በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በጌታ ብቻ” ማግባት—በዘመናችንም ይቻላል?

“በጌታ ብቻ” ማግባት—በዘመናችንም ይቻላል?

“በጉባኤ ውስጥ የትዳር ጓደኛ የሚሆነኝ ሰው ማግኘት አልቻልኩም፤ ብቻዬን እንዳላረጅ እፈራለሁ።”

“በዓለም ውስጥ ያሉ አንዳንድ ወንዶች ደግ፣ ተወዳጅና አሳቢ ናቸው። ሃይማኖቴን አይቃወሙም፤ ደግሞም ከአንዳንድ ወንድሞች ይልቅ ደስ የሚል ነገር አላቸው።”

አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች የትዳር ጓደኛ ማግኘትን በተመለከተ እንዲህ ዓይነት አስተያየት ሰንዝረዋል። በእርግጥ ሐዋርያው ጳውሎስ “በጌታ ብቻ” ስለ ማግባት የሰጠውን ምክር በሚገባ ያውቃሉ፤ ደግሞም ሁሉም ክርስቲያኖች ይህን መመሪያ ሊታዘዙ ይገባል። (1 ቆሮ. 7:39) ታዲያ አንዳንድ ያላገቡ ክርስቲያኖች እንደዚህ ያሉ አስተያየቶች የሚሰነዝሩት ለምንድን ነው?

አንዳንዶች የሚጠራጠሩበት ምክንያት

እንደዚህ ብለው የሚናገሩ ክርስቲያኖች፣ ለጋብቻ የደረሱ ወንድሞችና እህቶች ቁጥር ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ይሰማቸው ይሆናል። በእርግጥም በብዙ አገሮች ይህ እውነት ነው። ሁለት ምሳሌዎችን እንውሰድ፦ ኮሪያ ውስጥ ካላገቡ 100 የይሖዋ ምሥክሮች መካከል በአማካይ 57ቱ እህቶች ሲሆኑ 43ቱ ወንድሞች ናቸው። በኮሎምቢያ ደግሞ 66 በመቶ የሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች እህቶች ሲሆኑ 34 በመቶዎቹ ወንድሞች ናቸው።

በአንዳንድ አገሮች ችግሩን የሚያወሳስበው፣ የማያምኑ ወላጆች ከፍተኛ መጠን ያለው ጥሎሽ መጠየቃቸው ነው፤ ይህም ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆኑ ወንድሞች ማግባት ከባድ እንዲሆንባቸው አድርጓል። እንዲህ ዓይነት እንቅፋቶች በመኖራቸው አንዲት እህት “በጌታ” የማግባት አጋጣሚዋ የመነመነ እንደሆነ ይሰማት ይሆናል። በመሆኑም “ከእምነት አጋሮቼ መካከል ለእኔ የሚሆን ሰው ማግኘት እችላለሁ?” ብላ ታስብ ይሆናል። *

በይሖዋ መተማመን አስፈላጊ ነው

አንቺም እንዲህ ተሰምቶሽ የሚያውቅ ከሆነ ይሖዋ ሁኔታሽን እንደሚረዳ እርግጠኛ ሁኚ። ይሖዋ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚሰማሽ ያውቃል።—2 ዜና 6:29, 30

ያም ሆኖ ይሖዋ፣ በጌታ ብቻ ማግባት እንዳለብን የሚገልጽ መመሪያ በቃሉ ውስጥ አስፍሮልናል። ለምን? ምክንያቱም ሕዝቦቹን የሚጠቅማቸውን ነገር ያውቃል። አገልጋዮቹ ጥበብ የጎደለው አካሄድ መከተል የሚያስከትለው ሥቃይ ውስጥ እንዳይገቡ ሊጠብቃቸው ብቻ ሳይሆን ደስተኞች እንዲሆኑም ጭምር ይፈልጋል። በነህምያ ዘመን ብዙ አይሁዳውያን፣ ይሖዋን የማያመልኩ የሌላ አገር ሴቶችን ያገቡ ነበር፤ በመሆኑም ነህምያ፣ የሰለሞንን መጥፎ ምሳሌነት ጠቀሰላቸው። ሰለሞን ‘በአምላኩ የተወደደ ሰው ቢሆንም ባዕዳን ሴቶች ወደ ኃጢአት መርተውታል።’ (ነህ. 13:23-26) እንግዲያው ይሖዋ፣ እውነተኛ አምላኪዎቹን ብቻ እንድናገባ ያዘዘን ለገዛ ጥቅማችን ሲል ነው። (መዝ. 19:7-10፤ ኢሳ. 48:17, 18) እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላክ ለሚያሳያቸው ፍቅራዊ አሳቢነት አመስጋኞች ናቸው፤ እንዲሁም እሱ በሚሰጠው መመሪያ ይተማመናሉ። በዚህ መንገድ ለእሱ ሲገዙ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዢ መሆኑን እንደሚቀበሉ ያሳያሉ።—ምሳሌ 1:5

አንቺም ከአምላክ ሊያርቅሽ ከሚችል ሰው ጋር “አቻ ባልሆነ መንገድ [ከመጠመድ]” መራቅ እንደምትፈልጊ ጥርጥር የለውም። (2 ቆሮ. 6:14) ብዙ ክርስቲያኖች ጊዜ የማይሽረውንና ለሰው ልጆች ጥበቃ የሚያስገኘውን የአምላክ መመሪያ የተከተሉ ሲሆን ይህም የጥበብ አካሄድ እንደሆነ ተገንዝበዋል። አንዳንዶች ግን ከዚህ የተለየ አካሄድ ለመከተል መርጠዋል።

በዘመናችንም ይቻላል?

ማጊ * የምትባል በአውስትራሊያ የምትኖር አንዲት እህት ከማያምን ሰው ጋር የፍቅር ጓደኝነት በጀመረች ጊዜ የሆነውን ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ከእሱ ጋር ለመሆን ስል ብቻ ብዙ ጊዜ ከስብሰባዎች እቀር ነበር። መንፈሳዊነቴ በጣም አሽቆለቆለ።” በሕንድ የምትኖረው ራታና ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ከሚያጠና የክፍሏ ልጅ ጋር የፍቅር ጓደኝነት ጀመረች። ከጊዜ በኋላ እንደታየው ግን የልጁ ዓላማ እሷን ማግኘት ነበር። ራታና እሱን ለማግባት ስትል እውነትን ትታ የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ሆነች።

ሌላዋ ምሳሌ በካሜሩን የምትኖረው ንዴንኬ ናት። ስታገባ 19 ዓመቷ ነበር። እጮኛዋ፣ ሃይማኖቷን በነፃነት መከተል እንደምትችል ቃል ገብቶላት ነበር። ሠርጉ ካለፈ ከሁለት ሳምንት በኋላ ግን ባለቤቷ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንዳትገኝ ከለከላት። እንዲህ ብላለች፦ “ያተረፍኩት ብቸኝነትና ለቅሶ ብቻ ሆነ። ሕይወቴ ከቁጥጥሬ ውጭ እንደሆነ ተገነዘብኩ። መቼም ቢሆን ልገላገለው በማልችል የጸጸት ስሜት ተዋጥኩ።”

እርግጥ ነው፣ የማያምኑ የትዳር ጓደኞች ሁሉ ጨካኝና ምክንያታዊነት የጎደላቸው ይሆናሉ ማለት አይደለም። የማያምን ሰው በማግባትሽ እነዚህ መዘዞች ባይደርሱብሽም እንኳ ይህን ማድረግሽ ከአፍቃሪው የሰማዩ አባትሽ ጋር ያለሽን ዝምድና የሚነካው እንዴት ነው? ይሖዋ ለገዛ ጥቅምሽ የሰጠውን ምክር ባለመስማትሽ ምን ይሰማሽ ይሆን? ከሁሉ በላይ ደግሞ ስላደረግሽው ውሳኔ ይሖዋ ምን ይሰማዋል?—ምሳሌ 1:33

በመላው ዓለም የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች “በጌታ ብቻ” ማግባት ከሁሉ የተሻለ ምርጫ መሆኑን ይመሠክራሉ። ያላገቡ ክርስቲያኖች፣ ከይሖዋ አምላኪዎች መካከል ብቻ የሚሆናቸውን ሰው መርጠው በማግባት አምላክን ለማስደስት ቆርጠዋል። በጃፓን የምትኖረውን ሚቺኮን እንውሰድ፤ ዘመዶቿ የማያምን ሰው እንድታገባ ሊያግባቧት ጥረት ያደርጉ ነበር። እንዲህ ካለው ተጽዕኖ በተጨማሪ አንዳንድ ጓደኞቿና የምታውቃቸው ክርስቲያኖች በጉባኤ ውስጥ የትዳር ጓደኛ ሲያገኙ መመልከቱ ለእሷ ከባድ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ‘ደስተኛ አምላክ’ ነው፤ በመሆኑም የእኛ ደስታ የተመካው ትዳር በመመሥረታችን ላይ እንዳልሆነ ሁልጊዜ ለማስታወስ እጥራለሁ። በተጨማሪም ይሖዋ የልባችንን ምኞት እንደሚሰጠን አምናለሁ። በመሆኑም ማግባት ብንፈልግም እንኳ የትዳር ጓደኛ ማግኘት ካልቻልን እስከዚያው ሳያገቡ መቆየቱ በጣም የተሻለ ነው።” (1 ጢሞ. 1:11) ከጊዜ በኋላ ሚቺኮ አንድ ጥሩ ወንድም ያገባች ሲሆን በመታገሷ ደስተኛ ነች።

አንዳንድ ወንድሞችም ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት መጠበቅ አስፈልጓቸዋል። በአውስትራሊያ የሚኖረው ቢል እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞታል። አንዳንድ ጊዜ ከጉባኤ ውጭ ያሉ ሴቶች ይማርኩት እንደነበረ ሳይሸሽግ ተናግሯል። ይሁን እንጂ ከእነሱ ጋር የቅርብ ጓደኝነት ላለመመሥረት ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጓል። ለምን? ‘ከማያምን ሰው ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ ወደ መጠመድ’ የሚመራውን የመጀመሪያ እርምጃ መውሰድ ስላልፈለገ ነው። ባለፉት ዓመታት፣ ቢል የወደዳቸው አንዳንድ እህቶች ነበሩ፤ እነሱ ግን ለእሱ እንዲህ ዓይነት ስሜት አልነበራቸውም። ቢል የምትስማማው እህት ያገኘው ከ30 ዓመት በኋላ ነው። እንዲህ ይላል፦ “የሚቆጨኝ ነገር የለም። እንደተባረክሁ ይሰማኛል፤ ምክንያቱም አብረን እናገለግላለን፣ አብረን እናጠናለን እንዲሁም አብረን እንጸልያለን። የባለቤቴ ጓደኞች በሙሉ እንደ እኛ የይሖዋ አምላኪዎች ስለሆኑ ከእነሱ ጋር መገናኘትና አብሬያቸው ጊዜ ማሳለፍም ያስደስተኛል። እኛም የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በመጠቀም ትዳራችንን ለማሻሻል እንጥራለን።”

ይሖዋን ስትጠባበቁ ማድረግ ያለባችሁ ነገር

ጉዳዩን አሳቢ ለሆነው አምላክሽ ትተሽ በትዕግሥት በምትጠባበቂበት ጊዜ ምን ማድረግ ትችያለሽ? አንዱ ነገር ያላገባሽው ለምን እንደሆነ ማሰብ ነው። ያላገባሽበት ዋነኛ ምክንያት “በጌታ ብቻ” ስለ ማግባት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተሰጠውን መመሪያ ለመጠበቅ ብለሽ ከሆነ ይህን መለኮታዊ ትእዛዝ በማክበርሽ ልትመሰገኚ ይገባል። ይሖዋ፣ ቃሉን ለመታዘዝ ባደረግሽው ቁርጥ ውሳኔ እንደሚደሰት እርግጠኛ ሁኚ። (1 ሳሙ. 15:22፤ ምሳሌ 27:11) ለአምላክ ‘ልብሽን በማፍሰስ’ መጸለይሽን ቀጥዪ። (መዝ. 62:8) ይሖዋን አዘውትረሽ ከልብ ስትማጸኚው ከእሱ ጋር ያለሽ ዝምድና ይጠናከራል። ሌሎች የሚያደርጉብሽን ተጽዕኖም ሆነ ከራስሽ ጋር የምታደርጊውን ትግል ተቋቁመሽ ስትጸኚ ከአምላክ ጋር ያለሽ ዝምድና በየዕለቱ እየተጠናከረ ይሄዳል። ልዑሉ አምላክ የሁሉም ታማኝ አገልጋዮቹ ሁኔታ እንደሚያሳስበውና አንቺም በእሱ ፊት ውድ እንደሆንሽ አትጠራጠሪ። ለሚያስፈልጉሽና ለምትፈልጊያቸው ነገሮች ትኩረት ይሰጣል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ለማንም ሰው ቢሆን የትዳር ጓደኛ ለመስጠት ቃል አልገባም። ሆኖም በእርግጥ የትዳር ጓደኛ የሚያስፈልግሽ ከሆነ አምላክ ተገቢ የሆነ ፍላጎትሽን ማርካት የሚቻልበትን ከሁሉ የተሻለ መንገድ ያውቃል።—መዝ. 145:16፤ ማቴ. 6:32

አንቺም “ፈጥነህ መልስልኝ፤ መንፈሴ ደከመች፤ . . . ፊትህን ከእኔ አትሰውር” በማለት ወደ ይሖዋ እንደጸለየው እንደ መዝሙራዊው ዳዊት የሚሰማሽ ጊዜ ሊኖር ይችላል። (መዝ. 143:5-7, 10) እንዲህ ባሉት ጊዜያት የሰማዩ አባትሽ ለአንቺ ያለው ፈቃድ ምን እንደሆነ እንዲያሳይሽ ጊዜ ስጪው። የእሱን ቃል ለማንበብና ባነበብሽው ነገር ላይ ለማሰላሰል ጊዜ በመመደብ ይህን ማድረግ ትችያለሽ። ይህን ስታደርጊ ትእዛዛቱን ይበልጥ መረዳትና ይሖዋ ባለፉት ዘመናት ለሕዝቡ ሲል የወሰዳቸውን እርምጃዎች ማስተዋል ትችያለሽ። አምላክን ስትሰሚ እሱን መታዘዝ የጥበብ አካሄድ መሆኑን ይበልጥ እርግጠኛ ትሆኛለሽ።

ያላገቡ ክርስቲያኖች ለጉባኤው ውድ ናቸው፤ ብዙውን ጊዜ ቤተሰቦችንና ልጆችን ይረዳሉ

ሳታገቢ የምታሳልፊያቸው ዓመታት አስደሳችና ፍሬያማ እንዲሆኑ ሌላስ ምን ማድረግ ትችያለሽ? ይህን ጊዜ እንደ መንፈሳዊ ማስተዋል፣ ለጋስነት፣ ታታሪነት፣ ተወዳጅ መሆን፣ ለአምላክ ማደርና መልካም ስም ያሉትን አስደሳች ለሆነ የቤተሰብ ሕይወት በጣም አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለማዳበር ልትጠቀሚበት ትችያለሽ። (ዘፍ. 24:16-21፤ ሩት 1:16, 17፤ 2:6, 7, 11፤ ምሳሌ 31:10-27) በስብከቱ ሥራና በሌሎችም ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ ከሁሉ አስቀድመሽ የአምላክን መንግሥት ፈልጊ፤ እንዲህ ማድረግሽ ጥበቃ ይሆንልሻል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ቢል ማግባት ቢፈልግም ትዳር ሳይመሠርት ስላሳለፋቸው ዓመታት ሲናገር “ጊዜው ሳላስበው ነው ያለፈው! በዚህ ጊዜ አቅኚ ሆኜ ይሖዋን አገልግያለሁ” ብሏል።

አዎን፣ “በጌታ ብቻ” ማግባት በዘመናችንም ይቻላል። ይህን መመሪያ መታዘዝ ይሖዋን እንድታስከብሪና ዘላቂ እርካታ እንድታገኚ ሊረዳሽ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ በትእዛዙም እጅግ ደስ የሚሰኝ የተባረከ ነው። ሀብትና ብልጽግና በቤቱ ይሞላል፤ ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል” ይላል። (መዝ. 112:1, 3) እንግዲያው “በጌታ ብቻ” እንድናገባ የተሰጠውን መለኮታዊ ትእዛዝ ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ አድርጊ።

^ አን.7 በዚህ ርዕስ ውስጥ ጉዳዩን ያቀረብነው ከእህቶች አንጻር ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ለወንድሞችም ይሠራሉ።

^ አን.13 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።