በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ዓላማ ይፈጸማል!

የይሖዋ ዓላማ ይፈጸማል!

“ተናግሬአለሁ፤ ደግሞም እፈጽመዋለሁ። ይህን ለማድረግ አስቤአለሁ፤ አደርገዋለሁም።”—ኢሳ. 46:11

መዝሙሮች፦ 25, 18

1, 2. (ሀ) ይሖዋ ምን ገልጾልናል? (ለ) በኢሳይያስ 46:10, 11 እና 55:11 ላይ ምን ማረጋገጫ እናገኛለን?

“በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ።” በመጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ላይ የሰፈሩት እነዚህ ቃላት ትልቅ ትርጉም ያዘሉ ናቸው። (ዘፍ. 1:1) በእርግጥ አምላክ ስለፈጠራቸው ነገሮች ያለን እውቀት ውስን ነው፤ እንደ ጠፈር፣ ብርሃን እና የስበት ኃይል ያሉትን ነገሮች በዚህ ረገድ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፤ ከአጽናፈ ዓለም ጋር በተያያዘም ቢሆን ማየት የቻልነው በጣም ትንሹን ክፍል እንደሆነ የታወቀ ነው። (መክ. 3:11) ያም ቢሆን ይሖዋ፣ ለምድርና ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ገልጾልናል። ዓላማው፣ ምድር በእሱ አምሳል ለተፈጠሩ ሰዎች ተስማሚ መኖሪያ እንድትሆን ነበር። (ዘፍ. 1:26) የይሖዋ ዓላማ እነዚህ ሰዎች ልጆቹ እንዲሆኑ፣ እሱ ደግሞ አባታቸው እንዲሆን ነበር።

2 ሆኖም በዘፍጥረት ምዕራፍ ሦስት ላይ እንደተገለጸው የይሖዋን ዓላማ ሊያስተጓጉል የሚችል ነገር ተፈጠረ። (ዘፍ. 3:1-7) የተፈጠረው ሁኔታ ግን ሊስተካከል የማይችል አይደለም። ይሖዋ ዓላማውን እንዳይፈጽም ሊያግደው የሚችል የለም። (ኢሳ. 46:10, 11፤ 55:11) በመሆኑም ይሖዋ መጀመሪያ ላይ የነበረው ዓላማ እሱ ባሰበው ጊዜ እንደሚፈጸም እርግጠኞች መሆን እንችላለን!

3. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመረዳት የትኞቹን እውነቶች ማወቃችን አስፈላጊ ነው? (ለ) እነዚህን ትምህርቶች በአሁኑ ወቅት መከለስ ያስፈለገው ለምንድን ነው? (ሐ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 አምላክ ለምድርም ሆነ ለሰው ዘር ስላለው ዓላማ እንዲሁም የይሖዋ ዓላማ እንዲፈጸም ኢየሱስ ስለሚጫወተው ጉልህ ሚና የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን እንደምናውቅ ጥርጥር የለውም። እነዚህ እውነቶች ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው፤ የአምላክን ቃል ስናጠና መጀመሪያ ላይ እነዚህን እውነቶች እንደተማርን የታወቀ ነው። እኛም በበኩላችን እነዚህን አስፈላጊ ትምህርቶች ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች ማሳወቅ እንፈልጋለን። ይህን ርዕስ በጉባኤ በምናጠናበት በዚህ ወቅት በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ በተቻለ መጠን ብዙዎች እንዲገኙ ለመጋበዝ ጥረት እያደረግን ነው። (ሉቃስ 22:19, 20) በበዓሉ ላይ የሚገኙ ሰዎች ስለ አምላክ ዓላማ ለመማር አጋጣሚ ያገኛሉ። ስለዚህ ከመታሰቢያው በዓል በፊት በቀሩት ጥቂት ቀናት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንንና ሌሎች ቅን ሰዎችን በዚህ አስፈላጊ ፕሮግራም ላይ እንዲገኙ ለማበረታታት ልንጠቀምባቸው የምንችላቸውን አንዳንድ ጥያቄዎች ማሰባችን ተገቢ ነው። እስቲ የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች እንመርምር፦ አምላክ ለምድርና ለሰው ዘር መጀመሪያ ላይ የነበረው ዓላማ ምንድን ነው? ዓላማው ምን መሰናክል ገጠመው? የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የአምላክ ዓላማ እንዲፈጸም ቁልፍ ሚና ይጫወታል የምንለው ለምንድን ነው?

ፈጣሪ መጀመሪያ ላይ የነበረው ዓላማ ምንድን ነው?

4. ፍጥረት የይሖዋን ክብር የሚያውጀው እንዴት ነው?

4 ይሖዋ በጣም አስደናቂ የሆነ ፈጣሪ ነው። የፍጥረት ሥራዎቹ በሙሉ ተወዳዳሪ አይገኝላቸውም። (ዘፍ. 1:31፤ ኤር. 10:12) በፍጥረት ሥራዎቹ ላይ ከምናየው ውበትና ሥርዓት ምን ትምህርት እናገኛለን? የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች በሙሉ ከእሱ ዓላማ ጋር በተያያዘ ጠቃሚ ሚና እንደሚጫወቱ እንገነዘባለን። በረቀቀ መንገድ የተሠራውን የሰው ልጆች ሴል፣ ፀሐይ ስትጠልቅ በዙሪያዋ የሚፈጠረውን አስደናቂ ውበት ወይም ደግሞ የሚያሳሳ አራስ ልጅ ስንመለከት ማናችንም ብንሆን መደመማችን አይቀርም። እነዚህን ፍጥረታት የምናደንቀው፣ ይሖዋ ውብ የሆነን ነገር የማስተዋል ችሎታ እንዲኖረን አድርጎ ስለፈጠረን ነው።መዝሙር 19:1ን እና 104:24ን አንብብ።

5. ይሖዋ ፍጥረታቱ በሙሉ ተቀናጅተው መሥራት እንዲችሉ ምን አድርጓል?

5 ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ለሁሉም የፍጥረት ሥራዎቹ ገደብ አበጅቷል። ሁሉም ነገር እርስ በርስ ተቀናጅቶ መሥራት እንዲችል የተፈጥሮ ሕጎችንና የሥነ ምግባር ደንቦችን አውጥቷል። (መዝ. 19:7-9) በመሆኑም በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉት ነገሮች በሙሉ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የየራሳቸው ቦታና ድርሻ አላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ የስበት ሕግ ከባቢ አየር ምንጊዜም በምድር ዙሪያ እንዲኖር ያደርጋል፤ እንዲሁም የባሕር ሞገድንና ውቅያኖሶችን ይቆጣጠራል። የስበት ኃይል ባይኖር ኖሮ በምድር ላይ ሕይወት አይኖርም ነበር። ይሖዋ ለፍጥረት ሥራዎቹ ያወጣቸው ገደቦች በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ፍጹም የሆነ ሥርዓት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ አድርገዋል። እንዲህ ያለ ሥርዓት መኖሩ አምላክ ምድርንም ሆነ የሰውን ዘር ሲፈጥር ዓላማ እንዳለው በግልጽ ያሳያል። በአገልግሎታችን ላይ የምናገኛቸውን ሰዎች፣ ይህን አስደናቂ አጽናፈ ዓለም የፈጠረውን አምላክ እንዲያውቁ ልንረዳቸው እንችላለን።—ራእይ 4:11

6, 7. ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን ከሰጣቸው ስጦታዎች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

6 መጀመሪያ ላይ ይሖዋ የሰው ዘር በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖር ዓላማ ነበረው። (ዘፍ. 1:28፤ መዝ. 37:29) አዳምና ሔዋን አስደሳች ሕይወት እንዲመሩ የሚያስችሏቸውን የተለያዩ ውድ ስጦታዎች ሰጥቷቸዋል፤ ይህም ለጋስ እንደሆነ ያሳያል። (ያዕቆብ 1:17ን አንብብ።) ይሖዋ የመምረጥ ነፃነት፣ የማመዛዘን ችሎታ እንዲሁም ሌሎችን የመውደድና ጓደኝነት የመመሥረት ችሎታ ሰጥቷቸዋል። ፈጣሪ አዳምን ያነጋግረው የነበረ ሲሆን ትክክል የሆነውን ነገር በተመለከተ መመሪያ ሰጥቶታል። በተጨማሪም የሚያስፈልጉትን ነገሮች እንዴት ማግኘት እንደሚችል ብሎም እንስሳትንና ምድርን እንዴት እንደሚንከባከብ ገልጾለታል። (ዘፍ. 2:15-17, 19, 20) ከዚህም ሌላ ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ሲፈጥራቸው የመቅመስ፣ የመዳሰስ፣ የማየት፣ የመስማትና የማሽተት ችሎታ ሰጥቷቸዋል። በመሆኑም ገነት በሆነችው መኖሪያቸው ውስጥ በሚገኙት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ውብ ነገሮች መደሰት ይችሉ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት፣ በሚያከናውኑት ሥራ እርካታ የማግኘት እንዲሁም በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን የመማር ሰፊ አጋጣሚ ነበራቸው።

7 የአምላክ ዓላማ ከዚህም ሌላ የሚያካትተው ነገር ነበር። ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ሲፈጥራቸው ፍጹም የሆኑ ልጆችን የመውለድ ችሎታ ሰጥቷቸዋል። ልጆቻቸውም እየተዋለዱ ምድርን እንዲሞሉ አስቦ ነበር። ይሖዋ ፍጹም የሆኑትን ሰብዓዊ ልጆቹን ይወድ እንደነበረ ሁሉ አዳምና ሔዋንም ሆኑ ከእነሱ በኋላ የሚኖሩት ወላጆች በሙሉ ልጆቻቸውን እንዲወዱ ይጠብቅባቸው ነበር። ምድርንም ሆነ በላይዋ የሚገኙትን ውድና ውብ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ለሰው ልጆች ሰጥቷል። ምድር ዘላለማዊ መኖሪያቸው እንድትሆን ዓላማው ነበር።—መዝ. 115:16

የአምላክ ዓላማ ምን መሰናክል ገጠመው?

8. አምላክ ዘፍጥረት 2:16, 17 ላይ ያለውን ሕግ የሰጠው ለምንድን ነው?

8 ይሁንና ለጊዜውም ቢሆን የአምላክን ዓላማ የሚያስተጓጉል ሁኔታ ተፈጠረ። ይህ ሁኔታ ምንድን ነው? አዳምና ሔዋን ነፃነታቸው ገደብ እንዳለው እንዲገነዘቡ ሲል ይሖዋ አንድ ቀላል ሕግ ሰጥቷቸው ነበር። ሕጉ እንዲህ ይላል፦ “በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ ከሚገኘው ዛፍ ሁሉ እስክትረካ ድረስ መብላት ትችላለህ። ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ ግን አትብላ፤ ምክንያቱም ከዚህ ዛፍ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።” (ዘፍ. 2:16, 17) ይህ ለመረዳት የሚከብድ ሕግ አልነበረም። አዳምና ሔዋን በአትክልቱ ስፍራ የተትረፈረፈ ምግብ ስለነበራቸው ይህን ሕግ መታዘዝ ሊከብዳቸው አይገባም።

9, 10. (ሀ) ሰይጣን በይሖዋ ላይ ምን ክስ ሰነዘረ? (ለ) አዳምና ሔዋን ምን ለማድረግ ወሰኑ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

9 ሰይጣን ዲያብሎስ በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን በማታለል በሰማዩ አባቷ በይሖዋ ላይ እንድታምፅ አደረጋት። (ዘፍጥረት 3:1-5ን አንብብ፤ ራእይ 12:9) ሰይጣን የአምላክ ሰብዓዊ ልጆች “በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም ዛፍ” መብላት የማይችሉ መሆኑ ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ ጥያቄ አነሳ። ሰይጣን ‘የምትፈልጉትን ነገር ማድረግ አትችሉም ማለት ነው?’ ያለ ያህል ነበር። ከዚያም “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም” በማለት ዓይን ያወጣ ውሸት ተናገረ። ቀጥሎም “አምላክ ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡ . . . ስለሚያውቅ ነው” በማለት ሔዋን አምላክን መታዘዝ እንደማያስፈልጋት ሊያሳምናት ሞከረ። ሰይጣን እንዲህ ሲል፣ ይሖዋ ከፍሬው እንዳይበሉ ያዘዛቸው ልዩ እውቀት እንዳያገኙ ብሎ እንደሆነ አድርጎ መናገሩ ነበር። በተጨማሪም ፍሬውን ቢበሉ “መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ” እንደሚሆኑ በመግለጽ የሐሰት ተስፋ ሰጣቸው።

10 አዳምና ሔዋን ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ሁኔታ ከፊታቸው ተደቀነ። ይሖዋን ይታዘዛሉ ወይስ እባቡ ያላቸውን ያደርጋሉ? አዳምና ሔዋን ይሖዋን ላለመታዘዝ ወሰኑ። በዚህ መንገድ ከሰይጣን ጋር ተባብረው በአምላክ ላይ ዓመፁ። የይሖዋን አባትነት ለመቀበል አሻፈረን አሉ፤ በዚህም የተነሳ የእሱን ጥበቃ አጡ።—ዘፍ. 3:6-13

11. ይሖዋ ዓመፅን ዝም ብሎ የማያየው ለምንድን ነው?

11 አዳምና ሔዋን በይሖዋ ላይ በማመፃቸው ፍጽምና የጎደላቸው ሆኑ። በተጨማሪም አለመታዘዛቸው ከአምላክ እንዲርቁ አደረጋቸው፤ ምክንያቱም የይሖዋ ዓይኖች “ክፉ የሆነውን ነገር እንዳያዩ እጅግ ንጹሐን ናቸው።” በመሆኑም ‘ክፋትን ዝም ብሎ ማየት አይችልም።’ (ዕን. 1:13) ይሖዋ ክፋትን ዝም ብሎ ቢያይ ኖሮ በሰማይም ሆነ በምድር ያሉ ሕያዋን ፍጥረታት የወደፊት ተስፋ አደጋ ላይ ይወድቅ ነበር። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ በኤደን የተፈጸመውን ኃጢአት በቸልታ ቢያልፈው ኖሮ እምነት የሚጣልበት አምላክ መሆኑ አጠያያቂ ይሆን ነበር። ይሖዋ ግን ላወጣቸው መሥፈርቶች ምንጊዜም ታማኝ ነው፤ መቼም ቢሆን መሥፈርቶቹን አይጥስም። (መዝ. 119:142) አዳምና ሔዋን የመምረጥ ነፃነት ቢኖራቸውም ይሖዋን አለመታዘዛቸው ከሚያስከትለው መዘዝ ማምለጥ አይችሉም። በመሆኑም ውሎ አድሮ መሞታቸውና ወደ አፈር መመለሳቸው አልቀረም።—ዘፍ. 3:19

12. አዳምና ሔዋን የሠሩት ኃጢአት በዘሮቻቸው ላይ ምን አስከትሏል?

12 አዳምና ሔዋን ፍሬውን ሲበሉ፣ የአምላክ አጽናፈ ዓለማዊ ቤተሰብ አባል የመሆን መብታቸውን አጡ። አምላክ ከኤደን ያባረራቸው ሲሆን ተመልሰው መግባትም አይችሉም ነበር። (ዘፍ. 3:23, 24) ይሖዋ ውሳኔያቸው የሚያስከትለውን ውጤት እንዲቀምሱ በማድረግ ፍትሐዊ እርምጃ ወስዷል። (ዘዳግም 32:4, 5ን አንብብ።) አዳምና ሔዋን ፍጽምና ስለጎደላቸው የአምላክን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ ማንጸባረቅ አልቻሉም። አዳም ሊያገኝ ይችል የነበረውን አስደናቂ ሕይወት ከማጣቱም ሌላ ለልጆቹ አለፍጽምናን፣ ኃጢአትንና ሞትን አውርሷል። (ሮም 5:12) ዘሮቹ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንዳያገኙ እንቅፋት ሆኗል። ከዚህም ሌላ አዳምና ሔዋንም ሆኑ ዘሮቻቸው ፍጹም የሆኑ ልጆች ሊወልዱ አይችሉም። ሰይጣን ዲያብሎስ የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን በአምላክ ላይ እንዲያምፁ ከማድረግም አልፎ በታሪክ ዘመናት በሙሉ የሰው ልጆችን ለማሳት ጥረት ማድረጉን ቀጥሏል።—ዮሐ. 8:44

ቤዛው ከአምላክ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት መንገድ ከፈተ

13. ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ የይሖዋ ፍላጎት ምንድን ነው?

13 አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ግን አልቀነሰም። አዳምና ሔዋን ቢያምፁም ይሖዋ፣ የሰው ልጆች ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖራቸው ይፈልጋል። ማንም ሰው እንዲጠፋ አይፈልግም። (2 ጴጥ. 3:9) ስለዚህ አዳምና ሔዋን ካመፁ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አምላክ የሰው ልጆች ከእሱ ጋር የነበራቸውን ዝምድና መልሰው እንዲያገኙ የሚያስችል ዝግጅት አደረገ፤ እርግጥ ይህን ያደረገው የጽድቅ መሥፈርቶቹን ሳያላላ ነው። ይህን ማድረግ የቻለው እንዴት ነው?

14. (ሀ) ዮሐንስ 3:16 እንደሚገልጸው አምላክ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ለመታደግ ምን አድርጓል? (ለ) ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ለየትኛው ጥያቄ መልስ እንዲያገኙ ልንረዳቸው እንችላለን?

14 ዮሐንስ 3:16ን አንብብ። በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ከምንጋብዛቸው ሰዎች አንዳንዶቹ ይህን ጥቅስ ያውቁታል። አሁን የሚነሳው ጥያቄ ግን ‘የኢየሱስ መሥዋዕት የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ መንገድ የከፈተው እንዴት ነው?’ የሚል ነው። በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ የምንጋብዛቸውን፣ በዓሉን አብረውን የሚያከብሩትን እንዲሁም ከበዓሉ በኋላ ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርግላቸውን ሰዎች ለዚህ አስፈላጊ ጥያቄ መልስ እንዲያገኙ የመርዳት አጋጣሚ አለን። እነዚህ ቅን ሰዎች ይሖዋ ቤዛውን በማዘጋጀት ፍቅሩንና ጥበቡን ያሳየው እንዴት እንደሆነ በሚገባ ሲረዱ ልባቸው ሊነካ ይችላል። ታዲያ ቤዛውን በተመለከተ የትኞቹን ነጥቦች ልናካፍላቸው እንችላለን?

15. ኢየሱስ ከአዳም የሚለየው እንዴት ነው?

15 ይሖዋ አንድ ፍጹም ሰው ቤዛ እንዲሆን ዝግጅት አደረገ። ይህ ፍጹም ሰው ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ መገኘት እንዲሁም ጥፋት ለተፈረደበት የሰው ዘር ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆን ይጠበቅበት ነበር። (ሮም 5:17-19) ይሖዋ የፍጥረት በኩር የሆነውን ኢየሱስን ከሰማይ ወደ ምድር ላከው። (ዮሐ. 1:14) አዳም ኃጢአት ከመሥራቱ በፊት እንደነበረው ሁሉ ኢየሱስም ፍጹም ሰው ሆነ። ይሁንና ኢየሱስ ከአዳም በተለየ መልኩ፣ ይሖዋ ፍጹም ከሆነ ሰው የሚጠብቀውን መሥፈርት ሳያጓድል መኖር ችሏል። በጣም ከባድ ፈተና ቢደርስበትም እንኳ ኃጢአት አልፈጸመም፤ እንዲሁም ከአምላክ ሕጎች መካከል አንዱንም አልጣሰም።

16. ቤዛው ውድ ስጦታ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

16 ኢየሱስ ፍጹም ሰው እንደመሆኑ መጠን በሰው ልጆች ምትክ በመሞት ከኃጢአትና ከሞት ሊታደጋቸው ይችላል። ኢየሱስ እንደ አዳም ፍጹም ሰው በመሆኑ ተመጣጣኝ ዋጋ መክፈል ችሏል። ፍጹም ከሆነ ሰው እንደሚጠበቀው ሁሉ ለአምላክ ሙሉ በሙሉ ታማኝና ታዛዥ ሆኗል። (1 ጢሞ. 2:6) ኢየሱስ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ በመስጠት “ብዙ ሰዎች” መጨረሻ የሌለው ሕይወት ማግኘት የሚችሉበት አጋጣሚ ከፍቷል። (ማቴ. 20:28) በእርግጥም ቤዛው አምላክ መጀመሪያ ላይ የነበረው ዓላማ እንዲፈጸም ቁልፍ ሚና ይጫወታል። (2 ቆሮ. 1:19, 20) ቤዛው ታማኝ የሆኑ ሰዎች በሙሉ የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲያገኙ አስችሏል።

ይሖዋ ወደ እሱ እንድንመለስ መንገድ ከፍቶልናል

17. ቤዛው ምን አስገኝቶልናል?

17 ይሖዋ ቤዛውን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ዋጋ መክፈል አስፈልጎታል። (1 ጴጥ. 1:19) የሰው ልጆችን ሕይወት ከፍ አድርጎ ስለሚመለከት አንድያ ልጁ ለእኛ ሲል እንዲሞት አድርጓል። (1 ዮሐ. 4:9, 10) ኢየሱስ በአዳም ምትክ አባታችን ሆኗል። (1 ቆሮ. 15:45) በዚህ መንገድ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችልበትን አጋጣሚ ያስገኘልን ከመሆኑም ሌላ ከጊዜ በኋላ እንደገና የአምላክ ቤተሰብ አባል መሆን የምንችልበትን መንገድ ከፍቶልናል። ኢየሱስ ሕይወቱን መሥዋዕት ስላደረገ ይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶቹን ሳይጥስ የሰው ልጆችን እንደገና የቤተሰቡ አባል አድርጎ መቀበል ይችላል። ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ፍጹማን ሲሆኑ ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን እስቲ አስበው! በሰማይም ሆነ በምድር ያሉ ፍጥረታት በሙሉ አንድ ቤተሰብ ይሆናሉ። በዚያ ጊዜ ሁላችንም የአምላክ ልጆች እንሆናለን።—ሮም 8:21

18. ይሖዋ “ለሁሉም ሁሉንም ነገር” የሚሆነው መቼ ነው?

18 የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ማመፃቸው ይሖዋ ለሰው ዘር ፍቅር እንዳያሳይ አላገደውም፤ እኛም ፍጹም ባንሆንም እንኳ ለይሖዋ ታማኝ እንዳንሆን ሰይጣን ሊያግደን አይችልም። ይሖዋ ቤዛውን በመጠቀም፣ ሁሉም ልጆቹ ሙሉ በሙሉ ጻድቃን እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። “ወልድን የሚያውቅና በእሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት” ሲያገኝ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር እስቲ አስበው! (ዮሐ. 6:40) አፍቃሪና ጥበበኛ የሆነው አባታችን ይሖዋ ዓላማውን ዳር በማድረስ የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ ይረዳቸዋል። ያን ጊዜ ይሖዋ “ለሁሉም ሁሉንም ነገር” ይሆናል።—1 ቆሮ. 15:28

19. (ሀ) ለቤዛው ያለን አድናቆት ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል? (“ መልእክቱን መስማት የሚገባቸውን መፈለጋችንን እንቀጥል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

19 ለቤዛው ያለን አድናቆት ሌሎችም ከዚህ ውድ ስጦታ እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ ለመናገር የተቻለንን ሁሉ ጥረት እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል። የሰው ልጆች ሁሉ የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲኖራቸው ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ በቤዛው አማካኝነት ዝግጅት እንዳደረገ ሰዎች ማወቅ አለባቸው። ይሁንና ቤዛው የሚያስገኘው ጥቅም በዚህ ብቻ የሚወሰን አይደለም። ሰይጣን በኤደን የአትክልት ስፍራ ላነሳው ጥያቄም መልስ ያስገኛል። የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ያብራራል።