በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቶስ—የአምላክ ኃይል

ክርስቶስ—የአምላክ ኃይል

‘ክርስቶስ የአምላክ ኃይል ነው።’—1 ቆሮ. 1:24

1. ጳውሎስ ‘ክርስቶስ የአምላክ ኃይል ነው’ ብሎ የተናገረው ለምንድን ነው?

ይሖዋ ኃይሉን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በአስደናቂ መንገዶች አሳይቷል። አራቱ ወንጌሎች ክርስቶስ ስላከናወናቸው አንዳንድ ተአምራት የያዟቸው ዝርዝር ዘገባዎች እምነት የሚያጠናክሩ ናቸው። ኢየሱስ ተመዝግበው ከምናገኛቸው በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ተአምራትንም እንደፈጸመ ግልጽ ነው። (ማቴ. 9:35፤ ሉቃስ 9:11) በእርግጥም የአምላክ ኃይል በኢየሱስ በኩል ተገልጧል። ሐዋርያው ጳውሎስም ‘ክርስቶስ የአምላክ ኃይል ነው’ ብሎ ለመናገር በቂ ምክንያት ነበረው። (1 ቆሮ. 1:24) ይሁንና ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት ለእኛ ምን ትርጉም አላቸው?

2. ከኢየሱስ ተአምራት ምን ልንማር እንችላለን?

2 ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ተአምራት እና “ድንቅ ነገሮች” እንዳከናወነ ተናግሯል። (ሥራ 2:22) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የፈጸማቸው ተአምራት በንጉሣዊ አገዛዙ ወቅት ለምናገኛቸው የላቁ በረከቶች እንደ ቅምሻ ናቸው። እንዲሁም በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚፈጽማቸው ተአምራት ጥላ ናቸው! ከዚህም በተጨማሪ የኢየሱስ ተአምራት ስለ እሱም ሆነ ስለ አባቱ ባሕርይ ጥልቅ ማስተዋል ይሰጡናል። እስቲ ከእነዚህ ተአምራት ጥቂቶቹን እንመልከት፤ ይህም ተአምራቱ አሁንም ሆነ ወደፊት ለእኛ ምን ትርጉም እንደሚኖራቸው ለማወቅ ያስችለናል።

ልግስናን የሚያስተምር ተአምር

3. (ሀ) ኢየሱስ የመጀመሪያ ተአምሩን እንዲፈጽም ያነሳሳው ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ለጋስ መሆኑ በቃና የታየው እንዴት ነው?

3 ኢየሱስ የመጀመሪያ ተአምሩን የፈጸመው በገሊላ በምትገኘው በቃና በተከናወነ የሠርግ ድግስ ላይ ነው። በድግሱ ላይ ከተጠበቀው በላይ ብዙ እንግዶች መጥተው ሊሆን ይችላል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን የወይን ጠጅ አለቀ። ከተጠሩት እንግዶች መካከል የኢየሱስ እናት ማርያም ትገኝበታለች። ማርያም ስለ ልጇ በተነገሩት ትንቢቶች ላይ ለዓመታት ስታሰላስል እንደቆየች ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም ልጇ ‘የልዑሉ አምላክ ልጅ’ ተብሎ እንደሚጠራ ታውቃለች። (ሉቃስ 1:30-32፤ 2:52) ማርያም፣ ኢየሱስ ለሰዎች እስካሁን ያላሳየው ኃይል እንዳለው ተማምና ይሆን? ያም ሆነ ይህ ማርያምና ኢየሱስ ለአዲሶቹ ተጋቢዎች እንዳዘኑላቸውና ከእፍረት ሊታደጓቸው እንደፈለጉ አሳይተዋል። ተጋቢዎቹ ለእንግዶች ጥሩ መስተንግዶ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ኢየሱስ ያውቃል። በመሆኑም 380 ሊትር የሚሆነውን ውኃ በተአምር ወደ ‘ጥሩ የወይን ጠጅ’ ለወጠው። (ዮሐንስ 2:3, 6-11ን አንብብ።) ኢየሱስ ይህን ተአምር የመፈጸም ግዴታ ነበረበት? በፍጹም። ይህን ያደረገው ለሰዎች ስለሚያስብና ለጋስ የሆነውን በሰማይ ያለውን አባቱን ምሳሌ ስለተከተለ ነው።

4, 5. (ሀ) የኢየሱስ የመጀመሪያ ተአምር ምን ያስተምረናል? (ለ) በቃና የተፈጸመው ተአምር ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ይጠቁመናል?

4 ኢየሱስ ለብዙ ሕዝብ የሚበቃ በርከት ያለ ጥሩ የወይን ጠጅ በተአምር አቅርቧል። ከዚህ ተአምር ምን ትምህርት እንደምናገኝ አስተዋልክ? ኢየሱስ እንዲህ ያለ አስደናቂ ድርጊት በፈቃደኝነት መፈጸሙ፣ እሱም ሆነ አባቱ የሰዎች ስሜት እንደሚያሳስባቸው ያስገነዝበናል። አብም ሆነ ወልድ ስስታም አይደሉም። ይሖዋ በአዲሱ ዓለም፣ በምድር ዙሪያ ለሚገኙ “ሕዝቦች ሁሉ” ታላቅ ግብዣ ለማድረግ ኃይሉን ምን ያህል በልግስና እንደሚጠቀምበት ለማሰብ ሞክር።ኢሳይያስ 25:6ን አንብብ።

5 እስቲ አስበው! እንደ ተመጣጣኝ ምግብና ጥሩ መኖሪያ ያሉት የሰዎች ልጆች መሠረታዊ ፍላጎቶችና የሚመኟቸው ነገሮች፣ ለሁሉም ሰው የሚሟሉበት ጊዜ በቅርቡ ይመጣል። ይሖዋ፣ ምድር ገነት በምትሆንበት ጊዜ በልግስና አትረፍርፎ የሚሰጠንን ጥሩ ነገሮች በጉጉት በመጠባበቅ ሐሴት እናድርግ።

ጊዜያችንን በልግስና ስንሰጥ ለጋስ የሆነውን የኢየሱስን ምሳሌ እንደምንከተል እናሳያለን (አንቀጽ 6ን ተመልከት)

6. ኢየሱስ ተአምራዊ ኃይሉን የተጠቀመው እነማንን ለመርዳት ነው? እኛስ በዚህ ረገድ ልንመስለው የምንችለው እንዴት ነው?

6 ድንጋዮቹን ወደ ዳቦ እንዲቀይር ዲያብሎስ በፈተነው ጊዜ ክርስቶስ ተአምር የመፈጸም ችሎታውን የራሱን ጥቅም ለማርካት እንዳልተጠቀመበት ልብ ሊባል ይገባል። (ማቴ. 4:2-4) ይሁንና ሌሎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ኃይሉን ተጠቅሞበታል። እኛስ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ለሌሎች አሳቢነት በማሳየት ረገድ ኢየሱስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ የአምላክ አገልጋዮችን “ስጡ” በማለት አበረታቷቸዋል። (ሉቃስ 6:38) እኛስ ሌሎችን ቤታችን ጠርተን ምግብ በመጋበዝና በመንፈሳዊ በመተናነጽ ግሩም ባሕርይ የሆነውን ልግስናን ማሳየት እንችላለን? እገዛ የሚያስፈልጋቸውን በመርዳት ለምሳሌ ከስብሰባ በኋላ አንድ ወንድም ንግግሩን ሲለማመድ በማዳመጥ፣ ጊዜያችንን በልግስና መስጠት እንችላለን? በአገልግሎት እገዛ የሚያስፈልጋቸውንስ እንዴት መርዳት እንችላለን? አዎ፣ አቅማችን በፈቀደ መጠን ለሌሎች ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ነገሮችን በልግስና በማካፈል የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን።

“ሁሉም በልተው ጠገቡ”

7. ይህ ሥርዓት እስካልጠፋ ድረስ ምን ሁኔታ ይኖራል?

7 ድህነት በእኛ ዘመን የጀመረ ነገር አይደለም። ይሖዋ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን መቼም ቢሆን ከምድሪቱ ላይ ድሆች እንደማይጠፉ ነግሯቸዋል። (ዘዳ. 15:11) ከበርካታ ዘመናት በኋላ ደግሞ ኢየሱስ “ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው” ብሏል። (ማቴ. 26:11) ኢየሱስ ይህን ሲል በምድር ላይ ምንጊዜም ቢሆን ድሆች እንደሚኖሩ መናገሩ ነበር? አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ይህ ብልሹ ሥርዓት እስካልጠፋ ድረስ ድሆች መኖራቸው እንደማይቀር መግለጹ ነው። በእርግጥም የኢየሱስ ተአምራት ወደፊት በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣና ሁሉም ሰው በቂ ምግብ አግኝቶ እንደሚጠግብ ተስፋ የሚሰጡ እንደሆኑ ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው!

8, 9. (ሀ) ኢየሱስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በተአምር እንዲመግብ ያነሳሳው ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንደመገበ የሚናገረውን ታሪክ ስታነብ ምን ይሰማሃል?

8 መዝሙራዊው፣ ይሖዋን “አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታሟላለህ” ብሎታል። (መዝ. 145:16) ‘የአምላክ ኃይል የሆነው ክርስቶስም’ የአብን ምሳሌ በመከተል እጆቹን ዘርግቶ የተከታዮቹን ፍላጎት ብዙ ጊዜ አሟልቷል። ይህን ያደረገው ኃይሉን ለማሳየት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ተአምራት እንዲፈጽም ያነሳሳው ለሌሎች ያለው ልባዊ አሳቢነት ነው። እስቲ ማቴዎስ 14:14-21እንመልከት። (ጥቅሱን አንብብ።) ደቀ መዛሙርቱ በቂ ምግብ አለመኖሩን ለኢየሱስ ነገሩት። ይህን ያደረጉት እነሱ ራሳቸው ስለራባቸው ሊሆን ይችላል፤ በተጨማሪም ኢየሱስን ተከትለው ከየከተማዎቹ በእግር የመጡት ሰዎች ርቧቸውና ደክሟቸው ስለሚሆን ይህ ሁኔታ ደቀ መዛሙርቱን አሳስቧቸዋል። (ማቴ. 14:13) ታዲያ ኢየሱስ ምን አደረገ?

9 በአምስት ዳቦና በሁለት ዓሣ፣ ከሴቶችና ከልጆች ሌላ 5,000 ወንዶችን መገበ! ኢየሱስ ትናንሽ ልጆችን ጨምሮ ለሕዝቡ በሙሉ ርኅራኄ በማሳየት ተአምር የመፈጸም ኃይሉን ስለተጠቀመበት መንገድ ስናስብ ልባችን አይነካም? መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም በልተው ጠገቡ” ይላል። ይህም የተትረፈረፈ ምግብ እንደነበር ይጠቁማል። ኢየሱስ በደግነት ለሕዝቡ ያቀረበው ምግብ እንዲያው ቅምሻ ብቻ ሳይሆን ወደ ቤታቸው ለሚያደርጉት ረጅም ጉዞ ኃይል የሚሰጣቸው ነበር። (ሉቃስ 9:10-17) የተረፈውም ምግብ 12 ቅርጫት ሙሉ ሆነ!

10. ከድህነት ጋር በተያያዘ በቅርቡ ምን ለውጥ ይመጣል?

10 በዛሬው ጊዜ፣ በግፍ በተሞላው ሰብዓዊ አገዛዝ የተነሳ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መሠረታዊ ፍላጎት ሊሟላ አልቻለም። አንዳንድ ወንድሞቻችን ጦማቸውን ባያድሩም እንኳ በቂ ምግብ የማያገኙበት ጊዜ አለ። ይሁንና ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች፣ ሙስናና ድህነት በሌለበት ዓለም ውስጥ የሚኖሩበት ጊዜ ቀርቧል። አንተ ኃይል ቢኖርህ ኖሮ የሰው ልጆችን ፍላጎት አታሟላም ነበር? ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ይህን ለማድረግ ኃይሉም ሆነ ፍላጎቱ አለው፤ በቅርቡም ይህን ያደርጋል። አዎ፣ እፎይታ የምናገኝበት ጊዜ ሩቅ አይደለም!መዝሙር 72:16ን አንብብ።

11. ክርስቶስ በቅርቡ ኃይሉን በመላው ምድር ላይ እንደሚጠቀምበት እንድትተማመን ያደረገህ ምንድን ነው? ይህስ ምን እንድታደርግ ያነሳሳሃል?

11 ኢየሱስ በምድር እያለ ተአምራትን የፈጸመው በአንጻራዊ ሁኔታ በትንሽ ክልል ውስጥ ለአጭር ጊዜ ይኸውም ለሦስት ዓመት ተኩል ነው። (ማቴ. 15:24) ንጉሥ ሆኖ በክብር ሲመጣ ግን መላዋን ምድር ያስተዳድራል። (መዝ. 72:8) የኢየሱስ ተአምራት፣ ሥልጣኑን እኛን በሚጠቅም መንገድ ለማዋል ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ እንዳለው እንድንተማመን ያደርጉናል። እኛም ተአምራት መፈጸም ባንችልም እንኳ ሰዎች በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ በግለት ልንረዳቸው እንችላለን። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ያረጋግጡልናል። ታዲያ ስለ ወደፊቱ ጊዜ እንዲህ ያለ ልዩ እውቀት ያለን ራሳችንን የወሰነን የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን፣ ለሰዎች ዕዳ እንዳለብን ሊሰማን አይገባም? (ሮም 1:14, 15) በዚህ ጉዳይ ላይ ማሰላሰላችን ለሌሎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመናገር ያነሳሳናል።—መዝ. 45:1፤ 49:3

የተፈጥሮ ኃይሎችን መቆጣጠር

12. ኢየሱስ ስለ ምድር ሥነ ምህዳር በሚገባ እንደሚያውቅ እርግጠኛ የምንሆነው ለምንድን ነው?

12 አምላክ ምድርንና በውስጧ ያሉትን ነገሮች ሲፈጥር “የተዋጣለት ሠራተኛ” የሆነው አንድያ ልጁ ከጎኑ ነበር። (ምሳሌ 8:22, 30, 31፤ ቆላ. 1:15-17) በመሆኑም ኢየሱስ ስለ ምድር ሥነ ምህዳር በሚገባ ያውቃል። የምድርን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መጠቀም፣ ማስተዳደር እንዲሁም ለነዋሪዎቹ ማዳረስ ይችልበታል።

ኢየሱስ ተአምር የመፈጸም ኃይሉን ከተጠቀመበት መንገድ ጋር በተያያዘ የሚያስገርምህ ምንድን ነው? (አንቀጽ 13, 14ን ተመልከት)

13, 14. ክርስቶስ የተፈጥሮ ኃይሎችን መቆጣጠር እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ስጥ።

13 ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ የተፈጥሮ ኃይሎችን በመቆጣጠር “የአምላክ ኃይል” መሆኑን አሳይቷል። የደቀ መዛሙርቱን ሕይወት አደጋ ላይ የጣለ አውሎ ነፋስ በተነሳበት ወቅት ምን እንዳደረገ እንመልከት። (ማርቆስ 4:37-39ን አንብብ።) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “[ማርቆስ 4:37 ላይ “አውሎ ነፋስ” ተብሎ የተተረጎመው] የግሪክኛ ቃል የሚሠራበት ከባድ ማዕበልን ወይም ውሽንፍርን ለማመልከት ነው። ቀለል ያለ ነፋስን . . . በፍጹም አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ ሰማዩ በጥቁር ደመና እንዲሸፈን ብሎም ነፋስ የቀላቀለና ነጎድጓድ አዘል ዶፍ እንዲጥል እንዲሁም ሁሉ ነገር ምስቅልቅል እንዲል የሚያደርግ ኃይለኛ ወጀብን ያመለክታል።” የማቴዎስ ዘገባ ይህን አውሎ ነፋስ “ኃይለኛ ማዕበል” በማለት ይገልጸዋል።—ማቴ. 8:24

14 የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር፦ ክርስቶስ አገልግሎቱን ሲያከናውን በመዋሉ በጣም ደክሞታል። ማዕበሉ ጀልባዋን እያንገላታት ብሎም ጀልባዋ ውስጥ ውኃ ተረጭቶ እየገባ ነው። የማዕበሉ ድምፅ ኃይለኛ ከመሆኑም ሌላ ጀልባዋ እየተናጠች ቢሆንም ኢየሱስ ድብን ያለ እንቅልፍ ወስዶታል። ሰውነቱ በጣም ዝሏል። በፍርሃት የተዋጡት ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን ቀስቅሰው “ማለቃችን እኮ ነው” አሉት። (ማቴ. 8:25) ኢየሱስ ከእንቅልፉ ተነስቶ ነፋሱንና ባሕሩን “ጸጥ በል! ረጭ በል!” አለው፤ አውሎ ነፋሱም ቆመ። (ማር. 4:39) ኢየሱስ ነፋሱንና ባሕሩን ረጭ እንዲሉ እያዘዘ ነበር። ውጤቱ ምን ሆነ? መጽሐፍ ቅዱስ “ታላቅ ጸጥታም ሰፈነ” ይላል። ኢየሱስ ምንኛ ታላቅ ኃይል አለው!

15. ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የተፈጥሮ ኃይሎችን መቆጣጠር እንደሚችል ያሳየው እንዴት ነው?

15 ክርስቶስ ኃይል ያገኘው ከይሖዋ ነው፤ በመሆኑም ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የተፈጥሮ ኃይሎችን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር እንደሚችል እርግጠኞች ለመሆን የሚያበቃ ምክንያት አለን። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎች እንመልከት። ከጥፋት ውኃ በፊት ይሖዋ “ከሰባት ቀን በኋላ በምድር ላይ 40 ቀንና 40 ሌሊት ዝናብ አዘንባለሁ” ብሎ ነበር። (ዘፍ. 7:4) በተመሳሳይም ዘፀአት 14:21 “ይሖዋም ሌሊቱን ሙሉ ኃይለኛ የምሥራቅ ነፋስ በማምጣት ባሕሩ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደረገ” ይላል። በዮናስ 1:4 ላይ ደግሞ “ይሖዋ በባሕሩ ላይ ኃይለኛ ነፋስ አመጣ፤ ከባድ ማዕበል ስለተነሳ መርከቧ ልትሰበር ተቃረበች” የሚል ሐሳብ እናገኛለን። ይሖዋ የተፈጥሮ ኃይሎችን እንደሚቆጣጠር ማወቁ የሚያጽናና ነው። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የፕላኔታችን የወደፊት ዕጣ አስጊ አይደለም።

16. ፈጣሪያችንም ሆነ የበኩር ልጁ የተፈጥሮ ኃይሎችን መቆጣጠር እንደሚችሉ ማወቃችን የመተማመን ስሜት እንዲያድርብን የሚያደርገው ለምንድን ነው?

16 ፈጣሪያችን እንዲሁም “የተዋጣለት ሠራተኛ” የሆነው ልጁ ባላቸው አስደናቂ ኃይል ላይ ማሰላሰላችን የመተማመን ስሜት እንዲያድርብን ያደርጋል! ይሖዋና ኢየሱስ ለ1,000 ዓመታት ያህል ሙሉ ትኩረታቸውን በምድር ላይ በሚያደርጉበት ወቅት ሁሉም ሰው ያለ ስጋት መኖር ይችላል። አስፈሪ የሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ ታሪክ ብቻ ሆነው ይቀራሉ። በአዲሱ ዓለም ውስጥ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ፣ ማዕበል፣ እሳተ ገሞራ ወይም የምድር መናወጥ ጉዳት ያደርሱብናል ብለን የምንፈራበት ምክንያት አይኖርም። “የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር” ስለሚሆን በተፈጥሮ ኃይሎች ምክንያት የሚሞቱ ወይም የአካል ጉዳተኛ የሚሆኑ ሰዎች እንደማይኖሩ ማወቁ እንዴት ያስደስታል! (ራእይ 21:3, 4) በሺው ዓመት ግዛት ወቅት አምላክ በክርስቶስ በኩል ኃይሉን በመጠቀም የተፈጥሮ ኃይሎችን እንደሚቆጣጠር መተማመን እንችላለን።

ከአሁኑ አምላክንና ክርስቶስን ምሰሉ

17. በአሁኑ ጊዜ አምላክንና ክርስቶስን መምሰል የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

17 እርግጥ ነው፣ እንደ ይሖዋና እንደ ኢየሱስ እኛ የተፈጥሮ አደጋዎች እንዳይደርሱ ማድረግ አንችልም፤ ያም ቢሆን በተወሰነ መጠን ኃይል አለን። ታዲያ ኃይላችንን እንዴት እንጠቀምበታለን? አንዱ መንገድ ምሳሌ 3:27 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ተግባራዊ ማድረግ ነው። (ጥቅሱን አንብብ።) ወንድሞቻችን መከራ ሲደርስባቸው ቁሳዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ድጋፍ ልናደርግላቸው እንዲሁም ልናጽናናቸው እንችላለን። (ምሳሌ 17:17) ለምሳሌ፣ ከተፈጥሮ አደጋ በኋላ እንደገና እንዲቋቋሙ ልንረዳቸው እንችላለን። ባሏ የሞተባት አንዲት እህት ኃይለኛ ወጀብ ቤቷን አፈራርሶባት ነበር፤ የተደረገላትን እርዳታ አስመልክታ እንደሚከተለው በማለት ምስጋናዋን ገልጻለች፦ “በይሖዋ ድርጅት ውስጥ በመሆኔ ለተደረገልኝ ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ድጋፍም እጅግ በጣም አመስጋኝ ነኝ።” አንዲት ያላገባች እህት ደግሞ ዝናብ የቀላቀለ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ በቤቷ ላይ ያደረሰውን ጉዳት ስትመለከት ግራ ተጋብታና በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተውጣ ነበር። ይህች እህት እርዳታ ካገኘች በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “ምን እንደሚሰማኝ መግለጽ አልችልም! ስሜቴን ሙሉ በሙሉ ለመግለጽ ቃላት ያጥሩኛል። . . . ይሖዋ አመሰግንሃለሁ!” በእርግጥም ሌሎች ለሚያስፈልጋቸው ነገር እውነተኛ አሳቢነት በሚያሳይ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ መታቀፋችን ያስደስተናል። ይበልጥ የሚያስደስተን ደግሞ ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ ለአምላክ ሕዝቦች በጥልቅ ማሰባቸው ነው።

18. ኢየሱስ ተአምራት የፈጸመበትን ምክንያት በተመለከተ ትኩረታችንን የሚስበው ምንድን ነው?

18 ኢየሱስ “የአምላክ ኃይል” መሆኑን አገልግሎቱን ሲያከናውን አሳይቷል። ይሁንና እንዲህ እንዲያደርግ ያነሳሳው ምንድን ነው? ሌሎችን ለማስደመም ወይም ራሱን ለመጥቀም ኃይሉን የተጠቀመበት ጊዜ የለም። እንዲያውም ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር ያሳያሉ። ይህን ጉዳይ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመረምራለን።