በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን ማወቅህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?

አምላክን ማወቅህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?

እስካሁን ባየናቸው ተከታታይ ርዕሶች ላይ ‘አምላክ ማን ነው?’ ለሚለው ጥያቄ ደረጃ በደረጃ መልስ ለማግኘት ሞክረናል። በመጀመሪያ የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነና ዋነኛ ባሕርይው ፍቅር እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመልክተናል። ከዚያም ለሰብዓዊ ፍጥረታቱ ሲል ከዚህ በፊት ያደረገውንና ወደፊትም የሚያደርገውን ነገር አይተናል። ይሁንና ስለ አምላክ ማወቅ የሚያስፈልግህ ገና ብዙ ነገር አለ። ሆኖም ‘ስለ አምላክ ማወቄ ምን ጥቅም ያስገኝልኛል?’ ብለህ ታስብ ይሆናል።

ይሖዋ ‘ከፈለግከው እንደሚገኝልህ’ ቃል ገብቷል። (1 ዜና መዋዕል 28:9) አምላክን መፈለግህና እሱን ይበልጥ እያወቅከው መሄድህ የሚያስገኝልህን ግሩም ሽልማት ለማሰብ ሞክር፤ “ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት” መመሥረት ትችላለህ! (መዝሙር 25:14) እንዲህ ያለ ወዳጅነት መመሥረትህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

እውነተኛ ደስታ ያስገኝልሃል። ይሖዋ “ደስተኛው አምላክ” ተብሎ ተጠርቷል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11) ወደ እሱ ለመቅረብና እሱን ለመምሰል ጥረት ማድረግህ እውነተኛ ደስታ እንዲኖርህ ያደርጋል፤ ይህም ስሜታዊ፣ አእምሯዊና አካላዊ ጥቅም እንድታገኝ ያስችልሃል። (መዝሙር 33:12) በተጨማሪም ጎጂ ከሆነ አኗኗር ስለምትርቅ፣ ጤናማ ልማዶችን ስለምታዳብርና ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ስለሚኖርህ በሕይወትህ ደስተኛ ትሆናለህ። በመሆኑም መዝሙራዊው “ወደ አምላክ መቅረብ ይበጀኛል” በማለት የተናገረው ሐሳብ እውነት መሆኑን በገዛ ሕይወትህ ትመለከታለህ።—መዝሙር 73:28

በግለሰብ ደረጃ ትኩረትና እንክብካቤ እንድታገኝ ያስችልሃል። ይሖዋ ለአገልጋዮቹ “ዓይኔን በአንተ ላይ አድርጌ እመክርሃለሁ” በማለት ቃል ገብቶላቸዋል። (መዝሙር 32:8) በመሆኑም ይሖዋ ለአገልጋዮቹ በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ይሰጣቸዋል፤ እንዲሁም ለእያንዳንዳቸው የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ ያደርግላቸዋል። (መዝሙር 139:1, 2) ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ከመሠረትክ ይሖዋ ምንጊዜም ከጎንህ እንደሚሆን ማስተዋል ትችላለህ።

አስደሳች ተስፋ ይኖርሃል። ይሖዋ አምላክ በዛሬው ጊዜ አስደሳችና እርካታ ያለው ሕይወት እንድትመራ ከማድረግ በተጨማሪ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ብሩሕ ተስፋ እንዲኖርህ አድርጓል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) መጽሐፍ ቅዱስ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው” በማለት ይናገራል። (ዮሐንስ 17:3) አምላክ የሚሰጠው ተስፋ፣ ተነዋዋጭ በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ “አስተማማኝና ጽኑ” እንደሆነ መልሕቅ ይሆንልሃል።—ዕብራውያን 6:19

እስካሁን የተመለከትነው፣ አምላክን ይበልጥ ማወቃችንና ከእሱ ጋር የግል ዝምድና መመሥረታችን ከሚያስገኝልን በርካታ ጥቅሞች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የይሖዋ ምሥክሮችን ማነጋገር ወይም jw.org የተባለውን ድረ ገጻችንን መጎብኘት ትችላለህ።