በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

ፈተናዎችን በጽናት መቋቋም በረከት ያስገኛል

ፈተናዎችን በጽናት መቋቋም በረከት ያስገኛል

“አንተ በጣም ጨካኝ አባት ነህ” ሲል የኬጂቢ አዛዡ ጮኸብኝ። * ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “ነፍሰ ጡር የሆነችውን ሚስትህንና ይህችን አንዲት ፍሬ ልጅ ዝም ብለህ ስትተዋቸው ምንም አይገድህም? እነሱን ማን ሊንከባከባቸው ነው? ይሄን እንቅስቃሴህን ትተህ አርፈህ ወደ ቤትህ ብትመለስ ይሻልሃል!” እኔም “ቤተሰቤን አልተውኩም። ያሰራችሁኝ እናንተ ናችሁ! ደግሞስ ምን አጥፍቼ ነው?” አልኩት። አዛዡም “የይሖዋ ምሥክር ከመሆን የከፋ ምንም ወንጀል የለም” ሲል በቁጣ መለሰልኝ።

ከኬጂቢ አዛዡ ጋር ይህን የተነጋገርነው በ1959 በኢርኩትስክ፣ ሩሲያ ውስጥ በሚገኝ እስር ቤት በነበርኩበት ወቅት ነው። እኔና ባለቤቴ ማሪያ ‘ለጽድቅ ስንል መከራ ለመቀበል’ ራሳችንን ያዘጋጀነው ለምን እንደሆነና ታማኝነታችንን መጠበቃችን ምን በረከት እንዳስገኘልን እስቲ ላጫውታችሁ።—1 ጴጥ. 3:13, 14

የተወለድኩት በ1933 ዘለትኒኪ ተብላ በምትጠራ አንዲት የዩክሬን መንደር ውስጥ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የነበሩት አክስቴና ባለቤቷ በ1937 ሊጠይቁን ከፈረንሳይ መጥተው ነበር፤ ከዚያም መንግሥት እና መዳን (እንግሊዝኛ) የተባሉትን በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የተዘጋጁ መጻሕፍት ሰጥተውን ሄዱ። አባቴ እነዚህን መጻሕፍት ሲያነብ በአምላክ ላይ የነበረው እምነት እንደ አዲስ ተቀጣጠለ። የሚያሳዝነው በ1939 በጠና ታመመ፤ ከመሞቱ በፊት ግን ለእናቴ “እውነት ይህ ነው። ይህን እውነት ለልጆቹ አስተምሪያቸው” ብሏት ነበር።

ሳይቤሪያ—አዲስ የአገልግሎት መስክ

በሚያዝያ 1951 የመንግሥት ባለሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮችን ከምዕራብ ሶቪየት ኅብረት ወደ ሳይቤሪያ ማጋዝ ጀመሩ። እኔ፣ እናቴና ታናሽ ወንድሜ ግሪጎሪ ከምዕራብ ዩክሬን ወደ ሳይቤሪያ ተጋዝን። በባቡር ከ6,000 ኪሎ ሜትር በላይ ከተጓዝን በኋላ ሳይቤሪያ ውስጥ ወደምትገኝ ቱሉን የተባለች ከተማ ደረስን። ከሁለት ሳምንት በኋላ ደግሞ ታላቅ ወንድሜ ቦግዳን በቱሉን አቅራቢያ በምትገኝ አንጋርስክ የተባለች ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ ካምፕ መጣ። ወደዚህ ካምፕ የመጣው ለ25 ዓመት ከባድ የጉልበት ሥራ እንዲሠራ ተፈርዶበት ነው።

እኔ፣ እናቴና ግሪጎሪ በቱሉን አቅራቢያ በሚገኙ የሰፈራ መንደሮች እንሰብክ የነበረ ቢሆንም ዘዴኛ መሆን ያስፈልገን ነበር። ለምሳሌ “እዚህ አካባቢ ላም የሚሸጥ ሰው አለ?” ብለን እንጠይቅ ነበር። ላም የሚሸጥ ሰው ስናገኝ ላሞች እንዴት አስገራሚ በሆነ መንገድ እንደተፈጠሩ እንነግረዋለን። ከዚያም ጨዋታውን ወዲያው እንቀይረውና ለግለሰቡ ስለ ፈጣሪ እንነግረዋለን። በወቅቱ አንድ ጋዜጣ የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን ስለ ላም እንደሚጠይቁ ዘግቦ ነበር፤ እርግጥ እኛ የምንፈልገው በጎችን ነበር! ደግሞም በግ መሰል ሰዎችን አግኝተናል! ርቆ በሚገኘው በዚህ ክልል ውስጥ ለሚኖሩ ትሑትና እንግዳ ተቀባይ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማስጠናት በጣም አስደሳች ነበር። በአሁኑ ጊዜ በቱሉን ከ100 በላይ አስፋፊዎች ያሉት ጉባኤ ይገኛል።

የማሪያን እምነት የሚፈትን ሁኔታ

ባለቤቴ ማሪያ እውነትን የሰማችው ዩክሬን ውስጥ ሲሆን በወቅቱ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየተካሄደ ነበር። የ18 ዓመት ልጅ ሳለች አንድ የኬጂቢ አዛዥ ያስቸግራት ነበር፤ ይህ ሰው ከእሱ ጋር የፆታ ብልግና እንድትፈጽም ሊያስገድዳት ቢሞክርም እሷ ግን ፈቃደኛ አለመሆኗን በቁርጠኝነት ገልጻለት ነበር። አንድ ቀን ቤቷ ስትመለስ ይህን ሰው አልጋዋ ላይ ተኝቶ አገኘችው። በዚህ ጊዜ ማሪያ ሸሽታ አመለጠች። በዚህ የተበሳጨው የኬጂቢ አዛዥ የይሖዋ ምሥክር በመሆኗ እንደሚያሳስራት ዛተባት፤ እንዳለውም በ1952 አሥር ዓመት ተፈርዶባት እስር ቤት ገባች። ማሪያ፣ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቁ ለእስር እንደተዳረገው እንደ ዮሴፍ እንደሆነች ተሰምቷት ነበር። (ዘፍ. 39:12, 20) ማሪያን ከፍርድ ቤት ወደ እስር ቤት ይዟት የሄደው ሾፌር “አይዞሽ፣ አትፍሪ። ብዙ ሰዎች እስር ቤት ቢገቡም ክብራቸውን እንደጠበቁ ይወጣሉ” አላት። ይህ ሰው የተናገረው ሐሳብ ማሪያን በጣም አበረታታት።

ከ1952 እስከ 1956 ባለው ጊዜ ውስጥ ማሪያ በሩሲያ ውስጥ በምትገኝ ጎርኪ (የአሁኗ ኒዝህኒ ኖቭገረድ) የተባለች ከተማ አቅራቢያ ባለ አንድ የጉልበት ሥራ ካምፕ ውስጥ እንድትሠራ ተመደበች። በጣም ቀዝቃዛ በሆነ አየርም እንኳ ዛፍ እንድትቆርጥ ያዟት ነበር። በዚህ ምክንያት ጤናዋ ተቃውሶ ነበር። ይሁንና በ1956 ከእስር ተለቃ ወደ ቱሉን ሄደች።

ከባለቤቴና ከልጆቼ ርቆ መኖር

በቱሉን ያለ አንድ ወንድም፣ አንዲት እህት ወደ ቱሉን እየመጣች እንደሆነ ሲነገረኝ እህትን ልቀበላትና ሻንጣዎቿን በመሸከም ላግዛት በብስክሌት ወደ አውቶቡስ ተራው ሄድኩ። ማሪያን ልክ እንዳየኋት ወደድኳት። ልቧን ለመማረክ ብዙ ጥረት ማድረግ ቢጠይቅብኝም በመጨረሻ ተሳካልኝ። ከዚያም በ1957 ከማሪያ ጋር ተጋባን። ከአንድ ዓመት በኋላ ልጃችን ኢሪና ተወለደች። ሆኖም ገና አይቼ ሳልጠግባት ከእሷ ተነጠልኩ። በ1959 መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ሳትም በመገኘቴ እስር ቤት ገባሁ። ለስድስት ወራት ያህል ከሰው ተነጥዬ ታሰርኩ። በዚያን ወቅት አዘውትሬ መጸለዬ፣ የመንግሥቱን መዝሙሮች መዘመሬ እንዲሁም ከእስር ቤት ከወጣሁ በኋላ እንዴት እንደምሰብክ በዓይነ ሕሊናዬ ለመሳል መሞከሬ ውስጣዊ ሰላሜን ጠብቄ ለመቀጠል ረድቶኛል።

በ1962 በጉልበት ሥራ ካምፕ ውስጥ ሳለሁ

በእስር ቤት ውስጥ፣ ምርመራ ላይ በነበርኩበት ወቅት መርማሪው “እናንተን እንደ አይጥ እንጨፈልቃችኋለን!” በማለት ጮኸብኝ። እኔም “ኢየሱስ ይህ የመንግሥቱ ምሥራች በመላው ምድር ይሰበካል ሲል ተናግሯል፤ ይህን ደግሞ ማንም ሊያስቆመው አይችልም” በማለት መለስኩለት። ከዚያም መርማሪው ዘዴውን በመቀየር መግቢያው ላይ እንደተናገርኩት እምነቴን እንድክድ ሊያሳምነኝ ይሞክር ጀመር። ሆኖም የመርማሪው ማስፈራሪያም ሆነ ማባበያ እምነቴን እንድክድ ሊያደርገኝ አልቻለም፤ በመሆኑም ሳራንስክ ተብላ በምትጠራ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ የጉልበት ሥራ ካምፕ ውስጥ ለሰባት ዓመት እንድሠራ ተፈረደብኝ። ወደ ካምፑ እየወሰዱኝ ሳለ ሁለተኛዋ ልጃችን ኦልጋ እንደተወለደች ሰማሁ። ከባለቤቴና ከልጆቼ ርቄ ያለሁ ቢሆንም እኔና ማሪያ ለይሖዋ ታማኝ ሆነን መጽናታችንን ማሰቤ አጽናንቶኛል።

በ1965 ማሪያ፣ ከሴት ልጆቻችን ከኦልጋና ከኢሪና ጋር

ከቱሉን እስከ ሳራንስክ የደርሶ መልስ ጉዞ ለማድረግ በባቡር 12 ቀን የሚፈጅ ቢሆንም ማሪያ በዓመት አንድ ጊዜ እየመጣች ትጠይቀኝ ነበር። በየዓመቱ አዲስ ቡትስ ጫማ ይዛልኝ ትመጣ ነበር። በቡትሱ ሶል ውስጥ አዲስ የወጡ የመጠበቂያ ግንብ እትሞችን ደብቃ ታመጣልኝ ነበር። ማሪያ ሁለቱን ሴት ልጆቻችንን ይዛ ልትጠይቀኝ የመጣችበትን ዓመት ፈጽሞ አልረሳውም። እነሱን ማየትና አብሬያቸው መሆን በመቻሌ ምን ያህል እንደተደሰትኩ ልትገምቱ ትችላላችሁ!

አዲስ አካባቢና አዳዲስ ተፈታታኝ ሁኔታዎች

በ1966 ከጉልበት ሥራ ካምፑ ተለቀቅኩ፤ ከዚያም አራታችንም በጥቁር ባሕር አቅራቢያ ወደምትገኝ አርመቪር ተብላ ወደምትጠራ ከተማ ተዛወርን። በዚያም ወንዶች ልጆቻችን ያረስላቭና ፓቬል ተወለዱ።

ብዙም ሳይቆይ የኬጂቢ አዛዦች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማግኘት ቤታችንን ይፈትሹ ጀመር። እነዚህን ጽሑፎች ለማግኘት የማይፈትሹበት ቦታ አልነበረም፤ ሌላው ቀርቶ የከብቶቹ ገፈራ ውስጥ ሳይቀር ይፈትሹ ነበር። በአንድ ወቅት ቤታችንን እየፈተሹ የነበሩት ፖሊሶች ከሙቀቱ የተነሳ ላብ በላብ ሆነው ነበር፤ ልብሳቸውም በአቧራ ተሸፍኖ ነበር። ማሪያ እነዚህ ሰዎች እያደረጉ ያሉት የበላዮቻቸው ያዘዟቸውን እንደሆነ በማሰብ አዘነችላቸው። በመሆኑም የፍራፍሬ ጭማቂ የሰጠቻቸው ከመሆኑም ሌላ አቧራቸውን የሚያራግፉበት ብሩሽ፣ ውኃና ፎጣ ሰጠቻቸው። በኋላ ላይ የኬጂቢ ዋና አዛዡ ሲመጣ ፖሊሶቹ ስለተደረገላቸው ደግነት ነገሩት። ሲሄዱም ዋና አዛዡ ፈገግ ብሎ ተሰናበተን። “ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ” የሚለውን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ማድረጋችን የሚያስገኘውን ጥሩ ውጤት በመመልከታችን ተደሰትን።—ሮም 12:21

በአርመቪር ሳለን ፖሊሶች ድንገት እየመጡ ቤታችንን ይፈትሹ የነበረ ቢሆንም መስበካችንን አልተውንም። በተጨማሪም በአቅራቢያችን ባለች ኩርጋኒንስክ ተብላ በምትጠራ ከተማ ውስጥ ያሉትን ጥቂት አስፋፊዎች እንረዳ ነበር። በአሁኑ ጊዜ በአርመቪር ስድስት ጉባኤዎች፣ በኩርጋኒንስክ ደግሞ አራት ጉባኤዎች እንዳሉ ማወቄ በጣም ያስደስተኛል።

ባለፉት ዓመታት ውስጥ መንፈሳዊነታችን የተዳከመባቸው ጊዜያት እንደነበሩ አይካድም። ይሁንና ይሖዋ በታማኝ ወንድሞች አማካኝነት ማስተካከያ እንድናደርግና በመንፈሳዊ እንድንጠናከር ስለረዳን በጣም አመስጋኞች ነን። (መዝ. 130:3) እኛ ሳናውቀው ወደ ጉባኤው ሰርገው ከገቡ የኬጂቢ ሰላዮች ጋር አብሮ ማገልገልም ከባድ ፈተና ነበር። እነዚህ ሰላዮች ቀናተኛ ወንድሞች የሚመስሉ ከመሆኑም ሌላ በአገልግሎት ንቁ ተሳትፎ ያደርጉ ነበር። እንዲያውም አንዳንዶቹ በድርጅቱ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ እስከማግኘት ደርሰው ነበር። ውሎ አድሮ ግን ትክክለኛ ማንነታቸውን አወቅን።

ማሪያ በ1978፣ በ45 ዓመቷ ድጋሚ አረገዘች። ከባድ የልብ ሕመም ስለነበረባት ዶክተሮቹ እርግዝናው ለሕይወቷ እንደሚያሰጋት ፈርተው ነበር፤ ስለዚህ ፅንሱን እንድታስወርድ ሊያሳምኗት ሞክሩ። ማሪያ ግን ፈቃደኛ አልሆነችም። በመሆኑም አንዳንድ ዶክተሮች ማሪያን ያለጊዜዋ እንድትወልድ የሚያደርግ መድኃኒት ለመውጋት ስሪንጅ ይዘው ሆስፒታል ውስጥ በሄደችበት ሁሉ ይከተሏት ነበር። በመሆኑም ማሪያ ፅንሱን ለማዳን ስትል ከሆስፒታሉ አምልጣ ወጣች።

የኬጂቢ ባለሥልጣናት ከተማውን ለቅቀን እንድንወጣ አዘዙን። በመሆኑም በኢስቶኒያ (በወቅቱ የሶቪየት ኅብረት ክፍል ነበረች) ውስጥ በምትገኝ ታሊን ተብላ የምትጠራ ከተማ አቅራቢያ ወዳለች መንደር ተዛወርን። ማሪያ በታሊን፣ ወንድ ልጃችንን ቪታሊን ወለደች፤ ዶክተሮቹ የፈሩት ነገር ሳይከሰት በሰላም ተገላገለች።

ከጊዜ በኋላ ኢስቶኒያን ለቅቀን በደቡባዊ ሩሲያ ወደሚገኝ ኔዝሎብነየ ተብሎ ወደሚጠራ የሰፈራ መንደር ተዛወርን። ዘና ለማለት የሚፈልጉ ሰዎች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚመጡባቸው በዚህ መንደር አቅራቢያ ባሉ ከተሞች ውስጥ በዘዴ እንሰብክ ነበር። አንዳንዶች ወደዚህ የሚመጡት ከጤና ችግር ጋር በተያያዘ ቢሆንም የዘላለም ሕይወት ተስፋ ይዘው ይመለሳሉ!

ልጆቻችን ይሖዋን እንዲወዱ መርዳት

ልጆቻችን ለይሖዋ ፍቅር እንዲያድርባቸውና እሱን የማገልገል ፍላጎት እንዲኖራቸው ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት አድርገናል። በልጆቻችን ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ወንድሞችን ብዙ ጊዜ ቤታችን እንጋብዝ ነበር፤ ከ1970 እስከ 1995 በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ያገለገለው ወንድሜ ግሪጎሪም በተደጋጋሚ ቤታችን ያርፍ ነበር። ደስተኛና ተጫዋች ስለሆነ እሱ ሲመጣ ቤተሰባችን በጣም ይደሰታል። ቤታችን እንግዳ ሲመጣ በአብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ጨዋታዎችን እንጫወታለን፤ ይህም ልጆቻችን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን እንዲወዱ ረድቷቸዋል።

ወንዶች ልጆቻችን ከሚስቶቻቸው ጋር

ከግራ ወደ ቀኝ፣ ከኋላ፦ ያሮስላቭ፣ ፓቬል ጁኒየር፣ ቪታሊ

ከፊት፦ አልዮና፣ ራያ፣ ስቬትላና

በ1987 ልጃችን ያሮስላቭ፣ ሪጋ ወደተባለች የላትቪያ ከተማ ሄደ፤ በዚህች ከተማ ይበልጥ በነፃነት ማገልገል ችሎ ነበር። ይሁንና የውትድርና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል እንዲታሰር የተፈረደበት ሲሆን በዘጠኝ የተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ ታስሯል። በእስር ቤት ስላሳለፍኩት ሕይወት የነገርኩት ተሞክሮ እንዲጸና ረድቶታል። በኋላም አቅኚ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። በ1990 ልጃችን ፓቬል (በወቅቱ የ19 ዓመት ልጅ ነበር) ከጃፓን በስተ ሰሜን በምትገኝ ሳክኸሊን የተባለች ደሴት ውስጥ በአቅኚነት ማገልገል እንደሚፈልግ ነገረን። መጀመሪያ ላይ እንዲሄድ አልፈለግንም ነበር። በዚህች ደሴት ላይ የነበሩት አስፋፊዎች ብዛት 20 ብቻ ነበር፤ በዚያ ላይ ደግሞ ይቺ ደሴት የምትገኘው እኛ ካለንበት አካባቢ ከ9,000 ኪሎ ሜትር በላይ ርቃ ነው። በኋላ ላይ ግን በሐሳቡ ተስማማን፤ ደግሞም ጥሩ ውሳኔ ነበር። በዚያ ያሉት ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ ይሰጡ ነበር። በጥቂት ዓመታት ውስጥ ስምንት ጉባኤዎች ተቋቋሙ። ፓቬል እስከ 1995 ድረስ በሳክኸሊን አገልግሏል። በዚያን ወቅት ከልጆቻችን መካከል ቤት ውስጥ የቀረው የመጨረሻው ልጃችን ቪታሊ ብቻ ነበር። ቪታሊ ከልጅነቱ ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ይወድ ነበር። በ14 ዓመቱ አቅኚ ሆኖ ማገልገል የጀመረ ሲሆን እኔም ለሁለት ዓመት ያህል በአቅኚነት አብሬው አገልግያለሁ። በጣም አስደሳች ጊዜ አሳልፈናል። ቪታሊ 19 ዓመት ሲሆነው በልዩ አቅኚነት ለማገልገል ወደ ሌላ አካባቢ ሄደ።

በ1952 አንድ የኬጂቢ አዛዥ ማሪያን “እምነትሽን ካጂ፤ አለዚያ አሥር ዓመት ትታሰሪያለሽ። ከእስር ቤት የምትወጪው አርጅተሽ ነው፤ ደግሞም ዞር ብሎ የሚያይሽ አይኖርም” ብሏት ነበር። እውነታው ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነበር። ታማኙ አምላካችን ይሖዋ፣ ልጆቻችን እንዲሁም እውነትን እንዲያውቁ የረዳናቸው በርካታ ሰዎች ለእኛ ያላቸውን ፍቅር ማየት ችለናል። እኔና ማሪያ ልጆቻችን ያገለገሉባቸውን አካባቢዎች የመጎብኘት አጋጣሚ አግኝተን ነበር። ልጆቻችን ይሖዋን እንዲያውቁ የረዷቸው ሰዎች ልጆቻችን ላደረጉላቸው ነገር ምን ያህል አመስጋኞች እንደሆኑ ማየት ችለናል።

ይሖዋ ላሳየን ጥሩነት አመስጋኞች ነን

በ1991 የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ሕጋዊ እውቅና አገኘ። ይህ ውሳኔ የስብከቱን ሥራ ይበልጥ በቅንዓት እንድናከናውን አነሳስቶናል። እንዲያውም ጉባኤያችን በአቅራቢያችን ወዳሉ ከተሞችና መንደሮች ሄደን መስበክ እንድንችል አንድ አውቶቡስ ገዝቶ ነበር።

በ2011 ከባለቤቴ ጋር

ያሮስላቭና ባለቤቱ አልዮና እንዲሁም ፓቬልና ባለቤቱ ራያ በቤቴል እያገለገሉ ሲሆን ቪታሊና ባለቤቱ ስቬትላና ደግሞ በወረዳ ሥራ ላይ ይገኛሉ፤ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ። የመጀመሪያዋ ልጃችን ኢሪናና ቤተሰቧ የሚኖሩት ጀርመን ውስጥ ነው። ባለቤቷ ቭላዲሚርና ሦስት ወንዶች ልጆቻቸው የጉባኤ ሽማግሌ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው። ልጃችን ኦልጋ የምትኖረው በኢስቶኒያ ሲሆን አዘውትራ ትደውልልኛለች። የሚያሳዝነው ውዷ ባለቤቴ ማሪያ በ2014 አረፈች። እሷን በትንሣኤ ለማግኘት በጣም እጓጓለሁ! በአሁኑ ጊዜ የምኖረው ቤልጎረድ በተባለች ከተማ ውስጥ ሲሆን እዚህ ያሉት ወንድሞች ትልቅ ድጋፍ እያደረጉልኝ ነው።

በይሖዋ አገልግሎት ካሳለፍኳቸው ዓመታት፣ ንጹሕ አቋምን መጠበቅ ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም ይሖዋ በምላሹ የሚሰጠው ውስጣዊ ሰላም ግን በዋጋ ሊተመን የማይችል እንደሆነ ተምሬአለሁ። እኔና ማሪያ ከአቋማችን ፍንክች ሳንል በመጽናታችን ያገኘነው በረከት ፈጽሞ ልገምተው ከምችለው በላይ ነው። በ1991 ሶቪየት ኅብረት ከመፈራረሱ በፊት በዚያ የነበሩት አስፋፊዎች ቁጥር ከ40,000 ብዙም የማይበልጥ ነበር። በዛሬው ጊዜ ግን በአንድ ወቅት የሶቪየት ኅብረት ክፍል በነበሩት አገሮች ውስጥ ከ400,000 በላይ አስፋፊዎች አሉ! አሁን ዕድሜዬ 83 ዓመት ሲሆን በጉባኤ ሽማግሌነት ማገልገሌን ቀጥያለሁ። ይሖዋ ምንጊዜም የሚያስፈልገኝን ጥንካሬ በመስጠት እንድንጸና ረድቶኛል። በእርግጥም ይሖዋ በእጅጉ ክሶኛል።—መዝ. 13:5, 6

^ አን.4 ኬጂቢ የሚለው የሩሲያኛ ምህጻረ ቃል ለሶቪየት ኅብረት የደህንነት ኮሚቴ የተሰጠ መጠሪያ ነው።