በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስህተትን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መመልከት

ስህተትን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መመልከት

ዶንና ማርጋሬት * ሴት ልጃቸውና ቤተሰቧ ሊጠይቋቸው በመምጣታቸው ተደስተዋል። በምግብ ሥራ የሠለጠነች ባለሙያ የነበረችው ማርጋሬት፣ ከመለያየታቸው በፊት ሁለቱ የልጅ ልጆቿ በጣም የሚወዱትን ማካሮኒ በቺዝ አዘጋጀች።

ሁሉም ለመመገብ ሲቀርቡ ማርጋሬት የሠራችውን ምግብ አምጥታ ጠረጴዛው መሃል ላይ አስቀመጠችው። ከዚያም ክዳኑን ስትከፍተው በጎድጓዳ ሳህኑ ውስጥ ያለው ትኩስ የቺዝ ስጎ ብቻ ነበር! ማርጋሬት ዋናውን ነገር ማለትም ማካሮኒውን መጨመር እንደረሳች ስታውቅ በጣም ደነገጠች!

በየትኛውም ዕድሜ ላይ ብንገኝ ወይም ምንም ያህል ተሞክሮ ቢኖረን ሁላችንም ብንሆን ስህተት መሥራታችን አይቀርም። አሳቢነት የጎደለው ቃል እንናገር፣ አንድን ነገር ተገቢ ባልሆነ ጊዜ እናደርግ፣ ወይም ማድረግ ያለብንን ነገር እንረሳ ይሆናል። ሆኖም ስህተት የምንሠራው ለምንድን ነው? በምንሳሳትበት ወይም ሌሎች ሰዎች ስህተት በሚሠሩበት ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል? የምንሠራቸውን ስህተቶች ለመቀነስ ማድረግ የምንችለው ነገር አለ? ስህተትን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መመልከታችን የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ይረዳናል።

የሰው ልጆችና አምላክ ስህተትን የሚመለከቱበት መንገድ

አንድ ሰው ለሠራነው ጥሩ ነገር ቢያመሰግነን ምስጋናውን ደስ ብሎን እንቀበላለን። ታዲያ ስህተት በምንሠራበት ጊዜስ መሳሳታችንን አምነን መቀበላችን ተገቢ አይሆንም? ይህን ማድረግ የሚኖርብን ስህተት የሠራነው ሆን ብለን በማይሆንበት ወይም ሌሎች ስህተታችንን በማያስተውሉበት ጊዜም ጭምር ነው። እርግጥ ይህን ማድረግ ትሕትና ይጠይቃል።

ራሳችንን ከፍ አድርገን የምንመለከት ከሆነ የሠራነውን ስህተት አቅልለን ልንመለከት፣ በሌሎች ላይ ልናላክክ አልፎ ተርፎም ልንክድ እንችላለን። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ አብዛኛውን ጊዜ መጥፎ መዘዝ ያስከትላል። ችግሩ ሳይፈታ ሊቀርና ሌሎች ሰዎችም ያለጥፋታቸው ሊወቀሱ ይችላሉ። ለጊዜው ስህተታችንን አለባብሰን ማለፍ ብንችልም እንኳ የኋላ ኋላ “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ [መስጠታችን]” እንደማይቀር ማስታወስ ያስፈልገናል።—ሮም 14:12

አምላክ ስህተትን የሚመለከተው ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ነው። በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸው አምላክ “መሐሪና ርኅሩኅ” ነው፤ እንዲሁም “ሁልጊዜ ስህተት አይፈላልግም፤ ለዘላለምም ቂም አይዝም።” ሁላችንም ስንወለድ ጀምሮ ፍጹም እንዳልሆንን ያውቃል፤ እንዲሁም “አፈር መሆናችንን” ማለትም ደካማ እንደሆንን ያስታውሳል።—መዝሙር 103:8, 9, 14

ከዚህም በላይ አምላክ መሐሪ አባታችን እንደመሆኑ መጠን ስህተትን በተመለከተ የእሱ ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን ይፈልጋል። (መዝሙር 130:3) በፍቅር ተገፋፍቶ ያስጻፈልን ቃሉም እኛ ስህተት ስንሠራም ሆነ ሌሎች ስህተት በሚሠሩበት ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብን የሚገልጽ ብዙ ምክርና መመሪያ ይሰጠናል።

ስህተት በሚፈጸምበት ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

አብዛኛውን ጊዜ፣ ሰዎች ስህተት ሲሠሩ የተናገሩትን ወይም ያደረጉትን ነገር በሌሎች ላይ ለማላከክ ወይም ያደረጉት ነገር ስህተት እንዳልሆነ ለማስረዳት ብዙ ጊዜና ጉልበት ያጠፋሉ። ሆኖም ሌሎችን የሚያስቀይም ነገር ከተናገርክ ወዲያውኑ ይቅርታ ጠይቀህ ነገሮችን ማስተካከልህና ወዳጅነታችሁ እንዲቀጥል ማድረግህ የተሻለ አይሆንም? ትክክል ያልሆነ ነገር በማድረግህ ምክንያት በራስህ ወይም በሌሎች ላይ ችግር ብትፈጥርስ? በራስህ ከመናደድ ወይም ሌሎችን ከመውቀስ ይልቅ ነገሮችን ለማስተካከል የቻልከውን ሁሉ ብታደርግ የተሻለ ይሆናል። ስህተትህን በሌሎች ላይ ለማሳበብ መሞከር የተፈጠረው ውጥረት ቶሎ እንዳይረግብና ችግሩም እንዲባባስ ያደርጋል። ከዚህ ይልቅ ከስህተትህ ተማር፤ ነገሮችን ለማስተካከል ሞክር፤ ከዚያም ጉዳዩን እርሳው።

ሌሎች ስህተት በሚሠሩበት ጊዜ ግን መበሳጨት ይቀናን ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ምንኛ የተሻለ ነው፦ “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው።” (ማቴዎስ 7:12) ስህተት በምንሠራበት ጊዜ፣ ሌሎች በርኅራኄ ቢመለከቱን እንዲሁም ስህተታችንን ችላ ብለው ቢያልፉት ደስ እንደሚለን ጥርጥር የለውም። ታዲያ እኛስ ለሌሎች ተመሳሳይ ደግነት ለማሳየት ጥረት ማድረጋችን ተገቢ አይሆንም?—ኤፌሶን 4:32

የምንሠራቸውን ስህተቶች ለመቀነስ ሊረዱን የሚችሉ መመሪያዎች

አንድ ሰው ስህተት የሚሠራው ‘የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ሲደርስ፣ እውቀት ሲጎድለው፣ ወይም ትኩረት ሳይሰጥ ሲቀር’ እንደሆነ አንድ መዝገበ ቃላት ይገልጻል። ሁሉም ሰው የሆነ ወቅት ላይ እዚህ ከተጠቀሱት ነገሮች ቢያንስ አንዱ ሊያጋጥመው ይችላል። ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ጠቃሚ መመሪያዎች የምንሠራቸውን ስህተቶች ለመቀነስ ይረዱናል።

ከእነዚህ መመሪያዎች አንዱ የሚገኘው በምሳሌ 18:13 ላይ ነው፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “እውነታውን ከመስማቱ በፊት መልስ የሚሰጥ ሰው፣ ሞኝነት ይሆንበታል፤ ውርደትም ይከናነባል።” ትንሽ ጊዜ ወስደን ጉዳዩን በደንብ መስማታችንና ስለምንሰጠው ምላሽ ማሰባችን በችኮላ ከመናገር ወይም ስሜታዊ ሆነን አጉል እርምጃ ከመውሰድ እንድንቆጠብ ሊረዳን ይችላል። በትኩረት በማዳመጥ ስለ ጉዳዩ ይበልጥ ለማወቅ ጥረት ማድረጋችን የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ እንዳንደርስና ስህተት እንዳንሠራ ሊጠብቀን ይችላል።

ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ደግሞ “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ” የሚለው ነው። (ሮም 12:18) ከሌሎች ጋር ባለህ ግንኙነት ሰላማዊና ተባባሪ ለመሆን የቻልከውን ሁሉ አድርግ። ከሌሎች ጋር በምትሠራበት ጊዜ አሳቢና ሰው አክባሪ ሁን፤ እንዲሁም አብረውህ የሚሠሩትን ሰዎች ለማመስገንና ለማበረታታት ጥረት አድርግ። አብረው በሚሠሩ ሰዎች መካከል እንዲህ ያለ ጥሩ ግንኙነት መኖሩ አንድ ሰው ሌሎችን ሊያስቀይም የሚችል ነገር በሚናገርበት ወይም በሚያደርግበት ወቅት ችላ ብሎ ለማለፍ ወይም በቀላሉ ይቅር ለመባባል ይረዳል፤ ከበድ ያሉ ጥፋቶች በሚፈጸሙበት ጊዜ ደግሞ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ያስችላል።

ስህተት በምትሠራበት ወቅት ከስህተትህ በመማር አጋጣሚውን ለጥሩ ዓላማ ተጠቀምበት። ለተናገርከው ወይም ላደረግከው ነገር ሰበብ አስባብ ከመደርደር ይልቅ በዚያ አጋጣሚ ተጠቅመህ ጥሩ ባሕርያትን ለማዳበር ጥረት አድርግ። ምናልባት ትዕግሥት፣ ደግነት ወይም ራስን መግዛት ይጎድልህ ይሆን? ወይስ ገርነትን፣ ሰላምንና ፍቅርን ይበልጥ ማዳበር ያስፈልግሃል? (ገላትያ 5:22, 23) ሌላው ቢቀር ለሚቀጥለው ጊዜ ምን ማድረግ እንደሌለብህ ማወቅ ትችላለህ። ለጥፋትህ ኃላፊነቱን መውሰድህ ተገቢ ቢሆንም በስህተትህ ከመጠን በላይ ላለማዘን ሞክር። በራስህ ስህተት መሳቅህ የሰፈነውን ውጥረት ሊያረግብ ይችላል።

ተገቢ አመለካከት መያዝ ያለው ጥቅም

ስህተትን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መመልከታችን እኛ በምንሳሳትበትም ሆነ ሌሎች ሰዎች ስህተት በሚሠሩበት ጊዜ ጉዳዩን በጥሩ መንገድ ለመያዝ ይረዳናል። ውስጣዊ ሰላም እናገኛለን፤ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ይኖረናል። ከሠራነው ስህተት ትምህርት ለማግኘት የምንጥር ከሆነ ይበልጥ ጥበበኛና ተወዳጅ እንሆናለን። በስህተቶቻችን ከልክ በላይ አናዝንም ወይም ስለ ራሳችን መጥፎ ስሜት አይሰማንም። ሌሎችም እንደ እኛው ስህተት የሚሠሩ መሆናቸውን ማስታወሳችን እነሱን መቅረብ እንዲቀለን ያደርጋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ እንደ አምላክ አፍቃሪ መሆናችንና ሌሎችን በነፃ ይቅር ማለታችን ይጠቅመናል።—ቆላስይስ 3:13

በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰችው ማርጋሬት የሠራችው ስህተት ቤተሰቡ አብሮ የሚያሳልፈውን ጊዜ አበላሽቶት ይሆን? በጭራሽ። ማርጋሬትን ጨምሮ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት በሁኔታው በጣም ሳቁ፤ ከዚያም ማካሮኒ ባይኖረውም የቀረበውን ምግብ በደስታ ተመገቡ! የማርጋሬት ሁለት የልጅ ልጆች ካደጉ በኋላም በዚያ ዕለት የተፈጠረውን አስቂኝ ነገር ለልጆቻቸው በመናገር ከአያቶቻቸው ጋር ያሳለፉትን አስደሳች ጊዜ ያስታውሳሉ። ደግሞስ ስህተት የማይሠራ ማን አለ?

^ አን.2 ስሞቹ ተለውጠዋል።