በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሰይጣን ጋር ተዋግታችሁ ልታሸንፉት ትችላላችሁ!

ከሰይጣን ጋር ተዋግታችሁ ልታሸንፉት ትችላላችሁ!

“በእምነት ጸንታችሁ በመቆም [ሰይጣንን] ተቃወሙት።” —1 ጴጥ. 5:9

1. (ሀ) ከሰይጣን ጋር ለምናደርገው ውጊያ በተለይ በአሁኑ ወቅት ትኩረት መስጠት ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ከሰይጣን ጋር በምናደርገው ውጊያ ማሸነፍ እንችላለን የምንለው ለምንድን ነው?

ሰይጣን በቅቡዓን ቀሪዎችና ‘በሌሎች በጎች’ ላይ ጦርነት አውጇል። (ዮሐ. 10:16) የዲያብሎስ ዓላማ በቀረው ጥቂት ጊዜ ውስጥ ከይሖዋ አገልጋዮች መካከል የቻለውን ያህል ብዙዎችን መዋጥ ነው። (ራእይ 12:9, 12ን አንብብ።) ታዲያ ከሰይጣን ጋር በምናደርገው ውጊያ ማሸነፍ እንችላለን? እንዴታ! መጽሐፍ ቅዱስ “ዲያብሎስን . . . ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል” ይላል።—ያዕ. 4:7

2, 3. (ሀ) ሰዎች፣ ሰይጣን እንደሌለ ማመናቸው የእሱን ዓላማ ከግብ የሚያደርሰው እንዴት ነው? (ለ) ሰይጣን በእውን ያለ አካል ነው ብለህ የምታምነው ለምንድን ነው?

2 ብዙዎች ሰይጣን አለ ብሎ ማመን ቂልነት እንደሆነ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች ሰይጣንና አጋንንቱ በልብ ወለድ መጻሕፍት፣ በአስፈሪ ፊልሞችና በቪዲዮ ጨዋታዎች ውስጥ የሚገኙ ምናብ የፈጠራቸው ገጸ ባሕርያት እንደሆኑ ያስባሉ። የማመዛዘን ችሎታ ያለው ማንኛውም ሰው በክፉ መናፍስት እንደማያምን ይናገራሉ። ታዲያ ሰይጣን፣ እሱና በዓይን የማይታዩት ግብረ አበሮቹ በተረት ዓለም ውስጥ የሚገኙ ባለታሪኮች ብቻ እንደሆኑ ተደርገው መቆጠራቸው ቅር የሚያሰኘው ይመስልሃል? ይህ የሚያስከፋው አይመስልም! እንዲያውም ሰይጣን፣ እሱ መኖሩን የሚጠራጠሩ ሰዎችን አእምሮ ማሳወር ይቀለዋል። (2 ቆሮ. 4:4) ሰይጣን ሰዎችን ለማሳሳት ከሚጠቀምባቸው በርካታ ዘዴዎች አንዱ መንፈሳዊ ፍጥረታት የሉም የሚለውን ሐሳብ ማስፋፋት ነው።

3 የይሖዋ አገልጋዮች በመሆናችን እንዲህ ባለው አመለካከት አልተታለልንም። ሔዋንን በእባቡ ተጠቅሞ ያነጋገራት ሰይጣን ስለሆነ ዲያብሎስ በእውን ያለ አካል መሆኑን እናውቃለን። (ዘፍ. 3:1-5) ሰይጣን ከኢዮብ ጋር በተያያዘ በይሖዋ ላይ ተሳልቋል። (ኢዮብ 1:9-12) ኢየሱስን ሊፈትነው የሞከረውም ሰይጣን ነው። (ማቴ. 4:1-10) እንዲሁም በ1914 የአምላክ መንግሥት ከተወለደ በኋላ ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር ‘መዋጋት’ የጀመረው ሰይጣን ነው። (ራእይ 12:17) ሰይጣን የ144,000ዎቹን ቀሪዎችና የሌሎች በጎችን እምነት ለማጥፋት እየጣረ በመሆኑ ይህ ጦርነት አሁንም ቀጥሏል። በዚህ ጦርነት ለማሸነፍ፣ በእምነት ጸንተን በመቆም ሰይጣንን መቃወም ይኖርብናል። ይህ ርዕስ ይህን ማድረግ የምንችልባቸውን ሦስት መንገዶች ያብራራል።

ከኩራት ራቁ

4. ሰይጣን በኩራት የተወጠረ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

4 ሰይጣን ፈጽሞ ሊያንጸባርቀው የማይችለው ባሕርይ ቢኖር ትሕትና ነው። ለነገሩ ይህ መንፈሳዊ ፍጡር የይሖዋን ሉዓላዊ ገዢነት መገዳደሩና ራሱን አምላክ ለማድረግ መድፈሩ ምን ያህል በኩራትና በትዕቢት እንደተወጠረ የሚያሳይ ነው። በመሆኑም ሰይጣንን መቃወም የምንችልበት አንዱ መንገድ ከኩራት መራቅና ትሕትናን ማዳበር ነው። (1 ጴጥሮስ 5:5ን አንብብ።) ይሁንና ኩራት ምንድን ነው? ይህን ባሕርይ ማንጸባረቅ ሁልጊዜ ስህተት ነው?

5, 6. (ሀ) መኩራት ሁልጊዜ ስህተት ነው? አብራራ። (ለ) አደገኛ የሆነው ምን ዓይነት ኩራት ነው? ይህን የሚያሳዩት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?

5 አንድ መዝገበ ቃላት ኩራት የሚለውን ቃል “ለራስህ ጥሩ አመለካከትና አክብሮት ማዳበር” እንዲሁም “አንተም ሆነ የምትቀርባቸው ሰዎች ጥሩ ነገር በማድረጋችሁ አሊያም በማግኘታችሁ የሚሰማህ የደስታና የእርካታ ስሜት” በማለት ፈትቶታል። እንዲህ ያለው ስሜት በራሱ ስህተት አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች “እየደረሰባችሁ ያለውን ስደትና መከራ ሁሉ ችላችሁ በመኖር ባሳያችሁት ጽናትና እምነት የተነሳ በአምላክ ጉባኤዎች መካከል እኛ ራሳችን ስለ እናንተ በኩራት እንናገራለን” ብሏቸዋል። (2 ተሰ. 1:4) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ሌሎች ባከናወኑት ነገር መደሰት ሌላው ቀርቶ በተወሰነ መጠን በራሳችን መኩራት እንኳ ስህተት አይደለም። በቤተሰባችን፣ በባሕላችን ወይም ባደግንበት አካባቢ ማፈር አይኖርብንም።—ሥራ 21:39

6 በሌላ በኩል ግን ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነትም ሆነ ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ቀስ ቀስ የሚያበላሽ ኩራት አለ። እንዲህ ያለው ኩራት አስፈላጊ የሆነ ምክር ሲሰጠን በትሕትና ከመቀበል ይልቅ ቅር እንድንሰኝ ወይም ምክሩን እንዳንቀበል ሊያደርገን ይችላል። (መዝ. 141:5) ይህ ዓይነቱ ኩራት “ራስን ከሚገባው በላይ ከፍ አድርጎ መመልከት” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል፤ ወይም ደግሞ “ከሌሎች የተሻሉ እንደሆኑ የሚሰማቸው ሰዎች (ብዙውን ጊዜ እንዲህ ለማሰብ የሚያበቃ ምክንያት ባይኖራቸውም) የሚያሳዩት የትዕቢት ዝንባሌ” ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። ይሖዋ ከልክ ያለፈ ኩራትን ይጠላል። (ሕዝ. 33:28፤ አሞጽ 6:8) ሰይጣን ግን እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የእሱን የእብሪት ዝንባሌ የሚያንጸባርቅ በመሆኑ ሰዎች ሲታበዩ ማየት ያስደስተዋል። እንደ ናምሩድ፣ ፈርዖንና አቢሴሎም ያሉት ሰዎች በመታበይ ተገቢ ያልሆነ ኩራት ሲያሳዩ ምንኛ ፈንጥዞ ይሆን! (ዘፍ. 10:8, 9፤ ዘፀ. 5:1, 2፤ 2 ሳሙ. 15:4-6) ቃየንንም ለውድቀት ከዳረጉት ነገሮች አንዱ ኩራት ነው። አምላክ ራሱ ለቃየን ምክር ቢሰጠውም ኩራት እርማቱን እንዳይቀበል አድርጎታል። እልኸኛ በመሆን የይሖዋን ምክር ለመቀበል አሻፈረኝ ማለቱ ለውድቀት ዳርጎታል።—ዘፍ. 4:6-8

7, 8. (ሀ) ዘረኝነት ምንድን ነው? የኩራት መገለጫ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ኩራት የጉባኤን ሰላም ሊያደፈርስ የሚችለው እንዴት እንደሆነ አብራራ።

7 በዛሬው ጊዜ ሰዎች ኩራት የሚያሳዩባቸው አብዛኞቹ መንገዶች ጎጂ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ኩራት ከዘረኝነት ጋር ይያያዛል። አንድ መዝገበ ቃላት ዘረኝነት የሚለውን ቃል ሲፈታው “ሌላ ዘር ላላቸው ሰዎች ጭፍን ጥላቻ ማሳየት” እንደሆነ ገልጿል፤ እንዲሁም ቃሉ “የተለያዩ ዘሮች፣ የተለያየ ባሕርይና ችሎታ እንዳላቸው ብሎም አንዳንድ ዘሮች ከሌሎች የበለጡ ወይም ያነሱ እንደሆኑ ማመንን” እንደሚያመለክትም ተናግሯል። ሰዎች በዘራቸው ምክንያት የሚያድርባቸው ኩራት ዓመፅና ጦርነት አልፎ ተርፎም የጅምላ ጭፍጨፋ አስከትሏል።

8 እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያሉት ነገሮች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አይፈጸሙም። ያም ቢሆን አንዳንድ ጊዜ በኩራት ምክንያት በክርስቲያኖች መካከል የሚነሱ ግጭቶች ከቁጥጥር ውጭ ሊሆኑ ይችላሉ። ያዕቆብ “በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው?” የሚል ኃይለኛ ጥያቄ ያቀረበላቸው አንዳንድ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸው መሆን አለበት። (ያዕ. 4:1) በእርግጥም ሥር የሰደደ የጥላቻና የበላይነት ስሜት በንግግራችንና በተግባራችን ሊንጸባረቅ ይችላል፤ ይህም በሌሎች ላይ ከባድ ጉዳት ያደርሳል። (ምሳሌ 12:18) ኩራት የጉባኤን ሰላም እንደሚያደፈርስ ምንም ጥያቄ የለውም።

9. መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዘረኝነትን እንዲሁም ተገቢ ያልሆነ ኩራት የሚገለጽባቸውን ሌሎች ዝንባሌዎች ለማስወገድ የሚረዳን እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

9 ከሌሎች እንደምትበልጥ የሚሰማህ ከሆነ “ይሖዋ ኩሩ ልብ ያለውን ሁሉ ይጸየፋል” የሚለውን ጥቅስ ማስታወስ ይኖርብሃል። (ምሳሌ 16:5) ከዚህም ሌላ ከእኛ የተለየ ዘር፣ ዜግነት ወይም ባሕል ላላቸው ሰዎች ያለንን አመለካከት መመርመራችን ጠቃሚ ነው። በዘራችን ወይም በአገራችን የመኩራት ዝንባሌ ካለን አምላክ “የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ” የሚለውን እውነታ ዘንግተናል ማለት ነው። (ሥራ 17:26) ከዚህ ጥቅስ አንጻር፣ የሰው ልጆች ሁሉ ቅደመ አያት አዳም በመሆኑ በዓለም ላይ ያለው ዘር አንድ ብቻ ነው። እንግዲያው አንዳንድ ዘሮች ከሌሎች የበለጡ ወይም ያነሱ እንደሆኑ ማሰብ ምንኛ ሞኝነት ነው! እንዲህ ያለው አመለካከት ሰይጣን ክርስቲያናዊ ፍቅራችንንና አንድነታችንን እንዲያናጋ መንገድ ይከፍታል። (ዮሐ. 13:35) ሰይጣንን ተዋግተን ለማሸነፍ ማንኛውንም ተገቢ ያልሆነ ኩራት ማስወገድ ይኖርብናል።—ምሳሌ 16:18

ከፍቅረ ንዋይና ዓለምን ከመውደድ ተጠበቁ

10, 11. (ሀ) ዓለምን መውደድ ቀላል ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ዴማስ ዓለምን እንደሚወድ ያሳየው እንዴት ሊሆን ይችላል?

10 ሰይጣን “የዚህ ዓለም ገዢ” ሲሆን ዓለም በእሱ ቁጥጥር ሥር ነው። (ዮሐ. 12:31፤ 1 ዮሐ. 5:19) በመሆኑም ይህ ዓለም የሚያስፋፋው አብዛኛው ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር ይጋጫል። እርግጥ ነው፣ በዓለም ውስጥ ያለው ነገር ሁሉ መጥፎ ነው ማለት አይደለም። ያም ቢሆን ሰይጣን፣ በእሱ ቁጥጥር ሥር ባለው ዓለም ተጠቅሞ ምኞታችንን በማነሳሳት ኃጢአት እንድንፈጽም አሊያም ደግሞ ዓለምን በመውደድ ለይሖዋ የምናቀርበውን አምልኮ ችላ እንድንል ለማድረግ እንደሚጥር መጠበቅ ይኖርብናል።—1 ዮሐንስ 2:15, 16ን አንብብ።

11 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ዓለምን መውደድ ወጥመድ የሆነባቸው ይመስላል። ለምሳሌ “ዴማስ በአሁኑ ጊዜ ያለውን ሥርዓት ወዶ፣ ትቶኝ . . . ሄዷል” በማለት ጳውሎስ ጽፏል። (2 ጢሞ. 4:10) ዴማስ፣ ጳውሎስን እስከ መተው የደረሰው በዓለም ውስጥ ምን ወዶ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አይናገርም። ዴማስ ከመንፈሳዊ ግቦች በላይ ቁሳዊ ነገሮችን መውደድ ጀምሮ ሊሆን ይችላል። ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ዴማስ ውድ የሆኑ መንፈሳዊ መብቶችን አጥቷል፤ ምን ለማግኘት ሲል? እስቲ አስበው፣ የጳውሎስ ባልደረባ ሆኖ ሲያገለግል ይሖዋ ከሚሰጠው በረከት የላቀ ነገር ዓለም ሊያቀርብለት ይችላል?—ምሳሌ 10:22

12. “ሀብት ያለው የማታለል ኃይል” ሊያጠምደን የሚችለው እንዴት ነው?

12 እኛም ተመሳሳይ ነገር ሊያጋጥመን ይችላል። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር ለማሟላት መፈለጋችን ተገቢ ነው። (1 ጢሞ. 5:8) ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን ውብ መኖሪያ ማዘጋጀቱ ተመችቶን እንድንኖር እንደሚፈልግ በግልጽ ያሳያል። (ዘፍ. 2:9) ይሁንና ሰይጣን “ሀብት [ባለው] የማታለል ኃይል” ተጠቅሞ ተገቢ ያልሆነ ፍላጎት እንዲያድርብን ሊያደርግ ይችላል። (ማቴ. 13:22) ብዙዎች ገንዘብ ደስታ እንደሚያስገኝላቸው ወይም ለስኬት ቁልፉ ቁሳዊ ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። እንዲህ ብሎ ማሰብ በሰይጣን መታለል ነው፤ እንዲሁም ከምንም በላይ ትልቅ ቦታ የምንሰጠውን ነገር ይኸውም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና እንድናጣ ሊያደርገን ይችላል። ኢየሱስ ተከታዮቹን “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም” በማለት አስጠንቅቋቸዋል። (ማቴ. 6:24) ለሀብት ብቻ ባሪያ ከሆንን ይሖዋን ማገልገላችንን አቁመናል ማለት ነው፤ ሰይጣን የሚፈልገው ደግሞ ይህንኑ ነው! ገንዘብም ሆነ ገንዘብ ሊገዛቸው የሚችሉ ነገሮች ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ችላ እንድንል እንዲያደርጉን ፈጽሞ አንፍቀድ። ሰይጣንን ተዋግተን ማሸነፍ እንድንችል ለቁሳዊ ነገሮች ምንጊዜም ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል።1 ጢሞቴዎስ 6:6-10ን አንብብ።

ከፆታ ብልግና ሽሹ

13. ይህ ዓለም ጋብቻንና የፆታ ግንኙነትን በተመለከተ የተዛባ አመለካከት የሚያስፋፋው እንዴት ነው?

13 በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያለው ሌላው ወጥመድ ደግሞ የፆታ ብልግና ነው። በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆንን እንዲያውም ትዳርን ራሱ መፈናፈኛ የሚያሳጣና ጊዜ ያለፈበት ነገር እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት ታዋቂ ተዋናይ “በአንድ ሰው ብቻ ተወስኖ መኖር ለሁለቱም ፆታዎች የማይቻል ነገር ነው። ለትዳር ጓደኛው ታማኝ የሆነ ወይም መሆን የሚፈልግ ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም” ብላለች። ሌላ ተዋናይ ደግሞ “በሕይወታችን ሙሉ ከአንድ ሰው ጋር ብቻ መኖር ተፈጥሯችን አይመስለኝም” ብሏል። ታዋቂ የሆኑ ሰዎች የአምላክ ስጦታ ስለሆነው ትዳር እንዲህ ያሉ መጥፎ ነገሮችን ሲናገሩ ሰይጣን እንደሚደሰት የታወቀ ነው። ዲያብሎስ የጋብቻን ዝግጅት እንደማያበረታታ ወይም ትዳር ሲሰምር ለማየት እንደማይጓጓ ጥያቄ የለውም። እንግዲያው ከሰይጣን ጋር ተዋግተን ለማሸነፍ፣ የይሖዋ ዝግጅት የሆነውን ጋብቻን ከፍ አድርገን ልንመለከተው ይገባል።

14, 15. ከፆታ ብልግና መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?

14 ያገባንም እንሁን ያላገባን ከማንኛውም ዓይነት የፆታ ብልግና ለመራቅ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። ይሁንና ትግሉ ቀላል ነው? በፍጹም! ለምሳሌ ወጣት ከሆንክ አብረውህ የሚማሩት ልጆች ከተለያዩ ሰዎች ጋር የፆታ ግንኙነት ስለመፈጸም ወይም የብልግና መልእክቶችን በሞባይል ስልክ ስለመላላክ በኩራት ሲናገሩ ትሰማ ይሆናል፤ በአንዳንድ አገሮች እንዲህ ያሉ መልእክቶችን መላላክ ልጆች ያሉበት ፖርኖግራፊ ከማሰራጨት ተለይቶ አይታይም። መጽሐፍ ቅዱስ “ዝሙት የሚፈጽም ሁሉ . . . በራሱ አካል ላይ ኃጢአት እየሠራ ነው” ይላል። (1 ቆሮ. 6:18) የአባለዘር በሽታዎች መስፋፋት ሥቃይና ሞት እያስከተለ ነው። ከዚህም ሌላ ሳያገቡ የፆታ ግንኙነት የፈጸሙ አብዛኞቹ ወጣቶች ይህን በማድረጋቸው እንደተጸጸቱ ይገልጻሉ። የፆታ ብልግና የሚያስከትለው መዘዝ የመዝናኛው ዓለም ከሚገልጸው ነገር ፈጽሞ የተለየ ነው፤ ዓለም የአምላክን ሕግ መጣስ ምንም ጉዳት እንደሌለው ሊያሳምነን ይሞክራል። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ሰዎች “ኃጢአት ባለው የማታለል ኃይል” እንዲወድቁ ያደርጋል።—ዕብ. 3:13

15 የፆታ ብልግና ለመፈጸም የምትፈተን ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ድክመት እንዳለብህ አምነህ ተቀበል። (ሮም 7:22, 23) አምላክ ጥንካሬ እንዲሰጥህ ጸልይ። (ፊልጵ. 4:6, 7, 13) የሥነ ምግባር ብልግና ወደመፈጸም ሊመሩህ ከሚችሉ ሁኔታዎች ራቅ። (ምሳሌ 22:3) እንዲሁም ፈተና ሲያጋጥምህ ከፆታ ብልግና በመሸሽ ወዲያውኑ እርምጃ ውሰድ።—ዘፍ. 39:12

16. ኢየሱስ፣ ሰይጣን ሲፈትነው ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው? እኛስ ከእሱ ምሳሌ ምን እንማራለን?

16 ኢየሱስ ፈተናን በመቃወም ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። በሰይጣን ማማለያዎች አልተታለለም፤ እንዲሁም በቀረበለት ግብዣ ላይ ማሰብ ብሎም ጥቅምና ጉዳቱን ማመዛዘን አላስፈለገውም። ከዚህ ይልቅ “ተብሎ ተጽፏል” በማለት ወዲያውኑ ምላሽ ሰጠ። (ማቴዎስ 4:4-10ን አንብብ።) ኢየሱስ የአምላክን ቃል ያውቅ ስለነበር ፈተና ሲያጋጥመው ፈጣን እርምጃ መውሰድና ከቅዱሳን መጻሕፍት ጠቅሶ መልስ መስጠት ችሏል። እኛም ከሰይጣን ጋር ተዋግተን ማሸነፍ እንድንችል የፆታ ብልግና ፈተና እንዲሆንብን መፍቀድ የለብንም።—1 ቆሮ. 6:9, 10

በመጽናት ውጊያውን አሸንፉ

17, 18. (ሀ) ሰይጣን የትኞቹን ሌሎች መሣሪያዎች ይጠቀማል? ይህ ሊያስገርመን የማይገባውስ ለምንድን ነው? (ለ) ሰይጣን ወደፊት ምን ይጠብቀዋል? ይህስ እንድትጸና የሚያበረታታህ እንዴት ነው?

17 ሰይጣን የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች ኩራት፣ ፍቅረ ንዋይና የፆታ ብልግና ብቻ አይደሉም። ሌሎች ብዙ መሣሪያዎችም አሉት። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከቤተሰባቸው አባላት ተቃውሞ ወይም አብረዋቸው ከሚማሩት ልጆች ፌዝ ያጋጥማቸዋል፤ አሊያም በአንዳንድ ቦታዎች የመንግሥት ባለሥልጣናት የስብከቱን ሥራቸውን ያግዱባቸዋል። ኢየሱስ ተከታዮቹን “በስሜ የተነሳም ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል፤ እስከ መጨረሻው የጸና ግን ይድናል” በማለት ስላስጠነቀቃቸው እንዲህ ያሉት ፈተናዎች ቢያጋጥሙን አያስገርመንም።—ማቴ. 10:22

ሰይጣን ጨርሶ ከሕልውና ውጭ ይሆናል (አንቀጽ 18ን ተመልከት)

18 ከሰይጣን ጋር ተዋግተን ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ከጸናችሁ ሕይወታችሁን ታተርፋላችሁ” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 21:19) ሰዎች የሚያደርጉት ማንኛውም ነገር ዘላቂ ጉዳት አያስከትልብንም። እኛ ራሳችን ካልሆንን በቀር ማንም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያበላሽብን አይችልም። (ሮም 8:38, 39) የይሖዋ አገልጋዮች ቢሞቱ እንኳ ሰይጣን አሸነፈ ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ከሞት እንደሚያስነሳቸው ጥርጥር የለውም! (ዮሐ. 5:28, 29) በሌላ በኩል ግን የሰይጣን የወደፊት ተስፋ የጨለመ ነው። ፈሪሃ አምላክ የሌለው የሰይጣን ሥርዓት ከጠፋ በኋላ ሰይጣን ለ1,000 ዓመት ወደ ጥልቁ ይወረወራል። (ራእይ 20:1-3) የኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ሲጠናቀቅ ሰይጣን ለአጭር ጊዜ “ከእስራቱ ይፈታል”፤ በዚህ ጊዜ ፍጹም የሆኑ የሰው ልጆችን ለማሳት የመጨረሻ ሙከራ ያደርጋል። ከዚያ በኋላ ዲያብሎስ ይጠፋል። (ራእይ 20:7-10) ሰይጣን ወደፊት የመኖር ተስፋ የለውም፤ አንተ ግን ተስፋ አለህ! በእምነት ጸንተህ በመቆም ሰይጣንን ተቃወመው። ተዋግተህ ልታሸንፈው ትችላለህ!