በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኖኅን፣ የዳንኤልንና የኢዮብን ያህል ይሖዋን ታውቀዋለህ?

የኖኅን፣ የዳንኤልንና የኢዮብን ያህል ይሖዋን ታውቀዋለህ?

“ክፉዎች ፍትሕን መረዳት አይችሉም፤ ይሖዋን የሚፈልጉ ግን ሁሉን ነገር መረዳት ይችላሉ።”—ምሳሌ 28:5

መዝሙሮች፦ 126, 150

1-3. (ሀ) በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ለይሖዋ ታማኝ ሆነን ለመቀጠል ምን ሊረዳን ይችላል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

ወደ መጨረሻዎቹ ቀናት መደምደሚያ ይበልጥ እየቀረብን በሄድን መጠን ክፉዎች “እንደ አረም [መብቀላቸውን]” ይቀጥላሉ። (መዝ. 92:7) ከዚህ አንጻር፣ ሰዎች አምላክ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ችላ ማለታቸው የሚያስገርም አይደለም። እንዲህ ባለ ዓለም ውስጥ እየኖርን ‘በማስተዋል ችሎታችን የጎለመስን ለክፋት ግን ሕፃናት መሆን’ የምንችለው እንዴት ነው?—1 ቆሮ. 14:20

2 የጥናት ርዕሳችን የተመሠረተበት ጥቅስ የዚህን ጥያቄ መልስ ይሰጠናል። ጥቅሱ በከፊል “ይሖዋን የሚፈልጉ . . . ሁሉን ነገር መረዳት ይችላሉ” ይላል፤ ይህም ሲባል አምላክን ለማስደሰት የሚያስፈልጉ ነገሮችን በሙሉ መረዳት ይችላሉ ማለት ነው። (ምሳሌ 28:5) ይሖዋ “ለቅኖች ጥበብን እንደ ውድ ሀብት [እንደሚያከማች]” የሚናገረው በምሳሌ 2:7, 9 ላይ የሚገኘው ሐሳብም ተመሳሳይ መልእክት ያስተላልፋል። በዚህም ምክንያት ቅን የሆኑ ሰዎች “ጽድቅ፣ ፍትሕና ትክክል የሆነውን ነገር ይኸውም የጥሩነትን ጎዳና በሙሉ [መረዳት]” ይችላሉ።

3 ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ እንዲህ ያለውን ጥበብ አግኝተዋል። (ሕዝ. 14:14) በዛሬው ጊዜ ካሉ የአምላክ ሕዝቦች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አንተስ በግለሰብ ደረጃ ይህን ጥበብ አግኝተሃል? ይሖዋን ለማስደሰት የሚያስፈልጉትን ‘ሁሉንም ነገሮች መረዳት’ ችለሃል? ለዚህ ቁልፉ ስለ ይሖዋ ትክክለኛ እውቀት መቅሰም ነው። ይህን በአእምሯችን ይዘን የሚከተሉትን ነጥቦች እንመርምር፦ (1) ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ አምላክን ማወቅ የቻሉት እንዴት ነው? (2) ይህ እውቀት የጠቀማቸው እንዴት ነው? (3) እኛስ እንደ እነሱ በአምላክ ላይ እምነት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

ኖኅ በክፋት በተሞላ ዓለም ውስጥ ከአምላክ ጋር ሄዷል

4. ኖኅ ይሖዋን ማወቅ የቻለው እንዴት ነው? ስለ ይሖዋ ያገኘው ትክክለኛ እውቀት የጠቀመውስ እንዴት ነው?

4 ኖኅ ይሖዋን ማወቅ የቻለው እንዴት ነው? ከሰው ልጆች ታሪክ መጀመሪያ አንስቶ የእምነት ምሳሌ የሚሆኑ ወንዶችና ሴቶች ስለ አምላክ ማወቅ የቻሉት በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ነው፤ በዓይን የሚታዩትን የፍጥረት ሥራዎች በመመልከት፣ ፈሪሃ አምላክ ካላቸው ሰዎች ተሞክሮ በመማር እንዲሁም ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምቶ መኖር የሚያስገኛቸውን በረከቶች በገዛ ሕይወታቸው በመመልከት ነው። (ኢሳ. 48:18) ኖኅ የፍጥረት ሥራዎችን በመመልከት ስለ አምላክ መኖር ብቻ ሳይሆን ይሖዋ ስላሉት የማይታዩ ባሕርያትም ለምሳሌ ስለ “ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ” በግልጽ ማስተዋል ይችል ነበር። (ሮም 1:20) ይህም በአምላክ መኖር ከማመን ባለፈ በእሱ ላይ ጠንካራ እምነት ማዳበር እንዲችል ረድቶታል።

5. ኖኅ አምላክ ለሰው ዘር ስላለው ዓላማ ሊያውቅ የቻለው እንዴት ነው?

5 “እምነት የሚገኘው ቃሉን ከመስማት ነው።” (ሮም 10:17) ታዲያ ኖኅ ስለ ይሖዋ ሊሰማ የቻለው እንዴት ነው? ከዘመዶቹ ብዙ ነገር ተምሮ ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። ከእነዚህ መካከል የእምነት ሰው የነበረውና ለተወሰኑ ዓመታት ያህል ከአዳም ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ላይ የኖረው አባቱ ላሜህ ይገኝበታል። (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) ከአያቱ ከማቱሳላ እንዲሁም ኖኅ 366 ዓመት እስኪሆነው ድረስ በሕይወት ከኖረው ከቅም አያቱ ከያሬድም ስለ ይሖዋ ተምሮ ሊሆን ይችላል። * (ሉቃስ 3:36, 37) ኖኅ ከእነዚህ ሰዎች ምናልባትም ከሚስቶቻቸው ጭምር የሰው ዘር ወደ ሕልውና ስለመጣበት መንገድ፣ ምድር ጻድቅ በሆኑ የሰው ልጆች እንድትሞላ አምላክ ስላለው ዓላማ እንዲሁም በኤደን ስለተነሳው ዓመፅ ሰምቶ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፤ ይህ ዓመፅ ያስከተለውን ውጤት ደግሞ በገዛ ዓይኑ መመልከት ይችል ነበር። (ዘፍ. 1:28፤ 3:16-19, 24) ኖኅ እነዚህን ነገሮች የሰማበት መንገድ ምንም ይሁን ምን፣ የተማረው ነገር ልቡን የነካው ከመሆኑም ሌላ አምላክን ለማገልገል አነሳስቶታል።—ዘፍ. 6:9

6, 7. ተስፋ የኖኅን እምነት ያጠናከረለት እንዴት ነው?

6 ተስፋ፣ እምነት እንዲጠናከር ያደርጋል። ከዚህ አንጻር ኖኅ ተስፋ ያዘለውን የስሙን ትርጉም ሲረዳ ምን ተሰምቶት እንደሚሆን መገመት እንችላለን፤ ስሙ “እረፍት” ወይም “ማጽናኛ” የሚል ትርጉም ሳይኖረው አይቀርም። (ዘፍ. 5:29 ግርጌ) ላሜህ “ይህ ልጅ [ኖኅ]፣ ይሖዋ በረገማት ምድር የተነሳ . . . ከምንደክመው ድካም በማሳረፍ ያጽናናናል” በማለት በመንፈስ መሪነት ተናግሯል። ኖኅ አምላክ ሁኔታዎችን እንደሚያስተካክል ተስፋ ያደርግ ነበር። ከእሱ በፊት እንደነበሩት እንደ አቤልና ሄኖክ ሁሉ እሱም የእባቡን ራስ በሚጨፈልቀው “ዘር” ላይ እምነት ነበረው።—ዘፍ. 3:15

7 ኖኅ በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘውን ትንቢት ሙሉ በሙሉ ባይረዳውም እንኳ ትንቢቱ የመዳን ተስፋ ያዘለ እንደሆነ ሳይገነዘብ አልቀረም። ደግሞም በኤደን የተሰጠው ይህ ተስፋ አምላክ በክፉዎች ላይ እንደሚፈርድ ሄኖክ ካወጀው መልእክት ጋር የሚስማማ ነበር። (ይሁዳ 14, 15) በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ሙሉ ፍጻሜውን የሚያገኘው የሄኖክ መልእክት የኖኅን እምነትና ተስፋ አጠናክሮለት እንደሚሆን እርግጠኞች መሆን እንችላለን!

8. ኖኅ ስለ አምላክ ያገኘው ትክክለኛ እውቀት ጥበቃ የሆነለት እንዴት ነው?

8 ኖኅ ስለ አምላክ ያገኘው ትክክለኛ እውቀት የጠቀመው እንዴት ነው? ኖኅ ያገኘው ትክክለኛ እውቀት እምነትና አምላካዊ ጥበብ እንዲያዳብር ረድቶታል፤ ይህም ከተለያዩ አደጋዎች በተለይም ከመንፈሳዊ አደጋ ጠብቆታል። ለምሳሌ ኖኅ “ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ” ስለነበር ፈሪሃ አምላክ ከሌላቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነት አልመሠረተም። በወቅቱ የነበሩ እምነት የለሽና ሞኝ ሰዎች ሥጋ የለበሱት አጋንንት በነበራቸው ከሰው በላይ የሆነ ችሎታ ተደምመው እንደሚሆን እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ምናልባትም አንዳንዶቹ እነዚህን አጋንንት ማምለክ ጀምረው ሊሆን ይችላል። ኖኅ ግን በዚህ ፈጽሞ አልተታለለም። (ዘፍ. 6:1-4, 9) በተጨማሪም ኖኅ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት” የሚለው ትእዛዝ የተሰጠው ለሰው ልጆች እንደሆነ ያውቅ ነበር። (ዘፍ. 1:27, 28) በመሆኑም በሴቶችና ሥጋ በለበሱ መላእክት መካከል የሚደረገው የፆታ ግንኙነት ስህተትና ከተፈጥሮ ውጭ እንደሆነ ሳይገነዘብ አልቀረም። በዚህ መንገድ የተወለዱት ልጆች ከሰው ልጆች በጣም የተለዩ መሆናቸው ደግሞ ተጨማሪ ማረጋገጫ እንደሆነለት ምንም ጥርጥር የለውም። ከጊዜ በኋላ አምላክ ለኖኅ በምድር ላይ የጥፋት ውኃ እንደሚያመጣ የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ሰጠው። ኖኅ በዚህ ማስጠንቀቂያ ላይ እምነት ማሳደሩ መርከቡን እንዲሠራ ያነሳሳው ሲሆን ይህም ቤተሰቡን ለማትረፍ አስችሎታል።—ዕብ. 11:7

9, 10. እንደ ኖኅ በአምላክ ላይ እምነት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

9 እንደ ኖኅ በአምላክ ላይ እምነት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? ለዚህ ቁልፉ ትጉ የአምላክ ቃል ተማሪዎች መሆን፣ የተማርነው ነገር ወደ ልባችን ዘልቆ እንዲገባ ማድረግ እንዲሁም ያገኘነው እውቀት እንዲቀርጸንና እንዲመራን መፍቀድ ነው። (1 ጴጥ. 1:13-15) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ እምነትና አምላካዊ ጥበብ የምናገኝ ሲሆን ይህም ሰይጣን በሚሸርባቸው የተንኮል ዘዴዎችና በዚህ ዓለም ክፉ መንፈስ እንዳንታለል ጥበቃ ይሆነናል። (2 ቆሮ. 2:11) የዓለም መንፈስ ሰዎች ዓመፅንና የሥነ ምግባር ብልግናን እንዲወዱ እንዲሁም በሥጋ ምኞቶች ላይ እንዲያተኩሩ ያበረታታል። (1 ዮሐ. 2:15, 16) ሌላው ቀርቶ በመንፈሳዊ ደካማ የሆኑ ሰዎች ታላቁ የአምላክ ቀን መቅረቡን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ችላ እንዲሉ ሊያደርግ ይችላል። ኢየሱስ እኛ ያለንበትን ዘመን ከኖኅ ዘመን ጋር ሲያነጻጽር ትኩረት ያደረገው በዓመፅና በሥነ ምግባር ብልግና ላይ ሳይሆን መንፈሳዊ ነገሮችን ችላ ማለት በሚያስከትለው አደጋ ላይ እንደሆነ ልብ ማለት ይኖርብናል።—ማቴዎስ 24:36-39ን አንብብ።

10 በመሆኑም ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው፦ ‘አኗኗሬ ይሖዋን በትክክል እንደማውቀው ያሳያል? በአምላክ ላይ ያለኝ እምነት ከጽድቅ መሥፈርቶቹ ጋር ተስማምቶ ከመኖር ባለፈ ስለ እነዚህ መሥፈርቶች ለሌሎች እንድናገር ይገፋፋኛል?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው መልስ ‘ከእውነተኛው አምላክ ጋር እየሄድን’ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ይረዳናል።

ዳንኤል በጣዖት አምልኮ በተሞላችው በባቢሎን ውስጥ አምላካዊ ጥበብ እንዳለው አሳይቷል

11. (ሀ) ዳንኤል በወጣትነቱ ለአምላክ ያደረ መሆኑ ስለ አስተዳደጉ ምን ያስተምረናል? (ለ) ዳንኤል ካሉት ባሕርያት መካከል አንተ ማዳበር የምትፈልገው የትኛውን ነው?

11 ዳንኤል ይሖዋን ማወቅ የቻለው እንዴት ነው? ዳንኤል ለይሖዋና በጽሑፍ ለሰፈረው የአምላክ ቃል ፍቅር እንዲያዳብር ወላጆቹ ጥሩ ሥልጠና ሰጥተውት እንደነበር ከሁኔታዎች መረዳት እንችላለን። በዚህ መንገድ ያዳበረው ፍቅር እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ አብሮት ዘልቋል። ዕድሜው በጣም በገፋበት ወቅትም እንኳ ቅዱሳን መጻሕፍትን በትጋት ያጠና ነበር። (ዳን. 9:1, 2) ነቢዩ በጸጸት ስሜት ተውጦ ያቀረበው ከልብ የመነጨ ጸሎት በዳንኤል 9:3-19 ላይ ተመዝግቦ የሚገኝ ሲሆን በጸሎቱ ላይ የጠቀሳቸው ነገሮች ስለ አምላክም ሆነ አምላክ ከእስራኤላውያን ጋር ስለነበረው ግንኙነት ጥልቅ እውቀት እንደነበረው ያሳያሉ። ዳንኤል ያቀረበውን ይህን ጸሎት ለማንበብና በዚያ ላይ ለማሰላሰል ለምን ጊዜ አትመድብም? እንዲህ በምታደርግበት ወቅት ‘ይህ ጸሎት ስለ ዳንኤል ምን ያስተምረኛል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

12-14. (ሀ) ዳንኤል አምላካዊ ጥበብ እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ዳንኤል ለአምላክ ታማኝ ለመሆን ሲል የወሰደው ድፍረት የተሞላበት እርምጃ ምን በረከት አስገኝቷል?

12 ዳንኤል ስለ አምላክ ያገኘው ትክክለኛ እውቀት የጠቀመው እንዴት ነው? በጣዖት አምልኮ በተሞላችው በባቢሎን መኖር ለአንድ ታማኝ አይሁዳዊ በጣም ተፈታታኝ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ አይሁዳውያኑን “በግዞት ተወስዳችሁ እንድትኖሩባት ላደረግኳት [ከተማ] ሰላምን ፈልጉ” ብሏቸው ነበር። (ኤር. 29:7) በሌላ በኩል ደግሞ እሱን ብቻ እንዲያመልኩት ይጠብቅባቸው ነበር። (ዘፀ. 34:14) ዳንኤል እነዚህን ሁለት ትእዛዛት በመጠበቅ ረገድ ሚዛኑን እንዳይስት የረዳው ምንድን ነው? አምላካዊ ጥበብ፣ ለዓለማዊ ባለሥልጣናት መገዛት ያለበት አንጻራዊ በሆነ መንገድ እንደሆነ እንዲገነዘብ ረድቶታል። ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ይህንኑ መሠረታዊ ሥርዓት አስተምሯል።—ሉቃስ 20:25

13 ዳንኤል ለ30 ቀናት ያህል ከንጉሡ በስተቀር ለአምላክም ሆነ ለሰው ልመና ማቅረብን የሚከለክል አዋጅ በወጣ ጊዜ የወሰደውን እርምጃ እንደ ምሳሌ እንመልከት። (ዳንኤል 6:7-10ን አንብብ።) ‘ለ30 ቀን ብቻ እኮ ነው!’ በማለት ለራሱ ሰበብ ማቅረብ ይችል ነበር። ሆኖም ንጉሡ ያወጣው አዋጅ ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታውን ከመወጣት እንዲያግደው አልፈቀደም። እርግጥ ነው፣ ከሰዎች እይታ ተሰውሮ መጸለዩን መቀጠል ይችል ነበር። ይሁንና በየቀኑ የመጸለይ ልማዱ በሰዎች ዘንድ እንደሚታወቅ ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም ዳንኤል ሕይወቱን አደጋ ላይ መጣል የሚጠይቅበት ቢሆንም ለአምላክ በሚያቀርበው አምልኮ ረገድ አቋሙን እንዳላላ የሚያስመስል ነገርም እንኳ ላለማድረግ ወስኗል።

14 ይሖዋ ዳንኤልን ከተፈረደበት አሰቃቂ ሞት ተአምራዊ በሆነ መንገድ በማዳን ዳንኤል የወሰደውን በሚገባ የታሰበበትና ድፍረት የተሞላበት እርምጃ እንደባረከው አሳይቷል። በዚህ የተነሳ በሜዶ ፋርስ ግዛት ውስጥ ባሉ ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች ሳይቀር ስለ ይሖዋ አስደናቂ ምሥክርነት ሊሰጥ ችሏል!—ዳን. 6:25-27

15. እንደ ዳንኤል በአምላክ ላይ እምነት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

15 እንደ ዳንኤል በአምላክ ላይ እምነት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? ጠንካራ እምነት ለማዳበር የአምላክን ቃል ማንበብ ብቻውን በቂ አይደለም፤ የምናነበውን ነገር ‘ማስተዋልም’ ያስፈልጋል። (ማቴ. 13:23) በተጨማሪም የይሖዋን አስተሳሰብ መረዳት እንፈልጋለን፤ ይህም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መገንዘብን ይጠይቃል። በመሆኑም በምናነበው ነገር ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። በተጨማሪም አዘውትረን ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ያስፈልገናል፤ በተለይ ደግሞ መከራ ወይም ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን እንዲህ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። አምላክ ጥበብና ብርታት እንዲሰጠን በእምነት የምንጠይቀው ከሆነ በልግስና እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ያዕ. 1:5

ኢዮብ በጥሩውም ሆነ በመጥፎው ወቅት የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ አድርጓል

16, 17. ኢዮብ ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ያገኘው እንዴት ነው?

16 ኢዮብ ይሖዋን ማወቅ የቻለው እንዴት ነው? ኢዮብ እስራኤላዊ አልነበረም። ሆኖም የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ የሩቅ ዘመድ ሲሆን ይሖዋ ደግሞ ለእነዚህ ሰዎች ስለ ራሱም ሆነ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ ገልጾላቸዋል። ኢዮብ በሆነ መንገድ ስለ እነዚህ ውድ እውነቶች ሰምቶ መሆን አለበት። (ኢዮብ 23:12) “ጆሮዬ ስለ አንተ ሰምታ ነበር” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 42:5) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ራሱ ኢዮብ ስለ እሱ እውነቱን እንደተናገረ ገልጿል።—ኢዮብ 42:7, 8

በዓይን ከሚታዩት የፍጥረት ሥራዎች የአምላክን የማይታዩ ባሕርያት መመልከታችን እምነታችንን ለማጠናከር ይረዳናል (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)

17 በተጨማሪም ኢዮብ በዓይን ከሚታዩት የፍጥረት ሥራዎች የአምላክን የማይታዩ ባሕርያት መመልከት ችሎ ነበር። (ኢዮብ 12:7-9, 13) ከጊዜ በኋላ ኤሊሁም ሆነ ይሖዋ ከአምላክ ታላቅነት አንጻር የሰው ልጅ እዚህ ግባ የሚባል ፍጡር አለመሆኑን ለኢዮብ ለማስረዳት የፍጥረት ሥራዎችን ተጠቅመዋል። (ኢዮብ 37:14፤ 38:1-4) ኢዮብ እንደሚከተለው በማለት ለአምላክ በትሕትና መናገሩ ይሖዋ በተናገራቸው ነገሮች ልቡ እንደተነካ ያሳያል፦ “አንተ ሁሉን ነገር ማድረግ እንደምትችል፣ ደግሞም ያሰብከውን ነገር ሁሉ ማድረግ እንደማይሳንህ አሁን አወቅኩ። . . . በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬም ንስሐ እገባለሁ።”—ኢዮብ 42:2, 6

18, 19. ኢዮብ ይሖዋን በሚገባ እንደሚያውቅ ያሳየው እንዴት ነው?

18 ኢዮብ ስለ አምላክ ያገኘው ትክክለኛ እውቀት የጠቀመው እንዴት ነው? ኢዮብ አምላክ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሚገባ መረዳት ችሎ ነበር። ስለ ይሖዋ ትክክለኛ እውቀት የነበረው ሲሆን ከዚህ እውቀት ጋር በሚስማማ መንገድ ተመላልሷል። ለምሳሌ በአንድ በኩል በባልንጀራው ላይ ደግነት የጎደለው ድርጊት እየፈጸመ በሌላ በኩል ደግሞ አምላክን እንደሚወድ መናገር እንደማይችል ተገንዝቦ ነበር። (ኢዮብ 6:14) ራሱን ከሌሎች ከፍ አድርጎ ከመመልከት ይልቅ ሀብታም ድሃ ሳይል ለሁሉም ሰው ወንድማዊ ፍቅር ያሳይ ነበር። “እኔን በማህፀን ውስጥ የሠራኝ እነሱንስ አልሠራም?” በማለት ጠይቋል። (ኢዮብ 31:13-22) በግልጽ ማየት እንደምንችለው ኢዮብ የነበረው ክብርና ሀብት ስለ ራሱም ሆነ ስለ ሌሎች ያለውን አመለካከት እንዲያዛባበት አልፈቀደም። ኢዮብ በዘመናችን ካሉ ከፍተኛ ሥልጣንና ሀብት ያላቸው ሰዎች ምንኛ የተለየ ነበር!

19 ኢዮብ ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ ይርቅ ነበር፤ በልቡም እንኳ እንዲህ ያለውን ነገር ላለማሰብ ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። በሐሰት አምልኮ መካፈልም ሆነ ቁሳዊ ሀብትን ከይሖዋ ማስበለጥ “በላይ ያለውን እውነተኛውን አምላክ መካድ” እንደሆነ ተረድቷል። (ኢዮብ 31:24-28ን አንብብ።) በተጨማሪም ኢዮብ ጋብቻ፣ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚፈጸም ቅዱስ ጥምረት እንደሆነ ይሰማው ነበር። ሌላው ቀርቶ ድንግሊቷን ሥነ ምግባር በጎደለው መንገድ ላለመመልከት ከዓይኑ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል። (ኢዮብ 31:1) የሚገርመው ኢዮብ እንዲህ ዓይነት አመለካከት የነበረው አምላክ ከአንድ በላይ ማግባትን የሚከለክል ሕግ ባልሰጠበት ወቅት ነው። ስለዚህ ኢዮብ ቢፈልግ ኖሮ ሁለተኛ ሚስት ማግባት ይችል ነበር። * ሆኖም ኢዮብ አምላክ በኤደን የመሠረተውን ጋብቻ እንደ ምሳሌ በመውሰድ በዚያ መሠረት ለመመራት እንደወሰነ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። (ዘፍ. 2:18, 24) ኢየሱስ ክርስቶስ ከ1,600 ዓመታት ገደማ በኋላ ከጋብቻና ከፆታ ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ ተከታዮቹ ይህንኑ መሠረታዊ ሥርዓት እንዲከተሉ አስተምሯል።—ማቴ. 5:28፤ 19:4, 5

20. ስለ ይሖዋና እሱ ስላወጣቸው መሥፈርቶች ትክክለኛ እውቀት መቅሰማችን ጥሩ ጓደኞችና ጤናማ መዝናኛ ለመምረጥ የሚረዳን እንዴት ነው?

20 እንደ ኢዮብ በአምላክ ላይ እምነት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ለዚህ ቁልፉ ስለ ይሖዋ ትክክለኛ እውቀት መቅሰምና ይህ እውቀት በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች እንዲመራን መፍቀድ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙራዊው ዳዊት “ይሖዋ . . . ዓመፅን የሚወድን ማንኛውንም ሰው ይጠላል” በማለት የተናገረ ከመሆኑም ሌላ “አታላይ ከሆኑ ሰዎች ጋር” መቀራረብ ስለሚያስከትለው አደጋ አስጠንቅቋል። (መዝሙር 11:5⁠ን እና 26:4ን አንብብ።) እነዚህ ጥቅሶች ስለ አምላክ አስተሳሰብ ምን ያስገነዝቡሃል? ይህን መገንዘብህ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች፣ የኢንተርኔት አጠቃቀምህን እንዲሁም የጓደኛና የመዝናኛ ምርጫህን የሚነካውስ እንዴት ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ ይሖዋን ምን ያህል እንደምታውቀው ለመገንዘብ ይረዳሃል። ውጥንቅጡ በወጣውና በክፋት በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ ከነቀፋ ነፃ ሆነን ለመመላለስ ‘የማስተዋል ችሎታችንን በማሠራት ማሠልጠን’ ይኖርብናል፤ እንዲህ ማድረጋችን ትክክልና ስህተት በሆነው ነገር መካከል ያለውን ልዩነት ብቻ ሳይሆን ጥበብ በሚንጸባረቅበትና ጥበብ በጎደለው ውሳኔ መካከል ያለውን ልዩነትም ለማወቅ ይረዳናል።—ዕብ. 5:14፤ ኤፌ. 5:15

21. በሰማይ ያለውን አባታችንን ለማስደሰት የሚያስፈልጉትን ‘ሁሉንም ነገሮች ለመረዳት’ የሚያስችለን ምንድን ነው?

21 ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ ይሖዋን በሙሉ ልባቸው የፈለጉት ሲሆን እሱም ተገኝቶላቸዋል። እሱን ለማስደሰት የሚያስፈልጉትን ‘ሁሉንም ነገሮች እንዲረዱ’ አስችሏቸዋል። በመሆኑም የጽድቅ ምሳሌዎች ሆነው ለመቆጠርና የተሳካ ሕይወት ለመምራት በቅተዋል። (መዝ. 1:1-3) ስለዚህ ‘የኖኅን፣ የዳንኤልንና የኢዮብን ያህል ይሖዋን አውቀዋለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው። እንዲያውም መንፈሳዊው ብርሃን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ከእነሱ በተሻለ ይሖዋን ማወቅ እንችላለን! (ምሳሌ 4:18) እንግዲያው የአምላክን ቃል በጥልቀት እንመርምር፤ ባነበብናቸው ነገሮች ላይ እናሰላስል፤ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት እንጸልይ። እንዲህ ካደረግን በሰማይ ወዳለው አባታችን ይበልጥ እየቀረብን እንሄዳለን። እንዲሁም ፈሪሃ አምላክ በሌለው በዚህ ዓለም ውስጥ በማስተዋልና በጥበብ መመላለስ እንችላለን።—ምሳሌ 2:4-7

^ አን.5 የኖኅ ቅድመ አያት የሆነው ሄኖክም ‘ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ’ ነበር። ሆኖም ኖኅ ከመወለዱ ከ69 ዓመታት በፊት ‘አምላክ ወስዶታል።’—ዘፍ. 5:23, 24

^ አን.19 ከኖኅ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በኤደን ዓመፅ ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ ሰዎች ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት የጀመሩ ቢሆንም ኖኅ ያገባው አንዲት ሚስት ብቻ ነበር።—ዘፍ. 4:19