታ ገልጾ ነበር፤ ይኸውም የመንግሥቱ ምሥራች ‘በመላው ምድር መሰበኩ’ ነው። (ማቴ. 24:14) ስለ በጎቹና ፍየሎቹ ከመናገሩ በፊት ደግሞ የታላንቱን ምሳሌ ገልጿል። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተብራራው ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረው፣ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ደቀ መዛሙርቱ ወይም ‘ወንድሞቹ’ በስብከቱ ሥራ በቅንዓት መካፈል እንዳለባቸው አበክሮ ለመግለጽ ነው። ይሁንና ኢየሱስ በመንግሥቱ በሚገኝበት ወቅት በምድር ላይ የሚቀሩት ጥቂት ቁጥር ያላቸው ቅቡዓን መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት “ለሕዝቦች ሁሉ” ምሥራቹን መስበክ ከባድ እንደሚሆንባቸው የታወቀ ነው። የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ ቅቡዓኑ እርዳታ እንደሚያገኙ ይጠቁማል። በመሆኑም በጎች እንደሆኑ የሚፈረድላቸው ሰዎች ለክርስቶስ ወንድሞች ደግነት ማሳየት ከሚችሉባቸው ዋነኛ መንገዶች አንዱ በስብከቱ ሥራ እነሱን መደገፍ ነው። ይሁንና ይህ ድጋፍ ምን ይጨምራል? የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገር ወይም ማበረታቻ መስጠት ብቻ ነው? ወይስ ሌላም የሚያስፈልግ ነገር አለ?

የመስበክ ተልእኮ የተሰጠው ለማን ነው?

11. የትኛው ጥያቄ ሊነሳ ይችላል? ለምንስ?

11 በዛሬው ጊዜ ከሚገኙት ስምንት ሚሊዮን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከል አብዛኞቹ በመንፈስ የተቀቡ አይደሉም። ኢየሱስ ለቅቡዓን ባሪያዎቹ የሰጠውን ታላንት አልተቀበሉም። (ማቴ. 25:14-18) በመሆኑም ‘ኢየሱስ የሰጠው የስብከት ተልእኮ በመንፈስ ቅዱስ ያልተቀቡ ክርስቲያኖችንም ይመለከታል?’ የሚለው ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ‘አዎ’ ብለን እንድንመልስ የሚያደርጉ አንዳንድ ምክንያቶችን እንመልከት።

12. ማቴዎስ 28:19, 20 ላይ ከሚገኘው የኢየሱስ ሐሳብ ምን እንማራለን?

12 ኢየሱስ የመስበክ ተልእኮ የሰጠው ለሁሉም ደቀ መዛሙርቱ ነው። ኢየሱስ፣ እሱ ያዘዘውን “ሁሉ” እንዲጠብቁ ሰዎችን እያስተማሩ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለተከታዮቹ መመሪያ ሰጥቷል። እሱ ካዘዛቸው ነገሮች መካከል የስብከት ተልእኮ ይገኝበታል። (ማቴዎስ 28:19, 20ን አንብብ።) እንግዲያው ሁሉም የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት፣ ተስፋቸው በሰማይ መግዛትም ሆነ በምድር ላይ መኖር መስበክ ይጠበቅባቸዋል።—ሥራ 10:42

13. ዮሐንስ የተመለከተው ራእይ ምን ይጠቁማል? ለምንስ?

13 የራእይ መጽሐፍ ቅቡዓኑም ሆኑ ሌሎች ክርስቲያኖች በስብከቱ ሥራ እንደሚካፈሉ ይጠቁማል። ኢየሱስ ለሐዋርያው ዮሐንስ ባሳየው ራእይ ላይ ‘በሙሽራይቱ’ የተመሰሉት ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የሚገዙ 144,000 ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ ሰዎች “የሕይወትን ውኃ በነፃ [እንዲወስዱ]” እየጋበዙ ነው። (ራእይ 14:1, 3፤ 22:17) ይህ ምሳሌያዊ ውኃ፣ ይሖዋ በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ያደረገውን ዝግጅት ያመለክታል። (ማቴ. 20:28፤ ዮሐ. 3:16፤ 1 ዮሐ. 4:9, 10) ቤዛው የምንሰብከው መልእክት ቁልፍ ገጽታ ነው፤ ቅቡዓኑ ደግሞ ሰዎች ስለ ቤዛው እንዲያውቁና ከዚህ ዝግጅት እንዲጠቀሙ በመርዳት ረገድ ግንባር ቀደም ሆነው እየሠሩ ነው። (1 ቆሮ. 1:23) ይሁን እንጂ ዮሐንስ በራእዩ ላይ የሙሽራይቱ ክፍል ያልሆኑ ሌሎች ሰዎችን አይቷል። እነሱም “ና!” እንዲሉ ተነግሯቸዋል። ይህን መመሪያ በመታዘዝ ሌሎችም የሕይወትን ውኃ እንዲወስዱ ይጋብዛሉ። እነዚህ ሰዎች ተስፋቸው በምድር ላይ መኖር ነው። እንግዲያው ይህ ራእይ “ና!” የሚለውን ግብዣ የተቀበሉ ሁሉ ለሌሎች የመስበክ ኃላፊነት እንዳለባቸው በግልጽ ያሳያል።

14. “የክርስቶስን ሕግ” መታዘዝ ምንን ይጨምራል?

14 ‘በክርስቶስ ሕግ’ የሚመሩ ሁሉ መስበክ አለባቸው። (ገላ. 6:2) ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ሁለት ዓይነት መሥፈርት አያወጣም። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያንን “ለመጻተኛው ሆነ ለአገር ተወላጅ አንድ ዐይነት ሕግ ይኑራችሁ” ብሏቸዋል። (ዘሌ. 24:22፤ ዘፀ. 12:49) ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ እንዲመሩ አይጠበቅባቸውም። ይሁንና ቅቡዓኑ ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ክርስቲያኖች ‘በክርስቶስ ሕግ’ ሥር ናቸው። ይህ ሕግ ኢየሱስ ያስተማራቸውን ነገሮች በሙሉ ያካትታል። ኢየሱስ ካስተማራቸው ነገሮች ዋነኛው፣ ተከታዮቹ ፍቅር ማሳየት እንዳለባቸው የሚገልጸው ትምህርት ነው። (ዮሐ. 13:35፤ ያዕ. 2:8) ለአምላክ፣ ለክርስቶስና ለባልንጀራችን ፍቅር እንዳለን ማሳየት ከምንችልባቸው ዋነኛ መንገዶች አንዱ ደግሞ የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ ነው።—ዮሐ. 15:10፤ ሥራ 1:8

15. የኢየሱስ መመሪያ ለሁሉም ተከታዮቹ ይሠራል የምንለው ለምንድን ነው?

15 ኢየሱስ ለተወሰኑ ሰዎች የተናገረው ነገር ለብዙዎችም ሊሠራ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ የመንግሥት ቃል ኪዳን የገባው ከ11 ደቀ መዛሙርቱ ጋር ብቻ ቢሆንም 144,000ዎቹ በሙሉ በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ ይታቀፋሉ። (ሉቃስ 22:29, 30፤ ራእይ 5:10፤ 7:4-8) እንዲሁም ኢየሱስ የመስበክ ተልእኮ የሰጠው ለጥቂት ተከታዮቹ ይኸውም ከሞት ከተነሳ በኋላ ለተገለጠላቸው ብቻ ነው። (ሥራ 10:40-42፤ 1 ቆሮ. 15:6) ይሁንና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ታማኝ ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ ኢየሱስ ይህን ትእዛዝ ሲሰጥ ባይሰሙም እንኳ መመሪያው እነሱንም እንደሚመለከት ተገንዝበው ነበር። (ሥራ 8:4፤ 1 ጴጥ. 1:8) በተመሳሳይም ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ከሚገኙት ስምንት ሚሊዮን የመንግሥቱ ሰባኪዎች አንዳቸውንም በግለሰብ ደረጃ አላነጋገራቸውም። ያም ቢሆን ሁሉም ክርስቲያኖች፣ በክርስቶስ ማመንና በስብከቱ ሥራ አማካኝነት ይህን እምነታቸውን በተግባር ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው ይገነዘባሉ።—ያዕ. 2:18

ታማኝነታችንን የምናስመሠክርበት ጊዜ አሁን ነው

16-18. በጎች ሆነው የሚቆጠሩ ሰዎች የክርስቶስን ወንድሞች መደገፍ የሚችሉት እንዴት ነው? አሁኑኑ ይህን ማድረግ ያለባቸውስ ለምንድን ነው?

16 ሰይጣን በምድር በቀሩት የተቀቡ የክርስቶስ ወንድሞች ላይ ጦርነት አውጇል፤ የቀረው “ጥቂት ጊዜ” እያለቀ ሲሄድ ደግሞ ጥቃቱን ይበልጥ ያፋፍመዋል። (ራእይ 12:9, 12, 17) ቅቡዓኑ የሚገጥማቸውን ከባድ ፈተና ተቋቁመው በታሪክ ውስጥ ታላቅ የሆነውን የስብከት ዘመቻ ግንባር ቀደም ሆነው እየመሩ ነው። ኢየሱስም ከእነሱ ጋር ሆኖ በሥራቸው እየመራቸው እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።—ማቴ. 28:20

17 ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው ከበጎች ቡድን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በስብከቱ ሥራ ብቻ ሳይሆን በሌሎች መንገዶችም የክርስቶስን ወንድሞች መደገፍን እንደ መብት ይመለከቱታል። ለምሳሌ ያህል፣ የገንዘብ መዋጮ ያደርጋሉ፤ እንዲሁም በመንግሥት አዳራሾች፣ በትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች እና በቅርንጫፍ ቢሮዎች ግንባታ እገዛ ያበረክታሉ፤ ከዚህም ሌላ “ታማኝና ልባም ባሪያ” አመራር እንዲሰጡ ለሾማቸው ሰዎች በታማኝነት ይታዘዛሉ።—ማቴ. 24:45-47፤ ዕብ. 13:17

በበጎች የተመሰሉት ሰዎች የክርስቶስን ወንድሞች በተለያዩ መንገዶች ይደግፋሉ (አንቀጽ 17ን ተመልከት)

18 በቅርቡ መላእክት፣ የታላቁን መከራ የጥፋት ነፋሳት ይለቅቃሉ። ይህ የሚሆነው በምድር ላይ የቀሩት የክርስቶስ ወንድሞች በሙሉ የመጨረሻው ማኅተም ከተደረገባቸው በኋላ ነው። (ራእይ 7:1-3) አርማጌዶን ከመፈንዳቱ በፊት ቅቡዓኑ ወደ ሰማይ ይወሰዳሉ። (ማቴ. 13:41-43) በመሆኑም በጎች ተብለው እንዲፈረድላቸው የሚፈልጉ ሁሉ የክርስቶስን ወንድሞች በታማኝነት መደገፍ ያለባቸው አሁን ነው።

^ አን.6 ይህን ምሳሌ በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት በጥቅምት 15, 1995 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡትን “በፍርድ ዙፋኑ ፊት የምትቀርበው እንዴት ነው?” እና “የበጎቹና የፍየሎቹ የወደፊት ዕጣ ምንድን ነው?” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።