በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ስለ መንፈሳዊው ዓለም የሚገልጹ ራእዮች

በመንፈሳዊው ዓለም ስለሚኖሩ አካላት የሚነሱ ጥያቄዎች

በመንፈሳዊው ዓለም ስለሚኖሩ አካላት የሚነሱ ጥያቄዎች

ስለ መንፈሳዊው ዓለምም ሆነ በዚያ ስለሚኖሩት አካላት ጥያቄ ተፈጥሮብህ ያውቃል? ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሰዎች ይህን ጉዳይ በተመለከተ የተለያዩ ግምታዊ ሐሳቦችን ሲሰነዝሩ ኖረዋል። አንዳንዶች መንፈሳዊው ዓለም፣ ልዩ ክብር ይገባቸዋል ብለው የሚያስቧቸው የቀድሞ አባቶች መኖሪያ እንደሆነ ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ መላእክትና በሞት ያንቀላፉ ጥሩ ሰዎች የሚኖሩበት ሰላምና ጸጥታ የሰፈነበት ቦታ እንደሆነ አድርገው በአእምሯቸው ይስሉታል። መንፈሳዊው ዓለም በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አማልክት የሚኖሩበት ቦታ እንደሆነ አድርገው የሚያስቡ ሰዎችም አሉ።

አንዳንዶች ደግሞ ‘ሰማይ ሄዶ የመጣና ስለዚያ የነገረን ስለሌለ ስለ መንፈሳዊው ዓለም ምንም ማወቅ አንችልም’ ብለው ይናገራሉ። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት የተሳሳተ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ማለትም በመንፈሳዊው ዓለም ይኖር ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት የሃይማኖት መሪዎች “ከሰማይ የመጣሁት የራሴን ፈቃድ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ነው” በማለት በግልጽ ተናግሯል። ስለሆነም ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ ቦታ አለ” ብሎ ሲነግራቸው በገዛ ዓይኑ ስላየው ነገር እየገለጸ ነበር።—ዮሐንስ 6:38፤ 14:2

የኢየሱስ አባት የሆነው ይሖዋ ‘ቤቱ’ ማለትም መኖሪያው በሰማይ ነው። (መዝሙር 83:18) በመሆኑም በዓይን ስለማይታየው ዓለም ከይሖዋ አምላክና ከኢየሱስ ክርስቶስ የተሻለ ትክክለኛ መረጃ ሊሰጠን የሚችል አካል የለም። ይሖዋና ኢየሱስ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች ባሳዩአቸው አስደናቂ ራእዮች አማካኝነት ስለ መንፈሳዊው ዓለም ብዙ ነገሮችን ገልጸውልናል።

ቀጣዩ ርዕስ ሰዎች ስላዩአቸው በርካታ ራእዮች የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ያብራራል። ስለ እነዚህ ራእዮች ስታነብ፣ መንፈሳዊው ዓለም እኛ የሰው ልጆች ልናያቸውና ልንዳስሳቸው በምንችላቸው ነገሮች የተሞላ ግዑዝ ነገር እንዳልሆነ አስታውስ። በመሆኑም አምላክ፣ መንፈሳዊውን ዓለም የገለጸው መንፈሳዊ አካላት ብቻ ሊረዱት በሚችሉት ቋንቋ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ሊረዱት በሚችሉት መንገድ ለመግለጽ ሲል የተለያዩ ራእዮችን አሳይቷል። እነዚህ ራእዮች በመንፈሳዊው ዓለም ባለው “ብዙ መኖሪያ” ውስጥ የሚኖሩትን አካላት በተመለከተ ግንዛቤ እንድታገኝ ይረዱሃል።