በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመጨረሻዎቹ ቀናት በጓደኛ ምርጫችሁ ጥንቃቄ አድርጉ

በመጨረሻዎቹ ቀናት በጓደኛ ምርጫችሁ ጥንቃቄ አድርጉ

“መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል።”—1 ቆሮ. 15:33

መዝሙሮች፦ 73, 119

1. የምንኖረው በምን ዓይነት ዘመን ውስጥ ነው?

የምንኖረው በጣም አስቸጋሪ በሆነ ዘመን ውስጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከ1914 ወዲህ ያለውን ጊዜ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ በማለት ይጠራዋል። “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ” የተባለው ይህ ዘመን፣ ከዚያ ወሳኝ ዓመት በፊት በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከነበሩት ሁሉ ይልቅ አስከፊ የሆኑ ሁኔታዎች በጉልህ ታይተውበታል። (2 ጢሞ. 3:1-5) ከዚህም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት “ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች . . . በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ” ስለሚል በዓለም ላይ ያሉት ሁኔታዎች ይበልጥ እየተበላሹ መሄዳቸው አይቀርም።—2 ጢሞ. 3:13

2. ይህ ዓለም የሚያቀርበው መዝናኛ ምን ዓይነት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

2 ብዙ ሰዎች ለመዝናናት ብለው የሚያዩአቸው ወይም የሚፈጽሟቸው ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ ዓመፅ፣ የፆታ ብልግና፣ መናፍስትነት ወይም ርኩሰት እንደሆኑ የሚገልጻቸው ድርጊቶች ናቸው። ለምሳሌ ኢንተርኔት፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ፊልሞች፣ ልብ ወለድ መጻሕፍትና መጽሔቶች ዓመፅንና የፆታ ብልግናን እንደ መልካም ነገር አድርገው ያቀርባሉ። በአንድ ወቅት ተቀባይነት እንደሌላቸው የሚታዩ ድርጊቶች በአሁኑ ጊዜ ተቀባይነት ከማግኘትም አልፈው በአንዳንድ አገሮች ሕጋዊ ሆነዋል። ይህ መሆኑ ግን እነዚህ ድርጊቶች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ አያደርግም።ሮም 1:28-32ን አንብብ።

3. የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች አክብረው የሚኖሩ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ እንዴት ይታያሉ?

3 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ የኢየሱስ ተከታዮች ርኩስ ከሆነ መዝናኛ ይርቁ ነበር። እንዲህ በማድረጋቸውና አምላካዊ ባሕርያትን በማንጸባረቃቸው መጥፎ ስም ይሰጣቸው እንዲሁም ስደት ይደርስባቸው ነበር። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለክርስቲያኖች ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን በመሰለው ያዘቀጠ ወራዳ ሕይወት ከእነሱ ጋር መሮጣችሁን ስለማትቀጥሉ ግራ ይጋባሉ፤ በመሆኑም ይሰድቧችኋል።” (1 ጴጥ. 4:4) ዛሬም ቢሆን የአምላክን መሥፈርቶች አክብረው የሚኖሩ ሰዎች በዓለም ዘንድ ከሰው የተለዩ እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ። በተጨማሪም “የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል።”—2 ጢሞ. 3:12

“መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል”

4. ቅዱሳን መጻሕፍት ከዚህ ዓለም ጋር በተያያዘ ምን እንዳናደርግ ይመክሩናል?

4 ቅዱሳን መጻሕፍት፣ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ የሚፈልጉ ሁሉ ዓለምንም ሆነ በዓለም ላይ የሚፈጸሙትን ድርጊቶች መውደድ እንደሌለባቸው ይናገራሉ። (1 ዮሐንስ 2:15, 16ን አንብብ።) የዚህ ዓለም ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም የንግድ ድርጅቶችና የመረጃ መረባቸው “የዚህ ሥርዓት አምላክ” በሆነው በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ይገኛሉ። (2 ቆሮ. 4:4፤ 1 ዮሐ. 5:19) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በጓደኛ ምርጫችን ረገድ ጠንቃቃ መሆን ይኖርብናል። በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የአምላክ ቃል የሚከተለውን መሠረታዊ ሐቅ ይዟል፦ “አትታለሉ። መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል።”—1 ቆሮ. 15:33

5, 6. ከእነማን ጋር ጓደኝነት ሊኖረን አይገባም? ለምንስ?

5 መልካሙ አመላችን እንዳይበላሽ ከፈለግን መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች የቅርብ ጓደኞቻችን ሊሆኑ አይገባም። ይህም ሲባል መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙ የማያምኑ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ይሖዋን እናመልካለን እያሉ ሆን ብለው ሕጎቹን የሚጥሱ ሰዎችም ጓደኞቻችን መሆን የለባቸውም ማለት ነው። ክርስቲያን ነን የሚሉ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ከባድ ኃጢአት ፈጽመው ንስሐ የማይገቡ ከሆነ ከእነሱ ጋር ያለን ጓደኝነት መቋረጥ ይኖርበታል።—ሮም 16:17, 18

6 የአምላክን ሕግጋት ከማይታዘዙ ሰዎች ጋር ጓደኝነት ከመሠረትን በእነሱ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ስንል እነሱ የሚያደርጉትን ነገር ለመፈጸም ልንገፋፋ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ የፆታ ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎች የቅርብ ጓደኞቻችን ከሆኑ እኛም ብልግና ለመፈጸም ልንፈተን እንችላለን። ራሳቸውን የወሰኑ አንዳንድ ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ደርሶባቸዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ንስሐ ባለመግባታቸው ተወግደዋል። (1 ቆሮ. 5:11-13) እነዚህ ሰዎች ንስሐ ካልገቡ ጴጥሮስ የገለጸው ዓይነት ሁኔታ ይደርስባቸዋል።2 ጴጥሮስ 2:20-22ን አንብብ።

7. የቅርብ ጓደኞቻችን አድርገን መምረጥ የሚኖርብን እነማንን ነው?

7 የአምላክን ሕግ ለማይከተሉ ሰዎች እንኳ ደግነት ማሳየት ቢገባንም ከእነሱ ጋር ወዳጅነት ልንመሠርት ወይም የቅርብ ጓደኛችን ልናደርጋቸው አይገባም። በመሆኑም አንድ ያላገባ የይሖዋ ምሥክር፣ ራሱን ለአምላክ ካልወሰነና ለይሖዋ ታማኝ ካልሆነ እንዲሁም የአምላክን የላቁ መሥፈርቶች ከማያከብር ሰው ጋር የፍቅር ጓደኝነት መመሥረቱ ስህተት ይሆናል። በይሖዋ ሕግጋት በማይመሩ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ከማግኘት ይበልጥ ትልቅ ቦታ ልንሰጠው የሚገባው ነገር፣ ክርስቲያናዊ አቋማችንን ይዘን መቀጠላችን ነው። የቅርብ ወዳጆቻችን ሊሆኑ የሚገባው የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉ ሰዎች ናቸው። ኢየሱስ “የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ ለእኔ ወንድሜ፣ እህቴና እናቴ ነው” ብሏል።—ማር. 3:35

8. መጥፎ ጓደኝነት የጥንቶቹን እስራኤላውያን የጎዳቸው እንዴት ነው?

8 መጥፎ ጓደኝነት የሚያስከትለው አስከፊ መዘዝ በእስራኤላውያን ላይ ደርሷል። ይሖዋ፣ እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲመራቸው በዚያ ከሚኖሩት ሰዎች ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባው ግንኙነት እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ለአማልክታቸው አትስገድ፤ ወይም ተታለህ እነሱን አታገልግል፤ የሚያደርጉትን ነገር አታድርግ። ከዚህ ይልቅ አውድማቸው፤ የማምለኪያ ዓምዶቻቸውንም ሰባብር። አምላካችሁን ይሖዋን አገልግሉ።” (ዘፀ. 23:24, 25) የኋላ ኋላ ግን አብዛኞቹ እስራኤላውያን የአምላክን መመሪያዎች አልታዘዙም። (መዝ. 106:35-39) ለአምላክ ታማኝ ባለመሆናቸው ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ “እነሆ፣ ቤታችሁ ለእናንተ የተተወ ይሆናል” ብሏቸዋል። (ማቴ. 23:38) በመሆኑም ይሖዋ እስራኤላውያንን ትቶ በረከቱን አዲስ በተቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ ላይ አደረገ።—ሥራ 2:1-4

የምታነቡትንም ሆነ የምታዩትን በጥንቃቄ ምረጡ

9. የዚህ ዓለም የመገናኛ ብዙኃንና የመዝናኛው ኢንዱስትሪ የሚያቀርቧቸው ነገሮች አደገኛ የሆኑት ለምንድን ነው?

9 የዚህ ዓለም የመገናኛ ብዙኃንና የመዝናኛው ኢንዱስትሪ የሚያቀርቧቸው አብዛኞቹ ነገሮች የክርስቲያኖችን መንፈሳዊነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው። እነዚህ ነገሮች በይሖዋና እሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት እንድናዳብር አይረዱንም። ከዚህ በተቃራኒ ሰዎች በሰይጣን ክፉ ዓለም እንዲታመኑ የሚያበረታቱ ናቸው። በመሆኑም የምናየው፣ የምናነበው ወይም የምንሰማው ነገር “ዓለማዊ ምኞቶችን” የሚቀሰቅስ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል።—ቲቶ 2:12

10. ይህ ዓለም ሰዎች እንዲያነቧቸውም ሆነ እንዲመለከቷቸው የሚያቀርባቸው ጎጂ ነገሮች ምን ይሆናሉ?

10 ይህ ዓለም ሰዎች እንዲያነቧቸውም ሆነ እንዲመለከቷቸው የሚያቀርባቸው መጥፎ ነገሮች በቅርቡ ይወገዳሉ። የእነዚህ ነገሮች ምንጭ የሆነው የሰይጣን ዓለም ሲጠፋ እነሱም አብረው ይጠፋሉ። የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “ዓለምም ሆነ ምኞቱ ያልፋሉ፤ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።” (1 ዮሐ. 2:17) በተመሳሳይም መዝሙራዊው እንደሚከተለው በማለት ዘምሯል፦ “ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ምድርን ይወርሳሉ። የዋሆች . . . ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል።” ይህ የሚሆነው ለምን ያህል ጊዜ ነው? መዝሙራዊው “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት መልሱን ይሰጠናል።—መዝ. 37:9, 11, 29

11. አምላክ ለሕዝቡ ጥሩ መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርበው እንዴት ነው?

11 ከዚህ ዓለም በተቃራኒ የይሖዋ ድርጅት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ያደረገልን ዝግጅቶች የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝልን ምግባር እንድንከተል ያበረታቱናል። ኢየሱስ ለይሖዋ ባቀረበው ጸሎት ላይ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው” ብሏል። (ዮሐ. 17:3) በሰማይ ያለው አባታችን በድርጅቱ አማካኝነት የሚያንጹ መንፈሳዊ ምግቦችን አትረፍርፎ እያቀረበልን ነው። እውነተኛውን አምልኮ የሚያስፋፉ መጽሔቶች፣ ብሮሹሮች፣ መጻሕፍት፣ ቪዲዮዎች እንዲሁም ድረ ገጾች ያሉን በመሆኑ ምንኛ ተባርከናል! በተጨማሪም የአምላክ ድርጅት በዓለም ዙሪያ ከ110,000 በሚበልጡ ጉባኤዎች አማካኝነት ቋሚ የሆኑ ስብሰባዎች እንዲኖሩን ዝግጅት አድርጎልናል። በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ በአምላክ እንዲሁም እሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት እንድናዳብር የሚረዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች ይቀርባሉ።—ዕብ. 10:24, 25

“በጌታ ብቻ” አግቡ

12. መጽሐፍ ቅዱስ “በጌታ ብቻ” ማግባትን አስመልክቶ የሰጠውን ምክር አብራራ።

12 ማግባት የሚፈልጉ ክርስቲያኖች ጓደኝነትን በተመለከተ ይበልጥ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። የአምላክ ቃል የሚከተለውን ግልጽ ምክር ይሰጣል፦ “ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ። ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ኅብረት አለው? ወይስ ብርሃን ከጨለማ ጋር ምን ያገናኘዋል?” (2 ቆሮ. 6:14) መጽሐፍ ቅዱስ፣ የትዳር ጓደኛ የሚፈልጉ የአምላክ አገልጋዮች “በጌታ ብቻ” እንዲያገቡ ይኸውም ራሱን ወስኖ የተጠመቀና በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች የሚመራ የይሖዋ አገልጋይ ብቻ እንዲያገቡ ይመክራል። (1 ቆሮ. 7:39) ክርስቲያኖች ከእምነት ባልንጀራቸው ጋር በትዳር ሲጣመሩ፣ ራሱን ለይሖዋ የወሰነና ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው እንዲመላለሱ የሚያግዛቸው አጋር ያገኛሉ።

13. አምላክ ጋብቻን በተመለከተ ለእስራኤላውያን ምን መመሪያ ሰጥቶ ነበር?

13 ይሖዋ ለአገልጋዮቹ የተሻለው ነገር ምን እንደሆነ ያውቃል፤ በተጨማሪም ጋብቻን በተመለከተ ያለው አመለካከት ምንጊዜም አይለወጥም። በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን የሰጠውን የማያሻማ መመሪያ እንመልከት። እስራኤላውያን፣ በዙሪያቸው ያሉ ሕዝቦችን ይኸውም ይሖዋን የማያገለግሉ ሰዎችን በተመለከተ የሚከተለው መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበር፦ “ከእነሱ ጋር በጋብቻ አትዛመድ። ሴቶች ልጆችህን ለወንዶች ልጆቻቸው አትዳር ወይም ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንዶች ልጆችህ አትውሰድ። ምክንያቱም ልጆችህ ሌሎች አማልክትን ያገለግሉ ዘንድ እኔን ከመከተል ዞር እንዲሉ ያደርጓቸዋል፤ ከዚያም የይሖዋ ቁጣ በእናንተ ላይ ይነድዳል፤ አንተንም ወዲያው ያጠፋሃል።”—ዘዳ. 7:3, 4

14, 15. ሰለሞን የይሖዋን መመሪያ ችላ ማለቱ ምን አስከተለበት?

14 የዳዊት ልጅ ሰለሞን በንግሥና ዘመኑ መጀመሪያ ላይ ይሖዋ ጥበብ እንዲሰጠው ጸልዮ ነበር፤ አምላክም ጥበብን አብዝቶ ሰጥቶታል። በዚህም የተነሳ ንጉሥ ሰለሞን ባለጸጋ በሆነች አገር ላይ የሚገዛ ጥበበኛ ንጉሥ በመሆኑ ይታወቅ ነበር። እንዲያውም የሳባ ንግሥት፣ ሰለሞንን በጎበኘችው ወቅት እንደሚከተለው በማለት በአድናቆት ተናግራለች፦ “እኔ ራሴ መጥቼ በገዛ ዓይኔ እስከማይ ድረስ የተነገረኝን ነገር አላመንኩም ነበር። እንደዚያም ሆኖ ግማሹ እንኳ አልተነገረኝም! በጥበብም ሆነ በብልጽግና ከሰማሁት ሁሉ እጅግ የላቅክ ነህ።” (1 ነገ. 10:7) ይሁንና የሰለሞን ሕይወት፣ አንድ ሰው አምላክ የሰጠውን መመሪያ ችላ ብሎ የማያምን ሰው ሲያገባ ምን ሊከተል እንደሚችል የሚያሳይ አሳዛኝ ምሳሌ ነው።—መክ. 4:13

15 ሰለሞን፣ አምላክ ብዙ ነገር ያደረገለት ቢሆንም እስራኤላውያን ይሖዋን ከማያመልኩ የሌላ አገር ሴቶች ጋር ጋብቻ እንዳይፈጽሙ የሚያዘውን መለኮታዊ መመሪያ ጥሷል። ሰለሞን “ብዙ የባዕድ አገር ሴቶችን . . . አፈቀረ”፤ በመሆኑም 700 ሚስቶች እንዲሁም 300 ቁባቶች ነበሩት። ይህ ምን አስከተለበት? ሰለሞን በሸመገለ ጊዜ አረማዊ የሆኑ ሚስቶቹ “ልቡ ሌሎች አማልክትን ወደ መከተል እንዲያዘነብል አደረጉት፤ . . . ሰለሞንም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።” (1 ነገ. 11:1-6) ሰለሞን መጥፎ ጓደኝነት መመሥረቱ፣ የነበረውን ጥበብ እያደር እንዲያጣና ከእውነተኛው አምልኮ እንዲርቅ አድርጎታል። ይሖዋን የማይወድ ሰው ማግባት ለሚያስቡ ክርስቲያኖች ይህ ጥሩ ማስጠንቀቂያ ይሆናቸዋል!

16. አማኝ ያልሆነ የትዳር ጓደኛ ያለችው የአምላክ አገልጋይ የትኛውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር መከተል ይኖርበታል?

16 አንድ ሰው የአምላክ አገልጋይ የሆነው ከማያምን ሰው ጋር ትዳር ከመሠረተ በኋላ ቢሆንስ? መጽሐፍ ቅዱስ “እናንተ ሚስቶች፣ ለቃሉ የማይታዘዙ ባሎች ካሉ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው ምግባር እንዲማረኩ ለባሎቻችሁ ተገዙ” ይላል። (1 ጴጥ. 3:1) ይህ ሐሳብ የተጻፈው ለክርስቲያን ሚስቶች ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ይሖዋን ማምለክ ለጀመሩና የማያምኑ ሚስቶች ላሏቸው ባሎችም ይሠራል። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ግልጽ ነው፦ ጥሩ የትዳር አጋር ሁኑ፤ እንዲሁም አምላክ ለጋብቻ ያወጣቸውን የላቁ መሥፈርቶች ተግባራዊ አድርጉ። በርካታ የማያምኑ ሰዎች፣ የትዳር ጓደኛቸው የአምላክን መመሪያዎች መከተል ከጀመረ በኋላ ምን ያህል ለውጥ እንዳደረገ ሲመለከቱ እነሱም እውነትን ተቀብለዋል።

ይሖዋን ከሚወዱ ጋር ጓደኝነት መሥርቱ

17, 18. ኖኅም ሆነ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ ክርስቲያኖች በዘመናቸው የነበረው ሥርዓት ሲጠፋ በሕይወት ሊተርፉ የቻሉት ለምንድን ነው?

17 መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል እንደሚያበላሽ ሁሉ ጥሩ ጓደኝነት ደግሞ መልካም ባሕርያትን እንድናፈራ ይረዳናል። በክፋት በተሞላ ዓለም ውስጥ ይኖር የነበረውን ኖኅን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ኖኅ በዘመኑ የነበሩ ሰዎችን የቅርብ ጓደኞቹ አላደረገም። በዚያ ወቅት “ይሖዋ የሰው ልጅ ክፋት በምድር ላይ እንደበዛና የልቡም ሐሳብ ሁሉ ምንጊዜም ወደ መጥፎ ብቻ ያዘነበለ እንደሆነ ተመለከተ።” (ዘፍ. 6:5) በመሆኑም አምላክ ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ በማምጣት ያንን ክፉ ሥርዓትና ደጋፊዎቹን ጠራርጎ ለማጥፋት ወሰነ። በአንጻሩ ግን “ኖኅ ጻድቅ ሰው ነበር። በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች መካከል እሱ እንከን የሌለበት ሰው ነበር። ኖኅ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ ነበር።”—ዘፍ. 6:7-9

18 ኖኅ፣ ፈሪሃ አምላክ ከሌላቸው ሰዎች ጋር ፈጽሞ ወዳጅነት እንዳልመሠረተ ጥያቄ የለውም። እሱም ሆነ ሰባቱ የቤተሰቡ አባላት መርከብ መሥራትን ጨምሮ አምላክ የሰጣቸውን ኃላፊነት በመወጣት ላይ ትኩረት አድርገው ነበር። በተጨማሪም ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” ነበር። (2 ጴጥ. 2:5) ኖኅ መስበኩ፣ መርከብ መሥራቱና ከቤተሰቡ ጋር የነበረው ቅርርብ አምላክ የሚደሰትባቸውን መልካም ነገሮች በማከናወን እንዲጠመድ አስችሎታል። በዚህም የተነሳ ኖኅና ቤተሰቡ ከጥፋት ውኃው መትረፍ ችለዋል። በዛሬው ጊዜ ያለን በሙሉ የእነዚህ የይሖዋ አገልጋዮች ዘሮች ነን፤ ታማኙ ኖኅ፣ ሚስቱ፣ ልጆቹና ሚስቶቻቸው ባለውለታችን ናቸው። በተመሳሳይም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ታማኝና ታዛዥ ክርስቲያኖች አምላካዊ ፍርሃት ከሌላቸው ሰዎች በመራቃቸው በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌምና የአይሁድ ሥርዓት ሲጠፉ መትረፍ ችለዋል።—ሉቃስ 21:20-22

ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር የመሠረትነው የሚያንጽ ወዳጅነት በአዲሱ ዓለም ለሚኖረው ሕይወት ቅምሻ ነው (አንቀጽ 19ን ተመልከት)

19. የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

19 የይሖዋ አምላኪዎች እንደመሆናችን መጠን ኖኅ፣ ቤተሰቡና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ታዛዥ ክርስቲያኖች የተዉትን ምሳሌ መከተል ይኖርብናል። በዙሪያችን ካለው ክፉ ሥርዓት መራቃችን እንዲሁም በሚሊዮን ከሚቆጠሩት ታማኝ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መካከል የሚያንጹ ጓደኞች ለማፍራት ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። አምላክ በሚሰጠው ጥበብ ከሚመሩ ጋር መቀራረባችን በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ‘በእምነት ጸንተን ለመቆም’ ይረዳናል። (1 ቆሮ. 16:13፤ ምሳሌ 13:20) ወደፊት የሚጠብቁንን ግሩም ነገሮች እስቲ አስብ! በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት በጓደኛ ምርጫችን ረገድ ጠንቃቃ ከሆንን ይህ ክፉ ሥርዓት በሚጠፋበት ጊዜ በግለሰብ ደረጃ በሕይወት ተርፈን ይሖዋ በቅርቡ ወደሚያመጣው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም መግባት እንችላለን!