በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በይሖዋ ጽኑ ፍቅር ላይ አሰላስሉ

በይሖዋ ጽኑ ፍቅር ላይ አሰላስሉ

‘በሥራዎችህ ሁሉ ላይ አሰላስላለሁ።’—መዝ. 77:12

መዝሙሮች፦ 18, 61

1, 2. (ሀ) ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚወድ የምትተማመነው ለምንድን ነው? (ለ) ሁሉም ሰዎች በተፈጥሯቸው ምን ፍላጎት አላቸው?

ይሖዋ ሕዝቡን ይወዳል ብለህ እንድታምን ያደረገህ ምንድን ነው? ይህን ጥያቄ ከመመለስህ በፊት እስቲ እነዚህን ምሳሌዎች ተመልከት፦ ታሊን የተባለችን እህት የእምነት አጋሮቿ ሚዛናዊ እንድትሆንና ከራሷ ብዙ እንዳትጠብቅ ለረጅም ዓመታት በደግነት ሲያሳስቧት ቆይተዋል። ታሊን “ይሖዋ ባይወደኝ ኖሮ የዚህን ያህል በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ አይሰጠኝም ነበር” ብላለች። ባሏን በሞት በማጣቷ ምክንያት ሁለት ልጆቿን ብቻዋን ያሳደገች ብሪጀት የተባለች እናት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ሰይጣን በሚቆጣጠረው ሥርዓት ውስጥ ልጆችን ማሳደግ በተለይ ለነጠላ ወላጅ በጣም ከባድ ፈተና ነው። ሆኖም ይሖዋ እንደሚወደኝ እርግጠኛ ነኝ፤ ምክንያቱም ልብ የሚሰብርና የሚያስለቅስ ሁኔታ ባጋጠመኝ ጊዜ ሁሉ የሚያስፈልገኝን መመሪያ ሰጥቶኛል። እንዲሁም መሸከም ከምችለው በላይ እንድፈተን አልተወኝም።” (1 ቆሮ. 10:13) ሳንድራም መዳን ከማይችል ሕመም ጋር እየታገለች ትኖራለች። ብዙዎች የሚያውቁት አንድ ወንድም ሚስት፣ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ሳንድራን ትኩረት ሰጥታ አነጋገረቻት። የሳንድራ ባለቤት እንዲህ ብሏል፦ “ምንም እንኳ በቅርበት ባናውቃትም ጥልቅ አሳቢነቷ ልባችን በደስታ እንዲሞላ አድርጓል። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንደሚወዱን ለማሳየት የሚያደርጓቸው ትናንሽ ነገሮች እንኳ ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደን ያስታውሰኛል።”

2 ሰዎች በተፈጥሯችን የመውደድና የመወደድ ፍላጎት አለን። ይህ ፍላጎታችን ሳይሟላ ሲቀር በቀላሉ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን፤ እንደማንወደድ እንዲሰማን ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል ያልጠበቅናቸው ሁኔታዎች መከሰታቸው ወይም የጠበቅነው ሳይሆን መቅረቱ፣ ጤና ማጣት፣ የኢኮኖሚ ችግር አሊያም በአገልግሎት ውጤታማ አለመሆን ይገኙበታል። ይሖዋ እንደቀድሞው እንደማይወደን ከተሰማን በእሱ ፊት ውድ እንደሆንን ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው፤ እንዲሁም “ቀኝ እጅህን ይዣለሁ” ስላለን ከጎናችን ይሆናል፤ እርዳታውም አይለየንም። እኛ ለእሱ ታማኝ እስከሆንን ድረስ ይሖዋ መቼም አይረሳንም።—ኢሳ. 41:13፤ 49:15

3. ይሖዋ ለእኛ ጽኑ ፍቅር እንዳለው እርግጠኛ እንድንሆን ምን ይረዳናል?

3 ቀደም ብለው የተጠቀሱት ግለሰቦች በፈተና ወቅት አምላክ ከእነሱ ጋር እንደነበረ እርግጠኞች ናቸው። እኛም በተመሳሳይ ይሖዋ ከጎናችን እንደሆነ መተማመን እንችላለን። (መዝ. 118:6, 7) የአምላክ ፍቅር (1) ከፍጥረት ሥራዎቹ፣ (2) በመንፈስ መሪነት ከተጻፈው ቃሉ፣ (3) ከጸሎት እና (4) ከቤዛው ጋር በተያያዘ እንዴት እንደተገለጸ በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ ይብራራል። ይሖዋ ባከናወናቸው መልካም ሥራዎች ላይ ማሰላሰላችን እሱ ለሚያሳየን ጽኑ ፍቅር ያለንን አድናቆት እንደሚጨምረው ግልጽ ነው።መዝሙር 77:11, 12ን አንብብ።

በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ላይ አሰላስሉ

4. በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ላይ ማሰላሰላችን ምን እንድንገነዘብ ይረዳናል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

4 ይሖዋ የፈጠራቸውን ነገሮች በማየት ለእኛ ጽኑ ፍቅር እንዳለው ማወቅ እንችላለን? አዎ እንችላለን፤ ምክንያቱም ይሖዋ ለመፍጠር መነሳሳቱ በራሱ ፍቅሩን ይገልጻል። (ሮም 1:20) ምድርን ሲፈጥር ሕይወት ያለምንም ስጋት እንዲቀጥል የሚያስችል ሥነ ምህዳር እንዲኖራት አድርጓል። ያም ቢሆን በሕይወት ከመኖር ባለፈ እንድናገኝ የሚፈልገው ነገር አለ። ለምሳሌ በሕይወት ለመቀጠል መብላት ይኖርብናል። ይሖዋ ምድርን ሲፈጥር ለጤና ተስማሚ የሆነ ምግብ ለማዘጋጀት የሚያስችሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዕፀዋትን እንድታፈራ አድርጓታል። ሌላው ቀርቶ ምግብ መመገብ በራሱ አስደሳችና አርኪ እንዲሆንልን አድርጓል! (መክ. 9:7) ካትሪን የተባለች እህት፣ በተለይ መንፈስን በሚያድሰው የካናዳ የጸደይ ወቅት የፍጥረት ሥራዎችን መመልከት በጣም ያስደስታታል። ሕይወት ያላቸው ነገሮች የሚያደርጉት ለውጥ ምን ያህል እንደሚያስደንቃት ተናግራለች፤ እንዲህ ብላለች፦ “አበቦች ጊዜያቸውን ጠብቀው ማበባቸው፣ ወፎች ከፈለሱበት መመለስ መቻላቸው እንዲሁም ትንሿ ሃሚንግበርድ እንኳ ኩሽናዬ መስኮት ላይ ወዳስቀመጥኩላት ጎጆዋ ተመልሳ መምጣቷ ያስገርማል። ይሖዋ እነዚህን ሁሉ አስደሳች ነገሮች የሰጠን ቢወደን ነው።” አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን በፍጥረት ሥራዎቹ ይደሰታል፤ እኛም በእነዚህ ነገሮች እንድንደሰት ይፈልጋል።—ሥራ 14:16, 17

5. ሰዎች የተፈጠሩበት መንገድ የይሖዋን ፍቅር የሚያሳየው እንዴት ነው?

5 ይሖዋ ሲፈጥረን፣ ትርጉም ያለውና ውጤታማ ሥራ የማከናወን ችሎታ ሰጥቶናል፤ ይህ ደግሞ በሕይወታችን እንድንደሰት ተጨማሪ አስተዋጽኦ ያደርጋል። (መክ. 2:24) የይሖዋ ዓላማ ሰዎች ምድርን እንዲሞሏት፣ እንዲገዟት እንዲሁም በዓሣዎች፣ በወፎች ብሎም ሕይወት ባላቸው ሌሎች ነገሮች ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው ነው። (ዘፍ. 1:26-28) ይሖዋ፣ እሱን ለመምሰል የሚያስችሉን ባሕርያት እንዲኖሩን አድርጎ የፈጠረን መሆኑም ምን ያህል አፍቃሪ እንደሆነ ያሳያል።—ኤፌ. 5:1

በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱ

6. ለአምላክ ቃል ከፍተኛ አድናቆት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?

6 አምላክ በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን ቃሉን በመስጠት ለእኛ ታላቅ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። ቃሉ ስለ እሱ ማወቅ ያሉብንን ነገሮች እንዲሁም ከሰው ልጆች ጋር ስላለው ግንኙነት ይገልጽልናል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ በተደጋጋሚ ካመፁበት ከእስራኤላውያን ጋር ስለነበረው ግንኙነት ቅዱሳን መጻሕፍት ይናገራሉ። መዝሙር 78:38 እንዲህ ይላል፦ “እሱ . . . መሐሪ ነው፤ በደላቸውን ይቅር ይል ነበር፤ ደግሞም አላጠፋቸውም። ቁጣውን ሁሉ ከመቀስቀስ ይልቅ ብዙ ጊዜ ስሜቱን ይገታ ነበር።” በዚህ ጥቅስ ላይ ማሰላሰልህ ይሖዋ ስለ አንተ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብና እንደሚወድህ እንድትገነዘብ ሊያደርግህ ይችላል። በይሖዋ ፊት ውድ እንደሆንክ እርግጠኛ ሁን።1 ጴጥሮስ 5:6, 7ን አንብብ።

7. ለመጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ አክብሮት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?

7 አምላክ እኛን ለማነጋገር በዋነኝነት የሚጠቀመው በመጽሐፍ ቅዱስ ስለሆነ ለቃሉ ጥልቅ አክብሮት ሊኖረን ይገባል። ወላጆችም ሆኑ ልጆች አንዳቸው ለሌላው ፍቅር እንዳላቸው እንዲሰማቸው እንዲሁም በመካከላቸው የመተማመን ስሜት እንዲኖር፣ ትርጉም ያለውና ደግነት የሚንጸባረቅበት የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋቸው ወሳኝ ነው። ከይሖዋ ጋር በተያያዘስ ምን መጠበቅ ይኖርብናል? ይሖዋን አይተነውም ሆነ ድምፁን ሰምተን ባናውቅም እንኳ በመንፈስ መሪነት ባስጻፈው ቃሉ አማካኝነት “ያነጋግረናል”፤ እኛም ልናዳምጠው ይገባል። (ኢሳ. 30:20, 21) ራሳችንን ለእሱ የወሰንን ሕዝቦቹ በመሆናችን ይሖዋ ሊመራን እንዲሁም ከጉዳት ሊጠብቀን ይፈልጋል። በተጨማሪም እንድናውቀውና እንድንተማመንበት ይሻል።መዝሙር 19:7-11ን እና ምሳሌ 1:33ን አንብብ።

ኢዮሳፍጥ በኢዩ መመከር ቢኖርበትም እንኳ ይሖዋ በዚህ ንጉሥ ላይ “መልካም ነገር” አግኝቶበታል (አንቀጽ 8, 9ን ተመልከት)

8, 9. ይሖዋ ምን እንድናውቅ ይፈልጋል? ይህን የሚያሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ጥቀስ።

8 ይሖዋ፣ የሚወደንና ከጉድለታችን ባሻገር የሚመለከት አምላክ እንደሆነ እንድገነዘብ ይፈልጋል። በእኛ ውስጥ ያለውን መልካም ነገር ለማግኘት ይጥራል። (2 ዜና 16:9) ለምሳሌ ያህል፣ ከይሁዳ ንጉሥ ከኢዮሳፍጥ ጋር በተያያዘ ይህን አድርጓል። በአንድ ወቅት የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ፣ ራሞትጊልያድን ከሶርያውያን ለማስመለስ ባደረገው ዘመቻ አብሮት እንዲሄድ ለኢዮሳፍጥ ጥያቄ አቀረበለት፤ እሱም ተስማማ። ይህ ግን ጥበብ የጎደለው ውሳኔ ነበር። ምንም እንኳ 400 የሚያህሉ የሐሰት ነቢያት ክፉው አክዓብ ድል እንደሚያደርግ ቢናገሩም አክዓብ መሸነፉ እንደማይቀር እውነተኛው የይሖዋ ነቢይ ሚካያህ ተንብዮ ነበር። አክዓብ በጦርነቱ የሞተ ሲሆን ኢዮሳፍጥም ሕይወቱ የተረፈው ለጥቂት ነው። ኢዮሳፍጥ ከአክዓብ ጋር ጥምረት በመፍጠሩ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ ተግሣጽ ተሰጥቶታል። ያም ሆኖ ባለ ራእዩ የሃናኒ ልጅ ኢዩ፣ ኢዮሳፍጥን “መልካም ነገር ተገኝቶብሃል” ብሎታል።—2 ዜና 18:4, 5, 18-22, 33, 34፤ 19:1-3

9 ኢዮሳፍጥ በሥልጣን ዘመኑ መጀመሪያ ላይ መኳንንት፣ ሌዋውያንና ካህናት በይሁዳ ከተሞች ሁሉ እየተዘዋወሩ የይሖዋን ሕግ ለሕዝቡ እንዲያስተምሩ ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር። ዘመቻው በጣም ውጤታማ በመሆኑ በይሁዳ ዙሪያ የነበሩ ብሔራት ይሖዋን መፍራት ጀመሩ። (2 ዜና 17:3-10) በእርግጥ ኢዮሳፍጥ የሞኝነት ድርጊት ፈጽሟል፤ ሆኖም ቀደም ሲል ያከናወናቸውን መልካም ነገሮች ይሖዋ አልረሳም። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፣ ፍጹማን ባንሆንም እንኳ ይሖዋን ለማስደሰት በሙሉ ልባችን የምንጥር ከሆነ እሱም ለእኛ ጽኑ ፍቅር እንደሚኖረው ያስታውሰናል።

ለጸሎት መብት አድናቆት ይኑራችሁ

10, 11. (ሀ) ጸሎት ከይሖዋ ያገኘነው ልዩ መብት ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠን በየትኞቹ መንገዶች ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

10 አፍቃሪ የሆነ አባት፣ ልጆቹ ሊያነጋግሩት ሲፈልጉ ጊዜ ወስዶ ያዳምጣቸዋል። በልባቸው ያለው ነገር ስለሚያሳስበው ስሜታቸውንና የሚያስጨንቃቸውን ነገር ለማወቅ ይፈልጋል። የሰማዩ አባታችን ይሖዋም ውድ በሆነው የጸሎት መብታችን አማካኝነት ወደ እሱ ስንቀርብ ይሰማናል።

11 በማንኛውም ጊዜ ወደ ይሖዋ በጸሎት መቅረብ እንችላለን። አምላክ በዚህ ረገድ ምንም ዓይነት ገደብ አላስቀመጠም። ሁልጊዜ ጆሮ ሰጥቶ የሚያዳምጠን ወዳጃችን ነው። ቀደም ብላ የተጠቀሰችው ታሊን “የምንፈልገውን ማንኛውንም ነገር ምንም ሳናስቀር ለእሱ መናገር እንችላለን” ብላለች። የውስጣችንን አውጥተን ለአምላክ በጸሎት ስንነግረው እሱ በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ፣ መጽሔት ላይ በወጣ ርዕስ ወይም ደግሞ ከእምነት ባልንጀራችን በምናገኘው የሚያበረታታ ሐሳብ አማካኝነት ለጸሎታችን ምላሽ ሊሰጠን ይችላል። ይሖዋ ልመናችንን ይሰማል፤ እንዲሁም ስሜታችንን ማንም በማይረዳልን ጊዜም እንኳ እሱ የውስጣችንን ያውቃል። ለእኛ ጽኑ ፍቅር እንዳለው ከሚያሳይበት ግሩም መንገድ አንዱ ለጸሎታችን የሚሰጠው ምላሽ ነው።

12. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ለሚገኙት ጸሎቶች ትኩረት መስጠት ያለብን ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

12 በአምላክ ቃል ውስጥ ከተመዘገቡት ጸሎቶች ብዙ መማር እንችላለን። በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ በቤተሰብ አምልኮ ወቅት እንደዚህ ባሉ ጸሎቶች ላይ መወያየታችን በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ጥንት የነበሩት የይሖዋ አገልጋዮች የሚያሳስባቸውን ነገር ለአምላክ በገለጹበት መንገድ ላይ በማሰላሰል የጸሎታችንን ይዘት ማሻሻል እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ዮናስ በአንድ ትልቅ ዓሣ ሆድ ውስጥ ሆኖ በጸጸት ስሜት ያቀረበውን ጸሎት መመልከት ትችላላችሁ። (ዮናስ 1:17 እስከ 2:10) ሰለሞን የቤተ መቅደሱ ምረቃ ላይ ያቀረበውን ከልብ የመነጨ ጸሎትም መከለስ ይቻላል። (1 ነገ. 8:22-53) እንዲሁም ኢየሱስ ለእኛ ጥቅም ሲል ባስተማረው የጸሎት ናሙና ላይ ማሰላሰል ትችላላችሁ። (ማቴ. 6:9-13) ከሁሉ በላይ ደግሞ ያለማሰለስ “ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ።” እንዲህ ካደረጋችሁ “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።” ይህም ይሖዋ ላሳያችሁ ጽኑ ፍቅር ይበልጥ አመስጋኝ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል።—ፊልጵ. 4:6, 7

ለቤዛው አመስጋኝ ሁኑ

13. ፍቅር የተንጸባረቀበት የቤዛው ዝግጅት ለሰው ዘር ምን አጋጣሚ ከፍቷል?

13 አምላክ በጸጋው የሰጠን የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት “ሕይወት ማግኘት እንድንችል” መንገድ ከፍቶልናል። (1 ዮሐ. 4:9) ሐዋርያው ጳውሎስ ከሁሉ የላቀውን ይህን የአምላክ ፍቅር መግለጫ አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ክርስቶስ አስቀድሞ የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ ለኃጢአተኞች ሞቷልና። ለጻድቅ ሰው የሚሞት ማግኘት በጣም አዳጋች ነው፤ ለጥሩ ሰው ለመሞት የሚደፍር ግን ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ሆኖም አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ እንዲሞትልን በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል።” (ሮም 5:6-8) ይህ ታላቅ የአምላክ ፍቅር መገለጫ፣ መላው የሰው ዘር በይሖዋ ፊት ሞገስ እንዲያገኝ አጋጣሚ ከፍቷል።

14, 15. ቤዛው (ሀ) ለቅቡዓን ክርስቲያኖች (ለ) ምድራዊ ተስፋ ላላቸው ምን ያስገኝላቸዋል?

14 ይሖዋ ለጥቂቶች ጽኑ ፍቅሩን በጣም ልዩ በሆነ መንገድ አሳይቷቸዋል። (ዮሐ. 1:12, 13፤ 3:5-7) እነዚህ ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ በመቀባታቸው “የአምላክ ልጆች” መሆን ችለዋል። (ሮም 8:15, 16) ጳውሎስ ስለ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሲናገር ‘ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ስላላቸው ከእሱ ጋር ተነስተው በሰማያዊ ስፍራ እንደተቀመጡ’ ገልጿል። (ኤፌ. 2:6) ይህን መንፈሳዊ ውርሻ ሊያገኙ የቻሉት ‘ቃል በተገባው መንፈስ ቅዱስ በመታተማቸው ምክንያት ነው’፤ ይህም ‘ለውርሻቸው’ ማለትም ‘በሰማይ ለሚጠብቃቸው ተስፋ’ “አስቀድሞ የተሰጠ ማረጋገጫ ነው።”—ኤፌ. 1:13, 14፤ ቆላ. 1:5

15 በቤዛው የሚያምኑ አብዛኞቹ የሰው ዘሮች ደግሞ የይሖዋ ወዳጅ መሆን ይችላሉ፤ ወደፊት የአምላክ ልጆች የመሆን እንዲሁም ቃል በተገባው መሠረት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ አላቸው። ይሖዋ ይህን በማድረግ ለመላው የሰው ዘር ያለውን ፍቅር በቤዛው አማካኝነት አሳይቷል። (ዮሐ. 3:16) በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የምናደርግ እንዲሁም ይሖዋን ምንጊዜም በታማኝነት የምናገለግል ከሆነ በአዲሱ ዓለም አስደሳች ሕይወት እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንግዲያው የቤዛውን ዝግጅት፣ ከሁሉ የላቀ የአምላክ ጽኑ ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አድርገን መመልከታችን ምንኛ የተገባ ነው!

ይሖዋ ላሳየን ፍቅር ምላሽ ስጡ

16. ይሖዋ ፍቅሩን ባሳየባቸው በርካታ መንገዶች ላይ ማሰላሰላችን ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?

16 ይሖዋ ለእኛ ያለውን የማይነጥፍ ፍቅር የገለጸባቸውን መንገዶች ዘርዝረን መጨረስ አንችልም። መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ ሲል ዘምሯል፦ “ሐሳቦችህ ለእኔ ምንኛ ውድ ናቸው! አምላክ ሆይ፣ ቁጥራቸው ምንኛ ብዙ ነው! ልቆጥራቸው ብሞክር ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ።” (መዝ. 139:17, 18) ይሖዋ ለእኛ ፍቅራዊ አሳቢነቱን ባሳየባቸው መንገዶች ላይ ማሰላሰላችን በምላሹ እኛም በጥልቅ እንድንወደውና እሱን የማገልገል ፍላጎት እንዲኖረን ሊያነሳሳን ይችላል። እንግዲያው ለእሱ ምርጣችንን ለመስጠት ጥረት እናድርግ።

17, 18. ለአምላክ ፍቅር እንዳለን የምናሳይባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

17 ለይሖዋ ያለንን ፍቅር የምናሳይባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በመንግሥቱ የስብከት ሥራ በቅንዓት በመካፈል ለአምላክና ለሰዎች ፍቅር እንዳለን ማሳየት እንችላለን። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) የእምነት ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ንጹሕ አቋማችንን ከጠበቅን ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። (መዝሙር 84:11ን እና ያዕቆብ 1:2-5ን አንብብ።) የሚያጋጥሙን ፈተናዎች ከባድ በሚሆኑበት ጊዜም እንኳ አምላክ ሥቃያችንን እንደሚያውቅ እንዲሁም እንደሚደግፈን እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ምክንያቱም በእሱ ፊት ውድ ነን።—መዝ. 56:8

18 ለይሖዋ ያለን ፍቅር በፍጥረት ሥራዎቹ ላይ እንድናሰላስል እንዲሁም ስላደረጋቸው ሌሎች ድንቅ ነገሮች እንድናስብ ይገፋፋናል። መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት በማጥናት አምላክን እንደምንወደው እንዲሁም ለቃሉ የላቀ አክብሮት እንዳለን እናሳያለን። ለይሖዋ ያለን ፍቅር ይበልጥ በጸሎት እንድንቀርበው ያነሳሳናል። በተጨማሪም አምላክ ለኃጢአታችን ማስተሰረያ እንዲሆን ባደረገው የቤዛ ዝግጅት ላይ ስናሰላስል ለእሱ ያለን ፍቅር የበለጠ ይጨምራል። (1 ዮሐ. 2:1, 2) ይሖዋ ጽኑ ፍቅር ስላሳየን እኛም በምላሹ እሱን እንድንወደው ከሚያደርጉን ብዙ ምክንያቶች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ናቸው።