በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የምትወደውን ሰው በሞት ስታጣ

የሞቱ ሰዎች ይነሳሉ!

የሞቱ ሰዎች ይነሳሉ!

ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ጌል የባለቤቷ የሮብ ሞት ካስከተለባት ሐዘን መጽናናት እንደማትችል ተሰምቷት እንደነበር ትዝ ይልህ ይሆናል። ያም ቢሆን አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ ሮብን እንደምታገኘው ተስፋ ታደርጋለች። “በጣም የምወደው ጥቅስ ራእይ 21:3, 4 ነው” ትላለች። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ . . . ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቡ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል። እሱም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”

ጌል እንዲህ ብላለች፦ “ይህ ተስፋ መድኃኒት ነው። የሚወዱትን ሰው በሞት ቢያጡም ግለሰቡ ከሞት የመነሳት ተስፋ እንዳለው የማያውቁ ሰዎች በጣም ያሳዝኑኛል።” ጌል የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆና በፈቃደኝነት በማገልገል ይህን እምነቷን በሥራ ታሳያለች፤ ‘ሞት ስለማይኖርበት ጊዜ’ የሚገልጸውን አምላክ የሰጠውን ተስፋ ለሰዎች ትናገራለች።

ኢዮብ ዳግመኛ እንደሚኖር እርግጠኛ ነበር

‘ይህ የማይታመን ነገር ነው!’ ትል ይሆናል። ኢዮብ የተባለውን ሰው እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኢዮብ በጠና ታሞ ነበር። (ኢዮብ 2:7) ሞትን ተመኝቶ የነበረ ቢሆንም እንኳ አምላክ ከሞት አስነስቶ በድጋሚ ምድር ላይ እንደሚያኖረው እምነት ነበረው። በእርግጠኝነት እንዲህ ብሏል፦ “ምነው በመቃብር ውስጥ በሰወርከኝ! . . . አንተ ትጣራለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ። የእጅህን ሥራ ትናፍቃለህ።” (ኢዮብ 14:13, 15) ኢዮብ፣ አምላኩ እሱን ለማግኘት እንደሚናፍቅና ከሞት ሊያስነሳው እንደሚጓጓ እርግጠኛ ነበር።

በቅርቡ ምድር ወደ ገነትነት ስትለወጥ አምላክ፣ ኢዮብንና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች ሰዎችን ከሞት ያስነሳል። (ሉቃስ 23:42, 43) መጽሐፍ ቅዱስ በሐዋርያት ሥራ 24:15 ላይ ሰዎች “ከሞት እንደሚነሱ” ማረጋገጫ ይሰጣል። ኢየሱስ “በዚህ አትደነቁ፤ በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣልና፤ [ደግሞም] ይወጣሉ” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 5:28, 29) ኢዮብ ይህ ተስፋ ሲፈጸም ይመለከታል። “ብርቱ ወደነበረበት የወጣትነት ዘመኑ” የመመለስ ተስፋ አለው፤ “በወጣትነቱ ጊዜ ከነበረው የበለጠ ሥጋው” ለዘላለም ይለመልማል። (ኢዮብ 33:24, 25) ትንሣኤ አግኝቶ በምድር ላይ የመኖርን ተስፋ ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ሁሉ እነዚህን በረከቶች ያገኛሉ።

የምትወደውን ሰው በሞት በማጣትህ የተነሳ ስሜትህ ተጎድቶ ከሆነ እስካሁን የተመለከትናቸው ነጥቦች ሐዘንህን ሙሉ በሙሉ አያስወግዱልህ ይሆናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት አምላክ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ በማሰላሰል ግን እውነተኛ ተስፋ እንዲሁም ጥንካሬ ማግኘት ትችላለህ።—1 ተሰሎንቄ 4:13

የደረሰብህን ሐዘን ለመቋቋም የሚረዳ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ትፈልጋለህ? አሊያም ደግሞ “አምላክ ክፋትና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?” እንደሚለው ያሉ ጥያቄዎችን ጠይቀህ ታውቃለህ? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ተግባራዊ የሚሆንና የሚያጽናና መልስ ለማግኘት jw.org የተባለውን ድረ ገጻችንን እንድትጎበኝ እናበረታታሃለን።