በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“አትፍራ። እረዳሃለሁ”

“አትፍራ። እረዳሃለሁ”

በምሽት በእግርህ እየተጓዝክ እንዳለ አድርገህ አስብ። በድንገት አንድ ሰው እየተከተለህ እንደሆነ ተሰማህ። ስትቆም እሱም ይቆማል። ፈጠን ፈጠን እያልክ ስትራመድ እሱም በዚያው ፍጥነት ይከተልሃል። በዚያ አካባቢ ወደሚኖር አንድ ጓደኛህ ቤት እየሮጥክ በመሄድ በሩን በኃይል አንኳኳህ። በዚህ ጊዜ ጓደኛህ በሩን ከፍቶ ሲያስገባህ እፎይ ትላለህ።

እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ባያጋጥምህም በሕይወትህ ውስጥ የሚከሰቱ ሌሎች አስጨናቂ ሁኔታዎች በስጋት እንድትዋጥ ሊያደርጉህ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ልታሸንፈው የምትፈልገው ድክመት ይኖርብህ ይሆናል፤ የምትችለውን ያህል ጥረት ብታደርግም ድክመትህን ማሸነፍ አስቸጋሪ ሆኖብሃል? ሥራ ከፈታህ ረጅም ጊዜ ያለፈህ ሲሆን ሥራ ለማግኘት ብዙ ብትደክምም አልሳካ ብሎሃል? ዕድሜህ እየገፋ በመሆኑ ወደፊት የጤና እክል ሊያጋጥምህ እንደሚችል በማሰብ ትጨነቃለህ? አሊያም ሌላ የሚያስጨንቅ ነገር ገጥሞህ ይሆን?

የገጠመህ ችግር ምንም ይሁን ምን፣ ጭንቀትህን የሚጋራህና በሚያስፈልግህ ጊዜ ሊረዳህ የሚችል ወዳጅ ቢኖርህ ደስ አይልህም? እንዲህ ዓይነት የቅርብ ወዳጅ አለህ! በኢሳይያስ 41:8-13 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ለአብርሃም ወዳጅ እንደነበረው ሁሉ ለአንተም ወዳጅ ሊሆንልህ ይችላል። በቁጥር 10 እና 13 ላይ ይሖዋ አገልጋዮቹን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ። እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ። አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ፤ በጽድቅ ቀኝ እጄ አጥብቄ እይዝሃለሁ። ‘አትፍራ። እረዳሃለሁ’ የምልህ እኔ፣ አምላክህ ይሖዋ ቀኝ እጅህን ይዣለሁና።”

“አጥብቄ እይዝሃለሁ”

ይህ ሐሳብ የሚያበረታታ አይደለም? ይሖዋ የገባልንን ቃል በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ከይሖዋ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ መሄድ ደስ የሚል ነገር ቢሆንም ጥቅሱ ላይ የተገለጸው ሁኔታ ይህ እንዳልሆነ ልብ በል። ከይሖዋ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘህ እየሄድክ ቢሆን፣ በቀኝ እጁ የሚይዘው ግራ እጅህን ይሆን ነበር። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ‘የጽድቅ ቀኝ እጁን’ ዘርግቶ “ቀኝ እጅህን” እንደሚይዝህ ተገልጿል፤ ይሖዋ በሕይወትህ ውስጥ ከገጠመህ አስጨናቂ ሁኔታ ጎትቶ የሚያወጣህ ያህል ነው። ይህን በሚያደርግበት ጊዜም “አትፍራ። እረዳሃለሁ” የሚል ማረጋገጫ ይሰጥሃል።

ይሖዋን የምትመለከተው፣ የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ለእርዳታ እንደሚደርስልህ አፍቃሪ አባትና ወዳጅ አድርገህ ነው? እሱ ስለ አንተ ያስባል፤ ስለ ደህንነትህ ይጨነቃል እንዲሁም ምንጊዜም ሊረዳህ ዝግጁ ነው። መከራ ሲደርስብህ ወይም አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ይሖዋ የመረጋጋት ስሜት እንዲሰማህ ይፈልጋል፤ ምክንያቱም በጣም ይወድሃል። በእርግጥም ይሖዋ “በጭንቅ ጊዜ ፈጥኖ የሚደርስልን ረዳታችን ነው።”—መዝ. 46:1

ከዚህ በፊት የሠራሃቸው ስህተቶች የሚፈጥሩብህ የጥፋተኝነት ስሜት

አንዳንዶች ከዚህ በፊት የሠሩት ስህተት ሕሊናቸውን የሚያሠቃየው ከመሆኑም ሌላ አምላክ ይቅር እንዳላላቸው ስለሚሰማቸው ይጨነቃሉ። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ‘በወጣትነቱ ስለሠራቸው ኃጢአቶች’ የተናገረውን ታማኙን ኢዮብን አስታውስ። (ኢዮብ 13:26) መዝሙራዊው ዳዊትም ተመሳሳይ የጥፋተኝነት ስሜት ስለተሰማው “በወጣትነቴ የሠራኋቸውን ኃጢአቶችና በደሎች አታስብብኝ” በማለት ይሖዋን ተማጽኗል። (መዝ. 25:7) ሁላችንም ፍጹማን ባለመሆናችን ‘ኃጢአት ሠርተናል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኖናል።’—ሮም 3:23

በኢሳይያስ ምዕራፍ 41 ላይ ያለው መልእክት መጀመሪያ የተላከው በጥንት ጊዜ ለነበሩት የአምላክ ሕዝቦች ነው። የሠሩት ኃጢአት በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ይሖዋ በምርኮ ወደ ባቢሎን እንዲወሰዱ በማድረግ ቀጥቷቸዋል። (ኢሳ. 39:6, 7) ያም ቢሆን አምላክ፣ ንስሐ የገቡትንና ወደ እሱ የተመለሱትን ከምርኮ ነፃ እንደሚያወጣቸው አስቀድሞ አስነግሮ ነበር! (ኢሳ. 41:8, 9፤ 49:8) ይሖዋ በዛሬው ጊዜም የእሱን ሞገስ ለማግኘት ከልብ ለሚፈልጉ ሰዎች የዚህ ዓይነት ርኅራኄ ያሳያቸዋል።—መዝ. 51:1

ታኩያ * የተባለውን ወንድም እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ ታኩያ፣ ፖርኖግራፊ (የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች) የመመልከት እንዲሁም ማስተርቤሽን የመፈጸም ርኩስ ልማዱን ለማሸነፍ ይታገል ነበር። ታኩያ ይህ ልማዱ በተደጋጋሚ ያገረሽበት ነበር። ታዲያ በዚህ ጊዜ ምን ይሰማው ነበር? እንዲህ ብሏል፦ “ፈጽሞ የማልረባ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር፤ ያም ቢሆን በጸሎት ወደ ይሖዋ ቀርቤ ምሕረት እንዲያደርግልኝ ስለምነው ከወደቅኩበት ያነሳኛል።” ይሖዋ ይህን የሚያደርግለት እንዴት ነበር? በታኩያ ጉባኤ ውስጥ ያሉት ሽማግሌዎች፣ ይህ መጥፎ ልማድ ሲያገረሽበት ስልክ እንዲደውልላቸው ነገሩት። ታኩያ እንዲህ ብሏል፦ “ለሽማግሌዎቹ ስልክ መደወል ቀላል አልነበረም፤ ይሁን እንጂ ስደውልላቸው የሚያስፈልገኝን ብርታት እንዳገኝ ይረዱኝ ነበር።” ከዚያም ሽማግሌዎቹ፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ለታኩያ እረኝነት እንዲያደርግለት ዝግጅት አደረጉ። የወረዳ የበላይ ተመልካቹም እንዲህ አለው፦ “ዛሬ የተገናኘነው በአጋጣሚ አይደለም። የመጣሁት ሽማግሌዎቹ እንድመጣ ስለፈለጉ ነው። ሽማግሌዎቹ፣ ለአንተ እረኝነት እንዳደርግልህ መርጠውሃል።” ታኩያ፣ “ኃጢአት የሠራሁት እኔ ሆኜ ሳለሁ ይሖዋ በሽማግሌዎቹ አማካኝነት እርዳታ ላከልኝ” ብሏል። ታኩያ እድገት አድርጎ የዘወትር አቅኚ ሆነ፤ በአሁኑ ጊዜ በአንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በማገልገል ላይ ይገኛል። ከዚህ ወንድም ተሞክሮ ማየት እንደምንችለው አምላክ አንተንም ከወደቅክበት ያነሳሃል።

መተዳደሪያ ስለማግኘት መጨነቅ

ብዙዎች ከሚያስጨንቋቸው ነገሮች አንዱ ሥራ ማጣት ነው። አንዳንዶች ከሥራ ከተባረሩ በኋላ ሌላ የገቢ ምንጭ ለማግኘት በጣም ይቸገራሉ። የተለያዩ ቦታዎች ለመቀጠር ብትሞክርም ሳይሳካልህ ቢቀር ምን እንደሚሰማህ አስበው። አንዳንዶች እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ለራሳቸው ያላቸው ግምት ይቀንሳል። ታዲያ ይሖዋ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋ የሚረዳህ ለአንተ የሚስማማ ሥራ ወዲያውኑ እንድታገኝ በማድረግ ላይሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ ንጉሥ ዳዊት የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ እንድታስታውስ ሊረዳህ ይችላል፦ “በአንድ ወቅት ወጣት ነበርኩ፤ አሁን ግን አርጅቻለሁ፤ ይሁንና ጻድቅ ሰው ሲጣል፣ ልጆቹም ምግብ ሲለምኑ አላየሁም።” (መዝ. 37:25) አዎ፣ ይሖዋ እጅግ ውድ እንደሆንክ አድርጎ ስለሚመለከትህ እሱን ማገልገልህን ለመቀጠል የሚያስፈልጉህን ነገሮች እንድታገኝ ‘በጽድቅ ቀኝ እጁ’ ይረዳሃል።

ሥራህን ብታጣ ይሖዋ የሚረዳህ እንዴት ሊሆን ይችላል?

በኮሎምቢያ የምትኖረው ሣራ የይሖዋን የማዳን ኃይል በሕይወቷ ተመልክታለች። በአንድ ስመ ጥር ኩባንያ ውስጥ ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኝ ሆኖም ጊዜዋንና ጉልበቷን የሚያሟጥጥ ሥራ ነበራት። ይሁንና በይሖዋ አገልግሎት የበለጠ ተሳትፎ ማድረግ ስለፈለገች ሥራዋን ለቀቀችና አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች። ይሁን እንጂ በሳምንት ውስጥ ለተወሰነ ሰዓት ብቻ የምትሠራው ሥራ ማግኘት ቀላል አልሆነላትም። አይስክሬም የምትሸጥበት አንድ አነስተኛ ሱቅ ከፍታ የነበረ ቢሆንም ቀስ በቀስ የነበራት ገንዘብ ስላለቀ ሱቁን ለመዝጋት ተገደደች። ሣራ “ይህ ከሆነ ሦስት ዓመታት ያለፉ ቢሆንም በይሖዋ እርዳታ ይህን ፈታኝ ሁኔታ በጽናት መወጣት ችያለሁ” ብላለች። ሣራ የቅንጦት ሕይወት በመኖርና መሠረታዊ በሆኑ ነገሮች በመርካት መካከል ያለውን ልዩነት እንዲሁም ለነገ አለመጨነቅን ተምራለች። (ማቴ. 6:33, 34) ከጊዜ በኋላ የቀድሞ አሠሪዋ ስልክ ደወለላትና በፊት የነበራትን ሥራ እንድትሠራ ጠየቃት። እሷም ሥራውን የምትቀበለው ለተወሰነ ሰዓት ብቻ እንድትሠራ የሚፈቀድላትና ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቿ ጊዜ የምታገኝ ከሆነ ብቻ እንደሆነ ገለጸችለት። ሣራ የቀድሞውን ያህል ገቢ ባታገኝም በአቅኚነቷ መቀጠል ችላለች። በዚህ ጊዜ ሁሉ የይሖዋ ፍቅራዊ እርዳታ እንዳልተለያት ተናግራለች።

ዕድሜ መግፋት የሚያስከትለው ጭንቀት

ሌላው አሳሳቢ ነገር ደግሞ የዕድሜ መግፋት ነው። ብዙ ሰዎች፣ ጡረታ የሚወጡበት ዕድሜ ላይ ሲደርሱ ቀሪ ሕይወታቸውን ሳይቸገሩ ለመኖር የሚያስችላቸው ገንዘብ ሊኖራቸው ይችል እንደሆነና እንዳልሆነ በማሰብ ይጨነቃሉ። በተጨማሪም ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ የጤና ችግሮች ያስጨንቋቸዋል። አንድ መዝሙራዊ “በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፤ ጉልበቴ በሚያልቅበት ጊዜም አትተወኝ” በማለት ይሖዋን ተማጽኖታል፤ ይህን ያለው ዳዊት ሳይሆን አይቀርም።—መዝ. 71:9, 18

ታዲያ የይሖዋ አገልጋዮች በእርጅና ዘመናቸው ያለ ስጋት ለመኖር ምን ሊረዳቸው ይችላል? አምላክ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች እንደሚሰጣቸው በመተማመን በእሱ ላይ ያላቸውን እምነት ማጠናከር ያስፈልጋቸዋል። እርግጥ ነው፣ ቀደም ሲል በድሎት ይኖሩ ከነበረ አሁን አኗኗራቸውን ማቅለልና ከቀድሞው ባነሰ ቁሳዊ ነገር ረክተው መኖር ሊኖርባቸው ይችላል። “የሰባ ፍሪዳ ከመብላት ይልቅ . . . አትክልት መብላት” የተሻለ እንዲያውም ከጤንነት አንጻር ጠቃሚ መሆኑን ይገነዘቡ ይሆናል። (ምሳሌ 15:17) በዋነኝነት ትኩረት የምትሰጡት ነገር ይሖዋን ማስደሰት ከሆነ እሱም በእርጅና ዘመናችሁ የሚያስፈልጋችሁን ነገር ይሰጣችኋል።

ሆሴ እና ሮዝ ከቶኒ እና ከዌንዲ ጋር

ከ65 ዓመታት በላይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሲካፈሉ የኖሩትን የሆሴን እና የሮዝን ሁኔታ እንመልከት። የ24 ሰዓት ትኩረት ያሻቸው የነበሩትን የሮዝን አባት ለዓመታት ተንከባክበዋል። በዚህ ላይ ደግሞ ሆሴ በካንሰር ምክንያት ቀዶ ሕክምና የተደረገለት ሲሆን የኬሞቴራፒ ሕክምና ወስዷል። ታዲያ ይሖዋ ለእነዚህ ታማኝ ባልና ሚስት ቀኝ እጁን ዘርግቶላቸዋል? አዎ! ግን እንዴት? ቶኒ እና ዌንዲ በሚባሉ የጉባኤያቸው አባላት የሆኑ ባልና ሚስት በመጠቀም ነው፤ ቶኒና ዌንዲ በዕድሜ ለገፉት ባልና ሚስት የሚኖሩበት አፓርታማ ሰጧቸው። ቶኒና ዌንዲ አፓርታማውን አቅኚዎች ኪራይ ሳይከፍሉ እንዲኖሩበት መስጠት ይፈልጉ ነበር። ቶኒ ከዓመታት በፊት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለ ሆሴና ዌንዲ ዘወትር በመስክ አገልግሎት ሲካፈሉ በመስኮት ያያቸው ነበር። በአገልግሎት ቀናተኛ በመሆናቸው የሚወዳቸው ሲሆን የእነሱ ምሳሌነት በሕይወቱ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል። ቶኒና ዌንዲ፣ እነዚህ አረጋዊ ባልና ሚስት መላ ሕይወታቸውን ለይሖዋ እንደሰጡ መመልከታቸው ቤታቸውን እንዲሰጧቸው አነሳሳቸው። በአሁኑ ጊዜ ሆሴና ሮዝ በ80ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የሚገኙ ሲሆን ቶኒና ዌንዲ ላለፉት 15 ዓመታት ሲረዷቸው ቆይተዋል። እነዚህ አረጋውያን ባልና ሚስት፣ በዕድሜ ከእነሱ የሚያንሱት ባልና ሚስት የሚያደርጉላቸውን እርዳታ ከይሖዋ የተገኘ ስጦታ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።

አምላክ ለአንተም ‘የጽድቅ ቀኝ እጁን’ ዘርግቶልሃል። ታዲያ “አትፍራ። እረዳሃለሁ” በማለት ቃል የገባልህን አምላክ እጅ በመያዝ ምላሽ ትሰጥ ይሆን?

^ አን.11 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።