በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 2

በጉባኤ መካከል ይሖዋን አወድሱ

በጉባኤ መካከል ይሖዋን አወድሱ

“በጉባኤ መካከል . . . አወድስሃለሁ።”—መዝ. 22:22

መዝሙር 59 ያህን አብረን እናወድስ

የትምህርቱ ዓላማ *

1. ዳዊት ለይሖዋ ምን ስሜት ነበረው? ይህስ ምን ለማድረግ አነሳስቶታል?

ንጉሥ ዳዊት “ይሖዋ ታላቅ ነው፤ እጅግ ሊወደስም ይገባዋል” በማለት ጽፏል። (መዝ. 145:3) ዳዊት ይሖዋን ይወደው ነበር፤ ይህም “በጉባኤ መካከል” እሱን ለማወደስ አነሳስቶታል። (መዝ. 22:22፤ 40:5) አንተም ይሖዋን እንደምትወደውና ዳዊት “የአባታችን የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ውዳሴ ይድረስህ” በማለት የተናገረውን ሐሳብ እንደምትጋራ ምንም ጥርጥር የለውም።—1 ዜና 29:10-13

2. (ሀ) ይሖዋን ማወደስ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) አንዳንዶች በዚህ ረገድ ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል? በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ነጥቦች እንመረምራለን?

2 በዛሬው ጊዜ ይሖዋን ማወደስ የምንችልበት አንዱ መንገድ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት ነው። ሆኖም በርካታ ወንድሞችና እህቶች በዚህ ረገድ ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። በስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግ ቢፈልጉም ፍርሃት ስለሚያድርባቸው እንዲህ ከማድረግ ወደኋላ ይላሉ። ታዲያ ፍርሃታቸውን ማሸነፍ የሚችሉት እንዴት ነው? በተጨማሪም ሁላችንም የሚያበረታቱ ሐሳቦችን መስጠት እንድንችል የትኞቹን ጠቃሚ ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ከመመርመራችን በፊት በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ የምንሰጥባቸውን አራት ዋና ዋና ምክንያቶች እንመልከት።

በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ የምንሰጠው ለምንድን ነው?

3-5. (ሀ) ዕብራውያን 13:15 ላይ እንደተገለጸው በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ የምንሰጠው ለምንድን ነው? (ለ) ሁላችንም ተመሳሳይ ሐሳብ እንድንሰጥ ይጠበቅብናል? አብራራ።

3 ይሖዋ ለሁላችንም እሱን የማወደስ መብት ሰጥቶናል። (መዝ. 119:108) በስብሰባዎች ላይ የምንሰጠው ሐሳብ ለይሖዋ የምናቀርበው “የውዳሴ መሥዋዕት” አንዱ ክፍል ሲሆን ማንም ሰው በእኛ ፋንታ ይህን መሥዋዕት ሊያቀርብልን አይችልም። (ዕብራውያን 13:15ን አንብብ።) ሆኖም አምላክ በስብሰባዎች ላይ ከምንሰጠው ሐሳብ ጋር በተያያዘ ሁላችንም ተመሳሳይ መሥዋዕት እንድናቀርብ ይጠብቅብናል? በፍጹም!

4 ይሖዋ እያንዳንዳችን ያለንበት ሁኔታና ችሎታችን እንደሚለያይ ያውቃል፤ በመሆኑም እንደ አቅማችን የምናቀርበውን መሥዋዕት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። አምላክ እስራኤላውያን እንዲያቀርቡ ይጠብቅባቸው የነበረውን መሥዋዕት እንደ ምሳሌ እንመልከት። አንዳንድ እስራኤላውያን የበግ ጠቦት ወይም ፍየል የማቅረብ አቅም ነበራቸው። ሆኖም አንድ ድሃ እስራኤላዊ “ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን” መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ ይችል ነበር። ሁለት ወፎችን ማቅረብ የማይችል እስራኤላዊ ደግሞ “አንድ አሥረኛ ኢፍ የላመ ዱቄት” እንዲያቀርብ ይፈቀድለት ነበር። (ዘሌ. 5:7, 11) የዱቄት መሥዋዕት ከሌሎቹ መሥዋዕቶች አንጻር ሲታይ ዋጋው ዝቅተኛ ነው፤ ሆኖም ዱቄቱ “የላመ” ማለትም ምርጥ ተደርጎ የሚቆጠር የዱቄት ዓይነት እስከሆነ ድረስ መሥዋዕቱ በይሖዋ ዘንድ ከፍ ተድርጎ ይታይ ነበር።

5 ደግ የሆነው አምላካችን ዛሬም በዚህ ረገድ ያለው አመለካከት አልተቀየረም። ሐሳብ በምንሰጥበት ወቅት ሁላችንም እንደ አጵሎስ ጥሩ የመናገር ተሰጥኦ ወይም እንደ ጳውሎስ ሌሎችን የማሳመን ችሎታ እንዲኖረን አይጠብቅብንም። (ሥራ 18:24፤ 26:28) ይሖዋ የሚጠብቅብን የአቅማችንን ያህል ሆኖም ምርጣችንን እንድንሰጠው ብቻ ነው። ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች የሰጠችውን መበለት አስታውሱ። በይሖዋ ዓይን ከፍ ተደርጋ የታየችው ምርጧን ስለሰጠች ነው።—ሉቃስ 21:1-4

በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠታችን እኛንም ሆነ የሚሰሙንን ይጠቅማል (አንቀጽ 6-7⁠ን ተመልከት) *

6. (ሀ) በዕብራውያን 10:24, 25 መሠረት ሌሎች የሚሰጡትን ሐሳብ ማዳመጣችን በእኛ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? (ለ) ሌሎች ለሚሰጡት የሚያበረታታ ሐሳብ ያለህን አድናቆት ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

6 የምንሰጠው ሐሳብ እርስ በርሳችን ለመበረታታት ያስችለናል። (ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብብ።) ሁላችንም በስብሰባዎች ላይ የሚሰጡትን የተለያዩ ሐሳቦች ስንሰማ እንበረታታለን። ለምሳሌ አንድ ትንሽ ልጅ አጭር ሆኖም ከልብ የመነጩ ቃላትን ተጠቅሞ የሚሰጠውን ሐሳብ መስማት ያስደስተናል። በቅርቡ እውነትን የሰሙ አዲስ ክርስቲያኖች በደስታ ተሞልተው ስሜታቸውን ሲገልጹ ስንሰማ ልባችን በጥልቅ ይነካል። ዓይናፋር የሆኑ ወይም የእኛን ቋንቋ ገና መማር የጀመሩ ወንድሞችና እህቶች ‘እንደ ምንም ብለው ድፍረት’ በማሰባሰብ የሚሰጡትን ሐሳብ ስናዳምጥ ልባችን በአድናቆት ይሞላል። (1 ተሰ. 2:2) ታዲያ እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ለሚያደርጉት ጥረት አድናቆታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ስብሰባው ካበቃ በኋላ፣ ለሰጡት የሚያበረታታ ሐሳብ ልናመሰግናቸው እንችላለን። በተጨማሪም እኛ ራሳችን በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ በመስጠት ለእነሱ ያለንን አድናቆት እናሳያለን። እንዲህ ማድረጋችን በስብሰባዎች ላይ እኛ ብቻ ተበረታተን ከመሄድ ይልቅ ሌሎችንም እንድናበረታታ ያስችለናል።—ሮም 1:11, 12

7. ሐሳብ መስጠታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

7 ሐሳብ መስጠታችን ራሳችንን ይጠቅመናል። (ኢሳ. 48:17) እንዴት? አንደኛ፣ በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ለመስጠት ግብ ካወጣን ጥሩ ዝግጅት አድርገን ለመሄድ እንነሳሳለን። ጥሩ ዝግጅት ማድረጋችን የአምላክን ቃል በጥልቀት እንድንረዳ ያስችለናል። የአምላክን ቃል በጥልቀት መረዳታችን ደግሞ የተማርነውን ነገር በተሻለ መንገድ ተግባራዊ እንድናደርግ ይረዳናል። ሁለተኛ፣ በውይይቱ ላይ ተሳትፎ ስለምናደርግ ስብሰባው ይበልጥ አስደሳች ይሆንልናል። ሦስተኛ፣ ሐሳብ መስጠት ጥረት ማድረግ የሚጠይቅ ነገር ስለሆነ የሰጠነውን መልስ በአብዛኛው ለረጅም ጊዜ እናስታውሰዋለን።

8-9. (ሀ) በሚልክያስ 3:16 መሠረት፣ በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ስንሰጥ ይሖዋ ምን ይሰማዋል? (ለ) ሆኖም አንዳንዶች ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል?

8 እምነታችንን ስንገልጽ ይሖዋ ይደሰታል። ይሖዋ በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ስንሰጥ እንደሚያዳምጠንና በዚህ ረገድ የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ሚልክያስ 3:16ን አንብብ።) እሱን ለማስደሰት የምናደርገውን ብርቱ ጥረት በመባረክ አድናቆቱን ያሳየናል።—ሚል. 3:10

9 በግልጽ ማየት እንደምንችለው በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ እንድንሰጥ የሚያነሳሱን አጥጋቢ ምክንያቶች አሉን። ሆኖም አንዳንዶች እነዚህን ምክንያቶች ቢያውቁም እጃቸውን አውጥተው ሐሳብ መስጠት ይፈራሉ። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ተስፋ መቁረጥ የለብህም። ከዚህ ቀጥሎ በስብሰባዎች ላይ የምናደርገውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚረዱንን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች፣ ምሳሌዎችና አንዳንድ ጠቃሚ ምክሮች እንመረምራለን።

ፍርሃታችንን ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?

10. (ሀ) አብዛኞቻችን ምን ልንፈራ እንችላለን? (ለ) መልስ ለመመለስ መፍራታችን ስለ እኛ ምን አዎንታዊ ነገር ሊጠቁም ይችላል?

10 እጃችሁን አውጥታችሁ ሐሳብ ለመስጠት ባሰባችሁ ቁጥር ጭንቅ ይላችኋል? ከሆነ እንዲህ የሚሰማችሁ እናንተ ብቻ አይደላችሁም። እውነቱን ለመናገር አብዛኞቻችን ሐሳብ ስንሰጥ በተወሰነ መጠን እንፈራለን። ሐሳብ ከመስጠት ወደኋላ እንድትሉ የሚያደርጋችሁን ይህን ፍርሃት ማሸነፍ እንድትችሉ በቅድሚያ የምትፈሩበት ምክንያት ምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋችኋል። ምናልባት የምትናገሩት ነገር እንዳይጠፋባችሁ ወይም የተሳሳተ ነገር እንዳትናገሩ ስለምትሰጉ ይሆን? አሊያም እናንተ የምትሰጡት ሐሳብ የሌሎቹን ያህል ጥሩ እንዳልሆነ ስለሚሰማችሁ ይሆን? እርግጥ እንዲህ ያለው ስሜት ስለ እናንተ አዎንታዊ ነገር የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። ትሑት እንደሆናችሁና ሌሎችን ከራሳችሁ አስበልጣችሁ እንደምትመለከቱ ያሳያል። እንዲህ ያለው ባሕርይ ይሖዋን ያስደስተዋል። (መዝ. 138:6፤ ፊልጵ. 2:3) ሆኖም ይሖዋ በስብሰባዎች ላይ እሱን እንድታወድሱት እንዲሁም ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን እንድታበረታቱ ይፈልጋል። (1 ተሰ. 5:11) ደግሞም ስለሚወዳችሁ የሚያስፈልጋችሁን ድፍረት ይሰጣችኋል።

11. ፍርሃታችንን ለማሸነፍ የሚረዱን የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች ናቸው?

11 በዚህ ረገድ ሊረዱን የሚችሉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦችን እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ከምንናገረው ነገርም ሆነ ከምንናገርበት መንገድ ጋር በተያያዘ ሁላችንም ልንሳሳት እንደምንችል ይገልጻል። (ያዕ. 3:2) ይሖዋ ፍጹም እንድንሆን አይጠብቅብንም፤ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም ቢሆኑ ከእኛ ፍጽምና አይጠብቁም። (መዝ. 103:12-14) መንፈሳዊ ቤተሰባችን ስለሆኑ ይወዱናል። (ማር. 10:29, 30፤ ዮሐ. 13:35) አንዳንድ ጊዜ የምንናገረው፣ ለመናገር ያሰብነውን ነገር እንዳልሆነ ይረዱልናል።

12-13. ከነህምያና ከዮናስ ታሪክ ምን እንማራለን?

12 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ሰዎችን ምሳሌ መመልከታችሁ ፍርሃታችሁን ለማሸነፍ ይረዳችኋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ ነህምያ ነው። ነህምያ በአንድ ኃያል ንጉሥ ቤተ መንግሥት ውስጥ ያገለግል ነበር። በአንድ ወቅት፣ የኢየሩሳሌም ቅጥሮችና በሮች መፈራረሳቸውን በመስማቱ በጣም አዝኖ ነበር። (ነህ. 1:1-4) ነህምያ ፊቱ በሐዘን የጠቆረበትን ምክንያት እንዲናገር ንጉሡ ሲጠይቀው ምን ያህል ፈርቶ ሊሆን እንደሚችል መገመት እንችላለን! ነህምያ ወዲያውኑ ወደ ይሖዋ ከጸለየ በኋላ ለንጉሡ ምላሽ ሰጠው። ንጉሡም ነህምያ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የአምላክን ሕዝቦች ለመርዳት ብዙ ነገሮችን አድርጓል። (ነህ. 2:1-8) ሌላው ምሳሌያችን ደግሞ ዮናስ ነው። ይሖዋ ለነነዌ ነዋሪዎች መልእክት እንዲናገር ባዘዘው ጊዜ ዮናስ በጣም ከመፍራቱ የተነሳ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ሸሽቶ ነበር። (ዮናስ 1:1-3) ሆኖም በይሖዋ እርዳታ፣ የተሰጠውን ኃላፊነት ሊወጣ ችሏል። ደግሞም ያወጀው መልእክት የነነዌ ሰዎችን በጣም ጠቅሟቸዋል። (ዮናስ 3:5-10) የነህምያ ታሪክ፣ መልስ ከመስጠታችን በፊት መጸለያችን ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ያስገነዝበናል። የዮናስ ታሪክ ደግሞ ይሖዋ፣ የሚሰማንን ከፍተኛ ፍርሃት አሸንፈን እሱን ማገልገል እንድንችል እንደሚረዳን ያስተምረናል። ደግሞስ የነነዌ ነዋሪዎችን ያህል የሚያስፈራ ጉባኤ ሊኖር ይችላል?

13 በስብሰባዎች ላይ የሚያበረታቱ ሐሳቦችን ለመስጠት የሚረዱን የትኞቹ ጠቃሚ ምክሮች ናቸው? እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

14. ለስብሰባዎች በሚገባ መዘጋጀት ያለብን ለምንድን ነው? ለዝግጅት የትኛውን ጊዜ ልንመድብ እንችላለን?

14 ለእያንዳንዱ ስብሰባ ጥሩ ዝግጅት አድርግ። አስቀድመን ጥሩ ዝግጅት ማድረጋችን ሐሳብ መስጠት ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል። (ምሳሌ 21:5) እርግጥ ሁላችንም ዝግጅት የምናደርግበት ፕሮግራም የተለያየ ነው። ኤለዊዝ የተባሉ የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ በ80ዎቹ ዕድሜ የሚገኙ አንዲት እህት ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት መዘጋጀት የሚጀምሩት በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀናት ላይ ነው። “አስቀድሜ ተዘጋጅቼ ስሄድ ስብሰባው ይበልጥ አስደሳች ይሆንልኛል” በማለት ተናግረዋል። የሙሉ ጊዜ ሥራ የምትሠራ ጆይ የተባለች እህት ደግሞ መጠበቂያ ግንብ የምትዘጋጀው ቅዳሜ ቅዳሜ ነው። “እንዲህ የማደርገው የተዘጋጀሁት ነገር ከአእምሮዬ እንዳይጠፋ ስለምፈልግ ነው” ብላለች። በአቅኚነትና በጉባኤ ሽማግሌነት የሚያገለግለውና የተጣበበ ፕሮግራም ያለው ኢክ የተባለ ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “በአንድ ጊዜ ሙሉውን የጥናት ርዕስ ከመዘጋጀት ይልቅ በሳምንቱ ውስጥ የተወሰኑ ክፍሎችን በትንሽ በትንሹ ከፋፍዬ መዘጋጀቱን የተሻለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።”

15. ለስብሰባዎች ጥሩ ዝግጅት ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

15 ለስብሰባዎች ጥሩ ዝግጅት ማድረግ የትኞቹን ነገሮች ያካትታል? ምንጊዜም መዘጋጀት ከመጀመርህ በፊት ይሖዋ መንፈስ ቅዱሱን እንዲሰጥህ መጸለይ ይኖርብሃል። (ሉቃስ 11:13፤ 1 ዮሐ. 5:14) ከዚያም የተወሰኑ ደቂቃዎችን ወስደህ የጥናቱን አጠቃላይ ይዘት ለመቃኘት ሞክር። ይህም ዋናውን ርዕስ፣ ንዑስ ርዕሶቹን፣ ሥዕሎቹንና ሣጥኖቹን አንድ በአንድ መመልከትን ይጨምራል። ከዚያም እያንዳንዱን አንቀጽ ስትዘጋጅ፣ ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱ ጥቅሶችን ለማንበብ የቻልከውን ያህል ጥረት አድርግ። ልትመልሳቸው ባሰብካቸው ነጥቦች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ በትምህርቱ ላይ አሰላስል። ጥሩ ዝግጅት ባደረግክ መጠን ከስብሰባዎች የምታገኘው ጥቅምም የዚያኑ ያህል ይጨምራል፤ ከዚህም በላይ ሐሳብ መስጠት ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል።

16. የይሖዋ ድርጅት የትኞቹን መሣሪያዎች አዘጋጅቶልናል? አንተ እነዚህን መሣሪያዎች የምትጠቀምባቸው እንዴት ነው?

16 ሁኔታህ የሚፈቅድልህ ከሆነ በምታውቀው ቋንቋ የተዘጋጁ ድረ ገጾችንና አፕሊኬሽኖችን ተጠቀም። ይሖዋ ለስብሰባዎች ለመዘጋጀት የሚረዱንን ድረ ገጾችና አፕሊኬሽኖች በድርጅቱ አማካኝነት አቅርቦልናል። ጄ ደብልዩ ላይብረሪ የተባለውን አፕሊኬሽን ተጠቅመን ጉባኤ ላይ የሚጠኑ ጽሑፎችን በኤሌክትሮኒክ መሣሪያችን ላይ ማውረድ እንችላለን። ከዚያም ያወረድነውን ጽሑፍ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ማጥናት፣ ሌላው ቢቀር ማንበብ ወይም በድምፅ የተቀዳ ከሆነ ማዳመጥ እንችላለን። አንዳንዶች ከቦታ ቦታ ሲጓዙ አሊያም በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት ለምሳ እረፍት ሲወጡ ይህን አፕሊኬሽን ተጠቅመው ያጠናሉ። በተጨማሪም ዎችታወር ላይብረሪ (እንግሊዝኛ) እና የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት በአንዳንድ ርዕሶች ላይ ጥልቀት ያለው ምርምር ለማድረግ አመቺ ናቸው።

ለስብሰባዎች ዝግጅት ለማድረግ የመደብከው የትኛውን ጊዜ ነው? (አንቀጽ 14-16⁠ን ተመልከት) *

17. (ሀ) ከአንድ በላይ ሐሳብ ለመስጠት መዘጋጀትህ ጥሩ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የይሖዋ ወዳጅ ሁን—መልስ ለመስጠት መዘጋጀት ከሚለው ቪዲዮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

17 የሚቻል ከሆነ በእያንዳንዱ ጥናት ላይ ከአንድ በላይ ሐሳብ ለመስጠት ተዘጋጅ። ለምን? ምክንያቱም መጀመሪያ እጅህን እንዳወጣህ ላትጠየቅ ትችላለህ። ሌሎች ሰዎችም እጃቸውን ማውጣታቸው ስለማይቀር ጥናቱን የሚመራው ወንድም ከእነሱ መካከል አንዱን ሊጠይቅ ይችላል። በተጨማሪም ስብሰባው በሰዓቱ ማለቅ ስላለበት የጥናቱ መሪ በአንድ ነጥብ ላይ ሐሳብ የሚሰጡ ሰዎችን ቁጥር መገደብ ሊያስፈልገው ይችላል። በመሆኑም በጥናቱ መጀመሪያ አካባቢ ሐሳብ የመስጠት አጋጣሚ ባታገኝ ቅር ልትሰኝ ወይም ተስፋ ልትቆርጥ አይገባም። ከአንድ በላይ ሐሳብ ለመስጠት ተዘጋጅተህ ከሄድክ በጥናቱ ወቅት ሐሳብ የምትሰጥባቸው ሌሎች አጋጣሚዎች ታገኛለህ። ለምሳሌ ያህል፣ ጥቅስ ለማንበብ ተዘጋጅ፤ በተጨማሪም ከቻልክ በራስህ አባባል ሐሳብ ለመስጠት መዘጋጀትም ትችላለህ። *

18. አጠር ያሉ ሐሳቦችን መስጠት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

18 አጠር ያሉ ሐሳቦችን ስጥ። አብዛኛውን ጊዜ በጣም አበረታች የሆኑት መልሶች አጭርና ያልተወሳሰቡ ናቸው። በመሆኑም የምትሰጣቸውን ሐሳቦች አጠር ለማድረግ ሞክር። መልስህ ከ30 ሴኮንድ እንዳይበልጥ ጥረት አድርግ። (ምሳሌ 10:19፤ 15:23) ለበርካታ ዓመታት በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ስትሰጥ ከቆየህ መልስህን አጭር በማድረግ ረገድ ጥሩ ምሳሌ የመተው ኃላፊነት አለብህ። ረጅምና የተወሳሰበ ሐሳብ የምትሰጥ ከሆነ ሌሎች እንደ አንተ ዓይነት ሐሳብ የመስጠት ብቃት እንደሌላቸው በማሰብ መልስ ከመመለስ ወደኋላ ሊሉ ይችላሉ። አጠር ያለ ሐሳብ መስጠትህ በስብሰባው ላይ ተጨማሪ ሰዎች መሳተፍ እንዲችሉ አጋጣሚ ይከፍታል። በተለይ የመጀመሪያውን መልስ የምትመልሰው አንተ ከሆንክ ለጥያቄው ያልተወሳሰበና ቀጥተኛ መልስ ስጥ። በአንቀጹ ውስጥ ያሉትን ነጥቦች ሁሉ ለመሸፈን አትሞክር። የአንቀጹ ዋና ሐሳብ ከተመለሰ በኋላ በተጨማሪ ነጥቦች ላይ ሐሳብ መስጠት ትችላለህ።—“ ምን ሐሳብ ልሰጥ እችላለሁ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

19. ጥናቱን የሚመራው ወንድም ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው? ሆኖም አንተ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

19 ሐሳብ መስጠት የምትፈልግበትን አንቀጽ ጥናቱን ለሚመራው ወንድም ንገረው። እንዲህ የምታደርገው ስብሰባው ከመጀመሩ ቀደም ብለህ መሆን አለበት። ሐሳብ ለመስጠት ያሰብክበት አንቀጽ ጥያቄ ሲጠየቅ ቶሎ ብለህ እጅህን አውጣ፤ እጅህን ማውጣት ያለብህ ደግሞ ከፍ አድርገህ ነው። ይህም ጥናቱን የሚመራው ወንድም በቀላሉ እንዲያይህ ያስችላል።

20. የጉባኤ ስብሰባ ከጓደኞቻችን ጋር አብረን ከተገኘንበት ግብዣ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

20 የጉባኤ ስብሰባን ከጓደኞችህ ጋር አብረህ እንደተገኘህበት ግብዣ አድርገህ ልትመለከተው ትችላለህ። በጉባኤህ ውስጥ ያሉ ወንድሞች ግብዣ አዘጋጅተው ቢጠሩህና በግብዣው ላይ ቀለል ያለ ምግብ ይዘህ እንድትመጣ ቢጠይቁህ ምን ታደርጋለህ? ይህ በተወሰነ መጠን ሊያስጨንቅህ ቢችልም በግብዣው ላይ የተገኙት ሁሉ የሚወዱትን ነገር ይዘህ ለመሄድ አቅምህ የፈቀደውን ያህል እንደምታደርግ የታወቀ ነው። ጋባዣችን ይሖዋ፣ በስብሰባዎቻችን ላይ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ አቅርቦልናል። (መዝ. 23:5፤ ማቴ. 24:45) ሆኖም እያንዳንዳችን በስብሰባው ላይ የሆነች ነገር ይዘን ለመሄድ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ስናደርግ ይደሰታል። እንግዲያው ጥሩ ዝግጅት ለማድረግና የቻልከውን ያህል ብዙ ሐሳብ ለመስጠት ጥረት አድርግ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ይሖዋ ካዘጋጀው ማዕድ መመገብ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን የሚጠቅም ስጦታ ይዘህ መሄድም ትችላለህ።

መዝሙር 2 ስምህ ይሖዋ ነው

^ አን.5 ሁላችንም ልክ እንደ መዝሙራዊው ዳዊት ይሖዋን የምንወደው ከመሆኑም ሌላ እሱን ማወደስ ያስደስተናል። ከወንድሞቻችን ጋር ለአምልኮ ስንገናኝ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር የምንገልጽበት ልዩ አጋጣሚ እናገኛለን። ሆኖም አንዳንዶቻችን በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት ያስፈራናል። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ይህ ርዕስ የምትፈራበትን ምክንያት ለማወቅና ፍርሃትህን ለማሸነፍ ይረዳሃል።

^ አን.17 jw.org ላይ የሚገኘውን የይሖዋ ወዳጅ ሁን—መልስ ለመስጠት መዘጋጀት የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት። ቪዲዮው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > ልጆች በሚለው ሥር ይገኛል።

^ አን.63 የሥዕሉ መግለጫ፦ የአንድ ጉባኤ አባላት በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ በደስታ ተሳትፎ ሲያደርጉ።

^ አን.65 የሥዕሉ መግለጫ፦ ቀደም ሲል በታየው ፎቶግራፍ ላይ በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወቅት ተሳትፎ ሲያደርጉ የነበሩት የጉባኤው አባላት ሁኔታቸው የተለያየ ቢሆንም ሁሉም ለስብሰባ ተዘጋጀተው ለመሄድ ጊዜ መድበዋል።