በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አለባበሳችሁ አምላክን ያስከብራል?

አለባበሳችሁ አምላክን ያስከብራል?

“ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ።”—1 ቆሮ. 10:31

መዝሙሮች፦ 34, 61

1, 2. የይሖዋ ምሥክሮች ከአለባበስ ጋር በተያያዘ የላቁ መሥፈርቶችን ለመከተል የሚጥሩት ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

አንድ የደች ጋዜጣ፣ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ባደረጉት ስብሰባ ላይ የነበረውን ሁኔታ አስመልክቶ ሲዘግብ እንዲህ ብሏል፦ “አየሩ ሞቃት በመሆኑ የብዙዎቹ አለባበስ በመዝናኛ ቦታ እንደሚታየው ዓይነት ነው።” ጋዜጣው አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “በይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። ወንዶቹ (አዋቂዎችም ሆኑ ልጆች) ኮትና ክራባት ያደረጉ ሲሆን ትናንሾቹን ጨምሮ ሴቶቹ . . . ዘመናዊ ሆኖም በጣም አጭር ያልሆነ ቀሚስ ለብሰዋል።” በእርግጥም የይሖዋ ምሥክሮች ‘ልከኝነትና ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ’ የሚንጸባረቅበት እንዲሁም ‘የሚያስከብርና ለአምላክ ያደርን ነን’ ለሚሉ ሰዎች የሚገባ አለባበስ ስላላቸው ብዙዎች ያደንቋቸዋል። (1 ጢሞ. 2:9, 10 ግርጌ) ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን የጻፈው ስለ ሴቶች ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቱ ለክርስቲያን ወንዶችም ይሠራል።

2 የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ተገቢ አለባበስ ያለን መሆኑ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ሲሆን የምናመልከው አምላክም ቢሆን ይህን ጉዳይ ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። (ዘፍ. 3:21) ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ አለባበስና አጋጌጥ የያዙት ሐሳብ፣ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ እውነተኛ አገልጋዮቹ በአለባበስ ረገድ የላቀ መሥፈርት እንዲከተሉ እንደሚፈልግ በግልጽ ያሳያል። በመሆኑም ከአለባበስና ከአጋጌጥ ጋር በተያያዘ ምርጫችን እኛን በሚያስደስተን ነገር ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆን የለበትም። ሉዓላዊውን ጌታ ይሖዋን የሚያስደስተውንም ነገር ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል።

3. አምላክ ለእስራኤላውያን ከሰጠው ሕግ ስለ አለባበስ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

3 ለምሳሌ፣ አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግ በዙሪያቸው ያሉት ብሔራት የነበራቸውን ልቅ ሥነ ምግባር የተንጸባረቀበት አኗኗር እንዳይከተሉ የሚከለክሉ ደንቦችን የያዘ ነበር። አንድ ግለሰብ ወንድ ይሁን ሴት ለመለየት የሚያስቸግር አለባበስን ይሖዋ አጥብቆ እንደሚጠላ ሕጉ በግልጽ ያሳያል፤ በዛሬው ጊዜ ይህ ዓይነቱ አለባበስ ፋሽን እየሆነ መጥቷል። (ዘዳግም 22:5ን አንብብ።) አምላክ አለባበስን በተመለከተ ከሰጠው መመሪያ በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው ወንዶች ሴት እንዲመስሉ፣ ሴቶች ደግሞ ወንድ እንዲመስሉ አሊያም በሁለቱ ፆታዎች መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ አዳጋች እንዲሆን የሚያደርጉ አለባበሶችን አምላክ ይጠላል።

4. ክርስቲያኖች ከአለባበስ ጋር በተያያዘ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

4 የአምላክ ቃል፣ ክርስቲያኖች ከአለባበስ ጋር በተያያዘ ጥሩ ውሳኔ እንዲያደርጉ የሚረዷቸው መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል። ክርስቲያኖች የሚኖሩበት ቦታ፣ ባሕላቸው ወይም የአየሩ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የትኛው አለባበስ ተቀባይነት እንዳለውና የትኛው ደግሞ ተገቢ እንዳልሆነ የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያ አያስፈልገንም። በቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች የምንመራ ሲሆን እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንም ዓይነት የግል ምርጫ እንዳይኖረን የሚከለክሉ አይደሉም። እንግዲያው ከአለባበስ ጋር በተያያዘ “ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ” ለማወቅ የሚረዱንን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመልከት።—ሮም 12:1, 2

“ራሳችንን ብቁ የአምላክ አገልጋዮች አድርገን እናቀርባለን”

5, 6. አለባበሳችን በሌሎች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

5 ሐዋርያው ጳውሎስ በ2 ቆሮንቶስ 6:4 (ጥቅሱን አንብብ) ላይ የሚገኘውን አስፈላጊ መሠረታዊ ሥርዓት በመንፈስ መሪነት ጽፏል። አለባበሳችን ስለ እኛ ብዙ ይናገራል። ብዙ ሰዎች እኛን የሚመዝኑን ‘ውጫዊ ገጽታችንን’ ተመልክተው ነው። (1 ሳሙ. 16:7) በመሆኑም የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ለእኛ የሚመቸንንና የምንወደውን ነገር ከመልበስ ባለፈ ልናስብበት የሚገባ ነገር አለ። በአምላክ ቃል ውስጥ የሰፈሩት መሠረታዊ ሥርዓቶች፣ ሰውነት ላይ የሚጣበቅና ገላን የሚያጋልጥ ወይም የፆታ ስሜት የሚያነሳሳ ልብስ ከመልበስ እንድንቆጠብ ይገፋፉናል። ይህም ሲባል እርቃንን የሚያጋልጡ ወይም የሰውነትን ቅርጽ አጉልተው የሚያሳዩ ልብሶችን ማስወገድ አለብን ማለት ነው። አለባበሳችን ሌሎችን የሚያሸማቅቅ ወይም ዓይናቸውን የት እንደሚያሳርፉ እንዲጨንቃቸው የሚያደርግ መሆን የለበትም።

6 ሥርዓታማ፣ ንጹሕና ልከኛ አለባበስ ካለን ሰዎች የሉዓላዊው ጌታ የይሖዋ አገልጋዮች በመሆናችን ያከብሩናል። በተጨማሪም አለባበሳችን ወደምናመልከው አምላክ እንዲቀርቡ ሊያነሳሳቸው ይችላል። ተገቢ የሆነ አለባበስ ለይሖዋ ድርጅትም ክብር ያመጣል። ይህም ሰዎች ለምንነግራቸው ሕይወት አድን መልእክት ጆሮ እንዲሰጡ ሊያደርግ ይችላል።

7, 8. ለአለባበሳችን የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን መቼ ነው?

7 ቅዱስ ለሆነው አምላካችን፣ ለመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም በክልላችን ላሉ ሰዎች ያለን አክብሮት ለምንሰብከው መልእክትም ሆነ ለይሖዋ ክብር የሚያመጣ አለባበስ እንዲኖረን ያነሳሳናል። (ሮም 13:8-10) በተለይ ደግሞ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ስንካፈል ለምሳሌ፣ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ወይም ምሥራቹን ስንሰብክ ለአለባበሳችን ትኩረት መስጠት ይኖርብናል። አለባበሳችን “ለአምላክ ያደርን ነን” ለሚሉ ሰዎች የሚገባ መሆን ይኖርበታል። (1 ጢሞ. 2:10) እርግጥ ነው፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ተገቢ የሚባለው አለባበስ በሌሎች አካባቢዎች ተገቢ ላይሆን ይችላል። በመሆኑም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች ሌሎችን ቅር ላለማሰኘት ሲሉ የአካባቢውን ባሕል ግምት ውስጥ ያስገባሉ።

አለባበስህ ሰዎች ለምታመልከው አምላክ አክብሮት እንዲያድርባቸው ያደርጋል? (አንቀጽ 7, 8⁠ን ተመልከት)

8 አንደኛ ቆሮንቶስ 10:31ን አንብብ። በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ አለባበሳችን በዓለም ላይ የተለመደውን ወጣ ያለ ፋሽን የሚያንጸባርቅ ሳይሆን ተገቢና ልከኛ ሊሆን ይገባል። ሆቴል ስንይዝም ሆነ ሆቴሉን ለቅቀን ስንወጣ እንዲሁም ከስብሰባው በፊትና በኋላ ባሉት ጊዜያት ስንዝናና፣ አለባበሳችን ቅጥ ያጣ ወይም የተዝረከረከ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን። እንዲህ ካደረግን የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ለመናገር አንሸማቀቅም። ለመመሥከር የሚያስችል አጋጣሚ ካገኘንም ነፃነት ተሰምቶን እንመሠክራለን።

9, 10. ፊልጵስዩስ 2:4⁠ን ከአለባበስ ምርጫችን ጋር በተያያዘ ተግባራዊ ልናደርገው የሚገባው ለምንድን ነው?

9 ፊልጵስዩስ 2:4ን አንብብ። ክርስቲያኖች አለባበሳቸው በእምነት ባልንጀሮቻቸው ላይ ምን ስሜት እንደሚፈጥር ማሰብ ያለባቸው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት የአምላክ ሕዝቦች የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የሚጥሩ መሆኑ ነው፤ ጥቅሱ “በምድር ያሉትን የአካል ክፍሎቻችሁን ግደሉ፤ እነሱም የፆታ ብልግና፣ ርኩሰት፣ ልቅ የሆነ የፍትወት ስሜት . . . ናቸው” ይላል። (ቆላ. 3:2, 5) የእምነት ባልንጀሮቻችን ይህን ምክር በተግባር ማዋል ከባድ እንዲሆንባቸው ማድረግ አንፈልግም። ልቅ የፆታ ሥነ ምግባር የነበራቸውና እንዲህ ዓይነቱን ሕይወት የተዉ ወንድሞችና እህቶች የኃጢአት ዝንባሌዎች እንዳያሸንፏቸው መታገል ይኖርባቸው ይሆናል። (1 ቆሮ. 6:9, 10) ታዲያ እኛ ትግሉ ከባድ እንዲሆንባቸው ማድረግ እንፈልጋለን?

10 ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በምንሆንበት ጊዜ ለአለባበሳችን የምንጠነቀቅ ከሆነ ጉባኤው ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃ የሚጠብቁ ሰዎች ያሉበት ቦታ እንዲሆን አስተዋጽኦ እናደርጋለን። በስብሰባዎችም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ከወንድሞቻችን ጋር ስንሆን ይህን ማስታወስ ይኖርብናል። እርግጥ የምንለብሰውን ነገር የመምረጥ ነፃነት አለን። ያም ሆኖ ሁላችንም፣ ሌሎች በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆነው መመላለስ እንዲሁም በአስተሳሰባቸው፣ በንግግራቸውና በድርጊታቸው የአምላክን የቅድስና መሥፈርቶች መጠበቅ ቀላል እንዲሆንላቸው የሚያደርግ አለባበስ የመምረጥ ኃላፊነት ተጥሎብናል። (1 ጴጥ. 1:15, 16) እውነተኛ ፍቅር “ጨዋነት የጎደለው ምግባር አያሳይም፣ የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም።”—1 ቆሮ. 13:4, 5

ለወቅቱና ለቦታው የሚስማማ አለባበስ

11, 12. ከአለባበሳችን ጋር የተያያዘ ውሳኔ ስናደርግ በአእምሯችን ልንይዘው የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

11 የአምላክ አገልጋዮች አለባበስን በተመለከተ ውሳኔ ሲያደርጉ “ማንኛውም ድርጊትና ማንኛውም ተግባር ጊዜ አለው” የሚለውን ጥቅስ በአእምሯቸው ይይዛሉ። (መክ. 3:1, 17) የአየሩ ጠባይ፣ የወቅቶች መለዋወጥ እንዲሁም የተለያዩ ሁኔታዎች በአለባበሳችን ላይ ተጽዕኖ እንደሚያደርጉ የታወቀ ነው። የይሖዋ መሥፈርቶች ግን እንደ አየሩ ጠባይ አይለዋወጡም።—ሚል. 3:6

12 በተለይ በሞቃት አካባቢዎች አለባበሳችን ሥርዓታማ እንዲሁም ማስተዋልና ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ የተንጸባረቀበት እንዲሆን ማድረግ ፈታኝ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም በጣም የተጣበቀ ወይም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ሰውነትን የሚያጋልጥ ልብስ ከመልበስ ብንቆጠብ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ደስ ይላቸዋል። (ኢዮብ 31:1) በተጨማሪም በባሕር ዳርቻዎች ወይም በመዋኛ ስፍራዎች በምንዝናናበት ጊዜ የዋና ልብሳችን ሥርዓታማ ሊሆን ይገባል። (ምሳሌ 11:2, 20) በዓለም ላይ ብዙዎች ሰውነትን የሚያጋልጥ የዋና ልብስ ቢለብሱም እንኳ እኛ የይሖዋ አገልጋዮች ቅዱስ የሆነውንና የምንወደውን አምላካችንን የሚያስከብር አለባበስ ሊኖረን ይገባል።

13. በ1 ቆሮንቶስ 10:32, 33 ላይ የሚገኘው ምክር በአለባበስ ምርጫችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚገባው ለምንድን ነው?

13 ተገቢ አለባበስ እንዲኖረን የሚረዳን ሌላም ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓት አለ። ስለ እምነት ባልንጀሮቻችንም ሆነ ስለ ሌሎች ሕሊና ልናስብ ይገባል። (1 ቆሮንቶስ 10:32, 33ን አንብብ።) አለባበሳችን ሌሎችን ቅር የሚያሰኝ እንዳይሆን የተሰጠንን ምክር በቁም ነገር መመልከት ይኖርብናል። ጳውሎስ “እያንዳንዳችን ባልንጀራችንን የሚጠቅመውንና የሚያንጸውን ነገር በማድረግ እናስደስተው” በማለት ጽፏል። ይህን ያለበትን ምክንያት ሲገልጽ “ክርስቶስ እንኳ ራሱን አላስደሰተም” ብሏል። (ሮም 15:2, 3) በእርግጥም ኢየሱስ ከራሱ ምቾት ይልቅ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግና ሌሎችን ለመርዳት ቅድሚያ ይሰጥ ነበር። እኛም ምሥራቹን የምንነግራቸው ሰዎች ጆሯቸውን እንዳይሰጡን የሚያደርጉ ልብሶችንም ሆነ ፋሽኖችን፣ የምንወዳቸው ቢሆኑም እንኳ ልናስወግዳቸው ይገባል።

14. ወላጆች፣ አምላክን የሚያስከብር አለባበስ እንዲኖራቸው ልጆቻቸውን ሊያሠለጥኑ የሚችሉት እንዴት ነው?

14 ክርስቲያን ወላጆች፣ የቤተሰባቸው አባላት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ እንዲያደርጉ የማሠልጠን ኃላፊነት አለባቸው። ይህም ሲባል እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው በአለባበሳቸውና በአጋጌጣቸው ልከኛ በመሆን የአምላክን ልብ ደስ ለማሰኘት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል ማለት ነው። (ምሳሌ 22:6፤ 27:11) ወላጆች ለሚያመልኩት ቅዱስ አምላክ ልጆቻቸው አክብሮት እንዲያዳብሩ ለመርዳት፣ እነሱ ራሳቸው ጥሩ ምሳሌ መሆን እንዲሁም ፍቅር የተንጸባረቀበትና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መመሪያ መስጠት ይኖርባቸዋል። ልጆች ተገቢ የሆነ ልብስ ማግኘት የሚችሉት የትና እንዴት እንደሆነ ወላጆቻቸው ሊያስተምሯቸው ይገባል። ይህም እነሱ የወደዱትን ብቻ ሳይሆን የይሖዋ ምሥክር መሆን የሚያስከትልባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችላቸውንም ልብስ እንዲመርጡ መርዳትን ይጨምራል።

የመምረጥ ነፃነታችሁን በጥበብ ተጠቀሙበት

15. በአለባበስ ረገድ ጥበብ የተንጸባረቀበት ምርጫ ለማድረግ ምን ይረዳናል?

15 የአምላክ ቃል፣ ይሖዋን የሚያስከብር ጥበብ የተንጸባረቀበት ምርጫ ለማድረግ የሚረዱን ጠቃሚ መመሪያዎች ይዟል። ያም ቢሆን በአለባበስ ረገድ የራሳችንን ምርጫ ማድረግ እንችላለን። የገንዘብ አቅማችንም ሆነ ምርጫችን ሊለያይ ይችላል። ይሁንና ልብሳችን ምንጊዜም ያልተዝረከረከ፣ ንጹሕ፣ ልከኛና ለሁኔታው የሚስማማ እንዲሁም በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሆን ይኖርበታል።

16. ተገቢ አለባበስ እንዲኖረን የምናደርገው ጥረት አያስቆጭም የምንለው ለምንድን ነው?

16 ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ የተንጸባረቀበት፣ ማስተዋል የተሞላበትና ሁሉንም ነገሮች ግምት ውስጥ ያስገባ ውሳኔ ማድረግ ቀላል የማይሆንበት ጊዜ እንዳለ እሙን ነው። አብዛኞቹ ሱቆች የሚያቀርቡት በወቅቱ ፋሽን የሆነውን ነገር ስለሆነ ልከኛ የሆነ ቀሚስና የቀሚስ አላባሽ አሊያም በጣም ያልተጣበቀ ሙሉ ልብስ ወይም ሱሪ ለማግኘት ብዙ ጊዜና ጥረት ይጠይቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ ደስ የሚልና ተገቢ የሆነ ልብስ ለማግኘት የምናደርገውን ልባዊ ጥረት የእምነት ባልንጀሮቻችን ማስተዋላቸውና ማድነቃቸው አይቀርም። በተጨማሪም በሰማይ ያለውን አፍቃሪ አባታችንን የሚያስከብር አለባበስ እንዲኖረን ለማድረግ ስንል ምንም ያህል መሥዋዕትነት ብንከፍል የሚያስቆጭ አይደለም።

17. አንድ ወንድም ጢም ከማሳደግ ጋር በተያያዘ ግምት ውስጥ ሊያስገባቸው የሚገቡ ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?

17 በሌላ በኩል ደግሞ ወንድሞች ጢማቸውን ማሳደጋቸውስ ተገቢ ነው? በሙሴ ሕግ ሥር ወንዶች ጢማቸውን ማሳደግ ይጠበቅባቸው ነበር። ክርስቲያኖች ግን በሙሴ ሕግ ሥር ስላልሆኑ ሕጉን የማክበር ግዴታ የለባቸውም። (ዘሌ. 19:27፤ 21:5፤ ገላ. 3:24, 25) በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ፣ አንድ ወንድም ጢሙን ሥርዓታማ በሆነ መንገድ እስከተከረከመ ድረስ ጢሙን ማሳደጉ ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል፤ እንዲህ ማድረጉ ሰዎች እንዳያከብሩትና የመንግሥቱን መልእክት እንዳይቀበሉ እንቅፋት አይፈጥርም። ጢማቸውን የሚያሳድጉ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞችም አሉ። ያም ቢሆን አንዳንድ ወንድሞች ጢማቸውን ላለማሳደግ ይወስኑ ይሆናል። (1 ቆሮ. 8:9, 13፤ 10:32) በሌሎች ባሕሎች ወይም አካባቢዎች ደግሞ ጢም ማሳደግ የተለመደ አይደለም፤ በመሆኑም ክርስቲያን አገልጋዮች እንዲህ ማድረጋቸው ተቀባይነት የለውም። እንዲያውም አንድ ወንድም ጢሙን የሚያሳድግ ከሆነ በአለባበሱና በአጋጌጡ አምላክን የሚያስከብር ብሎም የማይነቀፍ ሰው እንደሆነ ተደርጎ ላይቆጠር ይችላል።—ሮም 15:1-3፤ 1 ጢሞ. 3:2, 7

18, 19. አለባበሳችን አምላክን የሚያስደስት እንዲሆን ሚክያስ 6:8 የሚረዳን እንዴት ነው?

18 ይሖዋ አለባበሳችንንና አጋጌጣችንን በተመለከተ ዝርዝር መመሪያዎች በመስጠት ሸክም ስላልጫነብን አመስጋኞች ነን። ይሖዋ እያንዳንዳችን የመምረጥ ነፃነታችንን በመጠቀም ማስተዋል የታከለበት እንዲሁም ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ከግምት ያስገባ ውሳኔ እንድናደርግ ፈቅዶልናል። በመሆኑም በአለባበሳችንና በአጋጌጣችንም ጭምር ‘ልካችንን አውቀን ከአምላካችን ጋር መሄድ’ እንችላለን።—ሚክ. 6:8

19 ልክን ማወቅ ሲባል ይሖዋ ንጹሕና ቅዱስ መሆኑን እንዲሁም እሱ ያወጣቸው መሥፈርቶች ከሁሉ የላቁ መሆናቸውን መገንዘብን ይጨምራል። ትሑቶችና ልካችንን የምናውቅ ከሆንን በሕይወታችን ውስጥ የእሱን መሥፈርቶች እንከተላለን። ልክን ማወቅ የሌሎችን ስሜትና አመለካከት ማክበርንም ይጨምራል። እንግዲያው ከይሖዋ የላቁ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን በመኖር እንዲሁም የሌሎችን ስሜት በማክበር ‘ልካችንን አውቀን ከአምላክ ጋር እንደምንሄድ’ እናሳይ።

20. አለባበሳችንና አጋጌጣችን ሌሎች ስለ እኛ ምን አመለካከት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ሊሆን ይገባል?

20 አለባበሳችን ሰዎች የይሖዋ አገልጋዮች መሆናችንን እንዲጠራጠሩ የሚያደርግ መሆን የለበትም። ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ጻድቅ የሆነውን አምላካችንን ለመወከል እንደምንበቃ ሊሰማቸው ይገባል። ይሖዋ የላቁ መሥፈርቶች አሉት፤ እኛም እነዚህን መሥፈርቶች ደስ እያለን በሕይወታችን ተግባራዊ እናደርጋለን። ግሩም አለባበስና ምግባር ያላቸው ወንድሞችና እህቶች፣ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ሕይወት አድን የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት እንዲቀበሉ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋን ያስከብራሉ እንዲሁም ያስደስታሉ፤ ለዚህም ሊመሰገኑ ይገባል። በአለባበሳችን ረገድ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ማድረጋችን “ሞገስንና ግርማን” ለተላበሰው አምላክ ምንጊዜም ክብር እንደሚያመጣ ምንም ጥርጥር የለውም።—መዝ. 104:1, 2