በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቶስ የደረሰበት የጉልምስና ደረጃ ላይ ለመድረስ እየተጣጣራችሁ ነው?

ክርስቶስ የደረሰበት የጉልምስና ደረጃ ላይ ለመድረስ እየተጣጣራችሁ ነው?

“እንደ ክርስቶስ የተሟላ የጉልምስና ደረጃ ላይ [ድረሱ]።”—ኤፌ. 4:13

መዝሙሮች፦ 69, 70

1, 2. እያንዳንዱ ክርስቲያን ምን ዓይነት እድገት ለማድረግ ጥረት ማድረግ አለበት? በምሳሌ አስረዳ።

አንዲት የቤት እመቤት ገበያ ወጥታ ፍራፍሬ ስትገዛ ሁልጊዜ ትላልቅ የሆኑትን ወይም ርካሽ የሆኑትን ብቻ አትመርጥም። ከዚህ ይልቅ የበሰሉ ፍሬዎችን ለማግኘት ትጥራለች። ፍላጎቷ ጣፋጭና ግሩም መዓዛ ያለውን እንዲሁም ለሰውነት ጠቃሚ የሆነውን ፍሬ ማግኘት ነው። አዎ፣ እድገቱን የጨረሰ በሌላ አባባል በደንብ የበሰለ ፍሬ ትመርጣለች።

2 አንድ ሰው ራሱን ወስኖ ከተጠመቀም በኋላ እድገት ማድረጉን ይቀጥላል። ግቡ የጎለመሰ የአምላክ አገልጋይ መሆን ነው። እዚህ ላይ እየተናገርን ያለነው ስለ አካላዊ ጉልምስና ሳይሆን ስለ መንፈሳዊ ጉልምስና ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ያሉ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ እድገት ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ጽፎላቸዋል። “በእምነትና ስለ አምላክ ልጅ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም ወደሚገኘው አንድነት እንዲሁም ሙሉ ሰው ወደ መሆን ይኸውም እንደ ክርስቶስ የተሟላ የጉልምስና ደረጃ ላይ” ለመድረስ እንዲጣጣሩ አበረታቷቸዋል።—ኤፌ. 4:13

3. በኤፌሶን ጉባኤና በዛሬው ጊዜ በሚገኙት የይሖዋ ሕዝቦች መካከል ምን ተመሳሳይ ሁኔታ ይታያል?

3 ጳውሎስ ደብዳቤውን በጻፈበት ወቅት የኤፌሶን ጉባኤ ከተቋቋመ የተወሰኑ ዓመታት አልፈው ነበር። በዚያ የሚገኙ በርካታ ደቀ መዛሙርት ከፍ ያለ መንፈሳዊ የእድገት ደረጃ ላይ ደርሰው ነበር። አንዳንዶቹ ግን አሁንም ወደ ጉልምስና ደረጃ ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸው ነበር። በዛሬው ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ብዙዎቹ ወንድሞችና እህቶች አምላክን ረዘም ላሉ ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩና በመንፈሳዊ የጎለመሱ ናቸው። ሆኖም ሁሉም የጉልምስና ደረጃ ላይ ደርሰዋል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ሰዎች ይጠመቃሉ፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ መንፈሳዊ ጉልምስና ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። አንተስ እድገት ማድረግ ያስፈልግህ ይሆን?—ቆላ. 2:6, 7

ክርስቲያናዊ እድገት

4, 5. የጎለመሱ ክርስቲያኖች አንዳቸው ከሌላው የሚለዩት በየትኞቹ መንገዶች ነው? ይሁንና ሁሉም የሚያመሳስላቸው ነገር ምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

4 ገበያ ወጥተህ የበሰሉ ፍራፍሬዎችን ስታማርጥ ሁሉም ፍራፍሬዎች አንድ ዓይነት እንዳልሆኑ ማስተዋልህ አይቀርም። ያም ሆኖ ሁሉም መብሰላቸው የሚታወቅበት መንገድ አለ። በተመሳሳይም የጎለመሱ ክርስቲያኖች በብሔር፣ በአስተዳደግ፣ በአካላዊ ጤንነት፣ በዕድሜና በልምድ ሊለያዩ ይችላሉ። አልፎ ተርፎም የባሕርይ ወይም የባሕል ልዩነት አላቸው። ይሁንና በመንፈሳዊ እድገት የሚያደርጉ ሁሉ የጎለመሱ መሆናቸውን የሚያሳዩ ባሕርያትን ያንጸባርቃሉ። እንዴት?

5 አንድ የጎለመሰ የይሖዋ አገልጋይ በአኗኗሩ ኢየሱስን ለመምሰልና ‘የእሱን ፈለግ በጥብቅ ለመከተል’ ጥረት ያደርጋል። (1 ጴጥ. 2:21) ኢየሱስ ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ አድርጎ የገለጸው ነገር ምንድን ነው? ይሖዋን በሙሉ ልብ፣ ነፍስና አእምሮ መውደድ እንዲሁም ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ ነው። (ማቴ. 22:37-39) አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ይህን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ይጥራል። አኗኗሩ ከይሖዋ ጋር ለመሠረተው ዝምድና ቅድሚያ እንደሚሰጥና ለሌሎች የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር እንዳለው ያሳያል።

በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች፣ ግንባር ቀደም ሆነው እየሠሩ ላሉት ወጣት ወንድሞች ድጋፍ በመስጠት የክርስቶስ ዓይነት ትሕትና ማሳየት ይችላሉ (አንቀጽ 6ን ተመልከት)

6, 7. (ሀ) አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ተለይቶ የሚታወቅባቸው አንዳንድ ባሕርያት ምንድን ናቸው? (ለ) ቀጥሎ ስለ ምን ጉዳይ እንመለከታለን?

6 ይሁንና ፍቅር አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ከሚያሳያቸው የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ ብቻ እንደሆነ ግልጽ ነው። (ገላ. 5:22, 23) እንደ ገርነት፣ ራስን መግዛትና ትዕግሥት ያሉት ሌሎች ገጽታዎችም በጣም አስፈላጊ ናቸው። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት እንዳይበሳጭ እንዲሁም ቅስም የሚሰብሩ አሳዛኝ ነገሮች ሲደርሱበት ተስፋ ሳይቆርጥ እንዲጸና ሊረዱት ይችላሉ። የግል ጥናት በሚያደርግበት ጊዜ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችል የሚረዱትን ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማግኘት ያለማሰለስ ምርምር ያደርጋል። ከዚያም በሕይወቱ ውስጥ የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች መንፈሳዊ ጉልምስና እንዳለው የሚያሳዩ ይሆናሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናው የሚነግረውን ያዳምጣል። አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን በራሱ ከመመራት ይልቅ ይሖዋ ባወጣቸው መመሪያዎችና መሥፈርቶች መመራት ምንጊዜም የተሻለ እንደሆነ አምኖ በመቀበል ትሕትና እንዳለው ያሳያል። * ምሥራቹን በቅንዓት ይሰብካል፤ እንዲሁም ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ ያበረክታል።

7 ይሖዋን ለረጅም ዓመታት ያገለገልንም እንሁን ለአጭር ጊዜ፣ እያንዳንዳችን ‘የኢየሱስን አርዓያ በጥብቅ በመከተልና መንፈሳዊ እድገት በማድረግ ረገድ አሁንም ማሻሻያ ማድረግ የምችልባቸው አቅጣጫዎች ይኖራሉ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።

‘ጠንካራ ምግብ ለጎልማሳ ሰዎች ነው’

8. ኢየሱስ ቅዱሳን መጻሕፍትን በተመለከተ ስለነበረው እውቀትና ግንዛቤ ምን ማለት ይቻላል?

8 ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክን ቃል በሚገባ ያውቅ ነበር። ገና የ12 ዓመት ልጅ እያለ በቤተ መቅደሱ ካሉ አስተማሪዎች ጋር ቅዱሳን መጻሕፍትን እየጠቀሰ ይወያይ ነበር። “በዚያ የነበሩት ሰዎችም ሁሉ በመረዳት ችሎታውና በመልሱ ተደንቀው ያዳምጡት ነበር።” (ሉቃስ 2:46, 47) ከጊዜ በኋላ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ከአምላክ ቃል ላይ ተስማሚ የሆኑ ሐሳቦችን በመጥቀስ ተቃዋሚዎቹን አፋቸውን አስይዟቸዋል።—ማቴ. 22:41-46

9. (ሀ) መንፈሳዊ እድገት ማድረግ የሚፈልግ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ረገድ ምን ዓይነት ልማድ ማዳበር ይኖርበታል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስን የምናጠናበት ዓላማ ምንድን ነው?

9 በመንፈሳዊ እድገት ማድረግ የሚፈልግ ክርስቲያን ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በመከተል ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖረው የተቻለውን ጥረት ያደርጋል። ‘ጠንካራ ምግብ ለጎልማሳ ሰዎች’ እንደሆነ በመገንዘብ በየጊዜው ቃሉን በጥልቀት ይቆፍራል። (ዕብ. 5:14) አንድ ጎልማሳ ክርስቲያን “ስለ አምላክ ልጅ ትክክለኛ እውቀት” መቅሰም እንደሚፈልግ የታወቀ ነው። (ኤፌ. 4:13) በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን የምታነብበት ፕሮግራም አለህ? የግል ጥናት የምታደርግበትስ ቋሚ ፕሮግራም አለህ? በየሳምንቱ የቤተሰብ አምልኮ ለማድረግ ጊዜ መድበሃል? የአምላክን ቃል ስታጠና የይሖዋን አመለካከትና ስሜት ይበልጥ እንድትረዳ የሚያስችሉህን ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማግኘት ጥረት አድርግ። ከዚያም በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተመሥርተህ ውሳኔ አድርግ፤ እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ይበልጥ ወደ ይሖዋ እየቀረብክ ትሄዳለህ።

10. አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ያለው እውቀት በዕለት ተዕለት ሕይወቱ ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?

10 አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን እውቀት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ይገነዘባል። ከእውቀት ባሻገር ለሚያውቃቸው የአምላክ መመሪያዎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ልባዊ ፍቅር ሊኖረው ይገባል። በሕይወቱ ውስጥ የራሱን ፍላጎት ሳይሆን ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማሙ ነገሮችን የሚያስቀድም ከሆነ እንዲህ ዓይነት ፍቅር እንዳለው ያሳያል። ከዚህም ሌላ ይህ ክርስቲያን ቀደም ሲል የነበረውን አስተሳሰብና አኗኗር ‘አውልቆ እንደጣለ’ ምንም ጥያቄ የለውም። አንድ ክርስቲያን ይህን ለውጥ ሲያደርግ “እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን” ክርስቶስ ያንጸባረቀውን ዓይነት አዲስ ስብዕና ይለብሳል። (ኤፌሶን 4:22-24ን አንብብ።) መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በአምላክ መንፈስ መሪነት ነው። አንድ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቱ እየጨመረና ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያለው ፍቅር እያደገ የሚሄድ ከሆነ መንፈስ ቅዱስ በልቡና በአእምሮው ውስጥ እንዲሠራ ይፈቅዳል። ይህ ደግሞ ለመንፈሳዊ እድገቱ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

አንድነት ይኑራችሁ

11. ኢየሱስ ከቤተሰቡና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በተያያዘ ምን ሁኔታ አጋጥሞታል?

11 ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሆኖ ምድር ላይ ባሳለፈው ሕይወት ፍጽምና ከሚጎድላቸው ሰዎች ጋር ኖሯል። ያሳደጉት ወላጆቹ ፍጹም አልነበሩም፤ እንዲሁም ፍጽምና ከሚጎድላቸው ዘመዶቹ ጋር ለብዙ ዓመታት አብሮ ኖሯል። የቅርብ ተከታዮቹ እንኳ ሳይቀር በብዙዎች ዘንድ የሚታየው ሥልጣን የማግኘት ፍላጎትና የራስ ወዳድነት መንፈስ ተጋብቶባቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ከመገደሉ በፊት በነበረው ምሽት “‘ከመካከላችን ታላቅ የሆነው ማን ነው?’ በሚል በመካከላቸው የጦፈ ክርክር ተነሳ።” (ሉቃስ 22:24) ይሁንና ኢየሱስ ፍጽምና የሚጎድላቸው ተከታዮቹ መንፈሳዊ እድገት እንደሚያደርጉና አንድነት ያለው ጉባኤ መመሥረት እንደሚችሉ እርግጠኛ ነበር። ኢየሱስ ሐዋርያቱ አንድነት እንዲኖራቸው በዚያው ዕለት ምሽት በሰማይ ለሚኖረው አባቱ እንዲህ ሲል ጸልዮአል፦ “ይህን ልመና የማቀርበውም ሁሉም አንድ እንዲሆኑ ነው፤ ይኸውም . . . አባት ሆይ፣ አንተ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለህና እኔም ከአንተ ጋር አንድነት እንዳለኝ ሁሉ እነሱም ከእኛ ጋር አንድነት እንዲኖራቸው ነው። እኛ አንድ እንደሆንን ሁሉ እነሱም አንድ እንዲሆኑ [ነው]።”—ዮሐ. 17:21, 22

12, 13. (ሀ) ኤፌሶን 4:15, 16 በጉባኤ ውስጥ አንድነት እንዲሰፍን የማድረግን አስፈላጊነት የሚያጎላው እንዴት ነው? (ለ) አንድ ወንድም የነበረበትን ድክመት ያሸነፈው እንዴት ነው? ይህስ ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የረዳው እንዴት ነው?

12 አንድ የጎለመሰ የይሖዋ አገልጋይ በጉባኤው ውስጥ አንድነት እንዲሰፍን ይጥራል። (ኤፌሶን 4:1-6, 15, 16ን አንብብ።) የአምላክ ሕዝቦች “እርስ በርስ ተስማምተው” እንዲኖሩና ሁሉም እርስ በርስ እንዲደጋገፉ እንፈልጋለን። የይሖዋ ቃል በሚለው መሠረት ይህ አንድነት እንዲኖር ከተፈለገ ትሕትናን ማዳበር ያስፈልገናል። አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን በሌሎች አለፍጽምና ቢጎዳም እንኳ የጉባኤው አንድነት እንዳይናጋ በትሕትና ጥረት ማድረጉን ይቀጥላል። በጉባኤ ውስጥ የሚገኝ አንድ ክርስቲያን ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲያደርግ ብታይ ምን ይሰማሃል? ወይም አንድ የጉባኤህ አባል በግለሰብ ደረጃ አንተን ቢበድልህ ምን ታደርጋለህ? ካስቀየመህ ሰው ጋር ላለመገናኘት ምሳሌያዊ ግንብ መገንባት ይቀናሃል? ወይስ በሁለታችሁ መካከል የተፈጠረው ክፍተት እንዳያራርቃችሁ ድልድይ ለመገንባት ትሞክራለህ? አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ግንብ ሳይሆን ድልድይ ለመገንባት ጥረት ያደርጋል።

13 የኡቨን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። በእምነት ባልንጀሮቹ አለፍጽምና ብዙ ጊዜ ይበሳጭ ነበር። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስንና ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ተጠቅሞ ስለ ዳዊት ሕይወት ለማጥናት ወሰነ። ዳዊትን የመረጠው ለምንድን ነው? ኡቨ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ዳዊት እንደ እሱ ይሖዋን የሚያመልኩ አንዳንድ ሰዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ባሕርይ ሲያንጸባርቁ ተመልክቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ንጉሥ ሳኦል ሊገድለው ሞክሮ የነበረ ሲሆን በድንጋይ ሊወግሩት የፈለጉ ሰዎችም ነበሩ፤ ሌላው ቀርቶ የገዛ ሚስቱ አሹፋበታለች። (1 ሳሙ. 19:9-11፤ 30:1-6፤ 2 ሳሙ. 6:14-22) ይሁን እንጂ ዳዊት ሌሎች የፈጸሙበት በደል ለይሖዋ ያለውን ፍቅር እንዲያዳፍንበት ፈጽሞ አልፈቀደም። ከዚህም በተጨማሪ ዳዊት ይቅር ባይ ነበር፤ ይህ ደግሞ እኔ ላዳብረው የሚገባ ባሕርይ ነው። በጥናቴ ያገኘሁት ይህ እውቀት ለእምነት ባልንጀሮቼ አለፍጽምና ያለኝ አመለካከት እንዲለወጥ አድርጓል። የበደል መዝገብ መያዝ ትቻለሁ። ከዚህ ይልቅ ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ ለማበርከት ጥረት አደርጋለሁ።” አንተስ ለጉባኤው አንድነት የበኩልህን ድርሻ ለማበርከት ጥረት ታደርጋለህ?

የአምላክን ፈቃድ የሚፈጽሙ ሰዎችን ጓደኞች ማድረግ

14. ኢየሱስ ወዳጆቹ እንዲሆኑ የመረጠው ምን ዓይነት ሰዎችን ነው?

14 ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉም ዓይነት ሰዎች ይቀርቡት ነበር። የተለያዩ ሰዎች ይኸውም ወንዶች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ በዕድሜ የገፉ ሌላው ቀርቶ ልጆች ከእሱ ጋር መሆን ያስደስታቸው ነበር። ሆኖም ኢየሱስ የቅርብ ወዳጆቹን በመምረጥ ረገድ ጠንቃቃ ነበር። ታማኝ ሐዋርያቱን “የማዛችሁን ነገር የምትፈጽሙ ከሆነ ወዳጆቼ ናችሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 15:14) ኢየሱስ እነዚህን ወዳጆቹን የመረጠው እሱን በታማኝነት ከተከተሉትና ይሖዋን በሙሉ ልባቸው ካገለገሉት ሰዎች መካከል ነው። አንተስ የቅርብ ጓደኞችህ እንዲሆኑ የምትመርጠው ራሳቸውን ሳይቆጥቡ ይሖዋን ከሚያገለግሉ ሰዎች መካከል ነው? እንዲህ ማድረግህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

15. ወጣቶች ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር መቀራረባቸው የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?

15 የተለያዩ ፍራፍሬዎች የፀሐይ ሙቀት ሲያገኙ በጥሩ ሁኔታ ይበስላሉ። በተመሳሳይም በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን መካከል ያለው ሞቅ ያለ መንፈስ ወደ ጉልምስና እንድታድግ ሊረዳህ ይችላል። በሕይወትህ ምን ማድረግ እንዳለብህ ለመወሰን እያሰብክ ያለህ ወጣት ልትሆን ትችላለህ። ይሖዋን በማገልገል የብዙ ዓመት ተሞክሮ ካላቸውና ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱ የእምነት ባልንጀሮችህ ጋር መቀራረብህ ምንኛ ጥበብ ነው! እነዚህ ክርስቲያኖች ባሳለፏቸው ዓመታት በሕይወታቸው ውስጥ የተለያዩ ውጣ ውረዶች አጋጥመዋቸው ወይም አምላክን ሲያገለግሉ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተጋፍጠው ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉ ክርስቲያኖች ከሁሉ የተሻለውን የሕይወት ጎዳና እንድትመርጥ ሊረዱህ ይችላሉ። እንዲህ ካሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር ሞቅ ያለና የሚያንጽ ወዳጅነት መመሥረትህ አንተም ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች እንድታደርግ የሚረዳህ ከመሆኑም ሌላ ወደ ጉልምስና እንድታድግ ያስችልሃል።—ዕብራውያን 5:14ን አንብብ።

16. በዕድሜ የጎለመሱ ክርስቲያኖች አንዲትን ወጣት እህት የረዷት እንዴት ነው?

16 ለምሳሌ ያህል፣ ሄልጋ ትምህርቷን በምታጠናቅቅበት የመጨረሻ ዓመት ላይ የክፍሏ ተማሪዎች ስለ ግቦቻቸው ያወሩ እንደነበር ታስታውሳለች። ብዙዎቹ ወደፊት የተሻለ ሥራ ለማግኘት ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የመማር ግብ ነበራቸው። ሄልጋ ይህን ጉዳይ በተመለከተ በጉባኤዋ ካሉ ጓደኞቿ ጋር ተነጋገረችበት። እንዲህ ብላለች፦ “አብዛኞቹ ከእኔ በዕድሜ ይበልጡ ነበር፤ በዚህ ረገድ በጣም ረድተውኛል። የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድጀምር አበረታቱኝ። ከዚያ በኋላ ለአምስት ዓመታት ያህል በአቅኚነት ማገልገል ችያለሁ። ዓመታት ካለፉ በኋላ መለስ ብዬ ሳስብ አብዛኛውን የወጣትነት ዕድሜዬን በይሖዋ አገልግሎት በማሳለፌ ደስተኛ ነኝ። እንዲህ በማድረጌ ፈጽሞ አልቆጭም።”

17, 18. መንፈሳዊ ጉልምስና ግባችን ላይ ለመድረስ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

17 ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ ለመከተል ጥረት ማድረጋችን ለክርስቲያናዊ እድገታችን አስተዋጽኦ ያበረክታል። ይበልጥ ወደ ይሖዋ እየቀረብን የምንሄድ ከመሆኑም ሌላ አቅማችን በሚፈቅደው ሁሉ እሱን ለማገልገል ያለን ፍላጎት ይጨምራል። አንድ የአምላክ አገልጋይ ለይሖዋ ምርጡን መስጠት የሚችለው የተሟላ መንፈሳዊ እድገት በማድረግ የጎለመሰ ክርስቲያን ሲሆን ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹን “ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” በማለት አበረታቷቸዋል።—ማቴ. 5:16

18 ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን በጉባኤ ውስጥ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። አንድ ክርስቲያን ከአምላክ ያገኘውን ሕሊናውን የሚጠቀምበትም መንገድ መንፈሳዊ ጉልምስናውን ያሳያል። ሕሊናችን ጥበብ የተሞላባቸው ውሳኔዎች እንድናደርግ የሚረዳን እንዴት ነው? የእምነት ባልንጀሮቻችን በሕሊናቸው ተመርተው የሚያደርጓቸውን ውሳኔዎች ማክበር የምንችለውስ እንዴት ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እነዚህን ነጥቦች እንመለከታለን።

^ አን.6 ለምሳሌ ያህል፣ በዕድሜ የገፉና ተሞክሮ ያላቸው ወንድሞች አንዳንድ ኃላፊነቶቻቸውን ለሌሎች እንዲያስረክቡና እነዚህን ኃላፊነቶች ለተረከቡት ወጣት ወንድሞች ድጋፍ እንዲሰጡ ሊጠየቁ ይችላሉ።