በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት አትፍረዱ

የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት አትፍረዱ

“የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት አትፍረዱ፤ ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ፍረዱ።”—ዮሐ. 7:24

መዝሙሮች፦ 142, 123

1. ኢሳይያስ ስለ ኢየሱስ ምን ትንቢት ተናግሯል? ይህ ትንቢት የሚያበረታታን ለምንድን ነው?

ኢሳይያስ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ትንቢት ልባችንን የሚያረጋጋና ተስፋ የሚሰጥ ነው። ኢሳይያስ እንደተናገረው፣ ኢየሱስ “ዓይኑ እንዳየ አይፈርድም ወይም ጆሮው በሰማው ነገር ላይ ብቻ ተመሥርቶ አይወቅስም።” ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ “ለችግረኞች በትክክል ይፈርዳል።” (ኢሳ. 11:3, 4) ይህን ማወቃችን የሚያበረታታን ለምንድን ነው? የምንኖረው አድልዎና ጭፍን ጥላቻ በተንሰራፋበት ዓለም ውስጥ ስለሆነ ነው። በውጫዊ ገጽታ ላይ ተመሥርቶ የማይፈርደው ፍጹም ዳኛ የሚያስተዳድርበትን ጊዜ ሁላችንም በጉጉት እንጠባበቃለን!

2. ኢየሱስ ምን እንድናደርግ አዞናል? በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

2 ሁላችንም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ከምናገኛቸው የተለያዩ ሰዎች ጋር በተያያዘ የራሳችን ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን። ያም ቢሆን እንደ ኢየሱስ ፍጹማን ስላልሆንን ስለ ሌሎች ያለን አመለካከት የተዛባ ሊሆን ይችላል። የሰዎች ውጫዊ ገጽታ ስለ እነሱ በሚኖረን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት “የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት አትፍረዱ፤ ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ፍረዱ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷል። (ዮሐ. 7:24) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ ኢየሱስ የእሱን ምሳሌ በመከተል በሰዎች ውጫዊ ገጽታ ላይ ተመሥርተን ከመፍረድ እንድንቆጠብ ይፈልጋል። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ስለ ሌሎች ባለን አመለካከት ላይ ብዙውን ጊዜ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሦስት ነገሮችን እንመለከታለን፤ እነሱም የሰዎች ዘር ወይም ብሔር፣ የኑሮ ደረጃ እንዲሁም ዕድሜ ናቸው። በተጨማሪም ከሦስቱም ነገሮች ጋር በተያያዘ የኢየሱስን ትእዛዝ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

ዘር ወይም ብሔር አይታችሁ አትፍረዱ

3, 4. (ሀ) ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ አሕዛብ የነበረውን አመለካከት እንዲያስተካከል ያደረገው ምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ጴጥሮስ የትኛውን አዲስ ግንዛቤ እንዲያገኝ ይሖዋ ረድቶታል?

3 ሐዋርያው ጴጥሮስ በቂሳርያ ወደሚኖረው ቆርኔሌዎስ የተባለ ከአሕዛብ ወገን የሆነ ሰው ቤት እንዲሄድ በተነገረው ጊዜ ወደ አእምሮው የተለያዩ ሐሳቦች መጥተው መሆን አለበት። (ሥራ 10:17-29) በዘመኑ እንደነበሩ ሌሎች አይሁዳውያን ሁሉ ጴጥሮስም አሕዛብ ርኩስ እንደሆኑ ከልጅነቱ አንስቶ ያምን ነበር። ይሁን እንጂ ይህን አመለካከቱን እንዲያስተካክል የሚያደርጉ ነገሮች አጋጠሙት። ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች ጴጥሮስ ጋ ከመድረሳቸው በፊት ሐዋርያው አንድ ራእይ ተመልክቶ ነበር። (ሥራ 10:9-16) ጴጥሮስ ያየው ራእይ ምን ነበር? እንደ ርኩስ በሚቆጠሩ እንስሳት የተሞላ ጨርቅ የሚመስል ነገር ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤ ከዚያም ከሰማይ አንድ ድምፅ “ጴጥሮስ፣ ተነሳና አርደህ ብላ!” አለው። ጴጥሮስ ግን ይህን ለማድረግ በጭራሽ ፈቃደኛ አለመሆኑን ገለጸ። በዚህ ጊዜ ከሰማይ የመጣው ድምፅ “አምላክ ንጹሕ ያደረገውን ነገር ርኩስ ነው ማለትህን ተው” አለው። ጴጥሮስ፣ ይህ ድምፅ ምን ሊነግረው እንደፈለገ ግራ ተጋብቶ እያለ ቆርኔሌዎስ የላካቸው መልእክተኞች መጡ። ጴጥሮስም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የተሰጠውን መመሪያ በመከተል ከመልእክተኞቹ ጋር ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት ሄደ።

4 ጴጥሮስ “የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት” ቢፈርድ ኖሮ በምንም ዓይነት ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት አይገባም ነበር። ምክንያቱም ለአይሁዳውያን ወደ አሕዛብ ቤት መግባት ጨርሶ የማይታሰብ ነገር ነበር። ታዲያ ጴጥሮስ በወቅቱ ሰፍኖ የነበረውን ሥር የሰደደ ጭፍን ጥላቻ አሸንፎ ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት የገባው ለምንድን ነው? ቀደም ሲል ያየው ራእይ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ የሰጠው ማረጋገጫ አመለካከቱን እንዲቀይር ስለረዳው ነው። ጴጥሮስ፣ ቆርኔሌዎስ የተናገረውን ከሰማ በኋላ በጣም ስለተገረመ በመንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “እነሆ፣ አምላክ እንደማያዳላ በእርግጥ አስተዋልኩ፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።” (ሥራ 10:34, 35) ጴጥሮስ በዚህ ወቅት ያገኘው አዲስ ግንዛቤ ልቡን ነክቶት መሆን አለበት፤ ደግሞም ይህ ሁሉንም ክርስቲያኖች የሚመለከት ጉዳይ ነው! እንዴት?

5. (ሀ) ይሖዋ ሁሉም ክርስቲያኖች የትኛውን እውነት እንዲገነዘቡ ይፈልጋል? (ለ) እውነትን ብናውቅም እንኳ በውስጣችን ምን ሊኖር ይችላል?

5 ይሖዋ የማያዳላ አምላክ መሆኑን ሁሉም ክርስቲያኖች እንዲገነዘቡ ለማድረግ በጴጥሮስ ተጠቅሟል። የዘር፣ የብሔር፣ የጎሳ፣ የአገር ወይም የቋንቋ ልዩነት በይሖዋ ፊት ምንም ቦታ የለውም። አምላክን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ማንኛውም ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው። (ገላ. 3:26-28፤ ራእይ 7:9, 10) ይህ እውነት መሆኑን አንተም እንደምትስማማ ጥርጥር የለውም። ይሁንና ያደግከው ጭፍን ጥላቻ በተስፋፋበት አካባቢ ወይም ቤተሰብ ውስጥ ቢሆንስ? አንተ በግልህ አድልዎ የማታደርግ ሰው እንደሆንክ ታስብ ይሆናል፤ ሆኖም በውስጥህ የቀረ የጭፍን ጥላቻ ርዝራዥ ሊኖር ይችላል። ይሖዋ የማያዳላ አምላክ መሆኑን ለሌሎች የማሳወቅ መብት አግኝቶ የነበረው ጴጥሮስም እንኳ ጭፍን ጥላቻ እንዳለው የሚያሳይ ነገር ከጊዜ በኋላ አድርጓል። (ገላ. 2:11-14) ታዲያ ኢየሱስ እንደነገረን የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት ከመፍረድ መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው?

6. (ሀ) ጭፍን ጥላቻን ከውስጣችን ነቅለን ለማውጣት ምን ይረዳናል? (ለ) ኃላፊነት ያለው አንድ ወንድም የጻፈው ሪፖርት ምን አመለካከት እንደነበረው ያሳያል?

6 በውስጣችን የቀረ ጭፍን ጥላቻ ይኖር እንደሆነ ለማወቅ የአምላክን ቃል በመጠቀም ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመር ይኖርብናል። (መዝ. 119:105) በተጨማሪም የቅርብ ጓደኛችን ጭፍን ጥላቻ እንዳለን ካስተዋለ እንዲነግረን ልንጠይቀው እንችላለን፤ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዳለን ለራሳችን ላይታወቀን ይችላል። (ገላ. 2:11, 14) መሠረተ ቢስ ጥላቻ በውስጣችን ለረጅም ጊዜ ከመቆየቱ የተነሳ እንዲህ ያለ አመለካከት እንዳለን እንኳ በቀላሉ አናስተውል ይሆናል። ኃላፊነት ያለው አንድ ወንድም ያጋጠመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ይህ ወንድም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ያሉ አንድ ግሩም ባልና ሚስትን በተመለከተ ለቅርንጫፍ ቢሮው ሪፖርት ጽፎ ነበር። ባልየው ብዙዎች ዝቅ አድርገው የሚመለከቱት ጎሳ አባል ነው። ሪፖርቱን የጻፈው ወንድም ይህን ጎሳ በተመለከተ እሱ ራሱ ጭፍን ጥላቻ እንዳለው አልተገነዘበም ነበር። በሪፖርቱ ላይ፣ ባልየው ያሉትን በርካታ መልካም ጎኖች ከጠቀሰ በኋላ መደምደሚያው ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ወንድም [የዚህ ጎሳ አባል] ቢሆንም እንኳ ለየት ያለ ምግባርና አኗኗር አለው፤ ይህም አንድ ሰው [የዚህ ጎሳ አባል] ስለሆነ ብቻ እንደ ብዙዎቹ [የዚህ ጎሳ አባላት] ይቆሽሻል ወይም ይዝረከረካል ማለት እንዳልሆነ ያሳያል።” ነጥቡ ምንድን ነው? በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ምንም ያህል ኃላፊነት ቢኖረን በውስጣችን ጭፍን ጥላቻ መኖር አለመኖሩን ለማወቅ ራሳችንን በሚገባ መመርመር እንዲሁም ሌሎች የሚሰጡንን ሐሳብ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን አለብን። ሌላስ ምን ማድረግ እንችላለን?

7. ልባችንን ወለል አድርገን መክፈት የምንችለው እንዴት ነው?

7 ልባችንን ወለል አድርገን ከከፈትን ልባችን በጭፍን ጥላቻ ፋንታ በፍቅር ይሞላል። (2 ቆሮ. 6:11-13) የአንተ ዓይነት ዘር፣ ብሔር፣ አገር፣ ጎሳ ወይም ቋንቋ ካላቸው ሰዎች ጋር ብቻ መቀራረብ ይቀናሃል? ከሆነ ልብህን ወለል አድርገህ መክፈት ይኖርብሃል። ከአንተ የተለየ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸውን ወንድሞች አብረውህ እንዲያገለግሉ ለምን አትጠይቃቸውም? ቤትህ ልትጋብዛቸውስ ትችል ይሆን? (ሥራ 16:14, 15) እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ልብህ በፍቅር ስለሚሞላ ለጭፍን ጥላቻ ቦታ አይኖረውም። እርግጥ በውጫዊ ገጽታ ላይ ተመሥርተን በሰዎች ላይ እንድንፈርድ የሚያደርጉን ሌሎች ነገሮችም አሉ። ከእነዚህ አንዱ የኑሮ ደረጃ ነው።

የኑሮ ደረጃ አይታችሁ አትፍረዱ

8. አንድ ሰው ሀብታም ወይም ድሃ መሆኑ ለእሱ ባለን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ዘሌዋውያን 19:15 የሚያሳየው እንዴት ነው?

8 ስለ ሌሎች ባለን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው ሌላው ነገር ደግሞ የሰዎች የኑሮ ደረጃ ነው። ዘሌዋውያን 19:15 “ለድሃው አታዳላ ወይም ባለጸጋውን ከሌሎች አስበልጠህ አትመልከት። ለባልንጀራህ ፍትሐዊ ፍርድ ፍረድ” ይላል።

9. ሰለሞን ስለ የትኛው አሳዛኝ እውነታ ጽፏል? ሰለሞን ከተናገረው ሐሳብ ምን እንማራለን?

9 አንድ ሰው ባለጸጋ አሊያም ድሃ መሆኑ ለእሱ ባለን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው እንዴት ነው? ሰለሞን፣ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎችን በተመለከተ አንድ አሳዛኝ እውነታ ጽፏል። በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ በምሳሌ 14:20 ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ድሃ በባልንጀሮቹ ዘንድ እንኳ የተጠላ ነው፤ የባለጸጋ ወዳጆች ግን ብዙ ናቸው።” ከዚህ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? እኛም ጥንቃቄ ካላደረግን ሀብታም ከሆኑ ወንድሞች ጋር ወዳጅነት የመመሥረት፣ ድሃ የሆኑ ወንድሞችን ግን ብዙም ያለመቅረብ አዝማሚያ ሊታይብን ይችላል። ለሌሎች የምንሰጠው ቦታ በቁሳዊ ንብረታቸው ላይ የተመሠረተ መሆኑ በጣም አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?

10. ያዕቆብ ስለ የትኛው ችግር ተናግሯል?

10 በቁሳዊ ንብረት ላይ ተመሥርተን በሌሎች ላይ የምንፈርድ ከሆነ በጉባኤ ውስጥ የመደብ ልዩነት እንዲፈጠር ልናደርግ እንችላለን። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ያለው አመለካከት በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩ አንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ መከፋፈል እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጿል። (ያዕቆብ 2:1-4ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜም እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በጉባኤዎቻችን ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር መጠንቀቅ አለብን። ታዲያ የሰዎችን ውጫዊ ገጽታ አይቶ የመፍረድን ዝንባሌ ማስወገድ የምንችለው እንዴት ነው?

11. አንድ ሰው ከይሖዋ ጋር ያለው ዝምድና በቁሳዊ ንብረቱ ላይ የተመካ ነው? አብራራ።

11 ለወንድሞቻችን የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል። አንድ ሰው ሀብታም ወይም ድሃ መሆኑ በይሖዋ ፊት የተለየ ቦታ አያሰጠውም። ብዙ ወይም ጥቂት ቁሳዊ ንብረት ያለን መሆኑ ከይሖዋ ጋር በሚኖረን ግንኙነት ረገድ አንዳች ለውጥ አያመጣም። እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ “ሀብታም ሰው ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት እጅግ አስቸጋሪ ይሆንበታል” ብሏል፤ ሆኖም ኢየሱስ ሀብታም ሰው ጨርሶ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም እንዳላለ ልብ ማለት ያስፈልጋል። (ማቴ. 19:23) በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ “እናንተ ድሆች የሆናችሁ ደስተኞች ናችሁ፤ የአምላክ መንግሥት የእናንተ ነውና” ብሏል። (ሉቃስ 6:20) ይህ ሲባል ግን ድሃ የሆኑ ሰዎች በሙሉ የተለየ በረከት አግኝተዋል ወይም የኢየሱስን ትምህርት ተቀብለዋል ማለት አይደለም። ድሃ የሆኑ ብዙ ሰዎች ኢየሱስን አልተቀበሉትም። ነጥቡ ግልጽ ነው፦ የአንድን ሰው ቁሳዊ ንብረት በመመልከት ግለሰቡ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና መገምገም አንችልም።

12. መጽሐፍ ቅዱስ ሀብታምም ሆነ ድሃ ለሆኑ ክርስቲያኖች ምን ማሳሰቢያ ይሰጣል?

12 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሀብታም አሊያም ድሃ የሆኑ በርካታ ወንድሞችና እህቶች አሉ፤ ሁሉም ይሖዋን የሚወዱ ከመሆኑም ሌላ በሙሉ ልባቸው ያገለግሉታል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሀብታም የሆኑ ክርስቲያኖች “ተስፋቸውን አስተማማኝነት በሌለው ሀብት ላይ ሳይሆን . . . [በአምላክ] ላይ እንዲጥሉ” ይመክራል። (1 ጢሞቴዎስ 6:17-19ን አንብብ።) በሌላ በኩል ደግሞ የአምላክ ቃል፣ ሀብታም ድሃ ሳይል ሁሉም ክርስቲያኖች የገንዘብ ፍቅር እንዳይጠናወታቸው መጠንቀቅ እንዳለባቸው ያሳስባል። (1 ጢሞ. 6:9, 10) በእርግጥም ለወንድሞቻችን የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ካለን በኑሮ ደረጃቸው ላይ ተመሥርተን በእነሱ ላይ አንፈርድም። ይሁንና በዕድሜ ላይ ተመሥርቶ በሌሎች ላይ ስለመፍረድስ ምን ማለት ይቻላል? ይህን ማድረግ ተገቢ ነው? እስቲ እንመልከት።

ዕድሜ አይታችሁ አትፍረዱ

13. ቅዱሳን መጻሕፍት በዕድሜ ለገፉ ክርስቲያኖች አክብሮት ማሳየትን በተመለከተ ምን ያስተምሩናል?

13 ቅዱሳን መጻሕፍት በዕድሜ ለገፉ ሰዎች ተገቢውን አክብሮት እንድናሳይ በተደጋጋሚ ይመክሩናል። ዘሌዋውያን 19:32 “በሸበተው ሰው ፊት ተነስ፤ አረጋዊውንም አክብር፤ አምላክህን ፍራ” ይላል። በተመሳሳይም ምሳሌ 16:31 “ሽበት በጽድቅ መንገድ ሲገኝ የውበት ዘውድ ነው” በማለት ይናገራል። ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ ጢሞቴዎስ ሽማግሌ የሆኑ ወንድሞችን በኃይለ ቃል እንዳይናገራቸው ከዚህ ይልቅ እንደ አባት እንዲቆጥራቸው መክሮታል። (1 ጢሞ. 5:1, 2) ጢሞቴዎስ በዕድሜ ለገፉት ለእነዚህ ወንድሞች መመሪያ ለመስጠት የተወሰነ ሥልጣን ቢኖረውም ወንድሞቹን በደግነትና በአክብሮት መያዝ ይጠበቅበት ነበር።

14. በዕድሜ ለሚበልጠን ሰው ምክር ወይም ተግሣጽ መስጠታችን ተገቢ የሚሆነው መቼ ነው?

14 ይሁንና ይህን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ የሚጠበቅብን እስከ ምን ድረስ ነው? ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ሆን ብሎ ኃጢአት የሚሠራ ወይም ይሖዋን የሚያሳዝን አካሄድ የሚከተል ቢሆን ግለሰቡ በዕድሜ ስለገፋ ብቻ በዝምታ ማለፍ እንዳለብን ሊሰማን ይገባል? ይሖዋ የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት አይፈርድም፤ ስለዚህ ሆን ብሎ ኃጢአት የሚሠራን ሰው በዕድሜ ስለገፋ ብቻ በቸልታ አያልፈውም። በኢሳይያስ 65:20 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ልብ እንበል፤ ጥቅሱ “ኃጢአተኛው መቶ ዓመት ቢሞላውም እንኳ ይረገማል” ይላል። ሕዝቅኤል በተመለከተው ራእይ ላይም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል መሠረታዊ ሥርዓት እናገኛለን። (ሕዝ. 9:5-7) በመሆኑም ምንጊዜም ቢሆን በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው ጉዳይ ከዘመናት በፊት ለነበረው ለይሖዋ አምላክ አክብሮት ማሳየታችን ነው። (ዳን. 7:9, 10, 13, 14) ለይሖዋ አክብሮት የምናሳይ ከሆነ አንድ ሰው ዕድሜው ምንም ያህል ቢሆን ምክር በሚያስፈልገው ጊዜ ምክር ከመስጠት ወደኋላ አንልም።—ገላ. 6:1

ወጣት ወንድሞችን ታከብራቸዋለህ? (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)

15. ለወጣት ወንድሞች አክብሮት ማሳየትን በተመለከተ ከሐዋርያው ጳውሎስ ምን እንማራለን?

15 በጉባኤ ውስጥ ለሚገኙ ወጣት ወንድሞችስ ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ሐዋርያው ጳውሎስ ለወጣቱ ጢሞቴዎስ “ወጣት በመሆንህ ማንም ሰው ሊንቅህ አይገባም። ከዚህ ይልቅ ታማኞች ለሆኑት በንግግር፣ በምግባር፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽሕና አርዓያ ሁን” በማለት ጽፎለታል። (1 ጢሞ. 4:12) ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት ጢሞቴዎስ በ30ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ሳይሆን አይቀርም። ያም ሆኖ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ከባድ ኃላፊነቶችን ሰጥቶት ነበር። ጳውሎስ ይህን ምክር የሰጠበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን ከተናገረው ሐሳብ የምናገኘው ትምህርት አለ። ወጣት ወንድሞችን ዕድሜያቸውን በማየት ብቻ ልንገመግማቸው አይገባም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎቱን በሙሉ ያከናወነው በ30ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ እያለ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል።

16, 17. (ሀ) አንድ ወንድም የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆኖ ለማገልገል ብቃቱን ማሟላቱን ሽማግሌዎች የሚገመግሙት ምንን መሠረት በማድረግ ነው? (ለ) የግል አመለካከታችን ወይም ባሕላችን ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር ሊጋጭ የሚችለው እንዴት ነው?

16 በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ ሰዎች ለወጣት ወንዶች አክብሮት ማሳየት ይከብዳቸዋል። እንዲህ ባሉት ባሕሎች ውስጥ የሚገኙ የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ ብቃቱን የሚያሟሉ ወጣት ወንድሞች የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆነው እንዲሾሙ የድጋፍ ሐሳብ ለማቅረብ ያመነቱ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሁሉም ሽማግሌዎች ልብ ሊሉት የሚገባ ነገር አለ፤ ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ወንድ የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆኖ ለመሾም የሆነ ዕድሜ ላይ መድረስ እንዳለበት የማይናገር መሆኑን ነው። (1 ጢሞ. 3:1-10, 12, 13፤ ቲቶ 1:5-9) አንድ የጉባኤ ሽማግሌ በባሕል ላይ ተመሥርቶ ሕግ የሚያወጣ ከሆነ የሚመራው በመጽሐፍ ቅዱስ አይደለም ማለት ነው። ሽማግሌዎች ወጣት ወንዶችን የሚገመግሙት፣ በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙት መሥፈርቶች መሠረት እንጂ በግል አመለካከታቸው ወይም በባሕላቸው ላይ ተመሥርተው ሊሆን አይገባም።—2 ጢሞ. 3:16, 17

17 እንዲህ ያለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ አመለካከት ብቃት ያላቸው ወንድሞች አንዳንድ መብቶችን እንዳያገኙ እንቅፋት ሊሆን ይችላል። አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ በአንድ አገር ያለ ጥሩ ብቃት ያለው የጉባኤ አገልጋይ ከበድ ያሉ ኃላፊነቶች ተሰጥተውት ነበር። የጉባኤው ሽማግሌዎች ይህ ወጣት ወንድም፣ ሽማግሌ ለመሆን የሚያስፈልጉትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ምክንያታዊ በሆነ ደረጃ እንዳሟላ ቢስማሙም ይህ ወንድም እንዲሾም የድጋፍ ሐሳብ አላቀረቡም። በዕድሜ የገፉ አንዳንድ ሽማግሌዎች፣ ወንድም በጣም ወጣት ስለሚመስል እንደ ሽማግሌ ላይታይ እንደሚችል ተሰምቷቸው ነበር። ወንድም፣ ወጣት በመምሰሉ ምክንያት ብቻ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ አለመሾሙ ያሳዝናል። አሁን የጠቀስነው አንድ ምሳሌ ብቻ ቢሆንም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተገኙ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ብዙዎች እንዲህ ያለ አመለካከት አላቸው። በግል አመለካከታችን ወይም በባሕላችን ሳይሆን በቅዱሳን መጻሕፍት መመራታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ኢየሱስ የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት እንዳንፈርድ የሰጠንን ምክር የምንታዘዘው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው።

በጽድቅ ፍረዱ

18, 19. ለሌሎች የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ምን ይረዳናል?

18 ፍጹማን ባንሆንም እንኳ እንደ ይሖዋ ሌሎችን ከአድልዎ ነፃ በሆነ መንገድ መመልከት እንችላለን። (ሥራ 10:34, 35) እንዲህ ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ግን የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ እንዲሁም በአምላክ ቃል ውስጥ ለሚገኙት ማሳሰቢያዎች ምንጊዜም ትኩረት መስጠት ይኖርብናል። እነዚህን ማሳሰቢያዎች ተግባራዊ ማድረጋችን ኢየሱስ የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት እንዳንፈርድ የሰጠንን መመሪያ ለመታዘዝ ያስችለናል።—ዮሐ. 7:24

19 በቅርቡ ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመላው የሰው ዘር ላይ ይፈርዳል፤ የሚፈርደውም ዓይኑ እንዳየ ወይም ጆሮው በሰማው ነገር ላይ ብቻ ተመሥርቶ ሳይሆን በጽድቅ ይሆናል። (ኢሳ. 11:3, 4) በእርግጥም ያንን ጊዜ ለማየት እንናፍቃለን!