በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 6

ንጹሕ አቋማችሁን ጠብቁ!

ንጹሕ አቋማችሁን ጠብቁ!

“እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!”—ኢዮብ 27:5

መዝሙር 34 በንጹሕ አቋም መመላለስ

የትምህርቱ ዓላማ *

1. በዚህ አንቀጽ ውስጥ የተጠቀሱት ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት እንደሚጠብቁ ያሳዩት እንዴት ነው?

በይሖዋ ምሥክሮች ሕይወት ውስጥ ሊያጋጥሙ የሚችሉትን የሚከተሉትን ሦስት ሁኔታዎች በዓይነ ሕሊናችሁ ለመሳል ሞክሩ፦ (1) አንዲት ትንሽ ልጅ ትምህርት ቤት ውስጥ ሳለች አስተማሪዋ ሁሉም ተማሪዎች በቅርቡ በሚከበር አንድ በዓል ላይ እንዲሳተፉ ጠየቀች። ይህች ልጅ በዓሉ አምላክን እንደማያስደስት ስለምታውቅ በበዓሉ ላይ እንደማትሳተፍ ለአስተማሪዋ በአክብሮት ነገረቻት። (2) ዓይናፋር የሆነ አንድ ወጣት ከቤት ወደ ቤት እያገለገለ ነው። ቀጣዩ ቤት ውስጥ አንድ አብሮት የሚማር ልጅ እንደሚኖርና ይህ ልጅ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እንደሚያሾፍ ትዝ ይለዋል። ሆኖም ይህ ወጣት በድፍረት ወደ በሩ ሄዶ አንኳኳ። (3) አንድ የቤተሰብ ራስ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ለማቅረብ ተግቶ ይሠራል። አንድ ቀን ግን አለቃው ሐቀኝነት የጎደለው ወይም ሕገ ወጥ የሆነ ነገር እንዲያደርግ ይጠይቀዋል። ይህ የቤተሰብ ራስ ሥራውን ሊያሳጣው እንደሚችል ቢያውቅም አምላክ አገልጋዮቹ ሐቀኛና ሕግ አክባሪ እንዲሆኑ ስለሚጠብቅባቸው እንዲህ ዓይነት ነገር እንደማያደርግ ለአለቃው ገለጸለት።—ሮም 13:1-4፤ ዕብ. 13:18

2. የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን? ለምንስ?

2 በእነዚህ ሦስት ሰዎች ላይ የትኛውን ባሕርይ አስተውላችኋል? ድፍረትንና ሐቀኝነትን ጨምሮ የተለያዩ ባሕርያትን አስተውላችሁ ይሆናል። ሆኖም ከሁሉ በላይ ጎላ ብሎ የሚታይ አንድ ባሕርይ አለ፤ ይህም ንጹሕ አቋም ነው። እነዚህ ሰዎች ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት ጠብቀዋል። የአምላክን መሥፈርቶች ለድርድር ለማቅረብ ፈቃደኞች እንዳልሆኑ አሳይተዋል። ሦስቱም እንዲህ ያለ እርምጃ ለመውሰድ የተነሳሱት ንጹሕ አቋም ስላላቸው ነው። ይሖዋ እነዚህ ሰዎች ይህን ባሕርይ በማንጸባረቃቸው እንደሚኮራባቸው ምንም ጥርጥር የለውም። እኛም በተመሳሳይ በሰማይ ያለው አባታችን እንዲኮራብን እንፈልጋለን። እንግዲያው የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመርመራችን ጠቃሚ ነው፦ ንጹሕ አቋም ሲባል ምን ማለት ነው? ንጹሕ አቋማችንን መጠበቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እንዲሁም ባለንበት በዚህ አስቸጋሪ ዘመን ውስጥ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?

ንጹሕ አቋም ሲባል ምን ማለት ነው?

3. (ሀ) ንጹሕ አቋም የሚለው አገላለጽ ከአምላክ አገልጋዮች ጋር በተያያዘ ምን ትርጉም አለው? (ለ) ለይሖዋ የምንሰጠው ነገር ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ መሆን እንዳለበት እንድንረዳ የሚያግዘን የትኛው ምሳሌ ነው?

3 ንጹሕ አቋም የሚለው አገላለጽ ከአምላክ አገልጋዮች ጋር በተያያዘ ሲሠራበት ይሖዋን እንደ እውን አካል በማየት እሱን በሙሉ ልብ መውደድንና ምንጊዜም ለእሱ ማደርን ያመለክታል፤ ይህም በምናደርጋቸው ውሳኔዎች ሁሉ የአምላክን ፈቃድ እንድናስቀድም ያነሳሳናል። እስቲ ይህ አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመልከት። ንጹሕ አቋም የሚለው አገላለጽ ከሚያስተላልፋቸው መሠረታዊ ትርጉሞች መካከል አንዱ ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ የሚል ነው። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን እንስሳትን ለይሖዋ መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ የነበረ ሲሆን ሕጉ እንስሳው እንከን የሌለበት እንዲሆን ያዛል። * (ዘሌ. 22:21, 22) የአምላክ ሕዝቦች እግሩ፣ ጆሮው ወይም ዓይኑ ላይ ችግር ያለበት አሊያም በበሽታ የተጠቃ እንስሳ እንዲያቀርቡ አይፈቀድላቸውም ነበር። ይሖዋ እንስሳው ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ እንዲሆን ይፈልግ ነበር። (ሚል. 1:6-9) ይሖዋ የሚቀርብለት መሥዋዕት እንከን የለሽ ወይም ሙሉ እንዲሆን የሚፈልገው ለምን እንደሆነ መረዳት አይከብደንም። ለምሳሌ የበሰበሰ ፍራፍሬ፣ ገጾቹ ያልተሟሉ መጽሐፍ ወይም የሆነ ዕቃ የጎደለው መሣሪያ መግዛት አንፈልግም። የምንገዛው ነገር ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ እንዲሆን እንፈልጋለን። ይሖዋም ለእሱ ከምናሳየው ፍቅርና ታማኝነት ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ነገር ይጠብቃል። ፍቅራችንና ታማኝነታችን ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ መሆን ይኖርበታል።

4. (ሀ) ፍጽምና የጎደለው ሰው ንጹሕ አቋሙን ሊጠብቅ ይችላል የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) መዝሙር 103:12-14 ይሖዋ ከእኛ ስለሚጠብቀው ነገር ምን ይጠቁማል?

4 ይህ ሲባል ታዲያ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ፍጹም መሆን አለብን ማለት ነው? እንደ እውነቱ ከሆነ ሁላችንም እንከን እንዳለብን አልፎ ተርፎም ብዙ ስህተት እንደምንሠራ ይሰማናል። ሆኖም ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ አንችልም የሚል ስጋት ሊያድርብን አይገባም፤ እንዲህ የምንለው ለምን እንደሆነ የሚያሳዩ ሁለት ምክንያቶችን እንመልከት። አንደኛ፣ ይሖዋ በጉድለቶቻችን ላይ አያተኩርም። ቃሉ እንዲህ ይላል፦ “ያህ ሆይ፣ አንተ ስህተትን የምትከታተል ቢሆን ኖሮ፣ ይሖዋ ሆይ፣ ማን ሊቆም ይችል ነበር?” (መዝ. 130:3) አምላክ ኃጢአተኞችና ፍጽምና የጎደለን እንደሆንን ስለሚያውቅ ምንጊዜም እኛን ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው። (መዝ. 86:5) ሁለተኛ፣ ይሖዋ ያለብንን የአቅም ገደብ ስለሚረዳ ከምንችለው በላይ እንድናደርግ አይጠብቅብንም። (መዝሙር 103:12-14ን አንብብ።) ታዲያ በእሱ ዓይን ጉድለት የሌለብን፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ መሆን ያለብን ከምን አንጻር ነው?

5. የይሖዋ አገልጋዮች ንጹሕ አቋማቸውን ለመጠበቅ በዋነኝነት ፍቅር የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

5 የይሖዋ አገልጋዮች ንጹሕ አቋማቸውን ለመጠበቅ የሚያስፈልጋቸው ዋነኛው ነገር ፍቅር ነው። በሰማይ ላለው አባታችን ያለን ፍቅርና ታማኝነት ምንጊዜም ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ መሆን አለበት። ፈተናዎች በሚደርሱብን ጊዜም እንኳ ፍቅራችን ሙሉ ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀናል ሊባል ይችላል። (1 ዜና 28:9፤ ማቴ. 22:37) መግቢያችን ላይ የጠቀስናቸውን ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች ሁኔታ በድጋሚ እንመልከት። እንዲህ ያለ አቋም የያዙት ለምንድን ነው? ትንሿ ልጅ አብረዋት ከሚማሩ ልጆች ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ስለማትፈልግ ነው? ወጣቱ ልጅስ ጓደኛው ቢያሾፍበት ደስ ስለሚለው ነው? ወይስ የቤተሰብ ራስ የሆነው ሰው ሥራውን ማጣት ስለሚፈልግ ነው? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች እንዳሉት ስለተገነዘቡና በሰማይ ያለው አባታቸውን በማስደሰት ላይ ትኩረት ስላደረጉ ነው። ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ውሳኔ በሚያደርጉበት ወቅት ለእሱ ፈቃድ ቅድሚያ እንዲሰጡ አነሳስቷቸዋል። በዚህ መንገድ ንጹሕ አቋም እንዳላቸው አስመሥክረዋል።

ንጹሕ አቋማችንን መጠበቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

6. (ሀ) ንጹሕ አቋማችንን መጠበቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) አዳምና ሔዋን ንጹሕ አቋማቸውን ሳይጠብቁ የቀሩት እንዴት ነው?

6 ንጹሕ አቋም ሁላችንም ሊኖረን የሚገባ አስፈላጊ ባሕርይ የሆነው ለምንድን ነው? ሰይጣን በይሖዋም ሆነ በእያንዳንዳችን ላይ ግድድር ስላነሳ ነው። ይህ ዓመፀኛ መልአክ በኤደን ገነት ውስጥ ራሱን ሰይጣን ወይም “ተቃዋሚ” አድርጓል። አምላክን መጥፎ፣ ራስ ወዳድና አታላይ ገዢ አስመስሎ በማቅረብ የይሖዋን መልካም ስም አጉድፏል። የሚያሳዝነው፣ አዳምና ሔዋን ከሰይጣን ጎን በመቆም በይሖዋ ላይ ዓመፁ። (ዘፍ. 3:1-6) በኤደን ገነት ውስጥ የነበራቸው ሕይወት፣ ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር የሚያጠናክሩበት ሰፊ አጋጣሚ ይሰጣቸው ነበር። ሆኖም ሰይጣን ግድድሩን ባስነሳበት ወቅት ፍቅራቸው እንከን የለሽ ወይም ሙሉ አልነበረም። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ‘ለይሖዋ አምላክ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ ታማኝነቱን የሚጠብቅ ሰው ሊኖር ይችላል?’ የሚል ጥያቄ ተነሳ። በሌላ አባባል ጥያቄው ‘የሰው ልጆች ንጹሕ አቋማቸውን ሊጠብቁ ይችላሉ?’ የሚል ነው። ይህ ጥያቄ የተነሳው ከኢዮብ ጋር በተያያዘ ነበር።

7. በኢዮብ 1:8-11 ላይ እንደተገለጸው የኢዮብን ንጹሕ አቋም በተመለከተ ይሖዋ ምን ተሰምቶታል? ሰይጣንስ?

7 ኢዮብ የኖረው እስራኤላውያን በግብፅ በነበሩበት ወቅት ነው። በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቅ ረገድ ተወዳዳሪ አልነበረውም። እርግጥ ኢዮብ ልክ እንደ እኛ ፍጽምና የጎደለው ሰው ስለሆነ ስህተት ሠርቷል። ሆኖም ንጹሕ አቋሙን በመጠበቁ ይሖዋ ይወደው ነበር። ሰይጣን ከዚያ በፊትም ‘የሰው ልጆች ንጹሕ አቋማቸውን ሊጠብቁ አይችሉም’ የሚል ክስ በመሰንዘር ይሖዋን ሳይሰድበው አልቀረም። በመሆኑም ይሖዋ ኢዮብን እንዲመለከት ለሰይጣን ነገረው። የኢዮብ ሕይወት ሰይጣን ውሸታም እንደሆነ የሚያጋልጥ ነበር! ሰይጣን ግን የኢዮብ ንጹሕ አቋም እንዲፈተን ጥያቄ አቀረበ። ይሖዋ በወዳጁ በኢዮብ ላይ እምነት ስለነበረው ሰይጣን እንዲፈትነው ፈቀደ።—ኢዮብ 1:8-11ን አንብብ።

8. ሰይጣን በኢዮብ ላይ ጥቃት የሰነዘረው እንዴት ነው?

8 ሰይጣን ጨካኝና ነፍሰ ገዳይ ነው። በኢዮብ ላይ የተለያዩ ጥቃቶችን ሰንዝሮበታል። በንብረቱ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ሀብቱንና አገልጋዮቹን አሳጥቶታል፤ እንዲሁም በማኅበረሰቡ ዘንድ የነበረውን መልካም ስም እንዲያጣ አድርጓል። በቤተሰቡ ላይ ጥቃት በመሰንዘር የሚወዳቸውን አሥር ልጆቹን ገድሎበታል። ከዚያም በአካሉ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ ድረስ ክፉኛ በሚያሠቃይ እባጭ መቶታል። የኢዮብ ሚስት በጭንቀትና በሐዘን ከመዋጧ የተነሳ አምላክን ሰድቦ እንዲሞት በመገፋፋት ኢዮብን ተስፋ ልታስቆርጠው ሞከረች። ኢዮብ ራሱም ቢሆን ሞቱን ተመኝቶ ነበር። ያም ሆኖ ንጹሕ አቋሙን አላጎደፈም። በመሆኑም ሰይጣን ጥቃት የሚሰነዝርበት ሌላ ዘዴ ቀየሰ። በዚህ ጊዜ የተጠቀመው የኢዮብ ወዳጆች የሆኑ ሦስት ሰዎችን ነበር። እነዚህ ሰዎች ከኢዮብ ጋር ለቀናት ቢቆዩም አንድም የሚያጽናና ቃል አልተናገሩም። ከዚህ ይልቅ ኢዮብን ጭካኔ በተሞላ መንገድ ነቅፈውታል። እየደረሰበት ካለው መከራ በስተጀርባ ያለው አምላክ እንደሆነና እሱ ንጹሕ አቋሙን መጠበቁ ወይም አለመጠበቁ ለአምላክ ግድ እንደማይሰጠው ገለጹ። ይባስ ብለው ደግሞ ኢዮብ ክፉ ሰው እንደሆነና ለፈጸማቸው መጥፎ ነገሮች የእጁን እያገኘ እንዳለ የሚጠቁም ነገር ተናገሩ!—ኢዮብ 1:13-22፤ 2:7-11፤ 15:4, 5፤ 22:3-6፤ 25:4-6

9. ኢዮብ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም ምን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም?

9 ኢዮብ ይህ ሁሉ መከራ ሲደርስበት ምን ምላሽ ሰጠ? ኢዮብ ፍጹም ሰው አልነበረም። እነዚያን የሐሰት አጽናኞች ተቆጥቷቸዋል፤ እንዲሁም እሱ ራሱ አምኖ እንደተቀበለው፣ እንዳመጣለት የተናገረባቸው ጊዜያት ነበሩ። ከዚህም በተጨማሪ ኢዮብን ይበልጥ ያሳሰበው፣ አምላክ ጻድቅ እንደሆነ የማረጋገጡ ጉዳይ ሳይሆን እሱ ጻድቅ እንደሆነ የማረጋገጡ ጉዳይ ነበር። (ኢዮብ 6:3፤ 13:4, 5፤ 32:2፤ 34:5) ሆኖም በጣም አስከፊ ሁኔታ ውስጥ በነበረበት ጊዜም እንኳ ለይሖዋ አምላክ ጀርባውን ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም። የሐሰት ወዳጆቹ የተናገሩትን ውሸት ማመን አልፈለገም። “በእኔ በኩል እናንተን ጻድቅ አድርጎ መቁጠር የማይታሰብ ነገር ነው! እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 27:5) እነዚህ ቃላት ትልቅ ትርጉም ያዘሉ ናቸው። ኢዮብ ፈጽሞ እጅ ላለመስጠት ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር፤ እኛም እንዲህ ማድረግ እንችላለን።

10. ሰይጣን በኢዮብ ላይ የሰነዘረው ክስ አንተን የሚነካህ እንዴት ነው?

10 ሰይጣን በእያንዳንዳችን ላይ ተመሳሳይ ክስ ሰንዝሯል። ይህ ክስ አንተን በግለሰብ ደረጃ የሚነካህ እንዴት ነው? በተዘዋዋሪ መንገድ ሰይጣን ይሖዋ አምላክን ከልብ እንደማትወደው፣ ራስህን ለማዳን ስትል እሱን ማገልገልህን እንደምታቆምና በፈተናዎች ሥር ንጹሕ አቋምህን እንደማትጠብቅ ተናግሯል! (ኢዮብ 2:4, 5፤ ራእይ 12:10) ይህን ማወቅህ ምን ስሜት ያሳድርብሃል? ስሜትህ በጣም እንደሚጎዳ ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም እስቲ የሚከተለውን ለማሰብ ሞክር፦ ይሖዋ፣ ንጹሕ አቋምህን እንዲፈትነው ለሰይጣን ፈቅዶለታል። ይህን ግሩም አጋጣሚ የሰጠህ በአንተ ላይ ሙሉ እምነት ስላለው ነው። ይሖዋ ንጹሕ አቋምህን እንደምትጠብቅና ሰይጣን ውሸታም መሆኑ እንዲረጋገጥ እንደምታደርግ ይተማመንብሃል። ደግሞም በዚህ ረገድ እንደሚረዳህ ቃል ገብቷል። (ዕብ. 13:6) የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ የሚተማመንብህ መሆኑ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ታዲያ ንጹሕ አቋምህን መጠበቅህ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተገነዘብክ? ንጹሕ አቋማችንን መጠበቃችን የሰይጣንን ውሸት ውድቅ ለማድረግ፣ ለአባታችን መልካም ስም ጥብቅና ለመቆም እንዲሁም የእሱን አገዛዝ ለመደገፍ ያስችለናል። ለመሆኑ ይህን አስፈላጊ ባሕርይ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

በዛሬው ጊዜ ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

11. ከኢዮብ ምን እንማራለን?

11 በመከራ በተሞሉት በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ሰይጣን በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዝረውን ጥቃት ይበልጥ አጠናክሯል። (2 ጢሞ. 3:1) ታዲያ እንዲህ ባለ በጨለማ የተዋጠ ጊዜ ውስጥ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ራሳችንን ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድም ቢሆን ከኢዮብ ብዙ ነገር እንማራለን። ኢዮብ በሰይጣን ከመፈተኑ ከረጅም ጊዜ በፊት አንስቶ ንጹሕ አቋሙን የሚጠብቅ ሰው እንደሆነ አስመሥክሯል። ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ያደረግነውን ውሳኔ ማጠናከር የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ ከኢዮብ የምንማራቸውን ሦስት ነገሮች እንመልከት።

ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ያደረግነውን ውሳኔ ማጠናከር የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት) *

12. (ሀ) በኢዮብ 26:7, 8, 14 መሠረት ኢዮብ ለይሖዋ አድናቆትና አክብሮት ያዳበረው እንዴት ነው? (ለ) እኛስ ልባችን በአድናቆት እንዲሞላ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

12 ኢዮብ ለይሖዋ ከፍተኛ አድናቆት በማዳበር ለእሱ ያለውን ፍቅር አጠናክሯል። ኢዮብ ድንቅ በሆኑት የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ላይ ጊዜ ወስዶ ያሰላስል ነበር። (ኢዮብ 26:7, 8, 14ን አንብብ።) ምድርን፣ ሰማይን፣ ደመናትንና ነጎድጓድን ሲያስብ ጥልቅ በሆነ የአድናቆት ስሜት ተውጦ ነበር፤ ያም ሆኖ ይሖዋ ስለፈጠራቸው ነገሮች ያለው እውቀት በጣም ውስን እንደሆነ አምኖ ተቀብሏል። በተጨማሪም ኢዮብ፣ ይሖዋ ለተናገራቸው ነገሮች አድናቆት ነበረው። “የተናገረውን ቃል . . . ከፍ አድርጌ ተመልክቻለሁ” በማለት ለአምላክ ቃል ያለውን አድናቆት ገልጿል። (ኢዮብ 23:12) ኢዮብ ለአምላክ ከፍተኛ አድናቆትና ጥልቅ አክብሮት ነበረው። ይህም ይሖዋን እንዲወደውና እሱን የማስደሰት ፍላጎት እንዲያድርበት አነሳስቶታል። ይህ ደግሞ ንጹሕ አቋሙን ለመጠበቅ ያደረገውን ውሳኔ ይበልጥ ለማጠናከር አስችሎታል። እኛም ልክ እንደ ኢዮብ ማድረግ ይኖርብናል። ድንቅ ስለሆኑት የአምላክ የፍጥረት ሥራዎች ያለን እውቀት በኢዮብ ዘመን ከነበሩት ሰዎች እጅግ የላቀ ነው። በተጨማሪም በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ስላለን የይሖዋን ማንነት በሚገባ ማወቅ እንችላለን። ስለ ይሖዋ የምንማራቸው ነገሮች ሁሉ ልባችን በአድናቆት እንዲሞላ ያደርጋሉ። ለይሖዋ ያለን አድናቆትና አክብሮት ደግሞ እሱን እንድንወደውና እንድንታዘዘው እንዲሁም ንጹሕ አቋማችንን የመጠበቅ ልባዊ ፍላጎት እንድናዳብር ይረዳናል።—ኢዮብ 28:28

የብልግና ምስሎችን ከመመልከት በመራቅ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ያደረግነውን ውሳኔ ማጠናከር እንችላለን (ከአንቀጽ 13-15⁠ን ተመልከት) *

13-14. (ሀ) ኢዮብ 31:1 ላይ እንደተገለጸው ኢዮብ ታዛዥ እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) የኢዮብን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

13 ኢዮብ በማንኛውም ነገር ታዛዥ በመሆን ንጹሕ አቋሙን ለመጠበቅ ያደረገውን ውሳኔ አጠናክሯል። ኢዮብ ንጹሕ አቋምን ለመጠበቅ ታዛዥ መሆን እንደሚያስፈልግ ተገንዝቦ ነበር። ይሖዋን ለመታዘዝ የምንወስደው እያንዳንዱ እርምጃ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል። ኢዮብ በዕለት ተዕለት ሕይወቱ አምላክን ለመታዘዝ ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ከተቃራኒ ፆታ ጋር በተያያዘ በሚያሳየው ምግባር ጠንቃቃ ነበር። (ኢዮብ 31:1ን አንብብ።) ባለትዳር እንደመሆኑ መጠን የትዳር ጓደኛው ላልሆነች ሴት የፍቅር ስሜት ማሳየት ተገቢ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። እኛም የምንኖርበት ዓለም የፆታ ፍላጎት የሚቀሰቅሱ ነገሮችን ያዥጎደጉድብናል። ልክ እንደ ኢዮብ፣ የትዳር ጓደኛችን ላልሆነ ሰው ተገቢ ያልሆነ ትኩረት ላለመስጠት እንጠነቀቃለን? በተጨማሪም ማንኛውንም ዓይነት የብልግና ምስል ወይም የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ነገር ላለመመልከት ከዓይናችን ጋር ቃል ኪዳን እንገባለን? (ማቴ. 5:28) በዚህ ረገድ በየዕለቱ ራሳችንን የምንገዛ ከሆነ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ያደረግነውን ውሳኔ ይበልጥ እናጠናክራለን።

ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት በመያዝ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ያደረግነውን ውሳኔ ማጠናከር እንችላለን (አንቀጽ 14ን ተመልከት) *

14 ኢዮብ ለቁሳዊ ነገሮች ካለው አመለካከት ጋር በተያያዘም ይሖዋን ታዟል። በቁሳዊ ንብረት መታመን ቅጣት የሚገባው ከባድ በደል እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። (ኢዮብ 31:24, 25, 28) ዛሬ የምንኖረው ለቁሳዊ ነገሮች ከልክ ያለፈ ቦታ በሚሰጥ ዓለም ውስጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር በመከተል ለገንዘብና ለቁሳዊ ንብረት ሚዛናዊ አመለካከት ካዳበርን ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ እናጠናክራለን።—ምሳሌ 30:8, 9፤ ማቴ. 6:19-21

ተስፋችን ምንጊዜም ሕያው ሆኖ እንዲታየን በማድረግ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ያደረግነውን ውሳኔ ማጠናከር እንችላለን (አንቀጽ 15ን ተመልከት) *

15. (ሀ) ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን እንዲጠብቅ የረዳው ምን ተስፋ ማድረጉ ነው? (ለ) ይሖዋ የሰጠንን ተስፋ ማስታወሳችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

15 ኢዮብ፣ አምላክ በሚከፍለው ወሮታ ላይ ትኩረት ማድረጉ ንጹሕ አቋሙን እንዲጠብቅ ረድቶታል። ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ለመጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት አምላክ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እምነት ነበረው። (ኢዮብ 31:6) ከባድ ፈተና ቢደርስበትም ይሖዋ በመጨረሻ ወሮታውን እንደሚከፍለው እርግጠኛ ነበር። በአምላክ ላይ ያለው ይህ ትምክህት ንጹሕ አቋሙን ለመጠበቅ እንደረዳው ምንም ጥርጥር የለውም። ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቁ ይሖዋ በጣም ተደስቷል፤ በመሆኑም ጉድለቶች እያሉበትም እንኳ የተትረፈረፈ በረከት አፍስሶለታል! (ኢዮብ 42:12-17፤ ያዕ. 5:11) ወደፊት ደግሞ ከዚህ እጅግ የላቀ ሽልማት ይጠብቀዋል። አንተስ ንጹሕ አቋምህን ለመጠበቅ ለምታደርገው ጥረት ይሖዋ ወሮታህን እንደሚከፍልህ ጠንካራ እምነት አለህ? አምላካችን አልተለወጠም። (ሚል. 3:6) ይሖዋ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት የምናስታውስ ከሆነ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ያለን ተስፋ ምንጊዜም ብሩሕ ሆኖ ይታየናል።—1 ተሰ. 5:8, 9

16. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?

16 እንግዲያው ምንጊዜም ንጹሕ አቋምህን ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ! አንዳንድ ጊዜ በዚህ ጎዳና ላይ ብቻህን እየተጓዝክ እንዳለህ ሊሰማህ ይችላል፤ ሆኖም ፈጽሞ ብቻህን አይደለህም። በዓለም ዙሪያ በታማኝነት ንጹሕ አቋማቸውን እየጠበቁ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች አሉ። በጥንት ዘመንም ቢሆን ሞትን መጋፈጥ ቢጠይቅባቸው እንኳ ንጹሕ አቋማቸውን የጠበቁ በርካታ የእምነት ሰዎች ነበሩ። ንጹሕ አቋምህን መጠበቅህ ከእነሱ እንደ አንዱ ለመቆጠር ያስችልሃል። (ዕብ. 11:36-38፤ 12:1) ሁላችንም “ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!” በማለት የተናገረውን የኢዮብን ምሳሌ እንከተል። ንጹሕ አቋማችንን በመጠበቅ ለዘላለም ለይሖዋ ክብር የምናመጣ ሰዎች እንሁን!

መዝሙር 124 ምንጊዜም ታማኝ መሆን

^ አን.5 ንጹሕ አቋም ሲባል ምን ማለት ነው? ይሖዋ ይህን ባሕርይ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ለምንድን ነው? እያንዳንዳችን ንጹሕ አቋማችንን መጠበቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህ ርዕስ መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ እንድንገነዘብ ይረዳናል። በተጨማሪም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ያደረግነውን ውሳኔ ማጠናከር የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይጠቁመናል። እንዲህ ማድረጋችን ብዙ በረከት ያስገኝልናል።

^ አን.3 ከእንስሳት ጋር በተያያዘ “እንከን የሌለበት” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ “ንጹሕ አቋም” ተብሎ ከተተረጎመው ቃል ጋር ተዛማጅነት አለው።

^ አን.50 የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢዮብ ጎልማሳ ሳለ ልጆቹን ድንቅ ስለሆኑት የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ሲያስተምራቸው።

^ አን.52 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም የብልግና ምስል ለማየት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ለሥራ ባልደረቦቹ ሲገልጽላቸው።

^ አን.54 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም እምብዛም የማያስፈልገውንና ለመግዛት አቅሙ የማይፈቅድለትን ትልቅና ውድ ቴሌቪዥን እንዲገዛ የሚደረግበትን ጫና ሲቋቋም።

^ አን.56 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም አምላክ በሰጠው የገነት ተስፋ ላይ ጊዜ ወስዶ ሲያሰላስል።