በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአምላክ ለተቀበልነው ጸጋ አመስጋኝ መሆን

ከአምላክ ለተቀበልነው ጸጋ አመስጋኝ መሆን

“ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋን ተቀብለናል።”—ዮሐ. 1:16

መዝሙሮች፦ 95, 13

1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ስለ ወይኑ እርሻ ባለቤት የተናገረውን ምሳሌ ግለጽ። (ለ) ይህ ምሳሌ ልግስናንና ጸጋን ከማሳየት ጋር በተያያዘ ምን ትምህርት ይዟል?

አንድ የወይን እርሻ ባለቤት፣ በወይን እርሻው ላይ የሚሠሩ ሠራተኞችን ለመቅጠር በጠዋት ተነስቶ ወደ ገበያ ቦታ ሄደ። ያገኛቸው ሰዎች በሚሰጣቸው ክፍያ ስለተስማሙ ወደ እርሻው ቦታ ሄደው መሥራት ጀመሩ። ይሁንና የእርሻው ባለቤት ተጨማሪ ሠራተኞች ስላስፈለጉት በቀኑ ውስጥ በተለያየ ሰዓት ወደ ገበያው ቦታ በመሄድ ሌሎች ሰዎችን ቀጠረ፤ የእርሻው ባለቤት አመሻሹ ላይ ለቀጠራቸው ሰዎችም ተገቢውን ክፍያ እንደሚከፍላቸው ነገራቸው። በመሸም ጊዜ የእርሻው ባለቤት ሠራተኞቹን በመሰብሰብ ደሞዛቸውን ከፈላቸው፤ ለብዙ ሰዓታት ሲለፉ ለዋሉትም ሆነ ለአንድ ሰዓት ብቻ ለሠሩት የሰጣቸው ክፍያ ተመሳሳይ ነው። መጀመሪያ የተቀጠሩት ሠራተኞች ይህን ሲያውቁ ቅሬታቸውን ገለጹ። የወይን እርሻው ባለቤትም ከመካከላቸው ለአንዱ እንዲህ አለው፦ ‘በዚህ ደሞዝ ለመሥራት ተስማምተህ አልነበረም? ለሁሉም ሠራተኞቼ የፈለግኩትን ያህል የመስጠት መብት የለኝም? እኔ ለጋስ በመሆኔ ልትመቀኝ ይገባሃል?’—ማቴ. 20:1-15 ግርጌ

2 ኢየሱስ የተናገረው ይህ ምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰውን አንድ የይሖዋ ባሕርይ ያስታውሰናል፤ ይህም የአምላክ “ጸጋ” ነው። [1] (2 ቆሮንቶስ 6:1ን አንብብ።) በወይን እርሻው ውስጥ ለአንድ ሰዓት ብቻ የሠሩት ሰዎች ሙሉ ደሞዝ ማግኘት አይገባቸው ይሆናል፤ ይሁንና የእርሻው ባለቤት ልዩ ደግነት አሳይቷቸዋል። አንድ ምሁር “ጸጋ” ተብሎ የተተረጎመውን ቃል በተመለከተ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የቃሉ መሠረታዊ ትርጉም፣ ተቀባዩ ይገባኛል ሊለው የማይችል ነፃ ስጦታን ያመለክታል፤ ስጦታውን ያገኘው ሰው የድካሜ ወይም የልፋቴ ዋጋ ሊለው የሚችል ነገር አይደለም።”

ይሖዋ በልግስና የሰጠን ስጦታ

3, 4. ይሖዋ ለሁሉም የሰው ልጆች ጸጋውን ያሳየው ለምንና እንዴት ነው?

3 ቅዱሳን መጻሕፍት ‘ስለ አምላክ ነፃ ስጦታ ይኸውም ስለ ጸጋው’ ይናገራሉ። (ኤፌ. 3:7) ይሖዋ ይህን “ነፃ ስጦታ” የሚሰጠው ለምንና እንዴት ነው? ይሖዋ የሚጠብቅብንን ነገሮች ሙሉ በሙሉ ማሟላት ብንችል ኖሮ እሱ የሚያሳየን ደግነት የሚገባን ነገር ይሆን ነበር። ሆኖም ይህን ማድረግ አንችልም። በመሆኑም ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “ሁልጊዜ ጥሩ ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኃጢአት የማይሠራ ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም” በማለት ጽፏል። (መክ. 7:20) ሐዋርያው ጳውሎስም በተመሳሳይ “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል” እንዲሁም “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው” በማለት ጽፏል። (ሮም 3:23፤ 6:23ሀ) እኛም የሚገባን ሞት ነው።

4 ይሁንና ይሖዋ፣ ኃጢአተኛ ለሆኑት የሰው ልጆች ጸጋውን በማሳየት ተወዳዳሪ በሌለው መንገድ ፍቅሩን ገልጿል። ከሁሉ የላቀው የይሖዋ ስጦታ፣ ለእኛ ሲል እንዲሞት ወደ ምድር የላከው “አንድያ ልጁ” ነው። (ዮሐ. 3:16) በመሆኑም ጳውሎስ ኢየሱስን አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እስከ ሞት ድረስ መከራ በመቀበሉ አሁን የክብርና የሞገስ ዘውድ ደፍቶ እናየዋለን፤ እሱ በአምላክ ጸጋ ለሰው ሁሉ ሲል ሞትን ቀምሷል።” (ዕብ. 2:9) በእርግጥም “አምላክ የሚሰጠው ስጦታ . . . በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።”—ሮም 6:23ለ

5, 6. (ሀ) ኃጢአት ገዢያችን ሲሆን ውጤቱ ምንድን ነው? (ለ) የአምላክ ጸጋ ገዢያችን ሲሆን ውጤቱ ምንድን ነው?

5 የሰው ልጆች በሙሉ የኃጢአትንና የሞትን እርግማን የወረሱት እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “በአንድ ሰው [በአዳም] በደል የተነሳ ሞት” በአዳም ዘሮች ላይ እንደነገሠ ይናገራል። (ሮም 5:12, 14, 17) ደስ የሚለው ግን የኃጢአት ተገዢዎች ወይም ባሪያዎች ላለመሆን መምረጥ እንችላለን። በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን፣ የይሖዋ ጸጋ በእኛ ላይ እንዲነግሥ እንደምንፈልግ እናሳያለን። እንዴት? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሰዎች ብዙ ኃጢአት ሲፈጽሙ አምላክ ታላቅ ጸጋ አሳያቸው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ኃጢአት ከሞት ጋር እንደነገሠ ሁሉ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የዘላለም ሕይወት ይገኝ ዘንድ ጸጋ በጽድቅ አማካኝነት እንዲነግሥ ነው።”—ሮም 5:20, 21

6 ኃጢአተኞች ብንሆንም እንኳ ኃጢአት ሕይወታችንን እንዲቆጣጠረው ከመፍቀድ ሌላ አማራጭ እንደሌለን አድርገን ልናስብ አይገባም። ኃጢአት ስንሠራ ይሖዋ ይቅር እንዲለን መለመን እንችላለን። ጳውሎስ ለክርስቲያኖች “በጸጋ ሥር እንጂ በሕግ ሥር ስላልሆናችሁ ኃጢአት በእናንተ ላይ ጌታ ሊሆን አይገባም” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል። (ሮም 6:14) በመሆኑም በእኛ ላይ የሚገዛው የአምላክ ጸጋ ነው። ይህ ምን ውጤት ያስገኛል? ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት አብራርቶታል፦ “የአምላክ ጸጋ . . . ፈሪሃ አምላክ በጎደለው መንገድ መኖርና ዓለማዊ ምኞቶችን መከተል ትተን አሁን ባለው በዚህ ሥርዓት ውስጥ ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ፣ በጽድቅና ለአምላክ በማደር እንድንኖር ያሠለጥነናል።”—ቲቶ 2:11, 12

“በልዩ ልዩ መንገዶች የተገለጸው የአምላክ ጸጋ”

7, 8. የይሖዋ ጸጋ ‘በልዩ ልዩ መንገዶች ተገልጿል’ ሲባል ምን ማለት ነው? (በመግቢያው ላይ ያሉትን ፎቶግራፎች ተመልከት።)

7 ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በልዩ ልዩ መንገዶች የተገለጸው የአምላክ ጸጋ መልካም መጋቢዎች እንደመሆናችሁ መጠን፣ እያንዳንዳችሁ በተቀበላችሁት ስጦታ መሠረት የተሰጣችሁን ስጦታ አንዳችሁ ሌላውን ለማገልገል ተጠቀሙበት።” (1 ጴጥ. 4:10) ‘የአምላክ ጸጋ በልዩ ልዩ መንገዶች ተገልጿል’ ሲባል ምን ማለት ነው? በሕይወታችን ውስጥ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን ይሖዋ ያንን ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል ይሰጠናል ማለት ነው። (1 ጴጥ. 1:6) ጥቅሱ፣ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም መከራ ለመቋቋም የሚያስችል የአምላክ ጸጋ እንዳለ ይጠቁማል።

8 በእርግጥም የይሖዋ ጸጋ በልዩ ልዩ መንገዶች ተገልጿል። ሐዋርያው ዮሐንስ “ከእሱ የጸጋ ሙላት የተነሳ ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋን ተቀብለናል” በማለት ጽፏል። (ዮሐ. 1:16) የይሖዋ ጸጋ በልዩ ልዩ መንገዶች በመገለጹ ብዙ በረከቶች ማግኘት ችለናል። ከእነዚህ በረከቶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

9. ከይሖዋ ጸጋ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ለዚህ በረከት አመስጋኝ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

9 የኃጢአት ይቅርታ ማግኘት። የይሖዋ ጸጋ የኃጢአት ይቅርታ እንድናገኝ መንገድ ከፍቶልናል፤ ይህ የሚሆነው ግን ንስሐ ከገባንና የኃጢአት ዝንባሌዎቻችንን ለማሸነፍ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋችንን ከቀጠልን ነው። (1 ዮሐንስ 1:8, 9ን አንብብ።) የአምላክ ምሕረት፣ ልባችን በአመስጋኝነት እንዲሞላና እሱን ለማክበር እንድንነሳሳ ሊያደርገን ይገባል። ጳውሎስ ለቅቡዓን ወንድሞቹ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “[ይሖዋ] ከጨለማው ሥልጣን ታድጎን ወደሚወደው ልጁ መንግሥት አሻግሮናል፤ ልጁም ቤዛውን በመክፈል ነፃ እንድንወጣ ይኸውም የኃጢአት ይቅርታ እንድናገኝ አድርጎናል።” (ቆላ. 1:13, 14) የኃጢአት ይቅርታ ማግኘታችን ሌሎች አስደናቂ በረከቶችን እንድናገኝ አጋጣሚውን ከፍቶልናል።

10. የአምላክ ጸጋ ምን እንድናገኝ አስችሎናል?

10 ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት መመሥረት። ስንወለድ ጀምሮ ኃጢአተኞች በመሆናችን የአምላክ ጠላቶች ነበርን። ጳውሎስ “ጠላቶች ሆነን ሳለን በልጁ ሞት አማካኝነት ከአምላክ ጋር [ታረቅን]” በማለት ይህንን እውነታ ገልጿል። (ሮም 5:10) በዚህ መንገድ እርቅ መፍጠራችን ከይሖዋ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ለመመሥረት አስችሎናል። ጳውሎስ ለቅቡዓን ወንድሞቹ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ከይሖዋ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት የመመሥረት መብት ማግኘታችንን ከይሖዋ ጸጋ ጋር አያይዞ ገልጾታል፦ “አሁን በእምነት አማካኝነት ጻድቃን ናችሁ ስለተባልን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከአምላክ ጋር ያለንን ሰላም ጠብቀን እንኑር፤ ደግሞም በኢየሱስ አማካኝነት የአምላክን ጸጋ ለማግኘት በእምነት ወደ እሱ መቅረብ የቻልን ሲሆን ይህን ጸጋ አሁን አግኝተናል።” (ሮም 5:1, 2) ይህ እንዴት ያለ በረከት ነው!

የአምላክ ጸጋ የሚገለጽባቸው መንገዶች፦ ምሥራቹን የመስማት መብት (አንቀጽ 11ን ተመልከት)

11. ቅቡዓን ‘ሌሎች በጎችን’ የጽድቅ ጎዳና እንዲከተሉ የረዷቸው እንዴት ነው?

11 የጽድቅን ጎዳና እንድንከተል ያገኘነው እርዳታ። ሁላችንም ስንወለድ ጀምሮ ከጽድቅ ጎዳና የራቅን ነበርን። ይሁንና ነቢዩ ዳንኤል፣ በፍጻሜው ዘመን “ጥልቅ ማስተዋል ያላቸው” ይኸውም ቅቡዓን ቀሪዎች “የጽድቅን ጎዳና እንዲከተሉ ብዙ ሰዎችን [እንደሚረዱ]” ትንቢት ተናግሯል። (ዳንኤል 12:3ን አንብብ።) ቅቡዓን፣ በሚያከናውኑት የስብከትና የማስተማር ሥራ አማካኝነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ “ሌሎች በጎች” በይሖዋ ፊት የጽድቅ አቋም እንዲኖራቸው ረድተዋል። (ዮሐ. 10:16) ይህ ሊሳካ የቻለው ግን በይሖዋ ጸጋ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ክርስቶስ ኢየሱስ የከፈለው ቤዛ በሚያስገኘው ነፃነት አማካኝነት [በአምላክ ጸጋ] ጻድቃን ናችሁ መባላቸው እንዲሁ የተገኘ ነፃ ስጦታ ነው።”—ሮም 3:23, 24

የጸሎት መብት (አንቀጽ 12ን ተመልከት)

12. ጸሎት ከአምላክ ጸጋ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

12 በጸሎት አማካኝነት ወደ አምላክ ዙፋን መቅረብ። ይሖዋ በሰማይ ወዳለው ዙፋኑ በጸሎት የመቅረብን መብት በጸጋው ሰጥቶናል። እንዲያውም ጳውሎስ የይሖዋን ዙፋን ‘የጸጋው ዙፋን’ በማለት የጠራው ሲሆን ወደዚህ ዙፋን “ያለ ምንም ፍርሃት” እንድንቀርብ ጋብዞናል። (ዕብ. 4:16ለ) ይሖዋ ይህን መብት የዘረጋልን በልጁ በኩል ነው፤ “በእሱም አማካኝነት ይህ የመናገር ነፃነት አለን፤ በክርስቶስ ላይ ባለን እምነት አማካኝነትም በልበ ሙሉነት ወደ አምላክ በነፃነት መቅረብ እንችላለን።” (ኤፌ. 3:12) በእርግጥም ይሖዋ በጸሎት አማካኝነት በነፃነት ወደ እሱ እንድንቀርብ መፍቀዱ አስደናቂ የሆነ የጸጋው መገለጫ ነው።

በሚያስፈልገን ጊዜ እርዳታ ማግኘት (አንቀጽ 13ን ተመልከት)

13. “እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ” አምላክ በጸጋው አማካኝነት የሚረዳን እንዴት ነው?

13 በሚያስፈልገን ጊዜ እርዳታ ማግኘት። ጳውሎስ “እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ምሕረትና ጸጋ እናገኝ ዘንድ” ወደ ይሖዋ በነፃነት እንድንጸልይ አበረታቶናል። (ዕብ. 4:16ሀ) በሕይወታችን ውስጥ መከራ ወይም አስጨናቂ ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜ ሁሉ ይሖዋ በምሕረቱ እንዲረዳን ወደ እሱ መጮኽ እንችላለን። እርዳታው የማይገባን ብንሆንም እንኳ ይሖዋ ልመናችንን ሰምቶ ብዙውን ጊዜ በእምነት ባልንጀሮቻችን በኩል ምላሽ ይሰጠናል፤ በመሆኑም “በሙሉ ልብ ‘ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?’ እንላለን።”—ዕብ. 13:6

14. ከይሖዋ ጸጋ ምን ጥቅም ማግኘት እንችላለን?

14 ለልባችን ማጽናኛ ማግኘት። ይሖዋ በጸጋው ከሰጠን ግሩም በረከቶች አንዱ ልባችን ሲጨነቅ ማጽናኛ ማግኘት መቻላችን ነው። (መዝ. 51:17) ጳውሎስ ስደት እየደረሰባቸው ለነበሩት በተሰሎንቄ የሚገኙ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንዲሁም የወደደን፣ በጸጋም አማካኝነት ዘላለማዊ መጽናኛና መልካም ተስፋ የሰጠን አባታችን የሆነው አምላክ ልባችሁን ያጽናኑ፤ እንዲሁም . . . ያበርቷችሁ።” (2 ተሰ. 2:16, 17 ግርጌ) ይሖዋ በልግስና በሰጠን ጸጋ አማካኝነት በፍቅር እንደሚንከባከበን ማወቁ እንዴት ያበረታታል!

15. የአምላክ ጸጋ ምን ዓይነት ተስፋ እንዲኖረን መንገድ ከፍቶልናል?

15 የዘላለም ሕይወት ተስፋ ማግኘት። ኃጢአተኞች በመሆናችን፣ ይሖዋ ባይረዳን ኖሮ ተስፋ አይኖረንም ነበር። (መዝሙር 49:7, 8ን አንብብ።) ይሁንና ይሖዋ አስደናቂ ተስፋ ሰጥቶናል። ኢየሱስ ለተከታዮቹ “የአባቴ ፈቃድ ወልድን የሚያውቅና በእሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 6:40) በእርግጥም የዘላለም ሕይወት ተስፋ፣ የአምላክ ጸጋ የተገለጸበት ግሩም ስጦታ ነው። ለዚህ ስጦታ አድናቆት የነበረው ጳውሎስ “የአምላክ ጸጋ ተገልጧልና፤ ጸጋው ለሁሉም ዓይነት ሰዎች መዳን ያስገኛል” ብሏል።—ቲቶ 2:11

የአምላክን ጸጋ ኃጢአት ለመፈጸም ሰበብ አታድርጉት

16. በጥንት ጊዜ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች የአምላክን ጸጋ አላግባብ የተጠቀሙበት እንዴት ነው?

16 የይሖዋ ጸጋ ብዙ በረከቶች የሚያስገኝልን ቢሆንም ይሖዋ የፈለግነውን ብናደርግ በቸልታ እንደሚያልፈን አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። ከጥንቶቹ ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ ‘በአምላክ ጸጋ እያሳበቡ ዓይን ያወጣ ምግባር ይፈጽሙ’ ነበር። (ይሁዳ 4) እነዚህ ታማኝ ያልሆኑ ክርስቲያኖች፣ ኃጢአት ቢፈጽሙም ይሖዋ ሁልጊዜ ይቅር እንደሚላቸው ያስቡ የነበረ ይመስላል። ይባስ ብለው ደግሞ ወንድሞቻቸውም የእነሱን አስጸያፊ አካሄድ እንዲከተሉ ይገፋፉ ነበር። ዛሬም ቢሆን እንዲህ የሚያደርግ ማንኛውም ሰው “የጸጋን መንፈስ በንቀት [እያጥላላ]” ነው።—ዕብ. 10:29

17. ጴጥሮስ ምን ጠንከር ያለ ምክር ሰጥቷል?

17 በዛሬው ጊዜ ሰይጣን፣ አንዳንድ ክርስቲያኖችን ኃጢአት ቢፈጽሙም አምላክ ምሕረት እንደሚያደርግላቸውና ምንም ቅጣት እንደማይደርስባቸው አድርገው እንዲያስቡ በማድረግ እያታለላቸው ነው። ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር የሚል ቢሆንም እንኳ የኃጢአት ዝንባሌያችንን ለማሸነፍ አጥብቀን እንድንታገል ይጠብቅብናል። ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት የሚከተለውን ጽፏል፦ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ይህን አስቀድማችሁ ስላወቃችሁ ሕግ የሚተላለፉ ሰዎች በሚፈጽሙት ስህተት ከእነሱ ጋር ተታልላችሁ እንዳትወሰዱና ጽኑ አቋማችሁ እንዳይናጋ ተጠንቀቁ። ከዚህ ይልቅ በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እድገት አድርጉ።”—2 ጴጥ. 3:17, 18

የአምላክ ጸጋ ኃላፊነት ያስከትላል

18. የይሖዋ ጸጋ ምን ኃላፊነት ያስከትልብናል?

18 ከይሖዋ ለተቀበልነው ጸጋ አመስጋኞች መሆናችን፣ ይህን ስጦታ አምላክን በሚያስከብርና ሌሎችን በሚጠቅም መንገድ የመጠቀም ኃላፊነት እንዳለብን እንዲሰማን ያደርጋል። ይህን ማድረግ የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “በመሆኑም በተሰጠን ጸጋ መሠረት የተለያዩ ስጦታዎች ስላሉን ስጦታችን . . . ማገልገል ከሆነ ማገልገላችንን እንቀጥል፤ የሚያስተምርም ቢሆን ማስተማሩን ይቀጥል፤ የሚያበረታታም ቢሆን ማበረታቻ መስጠቱን ይቀጥል፤ . . . የሚምር በደስታ ይማር።” (ሮም 12:6-8) ይሖዋ ያሳየን ጸጋ፣ እኛም በክርስቲያናዊ አገልግሎት ራሳችንን እንድናስጠምድ፣ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ እንድናስተምር፣ የእምነት ባልንጀሮቻችንን እንድናበረታታ እንዲሁም ቅር ያሰኙንን ይቅር እንድንል ግድ ይለናል።

19. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ስለ የትኛው ኃላፊነታችን እናጠናለን?

19 አምላክ ላሳየን ታላቅ ፍቅር አመስጋኝ መሆናችን “ስለ አምላክ ጸጋ የሚገልጸውን ምሥራች በተሟላ ሁኔታ በመመሥከር” ረገድ አቅማችን የሚፈቅደውን ሁሉ ለማድረግ ሊያነሳሳን ይገባል። (ሥራ 20:24) የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ኃላፊነታችንን የሚያብራራ ይሆናል።

^ [1] (አንቀጽ 2) በአዲስ ዓለም ትርጉም “የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፍቻ” ላይ “ጸጋ” የሚለውን ቃል ተመልከት።