በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውሳኔ የምታደርጉት እንዴት ነው?

ውሳኔ የምታደርጉት እንዴት ነው?

“የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ።”—ኤፌ. 5:17

መዝሙሮች፦ 69, 57

1. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ሕጎች የትኞቹ ናቸው? እነዚህን ሕጎች መታዘዛችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ቀጥተኛ የሆኑ በርካታ መመሪያዎችን ሰጥቶናል። ለምሳሌ የፆታ ብልግናን፣ የጣዖት አምልኮን፣ ስርቆትንና ስካርን ያወግዛል። (1 ቆሮ. 6:9, 10) በተጨማሪም የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለደቀ መዛሙርቱ የሚከተለውን ከባድ ሆኖም አስደሳች ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል፦ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው። እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴ. 28:19, 20) በእርግጥም መለኮታዊ ሕጎችና ትእዛዛት ለእኛ ጥበቃ ሆነውልናል! እነዚህን መመሪያዎች መታዘዛችን ለራሳችን ያለን አክብሮት እንዲጨምር፣ ጥሩ ጤንነት እንዲኖረንና ቤተሰባችን ይበልጥ ደስተኛ እንዲሆን አድርጓል። በስብከቱ ሥራ እንድንካፈል የተሰጠንን ትእዛዝ ጨምሮ የይሖዋን መመሪያዎች በሙሉ በታማኝነት መታዘዛችን ከሁሉም በላይ የእሱን ሞገስና በረከት አስገኝቶልናል።

2, 3. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥመንን እያንዳንዱን ጉዳይ አስመልክቶ ሕግ የማይሰጠው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመለከታለን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

2 ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ ቀጥተኛ መመሪያ የማይሰጥባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ፣ ለክርስቲያኖች ተገቢ የሆነው አለባበስ ምን ዓይነት እንደሆነ የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ይህ የይሖዋን ጥበብ የሚያሳይ ነው የምንለው ለምንድን ነው? ሰዎች ከአለባበስ ጋር በተያያዘ ያላቸው ባሕል ከቦታ ወደ ቦታ ይለያያል፤ እንዲሁም በየጊዜው ይለዋወጣል። መጽሐፍ ቅዱስ ተገቢውን አለባበስና አጋጌጥ በተመለከተ ዝርዝር መመሪያዎችን ይዞ ቢሆን ኖሮ እነዚህ መመሪያዎች አሁን ጊዜ ያለፈባቸው ይሆኑ ነበር። በተመሳሳይም የአምላክ ቃል አንድ ክርስቲያን ከሥራ፣ ከጤና አጠባበቅና ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ የሚያደርጋቸውን ምርጫዎች በተመለከተ ዝርዝር መመሪያዎችን የማይሰጠው ለዚህ ነው። በመሆኑም ግለሰቦችም ሆኑ የቤተሰብ ራሶች በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የራሳቸውን ውሳኔ ማድረግ ይችላሉ።

3 በሕይወታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የምናደርገው ውሳኔ ለውጥ ያመጣል? የመጽሐፍ ቅዱስን ሕግ እስካልጣስን ድረስ የምናደርገው ማንኛውም ውሳኔ በሰማይ በሚኖረው አባታችን ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል ማለት ነው? አንድን ጉዳይ አስመልክቶ ቀጥተኛ ሕግ በማይኖርበት ጊዜ ይሖዋን የሚያስደስት ውሳኔ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

የምናደርገው ውሳኔ ለውጥ ያመጣል?

4, 5. የምናደርጋቸው ውሳኔዎች በእኛም ሆነ በሌሎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉት እንዴት ነው?

4 አንዳንዶች፣ የፈለግነውን ውሳኔ ብናደርግ ምንም ለውጥ አያመጣም የሚል አመለካከት አላቸው። ይሁንና ይሖዋን የሚያስደስትና ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ለማድረግ ይሖዋ ባስጻፈው በቃሉ ውስጥ የሚገኙትን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች መመርመር ብሎም ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ደምን አስመልክቶ የሰጠውን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ አለብን። (ዘፍ. 9:4፤ ሥራ 15:28, 29) ጸሎት፣ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኙ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ሕጎች ጋር የሚስማማ ውሳኔ እንድናደርግ ይረዳናል።

5 በሕይወታችን ውስጥ የምናደርጋቸው ከበድ ያሉ ውሳኔዎች በመንፈሳዊ ጤንነታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። የምናደርገው እያንዳንዱ ውሳኔ ከይሖዋ ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ጥሩ ወይም መጥፎ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። ጥሩ ውሳኔ ማድረግ ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና እንደሚያጠናክረው ሁሉ መጥፎ ውሳኔ ማድረግም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ያበላሸዋል። በተጨማሪም መጥፎ ውሳኔ ማድረጋችን ሌሎች እንዲረበሹ አልፎ ተርፎም እንዲሰናከሉ በማድረግ እምነታቸውን ሊያናጋው ይችላል፤ አሊያም ደግሞ የጉባኤውን ሰላም ያደፈርሰዋል። በእርግጥም የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ለውጥ ያመጣሉ።ሮም 14:19ን እና ገላትያ 6:7ን አንብብ።

6. የምናደርገው ውሳኔ በምን ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል?

6 ቀጥተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ያልተሰጠባቸው ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ምን ማድረግ ይኖርብናል? በዚህ ጊዜ ውሳኔ የምናደርገው በግል ምርጫችን ላይ ብቻ ተመሥርተን መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱን ነገር በመመርመር በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል፤ ይህ ደግሞ የእሱን በረከት ያስገኝልናል።መዝሙር 37:5ን አንብብ።

የይሖዋን ፈቃድ አስተውሉ

7. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቀጥተኛ መመሪያ ያልተሰጠባቸው ጉዳዮች ሲያጋጥሙን ይሖዋ ምን እንድናደርግ እንደሚፈልግ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

7 ‘ታዲያ በአምላክ ቃል ውስጥ ቀጥተኛ መመሪያ ያልተሰጠባቸው ጉዳዮች ሲያጋጥሙን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ውሳኔ የትኛው እንደሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?’ የሚል ጥያቄ ይፈጠርብን ይሆናል። ኤፌሶን 5:17 “የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ” ይላል። ቀጥተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ በማይኖርበት ጊዜ የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ማስተዋል የምንችለው እንዴት ነው? ወደ እሱ በመጸለይና በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እንዲመራን በመፍቀድ ነው።

8. ኢየሱስ፣ አባቱ ከእሱ የሚፈልገውን ነገር ማስተዋል የቻለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

8 ኢየሱስ፣ አባቱ ከእሱ የሚፈልገውን ነገር ማስተዋል የቻለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ኢየሱስ ከጸለየ በኋላ በተአምር ብዙ ሰዎችን እንደመገበ የሚገልጹ ሁለት ዘገባዎችን እናገኛለን። (ማቴ. 14:17-20፤ 15:34-37) ያም ሆኖ በምድረ በዳ ተርቦ በነበረበት ወቅት ዲያብሎስ ድንጋዩን ዳቦ እንዲያደርግ ያቀረበለትን ጥያቄ ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነም። (ማቴዎስ 4:2-4ን አንብብ።) ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ የአባቱን አስተሳሰብ በሚገባ ያውቃል፤ በመሆኑም ድንጋዩን ወደ ዳቦ መለወጥ እንደሌለበት ተገንዝቦ ነበር። ኢየሱስ ያለውን ኃይል የግል ፍላጎቱን ለማሟላት እንዲጠቀምበት የአምላክ ፈቃድ እንዳልሆነ ያውቃል። ኢየሱስ ድንጋዩን ወደ ዳቦ ለመለወጥ ፈቃደኛ አለመሆኑ፣ መመሪያም ሆነ የሚያስፈልገውን ነገር ይሖዋ እንደሚሰጠው እምነት እንዳለው ያሳያል።

9, 10. ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል? በምሳሌ አስረዳ።

9 እኛም እንደ ኢየሱስ ጥበብ ያለበት ውሳኔ ለማድረግ ከፈለግን መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር ማለት ይኖርብናል። ከሚከተለው ጥበብ የተንጸባረቀበት ሐሳብ ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ አለብን፦ “በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ። በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ፤ እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል። በራስህ አመለካከት ጥበበኛ አትሁን። ይሖዋን ፍራ፤ ከክፉም ራቅ።” (ምሳሌ 3:5-7) መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት የይሖዋን አስተሳሰብ ማወቅ፣ አንድን ጉዳይ አስመልክቶ አምላክ ምን እንድናደርግ እንደሚፈልግ ለማስተዋል ይረዳናል። የይሖዋን አስተሳሰብ ይበልጥ እያወቅን ስንሄድ እሱ ለሚሰጠን አመራር ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ልብ ይኖረናል።—ሕዝ. 11:19 ግርጌ

10 ይህን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ገበያ የወጣችን አንዲት ባለትዳር እንመልከት። ይህች ሴት አንድን ጫማ በጣም ስለወደደችው ልትገዛው ፈለገች፤ ሆኖም ዋጋው በጣም ውድ ነው። ‘ለዚህ ጫማ ይህን ያህል ገንዘብ ባወጣ ባለቤቴ ምን ይሰማዋል?’ በማለት ራሷን ትጠይቃለች። ባለቤቷ አጠገቧ ባይሆንም ምን እንደሚሰማው ታውቃለች። እንዴት? አብረው ስለኖሩ ባለቤቷ፣ መጠነኛ የሆነውን ገንዘባቸውን እንዴት እንዲጠቀሙበት እንደሚፈልግ ታውቃለች። በመሆኑም ጫማውን ብትገዛ ባለቤቷ ምን እንደሚሰማው ማስተዋል ችላለች። በተመሳሳይም የይሖዋን አስተሳሰብና መንገዶች ይበልጥ እያወቅን ስንሄድ በሰማይ የሚኖረው አባታችን፣ የተለያዩ ጉዳዮች ሲያጋጥሙን ምን እንድናደርግ እንደሚፈልግ በቀላሉ ማስተዋል እንችላለን።

የይሖዋን አስተሳሰብ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

11. መጽሐፍ ቅዱስ ስናነብ ወይም ስናጠና ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ እንችላለን? (“ የአምላክን ቃል ስታጠና ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

11 የይሖዋን አስተሳሰብ በሚገባ ለማወቅ ለግል ጥናት ትልቅ ቦታ መስጠት ይኖርብናል። የአምላክን ቃል ስናነብ ወይም ስናጠና እንዲህ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው፦ ‘ይህ ሐሳብ ስለ ይሖዋ፣ ነገሮችን ስለሚያከናውንበት መንገድና ስለ እሱ አስተሳሰብ ምን ያስተምረኛል?’ መዝሙራዊው ዳዊት የነበረው ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል፤ እንዲህ በማለት ዘምሯል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ መንገድህን አሳውቀኝ፤ ጎዳናህንም አስተምረኝ። አንተ አዳኝ አምላኬ ስለሆንክ በእውነትህ እንድመላለስ አድርገኝ፤ አስተምረኝም። ቀኑን ሙሉ አንተን ተስፋ አደርጋለሁ።” (መዝ. 25:4, 5) በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ ስናሰላስል እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ይህን ሐሳብ ተግባራዊ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው? ተግባራዊ ማድረግ የምችለው የት ነው? በቤት ውስጥ? በሥራ ቦታ? በትምህርት ቤት? ወይስ በአገልግሎት?’ ያነበብነውን ነገር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው የት እንደሆነ ካወቅን በሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት እንደሆነ በቀላሉ ማስተዋል እንችላለን።

12. ጽሑፎቻችንና ስብሰባዎቻችን ይሖዋ ስለተለያዩ ጉዳዮች ያለውን አመለካከት እንድንገነዘብ የሚረዱን እንዴት ነው?

12 የይሖዋን አስተሳሰብ ይበልጥ ማወቅ የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ ከድርጅቱ ለምናገኛቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መመሪያዎች ትኩረት መስጠት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ) እና የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች የተባሉት ጽሑፎች የተዘጋጁት የግል ውሳኔ ማድረግ በሚጠይቁ የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የይሖዋ አስተሳሰብ ምን እንደሆነ እንድናውቅ ለመርዳት ነው። በተጨማሪም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በጥሞና ማዳመጥና ተሳትፎ ማድረግ በዚህ ረገድ ይጠቅመናል። በተማርናቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን የይሖዋን አስተሳሰብ ይበልጥ ለማወቅ እንዲሁም የእሱ ዓይነት አስተሳሰብ ለማዳበር ይረዳናል። ይሖዋ እኛን በመንፈሳዊ ለመመገብ ባደረገው ዝግጅት በሚገባ በመጠቀም ስለ ይሖዋ መንገዶች ይበልጥ እያወቅን መሄድ እንችላለን። እነዚህን ነገሮች በተግባር ላይ የምናውል ከሆነ የምናደርጋቸው ውሳኔዎች የአፍቃሪው አምላካችንን በረከት ያስገኙልናል።

ውሳኔያችሁ በይሖዋ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ይሁን

13. የይሖዋን አስተሳሰብ ከግምት ማስገባታችን ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ ስጥ።

13 የይሖዋን አስተሳሰብ ማወቅ ጥበብ ያዘለ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት። የመንግሥቱ አስፋፊዎች እንደመሆናችን መጠን የዘወትር አቅኚ በመሆን ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መግባት እንፈልግ ይሆናል። ይህን ለማሳካት ስንልም ሕይወታችንን ለማቅለል የሚረዱ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ጀመርን። ሆኖም ‘በጥቂት ነገሮች ተደስቼ መኖር እችል ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ ያሳስበን ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ‘አቅኚ ሁኑ’ የሚል የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ የለም፤ አስፋፊ ሆነንም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገል እንችላለን። ይሁን እንጂ ለመንግሥቱ ሲሉ መሥዋዕትነት የሚከፍሉ ሰዎች የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያገኙ ኢየሱስ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ሉቃስ 18:29, 30ን አንብብ።) በተጨማሪም ይሖዋ፣ ለእሱ ‘በፈቃደኝነት የውዳሴ መባ ስናቀርብና’ እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት ስንል የምንችለውን ሁሉ በደስታ ስናደርግ እንደሚደሰት ቅዱሳን መጻሕፍት ያሳያሉ። (መዝ. 119:108፤ 2 ቆሮ. 9:7) ታዲያ እነዚህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች በመመርመርና የእሱን አመራር ለማግኘት በመጸለይ የይሖዋን አስተሳሰብ ማወቅ አንችልም? በእነዚህ ነጥቦች ላይ ማሰላሰላችን፣ ከእኛ ሁኔታ ጋር የሚስማማና በሰማይ ያለውን አባታችንን በረከት የሚያስገኝ ውሳኔ ለማድረግ ሊረዳን ይችላል።

14. የምንመርጠው አለባበስ ይሖዋን የሚያስደስት መሆን አለመሆኑን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

14 እስቲ ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንመልከት። አንድ ልብስ መልበስ ፈለጋችሁ እንበል፤ ልብሱ የጉባኤውን አባላት ቅር የሚያሰኝ ሊሆን ይችል ይሆናል። ሆኖም ይህን ልብስ እንዳትለብሱ የሚከለክል ቀጥተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ እንደሌለ ታውቃላችሁ። ታዲያ ይሖዋ በዚህ ረገድ ያለውን አመለካከት ማወቅ የምትችሉት እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ “ሴቶች ፀጉር በመሸረብና በወርቅ ወይም በዕንቁ ወይም ደግሞ በጣም ውድ በሆነ ልብስ ሳይሆን በልከኝነትና በማስተዋል ተገቢ በሆነ ልብስ ራሳቸውን ያስውቡ፤ ለአምላክ ያደርን ነን የሚሉ ሴቶች ሊያደርጉት እንደሚገባ በመልካም ሥራ ይዋቡ።” (1 ጢሞ. 2:9, 10) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ለክርስቲያን ወንዶችም በእኩል ደረጃ ይሠራል። ለይሖዋ ያደርን እንደመሆናችን መጠን የራሳችን ምርጫ ብቻ ሳይሆን አለባበሳችንና አጋጌጣችን በሌሎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖም ያሳስበናል። ልከኛ ከሆንንና ለሰዎች ፍቅር ካለን፣ የእምነት ባልንጀሮቻችንን አመለካከት ግምት ውስጥ በማስገባት እነሱን ሊረብሽ ወይም ቅር ሊያሰኝ የሚችል ልብስ ከመልበስ እንቆጠባለን። (1 ቆሮ. 10:23, 24፤ ፊልጵ. 3:17) ቅዱሳን መጻሕፍት የሚሰጡትን ሐሳብ ግምት ውስጥ የምናስገባ ከሆነ ይሖዋ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አመለካከት ማወቅ እንዲሁም እሱን የሚያስደስት ውሳኔ ማድረግ እንችላለን።

15, 16. (ሀ) ስለ ፆታ ብልግና የምናውጠነጥን ከሆነ ይሖዋ ምን ይሰማዋል? (ለ) የመዝናኛ ምርጫችንን በተመለከተ ይሖዋን የሚያስደስተው ምን እንደሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? (ሐ) ከባድ ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቁ ነገሮች ሲያጋጥሙን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

15 የሰው ልጆች መጥፎ ጎዳና ሲከተሉና ‘የልባቸው ሐሳብ ምንጊዜም ወደ መጥፎ ብቻ ሲያዘነብል’ ይሖዋ እንደሚያዝን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፍጥረት 6:5, 6ን አንብብ።) ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ስለ ብልግና ድርጊቶች ማውጠንጠን ስህተት ነው፤ ምክንያቱም በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተወገዘና ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር የሚጋጭ ከባድ ኃጢአት ወደ መፈጸም ይመራል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ከሰማይ የሆነው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት እንዲሁም አድልዎና ግብዝነት የሌለበት ነው።” (ያዕ. 3:17) ይህን ማሳሰቢያ ልብ ማለታችን ንጹሕ ያልሆኑ ሐሳቦችና ዝንባሌዎች በውስጣችን እንዲቀሰቀሱ ከሚያደርጉ መዝናኛዎች እንድንርቅ ይረዳናል። አስተዋይ የሆኑ ክርስቲያኖች ይሖዋ የሚጠላቸውን ነገሮች በሚያንጸባርቁ መጻሕፍት፣ ፊልሞች ወይም ጌሞች መዝናናት ተገቢ ስለመሆኑ ጥያቄ አይፈጠርባቸውም። ምክንያቱም ይሖዋ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው አመለካከት በቃሉ ውስጥ በግልጽ ሰፍሯል።

16 ከአንድ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ይሖዋን የሚያስደስቱ የተለያዩ ውሳኔዎች ማድረግ ይቻላል። ከባድ ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቁ ነገሮች ሲያጋጥሙን ግን የሽማግሌዎችን ወይም ተሞክሮ ያላቸውን ክርስቲያኖች ምክር መጠየቁ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። (ቲቶ 2:3-5፤ ያዕ. 5:13-15) እርግጥ ነው፣ ሌሎች ለእኛ እንዲወስኑልን መጠየቁ ተገቢ አይደለም። ክርስቲያኖች የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት ማሠልጠን ይኖርባቸዋል። (ዕብ. 5:14) ጳውሎስ “እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል” በማለት በመንፈስ መሪነት ከጻፈው ሐሳብ ጋር ሁላችንም ተስማምተን መኖር ይገባናል።—ገላ. 6:5

17. ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎች ማድረጋችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

17 በይሖዋ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ስናደርግ ይበልጥ ወደ እሱ እንቀርባለን። (ያዕ. 4:8) የእሱን ሞገስና በረከት እናገኛለን። ይህ ደግሞ በሰማይ ባለው አባታችን ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። እንግዲያው የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች አምላክ ስለ አንድ ጉዳይ ያለውን አመለካከት እንድናውቅ ስለሚረዱን በእነሱ ለመመራት ጥረት እናድርግ። እርግጥ ነው፣ ምንጊዜም ስለ ይሖዋ የምንማራቸው አዳዲስ ነገሮች ይኖራሉ። (ኢዮብ 26:14) ያም ቢሆን ትጋት የተሞላበት ጥረት በማድረግ በዛሬው ጊዜም እንኳ ጥሩ ውሳኔ ለመወሰን የሚረዳንን ጥበብ፣ እውቀትና ማስተዋል ማግኘት እንችላለን። (ምሳሌ 2:1-5) ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች የሚያመነጯቸው ሐሳቦችና የሚያወጧቸው ዕቅዶች በየጊዜው ይለዋወጣሉ፤ ከዚህ በተቃራኒ መዝሙራዊው “የይሖዋ ውሳኔዎች ለዘላለም ይጸናሉ፤ የልቡ ሐሳብ ከትውልድ እስከ ትውልድ ጸንቶ ይኖራል” በማለት ተናግሯል። (መዝ. 33:11) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አስተሳሰባችንና ድርጊታችን፣ እጅግ ጥበበኛ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ አስተሳሰብ ጋር የሚስማማ ከሆነ ከሁሉ የተሻለ ውሳኔ ማድረግ እንችላለን።