በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጠላታችሁን እወቁ

ጠላታችሁን እወቁ

“[ሰይጣን] የሚሸርበውን ተንኮል እናውቃለን።”—2 ቆሮ. 2:11

መዝሙሮች፦ 150, 32

1. ይሖዋ ስለ ጠላታችን በኤደን ውስጥ ምን ተናግሯል?

አዳም፣ እባብ ማውራት እንደማይችል ያውቅ ነበር። በመሆኑም በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን ያነጋገራት አንድ መንፈሳዊ ፍጡር እንደሆነ ሳይገምት አልቀረም። (ዘፍ. 3:1-6) አዳምና ሔዋን ስለዚህ መንፈሳዊ ፍጡር ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም ማለት ይቻላል። ያም ቢሆን አዳም፣ አፍቃሪ ለሆነው ሰማያዊ አባቱ ጀርባውን በመስጠት ጨርሶ ከማያውቀው አካል ጋር ተባብሮ የአምላክን ፈቃድ ለመቃወም መረጠ። (1 ጢሞ. 2:14) አዳምና ሔዋን እንዲያምፁ ያደረጋቸውን ይህን ጠላት በተመለከተ ይሖዋ ወዲያውኑ አንዳንድ ነገሮችን የገለጸ ሲሆን ይህ ክፉ አካል ውሎ አድሮ እንደሚጠፋ ቃል ገባ። ይሁን እንጂ በእባቡ አማካኝነት የተናገረው ይህ መንፈሳዊ ፍጡር ለተወሰነ ጊዜ ያህልም ቢሆን የአምላክን ወዳጆች ሁሉ እንደሚቃወም ይሖዋ ገልጾ ነበር።—ዘፍ. 3:15

2, 3. መሲሑ ከመምጣቱ በፊት ስለ ሰይጣን ብዙ መረጃ ያልሰፈረው ለምን ሊሆን ይችላል?

2 ይሖዋ በእሱ ላይ ያመፀውን መልአክ ስም አልነገረንም፤ ይህም ጥበቡን የሚያሳይ ነው። * ይህ ጠላት በፈጸመው ተግባር ምክንያት የተሰጠውን መጠሪያ እንኳ አምላክ ያሳወቀን የመጀመሪያው ዓመፅ ከተቀሰቀሰ ወደ 2,500 ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ ነው። (ኢዮብ 1:6) እንዲያውም “ተቃዋሚ” የሚል ትርጉም ያለው ሰይጣን የሚለው መጠሪያ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘው በሦስት መጻሕፍት ይኸውም በ1 ዜና መዋዕል፣ በኢዮብና በዘካርያስ ላይ ብቻ ነው። ለመሆኑ መሲሑ ከመምጣቱ በፊት ስለ ጠላታችን የሚገልጽ ብዙ መረጃ ያልሰፈረው ለምንድን ነው?

3 ይሖዋ ስለ ሰይጣንና ስለ ሥራዎቹ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ሰፋ ያለ ማብራሪያ በማስፈር ለዚህ ጠላት አላስፈላጊ እውቅና መስጠት የፈለገ አይመስልም። ይሖዋ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲጻፉ ያደረገበት ዋነኛ ዓላማ፣ ሰዎች መሲሑን ማወቅና መከተል እንዲችሉ ለመርዳት ነው። (ሉቃስ 24:44፤ ገላ. 3:24) መሲሑ መጥቶ ይህ ዓላማ ከዳር ሲደርስ፣ ይሖዋ በመሲሑና በደቀ መዛሙርቱ በመጠቀም ስለ ሰይጣንና ግብረ አበሮቹ ስለሆኑት መላእክት ተጨማሪ መረጃ ሰጠ፤ * ሰይጣንና አጋንንቱን በተመለከተ ከምናውቀው መረጃ አብዛኛውን ያገኘነው በዚህ መንገድ ነው። ይህ መሆኑም ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ሰይጣንን እና ተከታዮቹን ለመጨፍለቅ ይሖዋ የሚጠቀመው በኢየሱስና አብረውት በሚገዙት ቅቡዓን ነው።—ሮም 16:20፤ ራእይ 17:14፤ 20:10

4. ዲያብሎስ ከመጠን በላይ ሊያስፈራን የማይገባው ለምንድን ነው?

4 ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ሰይጣን ዲያብሎስ “እንደሚያገሳ አንበሳ” እንደሆነ ተናግሯል፤ ዮሐንስ ደግሞ “እባብ” እና “ዘንዶ” በማለት ጠርቶታል። (1 ጴጥ. 5:8፤ ራእይ 12:9) ሆኖም ዲያብሎስ ከመጠን በላይ ሊያስፈራን አይገባም፤ ምክንያቱም ሰይጣን ያለው ኃይል ገደብ የለሽ አይደለም። (ያዕቆብ 4:7ን አንብብ።) ይሖዋ፣ ኢየሱስ እንዲሁም ታማኝ መላእክት ከጎናችን ናቸው። በእነሱ እርዳታ ጠላታችንን መቋቋም እንችላለን። ያም ቢሆን የሦስት ጥያቄዎችን መልስ ማወቅ ያስፈልገናል፦ ሰይጣን ምን ያህል ተጽዕኖ ማሳደር ይችላል? በሌሎች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚሞክረው በየትኞቹ መንገዶች ነው? ሰይጣን ማድረግ የማይችላቸው ነገሮችስ የትኞቹ ናቸው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንዲሁም ከመልሶቹ የምናገኘውን ትምህርት እስቲ እንመልከት።

ሰይጣን ምን ያህል ተጽዕኖ ማሳደር ይችላል?

5, 6. ሰብዓዊ መንግሥታት የሰው ልጆች ከምንም በላይ የሚያስፈልጓቸውን ለውጦች ማምጣት የማይችሉት ለምንድን ነው?

5 ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መላእክት ከሰይጣን ጋር በመተባበር በይሖዋ ላይ ዓምፀዋል። ከጥፋት ውኃው በፊት ከእነዚህ መካከል ቢያንስ የተወሰኑትን ከሰዎች ሴቶች ልጆች ጋር የፆታ ብልግና እንዲፈጽሙ ሰይጣን ገፋፍቷቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሁኔታ በምሳሌያዊ መንገድ ሲገልጽ፣ ዘንዶው ከሰማይ ከዋክብት መካከል አንድ ሦስተኛውን ጎትቶ ወደ ምድር እንደወረወረ ይናገራል። (ዘፍ. 6:1-4፤ ይሁዳ 6፤ ራእይ 12:3, 4) እነዚህ መላእክት የአምላክን ቤተሰብ ጥለው በመውጣት ከሰይጣን ጎን ተሰልፈዋል። ይሁንና እነዚህን ዓመፀኛ መላእክት እንደ ተራ ረብሸኞች አድርገን ልናስባቸው አይገባም። አምላክ መንግሥት እንዳለው ሁሉ ሰይጣንም የራሱን የማይታይ መስተዳድር በማቋቋም ራሱን ንጉሥ አድርጓል። ሰይጣን፣ አጋንንትን መንግሥታት አድርጎ አደራጅቷቸዋል፤ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል እንዲሁም የዓለም ገዢዎች አድርጓቸዋል።—ኤፌ. 6:12

6 ሰይጣን በማይታየው ድርጅቱ አማካኝነት ሁሉንም ሰብዓዊ መንግሥታት ይቆጣጠራል። ሰይጣን ለኢየሱስ “የዓለምን መንግሥታት ሁሉ” ካሳየው በኋላ “ይህ ሁሉ ሥልጣንና የእነዚህ መንግሥታት ክብር ተሰጥቶኛል፤ እኔ ደግሞ ለፈለግኩት መስጠት ስለምችል ለአንተ እሰጥሃለሁ” ማለቱ ይህን እውነታ በግልጽ ያሳያል። (ሉቃስ 4:5, 6) እርግጥ ነው፣ ሰይጣን መጥፎ ነገር እንዲያደርጉ በመንግሥታት ላይ ተጽዕኖ ቢያሳድርም በርካታ መንግሥታት ለዜጎቻቸው መልካም ለማድረግ ይጥራሉ። ቀና አስተሳሰብ ያላቸው አንዳንድ መሪዎችም ይኖራሉ። ይሁን እንጂ የትኛውም ሰብዓዊ መንግሥትም ሆነ መሪ የሰው ልጆች ከምንም በላይ የሚያስፈልጓቸውን ለውጦች ማምጣት አይችልም።—መዝ. 146:3, 4፤ ራእይ 12:12

7. ሰይጣን ከመንግሥታት በተጨማሪ በሐሰት ሃይማኖትና በንግዱ ሥርዓት የሚጠቀመው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

7 ሰይጣንና አጋንንቱ “መላውን ዓለም” ለማሳሳት ሰብዓዊ መንግሥታትን ብቻ ሳይሆን የሐሰት ሃይማኖትንና የንግዱን ሥርዓትም ይጠቀማሉ። (ራእይ 12:9) ሰይጣን በሐሰት ሃይማኖት አማካኝነት ስለ ይሖዋ የተሳሳቱ ትምህርቶችን ያስፋፋል። ከዚህም በተጨማሪ ዲያብሎስ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች የአምላክን ስም እንዲረሱ ለማድረግ ቆርጦ ተነስቷል። (ኤር. 23:26, 27) ይህም ቅን ልብ ያላቸው አንዳንድ ሰዎች አምላክን እያመለኩ እንዳለ ቢሰማቸውም ተታልለው አጋንንትን እንዲያመልኩ አድርጓቸዋል። (1 ቆሮ. 10:20፤ 2 ቆሮ. 11:13-15) ሰይጣን በንግዱ ሥርዓት አማካኝነትም ውሸት ያስፋፋል። ለምሳሌ የንግዱ ሥርዓት፣ ደስታ የሚያስገኘው ከሁሉ የተሻለ አካሄድ ሀብት ማሳደድና ንብረት ማካበት እንደሆነ ሰዎችን ለማሳመን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። (ምሳሌ 18:11) ይህን ውሸት የሚያምኑ ሰዎች ለአምላክ ሳይሆን “ለሀብት” ባሪያ ሆነው ይኖራሉ። (ማቴ. 6:24) ለቁሳዊ ነገሮች ያላቸው ፍቅር ለአምላክ የነበራቸውን ፍቅር ውሎ አድሮ ያንቀዋል።—ማቴ. 13:22፤ 1 ዮሐ. 2:15, 16

8, 9. (ሀ) ስለ አዳምና ሔዋን እንዲሁም ስለ ዓመፀኞቹ መላእክት ከሚናገሩት ዘገባዎች የትኞቹን ሁለት ትምህርቶች እናገኛለን? (ለ) ሰይጣን ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ማወቃችን ምን ጥቅም አለው?

8 ስለ አዳምና ሔዋን እንዲሁም ስለ ዓመፀኞቹ መላእክት ከሚናገሩት ዘገባዎች ቢያንስ ሁለት ጠቃሚ ትምህርቶችን እናገኛለን። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ከይሖዋ አሊያም ከሰይጣን ጎን ከመቆም አንዱን መምረጥ እንዳለብን እንማራለን። ለይሖዋ ታማኝ ካልሆንን ከሰይጣን ጎራ መመደባችን አይቀርም። (ማቴ. 7:13) ሁለተኛ፣ ከሰይጣን ጎን የሚቆሙ ሁሉ የሚያገኙት ጥቅም በጣም ውስን መሆኑን እንማራለን። አዳምና ሔዋን፣ መልካም እና ክፉ ስለሆነው ነገር የራሳቸውን መሥፈርት የማውጣት አጋጣሚ አግኝተው ነበር፤ አጋንንትም ቢሆኑ በሰብዓዊ መንግሥታት ላይ በተወሰነ መጠን ተጽዕኖ ማሳደር ችለዋል። (ዘፍ. 3:22) ይሁን እንጂ ከሰይጣን ጎን መሰለፍ ምንጊዜም ቢሆን ጉዳቱ ያመዝናል፤ ምንም ዓይነት እውነተኛ ጥቅም አያስገኝም!—ኢዮብ 21:7-17፤ ገላ. 6:7, 8

9 ሰይጣን ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ማወቃችን ምን ጥቅም አለው? ሰብዓዊ ባለሥልጣናትን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ ምሥራቹን እንድንሰብክ ያነሳሳናል። ይሖዋ የመንግሥት ባለሥልጣናትን እንድናከብር እንደሚፈልግ እናውቃለን። (1 ጴጥ. 2:17) በተጨማሪም ይሖዋ፣ ሰብዓዊ መንግሥታት የሚያወጧቸው ሕጎች ከእሱ መሥፈርቶች ጋር እስካልተጋጩ ድረስ እነዚህን ሕጎች እንድንታዘዝ ይጠብቅብናል። (ሮም 13:1-4) ያም ቢሆን ምንጊዜም የገለልተኝነት አቋማችንን መጠበቅ እንደሚገባን ይኸውም የትኛውንም የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ሰብዓዊ መሪ ከሌላው ማስበለጥ እንደሌለብን እንገነዘባለን። (ዮሐ. 17:15, 16፤ 18:36) በሌላ በኩል ደግሞ ሰይጣን የይሖዋ ስም እንዳይታወቅ ለማድረግና ስሙን ለማጉደፍ እንደሚጥር ስለምናውቅ ለሰዎች ስለ አምላካችን እውነቱን ለማስተማር ይበልጥ እንነሳሳለን። በይሖዋ ስም በመጠራታችንና በስሙ በመጠቀማችን እንኮራለን። ምክንያቱም ይሖዋን መውደድ፣ ገንዘብን ወይም ንብረትን ከመውደድ እጅግ የላቀ በረከት ያስገኛል።—ኢሳ. 43:10፤ 1 ጢሞ. 6:6-10

ሰይጣን በሌሎች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚሞክረው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

10-12. (ሀ) ሰይጣን አንዳንድ መላእክትን ለማጥመድ የትኞቹን አጓጊ ማባበያዎች ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል? (ለ) በርካታ መላእክት በሰይጣን ወጥመድ መውደቃቸው ምን ያስተምረናል?

10 ሰይጣን በሌሎች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚጠቀምባቸው ውጤታማ የሆኑ ዘዴዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሌሎች እሱ የሚፈልገውን ነገር እንዲፈጽሙ ለማድረግ አጓጊ የሆኑ ማታለያዎችን ያቀርባል። ከዚህም ሌላ፣ ቀጥተኛ ጥቃት በመሰንዘር ሌሎችን ለማንበርከክ ይሞክራል።

11 ሰይጣን በርካታ መላእክትን ለማጥመድ አጓጊ ማታለያዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት እንደተጠቀመ እስቲ እንመልከት። እነዚህን መላእክት አግባብቶ ከእሱ ጎን እንዲሰለፉ ከማድረጉ በፊት፣ በምን መንገድ ሊያጠምዳቸው እንደሚችል ለማወቅ ለረጅም ጊዜ ሳያጠናቸው አልቀረም። አንዳንዶቹ መላእክት ሰይጣን ባቀረበላቸው አጓጊ ግብዣ ተሸንፈው ከሰዎች ሴቶች ልጆች ጋር የፆታ ብልግና ፈጸሙ፤ በዚህ መንገድ የተወለዱት ዲቃላዎች የሰው ልጆችን የሚጨቁኑ ዓመፀኛ ፍጥረታት ነበሩ። (ዘፍ. 6:1-4) ሰይጣን ለይሖዋ ታማኝ ያልሆኑትን መላእክት ለማባበል የተጠቀመው የፆታ ብልግናን ብቻ ላይሆን ይችላል፤ ምናልባትም በሰው ልጆች ላይ ሥልጣን እንደሚኖራቸው ቃል ገብቶላቸው ይሆናል። የሰይጣን ዓላማ፣ ይሖዋ ‘የሴቲቱ ዘር’ እንደሚመጣ የተናገረው ትንቢት እንዳይፈጸም ማስተጓጎል ሊሆን ይችላል። (ዘፍ. 3:15) ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ የጥፋት ውኃውን በማምጣት የሰይጣንና የዓመፀኞቹ መላእክት ዕቅድ እንዲከሽፍ አድርጓል።

ሰይጣን በሥነ ምግባር ብልግና፣ ተገቢ ባልሆነ ኩራት እንዲሁም በምትሃታዊ ድርጊቶች በመጠቀም ሊያታልለን ይሞክራል (አንቀጽ 12, 13⁠ን ተመልከት)

12 ከዚህ ምን እንማራለን? የሥነ ምግባር ብልግና እና ተገቢ ያልሆነ ኩራት አደገኛ ማታለያዎች መሆናቸውን ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። ከሰይጣን ጋር ያበሩት መላእክት ሕልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዘመናት በአምላክ ፊት ያገለግሉ ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ ባለው የተቀደሰ ቦታ ሆነውም እንኳ መጥፎ ምኞቶች በውስጣቸው እንዲያቆጠቁጡና ሥር እንዲሰዱ ፈቅደዋል። እኛም በተመሳሳይ በይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ውስጥ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ስናገለግል ቆይተን ይሆናል። ይሁንና በመንፈሳዊ ሁኔታ ንጹሕ በሆነው በዚህ ቦታ እያገለገልንም እንኳ ንጹሕ ያልሆኑ ሐሳቦች በልባችን ሥር ሊሰዱ ይችላሉ። (1 ቆሮ. 10:12) በእርግጥም አዘውትረን ልባችንን መፈተሻችን እንዲሁም ሥነ ምግባር የጎደላቸውን ሐሳቦችና ተገቢ ያልሆነ ኩራትን ማስወገዳችን በጣም አስፈላጊ ነው!—ገላ. 5:26፤ ቆላስይስ 3:5ን አንብብ።

13. ሰይጣን የሚጠቀምበት ሌላው ውጤታማ ወጥመድ ምንድን ነው? በዚህ ወጥመድ ላለመያዝ ምን ማድረግ እንችላለን?

13 ሰይጣን የሚጠቀምበት ሌላው ውጤታማ ማጥመጃ፣ ሰዎች ምትሃታዊ ኃይል ስላላቸው ነገሮች የማወቅ ጉጉት እንዲያድርባቸው ማድረግ ነው። በዛሬው ጊዜ ሰይጣን፣ ሰዎች ከአጋንንት ጋር ንክኪ እንዲኖራቸው ለማድረግ በሐሰት ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን በመዝናኛው ኢንዱስትሪም ይጠቀማል። ፊልሞች፣ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች እንዲሁም ሌሎች መዝናኛዎች መናፍስታዊ ነገሮችን አጓጊ አስመስለው ያቀርባሉ። በዚህ ወጥመድ ላለመያዝ ምን ማድረግ እንችላለን? የይሖዋ ድርጅት፣ ተቀባይነት ያላቸውንና የሌላቸውን መዝናኛዎች ዝርዝር እንዲያቀርብልን መጠበቅ የለብንም። እያንዳንዳችን ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ ምርጫ ለማድረግ ሕሊናችንን ማሠልጠን ይኖርብናል። (ዕብ. 5:14) ሐዋርያው ጳውሎስ ለአምላክ ያለን ፍቅር “ግብዝነት የሌለበት” እንዲሆን የሰጠንን ምክር በተግባር ካዋልን ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ምርጫዎች ማድረግ እንችላለን። (ሮም 12:9) ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን እንጠይቅ፦ ‘የመዝናኛ ምርጫዬ ግብዝ እንደሆንኩ የሚያሳይ ነው? መጽሐፍ ቅዱስን የማስጠናቸው አሊያም ተመላልሶ መጠየቅ የማደርግላቸው ሰዎች የመዝናኛ ምርጫዬን ቢያዩ ምን ይሰማቸዋል? የማስተምረውን ነገር ተግባራዊ እንደማደርግ ያስባሉ?’ የምናስተምረውን ነገር ይበልጥ በተግባር ባዋልን መጠን በሰይጣን ወጥመድ የመውደቃችን አጋጣሚ ጠባብ ይሆናል።—1 ዮሐ. 3:18

ሰይጣን መንግሥታት በሚጥሉት እገዳ፣ በትምህርት ቤት በሚያጋጥም ተጽዕኖ እንዲሁም በቤተሰብ ተቃውሞ አማካኝነት ቀጥተኛ ጥቃት ይሰነዝርብናል (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)

14. ሰይጣን ቀጥተኛ ጥቃት የሚሰነዝረው እንዴት ነው? ይህን ፈተና ለመቋቋም የሚረዳንስ ምንድን ነው?

14 ሰይጣን አጓጊ ማታለያዎችን ከማቅረብ በተጨማሪ ቀጥተኛ ጥቃት በመሰንዘር ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት እንድናጓድል ለማድረግ ይሞክራል። ለምሳሌ ያህል፣ መንግሥታት በስብከቱ ሥራችን ላይ እገዳ እንዲጥሉ ተጽዕኖ ሊያሳድርባቸው ይችላል። አሊያም ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ለመመራት ባለን ፍላጎት ምክንያት የሥራ ባልደረቦቻችን ወይም አብረውን የሚማሩ ልጆች እንዲያፌዙብን ሊያደርግ ይችላል። (1 ጴጥ. 4:4) አሳቢ የሆኑ የቤተሰባችን አባላት ከጉባኤ ስብሰባዎች እንድንቀር እንዲገፋፉንም ያደርግ ይሆናል። (ማቴ. 10:36) ታዲያ እነዚህን ፈተናዎች መወጣት የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሰይጣን እንዲህ ያለ ቀጥተኛ ጥቃት ሊሰነዝርብን እንደሚችል መጠበቅ አለብን፤ ምክንያቱም በእኛ ላይ ጦርነት አውጇል። (ራእይ 2:10፤ 12:17) ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ካሉት ፈተናዎች በስተ ጀርባ ያለውን ዋነኛ ጉዳይ ማስታወስ ይኖርብናል፦ ሰይጣን፣ ይሖዋን የምናገለግለው ሁኔታዎች ሲመቻቹልን ብቻ እንደሆነ በመናገር ከሶናል። ችግሮች ሲደራረቡብን አምላክን እንደምንክድ ተናግሯል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4, 5) በመጨረሻም፣ የደረሱብንን ፈተናዎች ለመቋቋም ብርታት እንዲሰጠን ይሖዋን መጠየቅ አለብን። ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይጥለን አንዘንጋ።—ዕብ. 13:5

ሰይጣን ማድረግ የማይችላቸው ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

15. ሰይጣን የማንፈልገውን ነገር እንድናደርግ ሊያስገድደን ይችላል? አብራራ።

15 ሰይጣን፣ ሰዎች የማይፈልጉትን ነገር እንዲያደርጉ ማስገደድ አይችልም። (ያዕ. 1:14) እርግጥ ብዙዎች ሳያውቁት ከሰይጣን ጎራ ተሰልፈዋል። እውነትን ካወቁ በኋላ ግን ማንን እንደሚያገለግሉ በግለሰብ ደረጃ መምረጥ አለባቸው። (ሥራ 3:17፤ 17:30) የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም እስከቆረጥን ድረስ ሰይጣን ንጹሕ አቋማችንን በምንም መንገድ ማጉደፍ አይችልም።—ኢዮብ 2:3፤ 27:5

16, 17. (ሀ) ሰይጣንና አጋንንቱ ማድረግ የማይችሏቸው ነገሮች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ድምፃችንን ከፍ አድርገን ወደ ይሖዋ ለመጸለይ መፍራት የሌለብን ለምንድን ነው?

16 ሰይጣንና አጋንንቱ ማድረግ የማይችሏቸው ሌሎች ነገሮችም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የሰዎችን ልብ ወይም አእምሮ ማንበብ እንደሚችሉ የሚገልጽ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድም ቦታ ላይ አናገኝም። ይህ ችሎታ እንዳላቸው የተገለጹት ይሖዋ እና ኢየሱስ ብቻ ናቸው። (1 ሳሙ. 16:7፤ ማር. 2:8) ሆኖም ከሰዎች ጋር ስንነጋገር ወይም ጮክ ብለን ስንጸልይ ዲያብሎስና አጋንንቱ የምንናገረውን ሰምተው በእኛ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር እንዳይጠቀሙበት ልንፈራ ይገባል? በፍጹም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ዲያብሎስ ስለሚያየን ብለን ብቻ በይሖዋ አገልግሎት መልካም ነገሮችን ከማድረግ ወደኋላ እንደማንል የታወቀ ነው። በተመሳሳይም ዲያብሎስ ይሰማናል በሚል ፍርሃት ጮክ ብለን ከመጸለይ መቆጠብ የለብንም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ስለጸለዩ በርካታ የአምላክ አገልጋዮች ይናገራል፤ እነዚህ ሰዎች ዲያብሎስ እንዳይሰማቸው ፈርተው እንደነበር የሚጠቁም ሐሳብ አናገኝም። (1 ነገ. 8:22, 23፤ ዮሐ. 11:41, 42፤ ሥራ 4:23, 24) ንግግራችንም ሆነ ድርጊታችን ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማማ እንዲሆን ከልባችን ጥረት ካደረግን፣ ዲያብሎስ ዘላቂ ጉዳት እንዲያደርስብን ይሖዋ እንደማይፈቅድለት እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—መዝሙር 34:7ን አንብብ።

17 ጠላታችንን ማወቅ ይኖርብናል፤ ይህ ሲባል ግን በፍርሃት ልንርድ ይገባል ማለት አይደለም። ፍጹም ያልሆኑ ሰዎችም እንኳ በይሖዋ እርዳታ ሰይጣንን ማሸነፍ ይችላሉ። (1 ዮሐ. 2:14) ዲያብሎስን ከተቃወምነው ከእኛ ይሸሻል። (ያዕ. 4:7፤ 1 ጴጥ. 5:9) ሰይጣን በተለይ ትኩረት የሚያደርገው በወጣቶች ላይ ይመስላል። ታዲያ ወጣቶች ጸንተው ዲያብሎስን ለመቃወም ምን ማድረግ ይችላሉ? የሚቀጥለው ርዕስ መልሱን ይሰጠናል።

^ አን.2 የአንዳንድ መላእክት የግል ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሯል። (መሳ. 13:18፤ ዳን. 8:16፤ ሉቃስ 1:19፤ ራእይ 12:7) ይሖዋ እያንዳንዱን ኮከብ በስም የሚጠራው ከመሆኑ አንጻር (መዝ. 147:4) ከጊዜ በኋላ ሰይጣን የሆነውን መልአክ ጨምሮ ሁሉም መላእክት የግል ስም አላቸው ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ይሆናል።

^ አን.3 ሰይጣን የሚለው ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘው 18 ጊዜ ብቻ ሲሆን በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ግን ከ30 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል።