በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሽማግሌዎች ሌሎች ብቃቱን እንዲያሟሉ ማሠልጠን የሚችሉት እንዴት ነው?

ሽማግሌዎች ሌሎች ብቃቱን እንዲያሟሉ ማሠልጠን የሚችሉት እንዴት ነው?

ከእኔ የሰማኸውን . . . ነገር፣ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ።”—2 ጢሞ. 2:2

1. (ሀ) የአምላክ አገልጋዮች ሥልጠና ስለ መስጠት ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ምን ተገንዝበው ነበር? በዛሬው ጊዜስ? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

የአምላክ አገልጋዮች ሌሎችን ማሠልጠን ለስኬት እንደሚያበቃ ከጥንት ጀምሮ ተገንዝበዋል። ለምሳሌ አብራም ሎጥን ለማዳን ‘የሠለጠኑ አገልጋዮቹን ሰብስቦ’ ይዞ ሄዶ ነበር፤ ይህም ለስኬት አብቅቶታል። (ዘፍ. 14:14-16) በንጉሥ ዳዊት ዘመን በአምላክ ቤት የነበሩት መዘምራን “ለይሖዋ በሚቀርበው መዝሙር የሠለጠኑ” ነበሩ፤ ይህም ለአምላክ ውዳሴ አምጥቷል። (1 ዜና 25:7) ዛሬ ደግሞ ከሰይጣንና ከተከታዮቹ ጋር መንፈሳዊ ውጊያ እያካሄድን ነው። (ኤፌ. 6:11-13) በተጨማሪም ለይሖዋ ውዳሴ ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው። (ዕብ. 13:15, 16) በመሆኑም እንደ ጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች ስኬታማ መሆን ከፈለግን ሥልጠና ማግኘት ይኖርብናል። ይሖዋ በጉባኤ ውስጥ ሌሎችን የማሠልጠን ኃላፊነት ለሽማግሌዎች በአደራ ሰጥቷል። (2 ጢሞ. 2:2) ታዲያ ተሞክሮ ያላቸው ሽማግሌዎች፣ ሌሎች ወንድሞች መንጋውን የመንከባከብ ብቃት እንዲኖራቸው ለማሠልጠን የትኞቹን ዘዴዎች እየተጠቀሙ ነው?

ተማሪውን በመንፈሳዊ አጠናክሩት

2. አንድ ሽማግሌ ለተማሪው ሥልጠና ከመስጠቱ በፊት ምን ማድረግ ያስፈልገዋል? ለምንስ?

2 ሽማግሌዎች ከገበሬ ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። አንድ ገበሬ አፈሩ ይበልጥ ምርት እንዲሰጥ ከፈለገ ዘሩን ከመዝራቱ በፊት አፈሩ ውስጥ አልሚ ንጥረ ነገሮችን መጨመር ያስፈልገው ይሆናል። በተመሳሳይም ብዙ ተሞክሮ ለሌለው አንድ ተማሪ ሥልጠና ለመስጠት ከመነሳትህ በፊት የተማሪው ልብ ለሥልጠናው ዝግጁ እንዲሆን የሚረዱ ገንቢ የሆኑ አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦችን ማካፈል አስፈላጊ እንደሆነ ትገነዘብ ይሆናል።—1 ጢሞ. 4:6

3. (ሀ) ከተማሪው ጋር ውይይት ስታደርጉ በማርቆስ 12:29, 30 ላይ የሚገኘው ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ሊረዳችሁ የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) አንድ ሽማግሌ የሚያቀርበው ጸሎት በተማሪው ላይ ምን ውጤት ይኖረዋል?

3 የመንግሥቱ እውነት በተማሪው አስተሳሰብና ድርጊት ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳሳደረ ለማወቅ እንዲህ ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ፦ ‘ራስህን ለይሖዋ መወሰንህ ሕይወትህን በምትመራበት መንገድ ላይ ምን ለውጥ አስከትሏል?’ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ማንሳት ቅዱስ አገልግሎታችንን በሙሉ ነፍስ ማቅረብ ስለሚቻልበት መንገድ ትርጉም ያለው ውይይት ለመጀመር በር ይከፍታል። (ማርቆስ 12:29, 30ን አንብብ።) ከውይይታችሁ በኋላ ይሖዋ ለተማሪው መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጠው ልትጸልይ ትችላለህ፤ ይህም ሥልጠናው ግቡን እንዲመታ ይረዳል። ተማሪው ስለ እሱ ከልብ የመነጨ ጸሎት ስታቀርብ መስማቱ እንደሚያበረታታው ጥርጥር የለውም!

4. (ሀ) ተማሪው መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ የሚያነሳሱት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ናቸው? (ለ) ሽማግሌዎች ሌሎችን ሲያሠለጥኑ ግባቸው ምን መሆን አለበት?

4 ተማሪው ለማገልገል ፈቃደኛ፣ እምነት የሚጣልበትና ትሑት መሆኑ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚያስገነዝቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን በሥልጠናው የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ መጥቀስ ትችላለህ። (1 ነገ. 19:19-21፤ ነህ. 7:2፤ 13:13፤ ሥራ 18:24-26) አልሚ ንጥረ ነገሮች ለአፈር ወሳኝ እንደሆኑ ሁሉ እንዲህ ያሉ ባሕርያትም ተማሪውን ይጠቅሙታል። መንፈሳዊ እድገቱን ያፋጥኑታል። በፈረንሳይ የሚገኝ ዣን ክሎድ የተባለ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ሌሎችን በማሠለጥንበት ወቅት ዋነኛው ግቤ ተማሪው መንፈሳዊ ሰው እንዲሆን መርዳት ነው። ተማሪው ‘ዓይኖቹ’ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ‘አስደናቂ ነገሮች’ ማየት እንዲችሉ አንዳንድ ጥቅሶችን ለማንበብ አጋጣሚዎችን እፈልጋለሁ።” (መዝ. 119:18) ተማሪውን በመንፈሳዊ ለማጠናከር ሌላስ ምን ማድረግ ይቻላል?

ግብ እንዲያወጡ እርዷቸው፤ ምክንያቱን አስረዷቸው

5. (ሀ) ከተማሪው ጋር ስለ መንፈሳዊ ግብ መነጋገር ምን ያህል አስፈላጊ ነው? (ለ) ሽማግሌዎች ወንዶችን ከልጅነታቸው ጀምሮ ማሠልጠን ያለባቸው ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

5 ተማሪውን ‘ምን መንፈሳዊ ግቦች አሉህ?’ ብለህ ጠይቀው። በግልጽ የተቀመጡ ግቦች ከሌሉት ምክንያታዊና ሊደርስበት የሚችል ግብ እንዲያወጣ እርዳው። አንተ ራስህ በአንድ ወቅት የነበረህን አንድ መንፈሳዊ ግብ ንገረው፤ እዚህ ግብህ ላይ ስትደርስ የተሰማህን ደስታ ሞቅ ባለ ስሜት ግለጽለት። ይህ ቀላል ዘዴ ቢሆንም የሚያስገኘው ውጤት ግን የዋዛ አይደለም። ቪክቶር የተባለ በአፍሪካ የሚኖር አቅኚና ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ልጅ በነበርኩበት ጊዜ አንድ ሽማግሌ ስለ ግቦቼ አንዳንድ ጥያቄዎች ጠየቀኝ። ይህም ስለ አገልግሎቴ በቁም ነገር እንዳስብ አደረገኝ።” ተሞክሮ ያላቸው ሽማግሌዎች ለወንድሞች ከልጅነታቸው ማለትም ከአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ አንስቶ በጉባኤ ውስጥ ለዕድሜያቸው የሚመጥን ኃላፊነት በመስጠት ማሠልጠን ጥቅም እንዳለው ይናገራሉ። ልጆች ገና በለጋነታቸው እንዲህ ዓይነት ሥልጠና ማግኘታቸው ትኩረታቸውን የሚሰርቁ ነገሮች በሚዥጎደጎዱባቸው ማለትም በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይም ትኩረታቸውን በመንፈሳዊ ግቦች ላይ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል።መዝሙር 71:5, 17ን አንብብ። *

ሥራው ለምን መሠራት እንዳለበት ተናገር፤ እንዲሁም ተማሪው ኃላፊነቱን ለመወጣት ጥረት ሲያደርግ አመስግነው (ከአንቀጽ 5-8 ተመልከት)

6. ኢየሱስ የሰጠው ሥልጠና ውጤታማ እንዲሆን ካደረጉት ዘዴዎች አንዱ ምንድን ነው?

6 የተማሪውን የማገልገል ፍላጎት ማነሳሳት የምትችልበት ሌላው ዘዴ ደግሞ ምን ማድረግ እንዳለበት ብቻ ሳይሆን ለምን እንደሚያደርግ መንገር ነው። አንድን ነገር የሚያደርግበትን ምክንያት የምትነግረው ከሆነ ታላቅ አስተማሪ የሆነውን የኢየሱስን ምሳሌ ትከተላለህ። ለምሳሌ ኢየሱስ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ለሐዋርያቱ ተልእኮ ከመስጠቱ በፊት ይህን ትእዛዝ መፈጸም ያለባቸው ለምን እንደሆነ ነግሯቸዋል። “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል። ስለዚህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ” ብሏቸዋል። (ማቴ. 28:18, 19) አንተስ ኢየሱስ ሌሎችን ለማሠልጠን የተጠቀመበትን ይህን ዘዴ መከተል የምትችለው እንዴት ነው?

7, 8. (ሀ) ሽማግሌዎች የኢየሱስን የሥልጠና ዘዴ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ተማሪውን ማመስገን ምን ያህል አስፈላጊ ነው? (ሐ) ሽማግሌዎች ሌሎችን ለማሠልጠን የትኞቹ ሐሳቦች ሊረዷቸው ይችላሉ? (“ ሌሎችን ማሠልጠን የሚቻልበት መንገድ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

7 ተማሪውን አንድ ነገር እንዲያደርግ ስትጠይቀው ይህን የሚያደርግበትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት አብረህ ግለጽለት። በዚህ መንገድ ነገሮችን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር እንዲያስብ ታሠለጥነዋለህ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንድም የመንግሥት አዳራሹን መግቢያ ለእይታ ማራኪ እንዲያደርግና እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮችን ከአካባቢው እንዲያስወግድ ጠየቅከው እንበል። በዚህ ጊዜ ቲቶ 2:10ን በመጥቀስ በመንግሥት አዳራሹ የተሰጠውን ይህን ኃላፊነት መወጣቱ “አዳኛችን የሆነው አምላክ ትምህርት በሁሉም መንገድ ውበት እንዲጎናጸፍ” የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ ግለጽለት። በተጨማሪም ተማሪው የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣቱ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን አረጋውያን የሚጠቅመው እንዴት እንደሆነ ንገረው። ከተማሪው ጋር እንዲህ ያለ ውይይት ማድረግህ ሕግ በመፈጸም ላይ ሳይሆን ለሰዎች በማሰብ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ያሠለጥነዋል። እሱ የሚያከናውነው አገልግሎት በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችንና እህቶችን ምን ያህል እየጠቀማቸው እንደሆነ ሲመለከት ይደሰታል።

8 በተጨማሪም ተማሪው የሰጠኸውን ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ሲጥር ማመስገን እንዳለብህ አትርሳ። ይህን ማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? አንድ አትክልት ውኃ ማግኘቱ እንዲለመልም እንደሚያደርገው ሁሉ ተማሪውም ልባዊ ምስጋና ማግኘቱ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ ይረዳዋል።—ከማቴዎስ 3:17 ጋር አወዳድር።

ሌላው ፈታኝ ነገር

9. (ሀ) በበለጸጉ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ አንዳንድ ሽማግሌዎች ሌሎችን ከማሠልጠን ጋር በተያያዘ ምን ፈታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል? (ለ) አንዳንድ ወጣቶች በሕይወታቸው ውስጥ ለእውነት ቅድሚያ መስጠት የሚለው ጉዳይ የማይታያቸው ለምንድን ነው?

9 በበለጸጉ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሽማግሌዎች በ20ዎቹና በ30ዎቹ ዕድሜ የሚገኙ የተጠመቁ ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት እንዲቀበሉ ለማነሳሳት ጥረት ሲያደርጉ የሚያጋጥማቸው ሌላም ፈታኝ ነገር አለ። በምዕራባውያን አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ወጣት ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ከመቀበል ወደኋላ የሚሉት ለምን እንደሆነ እንዲህ ባሉ 20 አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ተሞክሮ ያካበቱ ሽማግሌዎችን ጠይቀን ነበር። በብዛት የሰጡት መልስ ‘አንዳንድ ወጣቶች በልጅነታቸው መንፈሳዊ ግብ እንዲያወጡ ማበረታቻ ስላልተሰጣቸው ነው’ የሚል ነው። እንዲያውም እንዲህ ያለ ግብ የነበራቸው አንዳንድ ወጣቶች ዓለማዊ ግብ እንዲያወጡ በወላጆቻቸው ተጽዕኖ ተደርጎባቸዋል! እንዲህ ያሉ ወጣቶች በሕይወታቸው ውስጥ ለእውነት ቅድሚያ መስጠት የሚለው ጉዳይ ፈጽሞ አይታያቸውም።—ማቴ. 10:24

10, 11. (ሀ) አንድ ሽማግሌ በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ወስዶ የማገልገል ፍላጎት የሌለውን ወንድም ቀስ በቀስ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል መርዳት የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) አንድ ሽማግሌ ከተማሪው ጋር በየትኞቹ ጥቅሶች ላይ ሊወያይ ይችላል? እንዲህ ማድረጉ ምን ጥቅም አለው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

10 አንድ ወንድም በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ወስዶ የማገልገል ፍላጎት ከሌለው፣ አስተሳሰቡን ለማስተካከል ብዙ ጥረትና ትዕግሥት ይጠይቃል፤ ያም ቢሆን የማይቻል ነገር አይደለም። አንድ ገበሬ ተጣምሞ ያደገን አንድ ተክል ቀስ በቀስ ግንዱ ቀጥ ያለ እንዲሆን ማድረግ እንደሚችል ሁሉ አንተም አንዳንድ ወንድሞች ኃላፊነት ስለመቀበል ያላቸውን አመለካከት ቀስ በቀስ እንዲያስተካክሉ መርዳት ትችላለህ። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

11 ከተማሪው ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ጊዜ መድብ። በጉባኤ ውስጥ ተፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘብ አድርግ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ በአንዳንድ ጥቅሶች ላይ በመወያየት ለይሖዋ የገባውን ቃል እንዲያስታውስ እርዳው። (መክ. 5:4፤ ኢሳ. 6:8፤ ማቴ. 6:24, 33፤ ሉቃስ 9:57-62፤ 1 ቆሮ. 15:58፤ 2 ቆሮ. 5:15፤ 13:5) ‘ራስህን ለይሖዋ ስትወስን ምን ቃል ገብተህ ነበር?’ ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ። ‘በተጠመቅክ ጊዜ ይሖዋ ምን ተሰምቶት የነበረ ይመስልሃል?’ ብለህ በመጠየቅ የቀድሞ ፍቅሩ እንዲቀሰቀስ አድርግ። (ምሳሌ 27:11) ከዚያም ‘ሰይጣንስ ምን ተሰምቶት ነበር?’ የሚል ጥያቄ ማንሳት ትችላለህ። (1 ጴጥ. 5:8) በደንብ የታሰበበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማንበብህ በተማሪው ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በፍጹም አቅልለህ አትመልከት።ዕብራውያን 4:12ን አንብብ። *

ተማሪዎች፣ ታማኝ መሆናችሁን አስመሥክሩ

12, 13. (ሀ) ኤልሳዕ ተማሪ በነበረበት ወቅት ምን ዓይነት ባሕርይ አሳይቷል? (ለ) ኤልሳዕ ታማኝ በመሆኑ ይሖዋ የባረከው እንዴት ነው?

12 እናንተ ወጣት ወንድሞች፣ ጉባኤው የእናንተን እርዳታ ይፈልጋል። ጉባኤውን በመርዳት ረገድ ስኬታማ ለመሆን ምን ዓይነት ባሕርይ ማዳበር ያስፈልጋችኋል? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በጥንት ዘመን የኖረን የአንድ ተማሪ ሁኔታ እንመልከት።

13 ወደ 3,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ነቢዩ ኤልያስ፣ ኤልሳዕ የተባለን አንድ ወጣት አገልጋዩ እንዲሆን ጠይቆት ነበር። ኤልሳዕም ግብዣውን ወዲያውኑ በመቀበል ዝቅ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን በማከናወን በዕድሜ የገፋውን ነቢይ በታማኝነት ማገልገል ጀመረ። (2 ነገ. 3:11) ኤልሳዕ ለስድስት ዓመት ያህል ከሠለጠነ በኋላ ኤልያስ በእስራኤል ውስጥ የሚያከናውነው አገልግሎት ሊያበቃ እንደሆነ ተገነዘበ። በዚህ ወቅት ኤልያስ በደንብ የሠለጠነው አገልጋዩ እሱን መከተሉን እንዲያቆም ጠየቀው፤ ኤልሳዕ ግን ከአንዴም ሦስቴ “ከአንተ አልለይም” አለው። ኤልሳዕ ከአስተማሪው ጋር የሚችለውን ያህል ረጅም ጊዜ ለማሳለፍ ቆርጦ ነበር። ኤልሳዕ ታማኝና የእምነት ሰው በመሆኑ ኤልያስ ተአምራዊ በሆነ ሁኔታ ሲወሰድ እንዲመለከት በማድረግ ይሖዋ ባርኮታል።—2 ነገ. 2:1-12

14. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ተማሪዎች የኤልሳዕን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) አንድ ተማሪ ታማኝ መሆኑ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

14 ተማሪ ከሆንክ የኤልሳዕን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው? ዝቅ ተደርገው የሚቆጠሩ ሥራዎችን ጨምሮ ማንኛውም ኃላፊነት ሲሰጥህ ሥራውን ለማከናወን ፈጣን እርምጃ ውሰድ። አስተማሪህን እንደ ጓደኛ ተመልከተው፤ እንዲሁም አንተን ለመርዳት የሚያደርገውን ጥረት እንደምታደንቅ ንገረው። ለሥልጠናው ጥሩ ምላሽ የምትሰጥ ከሆነ ለአስተማሪህ “ከአንተ አልለይም” እያልከው ያለ ያህል ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ የተሰጠህን ማንኛውንም ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ታማኝ መሆንህን አሳይ። ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋ በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነት እንድትቀበል የሚፈልግ መሆኑን ሽማግሌዎቹ እርግጠኞች የሚሆኑት ታማኝና እምነት የሚጣልበት ሰው መሆንህን ስታስመሠክር ነው።—መዝ. 101:6፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:2ን አንብብ።

ተገቢውን አክብሮት አሳዩ

15, 16. (ሀ) ኤልሳዕ ለአስተማሪው አክብሮት እንዳለው ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ኤልሳዕ ሌሎቹ ነቢያት በእሱ እንዲተማመኑ ምን አድርጓል?

15 የኤልያስ ተተኪ ስለሆነው ስለ ኤልሳዕ የሚናገረው ዘገባ ወንድሞች ተሞክሮ ላካበቱ ሽማግሌዎች ተገቢውን አክብሮት ማሳየት የሚችሉት እንዴት እንደሆነም ይጠቁማል። ኤልያስና ኤልሳዕ በኢያሪኮ የሚገኙ ነቢያትን ከጎበኙ በኋላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄዱ። በዚያም “ኤልያስ የነቢይ ልብሱን አውልቆ በመጠቅለል ውኃውን መታው፤ ውኃውም ግራና ቀኝ ተከፈለ።” የደረቀውን ወንዝ ከተሻገሩ በኋላ ‘እየተጨዋወቱ መሄዳቸውን’ ቀጠሉ። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ኤልሳዕ ሁሉንም ነገር ተምሮ እንደጨረሰ አልተሰማውም። ኤልያስ ከእሱ እስከተለየበት ጊዜ ድረስ አስተማሪው የሚናገረውን ሁሉ በጥሞና ይከታተል ነበር። ከዚያም ኤልያስ አውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ወደ ሰማይ ወጣ። በኋላም ኤልሳዕ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ተመልሶ ውኃውን በኤልያስ ልብስ በመምታት “የኤልያስ አምላክ ይሖዋ የት አለ?” አለ። ውኃውም በድጋሚ ለሁለት ተከፈለ።—2 ነገ. 2:8-14

16 ኤልሳዕ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈጸመው ተአምር ኤልያስ ለመጨረሻ ጊዜ ከፈጸመው ተአምር ጋር አንድ ዓይነት መሆኑን ልብ አልክ? ይህ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው? ኤልሳዕ አሁን በኃላፊነት ላይ ያለው እሱ ስለሆነ ኤልያስ ይጠቀምበት የነበረውን መንገድ ወዲያውኑ መቀየር እንዳለበት አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ አገልግሎቱን ኤልያስ ያከናውን በነበረበት መንገድ ማከናወኑን ቀጥሏል፤ ይህም ለአስተማሪው አክብሮት እንዳለው የሚያሳይ ሲሆን ሌሎች ነቢያትም በእሱ ላይ እንዲተማመኑ ረድቷቸዋል። (2 ነገ. 2:15) ከጊዜ በኋላ ግን ኤልሳዕ ለ60 ዓመታት በነቢይነት ባገለገለበት ወቅት በይሖዋ እርዳታ ከኤልያስ የበለጠ ብዙ ተአምራት ፈጽሟል። ታዲያ በዛሬው ጊዜ ያሉ ተማሪዎች ከዚህ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

17. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ተማሪዎች የኤልሳዕን ዓይነት ባሕርይ ማንጸባረቅ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ታማኝ የሆኑ ተማሪዎችን በጊዜ ሂደት እንዴት ሊጠቀምባቸው ይችላል?

17 በጉባኤ ውስጥ አንድ ዓይነት ኃላፊነት ስትቀበል ቶሎ ብለህ የራስህን መንገድ ለመከተል አትሞክር፤ በሌላ አባባል ከዚህ በፊት የነበረውን አሠራር ሙሉ በሙሉ መቀየር እንዳለብህ ሊሰማህ አይገባም። አንድ አሠራር መለወጥ ያለበት በአንተ ፍላጎት መሆን የለበትም፤ ከዚህ ይልቅ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የጉባኤው ጥቅምና ከይሖዋ ድርጅት የምናገኘው መመሪያ ነው። ኤልሳዕ የኤልያስን ዘዴ መጠቀሙን በመቀጠል ሌሎቹ ነቢያት እንዲተማመኑበት ማድረግና ለኤልያስ ያለውን አክብሮት ማሳየት እንደቻለ አስታውስ፤ አንተም በተመሳሳይ ሽማግሌዎቹ ሲጠቀሙባቸው የነበሩትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ዘዴዎች ተግባራዊ ማድረግህን በመቀጠል የእምነት ባልንጀሮችህ እንዲተማመኑብህ ማድረግ እንዲሁም ተሞክሮ ላካበቱ ሽማግሌዎች አክብሮት እንዳለህ ማሳየት ትችላለህ። (1 ቆሮንቶስ 4:17ን አንብብ።) ተሞክሮ እያገኘህ ስትሄድ ጉባኤው ወደፊት እየገሰገሰ ከሚሄደው የይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል እንዲራመድ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ግልጽ ነው። እንዲያውም ይሖዋ ለኤልሳዕ እንዳደረገው ሁሉ አንተም ታማኝ እስከሆንክ ድረስ ውሎ አድሮ አስተማሪዎችህ ካከናወኑት የበለጠ ነገር እንድትሠራ ሊጠቀምብህ ይችላል።—ዮሐ. 14:12

18. በዛሬው ጊዜ በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችን ማሠልጠን ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ለምንድን ነው?

18 በዚህና ባለፈው ርዕስ ላይ የወጡት ሐሳቦች ጊዜ መድቦ ሌሎችን በማሠልጠን ረገድ በርካታ ሽማግሌዎችን ለተግባር እንደሚያነሳሱ ተስፋ እናደርጋለን። ብቃት ያላቸው ወንድሞች ደግሞ የሚሰጣቸውን ሥልጠና በጉጉት እንደሚቀበሉና ሥልጠናውን ማስተዋል በተሞላበት መንገድ ተጠቅመው የይሖዋን በጎች እንደሚንከባከቡ ተስፋ እናደርጋለን። ይህም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ጉባኤዎች እንዲጠናከሩና ከፊታችን የሚጠብቁን ወሳኝ ክንውኖች በሚፈጸሙበት ጊዜ ሁላችንም ታማኝ ሆነን እንድንገኝ ይረዳናል።

^ አን.5 አንድ ወጣት መንፈሳዊ ብስለት ካለው፣ ትሑት ከሆነ እንዲሁም ሌሎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን ካሟላ 20 ዓመት ባይሞላውም እንኳ ሽማግሌዎች የጉባኤ አገልጋይ እንዲሆን ዕጩ አድርገው ሊያቀርቡት ይችላሉ።—1 ጢሞ. 3:8-10, 12፤ የሐምሌ 1, 1989 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 29ን ተመልከት።

^ አን.11 በሚያዝያ 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 14 አንቀጽ 8 እስከ ገጽ 16 አንቀጽ 13 እና ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 16 ከአንቀጽ 1-3 ላይ የወጡትን ሐሳቦች በውይይታችሁ ወቅት መጠቀም ትችላለህ።