በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ስእለትህን ፈጽም”

“ስእለትህን ፈጽም”

“ለይሖዋ የተሳልከውን ፈጽም።”—ማቴ. 5:33

መዝሙሮች፦ 124, 51

1. (ሀ) መስፍኑ ዮፍታሔና ሐና ምን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ? (በመግቢያው ላይ ያሉትን ሥዕሎች ተመልከት።) (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን?

መስፍኑ ዮፍታሔ፣ ኃያል መሪ እና ደፋር ተዋጊ ነበር። የሕልቃና ሚስት የሆነችው ሐና ደግሞ ባሏን የምትንከባከብና ቤቷን በአግባቡ የምትይዝ ትሑት ሴት ነበረች። እነዚህ ሁለት ሰዎች የይሖዋ አምላኪ ከመሆናቸው ባሻገር ምን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ? ሁለቱም ለአምላክ የተሳሉ ሲሆን ስእለታቸውንም በታማኝነት ፈጽመዋል። ዮፍታሔም ሆነ ሐና በዛሬው ጊዜ ለይሖዋ ቃል ለሚገቡ ወይም ለሚሳሉ ሰዎች ግሩም ምሳሌ ትተዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመረምራለን፦ ስእለት ምንድን ነው? አንድ ሰው ለአምላክ ከተሳለ ስእለቱን ምን ያህል አክብዶ ሊመለከተው ይገባል? ከዮፍታሔና ከሐና ምን ትምህርት እናገኛለን?

2, 3. (ሀ) ስእለት ምንድን ነው? (ለ) ቅዱሳን መጻሕፍት ለአምላክ ስለመሳል ምን ይላሉ?

2 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስእለት የሚለው ቃል የተሠራበት ለአምላክ ቃል መግባትን ለማመልከት ነው። አንድ ሰው አንድን ተግባር ለማከናወን፣ ስጦታ ለመስጠት፣ በአንድ ዓይነት አገልግሎት ለመካፈል ወይም ደግሞ ከአንዳንድ ነገሮች ለመታቀብ ቃል ሊገባ ይችላል። ስእለት የሚሳለው ሰው ይህን የሚያደርገው በፈቃደኝነት ወይም በራሱ ፍላጎት ተነሳስቶ ነው። ያም ቢሆን አምላክ፣ ግለሰቡ ቃሉን እንዲፈጽም ይጠብቅበታል። ምክንያቱም ስእለት ቅዱስ ከመሆኑም ሌላ የመሐላን ያህል ክብደት አለው፤ መሐላ አንድ ግለሰብ አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ላለማድረግ የሚገባው ቃል ነው። (ዘፍ. 14:22, 23፤ ዕብ. 6:16, 17) ታዲያ ለአምላክ የገባነውን ቃል ወይም ስእለታችንን ምን ያህል አክብደን ልንመለከተው ይገባል? ቅዱሳን መጻሕፍት ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?

3 የሙሴ ሕግ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው ለይሖዋ ስእለት ቢሳል ወይም . . . በመሐላ ራሱን ግዴታ ውስጥ ቢያስገባ ቃሉን ማጠፍ የለበትም። አደርገዋለሁ ብሎ የማለውን ነገር ሁሉ መፈጸም አለበት።” (ዘኁ. 30:2) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሰለሞን በመንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለአምላክ ስእለት በምትሳልበት ጊዜ ሁሉ ስእለትህን ለመፈጸም አትዘግይ፤ እሱ በሞኞች አይደሰትምና። ስእለትህን ፈጽም።” (መክ. 5:4) ኢየሱስም ስእለት ወይም መሐላ ምን ያህል በቁም ነገር ሊታይ እንደሚገባ ሲጠቁም እንዲህ ብሏል፦ “በጥንት ዘመን ለነበሩት ‘በከንቱ አትማል፤ ይልቁንም ለይሖዋ የተሳልከውን ፈጽም’ እንደተባለ ሰምታችኋል።”—ማቴ. 5:33

4. (ሀ) ለአምላክ የተሳልነውን ስእለት ምን ያህል አክብደን ልንመለከተው ይገባል? (ለ) ከዮፍታሔና ከሐና ጋር በተያያዘ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

4 በእርግጥም ለአምላክ የገባነውን ቃል በቁም ነገር ልናየው ይገባል። ቃላችንን መጠበቅ አለመጠበቃችን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ይነካዋል። ዳዊት “ወደ ይሖዋ ተራራ መውጣት የሚችል ማን ነው? በቅዱስ ስፍራውስ ሊቆም የሚችል ማን ነው?” ብሎ ከጠየቀ በኋላ “[በይሖዋ] ሕይወት በሐሰት ያልማለ፣ በማታለልም መሐላ ያልፈጸመ” በማለት መልስ ሰጥቷል። (መዝ. 24:3, 4 ግርጌ) ታዲያ ዮፍታሔና ሐና ለአምላክ ምን ተስለው ነበር? ስእለታቸውን መፈጸምስ ቀላል ነበር?

ስእለታቸውን በታማኝነት ፈጽመዋል

5. ዮፍታሔ ለይሖዋ ምን ተሳለ? ከዚያ በኋላስ ምን ሆነ?

5 ዮፍታሔ የአምላክን ሕዝቦች ይጨቁኑ ከነበሩት አሞናውያን ጋር ለመዋጋት ሲወጣ ለይሖዋ ስእለት ተስሎ ነበር። (መሳ. 10:7-9) ዮፍታሔ አሞናውያንን ድል ለማድረግ ይሖዋ እንዲረዳው እንዲህ ሲል ተማጸነ፦ “አሞናውያንን በእጄ አሳልፈህ ከሰጠኸኝ ከአሞናውያን ዘንድ በሰላም በምመለስበት ጊዜ ሊቀበለኝ ከቤቴ በር የሚወጣው ማንኛውም ሰው የይሖዋ ይሆናል።” አሞናውያን በውጊያው ስለተሸነፉ ለእስራኤላውያን ተገዙ፤ ዮፍታሔ ድል አድርጎ ሲመለስ ልትቀበለው የወጣችው የሚወዳት ልጁ ነበረች። በመሆኑም ዮፍታሔ በተሳለው መሠረት ‘የይሖዋ የምትሆነው’ እሷ ናት። (መሳ. 11:30-34) ታዲያ ይህ በእሷ ሕይወት ላይ ምን ለውጥ አስከተለ?

6. (ሀ) ዮፍታሔ ለአምላክ የተሳለውን ስእለት መፈጸም ለእሱም ሆነ ለልጁ ቀላል ነበር? (ለ) ዘዳግም 23:21, 23 እና መዝሙር 15:4 ስእለትን በተመለከተ ምን ያስተምሩናል?

6 የዮፍታሔ ሴት ልጅ፣ የአባቷን ስእለት ለመፈጸም በአምላክ ቤት ውስጥ ሙሉ ጊዜዋን እሱን ማገልገል ይጠበቅባት ነበር። ዮፍታሔ ይህን ስእለት የተሳለው በደንብ ሳያስብበት ነበር ማለት ነው? አይደለም፤ እሱን ለመቀበል ከቤቱ የምትወጣው ሴት ልጁም ልትሆን እንደምትችል ሳያውቅ አይቀርም። ይህን አወቀም አላወቀ፣ ስእለቱን ለመፈጸም እሱም ሆነ ልጁ ትልቅ መሥዋዕት መክፈል እንደሚጠይቅባቸው ጥያቄ የለውም። ዮፍታሔ፣ ልጁን ባያት ጊዜ “ልብሱን ቀደደ፤ እንዲህም አለ፦ ‘ወዮ፣ ልጄ! ልቤን ሰበርሽው።’” ልጁም ‘ስለ ድንግልናዋ አለቀሰች።’ እንዲህ የተሰማቸው ለምንድን ነው? ዮፍታሔ ወንድ ልጅ አልነበረውም፤ ያለችው አንዲት ልጅ ደግሞ ከዚያ በኋላ ስለማታገባና ልጅ ስለማትወልድ ዮፍታሔ የልጅ ልጆች ማየት አይችልም። የቤተሰቡን ስም የሚያስጠራ ዘር አይኖርም። ይሁን እንጂ ዮፍታሔና ልጁ ከራሳቸው ስሜት የበለጠ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር እንዳለ ተገንዝበው ነበር። ዮፍታሔ “አንዴ ለይሖዋ ቃል ገብቻለሁ፤ ልመልሰውም አልችልም” አለ። ልጁም “የገባኸውን ቃል በእኔ ላይ ፈጽምብኝ” አለችው። (መሳ. 11:35-39) ዮፍታሔና ሴት ልጁ ታማኝ ሰዎች ነበሩ፤ ለሉዓላዊው አምላክ የገቡትን ቃል መፈጸም ከፍተኛ ዋጋ ቢያስከፍላቸውም ቃላቸውን ለማጠፍ ጨርሶ አላሰቡም።—ዘዳግም 23:21, 23ን እና መዝሙር 15:4ን አንብብ።

7. (ሀ) ሐና ለአምላክ ምን ተሳለች? ይህን ያደረገችው ለምንድን ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ? (ለ) የሐና ስእለት በሳሙኤል ሕይወት ላይ ምን ለውጥ አስከትሏል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

7 ሐናም ለይሖዋ የተሳለችውን ስእለት በታማኝነት ፈጽማለች። ሐና መሃን በመሆኗ ምክንያት ውስጧ በብሶትና በጭንቀት ተሞልቶ ነበር፤ በዚያ ላይ ደግሞ ጣውንቷ ዘወትር ትሳለቅባት ነበር። (1 ሳሙ. 1:4-7, 10, 16) በዚህ የተነሳ ለአምላክ የልቧን አውጥታ በማፍሰስ እንዲህ ስትል ተሳለች፦ “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አገልጋይህ እየደረሰባት ያለውን መከራ ተመልክተህ ብታስበኝና አገልጋይህን ሳትረሳት ወንድ ልጅ ብትሰጣት በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለይሖዋ እሰጠዋለሁ፤ ራሱንም ምላጭ አይነካውም።” * (1 ሳሙ. 1:11) ሐና ያቀረበችው ልመና ምላሽ ያገኘ ሲሆን ወንድ ልጅ ወለደች። ይህ ምንኛ አስደስቷት ይሆን! ያም ቢሆን ለአምላክ የተሳለችውን ነገር አልረሳችም። ወንድ ልጅ ስትወልድ “ከይሖዋ የለመንኩት ነው” በማለት ተናግራለች።—1 ሳሙ. 1:20

8. (ሀ) ሐና ስእለቷን መፈጸም ቀላል ሆኖላት ነበር? (ለ) በመዝሙር 61 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ዳዊት የተናገረው ሐሳብ የሐናን ግሩም ምሳሌ የሚያስታውስህ እንዴት ነው?

8 ሳሙኤል ሦስት ዓመት ገደማ ሲሆነው ልክ ጡት እንደጣለ ሐና ለአምላክ የገባችውን ስእለት ፈጸመች። ቃሏን ለማጠፍ ጨርሶ አላሰበችም። ሳሙኤልን በሴሎ ባለው የማደሪያ ድንኳን ወደሚያገለግለው ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ኤሊ ይዛው በመሄድ እንዲህ አለችው፦ “ይህን ልጅ እንዲሰጠኝ ጸልዬ ነበር፤ ይሖዋም የለመንኩትን ሰጠኝ። እኔ ደግሞ በበኩሌ ልጁን ለይሖዋ እሰጠዋለሁ። በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ለይሖዋ የተሰጠ ይሆናል።” (1 ሳሙ. 1:24-28) ከዚያ በኋላ ሳሙኤል በማደሪያው ድንኳን ውስጥ መኖር ጀመረ። መጽሐፍ ቅዱስ “ብላቴናው ሳሙኤልም በይሖዋ ፊት እያደገ ሄደ” ይላል። (1 ሳሙ. 2:21) ይሁንና ሐና ስእለቷን መፈጸም ቀላል ሆኖላት ነበር? ሐና ሕፃን ልጇን በጣም እንደምትወደው የታወቀ ነው፤ ከዚያ በኋላ ግን በየቀኑ ልታገኘው አትችልም። ልጇን ማቀፍ፣ ከእሱ ጋር መጫወትና እሱን መንከባከብ ሊያምራት እንደሚችል ጥያቄ የለውም፤ ሐና፣ አንዲት እናት የምትወደውን ልጇን ስታሳድግ የሚኖራት አስደሳች ትዝታ ሁሉ ሊቀርባት ነው። ሆኖም ሐና ለአምላክ የተሳለችውን በመፈጸሟ አልተቆጨችም። “ልቤ በይሖዋ ሐሴት አደረገ” በማለት ተናግራለች።—1 ሳሙ. 2:1, 2፤ መዝሙር 61:1, 5, 8ን አንብብ።

ለይሖዋ የገባኸውን ቃል እየፈጸምክ ነው?

9. ቀጥሎ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

9 ለአምላክ ስእለት መሳል ወይም ቃል መግባት በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ ተመልክተናል። በመሆኑም የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመርመራችን የተገባ ነው፦ ክርስቲያኖች፣ ምን ለማድረግ ቃል ሊገቡ ይችላሉ? ቃላቸውን ለማክበርስ ምን ያህል ጥረት ሊያደርጉ ይገባል?

ራስህን ስትወስን የገባኸው ቃል

ራስህን ስትወስን የገባኸው ቃል (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)

10. አንድ ክርስቲያን በሕይወቱ ውስጥ ከሚገባው ቃል ሁሉ የላቀው የትኛው ነው? ይህ ቃለ መሐላ ምን ማድረግን ይጠይቃል?

10 አንድ ክርስቲያን ሕይወቱን ለይሖዋ ሲወስን የሚገባው ቃል ከሌሎች ቃለ መሐላዎች ሁሉ የላቀ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ራሱን ሲወስን፣ ለይሖዋ በግሉ በሚያቀርበው ጸሎት ላይ አምላክን ለዘላለም ለማገልገል ቃል ይገባል፤ በሕይወቱ ውስጥ የሚያጋጥመው ማንኛውም ነገር ይህን ውሳኔውን አይለውጠውም። ኢየሱስ እንደተናገረው አንድ ሰው ይህን ሲያደርግ ‘ራሱን ይክዳል’፤ በሌላ አባባል በሕይወቱ ውስጥ ከምንም ነገር በላይ የአምላክን ፈቃድ ለማስቀደምና የራሱን ፍላጎት ለመተው ቃል ይገባል። (ማቴ. 16:24) ግለሰቡ ራሱን ከወሰነበት ጊዜ አንስቶ ‘የይሖዋ ነው።’ (ሮም 14:8) ራሱን ለመወሰን ቃል የሚገባ ማንኛውም ሰው እንደ መዝሙራዊው ቃሉን በቁም ነገር ሊመለከተው ይገባል፤ መዝሙራዊው ለአምላክ ስለገባው ቃል ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ላደረገልኝ መልካም ነገር ሁሉ ለይሖዋ ምን እመልስለታለሁ? በሕዝቡ ሁሉ ፊት ስእለቴን ለይሖዋ እፈጽማለሁ።”—መዝ. 116:12, 14

11. መጠመቅህ ምን ያሳያል?

11 ራስህን ለይሖዋ ወስነሃል? ውሳኔህን በሕዝብ ፊት ለማሳየትስ በውኃ ተጠምቀሃል? ከሆነ ግሩም ውሳኔ አድርገሃል! በተጠመቅክበት ቀን ራስህን ለይሖዋ ስለመወሰንህ በሕዝብ ፊት ጥያቄ ቀርቦልህ እንደነበር ታስታውስ ይሆናል፤ በተጨማሪም “ራስህን ለአምላክ መወሰንህና መጠመቅህ በአምላክ መንፈስ በሚመራው ድርጅት ውስጥ ከታቀፉት የይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንዱ እንደሚያስቆጥርህ ተገንዝበሃል?” የሚል ጥያቄ ቀርቦልህ ነበር። ለእነዚህ ጥያቄዎች “አዎ” በማለት መመለስህ ሕይወትህን ያለምንም ገደብ ለአምላክ መስጠትህን የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ የተሾምክ የይሖዋ አምላክ አገልጋይ በመሆን ለመጠመቅ ብቁ መሆንህን ያረጋግጣል። ይህን ማድረግህ ይሖዋን በእጅጉ አስደስቶት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም!

12. (ሀ) የትኞቹን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው? (ለ) ጴጥሮስ የትኞቹን ባህርያት እንድናዳብር መክሮናል?

12 ይሁንና ጥምቀት የመጀመሪያው እርምጃ ነው። ከተጠመቅንበት ጊዜ አንስቶ አምላክን በታማኝነት በማገልገል ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን መኖር ይገባናል። በመሆኑም ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘ከተጠመቅኩ ወዲህ ምን ያህል መንፈሳዊ እድገት አድርጌያለሁ? አሁንም ይሖዋን በሙሉ ልቤ እያገለገልኩ ነው? (ቆላ. 3:23) አዘውትሬ እጸልያለሁ? መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ አነባለሁ? በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ዘወትር እገኛለሁ? አቅሜ በፈቀደ መጠን አዘውትሬ በአገልግሎት እካፈላለሁ? ወይስ በእነዚህ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የማደርገው ተሳትፎ በተወሰነ መጠን ቀንሷል?’ ሐዋርያው ጴጥሮስ በእምነታችን ላይ እውቀትን፣ ጽናትን እና ለአምላክ ማደርን እየጨመርን ከሄድን ለይሖዋ በምናቀርበው አገልግሎት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደምንችል ገልጿል።2 ጴጥሮስ 1:5-8ን አንብብ።

13. ራሱን ወስኖ የተጠመቀ አንድ ክርስቲያን ምን ነገር መገንዘብ አለበት?

13 ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን የገባነውን ቃል ማጠፍ የምንችልበት ምንም መንገድ የለም። አንድ ሰው ይሖዋን ማገልገል ወይም በክርስቲያናዊ መንገድ ሕይወቱን መምራት ቢታክተው፣ ራሱን ለአምላክ የወሰነው ከልቡ እንዳልሆነና ጥምቀቱም ሊጸና እንደማይችል በመግለጽ ወደኋላ ማለት አይችልም። * ይህ ግለሰብ ሲጠመቅ፣ ራሱን ሙሉ በሙሉ ለአምላክ እንደወሰነ አድርጎ አቅርቧል። በመሆኑም ማንኛውንም ከባድ ኃጢአት ቢፈጽም በይሖዋም ሆነ በጉባኤው ፊት ተጠያቂ ይሆናል። (ሮም 14:12) ማናችንም ብንሆን “መጀመሪያ ላይ የነበረህን ፍቅር ትተሃል” መባል አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ “ሥራህን፣ ፍቅርህን፣ እምነትህን፣ አገልግሎትህንና ጽናትህን አውቃለሁ፤ ደግሞም ከመጀመሪያው ሥራህ ይልቅ የአሁኑ እንደሚበልጥ አውቃለሁ” ብሎ ስለ እኛ እንዲናገር እንፈልጋለን። (ራእይ 2:4, 19) ሁላችንም ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን በመኖር ይሖዋን እናስደስት።

ትዳር ስትመሠርት የገባኸው ቃል

የጋብቻ ቃለ መሐላ (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)

14. አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ከሚገባቸው ቃለ መሐላዎች መካከል ሁለተኛ ቦታ የሚሰጠው የትኛው ነው? ለምንስ?

14 አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ከሚገባቸው ቃለ መሐላዎች መካከል ሁለተኛ ቦታ የሚሰጠው የጋብቻ ቃለ መሐላው ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ጋብቻ ቅዱስ ነው። ሙሽራውና ሙሽራይቱ ቃለ መሐላ የሚፈጽሙት በአምላክና በምሥክሮች ፊት ነው። በብዙ የዓለም ክፍሎች አንድ ወንድና አንዲት ሴት ሲጋቡ፣ ‘ሁለቱም በአምላክ የጋብቻ ሥርዓት ሥር በዚህች ምድር ላይ በሕይወት አብረው እስከኖሩ ድረስ’ አንዳቸው ሌላውን ለመውደድና ለመንከባከብ እንዲሁም እርስ በርስ ለመከባበር ቃል ይገባሉ። ሌሎችም ቢሆኑ በቀጥታ እነዚህን ቃላት በመጠቀም ቃል ባይገቡም በአምላክ ፊት ቃለ መሐላ ፈጽመዋል። ሙሽሮቹ በዚህ መንገድ ቃል ከገቡ በኋላ ባል እና ሚስት ተብለው ይጠራሉ፤ የአምላክ ዓላማ ጋብቻቸው የዕድሜ ልክ ጥምረት እንዲሆን ነው። (ዘፍ. 2:24፤ 1 ቆሮ. 7:39) በመሆኑም ኢየሱስ እንዳለው “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው” ይኸውም ባልም ሆነ ሚስት አሊያም ሌላ ሰው ‘ሊለያየው አይገባም።’ ስለዚህ ትዳር የሚመሠርቱ ሰዎች፣ ፍቺን እንደ አማራጭ ሊመለከቱት እንደማይገባ መገንዘብ ይኖርባቸዋል።—ማር. 10:9

15. ክርስቲያኖች ዓለም ለትዳር ያለው አመለካከት እንዳይጋባባቸው ሊጠነቀቁ የሚገባው ለምንድን ነው?

15 እርግጥ ነው፣ ፍጹም የሆነ ትዳር የለም። ትዳር ፍጽምና የሚጎድላቸው ሁለት ሰዎች ጥምረት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ያገቡ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ “መከራ” ሊያጋጥማቸው እንደሚችል የሚናገረው ለዚህ ነው። (1 ቆሮ. 7:28) የሚያሳዝነው በዓለም ላይ ያሉ በርካታ ሰዎች ትዳርን አቅልለው ይመለከቱታል። በትዳራቸው ውስጥ ችግር ሲያጋጥማቸው ችግሩን ለመፍታት ጥረት ከማድረግ ይልቅ የትዳር ጓደኛቸውን ትተው ይሄዳሉ። ክርስቲያኖች ግን እንዲህ ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው አይገባም። የጋብቻ ቃለ መሐላን ማፍረስ አምላክን ከመዋሸት ተለይቶ አይታይም፤ አምላክ ደግሞ ውሸታሞችን ይጠላል! (ዘሌ. 19:12፤ ምሳሌ 6:16-19) ሐዋርያው ጳውሎስ “በሚስት ታስረሃል? ከሆነ መፈታትን አትሻ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮ. 7:27) ጳውሎስ ይህን ያለው ይሖዋ፣ የትዳር ጓደኛን በማታለል የሚፈጸም ፍቺንም እንደሚጠላ ስለሚያውቅ ነው።—ሚል. 2:13-16

16. መጽሐፍ ቅዱስ ፍቺንና መለያየትን አስመልክቶ ምን ይላል?

16 ኢየሱስ እንደገለጸው በቅዱሳን መጻሕፍት መሠረት ፍቺ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችለው፣ ታማኝ የሆነው የትዳር አጋር፣ ምንዝር የፈጸመ የትዳር ጓደኛውን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ካልሆነ ብቻ ነው። (ማቴ. 19:9፤ ዕብ. 13:4) ከትዳር ጓደኛ ጋር ስለመለያየትስ ምን ማለት ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድም ግልጽ ሐሳብ ይዟል። (1 ቆሮንቶስ 7:10, 11ን አንብብ።) ባልና ሚስት ለመለያየት የሚያበቃቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ ምክንያት የለም። ይሁንና አንዳንድ ያገቡ ክርስቲያኖች ከትዳር ጓደኛቸው ጋር እንዲለያዩ የሚያደርጓቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ተሰምቷቸዋል፤ ለምሳሌ አካላዊ ጥቃት ከሚፈጽም ወይም ከሃዲ ከሆነ የትዳር ጓደኛ ጋር መኖር ለሕይወታቸው አሊያም ለመንፈሳዊነታቸው በጣም አስጊ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። *

17. ክርስቲያን ባለትዳሮች ጋብቻቸው ዘላቂ ጥምረት እንዲሆን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

17 ባለትዳሮች በትዳራቸው ውስጥ ስላጋጠማቸው ችግር ምክር ለመጠየቅ ወደ ሽማግሌዎች በሚሄዱበት ጊዜ ሽማግሌዎቹ እውነተኛ ፍቅር ምንድን ነው? (እንግሊዝኛ) የተባለውን ቪዲዮ እንዲመለከቱ እንዲሁም ደስተኛ ቤተሰብ ሊኖርህ ይችላል! የሚለውን ብሮሹር አብረው እንዲያጠኑ ማበረታቻ መስጠታቸው ጠቃሚ ነው። ለምን? ምክንያቱም እነዚህ መሣሪያዎች አምላክ ያወጣቸውን መመሪያዎች ይዘዋል፤ በርካቶች እነዚህን መመሪያዎች በመከተላቸው ትዳራቸውን ማጠናከር ችለዋል። አንድ ባልና ሚስት “ይህን ብሮሹር ማጥናት ከጀመርን ወዲህ በትዳራችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ደስተኞች ሆነናል” በማለት ተናግረዋል። በትዳር ውስጥ 22 ዓመታት ያሳለፈች አንዲት እህት ትዳሯ ሊፈርስ እንደተቃረበ ተሰምቷት ነበር፤ “ሁለታችንም የተጠመቅን ክርስቲያኖች ብንሆንም ለመግባባት በጣም ተቸግረን ነበር። ቪዲዮው የወጣው ልክ በሚያስፈልገን ጊዜ ነው! አሁን ትዳራችን በጣም ተሻሽሏል።” አንተስ ትዳር መሥርተሃል? እንግዲያው ይሖዋ ያወጣቸውን መመሪያዎች በትዳርህ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ጣር። ይህን ማድረግህ የጋብቻ ቃለ መሐላህን ጠብቀህና ደስተኛ ሆነህ ለመኖር ያስችልሃል!

የልዩ ሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሚገቡት ቃለ መሐላ

18, 19. (ሀ) በርካታ ክርስቲያን ወላጆች ምን አድርገዋል? (ለ) በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መስክ ስለተሰማሩ ክርስቲያኖች ምን ማለት ይቻላል?

18 ዮፍታሔና ሐና ሌላም የሚያመሳስላቸው ነገር አለ። የሁለቱም ስእለት ተመሳሳይ ውጤት አምጥቷል፤ ልጆቻቸው የወላጆቻቸውን ስእለት ለመፈጸም ሲሉ በማደሪያው ድንኳን ውስጥ ልዩና ቅዱስ የሆነ አገልግሎት ለማቅረብ ሕይወታቸውን ሰጥተዋል። ይህም ከፍተኛ እርካታ የሚያስገኝ ሕይወት ለመምራት አስችሏቸዋል። በዛሬው ጊዜም በርካታ ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጆቻቸውን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲሳተፉና በአምላክ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ሕይወት እንዲመሩ ያበረታቷቸዋል። እነዚህ ወላጆችም ሆኑ ልጆቻቸው በእጅጉ ሊመሰገኑ ይገባል።—መሳ. 11:40፤ መዝ. 110:3

የልዩ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ቃለ መሐላ (አንቀጽ 19⁠ን ተመልከት)

19 በአሁኑ ጊዜ የዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች የልዩ ሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሥርዓተ ማኅበር አባላት የሆኑ 67,000 ገደማ ወንድሞችና እህቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በቤቴል ያገለግላሉ፤ ሌሎቹ በግንባታ ወይም በወረዳ ሥራ ይካፈላሉ፤ ከዚህም ሌላ መስክ ላይ የሚያገለግሉ አስተማሪዎች፣ ልዩ አቅኚዎች፣ ሚስዮናውያን እንዲሁም የትላልቅ ስብሰባ አዳራሽ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት አገልጋዮች አሉ። * እነዚህ ክርስቲያኖች “የታዛዥነትና ከፍቅረ ንዋይ የመታቀብ ቃለ መሐላ” ፈጽመዋል፤ በመሆኑም የተሰጣቸውን ማንኛውንም የሥራ ምድብ በመሥራት የአምላክን መንግሥት ዓላማዎች ለማራመድ፣ ከፍቅረ ንዋይ ነፃ የሆነ ቀላል ኑሮ ለመኖር እንዲሁም ሳያስፈቅዱ ሰብዓዊ ሥራ ላለመሥራት ተስማምተዋል። ልዩ ተደርጎ የሚታየው ሥራው እንጂ ሰዎቹ አይደሉም። እነዚህ አገልጋዮች በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ እስካሉ ድረስ ትሑት በመሆን ከገቡት ቃለ መሐላ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል።

20. “በየቀኑ” ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለምንስ?

20 በዚህ ርዕስ ውስጥ ሦስት ቃለ መሐላዎችን ተመልክተናል፤ አንተም ከእነዚህ ቃለ መሐላዎች መካከል አንዱን፣ ሁለቱን ወይም ሦስቱንም ፈጽመህ ሊሆን ይችላል። በአምላክ ፊት የገባኸውን ቃለ መሐላ ወይም ስእለትህን አክብደህ ልትመለከተው እንደሚገባ የታወቀ ነው። (ምሳሌ 20:25) ለአምላክ የገባነውን ቃል ማጠፍና ስእለታችንን አለመፈጸም ከባድ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። (መክ. 5:6) እንግዲያው ‘ስእለታችንን በየቀኑ በመፈጸም ለይሖዋ ስም ለዘላለም የውዳሴ መዝሙር እንዘምር።’—መዝ. 61:8

^ አን.7 ሐና፣ ወንድ ልጅ የምትወልድ ከሆነ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ናዝራዊ እንደሚሆን ለይሖዋ ተስላ ነበር። ይህም ሲባል ልጇ ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት የተለየና የተወሰነ ይሆናል ማለት ነው።—ዘኁ. 6:2, 5, 8

^ አን.13 የጉባኤ ሽማግሌዎች አንድ ሰው ለመጠመቅ ብቁ እንደሆነ ለማረጋገጥ ከሚያደርጉት ጥረት አንጻር ግለሰቡ ከተጠመቀ በኋላ ጥምቀቱ የማይጸናበት አጋጣሚ በጣም ጠባብ ነው።

^ አን.19 መስክ ላይ የሚያገለግሉ አስተማሪዎች የሚባሉት በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት፣ በጉባኤ ሽማግሌዎች ትምህርት ቤት ወይም ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ለሚስቶቻቸው በተዘጋጀው ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ ወንድሞች ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ወንድሞች የሚያስተምሩት በትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች፣ በመንግሥት አዳራሾች ወይም ለዚህ ዓላማ በተዘጋጁ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው