በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ወደፊቱ ጊዜ መተንበይ

ስለ ወደፊቱ ጊዜ መተንበይ

‘የወደፊቱ ጊዜ ለእኔና ለቤተሰቤ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?’ የሚለው ጥያቄ ያሳስብሃል? ወደፊት ሀብታም የምትሆን ይመስልሃል ወይስ ድሃ? በምትወዳቸው ሰዎች ተከብበህ የምትኖር ይመስልሃል ወይስ ብቸኛ የምትሆን? ረጅም ዘመን ትኖራለህ ወይስ በአጭሩ ትቀጫለህ? የሰው ልጆች እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን መልስ አስቀድመው ለማወቅ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የተለያየ ጥረት ሲያደርጉ ኖረዋል።

በዛሬው ጊዜ ያሉ ሊቃውንት በዓለም ላይ የሚታዩ አዝማሚያዎችን በማጥናት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ይተነብያሉ። በርካታ ትንበያዎቻቸው በትክክል የተፈጸሙ ቢሆንም አንዳንዶቹ ግን ሳይፈጸሙ ቀርተዋል፤ እንዲያውም እነሱ ካሰቡት ፈጽሞ በተለየ መንገድ የተፈጸሙም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሽቦ አልባ ቴሌግራፍ የፈለሰፈው ጉሊየልሞ ማርኮኒ “ሽቦ አልባ መሣሪያዎች መፈልሰፋቸው ጦርነት ሙሉ በሙሉ እንዲቀር ያደርጋል” በማለት በ1912 እንደተነበየ ይነገራል። እንዲሁም በ1962 የዴካ ሪከርድ ኩባንያ ወኪል የሆነ አንድ ሰው ‘የጊታር ባንድ በቅርቡ ጊዜ ያለፈበት ይሆናል’ ብሎ በማሰብ ቢትልስ ከተባለው የሙዚቃ ባንድ ጋር ለመሥራት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

ብዙ ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ከሰው በላይ ኃይል ወዳላቸው አካላት ዘወር ብለዋል። አንዳንዶች ኮከብ ቆጣሪዎችን ያማክራሉ፤ እንዲያውም ኮከብ ቆጣሪዎች የሚናገሯቸው ትንበያዎች በብዙ መጽሔቶችና ጋዜጦች ላይ የሚወጡ ቋሚ አምዶች ሆነዋል። ሌሎች ደግሞ የጥንቆላ ካርዶችን፣ ቁጥሮችን ወይም የእጅ መዳፍን እናነብባለን የሚሉ ጠንቋዮችን ያማክራሉ።

በጥንት ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች የወደፊቱን ጊዜ ለማወቅ ሲሉ ጠንቋዮችን ያማክሩ ነበር፤ ጠንቋዮቹ ከሚያገለግሉት አምላክ የመጣን መረጃ እንደሚያስተላልፉ ይናገሩ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የሊዲያው ንጉሥ ክሪሰስ ከፋርሱ ንጉሥ ከቂሮስ ጋር ቢዋጋ ድል ያደርግ እንደሆነ ለማወቅ ስለፈለገ ግሪክ ውስጥ ባለችው በዴልፊ ወደሚገኝ አንድ ጠንቋይ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ስጦታ ልኮ ነበር። ጠንቋዩም ክሪሰስ በቂሮስ ላይ ቢዘምት “አንድ ታላቅ ግዛት” እንደሚደመሰስ ተናገረ። ክሪሰስም ድል እንደሚያገኝ በመተማመን በቂሮስ ላይ ዘመተ፤ ሆኖም የተደመሰሰው ታላቅ ግዛት የራሱ የክሪሰስ ነበር!

ይህ ጠንቋይ የተናገረው ትንቢት አሻሚ ነበር፤ ምክንያቱም ጦርነት ከገጠሙት ተፋላሚ ወገኖች መካከል የትኛውም ቢያሸንፍ ትንበያው በትክክል የተፈጸመ ሊመስል ይችላል። በመሆኑም ትንቢቱ ምንም ጥቅም አልነበረውም። ክሪሰስ ይህን የተሳሳተ መረጃ ማመኑ ከፍተኛ ኪሳራ አስከትሎበታል። በዛሬው ጊዜ ሰፊ ተቀባይነት ባገኙ የትንበያ ዘዴዎች የሚታመኑ ሰዎች የሚያገኙት ውጤትስ ከዚህ የተሻለ ሊሆን ይችላል?