በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆች—“ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ” እንዲያገኙ ልጆቻችሁን እርዷቸው

ወላጆች—“ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ” እንዲያገኙ ልጆቻችሁን እርዷቸው

“ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ እንድታገኝ የሚያስችሉህን ቅዱሳን መጻሕፍት ከጨቅላነትህ ጀምሮ አውቀሃል።”—2 ጢሞ. 3:15

መዝሙሮች፦ 141, 134

1, 2. ልጆች ራሳቸውን መወሰንና መጠመቅ እንደሚፈልጉ ሲገልጹ አንዳንድ ወላጆች ስጋት የሚያድርባቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለይሖዋ ራሳቸውን ወስነው ይጠመቃሉ። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ በእውነት ቤት ያደጉና ከሁሉ በተሻለው የሕይወት ጎዳና ላይ ለመጓዝ የመረጡ ወጣቶች ናቸው። (መዝ. 1:1-3) ክርስቲያን ወላጆች ከሆናችሁ እናንተም ልጆቻችሁ የሚጠመቁበትን ቀን በጉጉት እንደምትጠባበቁ ጥርጥር የለውም።—ከ3 ዮሐንስ 4 ጋር አወዳድር።

2 ያም ሆኖ የሚያሳስባችሁ ነገር ይኖር ይሆናል። ምናልባትም በወጣትነታቸው የተጠመቁ አንዳንዶች ከጊዜ በኋላ፣ ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖር የጥበብ አካሄድ ስለመሆኑ ጥርጣሬ እንዳደረባቸው አስተውላችሁ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም የተወሰኑት እውነትን ትተው ወጥተዋል። በመሆኑም ልጃችሁ በክርስትና ጎዳና ላይ መጓዝ ከጀመረ በኋላ አመለካከቱን እንዳይቀይርና ለእውነት የነበረውን የመጀመሪያ ፍቅር እንዳይተው ስጋት ሊያድርባችሁ ይችላል። ልጃችሁ በአንደኛው መቶ ዘመን በኤፌሶን ጉባኤ እንደነበሩትና ኢየሱስ ‘መጀመሪያ ላይ የነበራችሁን ፍቅር ትታችኋል’ እንዳላቸው ክርስቲያኖች ዓይነት አካሄድ እንዳይከተል ትፈሩ ይሆናል። (ራእይ 2:4) ታዲያ እንዲህ ዓይነት ነገር እንዳይከሰት ለመከላከል ብሎም ልጃችሁ “ወደ መዳን ማደግ” እንዲችል ለመርዳት ምን ማድረግ ይኖርባችኋል? (1 ጴጥ. 2:2) መልሱን ለማግኘት እስቲ የጢሞቴዎስን ምሳሌ እንመልከት።

‘ቅዱሳን መጻሕፍትን ማወቅ’

3. (ሀ) ጢሞቴዎስ ወደ ክርስትና የመጣው እንዴት ነው? ለተማራቸው ትምህርቶችስ ምን ምላሽ ሰጥቷል? (ለ) ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ትምህርት ከመቅሰም ጋር በተያያዘ የትኞቹን ሦስት ነጥቦች ጠቅሷል?

3 ጢሞቴዎስ ስለ ክርስትና የተማረው በ47 ዓ.ም. ሐዋርያው ጳውሎስ ልስጥራን ለመጀመሪያ ጊዜ በጎበኘበት ወቅት ሊሆን ይችላል። በወቅቱ ጢሞቴዎስ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም፤ ያም ቢሆን የተማረውን በተግባር ለማዋል ጥረት አድርጓል። በመሆኑም ከሁለት ዓመት በኋላ የጳውሎስ የጉዞ ጓደኛ መሆን ችሏል። ይህ ከሆነ ከ16 ዓመታት በኋላ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንዲህ ሲል ጽፎለታል፦ “በተማርካቸውና አምነህ በተቀበልካቸው ነገሮች ጸንተህ ኑር፤ ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች እነማን እንዳስተማሩህ ታውቃለህ፤ እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ እንድታገኝ የሚያስችሉህን ቅዱሳን መጻሕፍት [የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት] ከጨቅላነትህ ጀምሮ አውቀሃል።” (2 ጢሞ. 3:14, 15) ጳውሎስ (1) ቅዱሳን መጻሕፍትን ስለማወቅ፣ (2) የተማሩትን ነገር አምኖ ስለመቀበል እንዲሁም (3) በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ ስለማግኘት እንደተናገረ ልብ ማለት ያስፈልጋል።

4. ልጆቻችሁን ለማስተማር ውጤታማ ሆነው ያገኛችኋቸው መሣሪያዎች የትኞቹ ናቸው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

4 ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ እንዲያውቁ እንደምትፈልጉ ጥርጥር የለውም። (ቅዱሳን መጻሕፍት የሚለው አገላለጽ በዛሬው ጊዜ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትንና የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ያጠቃልላል።) ትናንሽ ልጆችም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱት ሰዎችና ክንውኖች መሠረታዊ የሆነ እውቀት መቅሰም ይችላሉ። የይሖዋ ድርጅት፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር ሊጠቀሙባቸው የሚችሉ የተለያዩ መሣሪያዎችን አዘጋጅቷል። ከእነዚህ መካከል በቋንቋችሁ የሚገኙትን መጥቀስ ትችላላችሁ? ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ዝምድና ለመመሥረት ቁልፉ የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት እንደሆነ አስታውሱ።

‘አምኖ መቀበል’

5. (ሀ) ‘አምኖ መቀበል’ ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) ጢሞቴዎስ ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ምሥራች አምኖ እንደተቀበለ እንዴት እናውቃለን?

5 የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት አስፈላጊ እንደሆነ ጥያቄ የለውም። ይሁንና ለልጆች መንፈሳዊ ነገሮችን ማስተማር ሲባል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱ ግለሰቦችና ክንውኖች እንዲያውቁ ከመርዳት ያለፈ ነገር ማድረግን ይጨምራል። ጢሞቴዎስ የተማራቸውን ነገሮች ‘አምኖ መቀበል’ እንዳስፈለገው እናስታውስ። ‘አምኖ መቀበል’ የሚለው ሐረግ በግሪክኛ “አንድ ነገር እውነት መሆኑን ተረድቶ ማመንና እርግጠኛ መሆን” የሚል ትርጉም አለው። ጢሞቴዎስ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ከጨቅላነቱ ጀምሮ ያውቅ ነበር። መሲሑ፣ ኢየሱስ መሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ሲያገኝ ደግሞ ይህን አምኖ ተቀበለ። በሌላ አባባል፣ እውቀት በማካበት ብቻ ሳይወሰን የተማረው ነገር ትክክል ስለመሆኑ እርግጠኛ ሆኖ ነበር። እንዲያውም ጢሞቴዎስ ስለ ምሥራቹ የተማረውን ነገር አሳማኝ ሆኖ ስላገኘው፣ ለመጠመቅ ከዚያም ከጳውሎስ ጋር በሚስዮናዊነት ለማገልገል ተነሳስቷል።

6. ልጆቻችሁ ከአምላክ ቃል የተማሩትን ነገር አምነው እንዲቀበሉ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

6 እናንተስ ልጆቻችሁ የተማሩትን ነገር ልክ እንደ ጢሞቴዎስ አምነው እንዲቀበሉ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ታጋሽ መሆን ያስፈልጋችኋል። አንድን ነገር ተረድቶ ለማመን ጊዜ ይወስዳል፤ በሌላ በኩል ደግሞ እናንተ አንድን ነገር አምናችሁ ስለተቀበላችሁት ብቻ ልጆቻችሁም ያምኑበታል ማለት አይደለም። እያንዳንዱ ልጅ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አምኖ ለመቀበል ‘የማሰብ ችሎታውን’ መጠቀም አለበት። (ሮም 12:1ን አንብብ።) ልጆች ይህን እንዲያደርጉ በመርዳት ረገድ ወላጆች ቁልፍ ሚና ይኖራችኋል፤ በተለይ ደግሞ ጥያቄዎች በሚጠይቋችሁ ወቅት ይህን ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ታገኛላችሁ። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።

7, 8. (ሀ) አንድ ክርስቲያን አባት ልጁን ሲያስተምር ትዕግሥት የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ወላጆች ልጆቻችሁን ስታስተምሩ ትዕግሥት ማሳየት አስፈላጊ እንደሆነ የሚሰማችሁ ለምንድን ነው?

7 የ11 ዓመት ሴት ልጅ ያለችው ቶማስ የተባለ አባት እንዲህ ብሏል፦ “ልጄ አንዳንድ ጊዜ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ታነሳለች፦ ‘ይሖዋ በምድር ላይ ሕይወት እንዲኖር ለማድረግ በዝግመተ ለውጥ ተጠቅሞ ቢሆንስ?’ አሊያም ደግሞ ‘ሁኔታዎችን ለማሻሻል ስንል ማኅበረሰቡን በሚጠቅሙ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፎ የማናደርገው፣ ለምሳሌ በምርጫ የማንካፈለው ለምንድን ነው?’ በዚህ ወቅት፣ እኔ ያመንኩበትን ነገር አምና እንድትቀበል ጫና እንዳላደርግባት መጠንቀቅ ያስፈልገኛል። ደግሞም አንድን እውነታ ማወቅ ብቻ አንድን ነገር አምኖ ለመቀበል ያስችላል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የተለያዩ ማስረጃዎችን መመርመር ያስፈልጋል።”

8 ቶማስ እንደተገነዘበው ልጆችን ማስተማር ትዕግሥት ይጠይቃል። በመሠረቱ ሁሉም ክርስቲያኖች ትዕግሥት ማሳየት ያስፈልጋቸዋል። (ቆላ. 3:12) ቶማስ፣ ልጁ አንድን ትምህርት አምና እንድትቀበል ለመርዳት በተለያዩ ጊዜያት መወያየት ሊያስፈልግ እንደሚችል ተገንዝቧል። በተጨማሪም ቅዱሳን መጻሕፍትን በመጠቀም ልጁን ሊያስረዳት እንደሚገባ አስተውሏል። ቶማስ እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ በተለይ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ትምህርቶች ጋር በተያያዘ ‘ልጃችን የምትማረውን ነገር በእርግጥ ታምንበታለች? ምክንያታዊ እንደሆነስ ይሰማታል?’ የሚለውን ነገር ማወቅ እንፈልጋለን። ጥያቄዎች ካሏት ደስ ይለናል። እውነቱን ለመናገር፣ ልጃችን ምንም ጥያቄ ሳታነሳ አንድን ሐሳብ ዝም ብላ ከተቀበለች ያሳስበኛል።”

9. የአምላክን ቃል በልጆቻችሁ ውስጥ መቅረጽ የምትችሉት እንዴት ነው?

9 ወላጆች፣ ልጆቻቸውን በትዕግሥት የሚያስተምሯቸው ከሆነ ልጆቹ የእውነት ‘ስፋት፣ ርዝመት፣ ከፍታና ጥልቀት ምን ያህል እንደሆነ’ ቀስ በቀስ ማስተዋል ይጀምራሉ። (ኤፌ. 3:18) ዕድሜያቸውንና የመረዳት ችሎታቸውን ባገናዘበ መልኩ ማስተማር ይኖርባችኋል። ልጆቻችሁ የሚማሩትን ነገር እያመኑበት ሲመጡ፣ አብረዋቸው ለሚማሩ ልጆችም ሆነ ለሌሎች ስለ እምነታቸው ማስረዳት ቀላል ይሆንላቸዋል። (1 ጴጥ. 3:15) ለምሳሌ ልጆቻችሁ መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን በተመለከተ ምን ብሎ እንደሚያስተምር ማስረዳት ይችላሉ? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ማብራሪያ አሳማኝ እንደሆነ ይሰማቸዋል? * እርግጥ ነው፣ የአምላክን ቃል በልጆቻችሁ ውስጥ መቅረጽ ትዕግሥት ይጠይቃል፤ ይሁንና የምታደርጉት ጥረት ፈጽሞ የሚያስቆጭ አይሆንም።—ዘዳ. 6:6, 7

10. ልጆቻችሁን በማስተማር ረገድ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ምንድን ነው?

10 እርግጥ ነው፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አምኖ በመቀበል ረገድ እናንተ ራሳችሁ ለልጆቻችሁ ምሳሌ መሆናችሁ በጣም አስፈላጊ ነው። የሦስት ሴቶች ልጆች እናት የሆነችው ስቴፋኒ እንዲህ ብላለች፦ “ልጆቼ ገና ሕፃናት ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ ራሴን እንዲህ እያልኩ እጠይቅ ነበር፦ ‘ይሖዋ መኖሩን፣ አፍቃሪ መሆኑን እንዲሁም መንገዶቹ ትክክል መሆናቸውን እኔ ራሴ አምኜ የተቀበልኩት ለምን እንደሆነ ለልጆቼ እነግራቸዋለሁ? እኔ ይሖዋን ከልቤ እንደምወደው ልጆቼ በግልፅ መመልከት ይችላሉ?’ እኔ ራሴ አምኜ ያልተቀበልኩትን ነገር ልጆቼ እንዲያምኑበት መጠበቅ አልችልም።”

“ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ” ማግኘት

11, 12. ጥበብ ምንድን ነው? የአንድ ሰው መንፈሳዊ ጉልምስና በዋነኝነት የሚለካው በዕድሜው አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

11 ጢሞቴዎስ (1) የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት እንደነበረው እና (2) የተማራቸውን ነገሮች አምኖ እንደተቀበለ ተመልክተናል። ይሁን እንጂ ጢሞቴዎስ “ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ” እንዲያገኝ ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚረዱት ጳውሎስ ገልጿል፤ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር?

12 ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 “ጥበብ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዴት እንደተሠራበት ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “እውቀትንና ማስተዋልን ተጠቅሞ ችግሮችን የመፍታት፣ ራስን ከአደጋ የመጠበቅ፣ ግብ ላይ የመድረስ ወይም ሌሎች ይህን እንዲያደርጉ ምክር የመስጠት ችሎታ ነው። ጥበብ የሞኝነት ተቃራኒ ነው።” መጽሐፍ ቅዱስ “ሞኝነት በልጅ ልብ ውስጥ ታስሯል” ይላል። (ምሳሌ 22:15) ከዚህ አንጻር፣ የሞኝነት ተቃራኒ የሆነው ጥበብ የጉልምስና መገለጫ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ነው ማለት ይቻላል። የአንድ ሰው መንፈሳዊ ጉልምስና በዋነኝነት የሚለካው በዕድሜው ሳይሆን ለይሖዋ ባለው ጤናማ ፍርሃት እንዲሁም ትእዛዞቹን ለማክበር ምንጊዜም ዝግጁ በመሆኑ ነው።—መዝሙር 111:10ን አንብብ።

13. ወጣቶች ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ እንዳላቸው ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

13 በመንፈሳዊ ጎልማሳ ለመሆን የሚጥሩ ወጣቶች ‘በማዕበል የሚነዱ ይመስል’ በራሳቸው ምኞት አሊያም በእኩዮቻቸው ተጽዕኖ ተሸንፈው ‘ወዲያና ወዲህ አይሉም።’ (ኤፌ. 4:14) ከዚህ ይልቅ “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት” ለማሠልጠን ጥረት ያደርጋሉ። (ዕብ. 5:14) እነዚህ ወጣቶች፣ ወላጆቻቸው ወይም ሌሎች ትላልቅ ሰዎች በማያዩአቸው ጊዜም እንኳ ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ውሳኔዎች ያደርጋሉ፤ ይህም ወደ ጉልምስና እያደጉ መሆናቸውን ያሳያል። (ፊልጵ. 2:12) መዳን ለማግኘት እንዲህ ዓይነቱ ጥበብ አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 24:14ን አንብብ።) ታዲያ ልጆቻችሁ እንዲህ ዓይነት ጥበብ እንዲያገኙ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ልጆቻችሁ የምትመሩባቸውን መሥፈርቶች በግልጽ እንዲያውቁ አድርጉ። ሕይወታችሁን የምትመሩት በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙት መሥፈርቶች መሠረት እንደሆነ በንግግራችሁም ሆነ በድርጊታችሁ አሳዩ።—ሮም 2:21-23

ወላጆች የማያቋርጥ ጥረት ማድረጋቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?(ከአንቀጽ 14-18⁠ን ተመልከት)

14, 15. (ሀ) ለመጠመቅ የሚፈልግ አንድ ልጅ የትኞቹን ጉዳዮች በቁም ነገር ሊያስብባቸው ይገባል? (ለ) ልጆቻችሁ የአምላክን ሕጎች መታዘዝ ስለሚያስገኛቸው በረከቶች በጥሞና እንዲያስቡ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው?

14 ይሁን እንጂ ልጆቻችሁ ጥበብ እንዲያዳብሩ ለመርዳት፣ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለእነሱ መናገራችሁ ብቻ በቂ አይደለም። ልጆቻችሁ እንደሚከተሉት ባሉ ጥያቄዎች ላይ ቆም ብለው እንዲያስቡ ማድረጋችሁ ተገቢ ነው፦ ‘መጽሐፍ ቅዱስ፣ ማራኪ የሚመስሉ አንዳንድ ነገሮችን እንዳናደርግ የሚከለክለው ለምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ምንጊዜም እንደሚጠቅሙኝ የሚያሳምነኝ ምንድን ነው?’—ኢሳ. 48:17, 18

15 ልጃችሁ የመጠመቅ ፍላጎት ካለው በቁም ነገር እንዲያስብበት ልትረዱት የሚገባ ሌላም ጉዳይ አለ፤ ይህም ‘ክርስቲያን መሆን ስለሚያስከትላቸው ኃላፊነቶች ምን አመለካከት አለኝ?’ የሚለው ነው። ክርስቲያን መሆን ምን ጥቅሞች አሉት? ምን መሥዋዕቶችንስ ያስከፍላል? ልጃችሁ የሚያገኘው ጥቅም ከሚከፍለው መሥዋዕት እንደሚልቅ የሚሰማው ለምንድን ነው? (ማር. 10:29, 30) አንድ ሰው ከተጠመቀ በኋላ በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ እንዲያስብ የሚያደርጉ ነገሮች በሕይወቱ ውስጥ ያጋጥሙታል። በመሆኑም ይህን ትልቅ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት እነዚህን ጉዳዮች ሊያጤናቸው ይገባል። ልጆቻችሁ፣ መታዘዝ የሚያስገኛቸውን በረከቶች እንዲሁም አለመታዘዝ የሚያስከትላቸውን ውጤቶች እንዲያመዛዝኑ እርዷቸው፤ ይህን ካደረጋችሁ የመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ምንጊዜም እንደሚጠቅሟቸው በግለሰብ ደረጃ አምነው መቀበል ቀላል ይሆንላቸዋል።—ዘዳ. 30:19, 20

አንድ የተጠመቀ ወጣት ያመነበትን ነገር ቢጠራጠር

16. አንድ የተጠመቀ ልጅ ያመነበትን ነገር መጠራጠር ቢጀምር ወላጆች ሊገነዘቡት የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

16 በሌላ በኩል ደግሞ ልጃችሁ ከተጠመቀ በኋላ ያመነበትን ነገር ውሎ አድሮ መጠራጠር ቢጀምርስ? ለምሳሌ ያህል፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ የተጠመቀ ልጅ በዓለም ላይ ባሉ ነገሮች ይማረክ አሊያም ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች መመራት ጠቃሚ መሆኑን ይጠራጠር ይሆናል። (መዝ. 73:1-3, 12, 13) ወላጆች፣ ልጃችሁ እንዲህ ዓይነት ዝንባሌ እንዳለው ካስተዋላችሁ፣ እናንተ ጉዳዩን የምትይዙበት መንገድ ይሖዋን ማገልገሉን እንዲቀጥል አሊያም ጨርሶ እንዲያቆም ሊያደርግ እንደሚችል መገንዘብ ይኖርባችኋል። ልጃችሁ በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኝ ቢሆን ከሚያነሳቸው ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከእሱ ጋር ጦርነት ልትከፍቱ አይገባም። ዓላማችሁ ልጃችሁን በፍቅርና በደግነት መርዳት ሊሆን ይገባል።

17, 18. አንድ ወጣት ያመነበትን ነገር መጠራጠር ቢጀምር ወላጆቹ እሱን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

17 እርግጥ ነው፣ አንድ የተጠመቀ ወጣት ለይሖዋ ራሱን እንደወሰነ ሊዘነጋ አይገባም። ራሱን ሲወስን፣ አምላክን ለመውደድና የእሱን ፈቃድ ከምንም ነገር በላይ ለማስቀደም ቃል ገብቷል። (ማርቆስ 12:30ን አንብብ።) ይሖዋ፣ አንድ ሰው በዚህ መንገድ የገባውን ቃል አቅልሎ አይመለከተውም፤ በመሆኑም እንዲህ ያለ ቃል የገባ ማንኛውም ሰው ጉዳዩን በቁም ነገር ሊመለከተው ይገባል። (መክ. 5:4, 5) ወላጆች፣ ተስማሚ ጊዜ መርጣችሁ ልጃችሁ ይህን እውነታ እንዲያስታውስ በደግነት እርዱት። በመጀመሪያ ግን የይሖዋ ድርጅት ለወላጆች ባዘጋጃቸው መሣሪያዎች በሚገባ መጠቀም ያስፈልጋችኋል። እንዲህ ማድረጋችሁ፣ ራስን ለይሖዋ መወሰን እና መጠመቅ የሚያስከትላቸውን ኃላፊነቶችና የሚያስገኛቸውን በረከቶች ለልጃችሁ ለማስገንዘብ ይረዳችኋል።

18 ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶችጥራዝ 1 በተባለው መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን ምክር እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ በተጨማሪ ክፍሉ ላይ “ወላጆች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች” በሚለው ርዕስ ሥር የሚከተለውን ጠቃሚ ሐሳብ ታገኛላችሁ፦ “ልጃችሁ [በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል የማያስደስተው] መሆኑ የእናንተን እምነት መከተል እንደማይፈልግ የሚያሳይ እንደሆነ ለመደምደም አትቸኩሉ። አብዛኛውን ጊዜ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ፍላጎት እንዲያጣ ያደረገው ሌላ ምክንያት ሊኖር ይችላል።” አንዱ ምክንያት የእኩዮቹ ተጽዕኖ ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ ብቸኝነት ይሰማው ይሆናል፤ ወይም ሌሎች ክርስቲያን ወጣቶች ከእሱ የበለጠ መንፈሳዊ ሰዎች እንደሆኑ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። መጽሐፉ ቀጥሎ እንዲህ ይላል፦ “እንደነዚህ ያሉት ጉዳዮች ልጃችሁ እምነታችሁ ትክክለኛ መሆኑን እንደተጠራጠረ የሚያሳዩ እንዳልሆኑ ልብ ልትሉ ይገባል። ከዚህ ይልቅ ልጃችሁ ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት ያጣው ይህን እምነት መከተል ተፈታታኝ እንዲሆንበት የሚያደርጉ ሁኔታዎች ስለገጠሙት ነው።” ተጨማሪ ክፍሉ ክርስቲያን ወላጆች፣ ያመነበትን ነገር የሚጠራጠርን ልጅ መርዳት የሚችሉባቸውን የተለያዩ መንገዶች ይጠቁማል።

19. ወላጆች ልጆቻቸው “ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ” እንዲያገኙ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

19 ወላጆች፣ ልጆቻችሁን “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” የማሳደግ መብት ተሰጥቷችኋል፤ ይህ ግን ከባድ ኃላፊነትም ያስከትላል። (ኤፌ. 6:4) እስካሁን እንደተመለከትነው ይህን ማድረግ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ማስተማርን ብቻ ሳይሆን ልጆቹ የተማሩትን ነገር አምነው እንዲቀበሉ መርዳትንም ይጨምራል። ደግሞም ልጆቹ የሚማሩትን ነገር በሚገባ ካመኑበት ራሳቸውን ለይሖዋ ለመወሰንና እሱን በሙሉ ልባቸው ለማገልገል ይነሳሳሉ። የይሖዋ ቃልና መንፈሱ እንዲሁም እናንተ የምታደርጉት ጥረት፣ ልጆቻችሁ “ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ” እንዲያገኙ የሚረዳቸው እንዲሆን ምኞታችን ነው!

^ አን.9ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?” ለተባለው መጽሐፍ የተዘጋጁት የማጥኛ ጽሑፎች፣ ወጣቶችም ሆነ አዋቂዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች መረዳትና ማብራራት እንዲችሉ የሚያግዙ ግሩም መሣሪያዎች ናቸው። እነዚህን የማጥኛ ጽሑፎች jw.org ላይ በብዙ ቋንቋዎች ማግኘት ይቻላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ መሣሪያዎች በሚለው ሥር ተመልከት።