በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሁኔታዎች ቢለዋወጡም ውስጣዊ ሰላማችሁን ጠብቃችሁ ኑሩ

ሁኔታዎች ቢለዋወጡም ውስጣዊ ሰላማችሁን ጠብቃችሁ ኑሩ

“ነፍሴን አረጋጋኋት፤ ደግሞም ጸጥ አሰኘኋት።”—መዝ. 131:2

መዝሙሮች፦ 128, 129

1, 2. (ሀ) አንድ ክርስቲያን ያልተጠበቁ ለውጦች በሚያጋጥሙት ጊዜ ምን ሊሰማው ይችላል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) በመዝሙር 131 መሠረት ውስጣዊ ሰላማችንን ጠብቀን ለመኖር የሚረዳን ምን ዓይነት አመለካከት መያዛችን ነው?

ሎይድ እና አሌግዛንድራ ከ25 ለሚበልጡ ዓመታት በቤቴል ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ መስክ ላይ እንዲያገለግሉ መመደባቸውን ሲሰሙ መጀመሪያ ላይ በጣም አዝነው ነበር። ሎይድ እንዲህ ብሏል፦ “ቤቴልም ሆነ በዚያ የማከናውነው ሥራ የማንነቴ ክፍል ሆኖ ነበር። ለውጡ የተደረገበትን ምክንያት ተረድቼው ነበር፤ ሆኖም ሳምንታት ብሎም ወራት እያለፉ ሲሄዱ፣ ተፈላጊ እንዳልሆንኩ ይሰማኝ ጀመር። ስሜቴ በተደጋጋሚ ይለዋወጥ ነበር። አንዴ አዎንታዊ አመለካከት እይዛለሁ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በጣም ይከፋኛል።”

2 በሕይወታችን ውስጥ ያልተጠበቀ ለውጥ ሲያጋጥመን ስጋት ሊያድርብንና ልንጨነቅ እንችላለን። (ምሳሌ 12:25) አልፎ ተርፎም ለውጡን መቀበል ሊከብደን ይችላል። ታዲያ በዚህ ጊዜ ነፍሳችንን ‘ማረጋጋትና ጸጥ ማሰኘት’ የምንችለው እንዴት ነው? (መዝሙር 131:1-3ን አንብብ።) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ሰዎችም ሆኑ በዘመናችን ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ ቢያጋጥማቸውም ውስጣዊ ሰላማቸውን ጠብቀው መኖር የቻሉት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

“የአምላክ ሰላም” የሚረዳን እንዴት ነው?

3. ዮሴፍ በሕይወቱ ውስጥ ምን ለውጥ አጋጥሞታል?

3 ዮሴፍ የገዛ ወንድሞቹ በቅናት ተነሳስተው ለባርነት ሲሸጡት ገና 17 ዓመቱ ነበር። አባቱ ከሌሎች ልጆቹ ሁሉ አስበልጦ የሚወደው እሱን ነበር። (ዘፍ. 37:2-4, 23-28) ዮሴፍ ከሚወደው አባቱ ከያዕቆብ ተለይቶ ለ13 ዓመታት ገደማ ግብፅ ውስጥ በባርነትና በእስር ኖሯል። ታዲያ በዚህ ወቅት ተስፋ እንዳይቆርጥና ምሬት እንዳያድርበት የረዳው ምንድን ነው?

4. (ሀ) ዮሴፍ እስር ቤት ውስጥ ሳለ ትኩረት ያደረገው በምን ላይ ነበር? (ለ) ይሖዋ፣ ዮሴፍ ላቀረበው ጸሎት ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?

4 ዮሴፍ እስር ቤት ውስጥ ይማቅቅ በነበረበት ወቅት፣ ትኩረቱ እንዲያርፍ ያደረገው ይሖዋ እየባረከው እንዳለ በሚያሳዩ ማስረጃዎች ላይ እንደነበር ጥርጥር የለውም። (ዘፍ. 39:21፤ መዝ. 105:17-19) በተጨማሪም ዮሴፍ ልጅ ሳለ ያያቸው ትንቢታዊ ትርጉም ያዘሉ ሕልሞች ይሖዋ ሞገሱን እንዳሳየው እርግጠኛ እንዲሆን አድርገውት መሆን አለበት። (ዘፍ. 37:5-11) ከዚህም ሌላ በተደጋጋሚ ወደ ይሖዋ በመጸለይ ስሜቱን አውጥቶ እንደተናገረ መገመት እንችላለን። (መዝ. 145:18) ይሖዋም በመከራው ሁሉ “ከእሱ ጋር” እንደሚሆን እርግጠኛ እንዲሆን በማድረግ ዮሴፍ ላቀረበው ከልብ የመነጨ ጸሎት ምላሽ ሰጥቷል።—ሥራ 7:9, 10 *

5. “የአምላክ ሰላም” ይሖዋን ማገልገላችንን እንድንቀጥል የሚረዳን እንዴት ነው?

5 እኛም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን፣ አእምሯችንን የሚጠብቀው “የአምላክ ሰላም” ያለውን የማረጋጋት ኃይል በገዛ ሕይወታችን መመልከት እንችላለን። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7ን አንብብ።) በመሆኑም በጭንቀት በምንዋጥበት ጊዜ የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት የምንጥር ከሆነ የአምላክ ሰላም መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ያለንን ቁርጠኝነት እንድናጠናክርና ተስፋ እንዳንቆርጥ ይረዳናል። የዚህን እውነተኝነት ለማየት፣ በዘመናችን ያሉ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ያጋጠማቸውን ሁኔታ እንመልከት።

ውስጣዊ ሰላማችሁን መልሳችሁ ለማግኘት የይሖዋን እርዳታ ጠይቁ

6, 7. የሚያስፈልገንን ነገር ለይተን በመጥቀስ መጸለያችን ውስጣዊ ሰላማችንን መልሰን ለማግኘት የሚረዳን እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

6 ራየንና ጁሊየት የጊዜያዊ ልዩ አቅኚነት አገልግሎታቸውን እንዲያቆሙ ሲነገራቸው በጣም አዝነው ነበር። ራየን እንዲህ ብሏል፦ “ወዲያውኑ ጉዳዩን አስመልክተን ወደ ይሖዋ ጸለይን። ሁኔታው በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት የምናሳይበት ልዩ አጋጣሚ እንደሆነ ተገንዝበን ነበር። አብዛኞቹ የጉባኤያችን አባላት በእውነት ቤት ውስጥ ብዙ ስላልቆዩ ለእነዚህ ወንድሞች ግሩም የእምነት ምሳሌ መሆን እንድንችል እንዲረዳን ይሖዋን ጠየቅነው።”

7 ታዲያ ይሖዋ ለጸሎታቸው ምላሽ የሰጣቸው እንዴት ነው? ራየን እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “ከጸለይን በኋላ፣ መጀመሪያ ላይ ተሰምቶን የነበረው አሉታዊ ስሜትና ጭንቀት ወዲያውኑ ጠፋ። የአምላክ ሰላም ልባችንንና አእምሯችንን ጠብቆልናል። ትክክለኛውን አመለካከት ይዘን እስከቀጠልን ድረስ ይሖዋ ምንጊዜም ሊጠቀምብን እንደሚችል ተገንዝበናል።”

8-10. (ሀ) የአምላክ መንፈስ ያጋጠመንን ጭንቀት ለመቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) መንፈሳዊ አመለካከት ይዘን ለመቀጠል የምናደርገውን ጥረት ይሖዋ የሚባርክልን እንዴት ነው?

8 የአምላክ መንፈስ ልባችንን ከማረጋጋት ባለፈ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ እንድንሰጥ በሚያበረታቱን ጥቅሶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንድንችል ይረዳናል። (ዮሐንስ 14:26, 27ን አንብብ።) ፊሊፕ እና ሜሪ የተባሉትን ለ25 ዓመታት ገደማ በቤቴል ያገለገሉ ባልና ሚስት ተሞክሮ እንመልከት። አራት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለቱም እናታቸውን በሞት አጡ፤ ፊሊፕ ደግሞ አንድ ሌላ ዘመዱንም በሞት አጣ። በተጨማሪም የአእምሮ በሽታ ያለበትን የሜሪን አባት የመንከባከብ ኃላፊነት ወደቀባቸው።

9 ፊሊፕ እንዲህ ብሏል፦ “ችግሩን በጥሩ ሁኔታ እየተወጣሁ ያለሁ ቢመስለኝም የሆነ ነገር እንደጎደለኝ ይሰማኝ ነበር። ከዚያም አንድ ቀን፣ ቆላስይስ 1:11 የተብራራበትን የመጠበቂያ ግንብ የጥናት ርዕስ አነበብኩ። ያነበብኩት ነገር ጽናት እያሳየሁ ቢሆንም የማሳየው ጽናት የተሟላ እንዳልነበር እንድገነዘብ ረዳኝ። ‘በትዕግሥትና በደስታ ሁሉንም ነገር በጽናት [መቋቋም]’ ያስፈልገኝ ነበር። ይህ ጥቅስ፣ በሕይወቴ ውስጥ የሚኖረኝ ደስታ የአምላክ መንፈስ በሕይወቴ ላይ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ላይ እንጂ ባለሁበት ሁኔታ ላይ የተመካ እንዳልሆነ አስታውሶኛል።”

10 ፊሊፕ እና ሜሪ አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም መንፈሳዊ አመለካከት ይዘው ለመቀጠል ያደረጉትን ጥረት ይሖዋ በብዙ መንገድ ባርኮላቸዋል። ከቤቴል ከወጡ ብዙም ሳይቆይ ሁለቱም በሳምንት ከአንድ ቀን በላይ የማጥናት ፍላጎት ያላቸው እድገት የሚያደርጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን አግኝተዋል። ሜሪ ያን ጊዜ መለስ ብላ በማሰብ እንዲህ ብላለች፦ “ጥናቶቻችን የደስታችን ምንጭ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ይሖዋ ‘አይዟችሁ፣ ሁሉም ነገር ይስተካከላል’ እያለን እንዳለ እንዲሰማን አድርገዋል።”

የይሖዋን በረከት የሚያስገኝ ነገር አድርጉ

ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ዮሴፍ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 11-13⁠ን ተመልከት)

11, 12. (ሀ) ዮሴፍ የይሖዋን በረከት የሚያስገኝ ምን ነገር አድርጓል? (ለ) ዮሴፍ ጽናት በማሳየቱ የተካሰው እንዴት ነው?

11 ድንገተኛ ለውጥ ሲያጋጥመን፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚሰማን ጭንቀት በቀላሉ ሊያሽመደምደን ይችላል። ዮሴፍ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊያጋጥመው ይችል ነበር። እሱ ግን ባለበት ሁኔታ ሥር አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ያደረገ ሲሆን ይህም የይሖዋን በረከት አስገኝቶለታል። ዮሴፍ በጶጢፋር ቤት ውስጥ ያደርግ እንደነበረው ሁሉ እስር ቤት ውስጥ ሳለም የእስር ቤቱ አለቃ ያዘዘውን ማንኛውንም ሥራ በትጋት ያከናውን ነበር።—ዘፍ. 39:21-23

12 አንድ ቀን ዮሴፍ፣ ቀደም ሲል በፈርዖን ቤተ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸውን ሁለት ሰዎች እንዲረዳ ኃላፊነት ተሰጠው። ዮሴፍ እነዚህን ሰዎች በደግነት ይይዛቸው ነበር። በመሆኑም ሰዎቹ ስላስጨነቃቸው ነገርና ሌሊት ስላዩት ግራ የሚያጋባ ሕልም ነገሩት። (ዘፍ. 40:5-8) ዮሴፍ በወቅቱ ባይገነዘበውም ከእነዚህ ሰዎች ጋር ያደረገው ውይይት ጥሩ ውጤት አስገኝቶለታል። ሁለት ተጨማሪ ዓመታትን በእስር ማሳለፍ ቢኖርበትም ከጊዜ በኋላ የተፈታ ሲሆን በዚያኑ ዕለት ከፈርዖን ቀጥሎ ሁለተኛው ባለሥልጣን ሆኖ ተሹሟል።—ዘፍ. 41:1, 14-16, 39-41

13. ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን የይሖዋን በረከት ለማግኘት ምን ማድረግ እንችላለን?

13 እኛም እንደ ዮሴፍ ከቁጥጥራችን ውጭ የሆኑ ሁኔታዎች ያጋጥሙን ይሆናል። በዚህ ጊዜ ታጋሾች ለመሆንና ባለንበት ሁኔታ ሥር አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ጥረት እናድርግ፤ ይህም የይሖዋን በረከት ያስገኝልናል። (መዝ. 37:5) እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ‘ግራ እንጋባ’ ይሆናል፤ ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ፈጽሞ “ተስፋ አንቆርጥም።” (2 ቆሮ. 4:8 ግርጌ) በተለይ በአገልግሎታችን ላይ ትኩረት የምናደርግ ከሆነ ጳውሎስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት በእኛ ላይ ሲፈጸሙ ማየት እንችላለን።

ምንጊዜም በአገልግሎታችሁ ላይ ትኩረት አድርጉ

14-16. ወንጌላዊው ፊልጶስ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ቢኖሩም ምንጊዜም በአገልግሎቱ ላይ ትኩረት ያደረገው እንዴት ነው?

14 ወንጌላዊው ፊልጶስ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ቢኖሩም ምንጊዜም በአገልግሎት ላይ ትኩረት በማድረግ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። ፊልጶስ በኢየሩሳሌም አዲስ የአገልግሎት መብት ተሰጥቶት ነበር። (ሥራ 6:1-6) ከዚያ ግን ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ ተለዋወጡ። የእስጢፋኖስን መገደል ተከትሎ በክርስቲያኖች ላይ ከባድ ስደት ተነሳ። * በስደቱ ምክንያት የክርስቶስ ተከታዮች ከኢየሩሳሌም ወደተለያዩ ቦታዎች ተበተኑ። በዚህ ወቅት ፊልጶስ እጁን አጣጥፎ ከመቀመጥ ይልቅ በወቅቱ ምሥራቹ እምብዛም ወዳልተሰበከባት ወደ ሰማርያ ሄዶ መስበክ ጀመረ።—ማቴ. 10:5፤ ሥራ 8:1, 5

15 ፊልጶስ የአምላክ መንፈስ ወደመራው ቦታ ሁሉ ለመሄድ ፈቃደኛ ስለነበር ይሖዋ አዳዲስ ክልሎችን ለመክፈት ተጠቅሞበታል። ፊልጶስ የነበረው ከአድልዎ ነፃ የሆነ አቀራረብ ሳምራውያንን ሳይማርካቸው አልቀረም፤ ምክንያቱም አይሁዳውያን ሳምራውያንን ይንቋቸው ነበር። ከዚህ አንጻር ሕዝቡ ፊልጶስን “በአንድ ልብ” ይሰማው የነበረ መሆኑ አያስገርምም!—ሥራ 8:6-8

16 ከዚያም ፊልጶስ በአምላክ መንፈስ መሪነት፣ አሽዶድና ቂሳርያ ወደተባሉ በርካታ አሕዛብ የሚኖሩባቸው ከተሞች ሄደ። (ሥራ 8:39, 40) ለመጀመሪያ ጊዜ በሰማርያ ከሰበከ በኋላ ባሉት ወደ 20 የሚጠጉ ዓመታት ውስጥ፣ ፊልጶስ ሌሎች ለውጦችም እንዳጋጠሙት ከሁኔታዎች መረዳት እንችላለን። በዚያው በሚያገለግልበት ክልል ውስጥ ቤተሰብ መሥርቶ መኖር ጀምሮ ነበር። ፊልጶስ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ቢኖሩም ትኩረቱ ምንጊዜም በአገልግሎቱ ላይ እንዲያርፍ አድርጎ ነበር፤ ይሖዋም እሱንና ቤተሰቡን አብዝቶ ባርኳቸዋል።—ሥራ 21:8, 9

17, 18. በአገልግሎት ላይ ትኩረት ማድረጋችን በሕይወታችን ውስጥ ለውጥ ሲያጋጥመን ሚዛናችንን እንዳንስት የሚረዳን እንዴት ነው?

17 በርካታ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በአገልግሎት ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ቢኖሩም ሚዛናቸውን እንዳይስቱ እንደረዳቸው ተናግረዋል። በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኦዝቦርንና ፖላይት የተባሉ ባልና ሚስት ከቤቴል ሲወጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ የሚኖሩበት ቤትና ሙሉ ጊዜያቸውን የማይወስድ ሥራ እንደሚያገኙ አስበው ነበር። ኦዝቦርን “የሚያሳዝነው ነገር፣ ሥራ ማግኘት ያሰብነውን ያህል ቀላል አልነበረም” በማለት ተናግሯል። ባለቤቱ ፖላይት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ለሦስት ወር ያህል ምንም ሥራ ማግኘት አልቻልንም፤ በዚያ ላይ ያጠራቀምነው ገንዘብ አልነበረንም። ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ ነበር።”

18 ታዲያ እንዲህ ያለውን አስጨናቂ ሁኔታ ለመወጣት የረዳቸው ምንድን ነው? ኦዝቦርን ሁኔታውን ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ከጉባኤው ጋር አብረን ማገልገላችን ትኩረታችን እንዳይከፋፈልና አዎንታዊ አመለካከት እንድንይዝ በጣም ረድቶናል። ቁጭ ብለን ከመቆዘም ይልቅ በስብከቱ ሥራ ለመጠመድ ወሰንን፤ ይህም ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶልናል። ሥራ ለማግኘት የቻልነውን ሁሉ ያደረግን ሲሆን በመጨረሻም ተሳካልን።”

ይሖዋን በትዕግሥት ተጠባበቁ

19-21. (ሀ) ውስጣዊ ሰላማችንን ጠብቀን ለመኖር ምን ይረዳናል? (ለ) ከሚያጋጥሙን ለውጦች ጋር ራሳችንን ማስማማታችን በግለሰብ ደረጃ ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

19 በዚህ ርዕስ ውስጥ እንደተመለከትነው፣ ባለንበት ሁኔታ ሥር አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረጋችንና በሙሉ እምነት ይሖዋን መጠባበቃችን ውስጣዊ ሰላማችንን ጠብቀን ለመኖር ይረዳናል። (ሚክያስ 7:7ን አንብብ።) እንዲያውም ካጋጠመን አዲስ ሁኔታ ጋር ለመላመድ ያደረግነው ጥረት ብዙ መንፈሳዊ ጥቅም እንዳስገኘልን እንገነዘብ ይሆናል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ፖላይት ከራሷ ተሞክሮ በመነሳት እንዲህ ብላለች፦ “በሌላ የአገልግሎት መስክ እንድናገለግል መመደባችን በጣም ከባድ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር በይሖዋ መታመን ምን ማለት እንደሆነ አስተምሮኛል። ከይሖዋ ጋር ያለኝ ዝምድና ይበልጥ ተጠናክሯል።”

20 ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሜሪም በዕድሜ የገፉ አባቷን እየተንከባከበች በአቅኚነት ማገልገሏን ቀጥላለች። እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “በጭንቀት በምዋጥበት ጊዜ የምሠራውን ነገር ቆም አድርጌ መጸለይና ራሴን ማረጋጋት እንደሚያስፈልገኝ ተምሬያለሁ። ከሁሉ በላይ ግን የሚያስጨንቀኝን ነገር ለይሖዋ መተውን ተምሬያለሁ፤ ይህ ደግሞ ለወደፊቱ ጊዜ በጣም የሚያስፈልገን ባሕርይ ነው።”

21 በመግቢያው ላይ የተጠቀሱት ሎይድና አሌግዛንድራ ሁኔታቸው መለወጡ ፈጽሞ ባልጠበቁት መንገድ እምነታቸውን እንደፈተነው ተናግረዋል። ሆኖም እንዲህ ብለዋል፦ “የሚያጋጥሙን የእምነት ፈተናዎች እምነታችን እውነተኛ መሆን አለመሆኑን እንዲሁም በአስቸጋሪ ጊዜያት ድጋፍና ማጽናኛ ሊሰጠን የሚችል መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ይረዱናል። በውጤቱም የተሻልን ሰዎች እንሆናለን።”

ያልተጠበቁ ለውጦች ያልተጠበቁ በረከቶችን ያስገኛሉ! (አንቀጽ 19-21⁠ን ተመልከት)

22. ባለንበት ሁኔታ ሥር አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ የምናደርግ ከሆነ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

22 የአገልግሎት ምድብ ለውጥን፣ የጤና ችግርንና ተጨማሪ የቤተሰብ ኃላፊነትን ጨምሮ በሕይወታችሁ ውስጥ ያልተጠበቁ ለውጦች ሲያጋጥሟችሁ ይሖዋ እንደሚንከባከባችሁና በተገቢው ጊዜ እንደሚረዳችሁ እርግጠኞች ሁኑ። (ዕብ. 4:16፤ 1 ጴጥ. 5:6, 7) እስከዚያው ድረስ ግን ባላችሁበት ሁኔታ ሥር አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ጥረት አድርጉ። በጸሎት አማካኝነት በሰማይ ካለው አባታችሁ ጋር ተቀራረቡ፤ እንዲሁም ችግሮቻችሁን ስለ እናንተ በሚያስበው በይሖዋ ላይ መጣልን ተማሩ። እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ እናንተም ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟችሁም ውስጣዊ ሰላማችሁን ጠብቃችሁ መኖር ትችላላችሁ።

^ አን.4 ዮሴፍ ከእስር ቤት ከወጣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይሖዋ ወንድ ልጅ በመስጠት፣ ያሳለፈውን ሥቃይ እንዲረሳ እንደረዳው ተናግሯል። “አምላክ የደረሰብኝን ችግር ሁሉ . . . እንድረሳ አደረገኝ” በማለት ለበኩር ልጁ ምናሴ የሚል ስም አውጥቶለታል።—ዘፍ. 41:51 ግርጌ

^ አን.14 በዚህ እትም ላይ የወጣውን “ይህን ያውቁ ኖሯል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።