በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ከበፊቱ ይበልጥ” እርስ በርስ እንበረታታ

“ከበፊቱ ይበልጥ” እርስ በርስ እንበረታታ

“አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ . . . እርስ በርስ እንበረታታ፤ ደግሞም ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ ይህን እናድርግ።”—ዕብ. 10:24, 25

መዝሙሮች፦ 90, 87

1. ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ዕብራውያን ክርስቲያኖች “ከበፊቱ ይበልጥ” እርስ በርስ እንዲበረታቱ አጥብቆ የመከራቸው ለምንድን ነው?

ሌሎችን ለማበረታታት የምናደርገውን ጥረት ከምንጊዜውም ይበልጥ ማጠናከር ያለብን ለምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ምክንያቱን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ እንበረታታ፤ ደግሞም ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ ይህን እናድርግ።” (ዕብ. 10:24, 25) በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች፣ ከአምስት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ “የይሖዋ ቀን” መቅረቡን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ይመለከታሉ፤ እንዲሁም ኢየሱስ በሰጣቸው ምልክት መሠረት ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ ከተማዋን ለቀው የሚወጡበት ጊዜ መድረሱን ይገነዘባሉ። (ሥራ 2:19, 20፤ ሉቃስ 21:20-22) በዚያን ወቅት የይሖዋ ቀን የመጣው በ70 ዓ.ም. ማለትም ሮማውያን ይሖዋ በኢየሩሳሌም ላይ ያስተላለፈውን የቅጣት ፍርድ ባስፈጸሙበት ጊዜ ነው።

2. በዛሬው ጊዜ አንዳችን ሌላውን ለማበረታታት ይበልጥ ትኩረት መስጠት ያለብን ለምንድን ነው?

2 በዛሬው ጊዜም የይሖዋ “ታላቅና እጅግ የሚያስፈራ” ቀን እንደቀረበ እንድናምን የሚያደርጉ በቂ ማስረጃዎች አሉን። (ኢዩ. 2:11) ነቢዩ ሶፎንያስ “ታላቁ የይሖዋ ቀን ቅርብ ነው! ቅርብ ነው፤ ደግሞም በፍጥነት እየቀረበ ነው!” ብሏል። (ሶፎ. 1:14) ይህ ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ ለዘመናችንም ይሠራል። የይሖዋ ቀን በቀረበበት ጊዜ ላይ ስለምንኖር ጳውሎስ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ” በማለት የሰጠው ምክር እኛንም ይመለከታል። (ዕብ. 10:24) በመሆኑም አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ሁሉ ወንድሞቻችንን ማበረታታት እንድንችል ለእነሱ ይበልጥ ትኩረት መስጠት ይኖርብናል።

ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸው እነማን ናቸው?

3. ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ማበረታቻ ምን ብሏል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

3 “በሰው ልብ ውስጥ ያለ ጭንቀት ልቡ እንዲዝል ያደርገዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።” (ምሳሌ 12:25) ይህ ሐሳብ ሁላችንንም ይመለከታል። አልፎ አልፎ ማበረታቻ የማያስፈልገው ማንም የለም። ጳውሎስ ሌሎችን የሚያበረታቱ ሰዎችም እንኳ ማበረታቻ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል። በሮም ለሚኖሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለመጽናት የሚያስችላችሁን መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እጓጓለሁና፤ ይህን ስል እኔ በእናንተ እምነት እናንተም በእኔ እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ ነው።” (ሮም 1:11, 12) አዎ፣ ለሌሎች ግሩም ማበረታቻ ይሰጥ የነበረው ጳውሎስ እንኳ ማበረታቻ ማግኘት ያስፈለገው ጊዜ ነበር።—ሮም 15:30-32ን አንብብ።

4, 5. በዛሬው ጊዜ እነማንን ማበረታታት እንችላለን? ለምንስ?

4 የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉ ክርስቲያኖች አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል። ከእነዚህ መካከል በታማኝነት የሚያገለግሉ አቅኚዎች ይገኙበታል። አብዛኞቹ በአቅኚነት ለማገልገል ሲሉ ብዙ መሥዋዕትነት ከፍለዋል። ከሚስዮናውያን፣ ከወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ከሚስቶቻቸው እንዲሁም በቅርንጫፍ ቢሮዎችም ሆነ በርቀት የትርጉም ቢሮዎች ውስጥ ከሚያገለግሉ ክርስቲያኖች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ሁሉም ለቅዱስ አገልግሎት የሚያውሉት ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት ሲሉ ብዙ ነገሮችን መሥዋዕት አድርገዋል። በመሆኑም ማበረታቻ ሊሰጣቸው ይገባል። በተጨማሪም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመቀጠል ልባዊ ፍላጎት ቢኖራቸውም በተለያዩ ምክንያቶች እንቅስቃሴያቸው የተገደበባቸው ወንድሞችና እህቶችም ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል።

5 “በጌታ ብቻ” እንዲያገቡ ለክርስቲያኖች የተሰጠውን መመሪያ ለመታዘዝ ሲሉ ሳያገቡ የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች ማበረታቻ ሊሰጣቸው ይገባል። (1 ቆሮ. 7:39) በተጨማሪም ትጉ የሆኑ ሚስቶች ከባሎቻቸው የሚያበረታቱ ቃላትን ቢሰሙ ደስ ይላቸዋል። (ምሳሌ 31:28, 31) ከዚህም ሌላ የሚደርስባቸውን ስደት ተቋቁመው ወይም ያለባቸውን ሕመም ችለው በታማኝነት የሚያገለግሉ ክርስቲያኖች ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። (2 ተሰ. 1:3-5) ይሖዋና ክርስቶስም እነዚህን ታማኝ አገልጋዮች ያጽናናሉ።—2 ተሰሎንቄ 2:16, 17ን አንብብ።

ሽማግሌዎች ሌሎችን ለማበረታታት ጥረት ያደርጋሉ

6. በኢሳይያስ 32:1, 2 ላይ እንደተገለጸው ሽማግሌዎች ምን ሚና ይጫወታሉ?

6 ኢሳይያስ 32:1, 2ን አንብብ። የምንኖረው አስቸጋሪ በሆነ ዘመን ውስጥ እንደመሆኑ መጠን ሁላችንም በቀላሉ ልናዝንና ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በቅቡዓን ወንድሞቹና የሌሎች በጎች ክፍል በሆኑ አጋሮቻቸው ማለትም “መኳንንት” ተብለው በተጠሩት ሽማግሌዎች አማካኝነት ማበረታቻ ይሰጠናል። እነዚህ ሽማግሌዎች በእምነታችን ላይ ‘የሚያዝዙ’ ሳይሆኑ ‘ለደስታችን ከእኛ ጋር የሚሠሩ’ በመሆናቸው የሚያስፈልገንን ማበረታቻ እንደሚሰጡን መጠበቅ እንችላለን።—2 ቆሮ. 1:24

7, 8. ሽማግሌዎች የሚያበረታቱ ቃላትን ከመናገር ባለፈ ሌሎችን ሊያንጹ የሚችሉት እንዴት ነው?

7 ሐዋርያው ጳውሎስ ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። በተሰሎንቄ ስደት እየደረሰባቸው ለነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለእናንተ ጥልቅ ፍቅር ስላለን የአምላክን ምሥራች ለማካፈል ብቻ ሳይሆን ራሳችንን ጭምር ለእናንተ ለመስጠት ቆርጠን ነበር፤ ምክንያቱም እናንተ በእኛ ዘንድ እጅግ የተወደዳችሁ ነበራችሁ።”—1 ተሰ. 2:8

8 ጳውሎስ የሚያበረታቱ ቃላትን መናገር ብቻ በቂ እንዳልሆነ ለማሳየት በኤፌሶን ለነበሩት ሽማግሌዎች የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል፦ “ደካማ የሆኑትን መርዳት [አለባችሁ]፤ . . . እንዲሁም ‘ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል’ በማለት ጌታ ኢየሱስ ራሱ የተናገረውን ቃል ማስታወስ ይኖርባችኋል።” (ሥራ 20:35) ጳውሎስ ወንድሞቹን ከማበረታታት ባለፈ ለእነሱ ሲል ‘ያለውን ሁሉ’ እንዲያውም ‘ራሱንም ጭምር ለመስጠት’ ፈቃደኛ ነበር። (2 ቆሮ. 12:15) ሽማግሌዎችም ወንድሞቻቸውን በቃላት ከማበረታታትና ከማጽናናት አልፈው በግለሰብ ደረጃ ከልብ የመነጨ አሳቢነት በማሳየት ሊያንጿቸው ይገባል።—1 ቆሮ. 14:3

9. ሽማግሌዎች በሚያበረታታ መንገድ ምክር መስጠት የሚችሉት እንዴት ነው?

9 ሌሎችን ማነጽ ምክር መስጠትን የሚጨምርበት ጊዜ ይኖራል፤ በዚህ ጊዜም ቢሆን ሽማግሌዎች በሚያበረታታ መንገድ ምክር መስጠት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን መከተል ይኖርባቸዋል። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ የሰጠው ምክር በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆናል። በትንሿ እስያ ለነበሩ አንዳንድ ጉባኤዎች ጠንከር ያለ ምክር መስጠት ባስፈለገው ጊዜ ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። በኤፌሶን፣ በጴርጋሞንና በትያጥሮን ለነበሩት ጉባኤዎች ምክር ከመስጠቱ በፊት ከልብ አመስግኗቸዋል። (ራእይ 2:1-5, 12, 13, 18, 19) በሎዶቅያ ለነበረው ጉባኤ ደግሞ “እኔ፣ የምወዳቸውን ሁሉ እወቅሳለሁ እንዲሁም እገሥጻለሁ። ስለዚህ ቀናተኛ ሁን፤ ንስሐም ግባ” በማለት ተናግሯል። (ራእይ 3:19) ሽማግሌዎች ምክር በሚሰጡበት ጊዜ የክርስቶስን ምሳሌ መከተላቸው ተገቢ ነው።

ለሽማግሌዎች ብቻ የተተወ ኃላፊነት አይደለም

ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ሌሎችን እንዲያበረታቱ እያሠለጠናችኋቸው ነው? (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)

10. አንዳችን ሌላውን በማነጽ ረገድ ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው?

10 ሌሎችን ማበረታታት ለሽማግሌዎች ብቻ የተተወ ኃላፊነት አይደለም። ጳውሎስ ሁሉም ክርስቲያኖች “እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎቹን ሊጠቅም የሚችል መልካም ቃል” እንዲናገሩ አሳስቧል። (ኤፌ. 4:29) እያንዳንዳችን ሌሎችን “እንደ አስፈላጊነቱ” ለማበረታታት ንቁዎች መሆን አለብን። ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ “የዛሉትን እጆችና የተብረከረኩትን ጉልበቶች አበርቱ፤ የተጎዳው የአካል ክፍል እንዲፈወስ እንጂ እንዳይናጋ እግራችሁ ዘወትር ቀና በሆነ መንገድ እንዲጓዝ አድርጉ።” (ዕብ. 12:12, 13) ልጆችን ጨምሮ ሁላችንም የሚያበረታቱ ቃላት በመናገር ሌሎችን ማነጽ እንችላለን።

11. ማርተ በመንፈስ ጭንቀት ትሠቃይ በነበረችበት ወቅት ምን እርዳታ አግኝታለች?

11 በመንፈስ ጭንቀት ትሠቃይ የነበረች ማርተ * የተባለች እህት እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “አንድ ቀን ማበረታቻ ለማግኘት ጸለይኩ፤ በዚያኑ ዕለት ከአንዲት በዕድሜ የገፋች እህት ጋር ተገናኘሁ፤ እሷም በጊዜው ያስፈልገኝ የነበረውን ፍቅርና ርኅራኄ አሳየችኝ። በተጨማሪም ተመሳሳይ ችግር አጋጥሟት እንደነበር ያጫወተችኝ ሲሆን ይህም የሚሰማኝ የብቸኝነት ስሜት ቀለል እንዲልልኝ አድርጓል።” ምናልባትም ይህች በዕድሜ የገፋች እህት፣ የተናገረቻቸው ቃላት በማርተ ላይ ምን ያህል በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደሩ አታውቅ ይሆናል።

12, 13. በፊልጵስዩስ 2:1-4 ላይ ያለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

12 ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ጉባኤ አባላት በሙሉ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ “እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ባላችሁ አንድነት በመካከላችሁ ማንኛውም ዓይነት ማበረታቻ፣ ማንኛውም ዓይነት ፍቅራዊ ማጽናኛ፣ ማንኛውም ዓይነት መንፈሳዊ ኅብረት፣ ማንኛውም ዓይነት ጥልቅ ፍቅርና ርኅራኄ ካለ፣ ፍጹም አንድነት ኖሯችሁና አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ይዛችሁ በአንድ ሐሳብና በአንድ ፍቅር በመኖር ደስታዬን የተሟላ አድርጉልኝ። ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ እንጂ በጠበኝነት መንፈስ ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር አታድርጉ፤ ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”—ፊልጵ. 2:1-4

13 አዎ፣ ሁላችንም “ፍቅራዊ ማጽናኛ” በመስጠት፣ ከሌሎች ጋር “መንፈሳዊ ኅብረት” በመፍጠር እንዲሁም “ጥልቅ ፍቅርና ርኅራኄ” በማሳየት ለሌሎች ሰዎች ፍላጎት ትኩረት ለመስጠት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፤ በዚህ መንገድ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ማበረታታት እንችላለን።

የብርታት ምንጭ የሚሆኑ ነገሮች

14. የብርታት ምንጭ ሊሆነን የሚችለው ምንድን ነው?

14 ከዚህ ቀደም የረዳናቸው ሰዎች ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ እንዳሉ መስማታችን ከፍተኛ የብርታት ምንጭ ሊሆነን ይችላል። ሐዋርያው ዮሐንስም ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቶት ነበር፤ “ልጆቼ በእውነት ውስጥ እየተመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የበለጠ ደስታ የለኝም” በማለት ጽፏል። (3 ዮሐ. 4) በርካታ አቅኚዎች ይህ እውነት መሆኑን ይመሠክራሉ፤ ከዓመታት በፊት ወደ እውነት እንዲመጡ የረዷቸው ሰዎች አሁንም ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ እንዳሉ አልፎ ተርፎም አቅኚዎች እንደሆኑ መስማታቸው በጣም አበረታቷቸዋል። በተስፋ መቁረጥ ስሜት የተዋጠን አንድ አቅኚ ከዚህ በፊት በይሖዋ አገልግሎት ስላሳለፈው አስደሳች ሕይወት ማስታወሳችን በራሱ የብርታት ምንጭ ሊሆነው ይችላል።

15. በታማኝነት የሚያገለግሉትን ማበረታታት የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

15 በርካታ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው አንድን ጉባኤ ከጎበኙ በኋላ ወንድሞች የጻፉላቸው አጭር የምስጋና ደብዳቤ እንኳ ምን ያህል እንዳበረታታቸው ገልጸዋል። ሽማግሌዎች፣ ሚስዮናውያን፣ አቅኚዎችና የቤቴል ቤተሰብ አባላትም ለሚያከናውኑት የታማኝነት አገልግሎት አድናቆት ሲቸራቸው ተመሳሳይ ስሜት ይሰማቸዋል።

ሁላችንም ሌሎችን ማበረታታት የምንችለው እንዴት ነው?

16. አንድን ሰው ለማበረታታት ምን ማድረግ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል?

16 በባሕርያችን ከሰዎች ጋር መግባባት ስለሚከብደን ብቻ ሌሎችን ማበረታታት እንደማንችል የሚሰማን ከሆነ ተሳስተናል። ለሌሎች የብርታት ምንጭ መሆን ያን ያህል ከባድ ነገር አይደለም፤ አንድን ሰው ሰላም ስንለው ሞቅ ያለ ፈገግታ ማሳየታችን ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። ግለሰቡ መልሶ ፈገግ ካላለ ይህ አንድ ችግር እንዳለ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል፤ በዚህ ጊዜ ግለሰቡ ሲናገር ማዳመጣችን ብቻ ያጽናናው ይሆናል።—ያዕ. 1:19

17. አንድ ወጣት ወንድም ተጨንቆ በነበረበት ወቅት እርዳታ ያገኘው እንዴት ነው?

17 ኦንሪ የተባለ አንድ ወጣት ወንድም በሌሎች ዘንድ የተከበረ የጉባኤ ሽማግሌ የነበረውን አባቱን ጨምሮ የቅርብ ዘመዶቹ እውነትን ሲተዉ በጣም ተረብሾ ነበር። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ኦንሪን ሻይ ቤት ወስዶ ከጋበዘው በኋላ የልቡን አውጥቶ እንዲናገር አጋጣሚ ሰጠው። ይህም ኦንሪን በጣም ያበረታታው ከመሆኑም ሌላ ቤተሰቦቹ ወደ እውነት እንዲመለሱ መርዳት የሚችለው በታማኝነት ከጸና ብቻ እንደሆነ እንዲገነዘብ ረድቶታል። በተጨማሪም መዝሙር 46⁠ን፣ ሶፎንያስ 3:17⁠ንና ማርቆስ 10:29, 30⁠ን ማንበቡ በእጅጉ አጽናንቶታል።

ሁላችንም እርስ በርስ መበረታታትና መተናነጽ እንችላለን (አንቀጽ 18⁠ን ተመልከት)

18. (ሀ) ንጉሥ ሰለሞን ምን በማለት ጽፏል? (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ ምን እንድናደርግ አበረታቷል?

18 የማርተና የኦንሪ ተሞክሮ፣ ማጽናኛ ለሚያስፈልጋቸው ወንድሞችና እህቶች የብርታት ምንጭ መሆን እንደምንችል ያሳያል። ንጉሥ ሰለሞን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በትክክለኛው ጊዜ የተነገረ ቃል . . . ምንኛ መልካም ነው! ብሩህ ዓይን [ወይም “በፈገግታ የተሞላ ፊት”] ልብን ደስ ያሰኛል፤ መልካም ዜናም አጥንትን ያበረታል።” (ምሳሌ 15:23, 30) በተጨማሪም በመጠበቂያ ግንብ ወይም በድረ ገጻችን ላይ የሚወጡትን ሐሳቦች ማንበባችን ተስፋ በምንቆርጥበት ጊዜ ሊያበረታታን ይችላል። ጳውሎስ የመንግሥቱን መዝሙሮች በአንድነት መዘመር የብርታት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በመዝሙራት፣ ለአምላክ በሚቀርብ ውዳሴና በአመስጋኝነት መንፈስ በሚዘመሩ መንፈሳዊ ዝማሬዎች ትምህርትና ማበረታቻ መስጠታችሁን ቀጥሉ፤ በልባችሁም ለይሖዋ ዘምሩ።”—ቆላ. 3:16፤ ሥራ 16:25

19. እርስ በርስ መበረታታት ይበልጥ አስፈላጊ እየሆነ የሚሄደው ለምንድን ነው? የትኛውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል?

19 የይሖዋ ቀን ይበልጥ ‘እየቀረበ ሲመጣ’ እርስ በርስ መበረታታት ይበልጥ አስፈላጊ እየሆነ ይሄዳል። (ዕብ. 10:25) በመሆኑም ጳውሎስ በዘመኑ ለነበሩት ክርስቲያኖች የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ እናድርግ፦ “አሁን እያደረጋችሁት እንዳለው እርስ በርስ ተበረታቱ እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ።”—1 ተሰ. 5:11

^ አን.11 ስሞቹ ተቀይረዋል።