በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም”

“ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም”

“ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።”—ፊልጵ. 4:7

መዝሙሮች፦ 112, 58

1, 2. ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ ምን አጋጠማቸው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

እኩለ ሌሊት ገደማ ነው። ሁለቱ ሚስዮናውያን ማለትም ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ ከተማ በሚገኝ አንድ እስር ቤት ውስጠኛ ክፍል ውስጥ ታስረዋል። እግራቸው በእግር ግንድ ጥፍር ተደርጎ ታስሯል፤ በተጨማሪም በደረሰባቸው ከባድ ድብደባ ምክንያት የቆሰለው ጀርባቸው እያሠቃያቸው ነው። (ሥራ 16:23, 24) ይህ ሁሉ ነገር የተፈጠረው በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው! በጣም የተበሳጩ ሰዎች ያለምንም ማስጠንቀቂያ ጳውሎስንና ሲላስን እየጎተቱ ወደ ገበያ ቦታው በመውሰድ በጥድፊያ በተሰየመ ሸንጎ ፊት አቆሟቸው። ከዚያም ልብሳቸውን ከገፈፏቸው በኋላ በበትር ክፉኛ ደበደቧቸው። (ሥራ 16:16-22) ይህ እንዴት ያለ ኢፍትሐዊ ድርጊት ነው! የሮም ዜግነት የነበረው ጳውሎስ በተገቢው መንገድ ሊዳኝ ይገባ ነበር። *

2 ጳውሎስ ጨለማ ውስጥ ተቀምጦ በዚያን ዕለት የተከሰቱትን ሁኔታዎች መለስ ብሎ እያሰበ ነው። ስለ ፊልጵስዩስ ነዋሪዎች ሳያስብ አልቀረም። ጳውሎስ ከጎበኛቸው በርካታ ከተሞች በተለየ መልኩ በዚህች ከተማ ውስጥ ምንም የአይሁድ ምኩራብ አልነበረም። በመሆኑም አይሁዳውያኑ ለአምልኮ ይሰበሰቡ የነበረው ከከተማው በር ውጭ ባለ አንድ ወንዝ አጠገብ ነበር። (ሥራ 16:13, 14) ይህ የሆነው በከተማዋ ውስጥ ያሉት አይሁዳውያን ወንዶች ብዛት አሥር ስለማይሞላ ይሆን? ምክንያቱም በአንድ ከተማ ውስጥ ምኩራብ እንዲኖር ከተፈለገ ቢያንስ አሥር አይሁዳውያን ወንዶች መኖር ነበረባቸው። የፊልጵስዩስ ሰዎች የሮም ዜግነት ያላቸው በመሆኑ በጣም ይኩራሩ ነበር። (ሥራ 16:21) እነዚህ ሰዎች፣ አይሁዳውያን የሆኑት ጳውሎስና ሲላስ የሮም ዜግነት ሊኖራቸው ይችላል ብለው ጨርሶ ያላሰቡት በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ሁለቱ ሰዎች ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለእስር ተዳርገዋል።

3. ጳውሎስ ለእስር መዳረጉ ግራ አጋብቶት መሆን አለበት የምንለው ለምንድን ነው? ሆኖም ምን አመለካከት እንዳለው አሳይቷል?

3 በተጨማሪም ጳውሎስ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ስለተከናወኑት ነገሮች አስቦ መሆን አለበት። ከጥቂት ወራት በፊት ጳውሎስ ከኤጅያን ባሕር ባሻገር በምትገኘው በትንሿ እስያ ውስጥ ነበር። እዚያ በነበረበት ወቅት በአንዳንድ ቦታዎች እንዳይሰብክ መንፈስ ቅዱስ በተደጋጋሚ ከልክሎታል። መንፈስ ቅዱስ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሄድ እየገፋው ያለ ይመስል ነበር። (ሥራ 16:6, 7) ግን ወዴት? ጳውሎስ በጥሮአስ ሳለ ያየው ራእይ ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ነበር። አንድ ሰው “ወደ መቄዶንያ ተሻገር” ብሎ ሲለምነው አየ። የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ በግልጽ የተረዳው ጳውሎስ ግብዣውን ወዲያው ተቀበለ። (የሐዋርያት ሥራ 16:8-10ን አንብብ።) ይሁንና ከዚያ በኋላ ምን ተፈጠረ? መቄዶንያ ከደረሰ ብዙም ሳይቆይ ለእስር ተዳረገ! ይሖዋ በጳውሎስ ላይ እንዲህ ያለ ነገር እንዲደርስ የፈቀደው ለምንድን ነው? በእስር የሚቆየው ለምን ያህል ጊዜ ይሆን? ምንም እንኳ እነዚህ ጥያቄዎች በጳውሎስ አእምሮ ውስጥ ይጉላሉ የነበረ ቢሆንም እምነቱንና ደስታውን እንዲነጥቁት አልፈቀደም። እሱም ሆነ ሲላስ ‘ይጸልዩና አምላክን በመዝሙር ያወድሱ ነበር።’ (ሥራ 16:25) የአምላክ ሰላም ልባቸውንና አእምሯቸውን አረጋግቶላቸው ነበር።

4, 5. (ሀ) ጳውሎስ ያጋጠመው ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥመን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ጳውሎስ የነበረበት ሁኔታ ባልተጠበቀ መንገድ የተለወጠው እንዴት ነው?

4 አንተም ልክ እንደ ጳውሎስ የአምላክን ቅዱስ መንፈስ አመራር ብትከተልም ነገሮች ባሰብከው መንገድ እየሄዱ እንዳልሆነ የተሰማህ ጊዜ ሊኖር ይችላል። በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ማድረግን የሚጠይቁ አሊያም ተፈታታኝ የሆኑ አዳዲስ ሁኔታዎች አጋጥመውህ ይሆናል። (መክ. 9:11) ወደኋላ መለስ ብለህ ስታስብ ይሖዋ አንዳንድ ነገሮችን የፈቀደበት ምክንያት ግራ ይገባህ ይሆናል። እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ በመተማመን እስከመጨረሻው እንድትጸና ምን ሊረዳህ ይችላል? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ቀደም ሲል ወደተጠቀሰው የጳውሎስና የሲላስ ታሪክ እንመለስ።

5 ጳውሎስና ሲላስ በመዝሙር አምላክን እያወደሱ ሳለ በተከታታይ ያልተጠበቁ ነገሮች ተከሰቱ። በድንገት ከባድ የምድር ነውጥ አካባቢውን አናጋው። የእስር ቤቱ በሮች ወለል ብለው ተከፈቱ። እስረኞቹ የታሰሩበት ማሰሪያ ሁሉ ተፈታ። ጳውሎስ የእስር ቤቱን ጠባቂ ራሱን ከመግደል አስጣለው። የእስር ቤቱ ጠባቂና መላው ቤተሰቡ ተጠመቁ። በማግስቱ ጠዋት የከተማዋ ሕግ አስከባሪዎች ጳውሎስንና ሲላስን ከእስር እንዲያስፈቱ መኮንኖችን ላኩ። ባለሥልጣናቱ፣ ጳውሎስና ሲላስ ከተማዋን ለቀው በሰላም እንዲሄዱ ጠየቋቸው። ከዚያም የሕግ አስከባሪዎቹ፣ ጳውሎስና ሲላስ የሮም ዜጎች መሆናቸውን ሲያውቁ ትልቅ ስህተት እንደሠሩ ገባቸው፤ በመሆኑም ጳውሎስንና ሲላስን ለማስወጣት እነሱ ወዳሉበት ሄዱ። ጳውሎስና ሲላስ ግን በመጀመሪያ በቅርቡ የተጠመቀችውን እህታቸውን ሊዲያን መሰናበት እንደሚፈልጉ ገለጹ። በተጨማሪም አጋጣሚውን ተጠቅመው ወንድሞችን አበረታቱ። (ሥራ 16:26-40) በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁኔታዎች የተለዋወጡበት መንገድ እንዴት አስገራሚ ነው!

“ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ”

6. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

6 ጳውሎስና ሲላስ ታስረው በነበሩበት ወቅት ከተከሰቱት ሁኔታዎች ምን እንማራለን? ይሖዋ ፈጽሞ ያልጠበቅነውን ነገር ሊያደርግ ስለሚችል ፈታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን መጨነቅ አያስፈልገንም። ጳውሎስ ከዚህ ክንውን ትልቅ ትምህርት እንዳገኘ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ከጊዜ በኋላ ጭንቀትንና ከአምላክ የሚገኘውን ሰላም አስመልክቶ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ ይህን ያሳያል። እስቲ በመጀመሪያ በፊልጵስዩስ 4:6, 7 (ጥቅሱን አንብብ) ላይ የሚገኘውን ጳውሎስ የተናገረውን ሐሳብ እንመልከት። ከዚያም ይሖዋ ያልተጠበቀ ነገር ሊያደርግ እንደሚችል የሚያሳዩ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እንመረምራለን። እንዲሁም “የአምላክ ሰላም” በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ በመተማመን እስከመጨረሻው ለመጽናት የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

7. ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ከጊዜ በኋላ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ማጉላት የፈለገው ነጥብ ምን ነበር? እኛስ ጳውሎስ ከተናገረው ሐሳብ ምን ትምህርት እናገኛለን?

7 በፊልጵስዩስ የነበሩት ወንድሞች ጳውሎስ የጻፈላቸውን ደብዳቤ ሲያነቡ ጳውሎስን ስላጋጠመው ሁኔታ እንዲሁም ይሖዋ ፈጽሞ ባልጠበቁት መንገድ እንዴት እንደረዳው አስታውሰው መሆን አለበት። ጳውሎስ ሊያስተምራቸው የፈለገው ነጥብ ምን ነበር? በአጭር አነጋገር፣ ‘አትጨነቁ’ እያላቸው ነበር። ወደ ይሖዋ ከጸለዩ የአምላክን ሰላም እንደሚያገኙ ገልጾላቸዋል። ይሁንና የአምላክ ሰላም “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ” እንደሆነ ልብ በል። ይህ ምን ማለት ነው? አንዳንድ ተርጓሚዎች ይህን አገላለጽ “ከምናልመው ሁሉ በላይ” አሊያም “ከሰዎች ግምት ሁሉ የላቀ” ብለው ተርጉመውታል። ጳውሎስ “የአምላክ ሰላም” በአእምሯችን ልናስበው ከምንችለው ሁሉ በላይ አስገራሚ እንደሆነ መናገሩ ነበር። በመሆኑም በሰብዓዊ አመለካከት ሲታይ ችግሮቻችንን መወጣት የምንችልበት ምንም መንገድ የሌለ ቢመስልም ይሖዋ ግን መውጫ መንገዱን የሚያውቅ ከመሆኑም ሌላ ፈጽሞ ያልጠበቅነውን ነገር ሊያደርግ ይችላል።—2 ጴጥሮስ 2:9ን አንብብ።

8, 9. (ሀ) ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ኢፍትሐዊ ድርጊት ቢፈጸምበትም በዚህ ምክንያት ምን ጥሩ ውጤት ተገኝቷል? (ለ) በፊልጵስዩስ የነበሩት ወንድሞች ጳውሎስ በጻፈው ሐሳብ ላይ ሙሉ እምነት መጣል የሚችሉት ለምን ነበር?

8 በፊልጵስዩስ የነበሩት ወንድሞች ቀደም ሲል የተገለጹት ክንውኖች ከተከሰቱ በኋላ ባሉት አሥር ዓመታት ውስጥ የተከናወኑትን ነገሮች መለስ ብለው ሲያስቡ በጣም ተበረታተው መሆን አለበት። ጳውሎስ የጻፈው ነገር በእርግጥም እውነት ነበር። ይሖዋ ኢፍትሐዊ የሆነ ነገር እንዲፈጸም የፈቀደ ቢሆንም በዚህ የተነሳ ጳውሎስ ‘ለምሥራቹ መሟገትና ምሥራቹ በሕግ የጸና እንዲሆን ማድረግ’ የሚችልበት አጋጣሚ አግኝቷል። (ፊልጵ. 1:7) ይህ ሁኔታ እነዚያን የሕግ አስከባሪዎች በከተማቸው ውስጥ በተቋቋመው አዲስ የክርስቲያን ጉባኤ ላይ ምንም ነገር ከማድረጋቸው በፊት ቆም ብለው ማሰብ እንደሚያስፈልጋቸው ሳያስገነዝባቸው አልቀረም። ምናልባትም የጳውሎስ የጉዞ አጋር የሆነው ሐኪሙ ሉቃስ፣ ጳውሎስና ሲላስ ከፊልጵስዩስ ከወጡ በኋላ እዚያው ሊቆይ የቻለው ጳውሎስ በወሰደው እርምጃ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። በመሆኑም ሉቃስ በከተማዋ ውስጥ ላሉት አዲስ ክርስቲያኖች ተጨማሪ እርዳታ መስጠት ችሏል።

9 በእርግጥም በፊልጵስዩስ የነበሩት ክርስቲያኖች የጳውሎስን ደብዳቤ ሲያነቡ ጳውሎስ እየጻፈላቸው ያለው ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት እንደሆነ ያውቁ ነበር። ጳውሎስ በጣም ከባድ ሁኔታዎች ያጋጠሙት ቢሆንም “የአምላክ ሰላም” እንደነበረው በግልጽ ታይቷል። እንዲያውም ደብዳቤውን በጻፈበት ወቅት ሮም ውስጥ የቁም እስረኛ ነበር። ይሁንና በዚህም ሁኔታ ሥር ቢሆን “የአምላክ ሰላም” እንዳልተለየው አሳይቷል።—ፊልጵ. 1:12-14፤ 4:7, 11, 22

“ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ”

10, 11. ባጋጠመን ችግር የተነሳ ከልክ በላይ ስንጨነቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ይሖዋስ ምን ሊያደርግልን እንደሚችል መጠበቃችን ምክንያታዊ ይሆናል?

10 ስለ ምንም ነገር እንዳንጨነቅ እንዲሁም “የአምላክ ሰላም” እንዲኖረን ምን ሊረዳን ይችላል? ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ የጭንቀት ማርከሻው ጸሎት እንደሆነ ያሳያል። በመሆኑም ምንም ነገር ሲያስጨንቀን ወደ ይሖዋ መጸለይ ይኖርብናል። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7ን አንብብ።) ይሖዋ እንደሚያስብልህ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ወደ እሱ ጸልይ። ከይሖዋ ያገኘኻቸውን በረከቶች በማስታወስ ጸሎትህን “ከምስጋና ጋር” አቅርብ። ይሖዋ “ከምንጠይቀው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ” እንደሚችል ማስታወሳችን በእሱ ላይ ያለን እምነት እንዲጠናከር ያደርጋል።—ኤፌ. 3:20

11 ይሖዋ በፊልጵስዩስ ለጳውሎስና ለሲላስ እንዳደረገላቸው ሁሉ ለእኛም በግለሰብ ደረጃ በሚያደርግልን ነገር ልንገረም እንችላለን። ይሖዋ ተአምር ባይፈጽምልንም እንኳ ምንጊዜም የሚያስፈልገንን ነገር እንደሚያደርግልን መጠበቅ እንችላለን። (1 ቆሮ. 10:13) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ሁኔታውን እስኪያስተካክልልን አሊያም ችግሩን እስኪያስወግድልን ድረስ እጃችንን አጣጥፈን እንጠብቃለን ማለት አይደለም። ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። (ሮም 12:11) እንዲህ ማድረጋችን ጸሎታችን ከልብ የመነጨ እንደሆነ የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ እኛን የሚባርክበት ነገር እንዲያገኝ ያስችለዋል። ይሁንና ይሖዋ እኛ በምንጠይቀው፣ በምናስበው ወይም በምንጠብቀው ነገር እንደማይገደብ ልንዘነጋ አይገባም። አንዳንድ ጊዜ ፈጽሞ ያልጠበቅነውን ነገር በመፈጸም እንድንገረም ሊያደርገን ይችላል። ይሖዋ እኛን ለመርዳት ሲል ያልጠበቅነውን ነገር ሊያደርግ እንደሚችል ያለንን እምነት የሚያጠናክሩ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን እስቲ እንመልከት።

ይሖዋ ያልተጠበቀ ነገር እንደሚያደርግ የሚያሳዩ ምሳሌዎች

12. (ሀ) ንጉሥ ሕዝቅያስ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ጥቃት እንደሚሰነዝር በዛተበት ወቅት ምን አደረገ? (ለ) ይሖዋ ችግሩን ከፈታበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን?

12 መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ይሖዋ ያልተጠበቁ ነገሮችን እንዳደረገ የሚያሳዩ በርካታ ዘገባዎችን እናገኛለን። ንጉሥ ሕዝቅያስ የኖረው የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ከኢየሩሳሌም በስተቀር ሁሉንም የተመሸጉ የይሁዳ ከተሞች ወርሮ በያዘበት ወቅት ነበር። (2 ነገ. 18:1-3, 13) ከዚያም ሰናክሬም ትኩረቱን ወደ ኢየሩሳሌም አዞረ። ንጉሥ ሕዝቅያስ ይህ አደጋ በተጋረጠበት ወቅት ምን አደረገ? ወደ ይሖዋ የጸለየ ከመሆኑም ሌላ የይሖዋ ነቢይ የሆነውን ኢሳይያስን ምክር ጠይቋል። (2 ነገ. 19:5, 15-20) በተጨማሪም ሕዝቅያስ፣ ሰናክሬም የጣለበትን ቅጣት በመክፈል ምክንያታዊ መሆኑን አሳይቷል። (2 ነገ. 18:14, 15) በኋላም ከተማዋን ለረጅም ጊዜ ከበባ ለማዘጋጀት አንዳንድ እርምጃዎችን ወስዷል። (2 ዜና 32:2-4) ይሁንና ጉዳዩ መፍትሔ ያገኘው እንዴት ነው? ይሖዋ መልአኩን በመላክ በአንድ ሌሊት 185,000 የሚያክሉትን የሰናክሬም ወታደሮች ገደለ። ማንም ሰው ሌላው ቀርቶ ሕዝቅያስም እንኳ እንዲህ ያለ ነገር ይከሰታል ብሎ ሊጠብቅ አይችልም!—2 ነገ. 19:35

ዮሴፍን ካጋጠመው ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን? —ዘፍ. 41:42 (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

13. (ሀ) ዮሴፍን ካጋጠመው ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) የአብርሃም ሚስት የሆነችው ሣራ ምን ያልጠበቀችው ነገር አግኝታለች?

13 የያዕቆብ ልጅ የሆነው ወጣቱ ዮሴፍ ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት። ዮሴፍ ግብፅ ውስጥ እስር ቤት በነበረበት ወቅት፣ ከዚያ ወጥቶ በምድሪቱ ላይ ከፈርዖን ቀጥሎ ከፍተኛ ባለሥልጣን እንደሚሆን ብሎም ይሖዋ ሕዝቡን ከረሃብ ለመታደግ እንደሚጠቀምበት ሊገምት ይችላል? (ዘፍ. 40:15 ግርጌ፤ ዘፍ. 41:39-43፤ 50:20) ይሖዋ የወሰደው እርምጃ ዮሴፍ ሊገምት ከሚችለው ሁሉ በላይ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። የዮሴፍ ቅድመ አያት የሆነችውን የሣራን ሁኔታም እንመልከት። ሣራ በዕድሜ ስለገፋች አገልጋይዋ ከምትወልድላት ልጅ ውጭ ይሖዋ የራሷን ልጅ እንደሚሰጣት ልትጠብቅ አትችልም። የይስሐቅ መወለድ፣ ሣራ ልትገምተው ከምትችለው ሁሉ በላይ እንደሚሆን ግልጽ ነው።—ዘፍ. 21:1-3, 6, 7

14. በይሖዋ ላይ ምን እምነት መጣል እንችላለን?

14 እርግጥ ነው፣ ቃል የተገባልን አዲስ ዓለም ከመምጣቱ በፊት ይሖዋ ችግሮቻችንን ሁሉ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ያስወግድልናል ብለን አንጠብቅም፤ እንዲሁም ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ አንድ ዓይነት ተአምር እንዲፈጽምልን አንጠይቅም። ይሁንና አምላካችን ይሖዋ አገልጋዮቹን ከዚህ በፊት አስገራሚ በሆነ መንገድ እንደረዳቸውና ዛሬም ቢሆን እንዳልተለወጠ እናውቃለን። (ኢሳይያስ 43:10-13ን አንብብ።) ይህን ማወቃችን በእሱ እንድንተማመን ይረዳናል። ይሖዋ ፈቃዱን በተሟላ መንገድ መፈጸም እንድንችል የሚያስፈልገንን ኃይል ለመስጠት አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ እርግጠኞች ነን። (2 ቆሮ. 4:7-9) ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ምን ትምህርት እናገኛለን? ከሕዝቅያስ፣ ከዮሴፍና ከሣራ ታሪክ መመልከት እንደምንችለው ይሖዋ ለእሱ ታማኝ እስከሆንን ድረስ ከአቅማችን በላይ እንደሆኑ የሚሰሙንን ችግሮች መወጣት እንድንችል ይረዳናል።

ይሖዋ ለእሱ ታማኝ እስከሆንን ድረስ ከአቅማችን በላይ እንደሆኑ የሚሰሙንን ችግሮች መወጣት እንድንችል ይረዳናል

15. ‘የአምላክን ሰላም’ ይዘን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? ይህ ሊሆን የቻለውስ እንዴት ነው?

15 በሕይወታችን ውስጥ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም ‘የአምላክን ሰላም’ ይዘን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? ከአምላካችን ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ጥሩ ዝምድና ጠብቀን በመኖር ነው። እንዲህ ያለ ዝምድና ሊኖረን የሚችለው ለእኛ ሲል ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ በሰጠው “በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት” ብቻ ነው። የቤዛው ዝግጅት አባታችን ይሖዋ ካከናወናቸው አስገራሚ ነገሮች መካከል አንዱ ነው። ይሖዋ በቤዛው አማካኝነት ኃጢአታችንን ይሸፍንልናል፤ ይህም ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረንና ወደ እሱ እንድንቀርብ ያስችለናል።—ዮሐ. 14:6፤ ያዕ. 4:8፤ 1 ጴጥ. 3:21

ልባችንንና አእምሯችንን ይጠብቃል

16. ‘የአምላክን ሰላም’ ማግኘታችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? በምሳሌ አስረዳ።

16 ‘ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነውን የአምላክን ሰላም’ ማግኘታችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (ፊልጵ. 4:7) “ይጠብቃል” ተብሎ የተተረጎመው ቃል መጀመሪያ ላይ በተጻፈበት ቋንቋ፣ አንድን የታጠረ ከተማ እንዲጠብቁ የተመደቡ ወታደሮችን የሚያመለክት ከውትድርና ጋር በተያያዘ የሚሠራበት ቃል ነው። ፊልጵስዩስ እንዲህ ባለ መንገድ የምትጠበቅ ከተማ ነበረች። የፊልጵስዩስ ነዋሪዎች ወታደሮቹ የከተማዋን በሮች እንደሚጠብቁ ስለሚያውቁ ያለምንም ስጋት ተኝተው ያድራሉ። እኛም በተመሳሳይ “የአምላክ ሰላም” ሲኖረን ልባችንና አእምሯችን ከስጋት ነፃ ይሆናል። ይሖዋ እንደሚያስብልንና እንዲሳካልን እንደሚፈልግ እናውቃለን። (1 ጴጥ. 5:10) ይህን ማወቃችን ከልክ በላይ በጭንቀት አሊያም በተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዳንዋጥ ይጠብቀናል።

17. የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እንድንጠብቅ ምን ሊረዳን ይችላል?

17 በቅርቡ የሰው ልጆች በምድር ላይ ተከስቶ የማያውቅ ታላቅ መከራ ያጋጥማቸዋል። (ማቴ. 24:21, 22) በዚያን ወቅት እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ ምን እንደሚያጋጥመን አናውቅም። ይሁንና በጭንቀት የምንዋጥበት ምንም ምክንያት የለም። ይሖዋ ስለሚወስደው እርምጃ በዝርዝር ባናውቅም አምላካችን ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ እናውቃለን። ከዚህ በፊት ስላደረጋቸው ነገሮች መመርመራችን ይሖዋ ዓላማውን ዳር እንዳያደርስ የሚያግደው ምንም ነገር እንደሌለ እንዲሁም ይህን ዓላማውን ዳር ለማድረስ አንዳንድ ጊዜ ፈጽሞ ያልተጠበቁ ነገሮችን እንደሚያደርግ እንድንገነዘብ አስችሎናል። ይሖዋ በዛሬው ጊዜ የሚያደርግልን ማንኛውም ነገር፣ ‘ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነውን የአምላክን ሰላም’ በሕይወታችን ውስጥ ልዩ በሆነ መንገድ የምናይበት አጋጣሚ ይሰጠናል።

^ አን.1 ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ሲላስም የሮም ዜግነት ነበረው።—ሥራ 16:37