በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ሥራው ታላቅ ነው’

‘ሥራው ታላቅ ነው’

በኢየሩሳሌም አንድ በጣም አስፈላጊ ስብሰባ እየተካሄደ ነው። ንጉሥ ዳዊት መኳንንቱን፣ የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣናቱን እንዲሁም ኃያላኑን በሙሉ ሰበሰበ። ሁሉም በስብሰባው ላይ አንድ ልዩ ማስታወቂያ በመስማታቸው በጣም ተደሰቱ። ይሖዋ፣ የዳዊት ልጅ የሆነውን ሰለሞንን ለእሱ አምልኮ የሚሆን ታላቅ ቤተ መቅደስ እንዲሠራ መርጦታል። ይሖዋ የሕንፃውን ንድፍ በዕድሜ ለገፋው የእስራኤል ንጉሥ በመንፈስ የገለጠለት ሲሆን ንጉሡም ይህን ንድፍ ለሰለሞን ሰጠው። ከዚያም ዳዊት “ሥራው . . . ታላቅ ነው፤ ቤተ መቅደሱ የሚሠራው ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ አምላክ ነውና” በማለት ተናገረ።—1 ዜና 28:1, 2, 6, 11, 12፤ 29:1

ዳዊት በመቀጠል “ታዲያ ዛሬ ለይሖዋ የሚሰጥ ስጦታ በእጁ ይዞ ለመቅረብ ፈቃደኛ የሆነ ማን ነው?” ሲል ጠየቀ። (1 ዜና 29:5) አንተ በቦታው ብትኖር ኖሮ ምን ምላሽ ትሰጥ ነበር? ይህን ታላቅ ሥራ ለመደገፍ ትነሳሳ ነበር? እስራኤላውያን ፈጣን ምላሽ ሰጡ። ዘገባው እንደሚገልጸው “በፈቃደኝነት መባ በመስጠታቸው እጅግ ተደሰቱ፤ በፈቃደኝነት ተነሳስተው ለይሖዋ መባ የሰጡት በሙሉ ልባቸው ነበርና።”—1 ዜና 29:9

ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ ይሖዋ ከቤተ መቅደሱ የሚበልጥ ዝግጅት አደረገ። ታላቁን መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ፣ ይኸውም በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ሰዎች እሱን ማምለክ የሚችሉበትን ዝግጅት አቋቋመ። (ዕብ. 9:11, 12) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ሰዎች ከእሱ ጋር እንዲታረቁ እያደረገ ያለው እንዴት ነው? ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራችን አማካኝነት ነው። (ማቴ. 28: 19, 20) በዚህ ሥራችን የተነሳ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይመራሉ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ደቀ መዛሙርት ይጠመቃሉ፤ እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ጉባኤዎች ይመሠረታሉ።

እንዲህ ያለ እድገት መኖሩ ደግሞ ተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማተም፣ የመንግሥት አዳራሾችን መገንባትና ማደስ እንዲሁም የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾችን ማግኘት አስፈላጊ እንዲሆን ያደርጋል። ምሥራቹን የማስፋፋቱ ሥራ ታላቅና የሚክስ ነው ቢባል አትስማማም?—ማቴ. 24:14

የአምላክ ሕዝቦች ለአምላክና ለባልንጀራቸው ፍቅር ያላቸው መሆኑ እንዲሁም የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ አጣዳፊ መሆኑን መገንዘባቸው፣ በፈቃደኝነት መዋጮ በማድረግ ‘ለይሖዋ የሚሰጥ ስጦታ በእጃቸው ይዘው እንዲቀርቡ’ ያነሳሳቸዋል። ‘ባሉን ውድ ነገሮች ይሖዋን ማክበር’ መቻላችን እንዲሁም ድርጅቱ የምናደርገውን መዋጮ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከሁሉ ይበልጥ ታላቅ የሆነውን ሥራ ለመሥራት በታማኝነትና በጥበብ ሲጠቀምበት ማየታችን ምንኛ አስደሳች ነው!—ምሳሌ 3:9