በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትዕግሥት—በተስፋ መጽናት

ትዕግሥት—በተስፋ መጽናት

የምንኖረው በጣም አስቸጋሪ በሆኑት “የመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ በመሆኑ የይሖዋ ሕዝቦች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ትዕግሥት ማዳበር ያስፈልጋቸዋል። (2 ጢሞ. 3:1-5) በዙሪያችን ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች ራስ ወዳዶች፣ ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑና ራሳቸውን የማይገዙ ናቸው። እንደዚህ ያሉትን ባሕርያት የሚያንጸባርቁ ሰዎች ትዕግሥት የሚባል ነገር የላቸውም። ከዚህ አንጻር እያንዳንዱ ክርስቲያን እንደሚከተለው በማለት ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል፦ ‘በዓለም ላይ እንዳሉት እንደ አብዛኞቹ ሰዎች ትዕግሥት አጣለሁ? ትዕግሥተኛ መሆን ሲባል በእርግጥ ምን ማለት ነው? ደግሞስ በሁሉም የሕይወቴ ዘርፎች ይህን ግሩም ባሕርይ ለማንጸባረቅ ምን ማድረግ እችላለሁ?’

ትዕግሥት ምንድን ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትዕግሥት የሚለው ቃል የተሠራበት አንድን ፈታኝ ሁኔታ እንዲሁ ችሎ ከማለፍ ያለፈ ነገርን ለማመልከት ነው። ታጋሽ የሆነ ሰው የሚጸናው በዓላማ ነው፤ ትዕግሥተኛ ሰው ነገሮች እንደሚሻሻሉ ተስፋ ያደርጋል። ታጋሽ ሰው ስለ ራሱ ብቻ ከማሰብ ይልቅ የሚያስከፋ ነገር ለፈጸመበት ሰውም ያስባል። በዚህም ምክንያት፣ በደል ቢፈጸምበትም እንኳ ከበዳዩ ጋር ያለው ግንኙነት ሊሻሻል እንደሚችል ምንጊዜም ተስፋ ያደርጋል። ከዚህ አኳያ፣ የአምላክ ቃል ከሚዘረዝራቸው ከፍቅር የሚመነጩ በርካታ መልካም ባሕርያት መካከል ‘ትዕግሥት’ መጀመሪያ ላይ መጠቀሱ አያስገርምም። * (1 ቆሮ. 13:4) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ትዕግሥት” ‘ከመንፈስ ፍሬ’ ገጽታዎች አንዱ እንደሆነ ይናገራል። (ገላ. 5:22, 23) ይሁንና ይህን ክርስቲያናዊ ባሕርይ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

ትዕግሥት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

ትዕግሥት ማዳበር የምንችለው የይሖዋን መንፈስ እርዳታ ለማግኘት የምንጸልይ ከሆነ ነው፤ ይሖዋ ለሚታመኑበት ሰዎች መንፈሱን ይሰጣል። (ሉቃስ 11:13) የአምላክ መንፈስ ከፍተኛ ኃይል ያለው ቢሆንም እኛም ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰድ የበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይጠበቅብናል። (መዝ. 86:10, 11) በሌላ አነጋገር፣ ይህን ባሕርይ በሚገባ ለማዳበር በየዕለቱ ትዕግሥት ማሳየት አለብን። ነገር ግን በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ትዕግሥተኛ ለመሆን ከዚህም ያለፈ ነገር ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። ታዲያ በዚህ ረገድ የሚረዳን ሌላው ነገር ምንድን ነው?

ኢየሱስ የተወውን ፍጹም ምሳሌ መመርመራችንና ምሳሌውን መከተላችን ትዕግሥት ለማዳበር ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ትዕግሥትን’ ስለሚያካትተው አዲሱ ስብዕና ከገለጸ በኋላ “የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ” የሚል ምክር ሰጥቷል። (ቆላ. 3:10, 12, 15) ኢየሱስ ትዕግሥት ያሳየው፣ አምላክ ነገሮችን በራሱ ጊዜ እንደሚያስተካክል ጠንካራ እምነት ስለነበረው ነው፤ እኛም የኢየሱስ ዓይነት እምነት በማዳበር የእሱ ሰላም በልባችን ‘እንዲገዛ’ ማድረግ እንችላለን። የኢየሱስን ምሳሌ የምንከተል ከሆነ በዙሪያችን ምንም ዓይነት ነገር ቢከናወን ትዕግሥታችን አያልቅም።—ዮሐ. 14:27፤ 16:33

አምላክ ቃል የገባልንን አዲስ ዓለም ለማየት እንደምንጓጓ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ይሖዋ ባሳየን ትዕግሥት ላይ ካሰላሰልን ይበልጥ ትዕግሥተኛ ለመሆን እንነሳሳለን። መጽሐፍ ቅዱስ “አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት ይሖዋ የገባውን ቃል ለመፈጸም አይዘገይም፤ ከዚህ ይልቅ እናንተን የታገሠው፣ ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ ነው” ይላል። (2 ጴጥ. 3:9) ይሖዋ ለእኛ ባሳየው ትዕግሥት ላይ ማሰላሰላችን ሌሎችን ይበልጥ በትዕግሥት ለመያዝ ያነሳሳናል። (ሮም 2:4) ታዲያ ትዕግሥት የሚጠይቁ አንዳንድ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

ትዕግሥት የሚጠይቁ ሁኔታዎች

በየዕለቱ ትዕግሥታችንን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ አስፈላጊ ነገር መናገር በምንፈልግበት ጊዜ ሌሎች እየተናገሩ ከሆነ እነሱን ላለማቋረጥ መታገሥ ያስፈልገን ይሆናል። (ያዕ. 1:19) ወይም ደግሞ አንዳንድ የእምነት ባልንጀሮቻችን የሚያደርጉት ነገር ያበሳጨን ይሆናል፤ እንዲህ ካሉት ወንድሞች ጋር ስንሆን ትዕግሥት ማሳየት ያስፈልገናል። ወንድሞቻችን በሚያደርጉት ነገር ከልክ በላይ ከመበሳጨት ይልቅ ይሖዋና ኢየሱስ እኛ ያሉብንን ድክመቶች እንዴት እንደሚመለከቷቸው ማሰባችን ተገቢ ይሆናል። ይሖዋና ኢየሱስ ጥቃቅን ጉድለቶቻችንን አጉልተው አይመለከቱም። ከዚህ ይልቅ በመልካም ባሕርያችን ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ሲሆን ማሻሻያ እስክናደርግ ድረስ ይታገሡናል።—1 ጢሞ. 1:16፤ 1 ጴጥ. 3:12

ሌሎች የተሳሳተ ነገር እንደተናገርን አሊያም እንዳደረግን በሚናገሩበት ጊዜም ትዕግሥታችን ሊፈተን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን መበሳጨትና ጥፋታችንን ማስተባበል ይቀናን ይሆናል። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል ከዚህ የተለየ ነገር እንድናደርግ ይመክረናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ትዕቢተኛ ከመሆን ይልቅ ታጋሽ መሆን ይሻላል። የሞኞች ቁጣ በጉያቸው ውስጥ ስለሆነ ለቁጣ አትቸኩል” በማለት ይናገራል። (መክ. 7:8, 9) ስለዚህ የተሰነዘረብን ውንጀላ ሙሉ በሙሉ ሐሰት ቢሆንም እንኳ ትዕግሥተኛ በመሆን የምንሰጠውን ምላሽ ማመዛዘን ይኖርብናል። ኢየሱስ ሌሎች በሐሰት ሲወነጅሉት ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ አድርጓል።—ማቴ. 11:19

በተለይ ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ያዩትን የተሳሳተ አመለካከት፣ ምኞት ወይም ዝንባሌ ለማስተካከል በሚሞክሩበት ጊዜ ትዕግሥት ማሳየት ያስፈልጋቸዋል። የስካንዲኔቪያ ቤቴል ቤተሰብ አባል ሆኖ የሚያገለግለውን የማቲያስን ተሞክሮ እንመልከት። ማቲያስ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ በነበረበት ወቅት የክፍሉ ተማሪዎች በእምነቱ የተነሳ በጣም ያሾፉበት ነበር። መጀመሪያ ላይ ወላጆቹ ይህን አላወቁም። ሆኖም ልጃቸው የሚያምንበት ነገር እውነት መሆኑን መጠራጠር እንደጀመረ አስተዋሉ። የማቲያስ አባት የሆነው ዪሊስ “ሁኔታው በጣም ትዕግሥት የሚጠይቅ ነበር” በማለት ይናገራል። ማቲያስ “አምላክ ማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ባይሆንስ? አንድን ነገር እንድናደርግ ያዘዘን አምላክ እንደሆነ እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን?” እያለ ይጠይቅ ነበር። በተጨማሪም አባቱን “የአንተ ዓይነት ስሜት ወይም እምነት ስለሌለኝ ብቻ እንደተሳሳትኩ ልቆጠር ይገባል?” ይለው ነበር።

ዪሊስ እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ ልጃችን ጥያቄዎቹን የሚያቀርበው በንዴት ነበር፤ ግን የተናደደው በእኔ ወይም በእናቱ ላይ ሳይሆን በእውነት ላይ ነበር፤ እውነት ሕይወቱን በጣም አስቸጋሪ እንዳደረገበት ይሰማው ነበር።” ታዲያ ዪሊስ ምን አደረገ? እንዲህ ይላል፦ “ከልጄ ጋር ቁጭ ብለን ለሰዓታት እናወራ ነበር። ስሜቱና ሐሳቡ እንዲገባኝ ስል አብዛኛውን ጊዜ ዝም ብዬ አዳምጠዋለሁ፤ አልፎ አልፎ ደግሞ ጥያቄዎችን እጠይቀዋለሁ። አንዳንድ ጊዜ ለጥያቄው ማብራሪያ ከሰጠሁት በኋላ ለተወሰኑ ቀናት በጉዳዩ ላይ እንዲያስብበት ጊዜ እሰጠዋለሁ፤ ከዚያ በኋላ ውይይታችንን እንቀጥላለን። ሌላ ጊዜ ደግሞ ሐሳቡን ከገለጸልኝ በኋላ በጉዳዩ ላይ እንዳስብበት ጥቂት ቀናት እንዲሰጠኝ እጠይቀው ነበር። በዚህ መንገድ አዘውትረን መወያየታችን ማቲያስ ስለ ቤዛው፣ ስለ አምላክ ሉዓላዊነት እና ስለ ይሖዋ ፍቅር የሚገልጹትን ትምህርቶች ቀስ በቀስ እንዲረዳና እንዲቀበል አስችሎታል። ይህን ማድረግ ከባድና ጊዜ የሚጠይቅ ነገር ነበር፤ በጊዜ ሂደት ግን ማቲያስ ለይሖዋ ያለው ፍቅር እያደገ ሄደ። እኔና ባለቤቴ፣ ልጃችን በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለ እሱን በትዕግሥት ለመርዳት ያደረግነው ጥረት በመሳካቱና የማቲያስን ልብ መንካት በመቻላችን በጣም ደስተኞች ነን።”

ዪሊስና ባለቤቱ ልጃቸውን በትዕግሥት ለመርዳት በሚጥሩበት ጊዜ ይሖዋ እንደሚደግፋቸው ይተማመኑ ነበር። ዪሊስ ስለዚያ ጊዜ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “እኔና እናቱ፣ እውነትን በደንብ ለመገንዘብ ይሖዋ እንዲረዳው አጥብቀን እንደምንጸልይ ለማቲያስ በተደጋጋሚ እነግረው ነበር፤ ይህን የምናደርገውም በጣም ስለምንወደው መሆኑን እገልጽለት ነበር።” እነዚህ ወላጆች በጣም አስፈላጊ የሆነውን የትዕግሥት ባሕርይ በማሳየታቸው ምንኛ አመስጋኞች ናቸው!

እውነተኛ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ እርዳታ ከመስጠት በተጨማሪ ሥር የሰደደ ሕመም ላለባቸው የቤተሰባቸው አባላት ወይም ጓደኞቻቸው እንክብካቤ ማድረግ ሊጠበቅባቸው ይችላል፤ በዚህ ጊዜም ትዕግሥት ማሳየት ያስፈልጋቸዋል። ስካንዲኔቪያ ውስጥ የምትኖረውን የኤለንን * ምሳሌ እንመልከት።

ከስምንት ዓመታት በፊት የኤለን ባል ሁለት ጊዜ ጭንቅላቱ ውስጥ ደም በመፍሰሱ ምክንያት አንጎሉ ላይ ከባድ ጉዳት ደረሰበት። በዚህም የተነሳ የርኅራኄ፣ የደስታም ሆነ የሐዘን ስሜት ማሳየት አይችልም። ይህም ለኤለን በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሮባታል። ኤለን “ከፍተኛ ትዕግሥት ማሳየት እንዲሁም አዘውትሬ መጸለይ አስፈልጎኛል” በማለት ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ፊልጵስዩስ 4:13 በጣም የምወደውና የሚያጽናናኝ ጥቅስ ነው፤ ጥቅሱ ‘ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ’ ይላል።” ኤለን ይሖዋ ኃይልና ድጋፍ ስለሰጣት በትዕግሥት መጽናት ችላለች።—መዝ. 62:5, 6

ትዕግሥት በማሳየት ይሖዋን ምሰሉ

ትዕግሥት በማሳየት ረገድ ሁላችንም ልንከተለው የሚገባን ከሁሉ የላቀው ምሳሌ ይሖዋ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። (2 ጴጥ. 3:15) ይሖዋ ከፍተኛ ትዕግሥት ስላሳየባቸው ወቅቶች የሚናገሩ ብዙ ታሪኮችን በአምላክ ቃል ውስጥ እናገኛለን። (ነህ. 9:30፤ ኢሳ. 30:18) ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ሰዶምን ለማጥፋት ያደረገውን ውሳኔ በተመለከተ አብርሃም በተደጋጋሚ ጥያቄ ባነሳበት ወቅት ይሖዋ ምን እንዳደረገ እንመልከት። በመጀመሪያ ደረጃ፣ አብርሃም ሲናገር ይሖዋ በመሃል ጣልቃ ገብቶ አላቋረጠውም። ከዚህ ይልቅ አብርሃም ጥያቄ ሲጠይቅና ያሳሰቡትን ነገሮች ሲገልጽ ይሖዋ በትዕግሥት አዳምጦታል። ከዚያም ይሖዋ አብርሃም የተናገረውን ነገር በድጋሚ በመናገር እያዳመጠው እንደሆነ አሳይቷል፤ በተጨማሪም ሰዶም ውስጥ አሥር ጻድቃን እንኳ ቢገኙ ከተማዋን እንደማያጠፋት አረጋግጦለታል። (ዘፍ. 18:22-33) ይሖዋ በትዕግሥት በማዳመጥና ቶሎ ባለመቆጣት ረገድ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል!

በእርግጥም ትዕግሥት ሁሉም ክርስቲያኖች ሊለብሱት የሚገባው የአዲሱ ስብዕና አስፈላጊ ክፍል ነው። ይህን ውድ ባሕርይ ለማዳበር ጠንክረን የምንሠራ ከሆነ አሳቢና ትዕግሥተኛ የሆነውን የሰማዩ አባታችንን እናስከብራለን፤ በተጨማሪም “አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች በእምነትና በትዕግሥት [ከሚወርሱት]” መካከል የመቆጠር መብት እናገኛለን።—ዕብ. 6:10-12

^ አን.4 ስለ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች ከሚያብራሩት ዘጠኝ ተከታታይ ርዕሶች የመጀመሪያው ስለ ፍቅር የሚያወሳ ነበር።

^ አን.15 ስሟ ተቀይሯል።