በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልታደርገው የሚገባ ጠቃሚ ንጽጽር

ልታደርገው የሚገባ ጠቃሚ ንጽጽር

የክርስትና እምነት ተከታይ ነህ? በዓለም ዙሪያ ከሁለት ቢሊዮን የሚበልጡ ሰዎች የክርስቶስ ተከታይ እንደሆኑ ይናገራሉ። በዛሬው ጊዜ ክርስቲያን ተብለው የሚጠሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሃይማኖቶች ያሉ ቢሆንም እርስ በርሱ በሚጋጭ መሠረተ ትምህርትና አመለካከት ተከፋፍለዋል። በመሆኑም የምታምንባቸው ነገሮች ክርስቲያን እንደሆኑ የሚናገሩ ሌሎች ሰዎች ከሚያምኑባቸው ነገሮች በጣም የተለዩ ሊሆኑ ይችላሉ። የምታምንበት ነገር ለውጥ ያመጣል? አዎ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን ክርስትና መከተል የምትፈልግ ከሆነ የምታምንበት ነገር ለውጥ ያመጣል።

የጥንቶቹ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች “ክርስቲያኖች” ተብለው ይጠሩ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 11:26) በወቅቱ አንድ የክርስትና እምነት ብቻ ስለነበር ተለይተው የሚታወቁባቸው ሌሎች ስሞች አላስፈለጓቸውም። ክርስቲያኖች፣ የክርስትና መሥራች የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርቶችና መመሪያዎች በአንድነት ይከተሉ ነበር። የአንተ ሃይማኖትስ በዚህ ረገድ እንዴት ነው? ቤተ ክርስቲያንህ ክርስቶስ ያስተማረውንና የጥንቶቹ የክርስቶስ ተከታዮች ያምኑበት የነበረውን ነገር እንደሚያስተምር ታምናለህ? ይህን በእርግጠኝነት ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? ይህን ማወቅ የምትችለው መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ሚዛን አድርገህ በመጠቀም ብቻ ነው።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ቅዱሳን መጻሕፍት የአምላክ ቃል እንደሆኑ ስለሚያምን ለእነሱ ጥልቅ አክብሮት ነበረው። ለወጎችና ለልማዶች ሲሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች የሚበርዙ ሰዎችን አይደግፍም ነበር። (ማርቆስ 7:9-13) ከዚህ አንጻር የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች ለእምነታቸው መሠረት የሚያደርጉት መጽሐፍ ቅዱስን ነው ብለን መደምደም እንችላለን። ስለዚህ እያንዳንዱ ክርስቲያን ‘የቤተ ክርስቲያኔ ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል?’ ብሎ ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል። ይህን ጥያቄ ለመመለስ ቤተ ክርስቲያንህ የሚያስተምረውን ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ለምን አታነጻጽርም?

ኢየሱስ፣ ለአምላክ የምናቀርበው አምልኮ በእውነት ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት ተናግሯል፤ እውነት የሚገኘው ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። (ዮሐንስ 4:24፤ 17:17) በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ መዳናችን የተመካው “የእውነትን ትክክለኛ እውቀት” በማግኘታችን ላይ እንደሆነ ተናግሯል። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) ስለዚህ እምነታችን በትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። ምክንያቱም መዳናችን ራሱ የተመካው በዚህ ላይ ነው!

የምናምንባቸውን ነገሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ማነጻጸር የምንችለው እንዴት ነው?

በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረቡትን ስድስት ጥያቄዎች እንድትመለከትና መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ እንድታስተውል እንጋብዝሃለን። የቀረቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንብባቸው፤ በመልሶቹም ላይ አሰላስል። ከዚያም ‘ቤተ ክርስቲያኔ የሚያስተምራቸው ትምህርቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሲነጻጸሩ እንዴት ናቸው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚገኘው አጭር ጥያቄና መልስ እጅግ ጠቃሚ የሆነ ንጽጽር እንድታደርግ ሊረዳህ ይችላል። ቤተ ክርስቲያንህ የሚያስተምራቸውን ሌሎች ትምህርቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ማነጻጸር ትፈልጋለህ? የይሖዋ ምሥክሮች ግልጽ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንድትመረምር ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው። ታዲያ ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱን መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ እንዲያስተምርህ ለምን አትጠይቀውም? ወይም ደግሞ jw.org የተባለውን ድረ ገጻችንን መጎብኘት ትችላለህ።