በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

በጥንት ዘመን ጥቅልሎች ይዘጋጁና ይሠራባቸው የነበረው እንዴት ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘውን የአስቴር መጽሐፍ የያዙ የቆዳና የብራና ጥቅልሎች፣ በ18ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የተዘጋጀ

የሉቃስ ወንጌል፣ ኢየሱስ የኢሳይያስን ጥቅልል ተርትሮ ከዚያ ላይ እንዳነበበ በኋላም መልሶ እንደጠቀለለው ይናገራል። ዮሐንስም እሱ በጻፈው ወንጌል መጨረሻ ላይ ስለ ጥቅልል የተናገረ ሲሆን በጥቅልሉ ላይ ኢየሱስ ያደረጋቸውን ተአምራዊ ምልክቶች በሙሉ ማካተት እንዳልቻለ ገልጿል።—ሉቃስ 4:16-20፤ ዮሐንስ 20:30፤ 21:25

ለመሆኑ ጥቅልል ይዘጋጅ የነበረው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ከቆዳ፣ ከብራና ወይም ከፓፒረስ የተዘጋጁ በርካታ ቁርጥራጮችን ቀጣጥሎ ማጣበቅ ያስፈልጋል። ከዚያም ጽሑፉ በውስጥ በኩል እንዲሆን ተደርጎ በአንድ ዘንግ ላይ ይጠቀለላል። በጥቅልሉ ላይ ጽሑፉ አጠር አጠር ባሉ ረድፎች ተከፋፍሎ ወደ ጎን ይሰፍራል። ጥቅልሉ ረጅም ከሆነ በሁለቱም ጫፍ ዘንግ ይኖረዋል፤ ይህ ደግሞ አንባቢው የሚፈልገውን ቦታ እስኪያገኝ ደረስ በአንድ እጁ እየተረተረ በሌላ እጁ ለመጠቅለል ያስችለዋል።

“የጥቅልል አንዱ ጥቅም፣ ረጅም ከመሆኑ የተነሳ [ብዙውን ጊዜ ወደ 10 ሜትር ገደማ ይሆናል] አንድን ሙሉ መጽሐፍ መያዝ ቢችልም ሲጠቀለል ብዙ ቦታ የማይፈጅ መሆኑ ነው” በማለት ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ የተባለው መጽሐፍ ገልጿል። ለምሳሌ ያህል፣ የሉቃስ ወንጌልን ለመጻፍ ወደ 9.5 ሜትር ገደማ ርዝመት ያለው ጥቅልል እንደሚያስፈልግ ይገመታል። አንዳንድ ጊዜ ጥቅልሎች፣ ላይኛውና ታችኛው ጠርዞቻቸው ከተከረከሙና በድንጋይ ከተፈተጉ በኋላ ይቀለማሉ።

በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሱት “የካህናት አለቆች” እነማን ናቸው?

በእስራኤል የክህነት ዝግጅት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሊቀ ካህናት ሆኖ የሚሾመው አንድ ሰው ብቻ ሲሆን መጀመሪያ አካባቢ እስከ ሕይወቱ ማብቂያ ድረስ ሹመቱን ይዞ ይቀጥል ነበር። (ዘኁልቁ 35:25) ሊቀ ካህናት ሆኖ የተሾመው የመጀመሪያው ሰው አሮን ነው። ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት፣ ይህን ሹመት ከአባቱ የሚወርሰው የመጀመሪያው ወንድ ልጅ ነበር። (ዘፀአት 29:9) አብዛኞቹ የአሮን ዘሮች ካህናት ሆነው ያገለገሉ ቢሆንም ሊቀ ካህናት ሆነው ያገለገሉት ግን ጥቂቶች ነበሩ።

እስራኤላውን በባዕድ አገር ይገዙ በነበረበት ወቅት ገዢዎቻቸው ሊቀ ካህናት ሆነው የሚያገለግሉ ሰዎችን እንዳሻቸው መሾምና መሻር ጀመሩ። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ የሚሾመው መብቱ ከሚገባቸው ቤተሰቦች መካከል ሲሆን ይህ ደግሞ በአብዛኛው ከአሮን ዘር ነበር። “የካህናት አለቆች” የሚለው መጠሪያ የሚያገለግለው በክህነት ሥርዓቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸውን ሰዎች ለማመልከት ሳይሆን አይቀርም። ሃያ አራት ምድብ ያለው የክህነት ሥርዓቱ መሪዎች፣ የሊቀ ካህናቱ ቤተሰቦች ዋና ዋና አባላት እንዲሁም ከኃላፊነታቸው የወረዱ እንደ ሐና ያሉ የቀድሞ ሊቀ ካህናት “የካህናት አለቆች” በሚለው ስያሜ ይጠሩ ነበር።—1 ዜና መዋዕል 24:1-19፤ ማቴዎስ 2:4፤ ማርቆስ 8:31፤ የሐዋርያት ሥራ 4:6