በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጃችሁ ይሖዋን እንዲያገለግል አሠልጥኑት—ክፍል 1

ልጃችሁ ይሖዋን እንዲያገለግል አሠልጥኑት—ክፍል 1

“የእውነተኛው አምላክ ሰው . . . የሚወለደውን ልጅ በተመለከተ ምን ማድረግ እንዳለብን መመሪያ ይስጠን።”—መሳ. 13:8

መዝሙሮች፦ 88, 120

1. ማኑሄ አባት ሊሆን እንደሆነ ሲነገረው ምን አደረገ?

ሰውየው፣ ሚስቱ የነገረችው ዜና በጣም አስደንቆታል። ሚስቱ መሃን እንደሆነች ይታሰብ ነበር። ይሁንና የይሖዋ መልአክ ለሴትየዋ የተገለጠላት ሲሆን ፈጽሞ የማይመስል የነበረው ነገር እውን እንደሚሆን ነገራት፤ ማኑሄና ሚስቱ ወንድ ልጅ ሊወልዱ ነው! ማኑሄ በጣም እንደተደሰተ ጥያቄ የለውም፤ ሆኖም በጫንቃው ላይ የወደቀው ኃላፊነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ተገንዝቧል። በክፋት በተሞላው ብሔር ውስጥ እሱና ባለቤቱ ልጃቸውን ሲያሳድጉ የይሖዋ አምላኪ እንዲሆን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው? ማኑሄ “እባክህ ልከኸው የነበረው ያ የእውነተኛው አምላክ ሰው [መልአኩ] እንደገና ወደ እኛ ይምጣና የሚወለደውን ልጅ በተመለከተ ምን ማድረግ እንዳለብን መመሪያ ይስጠን” በማለት ይሖዋን ተማጸነ።—መሳ. 13:1-8

2. ልጃችሁን ማሠልጠን ምን ነገሮችን ይጨምራል? (“ የላቀ ቦታ የምትሰጧቸው ጥናቶቻችሁ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

2 ወላጅ ከሆናችሁ ማኑሄ እንዲህ ያለ ልመና ያቀረበው ለምን እንደሆነ መረዳት አይከብዳችሁም። እናንተም ልጃችሁ ይሖዋን እንዲያውቅና እንዲወድ የመርዳት ከባድ ኃላፊነት ተጥሎባችኋል። (ምሳሌ 1:8) ክርስቲያን ወላጆች ይህን ግብ ለመምታት፣ ትርጉም ያለው እንዲሁም ልጆቻቸው ይሖዋን ይበልጥ እያወቁትና እየወደዱት እንዲሄዱ የሚረዳ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም እንዲኖራቸው ሊያደርጉ ይገባል። እርግጥ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ እንዲቀረጽ በየሳምንቱ የቤተሰብ ጥናት ማድረግ ብቻ በቂ እንዳልሆነ መገንዘብ ይኖርባችኋል። (ዘዳግም 6:6-9ን አንብብ።) ታዲያ በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ እውነትን ለመቅረጽ ጥረት ስታደርጉ የሚያጋጥሟችሁን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት የምትችሉት እንዴት ነው? በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ወላጆች የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። ኢየሱስ፣ አባት ባይሆንም እንኳ ወላጆች እሱ ካስተማረበት መንገድ ትምህርት መቅሰም ይችላሉ፤ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ያስተማረውና ያሠለጠነው በፍቅር፣ በትሕትና እንዲሁም በማስተዋል ነበር። እስቲ እነዚህን ባሕርያት አንድ በአንድ እንመልከት።

ለልጃችሁ ፍቅር አሳዩ

3. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንደሚወዳቸው ያሳየው እንዴት ነው?

3 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንደሚወዳቸው ከመናገር ወደኋላ አላለም። (ዮሐንስ 15:9ን አንብብ።) ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በመቀራረብና ከእነሱ ጋር አዘውትሮ ጊዜ በማሳለፍም ፍቅሩን አሳይቷል። (ማር. 6:31, 32፤ ዮሐ. 2:2፤ 21:12, 13) ኢየሱስ ከእነሱ ጋር ያለው ግንኙነት ሥልጠና በመስጠት ላይ ብቻ ያተኮረ አልነበረም። በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ ከልቡ እንደሚወዳቸው ተጠራጥረው አያውቁም። ልጆቻችሁን በማሠልጠን ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምትችሉት እንዴት ነው?

4. ልጆቻችሁ እንደምትወዷቸው እንዲያውቁ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

4 ልጆቻችሁን እንደምትወዷቸው ንገሯቸው፤ እንዲሁም ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንደምትሰጧቸው አዘውትራችሁ ግለጹላቸው። (ምሳሌ 4:3፤ ቲቶ 2:4) በአውስትራሊያ የሚኖረው ሳሙኤል እንዲህ ብሏል፦ “ትንሽ ልጅ እያለሁ አባዬ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ ከተባለው መጽሐፍ ላይ ሁልጊዜ ማታ ማታ ያነብልኝ ነበር። ጥያቄዎቼን ይመልስልኛል፤ አስተኝቶኝ ከመሄዱ በፊት እቅፍ አድርጎ ይስመኛል። አባቴ፣ ልጆችን ማቀፍና መሳም ያን ያህል የተለመደ ባልሆነበት ቤተሰብ ውስጥ እንዳደገ ከጊዜ በኋላ ሳውቅ በጣም ተገረምኩ! እሱ ግን እንደሚወደኝ ለማሳየት ልባዊ ጥረት ያደርግ ነበር። ይህም አባቴን በጣም እንድቀርበው ብሎም ደስተኛ እንድሆንና እንዳልፈራ አድርጎኛል።” እናንተም አዘውትራችሁ ልጃችሁን “እወድሃለሁ” የምትሉት ከሆነ እንደ ሳሙኤል ሊሰማው ይችላል። ለልጆቻችሁ ፍቅራችሁን ግለጹላቸው። አዋሯቸው፣ አብራችሁ ተመገቡ እንዲሁም አጫውቷቸው።

5, 6. (ሀ) ኢየሱስ ለሚወዳቸው ሰዎች ምን ያደርጋል? (ለ) ተገቢ ተግሣጽ ልጆች እንደሚወደዱ እንዲሰማቸውና ተረጋግተው እንዲኖሩ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

5 ኢየሱስ “እኔ፣ የምወዳቸውን ሁሉ እወቅሳለሁ እንዲሁም እገሥጻለሁ” ብሏል። * (ራእይ 3:19) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይከራከሩ የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ ተስፋ አልቆረጠባቸውም። የሰጣቸውን ምክር እንዳልሠሩበት ሲያይም ሁኔታውን በቸልታ አላለፈውም። ኢየሱስ አመቺ ጊዜና ቦታ መርጦ በፍቅርና በደግነት እርማት ሰጥቷቸዋል።—ማር. 9:33-37

6 እናንተም ለልጆቻችሁ ተግሣጽ በመስጠት እንደምትወዷቸው አሳዩአቸው። አንዳንድ ጊዜ፣ አንድ ድርጊት ትክክል ወይም ስህተት የሆነበትን ምክንያት ማስረዳቱ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። በእርግጥ ልጆቻችሁ የነገራችኋቸውን ተግባራዊ ሳያደርጉ የሚቀሩበት ጊዜ ይኖራል። (ምሳሌ 22:15) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ። ተስማሚ ጊዜና ቦታ መርጣችሁ ልጆቻችሁን ገሥጿቸው፤ ይህን የምታደርጉት በፍቅር፣ በደግነት ብሎም በትዕግሥት መመሪያ፣ ሥልጠናና እርማት በመስጠት ነው። በደቡብ አፍሪካ የምትኖር ኢሌን የተባለች እህት “ወላጆቼ ከተግሣጽ ጋር በተያያዘ አቋማቸው አይለዋወጥም” ብላለች። አክላም እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “አንድ ጥፋት ቅጣት እንደሚያስከትል ነግረውኝ ያን ጥፋት ከሠራሁ ቅጣቱ አይቀርልኝም። ሆኖም በቁጣ ወይም ምክንያቱን ሳያስረዱኝ ተግሣጽ ሰጥተውኝ አያውቁም። ይህም ሳልፈራ ተረጋግቼ እንድኖር አድርጎኛል። ማለፍ የሌለብኝ ገደብ ምን እንደሆነ እንዲሁም ከእኔ ምን እንደሚጠበቅ አውቃለሁ።”

ትሑት መሆናችሁን አሳዩ

7, 8. (ሀ) ኢየሱስ ሲጸልይ ትሕትና ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) የምታቀርቡት ጸሎት ልጆቻችሁ በአምላክ መታመንን እንዲማሩ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

7 ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ መገባደጃ ላይ እንዲህ የሚል ጸሎት አቅርቦ ነበር፦ “አባ፣ አባት ሆይ፣ አንተ ሁሉን ነገር ማድረግ ትችላለህ፤ ይህን ጽዋ ከእኔ አርቅ። ሆኖም እኔ የምፈልገው ሳይሆን አንተ የምትፈልገው ይሁን።” * (ማር. 14:36) ደቀ መዛሙርቱ፣ ኢየሱስ ይህን ጸሎት ሲያቀርብ ሲሰሙ ወይም ከጊዜ በኋላ ስለዚህ ጸሎት ሲያውቁ ምን ተሰምቷቸው ሊሆን እንደሚችል አስቡ። ኢየሱስ እንዲህ ያለ ልመና ማቅረቡ፣ ፍጹም የሆነው የአምላክ ልጅ እንኳ በትሕትና መለኮታዊ እርዳታ ከጠየቀ ተከታዮቹም ይህን ሊያደርጉ እንደሚገባ ደቀ መዛሙርቱን አስተምሯቸው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

8 ልጆቻችሁ እናንተ ከምታቀርቡት ጸሎት ምን ይማራሉ? እርግጥ ነው፣ ወደ ይሖዋ የምትጸልዩበት ዋነኛ ምክንያት ልጆቻችሁን ማስተማር አይደለም። ይሁንና ከልጆቻችሁ ጋር ሆናችሁ በትሕትና ስትጸልዩ ልጆቻችሁ በይሖዋ መታመንን ይማራሉ። በብራዚል የምትኖረው አና እንዲህ ብላለች፦ “በቤተሰባችን ውስጥ ችግሮች በሚኖሩበት ጊዜ ለምሳሌ አያቶቼ በታመሙበት ወቅት ወላጆቼ ሁኔታውን ለመቋቋም የሚያስችላቸው ጥንካሬና ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳቸው ጥበብ እንዲሰጣቸው ወደ ይሖዋ ይጸልዩ ነበር። በጣም የሚያስጨንቅ ሁኔታ በሚያጋጥማቸው ጊዜም እንኳ ጉዳዩን ለይሖዋ ይተዉት ነበር። ይህም በይሖዋ መታመንን አስተምሮኛል።” ከልጆቻችሁ ጋር ስትጸልዩ ስለ እነሱ ብቻ አትጸልዩ። ይሖዋ እናንተንም እንዲረዳችሁ ጠይቁት፤ ለምሳሌ በትልቅ ስብሰባ ላይ መገኘት እንድትችሉ አሠሪያችሁ ፈቃድ እንዲሰጣችሁ ለማነጋገር ወይም ለጎረቤታችሁ ለመመሥከር ይሖዋ ድፍረት እንዲሰጣችሁ አሊያም በሌሎች ጉዳዮች እንዲረዳችሁ ጸልዩ። ትሑት በመሆን በአምላክ እንደምትታመኑ ካሳያችሁ ልጆቻችሁም ይህን ማድረግ ይማራሉ።

9. (ሀ) ኢየሱስ ሌሎችን በትሕትና እንዲያገለግሉ ደቀ መዛሙርቱን ያስተማራቸው እንዴት ነው? (ለ) ሌሎችን ለማገልገል ፈቃደኞች ከሆናችሁ ልጆቻችሁ ምን ይማራሉ?

9 ኢየሱስ፣ ሌሎችን በትሕትና እንዲያገለግሉ በቃልም ሆነ በድርጊት ደቀ መዛሙርቱን አሠልጥኗቸዋል። (ሉቃስ 22:27ን አንብብ።) ሐዋርያቱን፣ በይሖዋ አገልግሎትና ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ እንዲያሳዩ አስተምሯቸዋል። እናንተም በትሕትና የራሳችሁን ጥቅም መሥዋዕት የምታደርጉ ከሆነ ልጆቻችሁ እንዲሁ እንዲያደርጉ ማስተማር ትችላላችሁ። ሁለት ልጆች ያሏት ዴቢ እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ሽማግሌ እንደመሆኑ መጠን ለሌሎች ጊዜ በመስጠቱ ፈጽሞ ቀንቼ አላውቅም። ባለቤቴ፣ እኔም ሆንኩ ልጆቼ በምንፈልገው ጊዜ ሁሉ ትኩረት እንደሚሰጠን አውቃለሁ።” (1 ጢሞ. 3:4, 5) ባለቤቷ ፕራናስ በማከል እንዲህ ብሏል፦ “ከጊዜ በኋላ ልጆቻችን ከትላልቅ ስብሰባዎችና ከሌሎች ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በፈቃደኝነት ያከናውኑ ጀመር። ልጆቻችን ደስተኞች ናቸው፤ ጥሩ ጓደኞችም አፍርተዋል እንዲሁም ከወንድሞቻቸውና ከእህቶቻቸው ጋር መሆን ያስደስታቸዋል!” በአሁኑ ወቅት መላው ቤተሰብ፣ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈለ ነው። እናንተም ትሕትናንና የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስን ማሳየታችሁ ልጆቻችሁ ሌሎችን እንዴት ማገልገል እንደሚችሉ እንዲማሩ ይረዳቸዋል።

አስተዋይ ሁኑ

10. ኢየሱስ አንዳንድ ሰዎች በተከተሉት ወቅት የተናገረው ነገር አስተዋይ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

10 ኢየሱስ ከላይ ከሚታየው ነገር ባሻገር በመመልከትና ሰዎች አንድን ነገር የሚያደርጉበትን ምክንያት ለመረዳት በመሞከር አስተዋይ መሆኑን አሳይቷል። በአንድ ወቅት በገሊላ ሲያስተምር ካዳመጡት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እሱን ለመከተል ጉጉት ያላቸው ይመስል ነበር። (ዮሐ. 6:22-24) ኢየሱስ ግን ልብ ማንበብ ስለሚችል ሰዎቹ ይበልጥ ያጓጓቸው ምግብ ማግኘታቸው እንጂ ትምህርቱ እንዳልነበረ አስተዋለ። (ዮሐ. 2:25) ስህተታቸው ምን እንደሆነ በመገንዘብ በትዕግሥት እርማት ሰጣቸው፤ እንዲሁም ማሻሻያ ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ነገራቸው።—ዮሐንስ 6:25-27ን አንብብ።

ልጃችሁ፣ የስብከቱ ሥራ አስደሳችና የሚክስ እንደሆነ ይሰማዋል? (አንቀጽ 11ን ተመልከት)

11. (ሀ) አስተዋይ መሆን ልጆቻችሁ አገልግሎቱን እንደሚወዱት ለማወቅ እንዴት ሊረዳችሁ እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር። (ለ) ልጆቻችሁ አገልግሎት አስደሳችና የሚክስ እንዲሆንላቸው መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

11 የልጆቻችሁን ልብ ማንበብ ባትችሉም አስተዋዮች ከሆናችሁ ልጆቻችሁ ለአገልግሎት ምን አመለካከት እንዳላቸው መገንዘብ ትችላላችሁ። በርካታ ወላጆች በአገልግሎት መሃል ልጆቻቸው ትንሽ አረፍ እንዲሉ ሻይ ይጋብዟቸዋል። ሆኖም ‘ልጄን የሚያስደስተው አገልግሎት ነው ወይስ እረፍቱ?’ ብላችሁ ራሳችሁን በመጠየቅ ስሜታቸውን ለማስተዋል ጥረት አድርጉ። ልጆቻችሁ፣ አገልግሎት አስደሳችና የሚክስ እንዲሆንላቸው እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ካስተዋላችሁ ግብ እንዲያወጡ አግዟቸው። አብረዋችሁ ሲያገለግሉ በስብከቱ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለመርዳት ምን ማድረግ እንደምትችሉ አስቡ።

12. (ሀ) ኢየሱስ ከሥነ ምግባር ብልግና እንዲርቁ ለተከታዮቹ የሰጠው ማስጠንቀቂያ አስተዋይ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ወቅታዊ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

12 ኢየሱስ ወደ ኃጢአት ሊመሩ የሚችሉ የተሳሳቱ እርምጃዎችን ለይቶ በመጥቀስም አስተዋይ መሆኑን አሳይቷል። አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ተከታዮቹ የፆታ ብልግና ኃጢአት መሆኑን ያውቁ እንደነበር ግልጽ ነው። ያም ሆኖ ወደ ብልግና ሊመሩ ከሚችሉ ድርጊቶች እንዲርቁ እንዲህ በማለት አስጠንቅቋቸዋል፦ “አንዲትን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል። ስለዚህ ቀኝ ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው።” (ማቴ. 5:27-29) ይህ ምክር በሮም ግዛት ውስጥ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ወቅታዊ ነበር። አንድ የታሪክ ምሁር እንደጻፉት በሮማውያን ቲያትሮች ላይ ተመልካቾች “አስጸያፊ የሆኑ ነገሮችን ይመለከቱና ይሰሙ ነበር። አስነዋሪ የሆኑ ነገሮች የሚታይባቸው ትዕይንቶች ይበልጥ ተወዳጅ ነበሩ።” ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸውን ጠብቀው መኖር አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው ስለሚያደርጉ ነገሮች ማስጠንቀቂያ መስጠቱ አፍቃሪና አስተዋይ መሆኑን ያሳያል።

13, 14. ልጆቻችሁ ከመጥፎ መዝናኛ እንዲርቁ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

13 አስተዋይ መሆናችሁ ልጆቻችሁን ከመንፈሳዊ ጉዳት እንድትጠብቋቸው ይረዳችኋል። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ፣ ልጆች ገና በትንሽነታቸው ለብልግና ምስሎችና ጽሑፎች እንዲሁም ለሌሎች አስጸያፊ ነገሮች ሊጋለጡ ይችላሉ። ክርስቲያን ወላጆች ብልግና የሞላባቸው መዝናኛዎች መጥፎ እንደሆኑ ለልጆቻቸው እንደሚነግሯቸው የታወቀ ነው። አስተዋይ መሆናችሁ ግን የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች የልጆቻችሁን ትኩረት እንዴት ሊስቡት እንደሚችሉ ለመገንዘብም ይረዳችኋል። ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦ ‘ልጄ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ለማየት እንዲፈተን የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል? እነዚህ ነገሮች በጣም አደገኛ የሆኑበትን ምክንያት ያውቃል? እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ለማየት ቢፈተን መጥቶ ሊያነጋግረኝ እንዲችል በቀላሉ የምቀረብ ነኝ?’ ልጆቻችሁ ገና ትናንሽ እያሉም እንኳ እንዲህ ልትሏቸው ትችላላችሁ፦ “ሳታስበው የብልግና ድረ ገጽ ብትከፍትና ለማየት ብትፈተን መጥተህ ንገረኝ። ፈጽሞ ልታፍር አይገባም። የእኔ ፍላጎት አንተን መርዳት ነው።”

14 አስተዋይ መሆናችሁ የራሳችሁን መዝናኛም በጥንቃቄ ለመምረጥ ያስችላችኋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ፕራናስ እንዲህ ብሏል፦ “እኛ ወላጆች ከሙዚቃ፣ ከፊልሞች ወይም ከመጻሕፍት ጋር በተያያዘ የምናደርገው ምርጫ ለቤተሰባችን ምሳሌ ይሆናል። ስለተለያዩ ነገሮች ለልጆቻችሁ ብዙ ነገር ትነግሯቸው ይሆናል፤ ልጆቻችሁ የሚያደርጉት ግን እናንተ ስታደርጉ የሚያዩትን ነው።” እናንተ ተጠንቅቃችሁ ጥሩ መዝናኛ ስትመርጡ ልጆቻችሁ ካዩ እነሱም ተመሳሳይ ምርጫ ያደርጉ ይሆናል።—ሮም 2:21-24

እውነተኛው አምላክ ይሰማችኋል

15, 16. (ሀ) ልጆቻችሁን ስታሠለጥኑ አምላክ እንደሚረዳችሁ እርግጠኞች መሆን የምትችሉት ለምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

15 ማኑሄ ልጁን በማሳደግ ረገድ ይሖዋ እንዲረዳው ላቀረበው ጥያቄ ምን ምላሽ አገኘ? ጥቅሱ “እውነተኛው አምላክ የማኑሄን ቃል ሰማ” ይላል። (መሳ. 13:9) ወላጆች፣ ይሖዋ እናንተንም ይሰማል። ለጸሎታችሁ ምላሽ በመስጠት ልጆቻችሁን ለማሠልጠን ይረዳችኋል። ልጆቻችሁን በፍቅር፣ በትሕትናና በማስተዋል ለማሠልጠን የምታደርጉት ጥረት ይሳካላችኋል።

16 ይሖዋ፣ ወላጆች ትናንሽ ልጆቻቸውን በማሠልጠን ረገድ እንዲሳካላቸው እንደሚረዳቸው ሁሉ በጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ልጆቻቸውን ሲያሠለጥኑም ይረዳቸዋል። የሚቀጥለው ርዕስ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጃችሁን የይሖዋ አገልጋይ እንዲሆን ስትረዱ ፍቅር፣ ትሕትናና ማስተዋል በማሳየት ኢየሱስን እንዴት መምሰል እንደምትችሉ ያብራራል።

^ አን.5 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው መሠረት ተግሣጽ በፍቅር የሚሰጥ ትምህርትን፣ ሥልጠናን፣ እርማትንና አንዳንድ ጊዜም ቅጣትን ይጨምራል፤ ተግሣጹ የሚሰጠው ግን በቁጣ አይደለም።

^ አን.7 ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ “በኢየሱስ ዘመን የኖሩ ሰዎች በዕለታዊ ሕይወታቸው ይጠቀሙበት በነበረው ቋንቋ፣ ‘አባ’ የሚለው ቃል በዋነኝነት የሚያገለግለው ልጆች ከአባታቸው ጋር ያላቸውን ቅርርብ እንዲሁም ለአባታቸው ያላቸውን አክብሮት ለመግለጽ ነበር።”