በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በእምነት ጸንታችሁ ቁሙ”

“በእምነት ጸንታችሁ ቁሙ”

“በእምነት ጸንታችሁ ቁሙ፤ . . . ብርቱዎች ሁኑ።” —1 ቆሮ. 16:13

መዝሙሮች፦ 60, 64

1. (ሀ) ጴጥሮስ በገሊላ ባሕር ላይ ማዕበል በተነሳበት ወቅት ምን አጋጠመው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ጴጥሮስ መስመጥ የጀመረው ለምንድን ነው?

አንድ ቀን ሌሊት ሐዋርያው ጴጥሮስና አንዳንድ ደቀ መዛሙርት በገሊላ ባሕር ላይ በጀልባ እየተጓዙ ሳለ ማዕበል ተነሳ፤ በዚህ ጊዜ እየቀዘፉ ባሕሩን ለማቋረጥ እየታገሉ ነበር። ድንገት፣ ኢየሱስ በባሕሩ ላይ ሲራመድ አዩት። ጴጥሮስ ኢየሱስን ጠርቶ በውኃው ላይ እየተራመደ ወደ እሱ መምጣት ይችል እንደሆነ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲመጣ ሲነግረው ጴጥሮስ ከጀልባዋ ላይ ወርዶ በሚናወጠው ውኃ ላይ በተአምር እየተራመደ ወደ ኢየሱስ ሄደ። ብዙም ሳይቆይ ግን ጴጥሮስ መስመጥ ጀመረ። ለምን? ምክንያቱም ማዕበሉን ሲያይ ፈራ። ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ እንዲረዳው ጮኸ፤ እሱም ወዲያውኑ እጁን ዘርግቶ ያዘውና “አንተ እምነት የጎደለህ! ለምን ተጠራጠርክ?” አለው።—ማቴ. 14:24-32

2. በዚህ ጥናት ላይ የትኞቹን ነጥቦች እንመለከታለን?

2 እስቲ ጴጥሮስ ካጋጠመው ሁኔታ በመነሳት ከእምነት ጋር የተያያዙ ሦስት ነጥቦችን እንመልከት፦ (1) ጴጥሮስ መጀመሪያ ላይ አምላክ እንደሚረዳው እምነት ያሳየው እንዴት ነው? (2) ጴጥሮስ እምነቱ የጠፋው ለምንድን ነው? እንዲሁም (3) ጴጥሮስ እምነቱን መልሶ እንዲያጠናክር የረዳው ምንድን ነው? እነዚህን ነጥቦች መመርመራችን ‘በእምነት ጸንተን መቆም’ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል።—1 ቆሮ. 16:13

አምላክ እንደሚረዳን እምነት ማሳደር

3. ጴጥሮስ ከጀልባው እንዲወርድ ያስቻለው ምንድን ነው? እኛስ ከዚህ ጋር ሊመሳሰል የሚችል ምን ነገር አድርገናል?

3 ጴጥሮስ ከጀልባዋ ወርዶ በውኃው ላይ እንዲራመድ ያስቻለው እምነት ነው። ኢየሱስ ጴጥሮስን ሲጠራው ጴጥሮስ የአምላክ ኃይል ኢየሱስን እንደረዳው ሁሉ እሱንም ሊረዳው እንደሚችል ተማምኖ ነበር። እኛም በተመሳሳይ ራሳችንን ለይሖዋ እንድንወስንና እንድንጠመቅ ያስቻለን እምነታችን ነው። ኢየሱስ የእሱ ተከታዮች እንድንሆን ይኸውም ፈለጉን እንድንከተል ጠርቶናል። ኢየሱስም ሆነ አምላክ በተለያዩ መንገዶች እንደሚረዱን በመተማመን በእነሱ ላይ እምነት እንዳለን ማሳየት ይኖርብናል።—ዮሐ. 14:1፤ 1 ጴጥሮስ 2:21ን አንብብ።

4, 5. እምነት ውድ ሀብት ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

4 በእርግጥም እምነት ውድ ሀብት ነው። ጴጥሮስ የነበረው እምነት በውኃ ላይ እንዲራመድ እንዳስቻለው ሁሉ እኛም ያለን እምነት በሰብዓዊ ዓይን ሲታይ የማይቻል የሚመስሉ ነገሮችን እንድናደርግ ያስችለናል። (ማቴ. 21:21, 22) ለምሳሌ ያህል፣ አብዛኞቻችን የቀድሞ ማንነታችንን ያውቁ የነበሩ ሰዎች ሊለዩን እስከማይችሉ ድረስ አስተሳሰባችንና ድርጊታችን በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል። ይሖዋ በእሱ በመታመን እነዚህን እርምጃዎች በመውሰዳችን ጥረታችንን ባርኮልናል። (ቆላስይስ 3:5-10ን አንብብ።) በእምነት ተነሳስተን ራሳችንን ለይሖዋ ከወሰንን በኋላ ከእሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረት ችለናል፤ ይህ ደግሞ በራሳችን ኃይል ልናደርገው የምንችለው ነገር አይደለም።—ኤፌ. 2:8

5 እምነታችን ምንጊዜም ጠንካሮች እንድንሆን ያደርገናል። ከሰው በላይ ኃይል ያለው ጠላታችን ዲያብሎስ የሚሰነዝርብንን ጥቃት መቋቋም የቻልነው በእምነት ነው። (ኤፌ. 6:16) በተጨማሪም በይሖዋ መታመናችን ፈታኝ በሆኑ ወቅቶች ከልክ በላይ በጭንቀት እንዳንዋጥ ይረዳናል። ይሖዋ በእምነት ተነሳስተን ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የምናስቀድም ከሆነ ቁሳዊ ፍላጎታችንን እንደሚያሟላልን ቃል ገብቷል። (ማቴ. 6:30-34) ከዚህ በላይ ደግሞ እምነታችን፣ የትኛውም ሰው በራሱ ጥረት ሊያገኝ የማይችለውን ስጦታ ይኸውም የዘላለም ሕይወት ያስገኝልናል።—ዮሐ. 3:16

ትኩረት ማጣት፣ እምነት ማጣት ያስከትላል

6, 7. (ሀ) በጴጥሮስ ዙሪያ የነበረውን ነፋስና ማዕበል ከምን ጋር ልናመሳስለው እንችላለን? (ለ) እምነታችንን ሊያዳክም የሚችልን የትኛውንም ሁኔታ አቅልለን ማየት የሌለብን ለምንድን ነው?

6 ጴጥሮስ በውኃው ላይ ሲራመድ በዙሪያው የነበረው ነፋስና ማዕበል ክርስቲያኖች ከሚያጋጥሟቸው ፈተናዎችና መከራዎች ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ፈተናውና መከራው እጅግ ከባድ ቢሆንም እንኳ በይሖዋ እርዳታ ጸንተን መቆም እንችላለን። ጴጥሮስ መስመጥ የጀመረው ከኃይለኛ ነፋሱ ወይም ሞገዱ የተነሳ አለመሆኑን አስታውስ። የተከሰተውን ሁኔታ በቅደም ተከተል ለማሰብ ሞክር፤ ጴጥሮስ “አውሎ ነፋሱን ሲያይ ፈራ።” (ማቴ. 14:30) ጴጥሮስ ትኩረቱን በኢየሱስ ላይ ማድረግ ባቃተው ጊዜ እምነቱ ተናወጠ። እኛም ‘አውሎ ነፋሱን ማየት’ ከጀመርን በሌላ አባባል በማዕበሉ ኃይለኝነት ላይ ካተኮርንና ይሖዋ እንደሚደግፈን ከተጠራጠርን መስመጥ ልንጀምር እንችላለን።

7 መጽሐፍ ቅዱስ የእምነት መዳከምን ወይም እምነት ማጣትን ‘በቀላሉ ተብትቦ የሚይዘን ኃጢአት’ ብሎ ይጠራዋል፤ ይህም እምነታችንን ሊያዳክም የሚችልን የትኛውንም ሁኔታ አቅልለን ማየት እንደሌለብን ያስገነዝበናል። (ዕብ. 12:1) ጴጥሮስ ከደረሰበት ሁኔታ ማየት እንደሚቻለው ትኩረታችን በተሳሳተ ነገር ላይ ካረፈ እምነታችን በቀላሉ ሊዳከም ይችላል። እንዲህ ዓይነት አደጋ እንደተደቀነብን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ራሳችንን ለመመርመር የሚረዱንን አንዳንድ ጥያቄዎች እንመልከት።

8. አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች ሊደበዝዙብን የሚችሉት እንዴት ነው?

8 አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች እንደቀድሞው ፍንትው ብለው ይታዩኛል? ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ አሁን ያለውን ሥርዓት ለማጥፋት ቃል ገብቷል። ሆኖም ዓለም በሚያቀርባቸው የተለያዩ ዓይነት መዝናኛዎች ትኩረታችን በመከፋፈሉ አምላክ በገባቸው ተስፋዎች ላይ ያለን እምነት ተዳክሟል? ከሆነ መጨረሻው በእርግጥ እንደቀረበ መጠራጠር ልንጀምር እንችላለን። (ዕን. 2:3) ሌላም ምሳሌ እንመልከት። አምላክ በቤዛው አማካኝነት ይቅር እንደሚለን ቃል ገብቶልናል። ይሁንና ከዚህ በፊት በሠራናቸው ጥፋቶች ከልክ በላይ በበደለኝነት ስሜት የምንዋጥ ከሆነ ይሖዋ በእርግጥ ኃጢአታችንን በሙሉ ‘ደምስሶልናል’ የሚለውን ሐሳብ መቀበል ሊከብደን ይችላል። (ሥራ 3:19) ከዚህም የተነሳ አምላክን በማገልገል የምናገኘውን ደስታ ልናጣና አገልግሎት ልናቆም እንችላለን።

9. ትኩረታችን የራሳችንን ጥቅም በማሳደድ ላይ ያረፈ ከሆነ ምን ሊከሰት ይችላል?

9 በአምላክ አገልግሎት እንደ በፊቱ በትጋት እሳተፋለሁ? ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋን በትጋት የምናገለግል ከሆነ “ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ የሆነውን ተስፋ እስከ መጨረሻው መያዝ” እንደምንችል ገልጿል። ይሁንና ይበልጥ ትኩረታችን ያረፈው የራሳችንን ጥቅም በማሳደድ ላይ ቢሆንስ? ለምሳሌ፣ አምልኳችንን የሚያስተጓጉልብን ቢሆንም እንኳ ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኝልን ሥራ ልንይዝ እንችላለን። ይህ ደግሞ እምነታችን እንዲዳከምና አቅማችን የሚፈቅደውን ያህል ይሖዋን ከማገልገል በመቆጠብ “ዳተኞች” እንድንሆን ሊያደርገን ይችላል።—ዕብ. 6:10-12

10. ሌሎችን ይቅር ስንል በይሖዋ ላይ እምነት እንዳለን የምናሳየው እንዴት ነው?

10 ሰዎች ሲያስቀይሙኝ ይቅር ማለት ይከብደኛል? ሌሎች ሲያስቀይሙን ወይም ሲጎዱን ስሜታዊ በመሆን ልክ ልካቸውን ለመንገር ወይም እነሱን ጭራሽ ላለማነጋገር ልንፈተን እንችላለን። በአንጻሩ ግን ይቅር የምንል ከሆነ በይሖዋ ላይ እምነት እንዳለን እናሳያለን። እንዴት? እኛ በኃጢአታችን የተነሳ በአምላክ ፊት ባለዕዳ እንደሆንን ሁሉ በእኛ ላይ በደል የፈጸሙ ሰዎችም በእኛ ፊት ባለዕዳ ይሆናሉ። (ሉቃስ 11:4) ሌሎችን ይቅር ካልን የአምላክን ሞገስ እናገኛለን፤ ይህ ደግሞ ዕዳቸውን ከማስከፈል የተሻለ እንደሆነ አምኖ መቀበልን ይጠይቃል። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሌሎችን ይቅር ማለት እምነት እንደሚጠይቅ ተገንዝበዋል። ኢየሱስ ደጋግመው የበደሏቸውን ሰዎች እንኳ ሳይቀር ይቅር ማለት እንዳለባቸው ሲነግራቸው “እምነት ጨምርልን” ብለው ለምነውታል።—ሉቃስ 17:1-5

11. ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ሲሰጠን ጥቅም ሳናገኝ ልንቀር የምንችለው እንዴት ነው?

11 ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ሲሰጠኝ እበሳጫለሁ? እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ከምክሩ ጥቅም የምናገኝበትን መንገድ ከመፈለግ ይልቅ ምክሩ ወይም ምክር ሰጪው ባለው እንከን ላይ ትኩረት ልናደርግ እንችላለን። (ምሳሌ 19:20) ይህ ደግሞ አስተሳሰባችን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር እንዲስማማ ማድረግ የምንችልበት አጋጣሚ እንዲያመልጠን ሊያደርግ ይችላል።

12. አንድ ክርስቲያን ይሖዋ ሕዝቡን እንዲመሩ በሾማቸው ላይ ሁልጊዜ የሚያጉረመርም ከሆነ ይህ ምን ያሳያል?

12 በጉባኤ ውስጥ በተሾሙ ወንድሞች ላይ አጉረመርማለሁ? እስራኤላውያን እምነት የሚጎድላቸው አሥሩ ሰላዮች ባመጡት መጥፎ ወሬ ላይ ባተኮሩ ጊዜ በሙሴና በአሮን ላይ ማጉረምረም ጀመሩ። ከዚያም ይሖዋ ሙሴን “ይህ ሕዝብ የሚንቀኝ እስከ መቼ ነው?” በማለት ጠይቆታል። (ዘኁ. 14:2-4, 11) አዎ፣ እስራኤላውያን ማጉረምረማቸው ሙሴንና አሮንን በሾመው አምላክ ላይ እምነት እንደሌላቸው ያሳያል። እኛም አምላክ ሕዝቡን እንዲመሩ በሚጠቀምባቸው ግለሰቦች ላይ ሁልጊዜ የምናጉረመርም ከሆነ ይህ በአምላክ ላይ ያለን እምነት መዳከሙን አያሳይም?

13. እምነታችን እንደተዳከመ የሚጠቁም ነገር ካስተዋልን ተስፋ መቁረጥ የማይኖርብን ለምንድን ነው?

13 ያም ሆነ ይህ፣ ራስህን ስትመረምር እምነትህ እንደተዳከመ የሚጠቁም ነገር ብታገኝ ተስፋ አትቁረጥ። ሐዋርያ የነበረው ጴጥሮስ እንኳ በፍርሃትና በጥርጣሬ የተሸነፈበት ጊዜ ነበር። እንዲያውም ኢየሱስ በአንድ ወቅት ሁሉንም ሐዋርያት ‘እምነት የጎደላቸው’ በመሆናቸው ገሥጿቸዋል። (ማቴ. 16:8) ጴጥሮስ ካጋጠመው ነገር ትልቅ ትምህርት የምናገኘው እምነቱ ከተዳከመና ባሕር ውስጥ መስመጥ ከጀመረ በኋላ ካደረገው ነገር መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም።

እምነታችሁን ለማጠናከር በኢየሱስ ላይ ትኩረት አድርጉ

14, 15. (ሀ) ጴጥሮስ መስመጥ በጀመረ ጊዜ ምን አደረገ? (ለ) ኢየሱስን በዓይናችን ማየት እንደማንችል የታወቀ ነው፤ ታዲያ እሱን ‘በትኩረት መመልከት’ የምንችለው እንዴት ነው?

14 ጴጥሮስ ማዕበሉን አይቶ መስመጥ በጀመረበት ጊዜ እንደ ምንም ተፍጨርጭሮ ወደ ጀልባዋ ለመመለስ ጥረት ማድረግ ይችል ነበር። ጎበዝ ዋናተኛ እንደመሆኑ መጠን ይህን በደመ ነፍስ ሊያደርገው ይችል ነበር። (ዮሐ. 21:7) ይሁንና በራሱ ከመመካት ይልቅ ትኩረቱን መልሶ በኢየሱስ ላይ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ ኢየሱስ የሰጠውን እርዳታ ተቀብሏል። እኛም እምነታችን እየተዳከመ እንደሆነ ከተሰማን የጴጥሮስን ምሳሌ መኮረጅ ይኖርብናል። ይሁንና እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

15 ጴጥሮስ ትኩረቱን እንደገና በኢየሱስ ላይ እንዳደረገ ሁሉ እኛም “የእምነታችን ‘ዋና ወኪል’ እና ‘ፍጹም አድራጊ’ የሆነውን ኢየሱስን በትኩረት” መመልከት ይኖርብናል። (ዕብራውያን 12:2, 3ን አንብብ።) እርግጥ እንደ ጴጥሮስ ኢየሱስን በዓይናችን ማየት አንችልም። ሆኖም ኢየሱስ ያስተማረውን እንዲሁም ያደረገውን ነገር በመመርመርና በጥብቅ በመከተል እሱን ‘በትኩረት መመልከት’ እንችላለን። ኢየሱስ በተወው አርዓያ ላይ ተመሥርተን መውሰድ የምንችላቸውን አንዳንድ እርምጃዎች እንመልከት። እነዚህን ነገሮች ተግባራዊ ካደረግን እምነታችንን እንድናጠናክር የሚያስችለንን እርዳታ እናገኛለን።

ኢየሱስ በተወው ምሳሌ ላይ ትኩረት በማድረግና ፈለጉን በጥብቅ በመከተል በእምነት ጸንተን መቆም እንችላለን (አንቀጽ 15ን ተመልከት)

16. እምነታችን እንዲገነባ በሚያደርግ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የምንችለው እንዴት ነው?

16 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላችሁን እምነት አጠናክሩ። ኢየሱስ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ የተሻለ የሕይወት መመሪያ እንደሆነ በእርግጠኝነት ያምን ነበር። (ዮሐ. 17:17) የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ማንበብ፣ ማጥናትና ባወቅነው ነገር ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስን በጥቅሉ ከማጥናት በተጨማሪ ጥያቄዎች በሚፈጥሩብህ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምርምር አድርግ። ለምሳሌ ያህል፣ የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀኖች ውስጥ መሆኑን የሚያሳየውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ በዝርዝር በማጥናት የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ በእርግጥ እንደቀረበ ያለህን እምነት ማጠናከር ትችላለህ። ከዚህ በፊት ፍጻሜያቸውን ያገኙ በርካታ ትንቢቶችን በማጥናት ገና ፍጻሜያቸውን ባላገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ላይ ያለህን እምነት አጠናክር። መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት እንደሚለውጥ የሚያሳዩ ተሞክሮዎችን በማንበብ የአምላክ ቃል የያዘው ምክር ጠቃሚ መሆኑን በተመለከተ ያለህን እምነት ገንባ። *1 ተሰ. 2:13

17. ኢየሱስ ከባድ ፈተናዎች ቢደርሱበትም በታማኝነት መጽናት የቻለው ለምንድን ነው? አንተስ የእሱን አርዓያ መከተል የምትችለው እንዴት ነው?

17 ይሖዋ ቃል በገባልን በረከቶች ላይ ትኩረት አድርግ። ኢየሱስ ዓይኑ ‘ከፊቱ በሚጠብቀው ደስታ’ ላይ እንዲያተኩር በማድረጉ ከባድ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም በታማኝነት መጽናት ችሏል። (ዕብ. 12:2) ዓለም በሚያቀርባቸው ነገሮች ትኩረቱ አልተከፋፈለም። (ማቴ. 4:8-10) ይሖዋ በገባልህ ግሩም ተስፋዎች ላይ በማሰላሰል የኢየሱስን አርዓያ መከተል ትችላለህ። አምላክ ይህን ክፉ ሥርዓት ካስወገደ በኋላ ማድረግ የምትፈልጋቸውን ነገሮች በጽሑፍ በማስፈር ወይም በሥዕል በመግለጽ ራስህን በቦታው ላይ ለማስቀመጥ ሞክር። ከሞት ሲነሱ ማግኘት የምትፈልጋቸውን ሰዎች ስም ዝርዝርና ስለ ምን ጉዳይ ልታነጋግራቸው እንደምትፈልግ ጻፍ። አምላክ የሰጣቸው እነዚህ ተስፋዎች በጥቅሉ ለሰው ልጆች ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ለአንተ እንደተሰጡ አድርገህ አስብ።

18. ጸሎት እምነትህን እንድታጠናክር ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

18 ይሖዋ እምነት እንዲጨምርልህ ጸልይ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ይሖዋ መንፈስ ቅዱስ ይሰጣቸው ዘንድ እንዲለምኑት አስተምሯቸው ነበር። (ሉቃስ 11:9, 13) መንፈስ ቅዱስ ለማግኘት ስትጠይቅ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ አንዱ ገጽታ የሆነው እምነት እንዲጨመርልህም ጸልይ። ወደ አምላክ ስትጸልይ ያለብህን ድክመት ለይተህ ጥቀስ፤ ለምሳሌ ሌሎችን ይቅር ማለት የሚከብድህ ከሆነ እምነትህ እንደተዳከመ የሚጠቁም ምልክት ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ አምላክ ይህን ድክመትህን ማሸነፍ እንድትችል እንዲረዳህ መጠየቅ ትችላለህ።

19. ጓደኛችን እንዲሆን የምንመርጠው ሰው ምን ዓይነት ባሕርያት ሊኖሩት ይገባል?

19 ጠንካራ እምነት ያላቸውን ሰዎች ወዳጅ አድርግ። ኢየሱስ ወዳጆቹን በተለይ የቅርብ ጓደኞቹ እንዲሆኑ የሚፈልጋቸውን ሰዎች በጥንቃቄ ይመርጥ ነበር። የቅርብ ወዳጆቹ የሆኑት ሐዋርያት ያዘዛቸውን ነገር በመፈጸም እምነታቸውንና ታማኝነታቸውን አስመሥክረዋል። (ዮሐንስ 15:14, 15ን አንብብ።) በመሆኑም ጓደኞችህን ስትመርጥ ኢየሱስን በመታዘዝ ጠንካራ እምነት እንዳላቸው ያሳዩ ሰዎችን ለማግኘት ጥረት አድርግ። የጥሩ ወዳጅነት አንዱ ምልክት ደግሞ ምክር መስጠት ወይም መቀበል አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜም እንኳ በግልጽ መነጋገር ነው።—ምሳሌ 27:9

20. ሌሎች እምነታቸውን እንዲገነቡ ስንረዳ ምን ጥቅም እናገኛለን?

20 እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ ሌሎችን እርዱ። ኢየሱስ በቃልም ሆነ በተግባር የደቀ መዛሙርቱን እምነት ገንብቷል። (ማር. 11:20-24) እኛም የእሱን ምሳሌ መከተል ይኖርብናል፤ ምክንያቱም ሌሎች እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ ስንረዳ የእኛም እምነት ይጠናከራል። (ምሳሌ 11:25) በምትሰብኩበትና በምታስተምሩበት ጊዜ አምላክ መኖሩን፣ ለእኛ የሚያስብ መሆኑን እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ቃሉ መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ጎላ አድርጋችሁ ጥቀሱ። በተጨማሪም ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ እርዷቸው። የጥርጣሬ መንፈስ ቢታይባቸው፣ ምናልባትም በተሾሙ ወንድሞች ላይ ማጉረምረም ቢጀምሩ ከእነሱ ለመራቅ አትቸኩሉ። ከዚህ ይልቅ እምነታቸውን መልሰው እንዲያጠናክሩ የሚያስችሏቸውን እርምጃዎች እንዲወስዱ በዘዴ እርዷቸው። (ይሁዳ 22, 23) ተማሪ ከሆንክ ስለ ዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ትምህርት በሚሰጥበት ጊዜ ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ስለመሆኑ ያለህን እምነት በድፍረት ተናገር፤ ይህም ሌሎች ጥሩ ምላሽ እንዲሰጡ ሊያደርግ ይችላል።

21. ይሖዋ እምነታችንን በተመለከተ ለእያንዳንዳችን ምን ቃል ገብቷል?

21 ጴጥሮስ፣ አምላክ በኢየሱስ አማካኝነት በሰጠው እርዳታ ተጠቅሞ ፍርሃቱንና ጥርጣሬውን በማሸነፍ በቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ዘንድ የእምነት ዓምድ ለመሆን በቅቷል። በተመሳሳይም ይሖዋ በእምነት ጸንተን እንድንቆም ሁላችንንም ይረዳናል። (1 ጴጥሮስ 5:9, 10ን አንብብ።) እምነታችንን ለመገንባት የምናደርገው ጥረት የሚያስቆጭ አይደለም፤ ምክንያቱም እምነት የሚያስገኘው ወሮታ የሚተካከለው ነገር የለም።

^ አን.16 ለምሳሌ ያህል፣ ለሕዝብ በሚሰራጨው የመጠበቂያ ግንብ እትም ላይ “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” በሚለው ዓምድ ሥር የወጡትን ተሞክሮዎች አንብብ።