በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በይሖዋ ታመን፤ መልካም የሆነውንም አድርግ”

“በይሖዋ ታመን፤ መልካም የሆነውንም አድርግ”

“በይሖዋ ታመን፤ መልካም የሆነውንም አድርግ።”—መዝ. 37:3

መዝሙሮች፦ 150, 124

1. ይሖዋ ለሰው ልጆች የትኞቹን አስደናቂ ችሎታዎች ሰጥቷቸዋል?

ይሖዋ፣ የሰው ልጆችን የፈጠረው አስደናቂ ችሎታዎች እንዲኖሯቸው አድርጎ ነው። ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማቀድና ለችግሮቻችን መፍትሔ ማበጀት እንድንችል የማመዛዘን ችሎታ ሰጥቶናል። (ምሳሌ 2:11) ደግሞም ያቀድነውን ነገር ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል ስለሰጠን ግባችን ላይ መድረስ እንችላለን። (ፊልጵ. 2:13) በተጨማሪም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት የምንችልበት ሕሊና ሰጥቶናል፤ ይህ በተፈጥሮ ያገኘነው ችሎታ ከመጥፎ ድርጊቶች እንድንርቅ እንዲሁም የሠራናቸውን ስህተቶች እንድናርም ይረዳናል።—ሮም 2:15

2. ይሖዋ ችሎታዎቻችንን እንዴት እንድንጠቀምባቸው ይፈልጋል?

2 ይሖዋ ያሉንን ችሎታዎች በጥሩ ሁኔታ እንድንጠቀምባቸው ይፈልጋል። ለምን? ምክንያቱም እኛን ይወደናል፤ እንዲሁም ያሉንን ችሎታዎች በዚህ መንገድ መጠቀማችን ደስታና እርካታ እንደሚያስገኝልን ያውቃል። ይሖዋ፣ ችሎታዎቻችንን መልካም ነገር ለማድረግ ልንጠቀምባቸው እንደሚገባ በቃሉ አማካኝነት በተደጋጋሚ አሳስቦናል። ለምሳሌ ያህል፣ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚከተሉት ሐሳቦች ይገኛሉ፦ “የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል” እንዲሁም “እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኃይልህ አከናውን።” (ምሳሌ 21:5፤ መክ. 9:10) በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ደግሞ “አጋጣሚ እስካገኘን ድረስ ለሁሉም . . . መልካም እናድርግ” እንዲሁም “እያንዳንዳችሁ በተቀበላችሁት ስጦታ መሠረት የተሰጣችሁን ስጦታ አንዳችሁ ሌላውን ለማገልገል ተጠቀሙበት” የሚሉ ምክሮች ይገኛሉ። (ገላ. 6:10፤ 1 ጴጥ. 4:10) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ ይሖዋ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን የሚጠቅም ነገር እንድናደርግ ይፈልጋል።

3. የሰው ልጆች ምን የአቅም ገደቦች አሉባቸው?

3 ይሁንና ይሖዋ፣ የሰው ልጆች የአቅም ገደብ እንዳለባቸው ያውቃል። በራሳችን ጥረት አለፍጽምናን፣ ኃጢአትንና ሞትን ማስወገድ አንችልም፤ በተጨማሪም እያንዳንዱ ሰው የመመረጥ ነፃነት ስላለው ሌሎች የሚያደርጉትን ነገር መቆጣጠር አንችልም። (1 ነገ. 8:46) ከዚህም ሌላ የቱንም ያህል እውቀትና ተሞክሮ ያካበትን ብንሆን ከይሖዋ አንጻር ስንታይ ምንጊዜም ሕፃናት ነን።—ኢሳ. 55:9

ችግሮች ሲያጋጥሙህ “በይሖዋ ታመን፤ መልካም የሆነውንም አድርግ”

4. በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

4 ይሖዋ እንደሚደግፈንና እኛ ማድረግ የማንችለውን ነገር ለእኛ ሲል እንደሚያደርግልን በመተማመን ምንጊዜም የእሱን መመሪያዎች መፈለግ ይኖርብናል። በሌላ በኩል ደግሞ እጃችንን አጣጥፈን ከመቀመጥ ይልቅ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመፍታትና ሌሎችን ለመርዳት አቅማችን የሚፈቅደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። (መዝሙር 37:3ን አንብብ።) በሌላ አባባል ‘በይሖዋ መታመን’ እና ‘መልካም የሆነውን ማድረግ’ ያስፈልገናል። በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ ኖኅ፣ ዳዊት እና ሌሎች ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በይሖዋ በመታመንና ተገቢ እርምጃ በመውሰድ ረገድ ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመረምራለን። እነዚህ ግለሰቦች ማድረግ የማይችሉትን እና ማድረግ የሚችሉትን ነገር ለይተው አውቀዋል፤ እንዲሁም ከሁኔታው ጋር የሚስማማ እርምጃ ወስደዋል።

በክፋት በተሞላ ዓለም ውስጥ ስንኖር

5. ኖኅ የነበረበትን ሁኔታ ግለጽ።

5 ኖኅ ይኖር የነበረው ‘በዓመፅና’ በሥነ ምግባር ብልግና በተሞላ ዓለም ውስጥ ነበር። (ዘፍ. 6:4, 9-13) ይሖዋ በወቅቱ የነበረውን ክፉ ዓለም ማጥፋቱ እንደማይቀር ቢያውቅም አምላክን የማይፈሩ ሰዎች በሚፈጽሟቸው ድርጊቶች ተጨንቆ መሆን አለበት። ያም ቢሆን ኖኅ ሊያደርጋቸው የማይችላቸው ነገሮች እና ሊያደርጋቸው የሚችላቸው ነገሮች እንዳሉ ተገንዝቦ ነበር።

በስብከቱ ሥራ ተቃውሞ ሲያጋጥመን (አንቀጽ 6-9ን ተመልከት)

6, 7. (ሀ) ኖኅ ማድረግ የማይችለው ነገር ምን ነበር? (ለ) እኛ ያለንበት ሁኔታ ከኖኅ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

6 ኖኅ ማድረግ የማይችለው ነገር፦ ኖኅ የይሖዋን የማስጠንቀቂያ መልእክት በታማኝነት የሰበከ ቢሆንም በዙሪያው ያሉት ክፉ ሰዎች መልእክቱን እንዲቀበሉ ማስገደድም ሆነ የጥፋት ውኃው የሚመጣበትን ጊዜ ማፋጠን አይችልም። ኖኅ፣ ይሖዋ ክፋትን ለማጥፋት የገባውን ቃል በትክክለኛው ጊዜ ላይ እንደሚፈጽም መተማመን ያስፈልገው ነበር።—ዘፍ. 6:17

7 እኛም የምንኖረው በክፋት በተሞላ ዓለም ውስጥ ሲሆን ይሖዋ ይህን ክፉ ዓለም ለማጥፋት ቃል እንደገባ እናውቃለን። (1 ዮሐ. 2:17) ያም ቢሆን ሰዎች ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ እንዲቀበሉ ማስገደድ አንችልም። ‘ታላቁ መከራ’ የሚጀምርበትን ጊዜ ማፋጠን እንደማንችልም የታወቀ ነው። (ማቴ. 24:14, 21) ልክ እንደ ኖኅ፣ እኛም ይሖዋ በቅርቡ እርምጃ እንደሚወስድ በመተማመን ጠንካራ እምነት እንዳለን ልናሳይ ይገባል። (መዝ. 37:10, 11) ይሖዋ፣ ይህን ክፉ ሥርዓት የሚያጠፋበትን ጊዜ ወስኗል፤ ይህ ጊዜ በአንድ ቀንም እንኳ እንዲራዘም እንደማይፈቅድ እርግጠኞች ነን።—ዕን. 2:3

8. ኖኅ ማድረግ በሚችለው ነገር ላይ ያተኮረው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

8 ኖኅ ማድረግ የሚችለው ነገር፦ ኖኅ ማድረግ በማይችለው ነገር ላይ በማተኮር ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ማድረግ በሚችለው ነገር ላይ ትኩረት አድርጓል። “የጽድቅ ሰባኪ” የነበረው ኖኅ፣ አምላክ የማስጠንቀቂያ መልእክት እንዲያውጅ የሰጠውን ሥራ በታማኝነት አከናውኗል። (2 ጴጥ. 2:5) ኖኅ እንዲህ ማድረጉ እምነቱን ለማጠናከር እንደረዳው ግልጽ ነው። ከስብከት ሥራው በተጨማሪ ጉልበቱንና የማሰብ ችሎታውን ተጠቅሞ አምላክ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት መርከብ ሠርቷል።—ዕብራውያን 11:7ን አንብብ።

9. የኖኅን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

9 ልክ እንደ ኖኅ፣ እኛም ‘የጌታ ሥራ የበዛልን’ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን። (1 ቆሮ. 15:58) ይህ ሥራ፣ የአምልኮ ቦታዎችን መገንባትንና መጠገንን፣ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ በፈቃደኝነት ማገልገልን እንዲሁም በቅርንጫፍ ቢሮ ወይም በርቀት የትርጉም ቢሮዎች ውስጥ ማገልገልን ይጨምራል። ከሁሉም በላይ ግን ምንጊዜም በስብከቱ ሥራ መጠመድ ይኖርብናል፤ ይህም ተስፋችን ይበልጥ ብሩህ እንዲሆንልን ያደርጋል። አንዲት ታማኝ እህት እንዲህ ብላለች፦ “የአምላክ መንግሥት ስለሚያመጣቸው በረከቶች ለሌሎች ስትናገር፣ የምታነጋግራቸው ሰዎች ምንም ተስፋ እንደሌላቸውና ችግሮቻቸው ዘላቂ መስለው እንደሚታዩአቸው [ትገነዘባለህ]።” በእርግጥም በስብከቱ ሥራ መካፈላችን የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ምንጊዜም አዎንታዊ አመለካከት እንድንይዝ እንዲሁም ለሕይወት በምናደርገው ሩጫ ተስፋ እንዳንቆርጥ ይረዳናል።—1 ቆሮ. 9:24

ስህተት ስንሠራ

10. ዳዊት ያጋጠመውን ሁኔታ ግለጽ።

10 ይሖዋ፣ ንጉሥ ዳዊትን “እንደ ልቤ የሆነ” ሰው በማለት ጠርቶታል። (ሥራ 13:22) በጥቅሉ ሲታይ ዳዊት ታማኝ ሰው ነበር። ያም ሆኖ ከባድ ኃጢአት የሠራበት ወቅት ነበር። ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር ፈጽሟል። ይባስ ብሎም ጉዳዩን ለመሸፋፈን ሲል ባለቤቷ ኦርዮ በጦር ሜዳ እንዲገደል ሁኔታዎችን አመቻችቷል። የሚገርመው ደግሞ ስለዚህ ጉዳይ የሚገልጸውን ደብዳቤ የላከው በራሱ በኦርዮ እጅ ነበር! (2 ሳሙ. 11:1-21) ሆኖም የዳዊት ኃጢአት ይፋ መውጣቱ አልቀረም። (ማር. 4:22) ታዲያ ዳዊት በዚህ ወቅት ምን አደረገ?

ቀደም ሲል የሠራናቸው ኃጢአቶች (አንቀጽ 11-14ን ተመልከት)

11, 12. (ሀ) ዳዊት፣ ኃጢአት ከፈጸመ በኋላ ማድረግ የማይችለው ነገር ምን ነበር? (ለ) ከባድ ስህተት ብንሠራም ንስሐ እስከገባን ድረስ ይሖዋ ምን እንደሚያደርግልን ልንተማመን እንችላለን?

11 ዳዊት ማድረግ የማይችለው ነገር፦ ዳዊት የሠራውን ስህተት ወደ ኋላ ተመልሶ ማስተካከልም ሆነ የሠራው ስህተት ከሚያስከትልበት መዘዝ ማምለጥ አይችልም። እንዲያውም አንዳንዶቹ መዘዞች እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ የሚዘልቁ ነበሩ። (2 ሳሙ. 12:10-12, 14) ስለዚህ እምነት ያስፈልገው ነበር። ከልቡ ንስሐ ከገባ ይሖዋ ምሕረት እንደሚያደርግለትና የፈጸመው ስህተት ያስከተለበትን መዘዝ እንዲቋቋም እንደሚረዳው መተማመን ነበረበት።

12 ፍጹማን ስላልሆንን ሁላችንም ኃጢአት እንሠራለን። አንዳንዶቹ ስህተቶች ከሌሎቹ ከበድ ያሉ ሊሆኑ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ፣ የሠራናቸውን ስህተቶች ወደ ኋላ ተመልሰን ማስተካከል አንችል ይሆናል። በመሆኑም የሠራነው ስህተት የሚያስከትልብንን መዘዝ ተቀብለን ለመኖር እንገደዳለን። (ገላ. 6:7) ያም ቢሆን ይሖዋ ንስሐ እስከገባን ድረስ ችግሮች በሚያጋጥሙን ወቅት እንደሚደግፈን በገባው ቃል ላይ መተማመን እንችላለን፤ ሌላው ቀርቶ ችግር ውስጥ የገባነው በራሳችን ጥፋት ቢሆንም እንኳ ይረዳናል።—ኢሳይያስ 1:18, 19ን እና የሐዋርያት ሥራ 3:19ን አንብብ።

13. ዳዊት ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ያደሰው እንዴት ነው?

13 ዳዊት ማድረግ የሚችለው ነገር፦ ዳዊት ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና የማደስ ፍላጎት ነበረው። ይህን ያሳየው እንዴት ነው? የይሖዋን እርዳታ በፈቃደኝነት በመቀበል ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋ ተወካይ የሆነው ነቢዩ ናታን የሰጠውን እርማት ተቀብሏል። (2 ሳሙ. 12:13) በተጨማሪም ዳዊት ወደ ይሖዋ በመጸለይ ኃጢአቱን የተናዘዘ ከመሆኑም ሌላ የይሖዋን ሞገስ መልሶ የማግኘት ልባዊ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል። (መዝ. 51:1-17) ዳዊት የጥፋተኝነት ስሜት እንዲያሽመደምደው ከመፍቀድ ይልቅ ከሠራው ስህተት ተምሯል። ደግሞም እንደዚያ ያሉ ከባድ ኃጢአቶችን ዳግመኛ አልፈጸመም። ከጊዜ በኋላ ዳዊት ታማኝነቱን እንደጠበቀ ሞቷል፤ ይሖዋም ቢሆን ዳዊትን የሚያስታውሰው በዚህ የታማኝነት አቋሙ ነው።—ዕብ. 11:32-34

14. ዳዊት ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

14 ዳዊት ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? ከባድ ኃጢአት ከሠራን ከልብ ንስሐ መግባትና የይሖዋን ምሕረት ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ኃጢአታችንን ለእሱ መናዘዝ አለብን። (1 ዮሐ. 1:9) በተጨማሪም መንፈሳዊ እርዳታ ወደሚሰጡን የጉባኤ ሽማግሌዎች መቅረብ ያስፈልገናል። (ያዕቆብ 5:14-16ን አንብብ።) ይሖዋ ባደረገልን በእነዚህ ዝግጅቶች መጠቀማችን አምላክ እኛን ለመፈወስና ይቅር ለማለት በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳለን ያሳያል። ከዚያም ከስህተታችን መማርና ይሖዋን በሙሉ ልብ ማገልገላችንን መቀጠል ይኖርብናል።—ዕብ. 12:12, 13

ሌሎች ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን

የጤና ችግር ሲያጋጥመን (አንቀጽ 15ን ተመልከት)

15. ሐና ከተወችው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

15 በይሖዋ በመታመንና አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ በጥንት ዘመን የኖሩ ሌሎች ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችንም ታስታውስ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐና መሃንነቷን ለማስወገድ ማድረግ የምትችለው ነገር አልነበረም። ነገር ግን ይሖዋ ሊያጽናናት እንደሚችል እምነት ነበራት፤ በመሆኑም ወደ መገናኛው ድንኳን በመሄድ እሱን ማምለኳን የቀጠለች ሲሆን የልቧን አውጥታ ለይሖዋ ተናግራለች። (1 ሳሙ. 1:9-11) በእርግጥም ይህ ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ አይደለም? የጤና ችግርን ጨምሮ ከቁጥጥራችን ውጭ የሆኑ ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ይሖዋ እንደሚያስብልን በመተማመን የሚያስጨንቀንን ነገር ሁሉ በእሱ ላይ እንጣል። (1 ጴጥ. 5:6, 7) በተጨማሪም ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና ከሌሎች መንፈሳዊ ዝግጅቶች ጥቅም ለማግኘት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናድርግ።—ዕብ. 10:24, 25

ልጆቻችን እውነትን ሲተዉ (አንቀጽ 16ን ተመልከት)

16. ወላጆች ከአረጋዊው ሳሙኤል ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

16 ከእውነት ቤት የወጡ ልጆች ስላሏቸው ታማኝ ወላጆችስ ምን ማለት ይቻላል? አረጋዊው ሳሙኤል ትላልቅ የሆኑ ልጆቹ እሱ ያስተማራቸውን የጽድቅ መሥፈርቶች እንዲጠብቁ ማስገደድ አይችልም ነበር። (1 ሳሙ. 8:1-3) ሳሙኤል ጉዳዩን ለይሖዋ ከመተው በቀር ምንም አማራጭ አልነበረውም። ሆኖም ንጹሕ አቋሙን ይዞ በመቀጠል የሰማይ አባቱን ማስደሰት ይችላል። (ምሳሌ 27:11) በዛሬው ጊዜም እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ክርስቲያን ወላጆች አሉ። ስለ አባካኙ ልጅ በሚናገረው ምሳሌ ላይ እንዳለው አባት ይሖዋም ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞች ወደ እሱ የሚመለሱበትን ጊዜ በጉጉት እንደሚጠባበቅ ይተማመናሉ። (ሉቃስ 15:20) በሌላ በኩል ደግሞ የእነሱ ታማኝነት ልጃቸው ወደ ይሖዋ እንዲመለስ እንደሚረዳው በመተማመን ምንጊዜም ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።

የኢኮኖሚ ችግር ሲያጋጥመን (አንቀጽ 17ን ተመልከት)

17. ድሃዋ መበለት የተወችው ምሳሌ የሚያበረታታን እንዴት ነው?

17 እስቲ በኢየሱስ ዘመን ስለነበረችው ድሃ መበለት ደግሞ እንመልከት። (ሉቃስ 21:1-4ን አንብብ።) በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበረውን ምግባረ ብልሹነት ማስወገድ አትችልም ነበር። (ማቴ. 21:12, 13) የኑሮ ደረጃዋን ለማሻሻልም ቢሆን ልታደርግ የምትችለው ነገር በጣም ውስን ነበር። ያም ሆኖ “ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች” ማለትም “ያላትን መተዳደሪያ ሁሉ” በፈቃደኝነት ሰጥታለች። ይህች ታማኝ ሴት፣ በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት እንዳላት አሳይታለች፤ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ከሰጠች ይሖዋ የሚያስፈልጋትን ቁሳዊ ነገር እንደሚያሟላላት ተገንዝባ ነበር። ይህች መበለት በይሖዋ መታመኗ በወቅቱ የነበረውን የእውነተኛ አምልኮ ዝግጅት እንድትደግፍ አነሳስቷታል። እኛም መንግሥቱን ካስቀደምን ይሖዋ የሚያስፈልገንን እንደሚያሟላልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ማቴ. 6:33

18. ትክክለኛ አመለካከት ስለነበረው አንድ ወንድም የሚገልጽ ተሞክሮ ተናገር።

18 በተመሳሳይም በዘመናችን የሚገኙ በርካታ ክርስቲያኖች በይሖዋ እንደሚታመኑ ያሳዩ ከመሆኑም ሌላ አስፈላጊውን እርምጃ ወስደዋል። በ2015 ሕይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በታማኝነት የጸናውን የወንድም ማልኮምን ተሞክሮ እስቲ እንመልከት። እሱና ባለቤቱ ይሖዋን ባገለገሉባቸው አሥርተ ዓመታት የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል። ወንድም ማልኮም እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ ያልጠበቅናቸው አልፎ ተርፎም አስጨናቂ የሆኑ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ በእሱ የሚታመኑ ሰዎችን ይባርካቸዋል።” ታዲያ ወንድም ማልኮም ምን ምክር ሰጥቷል? “በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ ውጤታማ እና ሥራ የበዛልን ለመሆን መጸለይ ይኖርብናል። ትኩረት የምናደርገው ልናከናውነው በማንችለው ነገር ላይ ሳይሆን ማከናወን በምንችለው ነገር ላይ መሆን አለበት።” *

19. (ሀ) የ2017 የዓመት ጥቅሳችን ካለንበት ጊዜ አንጻር ተስማሚ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) የ2017ን የዓመት ጥቅስ በሕይወትህ ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

19 ይህ ሥርዓት ‘በክፋት ላይ ክፋት እየጨመረ’ በመሄድ ላይ ነው፤ በመሆኑም ችግሮች እየተባባሱ እንደሚሄዱ እንጠብቃለን። (2 ጢሞ. 3:1, 13) ሆኖም እነዚህ ችግሮች እንዲያሽመደምዱን መፍቀድ የለብንም። ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር አለብን፤ እንዲሁም አቅማችን እስከፈቀደው ድረስ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። በእርግጥም የ2017 የዓመት ጥቅሳችን “በይሖዋ ታመን፤ መልካም የሆነውንም አድርግ” የሚል መሆኑ ምንኛ የተገባ ነው!—መዝ. 37:3

የ2017 የዓመት ጥቅስ፦ “በይሖዋ ታመን፤ መልካም የሆነውንም አድርግመዝ. 37:3