በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቲያናዊ አንድነታችን እንዲጠናከር የበኩልህን ማድረግ ትችላለህ—እንዴት?

ክርስቲያናዊ አንድነታችን እንዲጠናከር የበኩልህን ማድረግ ትችላለህ—እንዴት?

“በእሱ አማካኝነት የአካል ክፍሎች ሁሉ . . . እርስ በርስ ተስማምተው ተገጣጥመዋል።”​—ኤፌ. 4:16

መዝሙሮች፦ 53, 107

1. ከመጀመሪያው አንስቶ በአምላክ ፍጥረታት መካከል የትኛው ባሕርይ ታይቷል?

ከፍጥረት መጀመሪያ አንስቶ የዓላማ አንድነት በግልጽ ሲታይ ቆይቷል። በጥበብ የተመሰለው የአምላክ የመጀመሪያ ፍጡር እንዲህ ብሏል፦ “የተዋጣለት ሠራተኛ ሆኜ ከጎኑ [ከይሖዋ ጎን] ነበርኩ። በየዕለቱ በእኔ የተነሳ ልዩ ደስታ ይሰማው ነበር።” (ምሳሌ 8:30) አባትና ልጅ አንድ ላይ በመሥራት ዛሬ የምናያቸውን ልዩ ልዩ ፍጥረታት አስገኝተዋል። የአምላክ ፍጥረታትም እርስ በርስ ባላቸው የትብብር መንፈስ ይታወቃሉ። ኖኅና ቤተሰቡ መርከብ ሲሠሩ፣ በምድረ በዳ ይጓዝ የነበረው የአምላክ ሕዝብ የማደሪያውን ድንኳን ሲተክል፣ ሲያፈርስና ከቦታ ቦታ ሲያጓጉዝ አልፎ ተርፎም መዘምራን በይሖዋ ቤተ መቅደስ በሙዚቃ መሣሪያዎች ታጅበው በኅብረት እየዘመሩ እሱን ሲያወድሱ አገልጋዮቹ አንድነት እንዳላቸው ታይቷል። የእነዚህ ሁሉ ሥራዎች መሳካት በሰዎቹ መተባበር ላይ የተመካ ነበር።—ዘፍ. 6:14-16, 22፤ ዘኁ. 4:4-32፤ 1 ዜና 25:1-8

2. (ሀ) የጥንቱን የክርስቲያን ጉባኤ በተመለከተ ትኩረታችንን የሚስበው ጉዳይ ምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመለከታለን?

2 በኢየሱስ ክርስቶስ ራስነት ሥር የነበረው የጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤም በኅብረት በመሥራት ይታወቅ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች በግለሰብ ደረጃ “ልዩ ልዩ ስጦታዎች” የነበሯቸው ከመሆኑም ሌላ “ልዩ ልዩ አገልግሎቶች” እና “ልዩ ልዩ ሥራዎች” በማከናወን ይሳተፉ ነበር፤ ይሁንና ሁሉም ‘የአንድ አካል’ ክፍል ነበሩ። (1 ቆሮንቶስ 12:4-6, 12ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜ ስላለው ሁኔታስ ምን ማለት ይቻላል? ምሥራቹን በመስበክ ረገድ እርስ በርስ ተስማምተን መሥራት የምንችለው እንዴት ነው? በጉባኤም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ ተባብረን መሥራት የምንችለው እንዴት ነው?

የስብከቱን ሥራ ተባብራችሁ አከናውኑ

3. ሐዋርያው ዮሐንስ ያየው ራእይ ምን ነበር?

3 በአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. መደምደሚያ አካባቢ ሐዋርያው ዮሐንስ ሰባት መላእክትን በራእይ የተመለከተ ሲሆን እያንዳንዳቸው መለከት ይነፉ ነበር። አምስተኛው መልአክ መለከቱን ሲነፋ ዮሐንስ ከሰማይ ወደ ምድር የወደቀ አንድ “ኮከብ” አየ። “ኮከቡ” በእጁ ቁልፍ ይዞ ነበር፤ በዚያም የጥልቁን መግቢያ ከፈተው። በዚህ ጊዜ ጥቁር ጭስ ተትጎለጎለ፤ ከጭሱም የአንበጣ መንጋ ወጣ። እነዚህ ምሳሌያዊ አንበጦች ዕፀዋትን ከመጉዳት ይልቅ “የአምላክ ማኅተም በግንባራቸው ላይ የሌላቸውን ሰዎች” አጠቁ። (ራእይ 9:1-4) ዮሐንስ የአንበጣ መንጋ ምን ያህል አውዳሚ እንደሆነ እንደሚያውቅ ጥርጥር የለውም። በሙሴ ዘመን አንበጦች በጥንቷ ግብፅ ላይ ውድመት አስከትለው አልነበረም? (ዘፀ. 10:12-15) ዮሐንስ የተመለከተው ምሳሌያዊ የአንበጣ መንጋ የይሖዋን ኃይለኛ የፍርድ መልእክት የሚያውጁትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። ምድራዊ ተስፋ ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ከቅቡዓኑ ጋር አብረው እየሠሩ ነው። በእርግጥም በኅብረት የምናከናውነው የስብከት ሥራ ሰይጣን በዓለም አቀፉ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ላይ ያለውን ሥልጣን የሚያዳክም መሆኑ ምንም አያስገርምም!

4. የአምላክ ሕዝቦች የትኛውን ሥራ ማከናወን አለባቸው? ይህን ማድረግ የሚችሉበት ብቸኛው መንገድስ ምንድን ነው?

4 የይሖዋ ሕዝቦች ይህ ሥርዓት ከመጥፋቱ በፊት ‘ምሥራቹን’ በዓለም ዙሪያ የመስበክ ከባድ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) ይህ ደግሞ ‘የተጠሙ ሁሉ የሕይወትን ውኃ በነፃ እንዲወስዱ’ መጋበዝን ይጨምራል። (ራእይ 22:17) የክርስቲያን ጉባኤ አባል እንደመሆናችን መጠን ይህን ሥራ በተሳካ ሁኔታ ማከናወን የምንችለው እንዴት ነው? እንደ አንድ አካል ‘ተገጣጥመንና’ እርስ በርስ ‘ተስማምተን’ የምንሠራ ከሆነ ብቻ ነው።—ኤፌ. 4:16

5, 6. ምሥራቹን ስንሰብክ አንድነት እንዳለን የሚታየው እንዴት ነው?

5 የመንግሥቱን ምሥራች በተቻለን መጠን ለብዙ ሰዎች ማካፈል ከፈለግን የስብከቱን ሥራ በተደራጀ መልኩ ማከናወን ይኖርብናል። ለዚህም ሲባል መመሪያዎች ይሰጡናል። በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ጉባኤዎች አማካኝነት የሚሰጠን መመሪያ ጥረታችንን አስተባብረን እንድንሠራ ያስታጥቀናል። የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ካደረግን በኋላ የመንግሥቱን መልእክት ለሰው ሁሉ ለመስበክ እንወጣለን። በአንደበታችንም ሆነ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በማበርከት ለሰዎች ምሥራቹን እናሰራጫለን። አንተስ በልዩ የአገልግሎት ዘመቻዎች እንድንካፈል የሚሰጡንን መመሪያዎች ለመታዘዝ ጥረት ታደርጋለህ? እንዲህ የምታደርግ ከሆነ በራእይ 14:6 ላይ የተገለጸው ‘በሰማይ መካከል የሚበረው መልአክ’ የያዘውን መልእክት ከሚያስተጋቡት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ምሥራቹን በኅብረት ታውጃለህ።

6 የምናከናውነው ሥራ ያለውን ድምር ውጤት በዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ላይ ማንበብ ምንኛ ያስደስታል! በተጨማሪም ለክልልም ሆነ ለብሔራት አቀፍ ስብሰባ እንዲሁም ለልዩ የክልል ስብሰባ የመጋበዣ ወረቀት ስናሰራጭ የሚኖረንን አንድነት ለማሰብ ሞክር። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ስሜት የሚቀሰቅሱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮች የምናዳምጥ ከመሆኑም ባሻገር ድራማዎችና ሠርቶ ማሳያዎች እንመለከታለን። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ክፍሎች አምላክ በሙሉ ነፍሳችን እንድናገለግለው ያቀረበልንን ፍቅራዊ ግብዣ ጎላ አድርገው ይገልጻሉ። የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓልም በመካከላችን አንድነት እንዲኖር ያደርጋል። ለአምላክ ጸጋ አድናቆት ስላለን እንዲሁም ለኢየሱስ መመሪያ ታዛዥ ስለሆንን ኒሳን 14 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ሁላችንም ይህን ዓመታዊ በዓል ለማክበር እንሰበሰባለን። (1 ቆሮ. 11:23-26) በዚህ በዓል ላይ መገኘት የሚችሉት የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ አይደሉም። የመታሰቢያው በዓል ከሚከበርበት ቀን በፊት ባሉት ሳምንታት የቻልነውን ያህል የጉባኤያችንን ክልል በመሸፈን ሌሎችም ትልቅ ቦታ በሚሰጠው በዚህ በዓል ላይ አብረውን እንዲገኙ እንጋብዛለን።

7. በኅብረት ስንሠራ ምን ማከናወን እንችላለን?

7 አንድ አንበጣ ብቻውን ሆኖ ብዙ ጉዳት ሊያደርስ አይችልም። በተመሳሳይም በግለሰብ ደረጃ የምናደርገው ጥረት እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ያለው ላይመስል ይችላል። በኅብረት ስንሠራ ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ውዳሴና ክብር ለሚገባው ለይሖዋ ትኩረት እንዲሰጡ እናደርጋለን! ይሁንና የአምላክ ሕዝቦች አንድነት እንዲኖራቸው የሚያደርገው በዚህ መንገድ መተባበራችን ብቻ አይደለም።

በጉባኤ ውስጥ የትብብር መንፈስ አሳዩ

8, 9. (ሀ) ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች አንድነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ለማስተማር ምን ምሳሌ ተጠቅሟል? (ለ) በጉባኤ ውስጥ የትብብር መንፈስ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

8 ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ጉባኤው የተደራጀ መሆን እንዳለበትና አባላቱ ‘በሁሉም ነገር ማደግ’ እንደሚያስፈልጋቸው ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ኤፌሶን 4:15, 16ን አንብብ።) በግለሰብ ደረጃ እድገት አድርገን እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ምን ይረዳናል? ጳውሎስ የሰውን አካል እንደ ምሳሌ በመጥቀስ የጉባኤው ራስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ሥር አንድነት ሊኖረን እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጿል። ሐዋርያው “አስፈላጊ የሆነውን ነገር በሚያሟላው በእያንዳንዱ መገጣጠሚያ አማካኝነት” መተባበር እንደሚያስፈልግ ተናግሯል። ልጅ አዋቂ፣ ብርቱ ደካማ ሳይል ሁላችንም ለጉባኤው አንድነትና መንፈሳዊነት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው?

9 ቁልፉ ነገር ኢየሱስ በጉባኤ ውስጥ አመራር እንዲሰጡ የሾማቸውን ሽማግሌዎች ማክበርና ለእነሱ መገዛት ነው። (ዕብ. 13:7, 17) እርግጥ እንዲህ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል። ነገር ግን አምላክ እንደሚረዳን እርግጠኛ በመሆን አመራሩን መጠየቅ እንችላለን። ቅዱስ መንፈሱ የጉባኤውን ዝግጅቶች በሙሉ ልባችን መደገፍ እንድንችል ይረዳናል። ስለዚህ የተሰጠንን አመራር መከተል ከባድ በሚሆንብን ጊዜ በትሕትና መንፈስ ተባባሪ መሆናችን ለጉባኤው አንድነት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ማሰብ ይኖርብናል። በተጨማሪም በዚህ ረገድ መተባበራችን ሁላችንም በፍቅር እንድናድግ ሊረዳን ይችላል።

10. የጉባኤ አገልጋዮች ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱት እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

10 የጉባኤ አገልጋዮች ለጉባኤው አንድነት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እጅግ ይደነቃል። እነዚህ ወንድሞች በየትኛውም የዕድሜ ክልል ቢሆኑ ሌሎችን ለማገልገል ሲሉ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ያደርጋሉ። ለምሳሌ ለአገልግሎት የሚያስፈልጉን ጽሑፎች መሟላታቸውን በመከታተል ሽማግሌዎችን ይረዳሉ። ከዚህም በተጨማሪ የመንግሥት አዳራሹን ጽዳትና ጥገና አዘውትረው ይከታተላሉ፤ እንዲሁም አዳዲስ ሰዎች ወደ ስብሰባ ሲመጡ ያስተናግዳሉ። ከእነዚህ ወንድሞች ጋር ተባብረን ስንሠራ የጉባኤው እንቅስቃሴ የተቀላጠፈ እንዲሆን አስተዋጽኦ እናበረክታለን።—ከሐዋርያት ሥራ 6:3-6 ጋር አወዳድር።

11. ወጣት ወንድሞች ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉት እንዴት ነው?

11 ብዙ የጎለመሱ ወንድሞች የጉባኤ ኃላፊነቶችን ለበርካታ ዓመታት ተሸክመው ኖረዋል። ሆኖም ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ ከዚህ በፊት የሚያደርጓቸውን ነገሮች ማከናወን እየከበዳቸው ሊመጣ ይችላል፤ እንግዲያው በዚህ ጊዜ ማስተካከያዎች ማድረግ ያስፈልጋል። ወጣት ወንድሞች በዚህ ረገድ ከፍተኛ እርዳታ ሊያበረክቱ ይችላሉ። ብዙ ተሞክሮ ባይኖራቸውም እንኳ ሥልጠና ካገኙ ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ለመቀበል ብቁ ይሆናሉ። የጉባኤ አገልጋዮች፣ ሽማግሌ ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት መጣጣራቸው እንዴት ያስደስታል! (1 ጢሞ. 3:1, 10) ወጣት ሽማግሌዎች እድገት አድርገው የወረዳ የበላይ ተመልካች በመሆን በበርካታ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችንና እህቶችን ያገለግላሉ። እነዚህ ወንድሞች በፈቃደኝነት ለሚያደርጉት ድጋፍ አመስጋኞች ልንሆን አይገባም?​—መዝሙር 110:3ን እና መክብብ 12:1ን አንብብ።

በቤተሰብ ውስጥ የትብብር መንፈስ አሳዩ

12, 13. ሁሉም የቤተሰብ አባላት የትብብር መንፈስ እንዲያሳዩ የሚረዳቸው ምንድን ነው?

12 አሁን ደግሞ በቤተሰብ ውስጥ የትብብር መንፈስ እንዲኖር ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ብዙዎች፣ በየሳምንቱ የሚደረግ ውጤታማ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም በወላጆችና በልጆች መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር እንደሚጠቅም ተገንዝበዋል። በዚህ አስደሳች ወቅት ቤተሰቡ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ ቤተሰቡ አንድነት እንዲኖረው ያስችላል። በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ወቅት ለመስክ አገልግሎት ልምምድ ማድረግ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመስበክ የታጠቁ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። ከዚህም ሌላ የአንድ ቤተሰብ አባላት ለአምላክ ፍቅር ያላቸውና የእሱን ፈቃድ ማድረግ የሚፈልጉ እንደመሆናቸው መጠን ከአምላክ ቃል ባገኟቸው ሐሳቦች ላይ መወያየታቸው እርስ በርስ እንደሚያቀራርባቸው መገመት አያዳግትም።

የቤተሰብ አምልኮ በወጣቶችና በአዋቂዎች መካከል ያለውን ትስስር ያጠናክራል (አንቀጽ 12, 15⁠ን ተመልከት)

13 ባለትዳሮች እርስ በርስ በመተባበር ለይሖዋ ውዳሴ ለማምጣት ምን ማድረግ ይችላሉ? ሁለቱም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸው ደስታና አንድነት ያስገኝላቸዋል። አብርሃምና ሣራ፣ ይስሐቅና ርብቃ እንዲሁም ሕልቃናና ሐና ለትዳር ጓደኛቸው ያላቸውን ፍቅር ገልጸዋል። እኛም የእነሱን ምሳሌ መከተል ይኖርብናል። (ዘፍ. 26:8፤ 1 ሳሙ. 1:5, 8፤ 1 ጴጥ. 3:5, 6) ይህም ከትዳር ጓደኛችን ጋር አንድነት እንዲኖረን የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ በሰማይ ወዳለው አባታችን ይበልጥ እንድንቀርብ ያስችለናል።—መክብብ 4:12ን አንብብ።

14. የትዳር ጓደኛችሁ ይሖዋን የማያገለግል ቢሆን ትዳራችሁን ለማጠናከር ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

14 ክርስቲያኖች ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ ከመጠመድ መራቅ አለባቸው። (2 ቆሮ. 6:14) በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ ስለሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንስ ምን ማለት ይቻላል? አንዳንዶች እውነትን የሰሙት ትዳር ከመሠረቱ በኋላ በመሆኑ የትዳር ጓደኛቸው የይሖዋ ምሥክር ላይሆን ይችላል። ይሁንና በዚህም ሁኔታ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ ቤተሰቡ አንድነት እንዲኖረው ይረዳል። ይህም ክርስቲያናዊ አቋምን ሳያላሉ አቅም በፈቀደ መጠን የትብብር መንፈስ ማሳየትን ያካትታል። እርግጥ ይህ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም እንዲህ ማድረግ የሚያስገኘውን ጥቅም አስብ። በሌላ በኩል አንደኛው የትዳር ጓደኛ ከጉባኤ በሚርቅበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ ከባድ ሊሆን ይችላል። ሜሪ የተባለች እህት እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟታል። እሷና ባለቤቷ ዴቪድ አንድ ላይ ይሖዋን ያገለግሉ ነበር። ሆኖም ከ25 ዓመታት ገደማ በፊት ዴቪድ ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች መሄድ አቆመ። ሜሪ ግን በታማኝነት በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ መገኘቷን ቀጠለች፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ታደርግ ነበር፤ በመሆኑም ስድስት ልጆቻቸውን መጽሐፍ ቅዱስ አስተምራለች። ልጆቹ ራሳቸውን ችለው ከቤት ሲወጡ ሜሪ ከፍተኛ የብቸኝነት ስሜት አደረባት። ከጊዜ በኋላ ግን ዴቪድ ሜሪ የምታስቀምጥለትን መጽሔቶች ማንበብ ጀመረ። ውሎ አድሮ እንደገና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ፤ በዚህ ጊዜ ስድስት ዓመት የሆነው የልጅ ልጁ ቦታ ይዞ ይጠብቀው ነበር። ዴቪድ ጉባኤ ሳይመጣ ከቀረ ይህ ልጅ “አያቴ፣ ዛሬ ጉባኤ ስላልመጣህ ቅር ብሎኛል” ይለዋል። በአሁኑ ጊዜ ዴቪድ ይሖዋን በደስታ እያገለገለ ነው፤ ሜሪም ከባለቤቷ ጋር ይሖዋን በማገልገሏ ደስተኛ ናት።

15. በዕድሜ የጎለመሱ ባለትዳሮች ከእነሱ በዕድሜ ለሚያንሱ ባለትዳሮች ድጋፍ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

15 ሰይጣን በቤተሰቦች ላይ ጥቃት እየሰነዘረ በመሆኑ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ በትዳራቸው ውስጥ ጥሩ የትብብር መንፈስ ማሳየታቸው አስፈላጊ ነው። በትዳር ዓለም የቆያችሁት ለምንም ያህል ዓመታት ቢሆን ትዳራችሁን ለማጠናከር በግለሰብ ደረጃ በቃልም ሆነ በተግባር ምን ማድረግ እንደምትችሉ ቆም ብላችሁ አስቡ። በዚህ ረገድ በዕድሜ የጎለመሱ የጉባኤው አባላት ከእነሱ በዕድሜ ለሚያንሱት ድጋፍ ማድረግ፣ ለምሳሌ አንዳንድ ጊዜ ወጣት ባለትዳሮች በቤተሰብ አምልኳቸው ላይ እንዲገኙ ቤታቸው መጋበዝ ይችላሉ። ወጣት ባለትዳሮች ከእናንተ ጋር ጊዜ ሲያሳልፉ አንድ ሰው በትዳር ውስጥ ምንም ያህል ረጅም ጊዜ ቢኖር ፍቅርና አንድነት ትልቅ ዋጋ እንዳላቸው ሊያስተውሉ ይችላሉ።—ቲቶ 2:3-7

‘ወደ ይሖዋ ተራራ እንውጣ’

16, 17. አንድነት ያላቸው የአምላክ አገልጋዮች የትኛውን ዘመን በጉጉት ይጠባበቃሉ?

16 በጥንት ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን ዓመታዊ በዓል በሚከበርበት ወቅት ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ተገኝተው ይሖዋን ሲያወድሱ ይታይህ። ለጉዞ መዘጋጀት፣ በጉዞ ወቅት እርስ በርስ መረዳዳት ከዚያም ቤተ መቅደስ ውስጥ ይሖዋን በአንድነት ማምለክ ነበረባቸው። ይህ ሁሉ ትብብር የሚጠይቅ ነገር ነው። (ሉቃስ 2:41-44) እኛም ወደ አዲሱ ዓለም በምናደርገው ጉዞ ላይ እርስ በርስ መስማማትና መተባበር ያስፈልገናል። ይህ ደግሞ ቀጣይ የሆነና የታሰበበት ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። ለዚህ ጉዳይ የበለጠ ትኩረት መስጠት እንዳለብህ ይሰማሃል?

17 እስቲ ስለሚጠብቁን በረከቶች አስብ! በአሁኑ ጊዜ እንኳ በዓለም ውስጥ ከሚታየው መከፋፈልና ግራ መጋባት ተገላግለናል። ኢሳይያስና ሚክያስ የተናገሩት ትንቢት ሲፈጸም እየተመለከትን ነው፤ የአምላክ ሕዝቦች አንድ ላይ ሆነው “ወደ ይሖዋ ተራራ” እየወጡ ነው። (ኢሳ. 2:2-4፤ ሚክያስ 4:2-4ን አንብብ።) በእርግጥም “በዘመኑ መጨረሻ” ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ እጅግ የላቀ ነው። ወደፊት ደግሞ የሰው ዘር በሙሉ እርስ በርስ ተስማምቶና ተባብሮ ሲኖር የምናገኘው ደስታና እርካታ ምንኛ ታላቅ ይሆናል!