በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

ኢየሱስ የተሠቃየውና የሞተው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ የተሠቃየውና የሞተው ለምንድን ነው?

“በአንድ ሰው [በአዳም] አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ።” ሮም 5:12

“ለዘላለም መኖር ትፈልጋለህ?” ተብለህ ብትጠየቅ ምን መልስ ትሰጣለህ? አብዛኞቹ ሰዎች ለዘላለም መኖር እንደሚፈልጉ ቢናገሩም ይህ የሕልም እንጀራ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ሞት ያለ ነገር እንደሆነና ማንም ሰው መሞቱ እንደማይቀር ይናገራሉ።

ይሁንና ጥያቄው ለወጥ ተደርጎ “መሞት ትፈልጋለህ?” ተብለህ ብትጠየቅስ? ጤናማ የሆነ ማንኛውም ሰው መሞት አይፈልግም። ይህ ምን ያሳያል? መከራና ችግር ቢደርስብንም እንኳ ተፈጥሯዊው ፍላጎታችን በሕይወት መኖር ነው። አምላክ ሰዎችን ሲፈጥራቸው በሕይወት የመኖር ፍላጎት እንዲኖራቸው እንዳደረገ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። “ዘላለማዊነትን በልባቸው ውስጥ አኑሯል” ይላል።—መክብብ 3:11

ይሁንና ሰዎች ለዘላለም እየኖሩ አይደለም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ደግሞስ አምላክ ሁኔታውን ለማስተካከል ያደረገው ነገር አለ? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መልስ የሚያጽናና ሲሆን ኢየሱስ የተሠቃየውና የሞተው ለምን እንደሆነ ለመረዳትም ያስችለናል።

ሰዎች ለዘላለም የማይኖሩት ለምንድን ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ምዕራፎች፣ አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ይኸውም ለአዳምና ለሔዋን ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንደሰጣቸው ይነግሩናል፤ እንዲህ ያለ ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለባቸውም ገልጾላቸዋል። ዘገባው ቀጥሎም አዳምና ሔዋን፣ አምላክን ሳይታዘዙ በመቅረታቸው ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንዳጡ ይናገራል። ታሪኩ የተቀመጠው ለመረዳት ቀላል በሆነ መንገድ በመሆኑ አንዳንዶች ተረት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ እንደ ወንጌል ዘገባዎች ሁሉ የዘፍጥረት መጽሐፍም እውነተኛ ታሪክ እንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃ አለ። *

አዳም ሳይታዘዝ መቅረቱ ምን አስከተለ? መጽሐፍ ቅዱስ “በአንድ ሰው [በአዳም] አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ” የሚል መልስ ይሰጣል። (ሮም 5:12) አዳም አምላክን ባለመታዘዙ ኃጢአት ሠርቷል። በዚህ ምክንያት ለዘላለም የመኖር አጋጣሚውን ያጣ ሲሆን ውሎ አድሮም ሞተ። እኛም የእሱ ዘሮች በመሆናችን ኃጢአትን ከእሱ ወርሰናል። በዚህም የተነሳ ለሕመም፣ ለእርጅናና ለሞት ተዳርገናል። የምንሞተው ለምን እንደሆነ የሚገልጸው ይህ ሐሳብ፣ በዛሬው ጊዜ ልጆች ከወላጆቻቸው በዘር ስለሚወርሷቸው ነገሮች ሳይንስ ከደረሰበት ግንዛቤ ጋር ይስማማል። ይሁንና አምላክ ሁኔታውን ለማስተካከል ያደረገው ነገር አለ?

አምላክ ምን አድርጓል?

አምላክ፣ አዳም ለዘሮቹ ያሳጣቸውን ነገር ይኸውም ለዘላለም የመኖርን አጋጣሚ የሰው ልጆች እንዲያገኙ የሚያስችል ዝግጅት አድርጓል፤ ይህም ዋጋ መክፈል ጠይቆበታል። አምላክ ይህን ያደረገው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ በሮም 6:23 ላይ “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው” ይላል። ይህም ሲባል ሞት የኃጢአት ውጤት ነው ማለት ነው። አዳም ኃጢአት ስለሠራ ሞተ። እኛም ኃጢአት ስለምንሠራ የኃጢአት ደሞዝ ከሆነው ሞት አናመልጥም። ይሁንና ኃጢአተኞች የሆንነው በራሳችን ጥፋት አይደለም፤ ስንወለድ ጀምሮ ኃጢአተኞች ነን። ስለዚህ አምላክ በፍቅር ተገፋፍቶ ልጁ ኢየሱስ ‘የኃጢአትን ደሞዝ’ ስለ እኛ እንዲሸከምልን ዝግጅት አደረገ። ይህ ዝግጅት የሚሠራው እንዴት ነው?

የኢየሱስ ሞት ደስተኞች ሆነን ለዘላለም እንድንኖር መንገድ ከፍቶልናል

ኃጢአትንና ሞትን የወረስነው አንድ ሰው ይኸውም ፍጹም የነበረው አዳም ባለመታዘዙ ምክንያት በመሆኑ፣ ከኃጢአት ደሞዝ ነፃ እንድንወጣ እስከ ሞት ድረስ ታዛዥ የሆነ አንድ ፍጹም ሰው ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጉዳይ ሲያብራራ “በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ ሁሉ በአንዱ ሰው መታዘዝም ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ” ይላል። (ሮም 5:19) እዚህ ላይ የተጠቀሰው ‘አንድ ሰው’ ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ ሰማይን ትቶ ወደ ምድር በመምጣት ፍጹም ሰው * ሆኖ ስለ እኛ ሞተ። በዚህም የተነሳ በአምላክ ዘንድ እንደ ጻድቅ ሆነን መቆጠር እንዲሁም ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ማግኘት ችለናል።

ኢየሱስ የተሠቃየውና የሞተው ለምንድን ነው?

ታዲያ ኢየሱስ እኛን ከኃጢአት ደሞዝ ነፃ ለማውጣት መሞት ያስፈለገው ለምንድን ነው? ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ፣ የአዳም ዘሮች ለዘላለም እንዲኖሩ መፍቀዱን የሚገልጽ አዋጅ ማውጣት አይችልም ነበር? እንዲህ የማድረግ ሥልጣን እንዳለው ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ እንዲህ ቢያደርግ የኃጢአት ደሞዝ ሞት እንደሆነ በግልጽ ያስቀመጠውን ሕግ መጣስ ይሆንበታል። ይህ ሕግ ደግሞ ሳይመች ሲቀር፣ ሊሰረዝ ወይም ሊለወጥ የሚችል ተራ ደንብ አይደለም። ፍትሕ እንዲኖር ይህ ሕግ በጣም አስፈላጊ ነው።—መዝሙር 37:28

አምላክ በዚህ ረገድ ፍትሐዊ የሆነውን እርምጃ ባይወስድ ኖሮ ‘በሌሎች ነገሮችም እንዲሁ ያደርግ ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ የሰው ልጆችን ሊያሳስባቸው ይችል ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ‘ከአዳም ዘሮች መካከል የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ብቁ የሆኑት እነማን እንደሆኑ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይወስን ይሆን? የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እምነት ሊጣልበት ይችላል?’ የሚሉት ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። አምላክ፣ እኛ መዳን እንድናገኝ ያደረገው ዝግጅት የፍትሕ መሥፈርቱን የተከተለ መሆኑ ምንጊዜም ትክክል የሆነውን እንደሚያደርግ ዋስትና ይሰጠናል።

አምላክ፣ ኢየሱስ መሥዋዕት ሆኖ እንዲሞት ማድረጉ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንዲከፈትልን አስችሏል። በዮሐንስ 3:16 ላይ የሚገኘውን ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ ልብ በል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” በመሆኑም የኢየሱስ ሞት፣ የአምላክ ፍትሕ ዝንፍ የማይል እንደሆነ ያሳያል፤ ከዚህ ይበልጥ ደግሞ አምላክ ለሰዎች ያለው ታላቅ ፍቅር መግለጫ ነው።

ይሁንና ኢየሱስ በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ በተገለጸው መንገድ የተሠቃየውና የሞተው ለምንድን ነው? ኢየሱስ በጣም ከባድ በሆነ ፈተና ሥር አልፎ ታማኝነቱን መጠበቁ፣ ዲያብሎስ የሰው ልጆች መከራ ሲደርስባቸው ለአምላክ ታማኝ እንደማይሆኑ የተናገረው ሐሳብ ስህተት መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጧል። (ኢዮብ 2:4, 5) ሰይጣን ፍጹም የነበረውን አዳምን ኃጢአት እንዲሠራ ማድረግ ስለቻለ፣ ሰዎች ፈተና ቢደርስባቸው ለአምላክ ታማኝ እንደማይሆኑ የሰነዘረው ሐሳብ እውነት ሊመስል ይችላል። ያም ሆኖ ልክ እንደ አዳም ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ ከባድ መከራ ቢደርስበትም ለአምላክ ታዛዥ ሆኗል። (1 ቆሮንቶስ 15:45) በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ አዳምም ቢፈልግ ኖሮ አምላክን ለመታዘዝ ሊመርጥ ይችል እንደነበረ አረጋግጧል። ኢየሱስ መከራ ሲደርስበት በመጽናት እኛም ልንከተለው የሚገባ አርዓያ ትቶልናል። (1 ጴጥሮስ 2:21) አምላክ፣ ልጁ ኢየሱስ ፍጹም ታዛዥነት በማሳየቱ፣ በሰማይ የማይሞት ሕይወት በመስጠት ወሮታውን ከፍሎታል።

የኢየሱስ ሞት አንተን የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

ኢየሱስ መሞቱ እውነት ነው። የእሱ ሞት፣ ለዘላለም ሕይወት መንገድ ከፍቷል። ታዲያ ለዘላለም መኖር ትፈልጋለህ? ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገን እንዲህ በማለት ገልጿል፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው።”—ዮሐንስ 17:3

የዚህ መጽሔት አዘጋጆች፣ እውነተኛ አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋ እና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መማርህን እንድትቀጥል ያበረታቱሃል። በአካባቢህ የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው። በተጨማሪም www.pr418.com/am የተሰኘውን ድረ ገጻችንን በመጎብኘት ጠቃሚ መረጃ ማግኘት ትችላለህ።

^ አን.8 ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 በተባለው መጽሐፍ ገጽ 922 ላይ “ዘ ሂስቶሪካል ካራክተር ኦቭ ጀነስስ” የሚለውን ንዑስ ርዕስ እንዲሁም በጥር 1, 2011 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 4 ላይ የወጣውን “ኤደን ገነት በእውን የነበረ ቦታ ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት፤ ሁለቱም ጽሑፎች በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ናቸው።

^ አን.13 አምላክ የልጁን ሕይወት ከሰማይ ወደ ማርያም ማህፀን በማዛወር ማርያም እንድትፀንስ አድርጓል፤ ኢየሱስ ከማርያም ኃጢአት እንዳይወርስ ደግሞ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ተከላክሎለታል።—ሉቃስ 1:31, 35