በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በልግስና መስጠት ደስታ ያስገኛል

በልግስና መስጠት ደስታ ያስገኛል

“መስጠት . . . ደስታ ያስገኛል።”—ሥራ 20:35

መዝሙሮች፦ 76, 110

1. ፍጥረት ይሖዋ ለጋስ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

ይሖዋ መፍጠር ከመጀመሩ በፊት የሚኖረው ብቻውን ነበር። ሆኖም ለሌሎች የሕይወትን ስጦታ መስጠት ስለፈለገ መንፈሳዊና ሰብዓዊ ፍጡራንን ወደ ሕልውና አመጣ። ‘ደስተኛ አምላክ’ የሆነው ይሖዋ ለሌሎች መልካም ነገሮችን መስጠት ይወዳል። (1 ጢሞ. 1:11፤ ያዕ. 1:17) እኛም ደስተኞች እንድንሆን ስለሚፈልግ ለጋሶች እንድንሆን ያስተምረናል።—ሮም 1:20

2, 3. (ሀ) መስጠት ደስታ የሚያስገኝልን ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ነጥቦች እንመረምራለን?

2 አምላክ ሰውን የፈጠረው በራሱ መልክ ነው። (ዘፍ. 1:27) ይህም ሲባል የተፈጠርነው የእሱን ባሕርይ ማንጸባረቅ እንድንችል ተደርገን ነው ማለት ነው። በመሆኑም ሕይወታችን ደስታና እርካታ ያለው እንዲሆን ከፈለግን የይሖዋን ምሳሌ በመከተል ለሌሎች ሰዎች ፍላጎት ትኩረት መስጠትና ለጋስ መሆን ያስፈልገናል። (ፊልጵ. 2:3, 4፤ ያዕ. 1:5) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በአጭሩ፣ ይሖዋ የፈጠረን በዚህ መልኩ ስለሆነ ነው። ፍጹማን ባንሆንም ለጋስ በመሆን ረገድ ይሖዋን መምሰል እንችላለን።

3 መጽሐፍ ቅዱስ በልግስና መስጠት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይናገራል። እስቲ ቅዱሳን መጻሕፍት በዚህ ረገድ የሚሰጡንን አንዳንድ ሐሳቦች እንመልከት። ለጋስ መሆናችን የአምላክን ሞገስ የሚያስገኝልን እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ይህ ባሕርይ አምላክ የሰጠንን ሥራ ለማከናወን እንዴት እንደሚረዳን እንመረምራለን። በተጨማሪም ለጋስ መሆናችን ከደስታችን ጋር ምን ተያያዥነት እንዳለውና ይህን ባሕርይ ምንጊዜም ማዳበራችን አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።

የአምላክን ሞገስ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

4, 5. ለጋስ በመሆን ረገድ ይሖዋና ኢየሱስ የተዉትን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

4 ይሖዋ የሰው ልጆች እሱን እንዲመስሉት ይፈልጋል፤ በመሆኑም ለጋስ ስንሆን ይደሰታል። (ኤፌ. 5:1) አፈጣጠራችንን ስናይ እንዲሁም ስፍር ቁጥር በሌላቸው የፍጥረት ሥራዎች ላይ የተንጸባረቀውን አስደናቂ ውበት ስንመለከት፣ አምላክ በእርግጥም የሰው ልጆች ደስተኞች እንዲሆኑ እንደሚፈልግ በግልጽ መረዳት እንችላለን። (መዝ. 104:24፤ 139:13-16) በመሆኑም ሌሎችን ለማስደስት ጥረት በማድረግ ይሖዋን ማክበር እንችላለን።

5 እውነተኛ ክርስቲያኖች ልግስና በማሳየት ረገድ ለሰው ልጆች ፍጹም ምሳሌ የሆነውን የክርስቶስን አርዓያ ይከተላሉ። ኢየሱስ “የሰው ልጅም የመጣው ለማገልገልና በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት እንጂ እንዲገለገል አይደለም” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 20:28) ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ይህ አስተሳሰብ በእናንተም ዘንድ ይኑር፤ እሱ ራሱን ባዶ በማድረግ የባሪያን መልክ ይዟል’ የሚል ምክር ለክርስቲያኖች የሰጣቸው ለዚህ ነው። (ፊልጵ. 2:5, 7) ከዚህ አንጻር ‘የኢየሱስን ምሳሌ በጥብቅ በመከተል ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እችላለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው።—1 ጴጥሮስ 2:21ን አንብብ።

6. ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ ከተናገረው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

6 ስለ ሌሎች ደህንነት በማሰብና የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ በመስጠት የይሖዋንና የክርስቶስን አርዓያ የምንከተል ከሆነ የአምላክን ሞገስ ማግኘት እንችላለን። ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ የተናገረው ምሳሌ፣ ተከታዮቹ ከሚጠበቅባቸው አልፈው በመሄድ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች እርዳታ እንዲያደርጉ እንደሚፈልግ በግልጽ የሚጠቁም ነው። (ሉቃስ 10:29-37ን አንብብ።) ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረው ለምንድን ነው? አንድ አይሁዳዊ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” የሚል ጥያቄ ስላቀረበለት ነው። ኢየሱስ የሰጠው መልስ እኛም የአምላክን ሞገስ ማግኘት የምንፈልግ ከሆነ ልክ እንደ ሳምራዊው በልግስና ለመስጠት ፈቃደኞች መሆን እንዳለብን ያስገነዝበናል።

7. ራስ ወዳድ መሆን ወይም አለመሆን ጽንፈ ዓለማዊ ይዘት ካለው አከራካሪ ጉዳይ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

7 እኛ ክርስቲያኖች ለጋስ እንድንሆን የሚያነሳሱን በርካታ ምክንያቶች አሉን። አንደኛው ምክንያት፣ ልግስና ሰይጣን በኤደን ካነሳው ጥያቄ ጋር ተያያዥነት ያለው መሆኑ ነው። እንዴት? ሰይጣን አዳምና ሔዋን አምላክን ከመታዘዝ ይልቅ ለራሳቸው ፍላጎት ቅድሚያ ቢሰጡ እንዲሁም በግል ጥቅማቸው ላይ ቢያተኩሩ የተሻለ ሕይወት እንደሚመሩ የሚጠቁም ሐሳብ ተናግሯል፤ ሰይጣን ያነሳው ይህ ክስ የሰውን ዘር በጠቅላላ የሚመለከት ነው። ሔዋን በራስ ወዳድነት ፍላጎት ተነሳስታ እንደ አምላክ መሆን ፈለገች። አዳምም ቢሆን ከአምላክ ይልቅ ሔዋንን ለማስደሰት መፈለጉ ራስ ወዳድ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። (ዘፍ. 3:4-6) እነዚህ ባልና ሚስት ያደረጉት ውሳኔ ያስከተለው መዘዝ ከማንም የተሰወረ አይደለም። ራስ ወዳድነት ደስታ አያስገኝም፤ እንዲያውም ውጤቱ የተገላቢጦሽ ነው። ለጋስ መሆናችን አምላክ ነገሮችን የሚያከናውንበት መንገድ ከሁሉ የተሻለ መሆኑን እንደምናምን ያሳያል።

አምላክ ለሕዝቦቹ የሰጠውን ኃላፊነት መወጣት

8. የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ስለ ሌሎች ማሰብ ነበረባቸው የምንለው ለምንድን ነው?

8 አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ስለ ሌሎች ማሰብ እንዳለባቸው የሚጠቁም መመሪያ የሰጣቸው ገና በኤደን ገነት ውስጥ ብቻቸውን እያሉ ነበር። ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን የባረካቸው ሲሆን እንዲባዙ፣ ምድርን እንዲሞሏትና እንዲገዟትም ነግሯቸዋል። (ዘፍ. 1:28) ፈጣሪያችን የፍጥረታቱ ደህንነት በጥልቅ እንደሚያሳስበው ሁሉ የመጀመሪያዎቹ ወላጆችም ወደፊት ስለሚወልዷቸው ልጆች ደስታ ማሰብ ነበረባቸው። ምድር ለአዳም ዘሮች ምቹ መኖሪያ እንድትሆን ለማድረግ ገነትን በመላው ምድር ላይ ማስፋፋት ይጠበቅባቸው ነበር። ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚመጣው የአዳም ቤተሰብ ይህን መጠነ ሰፊ ሥራ ለማከናወን ተባብሮ መሥራት ነበረበት።

9. ገነትን የማስፋፋቱ ሥራ አስደሳች ሊሆን ይችል ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

9 ፍጹም የሆኑ የሰው ልጆች መላዋን ምድር ገነት ለማድረግና የይሖዋን ዓላማ ለመፈጸም ከእሱ ጋር በቅርበት መሥራት ያስፈልጋቸው ነበር፤ ይህን ካደረጉ ወደ አምላክ እረፍት መግባት ይችላሉ። (ዕብ. 4:11) ይህ ሥራ ምን ያህል አስደሳችና አርኪ ይሆን እንደነበር መገመት አያዳግትም! የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ለሌሎች ደህንነት ማሰባቸው የይሖዋን የተትረፈረፈ በረከት ያስገኝላቸው ነበር።

10, 11. ምሥራቹን እንድንሰብክና ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠንን ተልእኮ መወጣት የምንችለው እንዴት ነው?

10 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ለሕዝቦቹ ሰጥቷቸዋል። ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ስለ ሌሎች ደህንነት ከልብ ማሰብ ይኖርብናል። በዚህ ሥራ መጽናት የምንችለውም ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ካለን ማለትም አምላክንና ሰዎችን የምንወድ ከሆነ ብቻ ነው።

11 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ጳውሎስ ራሱንና የእምነት አጋሮቹን አስመልክቶ ሲናገር “ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን” ብሏል፤ ይህን ያለው የመንግሥቱን እውነት ዘር የመዝራትና የማጠጣት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ስለነበር ነው። (1 ቆሮ. 3:6, 9) እኛም በተመሳሳይ አምላክ ከሰጠን የስብከት ሥራ ጋር በተያያዘ ጊዜያችንን፣ ሀብታችንንና ኃይላችንን ምንም ሳንሰስት በልግስና በመስጠት ‘ከአምላክ ጋር አብረን መሥራት’ እንችላለን። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!

ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ መርዳት ታላቅ ደስታ ያስገኛል (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት)

12, 13. ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ምን በረከቶች ያስገኛል?

12 በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ጊዜያችንንና ጉልበታችንን በልግስና መስጠታችን ታላቅ ደስታ ያስገኝልናል። ጥሩ እድገት የሚያደርጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን የመምራት አጋጣሚ ያገኙ በርካታ ወንድሞችና እህቶች በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። ሰዎች መንፈሳዊውን እውነት ሲረዱ፣ እምነታቸው እየተጠናከረ ሲሄድ፣ በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ ሲያደርጉና ያገኙትን እውነት ለሌሎች ሲያካፍሉ የማየትን ያህል በጣም የሚያስደስት ነገር የለም። ኢየሱስም ቢሆን፣ እንዲሰብኩ የላካቸው 70 ደቀ መዛሙርት ባገኙት መልካም ውጤት የተነሳ ‘ደስ እያላቸው ሲመለሱ’ በማየቱ ሐሴት አድርጓል።—ሉቃስ 10:17-21

13 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ምሥራቹ በሰዎች ሕይወት ላይ የሚያሳድረውን በጎ ተጽዕኖ ማየታቸው ያስደስታቸዋል። አገልግሎቷን ለማስፋት ስትል በምሥራቅ አውሮፓ ወደሚገኝ አንድ አካባቢ የተዛወረችውን አና የተባለች ነጠላ እህት ተሞክሮ እንመልከት። * ይህች ወጣት እህት እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “አሁን በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን የመምራት መብት አግኝቻለሁ፤ ይህ ለእኔ ልዩ አጋጣሚ ነው። አገልግሎቴ ታላቅ ደስታ አስገኝቶልኛል። ከአገልግሎት በኋላ ወደ ቤቴ ስመለስ ስለ ችግሮቼ እንኳ የማስብበት ጊዜ የለኝም። የማስበው ጥናቶቼን ስለሚያስጨንቋቸው ነገሮችና ስላሉባቸው ችግሮች ነው። እነሱን ማበረታታትና መርዳት የምችልባቸውን መንገዶች እፈልጋለሁ። በመሆኑም ‘ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል’ የሚለው ሐሳብ እውነት መሆኑን ይበልጥ ተረድቻለሁ።”—ሥራ 20:35

በክልላችን ውስጥ ያለውን እያንዳንዱን ቤት ስናንኳኳ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት እንዲሰሙ አጋጣሚ እየሰጠናቸው ነው (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)

14. ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ብዙ ባይሆኑም በአገልግሎታችን ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

14 መልእክቱን መስማት የማይፈልጉ ሰዎችን ጨምሮ ሁሉም ሰው ምሥራቹን ለመስማት አጋጣሚ እንዲያገኝ ማድረጋችን ደስታ ያስገኝልናል። ተልእኳችን ለነቢዩ ሕዝቅኤል ከተሰጠው ሥራ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ይሖዋ ሕዝቅኤልን “ቢሰሙም ባይሰሙም ቃሌን ንገራቸው” ብሎት ነበር። (ሕዝ. 2:7፤ ኢሳ. 43:10) ሰዎች ምሥራቹን ባይቀበሉም እንኳ ይሖዋ የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። (ዕብራውያን 6:10ን አንብብ።) ይህን የተገነዘበ አንድ አስፋፊ የአገልግሎት እንቅስቃሴውን አስመልክቶ ሲጽፍ “የምንተክለው፣ የምናጠጣውም ሆነ የምንጸልየው ይሖዋ የግለሰቡን ፍላጎት እንደሚያሳድገው ተስፋ በማድረግ ነው” ብሏል።—1 ቆሮ. 3:6

ደስተኛ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

15. ብዙዎች ለምናሳየው ልግስና ምን ምላሽ ይሰጣሉ? የእነሱ ምላሽ በእኛ ላይ ተጽዕኖ ማድረግ የሌለበትስ ለምንድን ነው?

15 ኢየሱስ ለጋሶች በመሆን ደስታ እንድናገኝ ይፈልጋል። ብዙዎች፣ ሌሎች ልግስና ሲያሳዩአቸው መልካም ምላሽ ይሰጣሉ።ኢየሱስ የሚከተለውን ምክር ሰጥቶናል፦ “ለሰዎች ስጡ፤ እነሱም ይሰጧችኋል። ተትረፍርፎ እስኪፈስ ድረስ በተጠቀጠቀና በተነቀነቀ ጥሩ መስፈሪያ ሰፍረው በእቅፋችሁ ይሰጧችኋል። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ መልሰው ይሰፍሩላችኋል።” (ሉቃስ 6:38) እርግጥ ነው፣ ለምናሳየው ልግስና አመስጋኝ የሚሆኑት ሁሉም ሰዎች አይደሉም፤ ሆኖም ለተደረገላቸው ነገር አድናቆት የሚያሳዩ ሰዎች ልክ እንደ እኛ ለሌሎች በልግስና ለመስጠት ሊነሳሱ ይችላሉ። ስለዚህ ሰዎች አድናቆት አሳዩም አላሳዩ በልግስና ከመስጠት ወደኋላ አትበሉ። የምታከናውኑት አንድ የልግስና ተግባር እንኳ በሰዎች ላይ ምን ያህል በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አታውቁም።

16. በልግስና ለመስጠት የሚያነሳሳን ምን ሊሆን ይገባል?

16 እውነተኛ ልግስና የሚያሳይ ሰው በምላሹ የሆነ ነገር ለማግኘት አይጠብቅም። ኢየሱስ ይህን ሐሳብ በአእምሮው በመያዝ የሚከተለውን ትምህርት ሰጥቷል፦ “ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችን፣ ሽባዎችን፣ አንካሶችንና ዓይነ ስውራንን ጥራ፤ ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ ደስተኛ ትሆናለህ።” (ሉቃስ 14:13, 14) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “ለጋስ ሰው ይባረካል” ብሏል። ሌላኛው ደግሞ “ለተቸገረ ሰው የሚያስብ ደስተኛ ነው” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 22:9፤ መዝ. 41:1) በእርግጥም ሌሎችን መርዳት ደስታ ስለሚያስገኝ በልግስና መስጠት ይኖርብናል።

17. ደስተኛ ለመሆን የትኞቹን ነገሮች መስጠት እንችላለን?

17 ጳውሎስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” በማለት ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ ጠቅሷል፤ ይህ ጥቅስ የሚናገረው ስለ ቁሳዊ ነገሮች ብቻ ሳይሆን ለሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ማበረታቻ፣ መመሪያና ሌላ ዓይነት ድጋፍ ስለመስጠት ጭምር ነው። (ሥራ 20:31-35) ይህ ሐዋርያ ጊዜን፣ ጉልበትን፣ ትኩረትን እና ፍቅርን በልግስና በመስጠት ረገድ በንግግሩም ሆነ በተግባሩ ምሳሌ ትቶልናል።

18. በርካታ ተመራማሪዎች ከልግስና ጋር በተያያዘ ምን መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል?

18 ስለ ሰዎች ባሕርይ የሚያጠኑ ተመራማሪዎችም መስጠት ሰዎችን ደስተኛ እንደሚያደርጋቸው ተገንዝበዋል። “አንዳንድ ሰዎች፣ ለሌሎች መልካም ካደረጉ በኋላ ደስታቸው በጣም እንደጨመረ ተናግረዋል” በማለት አንድ ጽሑፍ ገልጿል። ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ሰዎች ሌሎችን መርዳታቸው ሕይወታቸው “ይበልጥ ዓላማና ትርጉም ያለው እንዲሆን በማድረግ” ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፤ “ምክንያቱም መሠረታዊ የሆነው የሰው ልጆች ፍላጎት እንዲሟላ ያደርጋል።” በመሆኑም አንዳንድ ባለሙያዎች ሰዎች ጤንነታቸው እንዲሻሻልና ደስታቸው እንዲጨምር ከፈለጉ ማኅበረሰቡን በሚጠቅሙ ሥራዎች ላይ በፈቃደኝነት እንዲሳተፉ ያበረታታሉ። እርግጥ ይህ ሐሳብ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ያስጻፈው መጽሐፍ እንደሆነ አምነው ለሚቀበሉ ሰዎች የሚያስደንቅ አይደለም።—2 ጢሞ. 3:16, 17

ምንጊዜም ለጋስ መሆን

19, 20. ለጋስ እንድንሆን የሚያነሳሱን አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

19 የምንኖረው የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ ማስቀደም በሚፈልጉ ሰዎች መካከል ስለሆነ ምንጊዜም የልግስናን መንፈስ ማሳየት ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ኢየሱስ ሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት ይሖዋን በሙሉ ልባችን፣ በሙሉ ነፍሳችን፣ በሙሉ አእምሯችንና በሙሉ ኃይላችን መውደድ እንዲሁም ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን መውደድ እንደሆኑ ተናግሯል። (ማር. 12:28-31) በዚህ ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋን የሚወዱ ሰዎች እሱን ለመምሰል ጥረት ያደርጋሉ። ይሖዋ ሆነ ኢየሱስ ለሌሎች በልግስና መስጠት ያስደስታቸዋል። እኛም ተመሳሳይ ነገር እንድናደርግ ያበረታቱናል፤ ምክንያቱም ይህ እውነተኛ ደስታ እንደሚያስገኝልን ያውቃሉ። ከአምላክም ሆነ ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት የልግስናን መንፈስ ለማንጸባረቅ የምንጥር ከሆነ ይሖዋን እናስከብራለን፤ እንዲሁም ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን እንጠቅማለን።

20 ሌሎችን በተለይ ደግሞ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለመርዳት አሁንም ቢሆን ጥረት እያደረግን እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። (ገላ. 6:10) እንዲህ ማድረጋችንን ከቀጠልን ሌሎች እንደሚወዱንና ጥረታችንን እንደሚያደንቁ መተማመን እንችላለን፤ ይህ ደግሞ ደስታ ያስገኝልናል። ምሳሌ 11:25 “ለጋስ ሰው ይበለጽጋል፤ ሌሎችን የሚያረካም እሱ ራሱ ይረካል” ይላል። ከክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን ጋር በተያያዘ ራሳችንን ሳንቆጥብ ለሌሎች መስጠት እንዲሁም ደግነትና ልግስና ማሳየት የምንችልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ፤ ይህን ማድረጋችን መልሶ ይክሰናል። የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ባሕርያት ማንጸባረቅ የምንችልባቸውን የተለያዩ መንገዶች ያብራራል።

^ አን.13 ስሟ ተቀይሯል።