በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መፈጸማቸው የማይቀር ተስፋዎች

መፈጸማቸው የማይቀር ተስፋዎች

ኢየሱስ አስቀድሞ በተናገረው መሠረት የአምላክ መንግሥት ምሥራች በመላው ምድር ላይ እየተሰበከ ነው። (ማቴዎስ 24:14) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የዳንኤል መጽሐፍ ይህ መንግሥት አምላክ ያቋቋመው መስተዳድር እንደሆነ ይናገራል። ዳንኤል ምዕራፍ 2 ከጥንቷ ባቢሎን ጀምሮ እስከ ዘመናችን ድረስ በየተራ ስለሚነሱት አንዳንድ ኃያላን መንግሥታት የሚገልጽ ትንቢት ይዟል። ቁጥር 44 ላይ ወደፊት የሚመጣውን ነገር አስመልክቶ እንዲህ ይላል፦

“የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይጠፋ መንግሥት ያቋቁማል። ይህም መንግሥት ለሌላ ሕዝብ አይሰጥም። እነዚህን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ ፈጽሞም ያጠፋቸዋል፤ እሱም ብቻውን ለዘላለም ይቆማል።”

ይህ ጥቅስም ሆነ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የአምላክ መንግሥት ሁሉንም ሰብዓዊ መንግሥታት አጥፍቶ በእነሱ ምትክ እንደሚገዛ ይናገራሉ፤ በተጨማሪም በዚህ መንግሥት ሥር ሰዎች ተረጋግተውና ሰላም አግኝተው እንደሚኖሩ የሚገልጽ ተስፋ ይዘዋል። በአምላክ መንግሥት ሥር የሚኖረው ሕይወት ምን ይመስላል? በቅርቡ ከሚፈጸሙ አስደናቂ ተስፋዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

  • ጦርነት አይኖርም

    መዝሙር 46:9፦ “[አምላክ] ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ ያስወግዳል። ቀስትን ይሰባብራል፤ ጦርንም ያነክታል፤ የጦር ሠረገሎችን በእሳት ያቃጥላል።”

    በአሁኑ ጊዜ መንግሥታት የጦር መሣሪያዎችን ለማምረት በርካታ ገንዘብና ባለሙያዎችን ይመድባሉ፤ እነዚህ ነገሮች አጥፊ መሣሪያዎችን ለመሥራት ሳይሆን ሰዎችን የሚጠቅም ነገር ለማከናወን ቢውሉ ኖሮ ዓለማችን ምን ትመስል እንደነበር ለማሰብ ሞክር! ጦርነት እንደማይኖር የተሰጠው ተስፋ በአምላክ መንግሥት ሥር እውን ይሆናል።

  • በሽታ አይኖርም

    ኢሳይያስ 33:24፦ “በዚያም የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’ አይልም።”

    በልብ በሽታ፣ በካንሰር፣ በወባ፣ ወይም በሌላ በማንኛውም በሽታ የሚሠቃይ ሰው የማይኖርበት ዓለም ምን ሊመስል እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። በዚያን ጊዜ ሆስፒታሎችና መድኃኒቶች አያስፈልጉም። ወደፊት በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ፍጹም ጤንነት ይኖራቸዋል።

  • የምግብ እጥረት አይኖርም

    መዝሙር 72:16 “በምድር ላይ እህል ይትረፈረፋል፤ በተራሮችም አናት ላይ በብዛት ይኖራል።”

    በምድር ላይ ለሁሉም ሰው የሚበቃ ምግብ የሚኖር ሲሆን ማንም ሰው ምግብ አጥቶ አይቸገርም። ረሃብም ሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አይኖርም።

  • ሥቃይ፣ ሐዘን ወይም ሞት አይኖርም

    ራእይ 21:4 “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”

    ገነት በሆነች ምድር ላይ ፍጹም ሆነን ለዘላለም እንኖራለን! ይህ አፍቃሪ የሆነው ፈጣሪያችን ይሖዋ የገባልን ቃል ነው።

‘ዓላማው በእርግጥ ይፈጸማል’

እነዚህ ነገሮች ይፈጸማሉ ብሎ ማመን ይከብድሃል? ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን ሕይወት ለማግኘት የሚጓጉ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ እንዲህ ያለውን ሕይወት ማግኘት ፈጽሞ እንደማይቻል ይሰማቸዋል። ደግሞም እንዲህ ቢሰማቸው አያስገርምም፤ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት ሕይወት የኖረና ምን እንደሚመስል ሊነግረን የሚችል ሰው የለም።

የሰው ልጆች ለረጅም ዘመናት የኃጢአትና የሞት ባሪያ ሆነው በሥቃይ፣ በችግርና በመከራ ሲቃትቱ ኖረዋል፤ በመሆኑም እነዚህን ነገሮች የሰው ልጅ የሕይወት ክፍል እንደሆኑ አድርገው ተቀብለዋቸዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ሕይወት ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክ ለሰው ልጆች ከነበረው ዓላማ ፈጽሞ የተለየ ነው።

አምላክ እሱ የሰጠን ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጸሙ እርግጠኛ እንድንሆን ይፈልጋል፤ በመሆኑም ቃሉን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ደስ የሚያሰኘኝን ነገር ያደርጋል፣ የተላከበትንም ዓላማ በእርግጥ ይፈጽማል እንጂ ያላንዳች ውጤት ወደ እኔ አይመለስም።”—ኢሳይያስ 55:11

መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ‘ሊዋሽ የማይችል’ አምላክ እንደሆነ ይናገራል። (ቲቶ 1:2) ይሖዋ ወደፊት የምናገኛቸው በርካታ አስደሳች ነገሮችን አዘጋጅቶልናል፤ በመሆኑም የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመርመራችን ጠቃሚ ነው፦ የሰው ልጆች ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም መኖር ይችላሉ? አምላክ የገባው ቃል ሲፈጸም ለማየት ምን ማድረግ ይኖርብናል? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ በቀጣዮቹ ገጾች ላይ ይገኛል።