በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ”

“ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ”

“ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ . . . እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”—ማቴ. 28:19, 20

መዝሙሮች፦ 141, 97

1, 2. ኢየሱስ በማቴዎስ 24:14 ላይ የተናገረው ሐሳብ የትኞቹን ጥያቄዎች ያስነሳል?

የይሖዋ ምሥክሮችን የሚደግፉም ሆነ አምርረው የሚቃወሙ ሰዎች ሊክዱ የማይችሉት አንድ ሐቅ አለ፤ ይኸውም የይሖዋ ምሥክሮች በስብከቱ ሥራቸው በቡድን ደረጃ በስፋት የታወቁ መሆናቸው ነው። በምናምንባቸው ነገሮች ባይስማሙም በምናከናውነው ሥራ እንደሚያከብሩን የሚናገሩ ሰዎች በአገልግሎት ላይ አጋጥመውህ ያውቁ ይሆናል። ኢየሱስ የመንግሥቱ ምሥራች በመላው ምድር እንደሚሰበክ አስቀድሞ እንደተናገረ እናውቃለን። (ማቴ. 24:14) ይሁንና ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት፣ በምናከናውነው ሥራ አማካኝነት እየፈጸምን እንደሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ሥራ የምንሠራው እኛ እንደሆንን ማሰብ ድፍረት ይሆንብናል?

2 ወንጌሉን ወይም ምሥራቹን እየሰበኩ እንዳሉ የሚሰማቸው በርካታ ሃይማኖታዊ ቡድኖች አሉ። አብዛኛውን ጊዜ ግን የሚያከናውኑት የስብከት ሥራ ስለ ራሳቸው ተሞክሮ ምሥክርነት ከመስጠት፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከመስበክ አሊያም በመገናኛ ብዙኃን ይኸውም በቴሌቪዥን ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት ፕሮግራም ከማቅረብ ያለፈ አይደለም። ሌሎች ደግሞ የሚያከናውኗቸውን የበጎ አድራጎት ሥራዎች አሊያም በሕክምና እና በትምህርት መስኮች የሚያደርጉትን እርዳታ ይጠቅሳሉ። ለመሆኑ እነዚህን ነገሮች ስላደረጉ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸውን ትእዛዝ እየፈጸሙ ነው ማለት ይቻላል?

3. በማቴዎስ 28:19, 20 መሠረት የኢየሱስ ተከታዮች የትኞቹን አራት ነገሮች ማድረግ አለባቸው?

3 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምንም ጥረት ሳያደርጉ ሰዎች ወደ እነሱ እስኪመጡ ድረስ ይጠብቃሉ ማለት ነው? በፍጹም! ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ . . . እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።” (ማቴ. 28:19, 20) ይህን ለማድረግ አራት ነገሮች ያስፈልጋሉ። ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ማድረግ፣ ማጥመቅና ማስተማር ያስፈልገናል፤ ይሁንና በቅድሚያ ሊከናወን የሚገባው ነገር ምንድን ነው? ኢየሱስ “ሂዱ” ብሏል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ይህን ትእዛዝ በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፦ “እያንዳንዱ አማኝ፣ መንገድ ተሻግሮም ይሁን ውቅያኖስ አቋርጦ ‘መሄድ’ አለበት።”—ማቴ. 10:7፤ ሉቃስ 10:3

4. “ሰው አጥማጆች” መሆን ምን ይጠይቃል?

4 ኢየሱስ ይህን ትእዛዝ የሰጠው ተከታዮቹ ምሥራቹን በተናጠል እንዲሰብኩ አስቦ ነው? ወይስ በቡድን ተደራጅተው የስብከት ዘመቻ እንዲያካሂዱ? አንድ ግለሰብ ወደ “ሁሉም ብሔራት” መሄድ ስለማይችል ይህ ሥራ መከናወን ያለበት አንድ ላይ በተደራጁ ብዙ ሰዎች ነው። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን “ሰው አጥማጆች” እንዲሆኑ መጋበዙ ይህን ይጠቁማል። (ማቴዎስ 4:18-22ን አንብብ።) ኢየሱስ እዚህ ላይ የጠቀሰው፣ አንድ ሰው ዓሣዎችን ለመያዝ መንጠቆ ላይ ምግብ ካንጠለጠለ በኋላ ዓሣዎቹ መጥተው ምግቡን እስኪወስዱ ድረስ ለብቻው ቁጭ ብሎ የሚጠብቅበትን ዓይነት ዓሣ የማጥመድ ዘዴ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ የተናገረው ብዙ ሰዎች አንድ ላይ ተቀናጅተው መረብ በመጠቀም ስለሚያከናውኑት ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ዓሣ የማጥመድ ሥራ ነው።—ሉቃስ 5:1-11

5. ለየትኞቹ አራት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያስፈልገናል? ለምንስ?

5 በዛሬው ጊዜ ምሥራቹን በመስበክ፣ ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት እየፈጸሙ ያሉት እነማን እንደሆኑ ለማወቅ ለሚከተሉት አራት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያስፈልገናል፦

  • የሚሰበከው መልእክት ምን መሆን አለበት?

  • ሥራውን እንዲያከናውኑ የሚያነሳሳቸው ምክንያት ምን ሊሆን ይገባል?

  • የትኞቹን ዘዴዎች መጠቀም ይኖርባቸዋል?

  • ሥራው ምን ያህል ስፋት ይኖረዋል? ለምን ያህል ጊዜስ ይቆያል?

የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ፣ ይህን ሕይወት አድን ሥራ የሚሠሩት እነማን እንደሆኑ ለማወቅ የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ በዚህ ሥራ በታማኝነት ለመጽናት ያደረግነውን ውሳኔ ያጠናክርልናል።—1 ጢሞ. 4:16

የሚሰበከው መልእክት ምን መሆን አለበት?

6. ኢየሱስ ያዘዘውን መልእክት የሚሰብኩት የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን እርግጠኛ መሆን የምትችለው ለምንድን ነው?

6 ሉቃስ 4:43ን አንብብ። ኢየሱስ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች” ሰብኳል፤ ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሥራ እንዲሠሩ ይጠብቅባቸዋል። ታዲያ ‘በሁሉም ብሔራት’ ለሚገኙ ሰዎች ይህን መልእክት እየሰበከ ያለው የትኛው ቡድን ነው? መልሱ ግልጽ ነው፤ ይህን ሥራ የሚያከናውኑት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው። አንዳንድ ተቃዋሚዎችም እንኳ በዚህ ይስማማሉ። ለምሳሌ ሚስዮናዊ የሆነ አንድ ቄስ፣ በብዙ አገሮች እንደኖረ ለአንድ ወንድም ከነገረው በኋላ በእያንዳንዱ አገር ያገኛቸውን የይሖዋ ምሥክሮች ‘የምትሰብኩት መልእክት ምንድን ነው?’ ብሎ እንደጠየቃቸው ገለጸለት። ታዲያ ምን ምላሽ አገኘ? ቄሱ “ሁሉም በጣም ሞኞች ከመሆናቸው የተነሳ ‘የአምላክን መንግሥት ምሥራች’ በማለት አንድ ዓይነት መልስ ሰጥተውኛል” ብሏል። እነዚያ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያለ መልስ መስጠታቸው ግን “ሞኞች” መሆናቸውን የሚያሳይ ሳይሆን ከእውነተኛ ክርስቲያኖች የሚጠበቀው አንድነት እንዳላቸው የሚጠቁም ነው። (1 ቆሮ. 1:10) በተጨማሪም የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ በተባለው መጽሔት ውስጥ ያለውን መልእክት እንደሚያስተጋቡ የሚያሳይ ነው። ይህ መጽሔት በ254 ቋንቋዎች የሚገኝ ሲሆን እያንዳንዱ እትም በአማካይ ወደ 59 ሚሊዮን በሚጠጉ ቅጂዎች ይታተማል፤ በመሆኑም መጽሔቱ በዓለም ላይ በስፋት በመሰራጨት ረገድ ተወዳዳሪ የለውም።

7. የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ኢየሱስ ያዘዘውን መልእክት እየሰበኩ እንዳልሆነ እንዴት እናውቃለን?

7 የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ስለ አምላክ መንግሥት እየሰበኩ አይደሉም። ስለ መንግሥቱ ቢናገሩ እንኳ ብዙዎቹ፣ በክርስቲያኖች ልብ ውስጥ ያለ ስሜት ወይም ሁኔታ እንደሆነ አድርገው ይገልጹታል። (ሉቃስ 17:21) የአምላክ መንግሥት ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ የተሾመበት በሰማይ የሚገኝ መስተዳድር እንደሆነ፣ ለሰው ልጆች ችግሮች በሙሉ መፍትሔ እንደሚያመጣ እንዲሁም በቅርቡ ክፋትን ሁሉ ከምድር እንደሚያስወግድ ሰዎች እንዲገነዘቡ አያደርጉም። (ራእይ 19:11-21) ከዚህ ይልቅ ኢየሱስን የሚያስታውሱት በገና እና በፋሲካ በዓል ወቅት ነው። ኢየሱስ የምድር ንጉሥ ሲሆን ምን እንደሚያከናውን የሚያውቁት ነገር ያለ አይመስልም። እነዚህ ቀሳውስት ሊሰብኩት የሚገባውን መልእክት ካላወቁ የሚሰብኩበት ምክንያት ቢጠፋቸው ምን ይገርማል?

ሥራውን እንዲያከናውኑ የሚያነሳሳቸው ምክንያት ምን ሊሆን ይገባል?

8. የስብከቱ ሥራ የሚከናወንበት ዓላማ ምን ሊሆን አይገባም?

8 የስብከቱን ሥራ እንዲያከናውኑ የሚያነሳሳቸው ምክንያት ምን ሊሆን ይገባል? ዓላማው ገንዘብ መሰብሰብና የተንቆጠቆጡ ሕንፃዎችን መገንባት መሆን የለበትም። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን “በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ” ብሏቸዋል። (ማቴ. 10:8) በአምላክ ቃል ሊነገድ አይገባም። (2 ቆሮ. 2:17 ግርጌ) መልእክቱን የሚሰብኩ ሰዎች ከሚያከናውኑት ሥራ የግል ጥቅም ለማግኘት መሞከር የለባቸውም። (የሐዋርያት ሥራ 20:33-35ን አንብብ።) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ግልጽ መመሪያ የያዘ ቢሆንም አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ይበልጥ ትኩረት የሚያደርጉት ገንዘብ በመሰብሰብ ላይ ነው። ደሞዝ የሚከፈላቸው ቀሳውስትና በርካታ ተቀጣሪ ሠራተኞች ስላሏቸው እነዚህን ለማስተዳደር ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። አብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና መሪዎችም ይህ ነው የማይባል ሀብት አጋብሰዋል።—ራእይ 17:4, 5

9. የይሖዋ ምሥክሮች የስብከቱን ሥራ የሚያከናውኑት በትክክለኛው ዓላማ ተነሳስተው እንደሆነ ያሳዩት እንዴት ነው?

9 የገንዘብ መዋጮ ከመሰብሰብ ጋር በተያያዘ የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ምን ይመስላል? ሥራቸው የሚደገፈው በፈቃደኝነት በሚደረግ መዋጮ ነው። (2 ቆሮ. 9:7) በመንግሥት አዳራሾቻቸውም ሆነ በትላልቅ ስብሰባዎቻቸው ላይ ሙዳየ ምጽዋት አይዞርም። ያም ቢሆን ግን ባለፈው ዓመት ብቻ የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን በመስበክ 1.93 ቢሊዮን ሰዓት አሳልፈዋል፤ እንዲሁም በየወሩ ከዘጠኝ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን በነፃ መጽሐፍ ቅዱስን ያስተምራሉ። የሚያስገርመው ደግሞ ለሥራቸው ደሞዝ የማይከፈላቸው ከመሆኑም ሌላ ወጪያቸውን የሚሸፍኑት ራሳቸው ናቸው፤ ይህን የሚያደርጉትም በደስታ ነው። አንድ ምሁር፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑትን ሥራ በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፦ “ዋናው ግባቸው መስበክና ማስተማር ነው። . . . ቀሳውስት የሏቸውም፤ ይህም ወጪያቸውን በእጅጉ ይቀንሰዋል።” ታዲያ ይህን ሥራ ለማከናወን የሚያነሳሳን ምክንያት ምንድን ነው? በአጭር አነጋገር፣ ይህን ሥራ በፈቃዳችን የምናከናውነው ይሖዋንና ሰዎችን ስለምንወድ ነው። እንዲህ ያለ የፈቃደኝነት መንፈስ በማሳየት በመዝሙር 110:3 ላይ ያለው ትንቢት እንዲፈጸም እናደርጋለን። (ጥቅሱን አንብብ።)

የትኞቹን ዘዴዎች መጠቀም ይኖርባቸዋል?

ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ እንሰብካለን (አንቀጽ 10ን ተመልከት)

10. ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ለመስበክ የትኞቹን ዘዴዎች ተጠቅመዋል?

10 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ምሥራቹን ለመስበክ የትኞቹን ዘዴዎች ተጠቅመዋል? ምሥራቹን ለማድረስ፣ ሰዎች በብዛት ወደሚገኙባቸው ቦታዎችና ከቤት ወደ ቤት ሄደዋል። የስብከቱ ሥራ፣ ከቤት ወደ ቤት በመሄድ መልእክቱን መስማት የሚገባውን ሰው መፈለግን ይጨምራል። (ማቴ. 10:11፤ ሉቃስ 8:1፤ ሥራ 5:42፤ 20:20) እንዲህ ያለው የተደራጀ አሠራር ያለ አድልዎ ለመመሥከር ያስችላል።

11, 12. ምሥራቹን ከመስበክ ጋር በተያያዘ ሕዝበ ክርስትና የምታደርገው ጥረት የይሖዋ ሕዝቦች ከሚያከናውኑት ሥራ ጋር ሲነጻጸር ምን ይመስላል?

11 የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በዚህ ረገድ እንዴት ናቸው? አብዛኛውን ጊዜ ምዕመናኑ፣ የስብከቱን ሥራ ደሞዝ ለሚከፈላቸው ቀሳውስት መተዉን ይመርጣሉ። ቀሳውስቱ ደግሞ “ሰው አጥማጆች” ከመሆን ይልቅ ይበልጥ የሚያሳስባቸው ያላቸውን “ዓሣ” መጠበቅ ይመስላል። እውነት ነው፣ አንዳንድ ቀሳውስት አልፎ አልፎ ወንጌሉን ለመስበክ ጥረት ያደርጉ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ በ2001 መጀመሪያ አካባቢ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዳግማዊ ጆን ፖል በጻፉት ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “አዲስ የወንጌላዊነት ሥራ እንዲካሄድ የቀረበውን ጥሪ ባለፉት ዓመታት በተለያየ ጊዜ ደጋግሜ አሰምቻለሁ። አሁንም በድጋሚ ይህን ጥሪ አቀርባለሁ፤ . . . ‘ምሥራቹን ባልሰብክ ወዮልኝ!’ ብሎ በግለት የተናገረው የሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት ቅንዓት በውስጣችን እንዲያንሰራራ ማድረግ ይኖርብናል።” ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አክለውም ይህ ተልእኮ “‘ልዩ ሥልጠና ላገኙ’ የተወሰኑ ሰዎች ሊተው እንደማይገባ ከዚህ ይልቅ የአምላክ ሕዝብ አባላት በሙሉ ኃላፊነት” እንደሆነ ገልጸዋል። ሆኖም ለዚህ ጥሪ ምላሽ የሰጡት ምን ያህል ናቸው?

12 የይሖዋ ምሥክሮችስ በዚህ ረገድ ምን ታሪክ አስመዝግበዋል? ኢየሱስ ከ1914 ጀምሮ ንጉሥ ሆኖ እየገዛ መሆኑን የሚሰብኩት እነሱ ብቻ ናቸው። ኢየሱስ ባዘዘው መሠረት ለስብከቱ ሥራ ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። (ማር. 13:10) ፒለርስ ኦቭ ፌዝ—አሜሪካን ኮንግርጌሽንስ ኤንድ ዜር ፓርትነርስ የተባለው መጽሐፍ “የይሖዋ ምሥክሮች ከማንኛውም ነገር በላይ ትኩረት የሚሰጡት ለሚስዮናዊነቱ ሥራ ነው” ብሏል። የዚህ መጽሐፍ ደራሲ አንድ የይሖዋ ምሥክር የተናገረውን በመጥቀስ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የተራበ፣ ብቸኝነት ያጠቃውና የታመመ ሰው ሲያገኙ ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ፤ . . . ይሁንና ተቀዳሚ ሥራቸው፣ ስለ መጪው የዓለም ፍጻሜና ለመዳን ስለሚያስፈልገው ነገር የሚገልጸውን መንፈሳዊ መልእክት ማዳረስ መሆኑን ፈጽሞ አይዘነጉም።” የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የተጠቀሙባቸውን ዘዴዎች በመከተል ይህን መልእክት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል።

ሥራው ምን ያህል ስፋት ሊኖረውና ለምን ያህል ጊዜ ሊከናወን ይገባል?

13. የስብከቱ ሥራ ምን ያህል ስፋት ሊኖረው ይገባል?

13 ኢየሱስ ምሥራቹ “በመላው ምድር” እንደሚሰበክ ሲናገር ሥራው ምን ያህል ስፋት እንደሚኖረው ገልጿል። (ማቴ. 24:14) ተከታዮቹ፣ ደቀ መዛሙርት የሚያደርጉት “ከሁሉም ብሔራት” የተውጣጡ ሰዎችን ነው። (ማቴ. 28:19, 20) በመሆኑም ሥራው መካሄድ ያለበት በዓለም አቀፍ ደረጃ ነው።

14, 15. የይሖዋ ምሥክሮች በሚያከናውኑት ሥራ ስፋት ረገድ ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት እንደፈጸሙ የሚያሳዩ ምን ማስረጃዎች አሉ? (በመግቢያው ላይ ያሉትን ፎቶግራፎች ተመልከት።)

14 የይሖዋ ምሥክሮች የስብከቱ ሥራ ከሚከናወንበት ስፋት ጋር በተያያዘ ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት እንዴት እንደፈጸሙ መረዳት እንድንችል አንዳንድ ነጥቦችን እስቲ እንመልከት። በዩናይትድ ስቴትስ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ውስጥ ወደ 600,000 የሚጠጉ ቀሳውስት አሉ፤ በዚህች አገር 1,200,000 ገደማ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ። የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዙሪያ ያሏት ቀሳውስት ከ400,000 ብዙም አይበልጡም። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን የመንግሥቱን ስብከት ሥራ የሚያከናውኑት የይሖዋ ምሥክሮች ምን ያህል እንደሆኑ ደግሞ እንመልከት። በዓለም ዙሪያ በ240 አገሮች የሚገኙ ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ ፈቃደኛ አገልጋዮች ለሰዎች ምሥራቹን ይሰብካሉ። እንዴት ያለ አስደናቂ ሥራ እያከናወኑ ነው! ይህም ለይሖዋ ውዳሴና ክብር ያመጣል።—መዝ. 34:1፤ 51:15

15 የይሖዋ ምሥክሮች መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ምሥራቹን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ ይፈልጋሉ። በዚህም የተነሳ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በመተርጎምና በማተም ረገድ የምናከናውነው ሥራ ተወዳዳሪ የለውም። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መጻሕፍትን፣ መጽሔቶችን፣ ትራክቶችን እንዲሁም የትላልቅ ስብሰባዎችና የመታሰቢያው በዓል መጋበዣዎችን በነፃ ስናሰራጭ ቆይተናል። ከ700 በሚበልጡ ቋንቋዎች በርካታ ጽሑፎችን አዘጋጅተናል። አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ከ130 በሚበልጡ ቋንቋዎች ከ200 ሚሊዮን ቅጂዎች በላይ ተዘጋጅቷል። ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ 4.5 ቢሊዮን የሚጠጉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን አዘጋጅተናል። ሕጋዊ ድረ ገጻችን ላይ መንፈሳዊ ምግብ ከ750 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል። እንዲህ ያለ ሥራ የሚያከናውን ሌላ ሃይማኖታዊ ቡድን አለ?

16. የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ መንፈስ ድጋፍ እንዳላቸው እንዴት እናውቃለን?

16 አስቀድሞ የተነገረው የስብከት ሥራ የሚቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው? ኢየሱስ ይህ ዓለም አቀፋዊ የስብከት ሥራ በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥም እንደሚከናወንና ‘ከዚያም መጨረሻው እንደሚመጣ’ ተናግሯል። ታሪካዊ በሆኑት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ምሥራቹን እየሰበከ ያለ ሌላ ሃይማኖታዊ ቡድን አለ? በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው አንዳንድ ሰዎች “መንፈስ ቅዱስ ያለን እኛ ነን፤ ሥራውን የምታከናውኑት ግን እናንተ ናችሁ” ይሉናል። ይሁን እንጂ በሥራው በጽናት መቀጠላችን የአምላክ መንፈስ እንዳለን የሚያሳይ ማስረጃ አይደለም? (ሥራ 1:8፤ 1 ጴጥ. 4:14) አንዳንድ ሃይማኖታዊ ቡድኖች የይሖዋ ምሥክሮች አዘውትረው የሚያከናውኑትን ሥራ ለመሥራት የሞከሩባቸው ጊዜያት አሉ፤ ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ ጥረታቸው ውጤታማ አልሆነም። ሌሎች ደግሞ በሚስዮናዊነት ሥራ ለተወሰነ ጊዜ ቢሳተፉም ብዙም ሳይቆይ ወደ ወትሮው ኑሯቸው ይመለሳሉ። ከቤት ወደ ቤት ለመሄድ የሚሞክሩም አሉ፤ ሆኖም የሚሰብኩት ስለ ምንድን ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ እነዚህ ሰዎች ክርስቶስ የጀመረውን ሥራ እያከናወኑ እንዳልሆኑ በግልጽ ያሳያል።

በዛሬው ጊዜ ምሥራቹን እየሰበኩ ያሉት እነማን ናቸው?

17, 18. (ሀ) በዛሬው ጊዜ የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበኩ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ሥራ መቀጠል የቻልነው ለምንድን ነው?

17 ታዲያ በዛሬው ጊዜ የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበኩ ያሉት እነማን ናቸው? “የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው!” ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን። ይህን ያህል እርግጠኞች መሆን የቻልነው ለምንድን ነው? ትክክለኛውን መልእክት ይኸውም የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበክን ስለሆነ ነው። መልእክቱን ለመስበክ ወደ ሰዎች ስለምንሄድ ትክክለኛውን ዘዴ እየተጠቀምን ነው። በተጨማሪም የስብከቱን ሥራ የምናከናውነው በትክክለኛው ዓላማ ይኸውም በፍቅር ተነሳስተን እንጂ የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ብለን አይደለም። በሁሉም ብሔራት ውስጥ ለሚገኙና የተለያዩ ቋንቋዎች ለሚናገሩ ሰዎች ስለምንሰብክ ሥራችንን በተቻለን መጠን በስፋት እያከናወንን ነው። ከዚህም ሌላ ዓመት አልፎ ዓመት ቢተካም መጨረሻው እስኪመጣ ድረስ ሳንታክት ይህን ሥራ እናከናውናለን።

18 የአምላክ ሕዝቦች አሁን ባለንበት ታሪካዊ ወቅት እያከናወኑ ያሉት ሥራ በእርግጥም በጣም የሚያስደንቅ ነው! ይሁንና ይህ ሁሉ ሊከናወን የቻለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “እሱ ደስ ለሚሰኝበት ነገር ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ለተግባር እንድትነሳሱ በማድረግ ኃይል የሚሰጣችሁ አምላክ ነው” በማለት መልሱን ሰጥቶናል። (ፊልጵ. 2:13) እንግዲያው አፍቃሪው አባታችን በሚሰጠን ኃይል እየታገዝን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረጋችንንና አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ መፈጸማችንን እንቀጥል።—2 ጢሞ. 4:5