በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከታሪክ ማኅደራችን

“በብሪታንያ የምትገኙ የመንግሥቱ አስፋፊዎች—ንቁ!”

“በብሪታንያ የምትገኙ የመንግሥቱ አስፋፊዎች—ንቁ!”

“በብሪታንያ የምትገኙ የመንግሥቱ አስፋፊዎች—ንቁ!!” የሚል አስቸኳይ ጥሪ ቀረበ። (ኢንፎርማንት፣ * ታኅሣሥ 1937 የለንደን እትም) ይህን ጥሪ በያዘው ርዕስ ሥር “ለአሥር ዓመት ያህል ጎልቶ የሚታይ እድገት አልተመዘገበም” የሚል ትኩረት የሚስብ ንዑስ ርዕስ ይገኛል። በኢንፎርማንት የፊት ገጽ ላይ የሚገኘው ከ1928 እስከ 1937 ያለውን የአሥር ዓመት የአገልግሎት እንቅስቃሴ የሚያሳየው ሪፖርት ይህን ግልጽ አድርጎታል።

የአቅኚዎች ቁጥር በጣም በዝቶ ነበር?

በብሪታንያ የነበረው የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴ እንዲዳከም ያደረገው ምን ነበር? ጉባኤዎቹ ከብዙ ዓመታት በፊት የነበራቸውን አካሄድ ይከተሉ የነበረ ሲሆን ቅንዓታቸው የቀዘቀዘ ይመስል ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ቅርንጫፍ ቢሮው፣ ክልሉ ማስተናገድ የሚችለው 200 ያህል አቅኚዎችን ብቻ እንደሆነ ወስኖ ነበር፤ እነዚህ አቅኚዎችም ከጉባኤዎች ጋር ሆነው ከማገልገል ይልቅ ገለልተኛ በሆኑ ክልሎች ላይ ይሠሩ ነበር። በመሆኑም ቅርንጫፍ ቢሮው፣ አቅኚ መሆን ያሰቡ ክርስቲያኖችን በብሪታንያ ውስጥ እነሱ ሊያገለግሉ የሚችሉበት በቂ ክልል ስለሌለ ወደ ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ሄደው ቢያገለግሉ እንደሚሻል አበረታታቸው። በርካታ አቅኚዎች ብሪታንያን በመልቀቅ እንደ ፈረንሳይ ወዳሉ አገሮች መዛወራቸው የሚያስመሰግናቸው ነው፤ እነዚህ ክርስቲያኖች የሄዱበትን አካባቢ ቋንቋ ያን ያህል ወይም ጨርሶ ባይችሉም የተሰጣቸውን መመሪያ ታዘዋል።

“ለተግባር የሚያነሳሳ ጥሪ”

በ1937ቱ ኢንፎርማንት ላይ የወጣው ርዕስ በ1938 ከፍተኛ የሰዓት ግብ ላይ ለመድረስ ይኸውም አንድ ሚሊዮን ሰዓት ለማገልገል እንደታሰበ ይገልጻል! አስፋፊዎች በየወሩ 15 ሰዓት አቅኚዎች ደግሞ 110 ሰዓት ቢያገለግሉ በቀላሉ እዚህ ግብ ላይ መድረስ ይቻላል። ጉባኤዎች ይህን ለማድረግ እንዲችሉ ከቀረቡት ሐሳቦች መካከል የመስክ ስምሪት ቡድኖችን ማደራጀትና በቀን አምስት ሰዓት የሚገለገልባቸው ቀናት መመደብ እንዲሁም በተለይ በሥራ ቀናት ምሽት ላይ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ትኩረት መስጠት ይገኙበታል።

አቅኚዎች በመስክ አገልግሎት በቅንዓት ሲካፈሉ

በዚህ መልኩ ለአገልግሎት ለየት ያለ ትኩረት መሰጠቱ ብዙዎችን አስደስቷል። ሂልዳ ፓጄት * እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “ከዋናው መሥሪያ ቤት የመጣውን ይህን ለተግባር የሚያነሳሳ ጥሪ ለረጅም ጊዜ ስንጠብቀው ቆይተናል፤ ደግሞም ብዙም ሳይቆይ ግሩም ውጤት አስገኝቷል።” እህት ዋለስ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “በቀን አምስት ሰዓት እንድናገለግል የተሰጠው ጥቆማ በጣም ግሩም ነው! ለጌታ አገልግሎት ሙሉ ቀን ከማዋል የበለጠ ምን የሚያስደስት ነገር አለ? . . . ከአገልግሎት ስንመለስ ቢደክመንም እንኳ በጣም እንደሰታለን!” በወቅቱ ወጣት የነበረው ስቲቨን ሚለር የጉዳዩን አስቸኳይነት በመረዳቱ ለጥሪው ምላሽ ሰጥቷል። አጋጣሚው ሳያልፈው ሊጠቀምበት ፈልጎ ነበር! አስፋፊዎች በቡድን ሆነው በብስክሌታቸው እየሄዱ ሙሉ ቀን ያገለግሉ፣ በበጋ ወቅት ምሽት ላይ ደግሞ የተቀዱ ንግግሮችን ያጫውቱ እንደነበር ያስታውሳል። መልእክቶችን የያዙ ሰሌዳዎችን ይዘው ሰልፍ በመውጣት እንዲሁም መንገድ ላይ መጽሔቶችን በማበርከት በቅንዓት ያገለግሉ ነበር።

ኢንፎርማንት “1,000 የአቅኚዎች ሠራዊት ያስፈልገናል” የሚል ማሳሰቢያም ይዞ ወጥቶ ነበር። በአዲሱ የክልሎች ፖሊሲ መሠረት፣ አቅኚዎች ከጉባኤዎች ተለይተው ሳይሆን ከጉባኤዎቹ ጋር አብረው እየሠሩ እንዲደግፏቸውና እንዲያንጿቸው ተደርጎ ነበር። ጆይስ ኤሊስ (ከማግባቷ በፊት ጆይስ ባርበር) እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ወንድሞች አቅኚ መሆን እንዳለባቸው እየተገነዘቡ ነበር። በወቅቱ ገና የ13 ዓመት ልጅ ብሆንም ፍላጎቴ አቅኚ መሆን ነበር።” እህት ኤሊስ፣ ሐምሌ 1940 በ15 ዓመቷ ግቧ ላይ መድረስ ቻለች። ከጊዜ በኋላ ጆይስን ያገባው ፒተርም “ንቁ” የሚለውን ጥሪ መስማቱ “አቅኚ ለመሆን እንዲያስብ” አነሳሳው። ሰኔ 1940 ፒተር 17 ዓመት ሲሆነው በብስክሌት 105 ኪሎ ሜትር በመጓዝ የመጀመሪያ የአቅኚነት ምድቡ ወደሆነው ወደ ስካርበሮ ሄደ።

የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ካሳዩት አዲስ አቅኚዎች መካከል ሲሪል እና ኪቲ ጆንሰን ይገኙበታል። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሲካፈሉ ወጪያቸውን ለመሸፈን እንዲችሉ ቤታቸውንና ንብረታቸውን ሸጡ። ሲሪል ሥራውን የለቀቀ ሲሆን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አቅኚነት ለመጀመር የሚያስፈልጋቸውን ዝግጅት አጠናቀቁ። ሲሪል እንዲህ ሲል ያስታውሳል፦ “ይህን ያደረግነው በልበ ሙሉነት ነበር። በፈቃደኝነትና በደስታ ይህን እርምጃ ወስደናል።”

የአቅኚዎች ቤት ተቋቋመ

የአቅኚዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ሲሄድ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ይህን እያደገ ያለ ሠራዊት መደገፍ ስለሚቻልባቸው መንገዶች ማሰብ ጀመሩ። በ1938 የዞን አገልጋይ (አሁን የወረዳ የበላይ ተመልካች ይባላል) የነበረው ጂም ካር፣ በከተሞች ውስጥ አቅኚዎች አንድ ላይ የሚኖሩባቸው ቤቶች እንዲያዘጋጅ የቀረበለትን ሐሳብ ተግባራዊ አድርጓል። አቅኚዎች ወጪያቸውን መቀነስ እንዲችሉ በቡድን ሆነው እንዲኖሩና እንዲያገለግሉ ማበረታቻ ተሰጣቸው። ወንድሞች በሼፊልድ አንድ ትልቅ ቤት ከተከራዩ በኋላ ኃላፊነት ያለው አንድ ወንድም በበላይነት እንዲከታተለው አደረጉ። በአካባቢው የሚገኘው ጉባኤ በገንዘብ እንዲሁም የቤት ዕቃዎችን በማሟላት እርዳታ አበረከተ። ጂም “ዝግጅቱ የተሳካ እንዲሆን ለማድረግ ሁሉም ተባብረው ሠርተዋል” በማለት ተናግሯል። አሥር ቀናተኛ አቅኚዎች በዚያ ቤት አብረው የኖሩ ሲሆን ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ነበራቸው። “ማለዳ ላይ ቁርስ ሲመገቡ [በዕለቱ ጥቅስ] ላይ ይወያያሉ”፤ ከዚያም “አቅኚዎቹ በከተማው የተለያየ ክፍል ወደሚገኙት ክልሎቻቸው በየዕለቱ እየሄዱ ያገለግላሉ።”

በብሪታንያ የሚያገለግሉ አቅኚዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ጨመረ

አስፋፊዎችም ሆኑ አቅኚዎች ለጥሪው ምላሽ በመስጠታቸው በ1938 አንድ ሚሊዮን ሰዓት የማገልገል ግባቸው ላይ ደረሱ። እንዲያውም ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በሁሉም የአገልግሎት እንቅስቃሴዎች ላይ ጭማሪ ታይቷል። በአምስት ዓመት ውስጥ በብሪታንያ የአስፋፊዎች ቁጥር በሦስት እጥፍ ገደማ አደገ። ለመንግሥቱ አገልግሎት የተሰጠው ልዩ ትኩረት የይሖዋን ሕዝቦች በቀጣዮቹ ዓመታት በጦርነቱ ምክንያት ለሚገጥሟቸው ፈተናዎች አዘጋጅቷቸዋል።

አምላክ የሚያካሂደው የአርማጌዶን ጦርነት እየተቃረበ ባለበት በአሁኑ ወቅትም በብሪታንያ የሚገኙት አቅኚዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ባለፈው አሥር ዓመት ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ከፍተኛ የአቅኚዎች ቁጥር ተመዝግቧል፤ በጥቅምት 2015 የተገኘው ከፍተኛ የአቅኚዎች ቁጥር 13,224 ነበር። እነዚህ አቅኚዎች፣ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት በሕይወታቸው ውስጥ ሊያከናውኑት የሚችሉት ከሁሉ የተሻለ ሥራ እንደሆነ በሚገባ ተገንዝበዋል።

^ አን.3 ከጊዜ በኋላ የመንግሥት አገልግሎታችን ተብሏል።

^ አን.8 የእህት ፓጄት የሕይወት ታሪክ በጥቅምት 1, 1995 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 19-24 ላይ ይገኛል።