በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአምላክ ጋር አብሮ መሥራት—አስደሳች መብት

ከአምላክ ጋር አብሮ መሥራት—አስደሳች መብት

“ከእሱ ጋር አብረን የምንሠራ እንደመሆናችን መጠን የአምላክን ጸጋ ከተቀበላችሁ በኋላ ዓላማውን እንዳትስቱ እናሳስባችኋለን።”—2 ቆሮ. 6:1

መዝሙሮች፦ 75, 74

1. ይሖዋ ከሁሉ የላቀ አምላክ ቢሆንም ሌሎች ምን እንዲያደርጉ ጋብዟል?

ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ነው፤ የሁሉም ነገር ፈጣሪ እንዲሁም ተወዳዳሪ የሌለው ጥበብና ኃይል ያለው አምላክ ነው። ኢዮብ ይህን እውነታ ተገንዝቧል። ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎቹን በተመለከተ ለኢዮብ ጥያቄ ካቀረበለት በኋላ ኢዮብ “አንተ ሁሉን ነገር ማድረግ እንደምትችል፣ ደግሞም ያሰብከውን ነገር ሁሉ ማድረግ እንደማይሳንህ አሁን አወቅኩ” በማለት መልሷል። (ኢዮብ 42:2) ይሖዋ፣ ያሰበውን ለማከናወን የማንም እገዛ የማያስፈልገው ቢሆንም ዓላማውን ዳር በማድረስ ረገድ ሌሎችም አብረውት እንዲሠሩ ገና ከጅምሩ በመጋበዝ ፍቅሩን አሳይቷል።

2. ይሖዋ፣ የትኛውን ጠቃሚ ሥራ እንዲያከናውን ኢየሱስን ጋብዞታል?

2 የአምላክ የመጀመሪያ ፍጥረት፣ መንፈሳዊ አካል የሆነው አንድያ ልጁ ነው። ይሖዋ ከዚያ በኋላ ሕይወት ያላቸውንና የሌላቸውን ነገሮች በሙሉ ሲፈጥር ልጁ አብሮት እንዲሠራ አድርጓል። (ዮሐ. 1:1-3, 18) ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስን በተመለከተ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በሰማያትና በምድር ያሉ ሌሎች ነገሮች በሙሉ፣ የሚታዩትና የማይታዩት ነገሮች፣ ዙፋኖችም ሆኑ ጌትነት፣ መንግሥታትም ሆኑ ሥልጣናት የተፈጠሩት በእሱ አማካኝነት ነው። ሌሎች ነገሮች በሙሉ የተፈጠሩት በእሱ በኩልና ለእሱ ነው።” (ቆላ. 1:15-17) ይሖዋ አንድያ ልጁ በፍጥረት ሥራው እንዲካፈል በማድረግ እንዲሁም ኢየሱስ የተጫወተውን ቁልፍ ሚና ለሌሎች በመግለጽ ልጁን አክብሮታል።

3. ይሖዋ ለአዳም ምን ሥራ ሰጥቶታል? ለምንስ?

3 ይሖዋ የሰው ልጆችንም ከእሱ ጋር አብረው እንዲሠሩ ጋብዟቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ለእንስሳት ስም የማውጣትን ሥራ ለአዳም ሰጥቶታል። (ዘፍ. 2:19, 20) አዳም እነዚህን ፍጥረታት መመልከት፣ ባሕርያቸውን ማጥናትና ለእያንዳንዳቸው ተስማሚ የሆነ ስም ማውጣት ምን ያህል አስደስቶት ይሆን! እንስሳቱን የፈጠራቸው ይሖዋ ስለሆነ እሱ ራሱ ስም ሊያወጣላቸው ይችል ነበር። ያም ሆኖ ይሖዋ፣ አዳም ስም እንዲያወጣላቸው በማድረግ ፍቅሩን አሳይቶታል። በተጨማሪም አምላክ ከኤደን ውጭ ያለውን የምድር ክፍል ገነት የማድረግን መብት ለአዳም ሰጥቶታል። (ዘፍ. 1:27, 28) ውሎ አድሮ ግን አዳም ከአምላክ ጋር አብሮ ለመሥራት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ፤ ይህም በራሱና በዘሮቹ ሁሉ ላይ ጥፋት አስከተለ።—ዘፍ. 3:17-19, 23

4. የአምላክን ፈቃድ ዳር በማድረስ ረገድ ሌሎች ከይሖዋ ጋር አብረው የሠሩት እንዴት ነው?

4 ከጊዜ በኋላ አምላክ፣ ዓላማውን ዳር በማድረስ ረገድ ሌሎች ሰዎችም የራሳቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ጋብዟል። ኖኅ እሱም ሆነ ቤተሰቡ ከዓለም አቀፉ የጥፋት ውኃ ለመዳን የሚያስችላቸውን መርከብ ሠርቷል። ሙሴ የእስራኤልን ብሔር ከግብፅ ነፃ አውጥቷል። ኢያሱ ደግሞ ይህን ብሔር ወደ ተስፋይቱ ምድር ይዞ ገብቷል። ሰለሞን በኢየሩሳሌም ያለውን ቤተ መቅደስ ገንብቷል። ማርያም የኢየሱስ እናት የመሆን መብት አግኝታለች። እነዚህ ታማኝ አገልጋዮችና ሌሎች በርካታ ሰዎች የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም ከእሱ ጋር አብረው ሠርተዋል።

5. በየትኛው ሥራ ላይ መካፈል እንችላለን? ይሖዋ ይህን ሥራ ለማከናወን የእኛ እርዳታ ያስፈልገዋል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ምስል ተመልከት።)

5 በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ለመሲሐዊው መንግሥት ሙሉ ድጋፍ እንድንሰጥ ግብዣ አቅርቦልናል። ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ የምንችልባቸው በርካታ ዘርፎች አሉ። በእርግጥ በአንዳንዶቹ የአገልግሎት መስኮች መካፈል የሚችሉት ሁሉም ክርስቲያኖች አይደሉም፤ ሆኖም ሁላችንም የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ሥራ መካፈል እንችላለን። እውነት ነው፣ ይሖዋ ይህን ሥራ ለማከናወን የእኛ እርዳታ አያስፈልገውም። ይሖዋ ከፈለገ ከሰማይ ሆኖ በምድር ለሚኖሩ ሰዎች በቀጥታ መናገር ይችላል። ይሖዋ፣ መሲሐዊውን ንጉሥ በተመለከተ ድንጋዮች እንኳ እንዲጮኹ ማድረግ ይችል እንደነበር ኢየሱስ ተናግሯል። (ሉቃስ 19:37-40) ያም ሆኖ ይሖዋ ‘ከእሱ ጋር አብረን የመሥራት’ መብት ሰጥቶናል። (1 ቆሮ. 3:9) ሐዋርያው ጳውሎስ “ከእሱ ጋር አብረን የምንሠራ እንደመሆናችን መጠን የአምላክን ጸጋ ከተቀበላችሁ በኋላ ዓላማውን እንዳትስቱ እናሳስባችኋለን” ሲል ጽፏል። (2 ቆሮ. 6:1) ከአምላክ ጋር አብሮ መሥራት ታላቅ ክብር በመሆኑ ወደር የሌለው ደስታ ያስገኝልናል። እንዲህ እንድንል የሚያነሳሱንን አንዳንድ ምክንያቶች እስቲ እንመልከት።

ከአምላክ ጋር አብሮ መሥራት ደስታ ያስገኝልናል

6. የአምላክ የበኩር ልጅ ከአባቱ ጋር አብሮ በመሥራቱ ምን እንደተሰማው የገለጸው እንዴት ነው?

6 የይሖዋ አገልጋዮች ከጥንትም ጀምሮ ከእሱ ጋር አብረው በመሥራት ይደሰቱ ነበር። መንፈሳዊ ፍጥረት የሆነው የአምላክ የበኩር ልጅ በጥበብ ተመስሎ እንደሚከተለው ብሏል፦ “ይሖዋ የመንገዱ መጀመሪያ አድርጎ ፈጠረኝ፤ . . . የተዋጣለት ሠራተኛ ሆኜ ከጎኑ ነበርኩ። በየዕለቱ በእኔ የተነሳ ልዩ ደስታ ይሰማው ነበር፤ እኔም በፊቱ ሁልጊዜ ሐሴት አደርግ ነበር።” (ምሳሌ 8:22, 30) ኢየሱስ ከአባቱ ጋር አብሮ በደስታ ይሠራ የነበረ ሲሆን ባከናወነው ነገር እንዲሁም ይሖዋ በእሱ ደስ እንደሚሰኝ በማወቁ ሐሴት ያደርግ ነበር። ስለ እኛስ ምን ማለት ይቻላል?

ለአንድ ሰው የእውነትን መንገድ ከማስተማር ይበልጥ እርካታ የሚያስገኝ ምን አለ? (አንቀጽ 7ን ተመልከት)

7. የስብከቱ ሥራ ደስታ የሚያስገኝልን ለምንድን ነው?

7 ኢየሱስ መቀበልም ሆነ መስጠት ደስታ እንደሚያስገኝ ተናግሯል። (ሥራ 20:35) እውነትን ማግኘታችን አስደስቶናል፤ እውነትን ለሌሎች ማካፈላችንም ደስታ ያስገኝልናል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች የምንነግራቸው በመንፈሳዊ የተራቡ ሰዎች፣ ስለ አምላካችን ሲያውቁና በቃሉ ውስጥ የሰፈሩትን ውድ እውነቶች ሲገነዘቡ ልባቸው በደስታ ይሞላል። እኛም እነዚህ ሰዎች በአስተሳሰባቸው ብቻ ሳይሆን በሕይወታቸው ውስጥም ለውጦች ሲያደርጉ ስንመለከት ልባችን ሐሴት ያደርጋል። ምሥራቹን ለሰዎች የመስበኩ ሥራ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ እንገነዘባለን። የስብከቱ ሥራ ከአምላክ ጋር ለሚታረቁ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉበት መንገድ ይከፍታል። (2 ቆሮ. 5:20) ሰዎች የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝላቸውን መንገድ እንዲከተሉ ከመርዳት የሚበልጥ ምን አስደሳችና አርኪ ሥራ ሊኖር ይችላል?

8. ከይሖዋ ጋር መሥራት የሚያስገኘውን ደስታ በተመለከተ አንዳንዶች ምን ብለዋል?

8 ሰዎች የሰበክንላቸውን መልእክት ሰምተው ጥሩ ምላሽ ሲሰጡ መመልከት ያስደስተናል፤ ይሖዋ እንደሚደሰትብንና እሱን ለማገልገል የምናደርገውን ጥረት እንደሚያደንቅ ማወቃችን ደግሞ ይበልጥ ያስደስተናል። (1 ቆሮንቶስ 15:58ን አንብብ።) በጣሊያን የሚኖረው ማርኮ እንዲህ ብሏል፦ “ምርጤን የምሰጠው ለይሖዋ እንጂ ብዙም ሳይቆይ ሥራዬን ለሚረሱ የሰው ልጆች እንዳልሆነ ማወቄ ተወዳዳሪ የሌለው ደስታ ያመጣልኛል።” ፍራንኮም የሚያገለግለው በጣሊያን ሲሆን እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ይወደናል እንዲሁም ለእኛ ትንሽ መስሎ ቢታየንም እንኳ እሱን ለማገልገል የምናደርገውን ማንኛውንም ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከታል፤ ይህንንም በቃሉና በመንፈሳዊ ዝግጅቶቹ አማካኝነት በየዕለቱ ያስታውሰናል። ከአምላክ ጋር አብሬ መሥራቴ የሚያስደስተኝና ሕይወቴ ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርግልኝ ለዚህ ነው።”

ከአምላክ ጋር አብሮ መሥራት ከእሱና ከሰዎች ጋር ይበልጥ ያቀራርበናል

9. ይሖዋና ኢየሱስ ምን ዓይነት ግንኙነት አላቸው? ይህ የሆነውስ ለምንድን ነው?

9 ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር አብረን ስንሠራ ይበልጥ የምንቀራረብ ከመሆኑም ሌላ ስለ እነሱ በደንብ ማወቅ እንችላለን። ምን ማከናወን እንደሚፈልጉ ብቻ ሳይሆን ይህን የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነም ጭምር መረዳት እንችላለን። ኢየሱስ ከይሖዋ ጋር በቢሊዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት አብሮ ሳይሠራ አይቀርም፤ በመሆኑም አንዳቸው ለሌላው በጣም ጥልቅ ፍቅር አዳብረዋል፤ እንዲሁም ፈጽሞ ሊበጠስ የማይችል ጠንካራ ወዳጅነት መሥርተዋል። ኢየሱስ ምን ያህል እንደሚቀራረቡ ሲገልጽ “እኔና አብ አንድ ነን” ብሏል። (ዮሐ. 10:30) በመካከላቸው አስደናቂ አንድነት ያለ ሲሆን ምንጊዜም የሚሠሩት ፍጹም ስምም ሆነው ነው።

10. የስብከቱ ሥራ ከአምላክና ከሰዎች ጋር ይበልጥ እንድንቀራረብ የሚያደርገን ለምንድን ነው?

10 ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን እንዲጠብቃቸው ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? “እኛ አንድ እንደሆንን ሁሉ እነሱም አንድ እንዲሆኑ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 17:11) ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን ስንኖርና በስብከቱ ሥራ ስንካፈል የይሖዋን አስደናቂ ባሕርያት መረዳት እንችላለን። በእሱ መታመንም ሆነ መመሪያውን መከተል የጥበብ እርምጃ የሆነበትን ምክንያት እንገነዘባለን። ወደ አምላክ ስንቀርብ እሱም ወደ እኛ ይቀርባል። (ያዕቆብ 4:8ን አንብብ።) በተጨማሪም ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር እንቀራረባለን፤ ምክንያቱም የሚያጋጥሙን ችግሮች፣ አስደሳች ነገሮች እንዲሁም ግቦቻችን ተመሳሳይ ናቸው። በእርግጥም የምንሠራው፣ የምንደሰተውና ፈተናዎችን በጽናት የምንቋቋመው አብረን ነው። በብሪታንያ የምትኖረው ኦክታቪያ እንዲህ ብላለች፦ “ከይሖዋ ጋር አብሬ መሥራቴ ከሌሎች ጋር እንድቀራረብ ይረዳኛል፤ ምክንያቱም ወዳጅነታችንና ቅርበታችን የተመሠረተው ያን ያህል ጥልቀት በሌለው ትውውቅ ላይ ሳይሆን አንድ ዓይነት ግብ በመያዛችን ላይ ነው።” አንተስ እንዲህ አይሰማህም? ሌሎች ይሖዋን ለማስደሰት የሚያደርጉትን ጥረት ስትመለከት ይበልጥ ወደ እነሱ ለመቅረብ አትገፋፋም?

11. በአዲሱ ዓለም ውስጥ ከይሖዋና ከወንድሞቻችን ጋር ይበልጥ እንድንቀራረብ የሚያደርገን ምንድን ነው?

11 በአሁኑ ወቅት ለአምላክና ለሌሎች ሰዎች ያለን ፍቅር ጠንካራ ሊሆን ይችላል፤ ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ደግሞ ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል። ወደፊት የሚጠብቀንን ሥራ እስቲ አስበው! ከሞት የተነሱ ሰዎችን መቀበል እንዲሁም ስለ ይሖዋ መንገዶች ማስተማር ይኖርብናል። ምድርን ወደ ገነትነት የመለወጡ ሥራም አለ። እነዚህ ቀላል የሚባሉ ሥራዎች አይደሉም፤ በመሲሐዊው መንግሥት አገዛዝ ሥር እጅ ለእጅ ተያይዞ መሥራትና ወደ ፍጽምና መድረስ ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል! ሰብዓዊው ቤተሰብ እርስ በርስ እንዲሁም ከአምላክ ጋር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ይቀራረባል፤ በዚያ ወቅት አምላክ ‘የሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፍላጎት እንደሚያሟላ’ የተረጋገጠ ነው።—መዝ. 145:16

ከአምላክ ጋር አብሮ መሥራት ጥበቃ ይሆንልናል

12. የስብከቱ ሥራ ጥበቃ የሚሆንልን እንዴት ነው?

12 ክርስቲያኖች መንፈሳዊነታችንን መጠበቅ ያስፈልገናል። የምንኖረው ሰይጣን ዲያብሎስ በሚቆጣጠረው ዓለም ውስጥ ከመሆኑም ሌላ ፍጹማን አይደለንም፤ በመሆኑም የዓለምን የተሳሳተ አስተሳሰብና ምግባር በቀላሉ ልንኮርጅ እንችላለን። የዓለም መንፈስ፣ ወደማንፈልገው አቅጣጫ ሊወስደን ከሚታገል ወንዝ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ወንዙ ይዞን እንዳይሄድ ከፈለግን ወደ ተቃራኒው አቅጣጫ ለመዋኘት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለብን። በተመሳሳይም የሰይጣን ዓለም መንፈስ እንዳይወስደን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ምሥራቹን ስንሰብክ እምነታችንን በሚሸረሽሩ ሐሳቦች ላይ ሳይሆን አስፈላጊና ጠቃሚ በሆኑ መንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ እናተኩራለን። (ፊልጵ. 4:8) የስብከቱ ሥራ አምላክ የሰጣቸውን ተስፋዎችና ፍቅር የሚንጸባረቅባቸውን መሥፈርቶቹን እንድናስታውስ ስለሚረዳን እምነታችንን ያጠናክርልናል። መንፈሳዊ የጦር ትጥቃችን እንዳይላላም ይረዳናል።ኤፌሶን 6:14-17ን አንብብ።

13. በአውስትራሊያ የሚኖር አንድ ክርስቲያን ስለ ስብከቱ ሥራ ምን ተሰምቶታል?

13 በስብከቱ ሥራና በሌሎች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መጠመዳችን በራሳችን ችግሮች ላይ ከልክ በላይ እንዳናተኩር ይረዳናል፤ ይህ ደግሞ ጥበቃ ይሆነናል። በአውስትራሊያ የሚኖረው ጆኤል እንዲህ ብሏል፦ “የስብከቱ ሥራ እውነታውን እንዳልዘነጋ ይረዳኛል። ሌሎች ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወቴ ተግባራዊ በማድረጌ ያገኘሁትን ጥቅም እንዳስተውል ረድቶኛል። የስብከቱ ሥራ ምንጊዜም ትሑት ለመሆን እንድጥር ይረዳኛል፤ በይሖዋ እንዲሁም በወንድሞቼና በእህቶቼ እንድታመን አድርጎኛል።”

14. በስብከቱ ሥራ መጽናታችን የአምላክ መንፈስ ከእኛ ጋር መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

14 የስብከቱ ሥራ፣ የአምላክ መንፈስ ከእኛ ጋር እንደሆነ ያለንን እምነትም ያጠናክርልናል። አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ በአካባቢህ ለሚኖሩ ሰዎች ዳቦ የማከፋፈል ሥራ ተሰጠህ እንበል። ይህን ሥራ ስታከናውን ደሞዝ አይከፈልህም፤ ያወጣኸው ወጪም ቢሆን አይተካልህም። ይባስ ብሎ ደግሞ አብዛኞቹ ሰዎች ዳቦውን እንደማይፈልጉት እንደውም አንዳንዶቹ ይህን ሥራ በማከናወንህ እንደሚጠሉህ ትገነዘባለህ። በዚህ ሥራ ላይ ምን ያህል መቆየት የምትችል ይመስልሃል? የሰዎች አሉታዊ ምላሽ ተስፋ ስለሚያስቆርጥህ በሥራው ላይ ረዘም ላለ ጊዜ ለመቀጠል የሚያስችል የመንፈስ ጥንካሬ አይኖርህ ይሆናል። የሚገርመው ግን ብዙዎቻችን፣ ለምንሰብከው መልእክት አድናቆት የሌላቸው ሰዎች መሳቂያና መሳለቂያ ቢያደርጉንም በራሳችን ወጪ አገልግሎታችንን ለዓመታት በጽናት አከናውነናል። ታዲያ ይህ፣ የአምላክ መንፈስ በእኛ ላይ እየሠራ እንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃ አይደለም?

ከአምላክ ጋር አብሮ መሥራት ለእሱና ለሰዎች ፍቅር እንዳለን ያሳያል

15. ምሥራቹን የመስበኩ ሥራ አምላክ ለሰው ልጆች ካለው ዓላማ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

15 ምሥራቹን የመስበኩ ሥራ ይሖዋ ለሰው ልጆች ካለው ፍቅር የተንጸባረቀበት ዓላማ ጋር እንዴት እንደሚያያዝም አስብ። የአምላክ ዓላማ የሰው ልጆች ፈጽሞ ሞትን ሳያዩ በምድር ላይ እንዲኖሩ ነው፤ አዳም ኃጢአት ቢሠራም ይሖዋ ይህን ዓላማውን አልቀየረም። (ኢሳ. 55:11) እንዲያውም የሰው ልጆች ከኃጢአትና ከሞት ኩነኔ ነፃ የሚወጡበትን ዝግጅት አደረገ። ይህንን ዓላማ ከዳር ማድረስ እንዲቻል ኢየሱስ ወደ ምድር መጥቶ ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል። ይሁንና የሰው ልጆች ታዛዥ እንዲሆኑ አምላክ ከእነሱ ምን እንደሚጠብቅባቸው ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። በመሆኑም ኢየሱስ የአምላክን መሥፈርቶች ለሰዎች አስተምሯል፤ ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ እንዲያደርጉ ትእዛዝ ሰጥቷል። እኛም ሰዎች ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ ስንረዳ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ይሖዋ ባደረገው ፍቅራዊ ዝግጅት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ይኖረናል።

16. የስብከቱ ሥራችን ከሁሉ ከሚበልጡት የአምላክ ትእዛዛት ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?

16 ሰዎች ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ እንዲመላለሱ መርዳታችን ለእነሱም ሆነ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ያሳያል፤ የይሖዋ “ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።” (1 ጢሞ. 2:4) ኢየሱስ ለእስራኤል ብሔር ከተሰጡት ሕግጋት ሁሉ የሚበልጠው የትኛው እንደሆነ ሲጠየቅ እንዲህ ብሏል፦ “‘አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።’ ይህ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው። ሁለተኛውም ይህንኑ የሚመስል ሲሆን ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል።” (ማቴ. 22:37-39) በስብከቱ ሥራ በመካፈል እነዚህን ሕግጋት እንደምንታዘዝ እናሳያለን።የሐዋርያት ሥራ 10:42ን አንብብ።

17. ምሥራቹን ለሌሎች የመስበክ ክብር በማግኘትህ ምን ይሰማሃል?

17 በእርግጥም ምንኛ ተባርከናል! ይሖዋ ደስታን የሚያስገኝ፣ ወደ እሱም ሆነ ወደ ሌሎች ይበልጥ እንድንቀርብ የሚያደርግ እንዲሁም በመንፈሳዊ ጥበቃ የሚሆንልን ሥራ ሰጥቶናል። በተጨማሪም ይህ ሥራ ለአምላክም ሆነ ለሰዎች ያለንን ፍቅር ለማሳየት አጋጣሚ ይከፍትልናል። በዓለም ዙሪያ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች ሁኔታ በእጅጉ የተለያየ ነው፤ ያም ቢሆን ልጅ አዋቂ፣ ሀብታም ድሃ፣ ብርቱ ደካማ ሳይል በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአምላክ አገልጋዮች ስለ እምነታቸው ለሌሎች ለመናገር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ይጠቀማሉ። አንተም በፈረንሳይ የምትኖረው ሻንቴል ከተናገረችው ሐሳብ ጋር ትስማማ ይሆናል። እንዲህ ብላለች፦ “በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከማንም የበለጠ ኃይል ያለውና የሁሉም ነገሮች ፈጣሪ እንዲሁም ደስተኛ የሆነው አካል እንዲህ ብሎኛል፦ ‘ሂጂ! ተናገሪ! እኔን ወክለሽ በሙሉ ልብ ተናገሪ። የሚያስፈልግሽን ኃይልና ቃሌን መጽሐፍ ቅዱስን እሰጥሻለሁ፤ እንዲሁም ከሰማይ ድጋፍ፣ በምድር ደግሞ ረዳቶች፣ ቀጣይነት ያለው ሥልጠናና በተገቢው ጊዜ ግልጽ መመሪያ እሰጥሻለሁ።’ ይሖዋ የሚጠይቀንን ነገር ማከናወንና ከአምላካችን ጋር አብሮ መሥራት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!”