በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ወደፊት ምን ያደርጋል?

አምላክ ወደፊት ምን ያደርጋል?

ችግር ላይ በምትወድቅበት ጊዜ፣ የቅርብ ወዳጅህ በሆነ መንገድ እንዲረዳህ እንደምትጠብቅ ጥርጥር የለውም። ከዚህ አንጻር አንዳንድ ሰዎች አምላክ እነሱን ለመርዳት ምንም እርምጃ እንዳልወሰደ ስለሚሰማቸው ወዳጃቸው እንዳልሆነ ይናገራሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን አምላክ ለእኛ ሲል ብዙ ነገሮችን አድርጓል፤ ወደፊትም ቢሆን፣ እየደረሰብን ያለውን መከራና ችግር ለማስወገድ እርምጃ ይወስዳል። ለመሆኑ አምላክ ምን ነገሮችን ያደርጋል?

ክፋትን በሙሉ ያስወግዳል

አምላክ ክፋትን ከምንጩ በማድረቅ የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል። መጽሐፍ ቅዱስ “መላው ዓለም . . . በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው” በማለት የክፋት ምንጭ ማን እንደሆነ ለይቶ ይናገራል። (1 ዮሐንስ 5:19) “ክፉው” ተብሎ የተገለጸው አካል፣ ኢየሱስ “የዚህ ዓለም ገዢ” በማለት ከጠራው ከሰይጣን ዲያብሎስ ውጭ ማንም ሊሆን አይችልም። (ዮሐንስ 12:31) በሰው ልጆች ላይ አሳዛኝ ነገሮች እየደረሱ ያሉት ሰይጣን በዓለም ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ስለሆነ ነው። ታዲያ አምላክ ምን እርምጃ ይወስድ ይሆን?

ይሖዋ አምላክ “ለሞት የመዳረግ አቅም ያለውን ዲያብሎስን” በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በቅርቡ “እንዳልነበረ [ያደርገዋል]።” (ዕብራውያን 2:14፤ 1 ዮሐንስ 3:8) እንዲያውም ሰይጣን ራሱ፣ ሊጠፋ የቀረው “ጥቂት ጊዜ” እንደሆነ እንደሚያውቅ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ራእይ 12:12) በተጨማሪም አምላክ ክፉ አድራጊዎችን በሙሉ ያጠፋል።—መዝሙር 37:9፤ ምሳሌ 2:22

ምድርን ገነት ያደርጋል

ፈጣሪያችን ክፋትን በሙሉ ከምድር ላይ ካስወገደ በኋላ ከሰው ልጆችና ከምድር ጋር በተያያዘ ያለውን ዘላለማዊ ዓላማ ዳር ለማድረስ እርምጃ ይወስዳል። ታዲያ ወደፊት ምን ነገሮችን መጠበቅ እንችላለን?

ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት። “የዋሆች . . . ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:11

ለጤና ተስማሚ የሆነና የተትረፈረፈ ምግብ። “በምድር ላይ እህል ይትረፈረፋል፤ በተራሮችም አናት ላይ በብዛት ይኖራል።”—መዝሙር 72:16

ምቹ ቤቶችና አስደሳች ሥራ። “ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። . . . የመረጥኳቸው አገልጋዮቼም በእጃቸው ሥራ የተሟላ እርካታ ያገኛሉ።”—ኢሳይያስ 65:21, 22

እነዚህ ተስፋዎች ሲፈጸሙ ለማየት ትጓጓለህ? በቅርቡ እነዚህ ነገሮች የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ክፍል ይሆናሉ።

በሽታንና ሞትን ያስወግዳል

በዛሬው ጊዜ ከሕመምና ከሞት ማምለጥ የሚችል ሰው የለም፤ በቅርቡ ግን ሁኔታው ይቀየራል። አምላክ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ከሚያስገኛቸው በረከቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል፤ ይህም “በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ” ያስችላል። (ዮሐንስ 3:16) ታዲያ ወደፊት ምን ነገሮችን መጠበቅ እንችላለን?

በሽታ ይወገዳል። “በዚያም የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’ አይልም። በምድሪቱ ላይ የሚቀመጡ በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል።”—ኢሳይያስ 33:24

ሞት አይኖርም። “ሞትን ለዘላለም ይውጣል፤ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።”—ኢሳይያስ 25:8

ሰዎች ለዘላለም ይኖራሉ። “አምላክ የሚሰጠው ስጦታ . . . በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።”—ሮም 6:23

የሞቱ ሰዎች ይነሳሉ። “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት [ይነሳሉ]።” (የሐዋርያት ሥራ 24:15) የሞቱ ሰዎች ትንሣኤ የሚያገኙት አምላክ ካዘጋጀው የቤዛ ዝግጅት ተጠቃሚ ስለሚሆኑ ነው።

ታዲያ አምላክ ይህን ሁሉ የሚያከናውነው እንዴት ነው?

ፍጹም የሆነ መስተዳድር ይመሠርታል

አምላክ ለሰው ዘርና ለምድር ያለውን ዓላማ ዳር የሚያደርሰው በሰማይ ባቋቋመውና ክርስቶስ ኢየሱስ በሚገዛው መስተዳድር አማካኝነት ነው። (መዝሙር 110:1, 2) ኢየሱስ ተከታዮቹን “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ . . . መንግሥትህ ይምጣ” ብለው እንዲጸልዩ ያስተማራቸው ስለዚህ መስተዳድር ወይም መንግሥት ነው።—ማቴዎስ 6:9, 10

የአምላክ መንግሥት ምድርን የሚገዛ ሲሆን ሐዘንና መከራን በሙሉ ከግዛቱ ያስወግዳል። የሰው ዘር ከዚህ የተሻለ አገዛዝ ሊያገኝ አይችልም! ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት “የመንግሥቱን ምሥራች” ለመስበክ ከፍተኛ ጥረት ያደረገውና ደቀ መዛሙርቱም እንዲሁ እንዲያደርጉ ያስተማረው በዚህ ምክንያት ነው።—ማቴዎስ 4:23፤ 24:14

ይሖዋ አምላክ ለሰብዓዊ ፍጥረታቱ ካለው ታላቅ ፍቅር የተነሳ እነዚህን ድንቅ ነገሮች ሊያደርግላቸው ቃል ገብቷል። ታዲያ ይህን መገንዘብህ እሱን ይበልጥ ለማወቅና ወደ እሱ ለመቅረብ አያነሳሳህም? እንዲህ ማድረግህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል? ቀጣዩ ርዕስ የዚህን ጥያቄ መልስ ያብራራል።

አምላክ ወደፊት ምን ያደርጋል? አምላክ በሽታንና ሞትን ያስወግዳል፤ የሰውን ዘር እሱ ባቋቋመው መንግሥት አገዛዝ ሥር አንድ ያደርጋል፤ እንዲሁም ምድርን ወደ ገነትነት ይለውጣል